ይድረስ ለብአዴን አባላት  [ሙሉቀን ተስፋው]

ANDM - satenaw 6

ወያኔዎች “ሕዝቡን አረጋጉ፤ ሰላም ፍጠሩ” ወዘተ. እያሉ ቁም ስቅላችሁን እያበሏችሁ እንደሆነ እንረዳለን፡፡ እናንተም እኛም አሳምረን እንደምናውቀው ግን የሕዝባችን ሰላም ያደፈረሰው ራሱ ወሮበላው የወያኔ ቡድን ነው፡፡ በሕዝባችን ላይ የዘር ማጥፋት ጦርነት አውጆ ንጹሐንን የሚፈጀው፣ እንቡጥ ሕጻናትን የሚጨርሰው፣ በሺሕዎች የሚቆጠሩ የአማራ ወጣቶችን በየእስር ቤቱ አጉሮ ዘግናኝ ቶርቼር የሚፈጽመው፣ በርካታ ንጹሐን አማሮችን ከረሸነ በኋላ የወልቃይት ጠገዴን ጉዳይ ሁለቱ ክልሎች ተወያይተው ይፈቱታል እያለ በደማችን ላይ የሚቀልደው፣ የሰላም ጉባኤ እያለ እየሰበሰበ በብሶት የሚናገሩትን ወገኖቻችንን እየነጠለ የሚያስረው ወዘተ ወዘተ ራሱ ነብሰ ገዳዩ ወያኔ እንደሆነ ሁላችንም እናውቃለን፡፡ ሕዝባችን ሰላም ወዳድ ነው፡፡ የሰላም ጠንቅ፣ የሽብርና የሁከት አባት ወያኔ ነው፡፡ ስለሆነም ሰላም እንዲሰፍን ከተፈለገ መፍትሔው በጣም አጭርና ግልጽ ነው፡፡

ሰላም እንዲሰፍን ካስፈለገ መብታቸውን ስለጠየቁ ብቻ በየአካባቢው የታሰሩትና እንደተለመደው ወያኔ እጅግ ዘረኛ በሆነ መንገድ ቶርቼር የሚፈጽምባቸው ልጆቻችን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መፈታት ይኖርባቸዋል፡፡ ሰላም እንዲሰፍን ካስፈለገ በግፍ የተወሰደው የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት መሬት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መመለስ ይኖርበታል፡፡ ሰላም እንዲሰፍን ካስፈለገ ወያኔ ከሕዝባችን ጫንቃ ላይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲወገድና ሕዝባችን በወያኔ ምስለኔዎች ሳይሆን በልጆቹ እንዲመራ ያስፈልጋል፡፡ ሰላም እንዲሰፍን ካስፈለገ የአማራ ሕዝብ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚገባውን ሥልጣን ማግኘት ይኖርበታል፡፡ ከዚህ ውጪ ያለው ሁሉ ተራ የወያኔ ማዘናጊያና የክህደት መንገድ ነው፡፡ ወሮበላው ቡድንና የዚህ ቡድን ተላላኪ የሆነው ኃይለማርያም ደሳለኝ የወልቃይት ኮሚቴዎች ለትግራይ ክልል ያቀረቡት ጥያቄ የለም ሲሉ በአገርና በሕዝብ ላይ ክህደት መፈጸማቸው ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ አሁንም ቢሆን የወልቃይትን ጉዳይ ሁለቱ ክልሎችና ድርጅቶች ተወያይተው ይፈቱታል የሚባለው ባዶ ማዘናጊያ እንጂ ከዚህ ነብሰ ገዳይ ቡደን የሚገኝ መልካም ነገር የለም፡፡

Samora - Satenaw 80

የወያኔ መንገድ የሰላም መንገድ አይደለም፤ ሆኖም አያውቅም፡፡ ወያኔ የልጆቻችን ገዳይ የሆነ ደመኛችን እንጂ የሰላም አጋራችን አይደለም፡፡ ከዚህ ወሮበላ የጥፋት ኃይል ጋር ሰላምም ኅብረትም የለንም፤ አይኖረንም፡፡ ጠላቶቻችን የፈለገውን ያህል ቢያደቡም፣ የፈለገውን ያህል ልጆቻችን ቢያስሩና ቢገድሉም፣ የፈለገውን ያህል የዘር ማጥፋት እርምጃ ቢወስዱም፣ ከዚህ በኋላ ወደኋላ መመለስ ብሎ ነገር አይኖርም!! የአባቶቹን የአይበገሬነትና የጽናት መንፈስ የወረሰ ደም መላሽ ትውልድ ተፈጥሯልና በወያኔ ነብሰ ገዳይ ጦር የተፈጁት እንቡጥ ሕጻናት ደምም በከንቱ ፈሶ አይቀርም!!

ሕዝባችን አጋዚ የተባለው ነብሰ ገዳይ ጦር ግድያ ሳያንበረክከው በያለበት የሚዋደቀው፣ በወያኔ አገዛዝ ሲደርስበት የቆየው ይህ ነው የማይባል በደል አንገፍግፎት መሆኑን እናንተም እኛም አሳምረን እናውቃለን፡፡ የትግሉ አደራጅና መሪ (ወሮባለው ወያኔና የዚህ ነብሰ ገዳይ ቡድን ተላላኪ የሆነው ኃይለማርያም ደሳለኝ እንደሚለው የተወሰኑ ጽንፈኛ ዲያስፖራዎች ሳይሆኑ) ራሱ ሕዝቡ መሆኑንም በሚገባ እናውቃለን፡፡ ከዚህ ሐቅ በመነሳት የትግሉን መሠረታዊ ጥያቄ ስትደግፉ እንደቆያችሁ እንገነዘባለን፡፡ በዚህ ይበልጥ ሊጠናከር በሚገባው መልካም እርምጃችሁም የብዙዎችን አድናቆት አትርፋችኋል፤ ብዙዎቻችን ኮርተንባችኋል፡፡ አሁንም በዚህ ሕዝባዊ አቋማችሁ እንድትቀጥሉ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ አቋማችሁ እንድታፈገፍጉ ብዙ ግፊት እንደሚደረግባችሁ ብንገነዘብም፣ የወያኔ መንገድ የጥፋት መንገድ መሆኑን ከእናንተ በላይ የሚያውቀው የለምና የጥፋቱን መንገድ እንደማትመርጡ ደግሞ ባለሙሉ ተስፋ ነን፡፡

ሕዝባችን ሰላም ወዳድ ነው፡፡ ሕዝባችን ከየትኛውም ሕዝብ ጋር ጠብ የለውም፡፡ በነብሰ ገዳዩ የወያኔ ቡድን ፊታውራሪነት በየቦታው ሲዘመትበት ኖረ እንጂ የአማራ ሕዝብ በየትኛውም ሕዝብ ላይ አልዘመተም፤ አይዘምትም፡፡ ሐቁ ይህ ሆኖ ሳለ ነብሰ ገዳዩ የወያኔ ቡድን አማራ ክልል በሚኖሩ ትግሬዎች ላይ ጥቃት ተፈጽሟል እያለ መሠረተ ቢስ አሉባልታ እያወራና እናንተም ይህንን በሬ ወለደ እንድታስተጋቡ ብዙ ግፊት እያደረገባችሁ እንደሚገኝ እናውቃለን፡፡ ሆኖም ይህንን የወያኔ የጥፋት ወጥመድ በሚያስደንቅ ሐቀኝነትና ቁርጠኝነት ሳትቀበሉት በመቅረታችሁ ደግሞ ብዙዎች ኮርተውባችኋል፡፡ ይህ ትልቅ ከፍታ ነው፡፡ ከዚህ የሕዝብ ልጅነት ወደባንዳነት መውረድ የታሪክ አተላ መሆን ነውና በጀመራችሁት መንገድ እንድትገፉ ያስፈልጋል፡፡

ባንዳነት የአማራ ሕዝብ ዕሴት አይደለም፡፡ ሕዝባችን የሚታወቀው በአርበኝነቱ ነው፡፡ ሆኖም ሁልጊዜም ከውስጣችን ሆነው የሚያስጠቁን ባንዳዎችንና ምንደኞችን ደግሞ አጥተን አናውቅም፡፡ ትናንትና አባቶቻችን ሲያስጠቋቸው የነበሩት እነዚህ እንክርዳዶችና የታሪክ አተላዎች ናቸው፡፡ ላለፉት ሃያ አምስት ዓመታትም ቢሆን ሕዝባችን በመሠረተው አገሩ ባይተዋር ሆኖ ሲፈናቀል የኖረው፣ ልጆቹ በግፈኛው ወሮበላ ቡድን ሲሳደዱ፣ ሲታሰሩና ሲገደሉ የከረሙት በእነኝህ ምንደኞች አማካይነት መሆኑን እናንተም እኛም አሳምረን እናውቃለን፡፡ ስለሆነም የሕዝብ ልጅ የሆናችሁት የብአዴን አባላት እነዚህ ምንደኞችና የወያኔ ተላላኪዎች ለራሳችሁም እንደማይተኙላችሁ አውቃችሁ፣ ከሕዝቡ ጋር ሆናችሁ ልትመነጥሯቸው ይገባል፡፡ 40 ሚሊዮን ጀግና ሕዝብ ከኋላችሁ እያለ የምትፈሩበት ምንም ዓይነት ምክንያት የለም፡፡ ከሕዝባችሁ ጋር በማበራችሁ የሚመጣባችሁ መከራ እንኳ ቢኖር ለሕዝባችሁ ስትሉ የምትከፍሉት መከራ በታሪክ ፊት የማይሞት ስም ያስገኝላችኋል እንጂ ተጋድሏችሁ እንዲሁ ከንቱ ሆኖ አይቀርም፡፡ ከንቱዎች ለፍርፋሪ ሲሉ የሕዝባችን ግንባር ቀደም ጠላት ከሆነው የወያኔ ቡድን ጋር ኅብረት የመሠረቱት ምንደኞች ናቸው፡፡

እንግዲህ ብአዴንና የብአዴን አባላት በታሪካችሁ አግኝታችሁት የማታውቁት ዕድል ከፊታችሁ ተደቅኗል፡፡ ምርጫው የራሳችሁ ነው፡፡ ወይ እንደአቡነ ጴጥሮስ፣ አበበ አረጋይ፣ በላይ ዘለቀ፣ ኃይለማርያም ማሞ፣ አሞራው ውብነህ፣ ሙሉዓለም አበበ፣ ጄኔራል ተፈራ ማሞ፣ ኮ/ል ደመቀ … ከሕዝብ ጋር ቆማችሁ፣ በሕዝብ ላይ የመጣውን መከራ አብራችሁ ትታገሉና ደማቅ ታሪክ ትጽፋላችሁ፤ አልያም ደግሞ እንደ አቡነ አብርሐም፣ መላኩ ተፈራ፣ ታምራት ላይኔ፣ ካሳ ተክለብርሃን፣ ዓለምነው መኮንንና ሌሎች የለየላቸው ባንዳዎችና ጸረ ሕዝቦች ሕዝባችሁን ታስጨርሱና በታሪክ ትቢያነት ትመዘገባላችሁ፡፡ የሰላም ኮንፈረንስ እያላችሁ በምታካሒዱት ስብሰባ እንደምትረዱት የአማራ ሕዝብ ፍላጎት አርበኝነቱን እንድትመርጡ፣ መከራውንም ደስታውንም ከሕዝባችሁ ጋር እንድትጋሩ ነውና የሕዝቡን አደራ ተቀበሉ፡፡

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.