ክቡር ሚኒስትሩን ሊወስድ ሾፌራቸው ቤታቸው መጥቷል

Woyane oo

 • ደህና አደርክ?

[ዝም]

 • ምን ሆነሃል?

[ዝም]

 • አንተን አይደል እንዴ የማናግረው?

[ዝም]

 • ምን ይዘጋሃል?
 • ማውራት አልችልም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ለምን አታወራም?
 • በጣም ርቦኛል፡፡
 • ቁርስ አልበላህም?
 • ምግበ ከበላው ቆየሁ፡፡
 • ፆም አለ እንዴ አሁን?
 • አዎን፡፡
 • ምን የሚሉት ፆም?
 • የግዴታ ፆም፡፡
 • የምን ፆም ነው ደግሞ እሱ?
 • ችጋር በግድ እያፆመኝ ነው፡፡
 • ምንድን ነው የምታወራው?
 • እርስዎ አይገባዎትም ክቡር ሚኒስትር?
 • ምኑ ነው የማይገባኝ?
 • ውስጤ ቆስሏል?
 • ለምን ታዲያ በአልኮል አትጠርገውም?
 • እንደ እርስዎ ውስኪ የምራጭበት አቅም የለኝማ፡፡
 • ታዲያ በውኃ መጥረግ ነዋ፡፡
 • እሱን ማድረግ እንዳንችል አደረጋችሁን፡፡
 • እንዴት ሆኖ?
 • ውኃ ከተቋረጠብኝ እኮ ስንት ቀኔ?
 • ለምን?
 • ምን ነካዎት ክቡር ሚኒስትር ውኃ እኮ የሚመጣልኝ በወረፋ ነው?
 • እ…
 • ክቡር ሚኒስትር በጣም ከፍቶኛል፡፡
 • ከፋይ ልበሳ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር እኔ ብቻ ሳልሆን ሕዝቡም በጣም ከፍቶታል፡፡
 • ከሕዝቡ ጋር አብራችሁ ከፋይ ልበሱዋ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ከዚህ በኋላ እንደዚህ እያላገጡ የሚቀጥሉ አይመስለኝም፡፡
 • ምን ሆንኩ ነው የምትለው?
 • ክቡር ሚኒስትር ባለፈው የኮንዶሚኒየም ቤት እንደደረሰኝ ያውቃሉ?
 • ታዲያ መንግሥት ከዚህ በላይ ምን እንዲያደርግልህ ትፈልጋለህ?
 • እስቲ አይቸኩሉ፡፡
 • ምን ልትለኝ ነው?
 • ከስንት ዘመድ አዝማድ ተበድሬ ከፍዬ ቤት ውስጥ ገባሁ፡፡
 • እና ምን ትፈልጋለህ?
 • ውኃ የለው፣ መብራት የለው፡፡
 • ለምን?
 • እንደምንም ብዬ መብራት በአካባቢው ካለ የብሎኬት ማምረቻ አስገባው፡፡
 • እሺ፡፡
 • ከዛ በኋላ ግን ሆን ተብሎ ትራንስፎርመሩ ላይ ኃይል ተለቆበት ይኸው መብራት ካጣሁ ወራት ተቆጠሩ፡፡
 • ሆን ተብሎ መቃጠሉን በምን አወቅክ?
 • መብራት ኃይል ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞች ነው የነገሩኝ፡፡
 • ለምን ታምናቸዋለህ?
 • የሚያሳዝነኝ መንግሥት ለራሱ ፕሮፖጋንዳ በቲቪ ስለተሰጠን ዕድል አስወርቶ ዜና ከሠራብን በኋላ መብራቱን አጥፍቶ ጨለማ ውስጥ መቅረቴ ነው፡፡
 • ቴሌቪዥናችንማ ልማት ብቻ ነው የሚያሠራጨው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር በጣም የተቃጠልኩትም በዚህ ጣቢያ ነው፡፡
 • ለምን?
 • ጨለማውን ለመሸሽ ግሮሰሪ አረቄ ስጠጣ ትናንትና የእርስዎ ጓደኞች የሚያወሩትን ሰምቼ በጣም ተበሳጨሁ፡፡
 • ለምንድን ነው የተበሳጨኸው?
 • እነሱን እንደዚያ ሲሆኑ ማየት አልፈልግም፡፡
 • ምን ሲሆኑ?
 • ሲመጻደቁ!

[ክቡር ሚኒስትሩ በጣም ተናደው ቢሯቸው ሲገቡ አማካሪያቸውን አገኙት]

 • ምን ሆነዋል ክቡር ሚኒስትር የተናደዱ ይመስላሉ?
 • ለምን አልናደድ?
 • ምን አናደደዎት?
 • የማያናድድ ምን ነገር አለ ብለህ ነው?
 • ነገሮች ያናድዳሉ አይደል ክቡር ሚኒስትር?
 • በጣም ያናድዳሉ እንጂ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ሕዝቡ ለምን እንደሚናደድ እየገባዎት ነው ማለት ነው?
 • ሕዝቡ ራሱ ያናድዳል አይደል እንዴ?
 • እኔ እኮ ስለሕዝብ የሚያወሩ መስሎኝ ነበር፡፡
 • ስማ ሕዝብ ምንም ብታደርግለት አያመሰግንም፡፡
 • እንዴት ማለት?
 • ይኸው ሾፌሬ መንግሥት ቤት ቢሰጠውም አሁንም ማማረሩን አልተወም፡፡
 • ለዛ ነው የተናደዱት?
 • አዎን እንደዚህ ዓይነቱን ፀረ ልማት ግለሰብ ማባረር ነው፡፡
 • ኧረ ክቡር ሚኒስትር መባረር ያለበትማ ሌላው ነው፡፡
 • ሌላው ማን?
 • ከፍተኛ ኃላፊውና ኪራይ ሰብሳቢው ነዋ፡፡
 • ስማ ኢሕአዴግ ለሕዝቡ ምን ያላደረገው ነገር አለ?
 • እንዴ ምን አደረገ?
 • ይኸው የብሔር ብሔረሰቦች መብት አስከብሮ አይደል እንዴ?
 • ክቡር ሚኒስትር እናንተ የተገበራችሁት የብሔር ብሔረሰቦች መብት እኮ በደርግ ጊዜ በተጠና ጥናት መሠረት ነው፡፡
 • ምን?
 • ክቡር ሚኒስትር ይኼ በታሪክ ያለ እውነተኛ ነገር ነው፡፡
 • እሺ ቆይ አሁን እኛ ለሕዝቡ ይኸው ኃይል እያመረትን አይደል እንዴ?
 • የምን ኃይል?
 • ለምሳሌ የህዳሴ ግድቡን እኛ አይደል እንዴ የገነባነው?
 • ክቡር ሚኒስትር እንዳይሳሳቱ፡፡
 • ደግሞ እሱን ንጉሡ ነው በመጀመሪያ ያሰቡት እንዳትለኝ?
 • አልተሳሳቱም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምን?
 • የህዳሴ ግድቡ ጥናት የተጀመረው እኮ በንጉሡ ዘመን ነው፡፡
 • ነገርኩህ ሕዝቡ ምስጋና አያውቅም፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር እኔ እውነታውን ነው የነገርኩዎት፡፡
 • ስማ ለሕዝቡ ወርቅ ብታነጥፍለት ፋንድያ ነው የሚልህ፡፡
 • ይሄም አባባል እኮ በደርግ ጊዜ ነው የተባለው፡፡
 • እኔ ጠፋሁ?
 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • እንዴ ሁሉም ነገር በቀድሞ ሥርዓት ነው የተሠራው እያልከኝ ነው?
 • አልወጣኝም፡፡
 • ይኸው የ11 በመቶ ዕድገት እያስመዘገብን አይደል እንዴ?
 • ይኼ መመጻደቅ ነው እኮ ሕዝቡን የሚያስቆጣው፡፡
 • ይህቺ መመጻደቅ የምትለውን ቃል ከየት ነው የመዘዛችኋት ደግሞ?
 • ድርጊታችሁ ነዋ ያስመዘዛት፡፡
 • ቆይ እሺ አሁን ኢሕአዴግ ባቡር አልሠራም፡፡
 • እሱም ቢሆን በሚሊኒክ ጊዜ ኢትዮጵያ ነበራት፡፡
 • እ…
 • ክቡር ሚኒስትር እስቲ ምን አዲስ ነገር አምጥተናል ብላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ፡፡
 • ምን አልከኝ?
 • ክቡር ሚኒስትር ምን ሠርታችኋል እስቲ?
 • ምንም አልሠራችሁም እያልከኝ ነው?
 • እሱማ ሠርታችኋል፡፡
 • ለሕዝቡ ካልሠራን ለማን ነው የሠራነው?
 • ለራሳችሁ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ቤታቸው ምሳ እየበሉ ከልጃቸው ጋር እያወሩ ነው]

 • ዳዲ፡፡
 • አቤት ልጄ፡፡
 • ምን እየሆነ ነው?
 • የት ልጄ?
 • አገሪቷ ውስጥ ነዋ ዳዲ፡፡
 • ምን ሆነ ልጄ?
 • ኦሮሞና አማራ ክልል ተበጥብጧል፡፡
 • እ…
 • በየቦታው እስር ቤት ይቃጠላል፡፡
 • የት ነው የሰማሽው?
 • ይኸው ፌስቡክ ላይ ነዋ፡፡
 • ኢቢሲ ብቻ ተከታተይ አላልኩሽም?
 • ለምን ዳዲ?
 • ፌስቡክ የፀረ ልማቶች ነው፡፡
 • ተው እንጂ ዳዲ፡፡
 • ነገርኩሽ የፀረ ልማት ሚዲያውን ትተሽ ልማታዊ የሆነውን ኢቢሲ ተከታተይ፡፡
 • ዳዲ ምንም አልገባህም፡፡
 • እንዴት?
 • ሕዝቡ እኮ ትክክለኛ ጥያቄ ነው እያነሳ ያለው፡፡
 • ምን?
 • እንደ ባለሥልጣን የሕዝቡን ጥያቄ ሰምቶ መመለስ ነው የሚያዋጣው፡፡
 • ልጄ ኢሕአዴግ እኮ ብዙ ነገር ሠርቷል፡፡
 • እስቲ ምን ሠርቷል?
 • አየሽ በደርግ ጊዜ ሕዝብ ታፍኖ ነበር የሚኖረው፡፡
 • እ…
 • እንዳለኩሽ በደርግ ዘመን የግሉ ዘረፍ አልተነቃቃም ነበር፡፡
 • ደርግ ምንድን ነው?
 • አየሽ የዘመኑ ልጆች የማንበብ ችግር ስላለባችሁ ታሪክ አታውቁም፡፡
 • ስማ ዳዲ እኔ እንኳን በደንብ አነባለሁ፡፡
 • ታዲያ ለምንድን ነው ደርግ ምንድን ነው ብለሽ የምትጠይቂኝ?
 • ራሳችሁን ከደርግ ጋር እያወዳደራችሁ መመጻደቁ ተገቢ ስላልመሰለኝ ነው፡፡
 • ምን?
 • ለምን ራሳችሁን ከሠለጠኑት አገሮች አገዛዞች ጋር አታወዳድሩም?
 • እ…
 • ደርግን እኮ እኔ አላውቀውም፡፡
 • ስለማታነቢ ነዋ፡፡
 • ስለማላነብ ሳይሆን ማወቅ የምፈልገው ስለአደጉትና ከእኛ ስለሚሻሉት አገሮች ነው፡፡
 • እ…
 • እና ራሳችሁን ከደርግ ጋር እያወዳደራችሁ ከመመጻደቅ፣ ሌሎች የሠለጠኑ የአፍሪካ መሪዎችና የምዕራባዊያን አገሮች መሪዎችን ተመልክታችሁ ሕዝቡን ብትመሩት ጥሩ ይመስለኛል፡፡
 • ምን አልሽኝ ልጄ?
 • ለማንኛውም ሕዝብ በአስተሳሰቡ በጣም ቀድሟችኋል፡፡
 • እንዴት?
 • እናንተ የምታስቡት በኪሎ ባይት ነው፡፡
 • ሕዝቡ የሚያስበውስ?
 • በቴራ ባይት! ነው፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ ቀድሞ ሚኒስትር የነበሩ ባለሥልጣን ጋር ደወሉ]

 • እንዴት ነዎት ክቡር ሚኒስትር?
 • እንዴት ነህ ወዳጄ?
 • ምንም አልልም፡፡
 • ኧረ እንቅልፍ እምቢ አለኝ ባክህ?
 • የእንቅልፍ ኪኒን ውሰዱዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • በኪኒኑ ራሱ እንቅልፍ አልወስድ አለኝ እኮ፡፡
 • ምን ሆነዋል?
 • የአገሪቷ ሁኔታ እያስነጨቀኝ ነው፡፡
 • ምን ያስጨንቆታል?
 • ያው አገሪቷ ውስጥ ብዙ ኢንቨስትመንት ሲኖርህ የፀጥታው ጉዳይ ያስጨንቅሃል፡፡
 • አገሪቷ ምንም አትሆንም፡፡
 • አንተም ከእኔ ባትበልጥም አገሪቷ ውስጥ እኮ በርካታ ኢንቨስትመንት አለህ፡፡
 • እሱማ በሚገባ ነው ያለኝ፡፡
 • ስማ በቃ ፎቄ ሲቃጠል፣ ፋብሪካዬ ሲቃጠል ነው የሚታየኝ፡፡
 • ኧረ አይጨነቁ ማን ደፍሮ ነው የእርስዎን ንብረት የሚያቃጥለው፡፡
 • ከእሱ ባለፈ የሚያስጨንቀኝ ሌላ ነገር ነው፡፡
 • ምንድን ነው የሚያስጨንቅዎት?
 • ከሥልጣን እንዳልባረር?
 • ማን ሲባረር አይተው ያውቃሉ?
 • እሱስ እውነትህን ነው፤ ማንም ተባሮ አያውቅም፡፡
 • እኔ እንደዛ ሙሰኛ ሆኜ፣ ይኸው አማካሪ ተደርጌ ነው እኮ የተሾሙኩት፡፡
 • እኔንም አማካሪ አድርገው ይሾሙኛል ብለህ ታስባለህ?
 • ሌላ ታዲያ ምን ይሆናሉ?
 • የአማካሪው ቦታ ሞልቷል ብዬ ነው፡፡
 • ለእርሱ አያስቡ እኔ እሾሞታለሁ፡፡
 • አንተ ራስህ አማካሪ ነህ እኮ፡፡
 • እኮ የእኔ አማካሪ ይሆናሉ፡፡
 • የአማካሪ አማካሪ?
 • አዎን እኔ እኮ ከክቡር ሚኒስትርነት የተቀየርኩት ወደ ክቡር አማካሪነት ነው፡፡
 • እኔስ ምን ልባል ነው?
 • የክቡር አማካሪ…
 • እ…
 • ክቡር አማካሪ!

 

በጋዜጣዉ ሪፓርተር

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.