የአዲስ አበባ እንቅልፍ መንስዔው ምን ይሆን? [ይሄይስ አእምሮ]

ይሄይስ አእምሮ (yiheyisaemro@gmail.com)

22ውስጥ ውስጡን ከማጉረምረም ባለፈ አዲስ አበቤዎች የፍርሀት ቆፈናችንን አስወግደን በገጠራማዋ ኢትዮጵያ የተቀጣጠለውን ሕዝባዊ እምቢተኝነት ለመቀላቀል እስካሁን ድፍረቱን አላገኘንም፡፡ ይህ ነገር  በጣም አሳሳቢ ነው፡፡ አሳሳቢነቱ ደግሞ ለአዲስ አበባ ለራሷ እንጂ ለመላዋ ኢትዮጵያ እንዳልሆነ ወረድ ብዬ ለማስረዳት እሞክራለሁ፡፡  “ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ” ነው ነገሩ፡፡

አዲስ አበባ ለወትሮው የተቃውሞ ማዕከል ነበረች፡፡ እባብን ያዬ በልጥ በረዬ እንዲሉ ሆኖባት እንደሆነም አላውቅም ከ97 ምርጫ ወዲህ ግን ይህች ኩሩ የአፍሪካ መዲና ሕወሓትን በሰማንያ ያገባች የፍቅር እማውራ የሆነች ያህል በፀጥታ መዋጥን የመረጠች ይመስላል፡፡ እውነቱ ግን ሌላ ነው፡፡ በውስጧ ላለን እናውቀዋለን፡፡ የዜጎች ልቅሶና ዋይታ፣ የኑሮ ውድነትና የአፈናው መጠን ዜጎችን ከሰውነት ተራ አውጥቶ ወደ እንስሳነት እየለወጠ በመሆኑ የሕዝቡ ዝምታ ወያኔን ወዶና አፍቅሮ ሳይሆን በሆነ ደንቃራ ሳቢያ ፀጥ ረጭ ማለቱን እንደመረጠ መረዳት አይከብድም፡፡

ለመሆኑ ለምን ዝም አልን? ደንቃራው ምን ይሆን? የሚመስለኝን ልናገር፡፡

 

ደንቃራ አንድ – ከ97 የከሸፈ የወያኔ ምርጫ ወዲህ ሕወሓት በማን ምክር እንደሆነ አላውቅም የአዲስ አበባን የሕዝብ አሠፋፈር በከፍተኛ ደረጃ ለዋውጦታል፡፡ ከክፍለ ሀገር አዲስ አበባ ስትገቡ ትግራይ የገባችሁ እስኪመስላችሁ ድረስ ተጋሩ ወንድምና እህቶቻችን ከመቀሌና አካባቢዋ ዘመቻ በሚመስል መልክ ተጠራርገው ወደ አዲስ አበባና አካባቢዋ እንዲሠፍሩ የወያኔው ጉጅሌ ሣያደርግ አልቀረም፡፡ የትም ቦታ ስትሄዱ ሁለትም ሦስትም አሥርም ሃያም ሰዎች ሆነው ሲሄዱ የሚነጋገሩበት ቋንቋ አብዛኛውን ጊዜ ትግርኛ ነው –  ወትሮ በደጋግ ዘመናት ያልለመደበት ይህን መሰል ግምኛ ጠባይ ስለትግሬ ሲነገር ደማችሁ የሚንተከተክ (ዘረኛ) ሰዎች ታገሱኝ፤ እውነት ደምን ቀርቶ አጥንትን እንደምታፈላ ደግሞ አውቃለሁና በምለው ነገር ሀቅነት ማንም ቅንጣት ያህል እንዲጠራጠረኝ አልፈልግም፤ እውነትን ብትመር ብትጎመዝዝ እንዳለች መቀበል ነው፤ ይሉኝታና መሸፋፈን አስፈላጊ ሆኖ ቢገኝ እንኳን ተመክሮም ሆነ ተዘክሮ ዘመድ ለሚሆንህ ሰው እንጂ እንደበግ አጋድሞ ለሚያርድህ የትግሬ ወያኔ ዓይነቱ ደደብ ጭራቅ አይደለም፡፡ በአዲስ አበባም ሆነ በሌሎች ግዛቶች ብዙ ቀበሌዎች በትግርኛ ተናጋሪዎች እንደተሞሉ ለመረዳት የሥነ ሕዝብና የቤቶች ቆጠራ እስታትክቲክስ ሠራተኛ አያስፈልጋችሁም፡፡ በራሳችሁ ታውቃላችሁ፡፡ በነገራችን ላይ ትግሬዎች ኢትዮጵያን ለምን ሞሏት የሚል ቅሬታ የለኝም፤ ብዙዎቹ ከሕወሓት ጋር ያላቸው የክፋት ቁርኝት ነው የሚከነክነኝ፡፡ አንዳንድ ወንድሞች ታዲያን ይህን ዐይን ያወጣ “የወንድሞቻቸውን” ስህተት እየታዘቡ ሌላው ስለዚህ ስህተት ሲናገር መናደድ የለባቸውም – በአኮርባጅ እየተገረፈ ያለን ሕጻን “ዋ ታለቅስና! ዝም ብለህ ተገረፍ!” ብሎ እንደመቆጣትና ፈረንጆቹ `Adding an insult to injury” እንደሚሉት ነው – ድርብ በደል፡፡ ተጠቅመህም፣ እንዳልተጠቀምክ እንዲቆጠርልህ ፈልገህም እንዴት ሊሆን ይችላል? ብዙ ዕንቆቅልሽ … ብዙ ሞኝነት፡፡ በደል እንዲቆም ማድረግ ሲገባ “በደልህን ገሃድ አታውጣ” ብሎ ተበዳይ ላይ መፍረድ በሰማይም በምድርም ኩነኔ ነው፡፡ ከታላላቅ ምሁራን ጀምሮ ብዙ ብሶት ስላለኝ ነው …

የመንግሥት ሠራተኞች ባብዛኛው፣ ጦሩ ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ሁኔታ፣ መከላከያንና ደኅንነትን፣ የውጭ ጉዳይንና ሌሎችንም የሚንስቴር መሥሪያ ቤቶች እንዲሁም ንግዱንና የዕድርና የዕቁብ፣ የሰንበቴና የፅዋ ማኅበሩን የዜጎች ስብስብ የአመራር ቦታ ሣይቀር ሙሉ በሙሉ ወይም በአብዛኛው የያዙት ትግሬዎች መሆናቸውን መመስከር በተቃራኒ የቆመ ዘረኝነት አይመስለኝም፡፡ የዐዋጁን በጆሮ የመናገር ያህል ግልጽነት ነው፡፡ አንድ ወቅት ወደ ትግራይ ሄጄ ስመለስ በትግራይ ውስጥ የሚኖረው ትግሬ ሁለት ሚሊየን እንኳን እንደማይሆንና ቀሪው በመላዋ ኢትዮጵያ ተበትኖ በተቻለው መጠን እንደመዥገር ሀገሪቱን እየመጠመጠ እንደሆነ ከነባራዊው እውነት በመነሳት በጊዜው ገልጬ ነበር፡፡ ( በነገራችን ላይ ያን ትዝብት በድረ-ገፆች ከገለጥኩ ከጥቂት ሣምንታት በኋላ የኢሳት እንግዳ ሆና የቀረበችው ወ/ሮ ርስቴ የተባለች ጎንደሬ-ወልቃይቴዋ የቀድሞ የሕወሓት ቀጥሎም የኢሕዲን ተብዬው ታጋይ ስትናገርም ይህንኑ ነበር የተናገረችው፡፡ የኔን መጣጥፍ እንዳላነበበች እገምታለሁ፡፡ ግን እውነት እውነት በመሆኑ ሳይነጋገሩ ይግባቡበታልና እንዲያ ስትል እኔንም በጣም ገረመኝ፡፡ ለእውነቱ እርሷ ይበልጥ የቀረበች በመሆኗ የኔ የ2 ሚሊዮን ግርድፍ ግምት በዕውቀት ላይ በተደገፈ የርሷ መረጃ ጽድቅን አገኘ፡፡ በርግጥም ትግራይ ላይ ሰው ያለም አይመስልም፡፡ በወያኔ ተጠርተው ወደሌሎቹ ግዛች በመሄድ “ሥራ እየሠሩ” ነው፡፡)

ይህ የትግሬዎች – ማለትም የወያኔን ዕድሜ መርዘም የሚፈልጉና ለዚያ የሚዋደቁ የትግሬዎች ምልዓት ባለባት አዲስ አበባ ሕዝባዊ ተቃውሞን በቀላሉ መቀስቀስ ባይቻል አይገርምም፡፡ ሰው ለጥቅሙ ሲል የማያደርገው ነገር ስለሌለ እንኳንስ እነዚህ በዘረኝነትና በግል ጥቅም ታውረው ከትግራይ የመጡ ዜጎች ሌላው ጎሣ ሳይቀር ለነሱ ባሪያ በሆነበት ሁኔታ ከሕዝቡ ብዙ ነገር መጠበቅ በእስካሁኑ አካሄድ የሚቻል አልሆነም፡፡ ለምን ቢባል ትግሬው በዛ ማለት ስለላውም፣ ፀጥታውም፣ ምኑም ምናኑም በነሱ ቁጥጥር ሥር ስለሆነ ሰው ይፈራል – የሚገርማችሁ ዕብድና ሰካራም፣ ሴተኛ አዳሪና ቁራሌ እየሆኑ አሁን መንግሥት ከሆኑ በኋላም ሕዝቡን በስለላ ጥምድ አድርገው ይዘውታል – ሰሞኑን ደግሞ ብሶባቸዋል አሉ፡፡ በዚህ ምክንያት አዲስ አበቤ እርስ በርሱ አይተማመንም – አንዱ አንዱን ይጠራጠራል፤ ጥላውንም ማመን አቅቶታል፡፡ ጎመን በጤና ባዩ በዝቶ የእንስሳነት ኑሮ ሰፍኗል፡፡ ምሁር የለ ወታደር፣ ፖሊስ የለ ነጋዴ፣ ማይም የለ ዐዋቂ፣ ዲያቆን የለ ቀሲስ፣ ጳጳስ የለ ፓትርያርክ፣ ደረሣ የለ ኢማም፣ ሼህ የለ ቃዲ … ሁሉም ተያይዞ ነፈዝ ሆኖላችኋል፡፡ ስኬታማ ውድቀት ማለት እንዲህ ነው፤ ስንገርም!!

ደንቃራ ሁለት – ሕወሓት ብዙ ወጣቶችን በአነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች አደራጅቶ የጥቅም ተጋሪ እንዲሆኑ አድርጓል፤ አእምሮ በጫጫበትና ስለሀገርና ወገን ማሰብ ዕርም በሆነበት ማኅበረሰብ ውስጥ ይህ ዓይነቱ ከፋፋይ ሥልት የራሱን አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚፈጥር መገመት አለብን፡፡ ብዙ ሰዎች ስለሚያደርጉት ነገር ሳይሆን የሚያደርጉት ነገር በምን ያህል ፍጥነት ከበርቴ እንደሚያደርጋቸው ነው የሚያስቡት፡፡ ገንዘብ የሚገዛው ጭንቅላት ደግሞ ስለሀገር ቀርቶ ስለራሱም ማሰብ አይችልም፡፡ ሚሰቱንና ልጆቹን ሳይቀር ሸጦ በአቋራጭ መክበር የሚፈልግ ዜጋ በተበራከተበት የጨለማ ዘመን ውስጥ ብዙ መጠበቅ ያስቸግራል፡፡ አዎ፣ ብዙው ስታዩት ቀንም ሌትም፣ ቆሞም ተኝቶም የሚጨነቀውና የሚዋትተው ገንዘብ ስለማግኘት ነው – “የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው”፡፡ ይህ ዓይነቱ ለሥጋው ብቻ ያደረ ገልቱ ዜጋ ሀገሪቱን ብቻ ሳይሆን ከፍ ሲል እንዳልኩት ወንድሙንና እህቱንም ይሸጣል፡፡ እንደነዚህ ዓይነት ሰዎች እየበዙ ሲሄዱ ሀገር በባርነት ሥር እንዳለች የመቆየቷ ዕድል ከፍ ያለ ነው፡፡ መጸለይ ነው ጎበዝ! የተያዝነው የውጥርት ነው፡፡

ደንቃራ ሦስት – የ97ን ምርጫ ተከትሎ ሕወሓት አዲስ አበባ ላይ ያወረደው ዘግናኝ ጭፍጨፋ ከሕዝቡ አእምሮ ገና አልወጣም፡፡ እንዲያውም ይባስ ብሎ የወያኔው ጉጅሌ ዐረመኔነቱን በየጊዜው እያደሰ መጥቶ ሰሞኑን ደግሞ በጭራሽ ሊታመን የማይችል ጭፍጨፋ በእስረኞች ላይ ፈጽሟል – ይህን መሰሉ በ“ሕግ ጥላ” ሥር ያለን ምስኪን ዜጋ በዚህ መንገድ መጨፍጨፍ ደግሞ የመጀመሪያው አይደለም፡፡ ይህ ጭፍጨፋ ሁለት መልእክት አለው ብዬ አስባለሁ- አንደኛው ሊያጠፋቸው የሚፈልጋቸውን የኅሊናና የደረቅ ወንጀል “የሕግ” እስረኞች ማጥፋት ሲሆን ሁለተኛው ሕዝቡን ማስፋራራትና ጭራቅ የመጣበት ያህል ቆጥሮ አንዳችም ተቃውሞ ሳያሳይ አርፎ እንዲቀመጥ ለማስጠንቀቅ ነው፡፡ በተለይ ባለፉት 25 ዓመታት ውስጥ ሁሉንም አየነው፤ ለየነው፡፡ በዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ዕይታ ውስጥ ሆኖ ይህን ወንጀል በጠራራ ፀሐይ ሲሠራ ወያኔን አንድም አካል ዝምቡን እሽ ማለት ቀርቶ ከረር ያለ የቃላት ማስጠንቀቂያ እንኳን የሰጠው የለም –  ከተለመደው የ“ይህ ጉዳይ አሳስቦናል” ዲፕሎማሲያዊ የከንፈር ሽንገላ ውጪ ማለቴ ነው፡፡ ወያኔዎች “ምንም ብናደርግ የሚደርስላችሁ ስለሌለ ፀጥ ረጭ ብላችሁ ለኛ ተገዙ! አለበለዚያ አንድ ባንድ እንፈጃችኋለን፤ የዓለምን ፖለቲካ እንዳሻቸው የሚወስኑት ወገኖች እንደሆኑ ከኛ ጎን ናቸው” የሚል መልእክት ነው እያስተላለፉ ያሉት – ደግሞም እውነታቸውን ነው፡፡ እንዲህ ያለ ግፍ ሌላ ሀገር ቢሠራ ኖሮ ብዙ ዓለም አቀፋዊ ጩኸትና ውግዘት እንዲሁም እስከማዕቀብ የሚደርስ ከፍተኛ ግጭት ይፈጠር ነበር – ወያኔዎች ግን እስካሁን መንገዳቸው ሁሉ ቀኝ በቀኝ የሆነላቸው ይመስላል፡፡ ይህ እስር ቤቶችን በእሳት በማጋየት ከእሳት ለመዳን በደመነፍስ የሚሮጥን ወይም እሳቱ የተነሣው እስረኛን ለመፍጀት ሆን ተብሎ በወያኔ ሣይሆን በድንገተኛ አደጋ መስሎት እሳቱን ለማጥፋት የሚሞክርን እስረኛ ቀድሞ በተዘጋጀ አልሞ ተኳሽ ማስጨፍጨፍ የትም ሀገር ያልታዬ አዲስ የወያኔ ግኝት ለመሆኑ ማንም የማይክደው እውነታ ነው፡፡ ይህ ዐረመኔነታቸው ሕዝብን በፍርሀት ቆፈን ውስጥ እንዳለ እስከወዲያኛው እንዲቆይ ለማድረግ የታለመ እንጂ እስረኛን ለመግደል የሚከለክላቸው ምድራዊ ኃይል ኖሮ አይደለም፡፡ ይህን ፍርሀት ባፋጣኝ ካልገፈፍን ይበልጥ የምንጎዳው እኛው አዲስ አበቤዎች ነን፡፡ እነሱ እንደሆኑ እኛ ፈርተን እስከተቀመጥን ድረስ እየጨፈጨፉን ለዘላለሙ ይኖራሉ፡፡ ከነሱ የጭካኔ በትር የሚያድነን የውጭ ኃል እንደሌለ ደግሞ በሚገባ መረዳት ይኖርብናል፤ ግፋ ቢል ከንፈር ይመጡልን እንደሆነ እንጂ አንዲትም ወንጭፍ ሰንዝረው በኛ ላይ የሚተኩሱትን ወያኔዎች አደብ ግዙ አይሉልንም፡፡ ይህን ጠንቅቀን ማወቅ አለብን፡፡ እኛ ስንጠነክር ወደኛ ሊሳቡ ይችላሉ፤ ከተልፈሰፈስን ግን የወያኔዎች እንደሆኑ በዚያው ይቀራሉ፡፡ ግልጽ እኮ ነው፡፡ ጥሌ “እያለህ ካልሆነ ከሌለህ የለህም” ብሎ ጨርሶታል፡፡

ደንቃራ አራት – የገጠሩ ሕዝብ በጎታውና በጉስጉሻው ለአንድ ሰሞን የሚያጋድደው(የሚሆነው) ጥራጥሬ አያጣም – እንደአብዛኛው ከተሜ ሙልጭ የወጣ ድሃ አይመስለኝም፡፡ እርግጥ ነው ተቃውሞውና ትግሉ ከተራዘመ ያም ያልቃል፡፡ ከተሜው በተለይም አዲስ አበቤው ግን ዛሬ ከሥራ ቢፈናቀል ቀጣዩ ቀን አሣር የሚሆንበትና ኑሮውን በብድር የሚገፋ ብዙ ጦም አዳሪ የመንግሥትና የግል ሠራተኛ የታጨቀባት ከተማ ናትና “ምን ላስጣ ከደጄ፣ ምን ልስጥ ለልጄ” በሚሉ ድሃ ዜጎች የተሞላች ናት፡፡ ሕዝብን አደሕይተው የሚገዙ ክፉ መንግሥታት የሚጠቀሙት እንግዲህ በዚህን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ሕዝቡ “ምን ልቅመስ?” እያለ ከጋራ ትግል ወደኋላ ሲያፈገፍግ ነው፡፡

ለሕዝባዊ ትግል ዝግጅት ያስፈልገዋል፤ ምክክር ያስፈልገዋል፤ ስምምነት ያስፈልገዋል፡፡ ያ እንዳይሆን ግን በሃሳብ መለያየት ይኖራል፤ በኑሮና በኢኮኖሚ አቅም መለያየት ይኖራል፤ የአሰባሳቢ ማጣትም ይኖራል…፡፡ ችግሮች ተደራራቢና ውስብስብም ናቸው፡፡ ይህን ሁሉ ችግር በጣጥሶ ለማለፍ ድፍረትና ጀግንነት ያስፈልጋል፡፡ ከራስ ማሰብ ባለፈ የትልቅ አእምሮ ባለቤት መሆንንና ዘመን ተሻጋሪ ታሪካዊ ሥራ ለመሥራት ዝግጁ ሆኖ መገኘትን ይጠይቃል፡፡ ይህን ሚና ማን ይረከብ? አሳሳቢ ወቅታዊ ጥያቄ ይመስለኛል፡፡

ደንቃራ አምስት – በገጠሩ አካባቢ ያለው ሕዝብ ከፍተኛ ተመሳሳይነት (homogeneity) ስላለው ለመተማመንና ጥርጣሬን ለመቀነስ ብሎም በሂደት ለማስወገድ ትልቅ ዕድል አለው፡፡ በጎሣ ስብጥርም ሆነ በማኅበራዊ ትስስሩ ገጠሩ ከከተማው ይልቅ ይበልጥ እርስ በርስ ስለሚተዋወቅ ወኔው ካለው አንድን ነገር በጋራ አስቦ በጋራ ማድረግ አይቸግረውም – አሁን እያየነው ያለነውም ይህንን ነው፡፡ ከተማው ግን በተለይ አዲስ አበባ በየቀኑ በሚመጡላትና በሚመጡባት በርካታ ዜጎች የምትጥለቀለቅና በአንድ አዳር ከብረው በሚያድሩ ባለጊዜዎች የምትታመስ ከተማ በመሆኗና በገንዘብ ዝውውር ረገድም የት መጣ የማይባል እጅግ ብዙ ብር ሲረጭባት የሚውልና የሚያድር ከተማ ስለሆነች ሰው እርስ በርስ ለመተማመንና ልብ ለልብ ለመገናኘት ይቸግረዋል –  (ስለሆነም Heterogeneity አንዳንዴ አስቸጋሪ ነውና ማንኛውም ዕቅድና ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ይህን ችግር ታሳቢ አድርጎ መነሳት አለበት፡፡) በዚያ ላይ የወያኔ አጋፋሪዎች ሕዝብን በዘርና በጎሣ፣ በሃይማኖትና በጥቅማጥቅም በእጅጉ ከፋፍለውታልና ብሶቱ ሰማይ ቢነካም ለሕዝባዊ እምቢተኝነት ተቃውሞ ተጠራርቶ ለመነሣት አቀበት ሆኖብናል፡፡ ከውጪ እየገፋ የሚመጣ ኃይል ካልተገኘ በእስካሁኑ ሁኔታ ከአዲስ አበባ ብዙም መጠበቅ የሚቻል አልመሰለኝም፡፡ እንዲህ እንደሆነ ይቀራል ማለት እንዳልሆነ ግን በተለይ ወያኔዎች ሊረዱት ይገባል፡፡ የጊዜ ጉዳይ ነው፡፡

 

መግቢያየ አካባቢ ወደጠቀስኩት ጉዳይ ልመለስና አዲስ አበቤዎች ሕዝባዊውን ሀገራዊ የእምቢተኝነት እንቅስቃሴ በሙሉ ንቃትና በስፋት ባለመሣተፋችን እንዴት ልንጎዳ እንደምንችል ልግለጽ፡፡

 

የአዲስ አበባ እስትንፋስ ወያኔ አይደለም፡፡ አዲስ አበባ የምትኖረው የገጠሩ ገበሬ ሲኖር ብቻ ነው፡፡ የገጠሩ ሕዝብ ሁሉን በሮቹን ቢዘጋ አዲስ አበባ ነፍሷን እንደምንም ብታውል አታሳድርም፡፡ ሁሉ ነገር የሚመጣው ከገጠር ነው – ከአየርና ከፀሐይ በስተቀር በአብዛኛው ሁሉም ነገር መነሻው ገጠር ነው፤ የፋብሪካ ግብኣቶች ሳይቀሩ የሚገኙት ከገበሬው ነው፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኘው ገዳይ የወሮበሎች መንግሥትና በሚሊዮን የሚቆጠር በላተኛ አፍ ያለው ተጨቋኝ የከተማ ነዋሪ እንጂ ጤፍና ስንዴ ወይም ምሥርና አተር ወይም የበሬ ቁርጥና የባቄላ አሹቅ አይደለም፡፡ ለቅንጦት የምናውለው ስኳርና ጨው ሳይቀር ከአዲስ አበባ ውጪ ነው የሚገኘው፡፡ ከሞላ ጎደል ሁሉም የምግብ ሸቀጦች ከገጠር ነው ወደ አዲስ አበባ የሚመጡት፡፡ የገፈርሳና የለገዳዲ ሕዝብ ቢያምጽና ውኃችንን አንሰጥም ቢል ራሱ – አያድርግብንና ለምሣሌ – አዲስ አበቤዎች በሕይወት የምንቆየው ግፋ ቢል ከሦስት እስከ ሰባት ቀን ቢሆን ነው፡፡ የኅልውናችን መሠረት ገጠሩ ነው፡፡ ከኛ ለኛ ምን አለን? ምንም፡፡ አልባሽ አጉራሻችን ገበሬው ነው፡፡ ካለ ገበሬው ምንም ማለት ነንና እርሱ በጥይት አረር በወያኔ እየተቆላ ዝምታችን የሚጠቁመው ወያኔን እንደመደገፍና ጠንከር ሲልም ጥይት እንደማቀበል ያህል ነው፡፡ ለምን ቢባል ወያኔ ለዱላ መግዣ የሚጠቀምበትን ግብርና ቀረጥ እንከፍላለንና፡፡ ዝምታችንም ተቃውሞን ብቻ ሣይሆን እንደድጋፍም ሊቆጠር ይችላልና፡፡

የጎጃምና የአድኣ ጤፍ፣ የቦረና በቆሎና የጨርጨር ሠንጋ፣ የጉራጌ ቆጮና የከፋና ሲዳሞ ወይም የወለጋና ጋሞጎፋ  ቡና፣ የሸኖ ቅቤና የአፋር-ዳሎል ጨው፣ የአዶላና ሻኪሶ ወርቅና የቤንሻንጉሉ የደን ዕጣን፣ የሙገሩ ስሚንቶና የጋምቤላው እምነ-በረድ፣… ወደ አዲስ አበባ ካልገባ በወያኔ ኢቢሲ በሚታየው እጅግ የተጋነነና የሀሰት የልማት ዜና ሆዳችንን ቀብትተን አንዲት ቀን ልናድር አንችልም፡፡

ስለዚህ አዲስ አበቤዎች የገጠሩን ሕዝብ የመቀላቀልና የሚደረገውን ሕዝባዊ የእምቢተኝነት ተቃውሞ ከዳር የማድረስ ኃላፊነትና ግዴታ አለብን፡፡ የኅልውናችን መሠረት የሆነው የገጠሩ ሕዝባችን ለሁላችንም መብት እየተዋደቀ እኛ በዝምታችን ብንጸና ፀፀቱ ለማያባራ የታሪክ ስብራት እንዳረጋለን፡፡ ይህን ውሸት ነው የምትል በአድራሻየ ተከራከረኝ፡፡ አዲስ አበባ ጌጧ ገጠሩ ነው፤ ካለገጠሩ ባዶና የባዶ ባዶ ነን፡፡ ይሄ ምንም ጥያቄ የለውም፡፡

አዲስ አበባ ያለገጠሩ ሽባ መሆንዋን ሰሞኑን እየታዘብን ነው፡፡ የሁለት ሺህ ብሩ ጤፍ እስከሦስት ሺህ ብር እንደገባ እየሰማን ነው፤ ይህም የሆነው በኦሮሞ ሕዝባዊ ትግል ምክንያት የገበያና መንገድ መዝጋት እንቅስቃሴዎች ከመጀመራቸው ገና ከማለዳው ነው፡፡ ይህ ትግል በስፋት ቢቀጥል መቶ ሺህ ብርም ይዘህ – ቢኖርህ እንኳን ማለቴ ነው – አንዲት ጣሣ ጤፍ ላታገኝ የምትችልበት ጠማማ ዕድል ሊፈጠር ይችላል፡፡ ስድስት ሚሊየን ገደማ አፍ ይዘህ ተዝናንተህ መቀመጥ አትችልም – እርስ በርስህ ትበላላለህ፡፡ ኦሮሞና አማራ በተባበሩ ማግሥት ወያኔዎች ድራሻቸው እንደሚጠፋ የምንናገረው እንግዲህ ለዚህ ነው፡፡ የሽሮ ድንፋታ ከእሳት እስክትወጣ ነው ይባላል – የወያኔም ድንፋታ ኦሮሞና አማራ እጅ ለእጅ ተያይዘው ከባርነት ለመውጣት እስኪወስኑ ድረስ ብቻ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ አለቀ!!!

ሕዝቡ የከተማ የገጠር ብሎ ሳይፎካከር ሕዝባዊ ተቃውሞውን በአንድ ጀምበር ካደረገ ወያኔም በአንድ ጀምበር ይወገዳል – በዚያው ተመሳሳይ ጀምበር፡፡ ወያኔዎች እርግጥ ነው በገንዘብ ዕጥረት አይወገዱም – ለሚሊዮኖች ዓመታት የሚሆናቸውን ከበቂ በላይ የሆነ ሀብትና ንብረት ዘርፈው አሽሽተዋልና፡፡ በጥይት ዕጥረትም አይወገዱም – በበቂ ሁኔታ አጠራቅመዋልና፡፡ ግን ግን የኅልውና አማራጭ የሚያጣ ሕዝብ እንደንብ በአንዴ ሆ ብሎ ከሠፈረባቸው አጋዚም በሉት መከላከያና ደኅንነት አቅሙ ውሱን ነውና በእግር አውጪኝ የትሚናውን እንደሚፈረጥጥ ግልጽ ነው፡፡ የሮማንያ ሕዝብ የሞተው ሞቶ የተረፈው ተርፎ ሀገሩን ከኒኮላይ ቻውቸስኮ አምባገነን አገዛዝ ነፃ ያወጣው ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ ባደረገው ሕዝባዊ ተጋድሎ ነው፡፡ በተናጠል ከሄድን ግን የትም አንደርስም፡፡ ለተራዘመ ትግል ደግሞ የሚያመች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዳራ የለንም፡፡ ስለዚህ ምርጫችን ሁለት ብቻ ነው፡፡ አንድም በነካካነው የቆሰለ የቤታችን (ዐውሬ) አነር እየተዘነጠሉ መኖር፣ አለዚያም በተናጠልም በቡድንም የነካካነውን ክፉኛ የቆሰለ አነር ገድለን ለሁላችንም የሚጠቅም አዲስ ሥርዓት መትከል፡፡ ለዚህ ደግሞ መሸዋወዱና “የነ እገሌ ትግል ይቅደም፣ የነ እገሌ ትግል ደግሞ ይቀጥል” በሚል የሞኛሞኞች የትግል ሥልት መጃጃል የለብንም፡፡ ከሆነ በአንዴ ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ደግሞ ወያኔን “ባጠፋን ይቅር በለን፣ የድፍረታችን ምንጭ ልማታችንና ሕዝባዊ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ሥርዓታችን ባመጡብን ጥጋብ የተወለደው አቅል አሳች ስካር ነው” ብለን ሕወሓትን ይቅርታ ጠይቀን የከፋ የከረፋውን የውስጥ ቅኝ አገዛዝና የአፓርታይድ ጉዞ ማስቀጠል ነው፡፡ ከዚህ ውጪ “ገመቹ ይቅመሳትና ደስታ በተራው ይታገላል፣ የለም – ሐጎስ እስኪነሣ አሸምቀን እንጠብቅ፣ አሃ፣ ደቻሳ የቀመሳትን ዱላ ስንሻው ካልቀመሳት እንዴት በጋራ እንታገላለን? …” እየተባባሉ ወንዝ በማያሻግርና ካለፈ ተሞክሮ አንዳችም መማማር በሌለበት የድንቁርና አካሄድ ከቀጠልን እመኑኝ የትም አንደርስም – ለነገሩ ይሄ የምለው ነገር የአደባባይ ምሥጢር እንጂ “እመኑኝ አትመኑኝ” የሚያስብል አዲስ ግኝት እንዳልሆነ አውቃለሁ፡፡ ግን ግን ካለፈ ታሪክና ከአሁን የግል ጠባሳችን የማንማረው ምን ቢዞርብን ወይም ወያኔ ምን ዓይነት አፍዝ አደንግዝ ቢያስደግምብን ይሆን?

ኢትዮጵያ ውስጥ ተፈጥረህ ከአንዱ ወይ ከሌላው ጎሣ ያልተቀላቀልህ የለህምና በዚህ በወያኔ ዘራሽ የጎሠኝነት ልምሻ የተኮደኮድክ ሁሉ በአሁኑ ወቅት ሙሉ የመንቂያ ጊዜ ላይ ደርሰሃልና በቶሎ ንቃ፡፡ የጋራ ጠላትህንም ባፋጣኝ ለይና በጋራ ሆነህ ባላንጣህን ተፋለም፡፡ በቃ፡፡ ሌላ መፍትሔ የለም፡፡

በውጪ ያላችሁትም በቻላችሁት ሁሉ በትግሉ ተሣተፉ፡፡ ማጨብጨብና መሰለፍ፣ በየተወሰነ ጊዜ ጠላትን በሰላማዊ ሰልፍ ማውገዝም ብቻውን በቂ አይደለምና የትግል ሥልትህን ለውጥ፤ ሲበቃ በቃ ነውና የትግል ዘዴህን ባለመለወጥ ትርፍ በማያመጣ መጯጯህ ጊዜህን በከንቱ አታባክን፡፡ ኢትዮጵያውያን ዳያስጶራዎች በአካልም፣ በመንፈስም፣ በገንዘብም፣ በዕውቀትም፣ …. በሁሉም ረገድ በትግሉ ተሣተፉ፡፡ “ሩቅ ሆነው በርገር እየቆመጡ ድሃውን ያገር ቤት ሰው ጃዝ ይላሉ” ከሚለው ወደ እውነት የቀረበ አቃቂር ለመዳን ሲሞቅ በማንኪያ ሲቀዘቅዝ በእጅ እንደሚባለው ሣይሆን በማንኛውም አቅጣጫ በንቃት መሣተፍ አለባችሁ – የመጨረሻው የጥፋት ወይም የትንሣዔ ዘመን የቀረበ ይመስለኛል – አሁንም ከሁለቱ አንዱን የመምረጡ ግዴታ የኛው ነው፡፡ የነፃነትን ዋጋ ሁሉም ይረዳ፡፡ በነፃ የሚገኝ ነገር ርካሽ ነው የሚባለው አንዳንዴ ትክክል ነው፡፡ ወዳገር ቤት ገብታችሁ በአመራርም ሆነ በውጊያ መሣተፍ ካለባችሁም በሩቅ ሆኖ በንዴት ከመብገንና ከመጨስ ባመቻችሁ ቀዳዳ ገብታችሁ ትግሉን ተቀላቀሉ፡፡ እርግጥ ነው – መናገር ቀላል ነው – ይህን የኔን ጨምሮ፡፡