መልካም አዲስ ዓመት! [ጌታቸው አበራ]

candle_light-satena-news-5

                የታሪክ አምድ ነባራዊ፣ ምድረ-ህይወት ፍልስፍና፣

                መውጣት መውረድ፣ የዓለም ህግ፣ የተፈጥሮ ገጽ ሆነና፣

                ጊዜ ክፉ፣ ጊዜ ደጉ..፣ እጥፍ-ዘርጋ፣ ዘመም-ቀና..፣

                አንዴ ጽልመት..፣ አንዴ ብርሃን..፣ ባለታሪክ፣ ባለዝና፤

                ስትወድቂ..፣ ስትነሺ..፣ በዘመናት ጉዞሽ ሂደት፣

                ለዚህ ደረስሽ፤ እልልልል! ሁለት ሺ ዘጠኝ ዓመት!

 

               ባለፊደል፣ ባለቀመር…፣ የባህል ጌጥ መናኸሪያ፣

               የእምነት አውራ፣ የእግዚአብሔር ቤት፣ የቃል-ኪዳኑ ማደሪያ፤

               በመለኮት ብፁዕ ጸጋ፣ ዙሪያ-ገባ የተከበብሽ፣

               በፈጣሪ ጥበቃ ስር፣  በኃያል ክንዱ የተደገፍሽ፤

‘አበቅቴ ውሉን ቢስት’፣ የዘመመ ቢመስል ቀኑ፣

እርኩስ መንፈስ ቢጣባሽም፣ ቢያስጨንቅሽ ሰቀቀኑ፣

               ያምላክሽ ኃይል፣ ብርቱ ክንዱ፣ በልጆችሽ መንፈስ አድሮ፣

               እማይቀር ነው ትንሣኤሽ፣ አዲስ ዘመን ዓመት ቆጥሮ፤

               እስከዚያው ግን ይመስገነው፣ ትንፋሽሽም በመኖሩ፣

               መልካም ዓመት! ለቅን ሕዝብሽ! ለውብ ገላሽ፣ ላገር-ምድሩ!

 

መፃዒ ዕድልሽ እንዲቃና  አዲስ ዘመናት እንዲኖሩሽ፣

በደማቸው ‘ጉንጉን አበባ’ ኃያል ፍቅር ላተሙልሽ፤

ሰላም፣ ፍትህ፣ እኩልነት… ዴሞክራሲ እንዲሰፍኑ ባገር ምድር፣

ውድ ህይወታቸውን ለግሰውሽ  ላሸለቡት በናትነት እቅፍሽ ስር፣

ለሰላማዊ ዜጎችሽ በጨካኞች የግፍ ጥይት ለወደቁት፣

“ክብር ሞቱ ለሰማዕታት” ይሁን! ለዘልዓለም-ዓለም ህይወት!

 

ለሰው ልጆች ክቡር ህይወት  ከቶም ዋጋ በማይሰጡ፣

ባረመኔ፣ እኩይ፣ ድንኮች..ውዶቻቸውን ላጡ፣

ለአባ-ወራ፣ አባቶችሽ፣ ለሀደ-ወራ፣ እናቶችሽ፣

ለወንድም ጋሼ፣ ወንድሞችሽ፣ ለእታለም፣ እህቶችሽ..፣

ባዲስ ዓመት ጥቁር ለብሰው  መሪር ሃዘን ላጠቃቸው፣

ብሩህ ዘመን፣ ተስፋ ስንቁን  መጽናናቱን ለግሻቸው!

 

የነጻነት ቀንዲል ዓርማ፣ ለልጆችሽ ብርቱ አለኝታ፣

               የታመቅሽው ገሞራ-እሳት፣ በልባቸው ደም ትርታ፣

               ስትጠቂ እሚጮኹት፣  ደስ ሲልሽ  እሚደምቁት፣

               በሄዱበት አንቺን ይዘው፣ እሚያመልኩሽ እንደ ጽላት፣

               እንደ ጨው ዘር ተበትነው፣ ባለም ዙሪያ ሰፍረው ላሉ፣

               ይድረሳቸው ለውዶችሽ፣ ያዲስ ዓመት ተስፋ ቃሉ!

 

               አንቺን ብለው እየማሉ፣ ለህልውናሽ ያደሩ፣

               የትውልዱ ባላደራ፣ ስም ዝናሽን ያስከበሩ፤

               ቤታቸውን ክፍቱን ጥለው፣ ለብዙኃን ሲታገሉ፣

               ባረመኔ፣ በግፈኞች – ከወህኒ-ቢት፣ “ባዶ ሰድስት” የተጣሉ፣

               ለሕዝብ ድምፅ፣ ለጀግኖችሽ፣ ለአጋሮችሽ የቁርጥ ቀን፣

               ጭለማው ያከትም-ዘንድ፣ በአዲስ ዓመት ተስፋ ብርሃን!

 

 

የግፍ ጽዋው ሞልቶ ሲፈስ፣ ውርደትሽን ያልታገሱ፣

               በራሳቸው ልዩ ቋንቋ – ሊታደጉሽ የተነሱ፣

 

 ዋሻ፣ ፈፋ፣ ሸንተረሩ..፣ ዱሩ ቤቴ ብለው ከተው፣

               አጋም-ቀጋ፣ ሾላ..በልተው፣ በእፍኝ ከውሃሽ ተጎንጭተው፣

               ለመስዋዕት ለቆረጡ፣ ባንቺው ፍቅር ለነደዱ፣

               መልካም ብሩህ አዲስ ዓመት! ጨርቅ ይሁንላቸው መንገዱ!

 

እንደ የዋኋ ላሜ ቦራ፣ በዥንጉርጉር የናት ሆድሽ፣

               እሳት ወልደሽ፣ እንዳትልሽው ለሚፈጅሽ፣

               እንዳትተይው፣ እሱም ልጅሽ…፣

                ልቦናውን አምላክ ቸሮት፣ ከእኩይ-መንፈስ ተላቆ፣

               ከበደለሽ ውድ እናቱ፣ ከእህት -ወንድሞቹ ታርቆ፣

               ትሆን ዘንዳ፣ ምስኪን ጎጆሽ፣ ሰላም፣ ደስታ..የሞላባት፣

               ህሊናውን መፈተሻ፣ ይሁንለት አዲስ ዓመት!

 

               ህመምሽ አሳስቧቸው፣ ለፈውስሽ ለሚቀምሙ፣

               ቅጠል በልተው..በምህላ..፣ በዱአ..ለታደሙ፣

               ለሰላምሽ በሰላም መንገድ፣ እምቢኝ ብለው ለሚታገሉ፣

               ፍትህ-አልባ ጉልበተኞችን፣ ከእንግዲህስ በቃ ላሉ፣

               ባዲስ ዓመት፣ ባዲስ ብራ — ይስመር ትግሉ ደምቆ ያብራ!

 

               የፍቅር እምነት ማተብ ገጽሽ፣ ህብረ-ቀለም ውብ ሰንደቅሽ፣

               የክብር አልባስ፣ የክት ልብስሽ፣ አረንጓዴ ቢጫቀይሽ

               ትውለብለብ ለዘላለም፣ ከፍ ብላ፣ በአየር-ምድርሽ!

 

               ከምዕራብ እስከ ምስራቅ፣ ከደቡብ ..እሰሜን ጫፍ፣

               የጥቁር አፈርሽ ግኝቶች፣ የሰፈሩ ባንቺው ማዕቀፍ፣

               የክርስቶስ፣ የአላህ ልጆች…፣ ፍጥረተ-ዓለም ያንቺ የሆኑ፣

               ብሩህ ተስፋ፣ የህይወት ምንጭ፣ ይሁንላቸው ዘመኑ!

 

               የዜጎችሽ ክብር ኩራት፣ ረቂቅ ውበት መጎናጸፊያ፣

               መልካም አዲስ ዓመት ይሁንልሽ! እናት ሀገር ኢትዮጵያ

 

 

ጌታቸው አበራ

 

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.