እንኳን ደህና መጣችሁ ጀግኖቻችን! [ድምጻችን ይሰማ]

እንኳን ወደ ቤታችሁ ተመለሳችሁ ውድ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን!
እንኳን ለነጻነታችሁ በቃችሁ ውድ ኡስታዞቻችን፣ ዳዒዎቻችን፣ አራማጆቻችን፣ ጋዜጠኞቻችን!!!
ለዲናችሁ ፍቅር የከፈላችሁትን መስዋእትነት ሁሉ አላህ ይቀበላችሁ!
ቅዳሜ ጳጉሜ 5/2008


dimsachin-1ውድ ጀግኖቻችን….! እንኳን ከቤተሰባችሁ፣ ዘመዶቻችሁና ከህዝባችሁ ለመገናኘት በቃችሁ! አስከፊ የቶርቸር ግርፋትን አስተናግዳችኋል፡፡ ከሌላ እስረኛ ተለይታችሁ ልዩ ጭቆና ተፈጽሞባችኋል፡፡ በሀሰት ክስ ሊወነጅሏችሁ ሞክረዋል፡፡ በርካታ ሀሰተኛ ምስክሮችን ታግሳችሁ ሰምታችኋል፡፡ እናንተን ለመጠየቅ የመጡ በርካታ ሺህ ወገኖቻችሁን እያበረታታችሁ ልካችኋል፡፡ በጨለማ ቤት ነጣጥለው ቢያስሯችሁም ወኔያችሁ አልተሰበረም፡፡ ከሌላ እስረኛ ለይተው በቤተሰብ፣ ዘመድና ወዳጆቻችሁ እንዳትጠየቁ ልዩ ማእቀብ ተደርጎባችኋል፡፡ የረጅም ዓመታት ፍርድ ሲበይኑባችሁ በጀግንነት ለፍርድ ቤቱና ለሚዘውረው ደህንነት አይበገሬነታችሁን ገልፃችኋል፡፡ በእስር ቆይታችሁ ለበርካታ ታራሚዎች የኢስላምን ምንነት በግብር አሳይታችኋል፡፡ እናንተ ዛሬም ለመላው ህዝባችሁ ታላላቅ ጀግኖች ናችሁ!

እናንተ ውድ ወንድሞቻችን ከአራት ዓመታት በፊት ቃል ባስገባችሁን መሰረት በሰላምና በጽናት ትግላችንን ስናካሂድ እስከዛሬዋ ቀን ድረስ ቆይተናል፡፡ በእናንተ መታሰር እኛም አብረን ታስረናል፡፡ እናንተ ቶርቸር ሲፈጸምባችሁ ኢትዮጵያዊው ሙስሊም ህመም ተሰምቶታል፡፡ ህዝባችሁ አንዲትም ቀን እናንተን ሳያስብ፣ ስለእናንተ ጸሎት ሳያደርግ ውሎ አላደረም፡፡

dimtsachin-3እናንተ በጨቋኙ መንግስት በግፍ ታስራችሁ ስትጋዙ ሙስሊሙ የጀመራችሁትንና ያስተማራችሁትን ሰላማዊ ትግል በተገቢው ዲሲፕሊን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ይህን ትግል ስንጀምር ሶስት ጥያቄዎችን ይዘን ነበር፡፡ የእናንተ መታሰር ጥያቄዎቻችንን ወደ አራት አሳደጋቸው፡፡ በሂደትም የግፉ መባባስ ጥያቄያችንን ከአራት አሳድጎ ብሄራዊ ጭቆናን የመግፈፍ ትግል አደረገው፡፡ ዛሬም ሳይፈቱ የቀሩ፣ ያለ ወንጀላቸው እየተቀጡ ያሉ በርካታ ሙስሊሞች በመላዋ አገሪቱ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ያለወንጀላቸው እየተሰቃዩ ያሉ የህሊና እስረኞች ሁሉ እንዲፈቱ መታገላችንም አይቀርም፡፡ ዛሬ ከኮሚቴ አባላት ክስ ጋር ተከስሰው ተለይተው ሳይፈቱ የቀሩት የኮሚቴው አባላት አህመዲን ጀበልና አህመድ ሙስጠፋ፣ አክቲቪስት ኻሊድ ኢብራሂምና ሙሃመድ አባተ፣ እንዲሁም በሌሎች የተለያዩ ክልሎች በትግሉ ሰበብ እስር ቤት እየማቀቁ ያሉ ሁሉ ለምን ሳይፈቱ እንደቀሩ መንግስት በቂ መልስ የለውም፡፡

ከእስር ያልተፈቱ የኮሚቴው አባላትና በሌላ መዝገብ የተከሰሱ፣ ከሙስሊሙ ትግል ጋር የታሰሩ ሙስሊሞች ቤተሰቦችም በአገር ውስጥም ይሁን ከአገር ውጭ ያለው ህዝበ ሙስሊም ከእናንተ ጎን እንደሆነ ታውቁታላችሁ፡፡ አሁንም በእስር ያሉት ጀግኖቻችን እስከዛሬ ከተፈቱት በምንም ዓይነት የተለዩ አይደሉም፡፡ ይህንን የመንግስት ድርጊት ከአንድ ዓመት በፊት በከፊል የተወሰኑትን ጀግና ታሳሪዎች ሲለቅ መላው ሙስሊም ቀድሞውኑ ያወቀው ጉዳይ ነበር፡፡ ያኔ ኡስታዝ ያሲን ኑሩ ከኡስታዝ አቡበከር አህመድ የሚለይበት አንዳችም ነገር እንዳልነበረ ሁሉ ዛሬም ኡስታዝ አቡበከርን ከአህመዲን ጀበል የሚለየው ነገር የለም፡፡ ህዝበ ሙስሊሙ ይህንን አስረግጦ ያውቀዋል፡፡ የመንግስት የመከፋፈል ሴራም ለምንጊዜውም አይሳካም፡፡

dimtsachin4ደስታውም ሆነ ሐዘኑ የትግል ዓለም ተጨባጭ ነውና ባጣናቸው መብቶቻችን አዝነን እየታገልን እናንተ ለነጻነት በመብቃታችሁ ደግሞ የተሰማንን ደስታ እንገልጻለን፡፡ አላህ ለደረሰባችሁ እንግልት ሁሉ የእናንተንም የቤተሰቦቻችሁንም ምንዳ አብዝቶ ይክፈላችሁ! የተሰቃያችሁለት ህዝበ ሙስሊም በአላህ እርዳታ ትግሉን በስኬት አጠናቅቆ ከብሄራዊ ጭቆና ነጻ የሚወጣበትን እና ፍትህ እና ነጻነት በሰፈነባት ኢትዮጵያ ከሌሎች ወገኖቹ ጋር የሰላም አየር የሚተነፍስባትን ወቅት በአይናችሁ ያሳያችሁ ዘንድ አላህን እንለምነዋለን፤ ድልም ከአላህ እንጂ ከሌላ አይደለምና!

ትግላችን እስከድል ደጃፎች በአላህ ፈቃድ ይቀጥላል!
ድምጻችን ይሰማል!
አላሁ አክበር!