የእናቶች ለቅሶ ያብቃ! [ከአንተነህ መርዕድ]

 

መስከረም 2016 ዓ ም

mother-co-satenaw-nrws-7አንድ እናት ስታለቅስ ሳይ ኢትዮጵያ እንደምታለቅስ ይሰማኛል። በአለፉት አርባ ዓመታት ኢትዮጵያ ወልዳ ያሳደገቻቸው፣ ለነገ ተስፋ ይሆኑኛል ያለቻቸው ወጣት ልጆቿ በአምባገነን ግዥዎቿ ሲቀጠፉ ማቅ ለብሳ አልቅሳለች። እጆቿን ዘርግታና ተንበርክካ አንብታለች። የአምላኳ መልስ ዘገዬ እንጂ መምጣቱ አልቀረም።

ጎንደር፣ ደብረ ታቦርና ቂሊንጦ እስር ቤቶች በግፍ መታሰራቸው አልበቃ ብሎ በጥይት የተለቀሙት ወጣቶች በእሳት እንዲጋዩ ሲደረግ የመስዋዕታቸው ጭስ ወደ ፈጣሪ ደርሷል። በልባችን ውስጥ ያለችው ኢትዮጵያ እንባ ጨኻኝ ልብ ላላቸው የልጆቿ ገዳዮች ባይታይም ህሊናውን ለገለጠ ዜጋ በየአደባባዩ፣ በየቤቱ፣ በየእስርቤቱ በር፣ በየጦር ካምፑ ጉበን በእውነት የሚያለቅሱ እናቶችን እንባ መሬት ሲያርስና ወደ ሰማይ ሲረጭ ማየት ይቻላል።

የአስራ ስድስት ዓመቱ የሃይሉ ኤፍሬም እናት ወይዘሮ ታደሉ ተማም በልጃቸው አስከሬን ላይ ተቀምጠው እንዲያለቅሱ፣ እንባቸውን ከደሙ እንዲቀላቅሉ ያስገደዳቸው ጨካኝ የወያኔ አገዛዝ የጣልያን ፋሺስቶች ከነበራቸው ጭካኔ በላይ አረመኔና ፋሺስትም መሆኑን ከዚህ ሌላ ምስክር አያሻውም።

የተመስገን ደሳለኝ እናት እንባ አልደረቀም። የተሾመ ተንኮሉ እናት የታፈነውን ልጃቸውን እየናፈቁ አየር ኃይል በር ላይ ያፈሰሱት እንባ ሳይደርቅ በሞት ተለይተዋል። የደፋሩና የቁርጠኛው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እናት እንደሱ ቆራጥ ቢሆኑም በተለያየ ጊዜ ሲታሰር እስርቤትና ፍርድ ቤት እየተመላለሱ አልቅሰዋል። የርዕዮት ዓለሙ ወላጆች፣ የብርቱካን ሚዴቅሳ እናት፣ የአንዳርጋቸው ፅጌ አባት እድሜ ባደከመው ዐይናቸው አልቅሰዋል።

ጨካኝ የስርዓቱ መሪዎች በቴሌቢዥንና በአደባባይ ብቅ እያሉ ገና ብዙ እናሳያችኋለን ዓይነት ፉከራና ማስፈራርያ ሲያዘንቡ፤ ህሊና ቢስ ደጋፊዎቻቸው የኢትዮጵያ ህዝብ በሚያለቅስበት ሰዓት እየተሰባሰቡ ሲጨፍሩ ማየት እጅግ ያማል። ወደ ኋላ የሚከፍሉት ዋጋ የከፋ እንደሚሆን ህሊናቸውን ጥቅም፣ ድሎትና ዘረኝነት ጋርዶታል።

ሚኒስትር ደብረፅዮን ሰላሳ ሚሊዮን ይቅርና አፍሪካን የሚያንበረክክ ጦር እንዳለው መፎከሩ የወያኔ ጥቃት ደመኛ ጠላቱ አድርጎ ከፈረጀው ከአማራ ህዝብ ላይ ማነጣጠሩን ቢያመለክትም የዘረኝነት ትዕቢቱ በህዝባዊ ትግል ፊት ባዶነቱን እንዳያይ የጋረደው ግብዝ መሆኑን አጋልጦታል። የአባይ ፀሃዬ ልክ የማስገባት ፉከራ ፣ እኛ ከስልጣን ከወረድን ኢትዮጵያ ትፈራርሳለች የተስፋ ቆራጭ ማስፈራርያነት  “ንጉሡ ከወረዱ ፀሃይ ትጠልቃለች” ወደሚለው የለመድነው ተረት ተቀይሯል። በመሬቱም በስኳሩም የዘረፈው ሃብት ብቻ ሳይሆን ባለፉት አርባ ዓመታት በጓደኞቹ ሆነ በንፁህ ኢትዮጵያውያን ደም የተነከረው እጁ የትም ቢሄድ አያስጥለውም።

ስዩም መስፍን ደቡብ ሱዳንንና ሌሎችንም የፈራረሱ አገሮች እንደምሳሌ እያደረገ “እንዳንጠፋፋ”ን ሰብኳል። አንድ የፌስቡክ ወዳጄ እንዲህ አስቀምጦታል። “መጠፋፋትን ምን አመጣው። እናንተን ለንግሥና እኛን ለባርነት የፈረደው የትኛው አምላክ ነው?” ብሏል። የኃይለማርያም ጨፍጭፉ ትዕዛዝ፣ የሳሞራ የኑስ ፉከራ፣ የአባይ ወልዱ የፍጅት አዋጅ ህዝባዊ ትግሉን ቅንጣት አያቀዘቅዘውም።

የኦጋዴኑ እርድ፣ የጋምቤላው ጭፍጨፋ፣ የዘጠና ሰባቱ የአዲስ አበባ ግድያ፣ የመላ ኦሮምያ ወጣቶች ፍጅትና የጎንደር፣ የባህርዳርና የሌላውም ቦታ ግድያ ለትግሉ ነዳጅ እየሆነ አጋጋለው እንጂ አላበረደውም።  ትግራይ ከምድር በታች በሆኑ እስር ቤቶች(ባዶ ስድስት)፣ ብርሸለቆ፣ ዴዴሳ፣ ቃሊቲ፣ ቂሊንጦ፣ ዝዋይ፣ ማዕከላዊ፣ አንገረብና በሁሉም የኢትዮጵያ መሬቶች በተገነቡ እስር ቤቶች ብዙ ሺህ ንፁህ ኢትዮጵያውያን እየተገረፉ፣ እየተገደሉና ዱካቸውንም ለማጥፋት እሳት እየነደደባቸው ነው። ዳር ድንበር መጠበቅ የሚገባው ሰራዊት ታንክ፣ ቢኤም፣ መትረየስ የመሳሰሉ ከባድ መሳርያዎች ይዞ ባዶ እጃቸውን ባሉ ዜጎቹ ላይ ሲዘምት ወያኔ ብቸኛው መንግስት ነው። ይህ ደግሞ ትግሉን የበለጠ ያበረታዋል እንጂ አያኮሰምነውም። ዝም ብሎ መሞት እንደማይገባው ህዝቡ የትግል ስልቱን እንዲቀይር አድርጎታል።

የገደለን መግደል እንዳስቆምክ አውቃለሁ

ይቅር እንዳልለው እኔ አንተን አይደለሁ።

ብሎ ለአምላኩ ነግሮ ደምን በደም መመለስ መጀመሩን ወያኔ አሁን ማየት ከተሳነው ሲቆይ ይገባዋል።

እሳትና ጭድ አድርገን ለያይተነዋል ያሉት አማራና ኦሮሞ “የአንተ ደም የእኔ ደም ነው፣ ሞትህም ሞቴ ነው” በማለት በአንድነት ተነስተዋል። “አማራንና ኦርቶዶክስን አከርካሪውን ሰብረነዋል” ያሉት አቦይ ስብሃት ነጋ ሳይሞቱ ሰብረነዋል ያሉት ዘረኛ ድርጅታቸውን ሲሰባብረው ለማየት እድሜ ይመፅወቱ። በዘረፋና በግድያ የተካኑት ጠፍተው የነበሩት አሮጌ ህወሃቶች ብቅ እያሉ ለማቅራራት የሞከሩት የድርጅታቸው ሞት ቀርቦ ስላዩ ነው። አልዘገየም እንዴ?

በአውሮፕላንና በመኪና ተቀማጥለው ትግራይ የገቡ “ተፈናቃይ” ተጋሩዎች ህዝቡ ምንም አላለንም እያሉ እንኳ የተጫጩትና ያለቀሱ ዘረኞች ጎንደር፣ ባህርዳር፣ ቅሊንጦና በመላ ኦሮምያ ለሚሞቱ ኢትዮጵያውያን ትንፍሽ አለማለታቸው ምን ይባላል? ስዩም መስፍን ስለሆሎኮስት ሲናገር የህዝቡን ጩኸት ለመቀማት ፈልጎ ካልሆነ በመላ ኢትዮጵያ እስር ቤቶችና በትግራይ ባዶ ስድስት የግዞት ቦታዎች የሚፈፀመው ከሆሎኮስቱ በምን ይለያል። የዘር ፍጅት እየፈፀሙ መሆኑን ዓለም ያውቀዋልና።

የኢትዮጵያ እናቶች ተንበርክከው አልቅሰዋል። ይህ እንባ መድረቅ አለበት። እንባው የሚደርቀው  በጫጫታ፣ በማውገዝ፣ በሰልፍ ወይንም አብሮ በማልቀስ አይደለም። ህዝባዊ ትግሉ አሁን በተከተለው መንገድ ማለትም በማዕቀብ፣ በዝምታ፣ አድርባይን በማግለልና ምታቸው በምት ሲመለስ ነው። ሰሞኑን በጭስ እንደታፈነ አይጥ ከየጎሬው ወጥተው እንዲያላዝኑ ያደረጋቸው ህዝባዊ ምቱ ነው። ኢትዮጵያን ያስለቀሷትን በማስለቀስና ዳግም መከራ እንዳይመጣ አገራችን በጥሩ ህዝባዊ መሰረት ላይ እንድትደላደል በጋራ በመስራት ግድ ይለናል። በሃዘን የተቀበልነውን አዲስ ዓመት ወደዘላቂ የእናቶቻችን ደስታ እንቀይረው። ወይዘሮ ታደሉ ተማም የኢትዮጵያ ተምሳሌት ናቸው። የእሳቸውን እንባ ስናብስ ኢትዮጵያን እንታደጋለን።

 

Amerid2000@gmail.com

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.