ዳንኤል ክብረት እና የመሃል ሰፋሪነት ፖለቲካው [ዳዊት ግርማ]

daniel-kibret.jpg satenaw
ዳንኤል ክብረት

ዳንኤል ክብረት የተባለው ጸሐፊ በ“የቄስ ሚስት አወቅሽ አወቅሽ ቢሏት…” ቡዳ ከተበሉ ጥቂት የሃገራችን “ልሂቃን” ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ምናልባትም የእሱን ያክል የሁሉንም ሊጥ ላቡካ የሚል “ምሁር” ለማግኘት የሚከብድ ይመስለኛል፡፡ እውነት ነው አንደበተ ርቱዕ ነው፤ እውነት ነው አዋቂነትም አለው፡፡ በመንፈሳዊ እንቅስቃሴውና በእውቀታዊ እይታው፣ በሚሰጣቸው ማኅበራዊ ሂሶች በብዛት የሚታወቀው ዳንኤል አሁን አሁን በታዋቂነትና ዝና አጋባሽነት ውዳሴ ከንቱ ተጠልፎ ከተራራው ጫፍ ላይ በመንከባለል እየወረደ ነው፡፡ እናም ብዙ ሁነቶችን ተከታትዬ ከመታገስ በላይ ሲሆን ልጽፍለት ወሰንኩ፡፡

የሰውዬው ህመም የሚጀምረው ከ“ሁሉን-አወቅ” ባህርይው ነው፡፡ ዳንኤል ክብረት ማብራሪያ ያልሰጠበት የእውቀት ዘርፍ ስለመኖሩ እጠራጠራለሁ፡፡ ለምሳሌ ከታዘብኩት እንኳ ስለቤተ ክርስቲያን ፖለቲካ፣ ስለትዳር፣ ስለአድዋ ድል፣ ስለኢትዮጵያዊነት፣ ስለነገረ ቤተ ክርስቲያን፣ ስለፖለቲካ፣ ስለታሪክ (የቤተ ክርስቲያንም፣ የኢትዮጵያም፣ የዓለምም)፣ ስለኢኮኖሚ፣ ስለ አስተዳደር፣ ስለማኅበረሰብ፣ ስለያ-ትውልድ ወዘተ ዲስኩር ሰርቷል፤ ጽሑፍ ጽፏል፡፡ እያንዳንዱን ከላይ የተጠቀሱ ጉዳዮች ስንመለከት ራሳቸውን የቻሉ ትልልቅ የእውቀት ዘርፎች ናቸው- ዳንኤል የጨፈለቃቸው፡፡ በታሪክ የምናውቃቸው ትልልቅ ልሂቃን፣ ፍልሱፋን፣ አሰላሳዮች አንድ ዘርፍ ላይ አድምተው ይራቀቃሉ (specialize ያረጋሉ)፡፡ በርግጥ ከሁሉም አይነት ዘርፍ እውቀት ቢኖር እሰይ ነው፡፡ እንደአርስጣጣሊስ አይነት በሁሉም አውድ የበቁ አሰላሳዮች ነበሩ፡፡ ይህ ግን ሁሌም አይደገምም፡፡ ከየእውቀት ዘርፉ መረጃ ቢኖር ምሉዕነት ነው፤ በሁሉም አለሁበት ማለት ግን ያስገምታል፡፡

ይህን ሁሉ ዲስኩር ሲደሰኩርና ሲጽፍ ግን እውነትን ሲሸሻትና በተረት ሲያሽሞነሙናት እንጂ ከግፉዓን ተርታ በወጥ አቋም ሲሰለፍ አላየነውም፡፡ ይህን ያደርግ ዘንድ ግዴታ የለበትም ብለን አንዳንተወው ሁሉም ጋ አለሁ ብሎ ሲፈተፍት እናየዋለን- ፖለቲካውም ቤተ ክህነቱም ጋር፡፡ አጨብጫቢና ጭብጨባን ፍለጋ ሁሉ አይቅረኝ ማለት ግን እደግመዋለሁ ያስገምታል፡፡ ለዚህም ነው ዳንኤል የመሃል ሰፋሪነት እቃቃ ይጫወታል የምለው፡፡ በዚህ ወቅት፣ በተለይ በዚህ ወቅት ግን የመሃል ሰፋሪነት ፖለቲካ (የwin-win ጥቅመኝነት) አያስኬድም፣ አያዋጣምም፤ በሚሞቱ ንጹሃን ላይ እንደማሾፍ ይቆጠራልና፡፡ በንጹሃን ዜጎች ሞት ነግደህ ማትረፍ አትችልም፡፡ ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሰውዬውን መሃል ሰፋሪነት ያሳበቁ ሁለት ዲስኩሮቹ ናቸው፡፡ አንዱ “ህዝብን ሚፈራ መንግስት፣ መንግስትን የሚፈራ ህዝብ” በሚል ያወጣው ጽሑፍና ሌላው በሰንደቅ ጋዜጣ ላይ የሰጠው ቃለ ምልልስ ነው፡፡ ወደዝርዝሩ…

መሃል ሰፋሪነት

“መሃል ሰፋሪነት በሁለት ጥይት ያስመታል” የሚል አባባል ነበር በያ-ትውልድ ዘመን፡፡ ባጭሩ ወይ ከህዝብ ነህ (እንደኢህአፓ አይነት የፓርቲ ፖለቲካ አቋም ትይዛለህ)፣ አሊያ ከፋሺስት ደርግ ወግነሃል ማለት ነወ፡፡ እናም ወይ ከደርግ ወይ ከኢህአፓ በተተኮሰ ጥይት ትመታለህ (ደርጉ ኢህአፓ ነው ብሎ፣ ኢህአፓው ደርግ ነህ ብሎ ይመታሃል)፡፡

በነገራችን ላይ እንዲህ አይነት ሰዎች ስለሁለት ነገር መሃል ሰፋሪነትን የሚመርጡ ይመስለኛል፡፡ የመጀመሪያው ቦቅቧቃነት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ጥቅመኝነት ነው፡፡ ሁለተኛውን በጥቂቱ ሳብራራው ተከታይን ላለማጣትና ላለማስከፋት (ለምሳሌ የስርዓቱ ደጋፊዎችን ላለማጣትና ላለማስከፋት)፤ በሌላ መልኩም ከስርዓቱ የምታገኘውን የይሁንታ ጥቅም ላለማጣት የሚመረጥ አካሄድ ነው፡፡ ይሄም የሃይል ሚዛኑ እስኪያጋድልና አብረውት ወዳጋደለበት እስኪያጋድሉ ድረስ ይዘልቃል፡፡

ዳንኤል በአንጻሩ የሃይማኖት አባቶችን በግልጽ ይተቻል፤ መተቸትም አለባቸው፡፡  በዚህ ረገድም የህዝብን ሙሉ-በሙሉ ይሁኝታ ይሸምታል (ህዝብ ስለሚጠላቸው)፤ ወዲያውም ማሰሪያ/ማጎሪያ ቤት ስለሌላቸው የሚያስፈራው ነገር የለም፡፡ ከዚያ ቀጥሎ መንግስት አለ፤ እዚህ ላይ ወራጅ ይላል ዳንኤል “በአንተም ተው አንቺም ተይ” ቁማሩ የwin-win ስልትን ይጫወታል፡፡ የሃይማኖት ተቋማትና አባቶችን በረመረመበት አውድ መንግስት ጋር አይሳፈጥም፡፡ ሌላው ቀርቶ ለመንፈሳዊ ተቋማቱ ተቋማዊ ክስረት መሃንዲሱ መንግስት ሆኖ እያለ መንግስትን ሊተች ግን አይሞክርም፡፡ እናም ከይሁንታ ጥቅም በዘለለ ግዘፍ የነሳ ጥቅማጥቅምም ሳይልስ እንደማይቀር ከሁነቶች እጠረጥራለሁ፡፡ አንድ ማሳያ በአዲስ መስመር…

አንድ ጊዜ የእሱ መጽሀፍ ሲመረቅ የአዜብ መስፍንን ስም ጠርቶ በአደባባይ ስለእገዛዋ ውዳሴ-አዜብ አዘነበ፡፡ እንደውም በዚህ ወቅት ብዙዎቹ አድናቂዎቹ ከሁሉም አይነት ወገኖች ጋር ያለው “ዲፕሎማቲክ” ግብቡነት አንዱ ማሳያ አርገው ሲያዳንቁ ነበር (በተለይ አንዳንዶቹ ከመንግስት ጋር አስታራቂ መሲህ አድርገው ቆጥረውት ተደስተው ነበር)፡፡ ያኔ በጥርጣሬ አይን ነው “አውሬ አየኝ” ያልኩት፡፡

በ2003ዓ.ም አንድ የማኅበሩ አመራር ከአንድ መጽሔት (“ሎሚ” ይመስለኛል) ጋር በነበረው ቆይታ ከማብራሪያው ውስጥ ለኔ ያልታዬኝ ለዳንኤል ግን “ዝናውን የነካበት” ሽራፊ ንግግር በቃለ ምልልሱ ተናገረ፡፡ ዳንኤል ያዙኝ ልቀቁኝ አለ፣ አቧራ አስነሳ፡፡ የመሃል ሰፋሪነት ካርታውን ስቦ ይቆምር ጀመር፡፡ መንፈሳዊውን ማኅበር ከመንግስት ጋር በማላተም ትርፍ ማጋበዝ ከጀለ፡፡ ከዚያም ለደጄ ሰላም በጻፈው ግብረ-መልስ “ማኅበሩ መንግስት ሊዘጋን ነው እያለ ተራ አባላትን ያስበረግጋል” የሚል ተንኮል ወሽቆ፣ ከዚያም ያልፍና  “አንድ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ቅጂ ይዘው…” መረጃ አገኘን ብለው እንደሚቦርቁ አድርጎ ባለታላቅ አገራዊ ራዕዩን ማኅበር ዝቅ አድርጎ ለመሳል ሞከረ፡፡ ይህን ካደረገበት ቅጽበት ጀምሮ ሰውው ራሱ ዝቅ አለብኝ፡፡ እዚህ ላይ የማነሳው አንድ ደማቅ ነጥብ አለ፡፡ ማኅበሩን ለወያኔ መራሹ መንግስት ጃዝ በማለት የተንኮል ሴራ ሸርቦ ከመንግስት ጋር ሙርጥ መጋጠሙን አሳዬን፡፡ የበላበትን ወጭት ሰብሮ ለጠላት እሳት መጫሪያነት በልግስና አበረከተ፡፡ ዳንኤል ለማኀበረ ቅዱሳን ከሰራው፣ ማኅበሩ ዳንኤልን “ሰው ለማድረግ” የሰራው ይበልጣል! ይሄን እውነት የሚክድበት አቅም ካለው ይሞክር፡፡ ይሄ እንግዲህ ማኅበሩን የመስዋዕት በግ አድርጎ በማቅረብ ከመንግስት ድጋፍን ለመቃረም የተጫወተው የባለጌ ቀልድ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ብዙዎቹ የዳንኤል ተከታዮች፣ በተከታይ ብዛት ያንበሸበሹት እና ዝናውን ያናኙለት አንድም የማኅበረ ቅዱሳን ልጆች፣ አሊያም ደጋፊዎች፣ ወይም ለማኅበሩና ለቤተ ክርስቲያን ጥሩ ስዕል ያላቸው፣ ወይም ደግሞ በእነዚህ ሰዎች ተጽዕኖ የመጡ ሌሎች ናቸው፡፡ ያሳወቁትም፣ ያገነኑትም እነሱው ናቸው፡፡ እውነቱ ይህ ሆኖ እያለ ግን ከምንም አንስቶ ሰው ያረገውና ሰገነት ላይ ያወጣው ማኅበር ላይ ተንጋሎ ሊተፋ ሞከረ፡፡ በርግጥ ባለመረዳት ለእርሱ ተከታይ/ጭፍራ (fan) ሲሰብኩ ከነበሩት ውስጥ አንዱ እንደነበርኩ መካድ አልችልም፡፡

በወቅታዊው ጉዳይ ላይ ነጥብ ወደጣለባቸው ሁለት ሁነቶች ልምጣ፡፡ “ሕዝብን የሚያዳምጥ መንግስት፣ መንግስትን የሚያዳምጥ ህዝብ” ይለናል ዳንኤል፡፡ ይህን “ተረት” ሲደርስ ወቅታዊ  ጉዳዩን ተንተርሶ ነው፡፡ ሕዝቡ “አሁንስ በቃኝ” ብሎ የተነሳው ሕዝብን የሚያዳምጥ መንግስት ሽቶ ነው፡፡ ስለሌለ፡፡ ስለዚህ ህዝብን የሚሳደብ፣ የሚያዋርድ፣ አገርና ታሪክ የሚጠላ፣ ድንበር ቸርቻሪ አገር ገንጣይ፣ ዘረኛና ነውረኛ፣ አንድን ህዝብ ጠላቴ ብሎ ፈርጆ የዘር ማጥፋት የሚፈጽምን ወንበዴ ስርዓት ለመቀየር ተነሳ፡፡ 25 አመት ተነግሮት ያልሰማ ነው፡፡ ህዝብ ለውጥ ፈለገ፡፡ መንግስት የማያዳምጥ፣ 25 ዓመት ተነግሮት ያልሰማ ዳፍንት ስርዓት ነው፡፡ በርግጥ ይህ ጠፍቶት አይደለም፤ ከሁለቱም ወገን ላለማጣት እንጂ፡፡ እስኪ በሞቴ፤ እንዴት ነው ይህ መንግስት ህዝቡን ሊያዳምጥ የሚችለው? የሸጠውን ድንበር መልሶ? ያፈረሰውን ታሪክ አድሶ? የፈጀውን ህዝብ መልሶ? ነው ወይስ ስልጣን ለቆ ሌላ የሚያዳምጥ መንግስት ይምጣ ነው አባባልህ? ይህን እንኳ እንደማትል እናውቃል፡፡

“ህዝብም ተው፣ መንግስትም ተው” ስትል ምን ለማለት ፈልገህ ነው? መንግስት 100 ንጹሃን ገድሎ ከሆነ በ“አንተም ተው አንቺም ተይ” የድርድር ዘይቤህ መሰረት 50 “ብቻ” ይግደል ማለትህ ነው? እዚህ ጽሑፉ ላይ አንድ የህዝብ የብሶት ግጥም ያቀርብልናል፤

እዚያ ማዶ ሆኖ አንድ ሰው ተጣራ፣

እዚህ ማዶ ሆኖ አንድ ሰው ወይ አለው፣

ጎበዝ ተነቃቃ ይህ ነገር ለኛ ነው፡፡

“ማለት የሚችለው የሚያዳምጥ መንግስት ሲኖር ነው” ይለናል፡፡ ምን ማለት ነው? የሚያዳምጥ መንግስት ከሌለ ምሬትንም መናገር አይቻልም? ሲጀምር የቃል ግጥሙ ብሶት የወለደው የ“ተነስ”፣ የ“ተጠንቀቅ” ህዝባዊ የጥሪ ድምጽ ነው፡፡ እና በአጭሩ ዳንኤል “ተደማመጡ” ነው የሚለን፡፡ ከዚህ መንግስት ጋር መሆኑ ነው፡፡ እንዴት ይሆን የምንደማመጠው? (የጥይቱ ጩኸትስ መች ያሰማማና- lol አሉ ቀላጆች)፡፡ መንግስት በህዝብ ተበልጣል፣ ሃገር መምራት ብቃት የለውም፣ እናም ይልቀቅ! ብቸኛው አማራጭ ይሄ ብቻ ነው፤ እያልን ባለንበት ወቅት ዳንኤል “መንግስትና ህዝብ ተደማመጡ” ብሎ የመንግስትን እድሜ ሊያራዝም ይታትራል፡፡ ለመንግስት የእፎይታ ጊዜ ሊሸምትለት፡፡  ይህ አባባሉ ግን ወደፊት ራሱን መልሶ ይጸጽተዋል፣ አንድ ቀን ህሊናውን ይጎረብጠዋል፡፡ ባልሆነ መላምት፣ በተኮላሸ ማብራሪያ ህዝብን ከማደናገር አርፎ መቀመጥ ትልቅ ፋይዳ አለው፡፡

“የአጼ ዘርአ ያዕቆብ ወታደሮች የሰው አንገት ቆርጠው ገና ይጫወቱ ነበር” እያለ ተረት የሚተርትልን ዳንኤል የአንድን መንግስት አምባገነናዊ አካሄድ ለመግለጽ 600 ገደማ ዓመታትን ወደኋላ አዝግሟል፡፡ ውድ ዳንኤል ስለአምባገነንነት ለማውራት ወቅታዊውን ጉዳይ ለመግለጽ ምንኛ ብትፈራ ነው 600 ዓመታት ገደማ የሸሸኸው? ትናንት ጎንደር (ዐማራ) ላይ የወያኔ/አጋዚ ወታደሮች አባትን ፊት ለፊት አቁመው እንዲያይ እያደረጉ ሴት ልጆቹንና ሚስቱን ሰደፍሩ ምነው ለምሳሌ አልበቃልህ አለ? ወጣት እየታደነ “ቶርቸር” ሲደረግበት፣ ሲሰቃይ፣ ትናንት ህዝብ (አማራውና ኦሮሞው) በጠራራ ጸሐይ በጨካኝ የወያኔ ጥይት ግንባር ግንባሩን ሲባል የት ነበርክ?  ለዚህ ነው የሽሽት ተረት ተረት አታውራን የምልህ!

ሁለተኛው፡፡ ከሰንደቅ ጋዜጣ ጋር ባደረገው ቆይታም በተመሳሳይ “መሃል ሰፋሪ” ትንታኔ ሰጥቷል፡፡ “የሃይማኖት መሪዎች መካከለኛ ሚና መጫወት አለባቸው” ይለናል ቃል በቃል- የእሱን መንፈስ ሲያጋባ፡፡ ደግነቱ “የሃይማኖት አባቶቹ” ከሱም ብሰው የመንግስት ብቻ አፍ ናቸው፡፡ ይባሱኑ እንዲህ ይላል፤ “መንግስትንም ሆነ ህዝቡን መደገፍ ሳይጠበቅባቸው (የሃይማኖት መሪዎቹ) እውነትን ደግፈው ሊቆሙ ይገባል”፡፡ ይሄኔ ነበር ጲላጦስ “እውነት ምንድነው?” ብሎ መጠየቅ የነበረበት፡፡ እውነት ግን ማናችን ጋር ነው ያለችው? ገዳዩና ግፈኛው መንግስት ጋር ወይስ ተገዳዩና አሳረኛው ንጹሃን ህዝብ ጋር? ወደፊት አንድ ቀን ትመልሰዋለህ፡፡ እንዲህ ይቀጥላል፤ “… አንተ አታስፈልገኝም የሚለውም ይህን አቋሙን ትቶ ተቀራርበው ወደ ሰላም የሚመጡበትን መንገድ…” እንግዲህ መንግስትና ህዝብ የሚታረቁበትን የመፍትሄ ሃሳብ ለሃይማኖት መሪዎቹ እየጠቆመ መሆኑ ነው፡፡ ዳንኤል እመከረን ነው እንግዲህ፣ ““አታስፈልገንም” (መንግስትን) የሚለውን አቋምህን ተውና መከራና ግፉን ችለህ ሰጥ ለጥ ብልህ አርፈህ ተገዛ”፡፡ ግሩም ተደራዳሪ ነህ ባክህ!፡፡ ህዝብ መከራውን ታግሶ መንግስትን 25 ዓመት ሙሉ የእፎይታ ጊዜ ሰጠው፡፡ የሚሆን ስላልሆነ የግፉ ጽዋ ሞልቶ ሲፈስ “በቃኝ” አለ፡፡  በእሱ አገላለጽ “አታስፈልገኝም” አለ፤ ወይም ለውጥ ፈለገ፡፡ ዳንኤልም ተረቱን ቀጠለ “ይህን አቋም” ተው እያለን ነው፡፡ ከዛም አፌዘ “ተቀራርበው” እና “ወደ ሰላም” ብሎ፡፡ በእውነት ገብተውት ከሆነ እነዚህን ሁለት ሹፈቶች ቢያብራራልኝ ምንኛ በወደድኩ፡፡ እየተገደሉ ያሉት ወገኖቹ አይደሉም? ነው ወይስ አሻግሮ አላሳይ ያለው ያለው ሌላ ምክንያት አለው?፡፡ ይህን ስል ሰላም ጠል ሆኜ አይደለም፤ ማንም ሰላምን የሚጠላ የለም፡፡ አሁን ለተነሳው አመጽ ግን ብቸኛው የመፍትሄ ሃሳብ የወያኔ ስርዓት መወገድና መወገድ ስለሆነ ብቻና ብቻ ነው፡፡

የዳንኤል ሃሳብ League of Nationsን አስታወሰኝ፡፡ ፋሺስት ጥሊያን በግፍ ሉአላዊዋን ኢትጵያ ወርራ ንጹሃንን በመርዝ ጭስ ጨረሰች፡፡ የኢትዮጵያ አርበኞችና እምቢ ለሃገሬ ያሉ ዘማቾ እጅግ ያልሰለጠነ የጦር መሳርያ መታጠቃቸውና ወራሪዋ ፋሽስት ደግሞ የአውሮፓ ስልጣኔ ያፈራቸውን ትልልቅ ዘመናዊ ጦር ታጥቃ እስከ መርዝ ጭስ ድረስ መጠቀሟ እየታወቀ League of Nations የተባለው ጉባኤ-ደናቁርት ግን ሁለቱም ሃገሮች ላይ አንድ አይነት (መሳርያ) ማዕቀብ ጣለ፡፡ የዳንኤል ዳኝነት ማለት ይሄ ነው፡፡ መንግስትና ህዝብን በእኩል አይን ያያል- “ተቀራርበው” ይልሃል፡፡ “ወደሰላም መንገድ” ምን ማለት ነው? አሁን ባለው ሁኔታ ነገሮች ጋብ አሉ፣ ቆሙ ወይም “ሰላም” ወረደ ማለት እኮ በሌላ ቋንቋ ወያኔ ይቀትል ማለት ነው፡፡

እዚሁ ቃለ ምልልስ ላይ ጋዜጠኛው ስለእምነት ተቋማት ተቋማዊ ክስረት ሲያነሳለት እንዲህ ይመልሳል፤ “ብዙ ሰው ቤተ ክህነቱን ያደከመው ቤተ መንግስቱ ነው ይላል፡፡ እኔ ግን በዚህ አልስማማም፡፡ ምክንያቱም ቅድም እንደነገርኩህ በነአምደ ጽዮንና አጼ ዘርዓ ያዕቆብ ጊዜ ቤተ መንግስቱ ባስቸገረ ጊዜ ጠንካራ ቤተ ክህነት ነበረን፡፡ በዚህ ዘመንም ጠነካራ ቤተ አምልኮዎች ቢኖሩ ጠንካራ ቤተ መንግስት ኖረን ነበር፡፡ ነገር ግን ቤተ መንግስቱ የቤተ አምልኮዎቹ  (ቤተ ክህነቶቹ) ነጸብራቅ ነው፡፡” ጽሁፍ ላይ መሳቅ ቢቻል ፍርፍር ብዬ እስቅ ነበር፡፡

ፓትርያርክ ሾሞ ሲኖዶስ ሰይሞ የሚሰጥ፤ የካድሬ ስብስብ መጅሊስ የሚፈጥር መንግስት ባለባት ሃገር ይህን መሰል አስተያየት መስጠት ወይ ህዝብን መናቅ ነው አሊያ መቅለል ነው፡፡ ጭራሹኑ “እንዲያውም የቤተ መንግስቱ ችግር ቤተ ክህነቱ ነው ባይ ነኝ” ብሎ ዘብጥያ ቤት የሌለበትን ተቋም በቴስታ አጋጭቶ ከባለከርቸሌው መንግስት ጋር ይሞዳሞዳል፡፡ እንዲህ ነው ከበለጥክም አይቀር፡፡ (በቅንፍ በምንም አይነት ሁኔታ ለቤተ ክህነቱ አልወገንኩም- አልወግንምም- የበከተ ተቋም መሆኑን አውቃለሁና)፡፡

ወያኔ ጫካ ውስጥ ሆና “አከርካሪውን ለመስበር” ያቀደችው አማራንና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን እንደነበር እና በለስ ቀንቷቸው መሃል አገር ሲገቡ ግማሾቹ በፖለቲካ ስልጣን የአራት ኪሎውን ቤተ መንግስት ሲይዙ ግማሾቹ ደግሞ በመንፈሳዊ ስልጣን የአራት ኪሎውን ቤተ ክህነት እንደተቆጣጠሩ መቼስ ላንተ አላስረዳህም፡፡ ይችን ይችን ደፍረህ አትላትም፤ ልጅ አሳዳጊ ነሃ፡፡ መተቸት ካለብህ አቋም ይዞ እውነትን ተመርኩዞ መተቸት፣ ያለፍርሃት፣ ካልሆነ ከዚያ የራቀ አንድ ሙያ መርጦ እዛ ላይ መራቀቅ፣ ካልሆነ ካልሆነ አርፎ ልጅን ማሳደግ፡፡ በርግጥ የቁርጡ ቀን ሲመጣ ምርጫ አይኖርም፡፡

በነገራችን ላይ ዳንኤል አያሌ ጭፍሮችን መሰብሰብ የቻለ ሰው ነውና ከጭፍሮቹ መራር ውርጅብኝ እንደሚደርስብኝ እጠብቃለሁ፡፡ በምክንያታዊነት ብትሞግቱኝ ጎንበስ ብዬ እቀበላለሁ፡፡ ከዚያ ባለፈ ከግለሰብ በላይ ለሃሳብ ልዕልና ብንገዛ መልካም ይሆናል፡፡ ለግለሰብ ከማጨብጨብና ግለሰብን ከማምለክ በላይ እውነታን ብናነጽር ወይም ሃሳብ ላይ ብንሟገት የተሸለ ነው፡፡ “አንተ ማን ሆነህ ነው ታላቁን እንትናን እንደዚህ የምትለው…” አይነት መከራከሪያ ስንኩል ነው፣ የትም አያደርሰንም፡፡

ለማጠቃለል

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም “መክሸፍ እንደኢትዮጵያ ታሪክ” የተሰኘው መጽሃፋቸው ላይ ዳንኤል ለሰጠው ችኩል አስተያየት መልስ ሲጽፉ፡- “ያውቃል እንዲባል የሚጽፍ እንጂ አውቆ የሚጽፍ አይመስልም” ብለውት ነበር፡፡ የመሃል ሰፋሪነት ፖለቲካ በአሁኑ ሰዓት አያዋጣም፣ ተበልቶበታል፡፡ ሊበላበት የመቻል እድል ቢኖር እንኳ አሁን ጊዜው አይደለም፡፡ አሁን ሰው እየሞተ ነው፡፡ በነብሰ በላ ስርዓት ደሙ በየጎዳናው እፈሰሰ ነው፡፡ አማራው ላይ የዘር ማጥፋት ዘመቻ ተከፍቶበታል- በመንግስት መሆኑን ነው እነገርኩህ ያለሁት፡፡ ኦሮሞ ሲገደል ነው የባተው፡፡ ኢትዮጵያ ላይ ጥፋት አውጇል፡፡ በንጹሃን ደም ላይ “ዊን-ዊን” መጫወትና ከሁለቱም አቅጣጫ ጥቅም ለማጋበስ መውተርተር ወራዳነት ነው፡፡ የእውቀት ማብላያ፣ የመረጃ መጋርያ፣ የአብዮት መድረክ በሆነው ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ስለሴት ልጅ አረማመድና ዳሌ በቁጭት የሚጽፈው አሌክስ አብርሃምም አንዱ ያንተ ቢጤ ነው፡፡ አውሬ አየኝ!፡፡ ሌሎች “ምሁራንን”፣ “ጸሐፍትን”፣ “የጥበብ ሰዎችን”፣ “ታዋቂዎች/ዝነኞችን”፣ “ፖለቲከኞችን”፣ “ድርጅቶችን”፣ “የፖለቲካ ፓርቲዎችን”፣ ሁሉንም ይመለከታል፡፡ እነዚህ ሁሉ ከህዝብ ጎን ቆመው መንግስትን የመውቀስ በቃህ የማለት ግዴታ አለባቸው፡፡ ይሄ የሰሞኑ ጉዳይ አማራጭ የምታማትርበት አይደለም፣ ወደጎን ገሸሽ የምትልበት አይደለም፣ “ፖለቲካ አልወድም” የምትልበት፣ ኮንሰርት የምታዘጋጅበት፣ የምትጠጣበት፣ የምትሰክርበት፣ የእንግሊዝ ኳስ የምታወራበት፣ ሚስቴ ልጄ የምትልበት፣ ሌላ ሌላም የምታረግበት፣ ሌላ ሌላም የምትልበት ጊዜ አይደልም፡፡ ወደህ አይደለም ተገደህ፤ ህሊናህ ረፍት ነስቶህ አሰላለፍክን  ከህዝብህ ጎን የምትቆምበት ጊዜ ነው! ስምንት ነጥብ!፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.