ኢቦላ የዘመኑ ታላቅ መቅሰፍት

ኢቦላ-ባለፉት ሰባት ወራት አራት ሺሕ ስድስት መቶ ያሕል ሰዎች ገድሏል።ከአስር ሺሕ በላይ ለክፏል።የሰወስቱን የምዕራብ አፍሪቃ ሐገራት ምጣኔ ሐብት አሽመድምዶታል።ዩናይትድ ስቴትስ እና ስፓኝም ቢያንስ አራት ዜጎቻቸዉ ተለክፈዋል።ዛሬ ሁሉም ዓለም ከISIS ቀጥሎ የመቅሰፍቱን ታላቅነት ያወራል።መቅሰፍቱን ለማስወገድ ግን አሁንም ሩቅ ነዉ።

«ያጋጠመን ይሕ የጤና ቀዉስ በዘመናዊዉ (ታሪክ) አቻ የለዉም።»

pc-140906-ebola-liberia-mn-1050_f3a0febfd3e2fd689b919385c5d00a81የዓለም ጤና ድርጅት ሐላፊ ብሩስ አይልዋርድ።የኤቦላ ቀዉስ የደረሰበት ደረጃ መነሻ፤ የዘመኑ ዓለም ሌሎች ቀዉሶችን ለማስወገድ የወሰደዉ እርምጃ ማነፃፀሪያ፤ በዘመኑ አቻ ያልተገኘለትን ቀዉስ ለማቃቀል የወሰደና የሚወስዳቸዉ እርምጃዎች እንዴትነት መድረሻችን ነዉ።ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።

ብዙ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚስማሙበት የአዲሱ ዓመአት ወታደራዊና ፖለቲካዊ ታላቅ ቀዉስ የዘመኑ ዓለም ብቸኛ ልዕለ ሐያል ሐገር ዩናይትድ ስቴትስ በአሸባሪዎች የተጠቃች ዕለት የተጀመረዉ ነዉ።መስከረም 11 2001 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ።)አስገድደዉ በጠለፏቸዉ የመንገደኞች አዉሮፕላኖች ኒዮርክና ዋሽግተንን ያሸባሩት አጥፍቶ ጠፊዎችን ያዘመተዉ አልቃኢዳ የተባለዉ አሸባሪ ድርጅት መሆኑን ለማመን፤ በአልቃኢዳና በተባባሪዎቹ ላይ ጦርነት ለማወጅ ዓለም የፈጀበት ጊዜ ዘጠኝ ቀን ነበር።

ዛሬ ምሽት ዩናትድ ስቴትስ ኦቭ አሜሪካ ለታሊባን የሚከተሉትን ጥያቄዎች ታቀርባለች።በሐገራችሁ የተሸሸጉ የአልቃኢዳ መሪዎችን በሙሉ ለዩናይትድ ስቴትስ አስረክቡ።አሜሪካኖችን ጨምሮ በሕገወጥ መንገድ ያሰራችኋቸዉን የዉጪ ዜጎች በሙሉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ልቀቁ።—–የአሸባሪዎች ማሰልጠኛ ተቋማትን በሙሉ ባስቸኳይና ለዘለቄታዉ ዝጉ።አሸባሪዎችንና ተባባሪዎቻቸዉን አስረክቡ፤አነዚሕ ጥያቄዎች ለዉይይትና ለድርድር አይቀርቡም።ታሊባን የተባለዉን ባስቸኳይ ገቢር ማድረግ አለበት።አሸባሪዎችን ማስረከብ አለባቸዉ።አለበለዚያ የነሱን እጣ ይጋራሉ።»

ፕሬዝዳንት ጆርጅ ዳብሊዉ ቡሽ።መስከረም 20 2001።ማስጠንቀቂያዉ በታወጀ በአሥራሰባተኛዉ ቀን አፍቃኒስታን በዩናይትድ ስቴትስና በተባባሪዎችዋ ጦር ቦምብ፤ሚሳዬል፤ ጥይት አረር ትጋይ ገባች።ድፍን ዓለምም ጦር ከማዝመትእስከ ምጣኔ ሐብት ማዕቀብ፤ ተጠርጣሪዎችን ከማሰርእስከማሰቃየት ለደረሰዉ ዘመቻ ቢሊዮነቢሊዮናት ዶላር ይከሰክስ ገባ።

ዓለም ከኢንፉሌንዛእስከ ተስቦ፤ ከታይፎይድ እስከ ኮሌራ፤ ከፈንጣጣ እስከ ሳምባ ነቀርሳ ባሉ ወረርሺኞች በየዘመኑ ሚሊዮናት ወገኖቹ ረግፈዉበታል።የየዘመኑ መሪዎች አደጋዎቹን ለመቀነስ ያደረጉት ጥረትና የወሰዱት እርምጃ በርግጥ ፖለቲካዊና ወታደራዊ የበላይነትን ለማረጋገጥ ከወሰዷችዉ እርምጃዎች እኩል ፈጣን፤ዉጤታማም አልነበሩም።


ፈጠነም ዘገየ
የየዘመኑ ገዢዎች፤ ፖለቲከኞች፤ ባለሐብቶችና አዋቂዎች ከየጥፋቶቹ ተምረዉ ወይም ለትርፍ አስበዉ ባደረጉት ጥረት የዛሬዉ ትዉልድ በጥንቶቹ የጤና ቀዉሶች ከማለቅ ድኗል።ከሌላ የጤና ቀዉስ ግን አላመለጠም።

በአንዲት አሜሪካ የደረሰ ጥቃትን ለመበቀል ወር ባልሞላ ጊዜ ጦሩን፤ ሐብቱን፤ አዉቀቱን ለጦርነት ለማፍሰስ ያደመዉ የዘመኑ ዓለም ከ1981 ጀምሮ ከ36ሚሊዮን በላይ ሕዝብ የፈጀዉን ኤች.አይ.ቪ አድስን ለማስወገድ አልቻለም።ወይም አልፈለገም።ለማስወገድ አይደለም የተሕዋሲዉን ስርጭት ለመቀነስ እስካሁን ያደረገዉ ጥረት ጥቂት፤ ዉጤም ኢምንት ነዉ።33 ዓመቱ።

ዛሬም ከ35 ሚሊዮን የሚበልጥ ሕዝብ ከHIV-AiDS ጋር ይኖራል።የዚሕ ሕዝብና የብጤዎቹ ሥጋትና ችግር ዓለምን የመዘወር ጉልበቱ፤ሐብቱ፤ እዉቀቱ ያላቸዉ ሐያላን ችግር ባለመሆኑ ሥጋትችግሩ የዓለም ርዕስ አይደለም።ኢቦላ ከኤች አይ ቪኤድስ በፊት ይታወቃል።1976

«ኢቦላ አስፈሪ በሽታ ነዉ።በሽታዉ ለመጀመሪያ ጊዜ ከታወቀበት ከ1976 ጀምሮ የገደላቸዉ ሰዎች ቁጥር ግን1500 ነዉ።ይሁንና ኢቦላ በጣም አደገኛ እና ብዙ ሰሰዉ ሊፈጅ እንደሚችል የጤና ባለሙያዎች የሚሰጉበት ብዙ ምክንያት አላቸዉ።»

የዓለም ሐያላን የቀድሞዉ የሊቢያ መሪ የኮሎኔል መዓመር ቃዛፊን ከነሥርዓታቸዉ የገደለዉን የአየርና የባሕር ድብደባ ለመክፈት የፈጀባቸዉ አንድ ወር ነበር።የካቲት አስራአምስት/2011። የቀድሞዎቹ አማፂያን ከጋዛፊ መንግሥት ጦር ጋር በነፍጥ መጋጭት ጀመሩ።መጋቢት19።የፈረንሳይ፤የብሪታንያና የዩናይትድ ስቴትስናጦር ሐይል የሊቢያን ሕዝብ ከሊቢያዉዊዉ ገዢዉ« ነፃ ለማዉጣት»ያየር፤ የባሕር ድብደባ ጀመረ።

የኢቦላ አስጊ፤ አስፈሪ፤መድሐኒት አልባነት ሲነገር በሽታዉ በጣሙን ከዛሬዋ ኮንጎ፤ ዩጋንዳና አካባቢዉ እያሰለሰ መቶዎችን እየገደለ ብቅ ጥልቅ ሲልዓመታት አስቆጥሯል።ገዳዩን በሽታ ለመከላከል የሚረዳ መድሐኒት ለመፈለግ የሞከረ አዋቂ፤ አዋቂዎች እንዲመራመሩ ገንዘብ የመደበ መንግሥት፤ ድርጅት፤ባለሐብት የለም።ካለም አልተሰማም ወይም ከቤተሙከራ አልወጣም።ሰላሳስምንት ዓመቱ።

በሠላሳሥምንት ዓመቱ ዘንድሮ ያዉ በሽታ ጊኒ ላይ ሰዉ መልከፍመግደሉ ሲነገርም ለዓለም ዘዋሪዎች ፖለቲከኞች፤ ቱጃሮች፤ አዋቂዎች እና ጋዜጠኞች «ለመደመጥ የሚበቃ» ዜና አልነበርም።የኢቦላ ገዳይ አስጊነት የሐያል ሐብታሙን ዓለም ቀልብ ለመሳብጊኒ፤ ላብሪያ እና ሴራሊዮን ሺ ዜጎቻቸዉ በበሽታዉ እስኪሞቱ፤ ሌሎች ብዙ ሺሕ ተጨማሪ ዜጎቻቸዉ ወደ ሞት በሚያጉዛቸዉ ተሕዋሲ እስኪለከፉ ወራት መጠበቅ ግድ ነበረባቸዉ።ኢቦላን ለመከላከል ዓለም አቀፍ እርምጃ መዉስድ እንደሚያስፈልግ የዓለም መሪዎች መናገር የጀመሩት መቅሰፍቱ መከሰቱ በታወቀ በሰባተኛ ወሩ ነበር።መስከረም።

« የፈጠጠዉ እዉነት ይሕ ነዉ።ኢቦላ ምዕራብ አፍሪቃ ዉስጥ ከዚሕ ቀደም አይተነዉ የማናዉቀዉ ከባድ ወረርሽ ነዉ።ከቁጥጥር ዉጪ እየወጣ ነዉ። ሥርጭቱ መግታት) ከባድ ፈተና ነዉ።ይሁንና ተስፋ የሚሰጠን ነገር አለ።በሽታዉን እንዴት መከላከል እንዳለበት ዓለም ያዉቀዋል።ድብቅ አይደለም።ሳይንሱን እናዉቀዋለን።መከላከያዉን እናዉቀዋለን።በተሕዋሲዉ የተለከፉትን እንዴት ማከም እንዳለብን እናዉቃለን።ተገቢዉን እርምጃ ከወሰድን ይሕወት ማዳን እንችላለን።ግን ፈጣን እርምጃ መዉሰድ አለብን።»

የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦቦማ።መስከረም 17-2014።ከለንደን፤ከበርሊን፤ ከፓሪስ፤ከኒዮርክ ብራስልስ፤ ከአዲስ አበባም ተመሳሳይ ጊዜ፤ተመሳሳይ ቃል ተሰምቷል።ቃሉ በርግጥ ዘግይቷል።ዘግይቶም እስካሁን በሽታዉን ለመከላከል የተወሰደዉ ተጨባጭ እርምጃ የበሽታዉን ሥርጭት ለመግታት ከሚያስፈልገዉ ጋር ሲነፃፀር ኢምንት ነዉ።

የበሽታዉን አደገኛነት፤የስርጭቱን ፈጣንነት ከብዙዎቹ መንግሥታትና ድርጅቶች ቀድሞ ያስታወቀዉ የተባበሩት መንግሥታት የጤና ድርጅት በሽታዉን ለመከላል ያስፈልገኛል ያለዉን መቶ ሚሊዮን ዶላር እንኳ እስካሁን አላገኘም።

I S A R-Germany የተሰኘዉ ድርጅት ሐላፊ ክርስቶፍ ቦንስማን እንደሚሉት ደግሞ የአለም ጤና ድርጅት ራሱ የበሽታዉን ሥርጭት አዉቆ ለማሳወቅዘግይቷል።

የዓለም ጤና ድርጅት በሚገባዉ ፍጥነት እርምጃ አልወሰደም።የቀዉሱን አደገኛነትም በቅጡ አላጤኑትም ነበር።ሥለዚሕ መልስ አልነበረም።ዛሬ ድረስ አንኳ ላይ ቤሪያ ዉስጥ የአለም ጤና ድርጅት አንድም (የበሽተኛ)አልጋ የለዉም።ያሉት በአብዛኛዉ ድንበር የለሽ ሐኪሞች ያቋቋመዉ (ሆስፒታል) 220 አልጋዎች ብቻ ናቸዉ።የዓለም ጤና ድርጅት 500 አልጋዎች ያሉት (ሆስፒታል) ለመክፈት አቅዷል።እስካሁን ግን መሬት ላይ ምንም የለም።»

ችግሩየበለፀገዉ ዓለም ችግር ሥላይደል የዓለምም፤ ሐያላኑ የሚያሾሩት፤የሚደጉሙት ድርጅትም ችግር አልሆነምም።ጋናዊዉ የቀድሞዉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ኮፊ አናንጥሩ አብነት አላቸዉ።«ሳርስ»የተሰኝዉ የመተንፈሺያ አካላት በሽታ በ2003 የተሠራጨ ጊዜዓለም የወሰደዉን ፈጣን እርምጃ ከኢቦላዉ ጋር ያነፃፅሩታል።

«ኢቦላ አዲስ አይደለም።ከእርባ ዓመት በፊት ነዉ የታወቀዉ።አሁንም የዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ አዝጋሚ እርምጃ በጣም አሳዝኖኛል።አንድ ዓለም ዉስጥ ነዉ ያለነዉ።ሳርስ የተከሰተ ጊዜ የተወሰደዉን እርምጃ አይተናል።በሽታዉ በተከሰተ በአስራሁለት ሰዓት ዉስጥ ባሕርገመገም አቋርጦ ከእስያ እስከ ካናዳ ፈጣን እርምጃ ነበር የተወሰደዉ።እኔ የምወቅሰዉ አቅም ያላቸዉን መንግሥታት።»

የችግሩ ባለቤቶችስ ምን አደረጉ?ነዉ የማይቀረዉ ጥያቄ። አፍሪቃ።የምዕራባዉያኑ ፍላጎት፤ ወጪ ና ትዕዛዝ ሲኖር ከማሊ እስከ ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፕብሊክ፤ ከሱዳን እስከ ሶማሊያ ጦር ለማዝመት የሚሽቀዳደሙት የአፍሪቃ መሪዎች ሺዎችን የሚያረግፈዉን በሽታ ለመግታት ወይም መግታት ለሚችሉት አቤት ለማለት ወራት ፈጅተዋል።

የአፍሪቃ ሕብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ወይዘሮ ድላሚኒ ዙማ የኢቦላ ስርጭትን ለመግታት ፖለቲካዊ እርምጃ እንደሚያስፈልግ የተናገሩት ባለፈዉ ሳምንት ነዉ።የበለፀጉት ሐገራት ርዳታ የሚሰጡት መልካም አስተዳደር ለመሠረቱ፤ሙስናን ለሚዋጉና ሠብአዊ መብት ለሚያከብሩ መንግሥታት እንደሆነ በጠጠር ያለ መልዕክት ማስተላለፍ ከጀመሩ ወዲሕ ብዙዎቹ የአፍሪቃ ፖለቲከኞች ምርጫ የሚሉትን ማሳከሪያ ያደራጃሉ።

ኢትዮጵያን ጨምሮ አብዛኞቹ የአፍሪቃ መንግሥታት የሰብአዊ መብት አስከባሪ ድርጅት፤ ፀረሙስና ኮሚሽን የሚሏቸዉን መስሪያ ቤቶች መሥርተዋል።መንግሥታት የሚቆጣጠሯቸዉ መስሪያ ቤቶች እራሳቸዉ መንግሥታቱ ወይም የመንግሥታቱ ባለሥልጣናት የሚፈፅሟቸዉን የሰብአዊ መብት ረገጣዎች፤ የሚያደርሱትን ዘረፋ ሊያስቆሙ በርግጥ አይችሉም።አላስቆሙም።

ጥናቶች እንደሚጠቁሙት አፍሪቃ በፀረሙስና ኮሚሽኖች ከተጥለቀለቅች ወዲሕም በየአመቱ በትንሽ ግምት አንድ ቢሊዮን ዶላር በሙሰኛ ባለሥልጣናትዋ ትዘረፋለች።ሚሊዮን ዜጎችዋ ግን በበሽታ፤ በረሐብና ዘራፊ ፖለቲከኞችዋ በሚዘዉሩት ጦርነት ያልቃሉ።ላይቤሪያ ለየአንድ መቶ ሺሕ ዜጎዋ አንድ ሐኪም ነዉ ያላት።የሴራሊዮን፤ የጊኒ የሌሎችም የብዙዎቹ የአፍሪቃ ሐገራት አዉነታም ከዚሕ የተለየ አይደለም።ኢቦላ ደግሞ ወትሮም ከቁጥር ከማይገቡት የሰወስቱ ሐገራት የጤና ባለሙያዎችና እነሱን ለመርዳት ከዘመቱ የዉጪ ሐገር የጤና ባለሙያዎች መሐል ከ400 የሚበልጡትን ለክፏል ገሚሶቹም ሞተዋል።

አቅም ያለዉዓለም ችግሩ ያልሆነዉን ችግር ለማሰወገድ ባለመጨነቁከተወቀሰ፤ አቅም የሌላቸዉ ግን ችግሩችግራቸዉ የሆነዉ መንግሥታት ማድረግ የሚችሉት ባለማድረጋቸዉ የማይወገዙበት ምክንያት በርግጥ ሊኖር አይችልም።

«ሞንሮቪያን በመሠለ ከተማ ኢቦላ በሽተኛ የሚታከምበት አንድም አልጋ አለመኖሩ ሲሰማ ሁኔታዎቹ ምን ያክል አሳሳቢ እንደሆኑ ትረዳለሕ።ሌላዉን መዉቀሱ ብቻ በቂ አይደለም። የአፍሪቃ መንግሥታትና የአካባቢዉ ሐገራት የበለጠ ማድረግ ነበረባቸዉ። ባስቸኳይ እርዳታ እንዲደረግ መጠየቅም ይችሉ ነበር።ዓለም አቀፉ ማሐበረሰብ የተሻለ መርዳት እና እርዳታዉን ለማቅረብ እራሳችንን በቅጡ ማደራጀት እንችል ነበር።ወራት ማስቆጠር አልነበረብንም። ኢቦላባለፉት ሰባት ወራት አራት ሺሕ ስድስት መቶ ያሕል ሰዎች ገድሏል። ከአስር ሺሕ በላይ ለክፏል።የሰወስቱን የምዕራብ አፍሪቃ ሐገራት ምጣኔ ሐብት አሽመድምዶታል።ማሕበራዊ እንቅስቃሴን አዉኮታል። ዩናይትድ ስቴትስ እና ስፓኝም ቢያንስ አራት ዜጎቻቸዉ ተለክፈዋል። ዛሬ ሁሉም ዓለም ከISIS ቀጥሎ የመቅሰፍቱን ታላቅነት ያወራል።መቅሰፍቱን ለማስወገድ ግን አሁንም ሩቅ ነዉ።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

source : dw

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.