የኛ ነገር፤ ትግሬን መነጠል፤ ሐሳዊ-ኢትዮጵያዊነት ነው፤ [ተክለሚካኤል አበበ]

ተክለሚካኤል አበበ፤

 • tigre 2ሰሞኑን በሰጠሁት በትግሬነት ላይ የሚሰነዘረው ውግዘት ትክክል አይደለም የሚል አስተያየት ላይ፤ የተለያዩ ሀሳቦች ተሰንዝረዋል፡፡ የሚነሳው የተዛባ አመለካከት ከገመትኩት በላይ አሳሳቢና፤ የመልስ ዘረኝነት ወይም ጥላቻ፤ ፈረንጆች reverse racism የሚሉት ነገር የተጸናወተው ይመስላል፡፡ የብዙዎቹ ትችት አሁን ያለው የኢትዮጵያ መንግስት የትግሬዎች መንግስት ስለሆነ፤ መንግስት ለሚፈጽመው ጥፋት ትግሬዎች ሁሉ ተጠያቂ ናቸው የሚል ድምጸት አለው፡፡ ብዙዎቹ ተቺዎች፤ ትግሬዎች ሕወሀት ካልሆኑ ያረጋግጡልን የሚል ፈተና ያቀርባሉ፡፡ ነጻ መሆናቸውን ካላረጋገጡ በስተቀር፤ ትግሬዎች ሁሉ ወንጀለኞች ናቸው አይነት ነገር፡፡ ይሄ፤ አለም የተቀበለውን፤ እኛም በአገራችን እንዲሰፍን የምንመኘውን የነጻነት መርህ የሚጻረር፤ ከምንም በላይ ደግሞ ጸረ-ኢትዮጵያዊ የሆነ አቋም ነው፡፡

 

 • ትናንትናና ዛሬ ሕወሀት/ኢህአዴግ፤ ነጋሪት ጎስሞ፤ አዋጅ ነግሮ፤ የኢትዮጵያን ችግር ሁሉ የፈጠረ አማራ ነው ሲል፤ ያንን ስንቃወም የኖርን ሁላ፤ አሁን ደግሞ መልሰን የኢትዮጵያ ችግር ሁሉ ፈጣሪ ትግሬ ነው ስንስል፤ ለሕወሀት/ኢህአዴግ የአመታት ዘመቻ እጅ ብቻ ሳይሆን፤ እግርም እየሰጠን ይመስላል፡፡ እነሆ ከ25 አመታት በኋላ፤ አያቶቻቸውና አባቶቻቸው፤ ኢትዮጵያን ከውስጥም ከውጭም ጠላት ለመከላከል፤ በኢትዮያዊነት ኩራት የሞቱ ጎንደሮች፤ ጎዣሞች፤ ሸዋዎች፤ ዛሬ የአማራ ምንትሴ፤ የአማራ ቅብርጥሴ ብለው ሲደራጁ ማየት እንዴት ያስፈራል፡፡ ያ ብቻም አይደለም፤ ትናንት ሕወሀቶች አማራን ጠላት ባደረገ ርእዮተ-አገር አሳብረው አራት ኪሎ ገብተዋልና፤ እኛም እነዚህን ዘረኞች የምናሸንፈው፤ ትግሬዎችን ሁሉ ጭራቅ አድርገን በመሳል ነው የሚው ቅኝት ነው ሌላው ትልቅ ስህተት፡፡ በዚህ አቋሜ፤ ከወዳጆቼ ጋር መጋጨቴ አልቀረም፡፡ ግን፤ ሀሳብን በነጻነት ከመግለጽ አንጻር፤ ወዳጄቼ ከኢህአዴግ እንደማያንሱ ስለማውቅ፤ የመሰለኝን ልጻፍ፡፡

 

 • አሁን ያለው መንግስት የትግሬዎች መንግስት ነው የሚለውን ዜማ ይዘው የሚከራከሩት ሰዎች የሚነሱት፤ አንደኛ የትግራይ ህዝብ ከስርአቱ ተጠቃሚ ስለሆነ ስርአቱን ይደግፋል ከሚል ግምት ነው፡፡ ይሄንን ለማስረዳት፤ አንዳንዶቹ ቦሌና 22 ላይ የተደረደሩትን ፎቆች ይቆጥራሉ፤ ይሄ የጀነራል ሰዓረ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ የጀኔራል ገብረዮሀንስ፡፡ ይሄ ደግሞ የአርከበ እቁባይ፡፡ ይቀጥላል፡፡ የግለሰቦች ሀብት በምን ስሌት የህዝብ እንደሚሆን አይረዳንም፡፡ በርግጥ፤ ባለፉት 25 አመታት በንጽጽር፤ ከሌሎች ክልሎች በተሻለ በትግራይ የተነገቡትን የኢኮኖሚና ማህበራዊ ተቋማት፤ እንዲሁም የትግሬዎችን በማእከላዊ መንግስት ውስጥ ያላቸውን የተዛባ ድርሻም ጠቅሰው የሚከራከሩ አሉ፡፡ ሁለተኛው የሚነሱት፤ ይሄንን በሌሎች ኢትዮጵያዊያን ላይ የሚደርሰውን ግፍ፤ ትግሬ ጠንቅቆ ያውቃል ከሚል ግምት ነው፡፡ የትግራይ ህዝብ በሙሉ፤ ወይም ባብዛኛው፤ የህወሀትን መንግስት አውቆ፤ ተጠቃሚ ከሆነም፤ ተጠቃሚነቱ በሌሎች ኪሳራ የመጣ እንደሆነ ተረድቶ፤ ሕወሀትን ይደግፋል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ያንን ሀሳብ የሚያራምዱ ሰዎች፤ ግምት እንጂ፤ አሳማኝ ማስረጃ አያቀርቡም፡፡

 

 • ቁሳዊ ሀብትና ንብረት፤ የባህል የበላይነትም እንደማስረጃ ከተቆጠረ፤ በተለይ ከኢህአዴግ በፊት በነበሩት ዘመናት፤ በኢትዮጵያ ውስጥ የአማራውን ያህል ሀብት ያከማቸ ብሄር የለምና ይሄኛው ክስ ከአማሮች ባይመጣ ይመረጣል፡፡ በርግጥ አማራው ባለፉት 25 አመታት ክፉኛ ተመቷል፡፡ አንዳንዶች፤ በተለይም የትግሬ ልሂቃን፤ እነስዬ አብርሀ፤ ሕወሀት በአማራው ላይ የፈጠነውን ደባ ለማሳነስ፤ በኢህአዴግ አገዛዝ ዘመን፤ ኦሮምኛ የእስርቤት ቋንቋ እስኪመስል ድረስ፤ ኦሮሞው ተጠቃ ይላሉ እንጂ፤ ባሳለፍነው 25 አመታት እንደአማራው የተጠቃ ብሄር የለም፡፡ ግን ደግሞ፤ ባብዛኛው በቀደሙት አመታት፤ በፊታውራሪነት ኢትዮጵያን የቃኘው ብሄር አማራው ስለሆነ፤ አማራው በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የቁሳዊና መንፈሳዊ ሀብት የበላይነት፤ እንዲህ በ25 አመታት አይደለም በ250 አመታትም የሚናድ አይደለም፡፡ እንደውም ሳስበው ሳስበው፤ የህወሀት ትልቁ የ25 አመታት ፈታና፤ እነሱ ራሳቸው የጠሉትን አማራ እየሆኑ መምጣታቸው ይመስለኛል፡፡ ሕወሀት፤ ጭራቅ አድርጎ የሳለውን አማራና የአማርኛ ባህል ማሸነፍ አቅቶት፤ እንደውም እለት እለት እንደጠላት በሚቆጥረው ባህል እየተሸነፈ መምጣቱ መሰለኝ ብጥብጥ ያደረገው፡፡ ይሄንን ወደፊት አስረዳለሁ፡፡ ለዛሬ ግን በትግራይ ህዝብ ላይ ስለሚቀርበው ጎዶሎና የነቂስ ክስ ስህተት ማስረዳት ልቀጥል፡፡

 

 • ብዙ ሰዎች የላይኛውን ትግሬ ነገሰብን፤ በዚህም የንግስና ሂደት፤ የትግራይ ህዝብ እንደደጋፊም፤ እንደአጃቢም፤ እንደባለቤትም ሆኖ፤ ከሕወሀት ጎን ቆሟል የሚል ሀሳብ ለማስረዳት በዋንኛነት እንደማስረጃ የሚጠቀሙት፤ ሁለት ነገሮችን ነው፡፡ አንደኛው፤ የህወሀት መሪዎች፤ እነሳሞራ የኑስ እነአባይ ጸሀዬ እነስብሀት ነጋ እነስዩም መስፍን፤ ብድግ ብለው የትግራይ ህዝብና ሕወሀት አንድ ነው፤ ማንም አይለያያቸውም ሲሉ፤ የትግራይ ህዝብ አላስተባበለም፡፡ ስለዚህ ዝምታ የመቀበል ያህል ይቆጠራል ነገር ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ፤ የሌሎች አካባቢዎች ህዝቦች ለመንግስት ያላቸውን ተቃውሞ በተለያየ መንገድ ሲያሰሙ፤ የትግራይ ህዝብ ግን ተቃውሞ አድርጎ አያውቅም የሚል ነው፡፡ ሁለቱም መከራከሪያዎች፤ አንዳንዶቻችን በጥላቻ አጥቅሰን ካልዋጥናቸው በቀር፤ ወይንም ገሚሶቻችን አገርቤት በሚፈጸመው ግድያ ደማችን ተንተክትኮ፤ አዝነን፤ በንዴት መንፈስ ካልተቀበልናቸው በስተቀር፤ ውሀ አይቋጥሩም፡፡

 

 • የትግራይ ህዝብ፤ በርግጥም ሕወሀትን ወይንም አሁን ያለውን መንግስት ደግፎ ከሆነ፤ ፈረንጆች የምክንያታዊ ሰው መስፈሪያ (the reasonable person standard) በሚሉት ሚዛን ሲለካ፤ የትግራይ ህዝብ ደግ ነው ያደረገው፡፡ የትግራይ ህዝብ ህወሀትን ለመደገፍ የሚያበቃ፤ ማንም ምክንያታዊ ሰው የሚቀበለው፤ በቂ ምክንያት አለው፡፡ ቢያንስ ከማህጸናቸው የወጡ ልጆች፤ አንድን፤ ሀያል የተባለን ሰራዊትና ስርአት አሸንፈው፤ በማእከላዊ መንግስት ውስጥ ጉልህ ሚና ሲጫወቱ ማየት ማንንም ያኮራል፡፡ ስለዚህ የትግራይ ህዝብ በልጆቹ ቢኮራ፤ ህወሀትን ቢደግፍ ብዙም አያሰደንቅም፡፡ አያስቆጣምም፡፡ ትናንት ጦርነት ይካሄድበት የነበረ ምድረ፤ በተወሰነ መልኩ፤ ከጦርነት ተላቆ፤ ከብቶች በሰላም የሚግጡበት፤ ሰዎችም በሰላም ወደስራ የሚሰማሩበት፤ ልጆች የሚማሩበት፤ የስራ እድሎችና የንግድ እንቀስቃሴዎች የሚሟሟቁበት ሁኔታ ሲፈጠር፤ ቀድሞ ከነበረው ጦርነት ጋር በማስተያየትም ይሁን በራሱ፤ ያንን ሰላማዊ ህይወት የሰጠን ህወሀት ነው ብለው ቢያምኑና ቢደግፉት ሊያስከስሳቸው አይገባም፡፡

 

 • ሕዝብ ባይወቀስም፤ የትግራይ ህዝብ ግን መወቀስ ካለበት ሊያስወቅሰው የሚገባው፤ ሕወሀት በሌሎች ኢትዮጵያዊያን ወገኖቹ ላይ የሚሰራውን ሸፍጥና ተንኮል ያወቀና የተባበረ እንደሁ ነው፡፡ ከላይ እንዳልኩት፤ የትግራይ ህዝብለ ራሱም የጭቆና ሰለባ በመሆኑ እንጂ፤ በሌሎች ወገኖቹ ላይ የሚደርሰውን ግፍ አውቆ ሕወሀትን አይደግፍም፡፡ በዚህ የትግራይ ህዝብ በሙሉ ሕወሀትን አውቆና ነቅቶ ይደግፋል በሚለው የአስተሳሰብ መንገድ ከተጓዝን፤ እድለኞች ሆነን፤ እንደብርሀኑ ነጋ ሸዋ፤ እንደኤፍሬም ማዴቦ ሌላ ቦታ፤ እንደኔ ቦረና ካልተወለድን በስተቀር፤ ሁላችንም ከዚህ ክስ አንተርፈም፡፡ ሁላችንም፤ ትግራይ ተወልደን አድገን ቢሆን፤ እስከተወሰነ ደረጃ ሕወሀትን ከመደገፍ ወደኋላ አንልም፡፡ ነአምን ዘለቀ፤ አልማዝ መኮ፤ ኡስታዝ አቡበከር፤ አበበ ገላው፤ ሲሳይ አጌና፤ ተክሌ የሻው፤ ብርሀኑ ነጋ፤ ሌንጮ ለታ፤ ጃዋር መሀመድ፤ ታማኝ በየነ፤ ወይም እኔም ራሴ ትግራይ ብንወለድ ሕወሀትን የመደገፍ እድላችን በጣም ሰፊ ነው፡፡ እኔ እንኳን ዘወትርም የተቃራኒን ጎራ ክርክር ማየት ደስ ስለሚለኝ፤ ቀንደኛ የህወሀት ደጋፊ ላልሆን እችላለሁ፡፡ የሆነ ሆኖ ግን፤ ዛሬ መፈክር ይዘው ትግሬ ይውደም የሚሉ ሁሉ፤ ትግራይ ተወልደው ቢያድጉ አክራሪ ትግሬዎች ነበር የሚሆኑት፡፡

 

 • ብዙ ታዋቂ አክራሪ ኢትዮጵያዊያን አሉ፡፡ ብዙ አክራሪ ኦሮሞዎችም አሉ፡፡ ብዙ አክራሪ አማሮችም እተፈጠሩ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ትግራይ ተወልደው ቢያድጉ፤ አክራሪ ትግሬዎች ነበር የሚሆኑት፡፡ የትግራይ ህዝብ ሁሉ ወያኔን ይደግፋል የሚለው መከራከሪያ ካሳመነን፤ እንግዲያውስ ማናችንም ትግራይ ብንወለድ እንደትግራይ ህዝብ ነው የምናደርገው፤ ወያኔንን እንደግፋለን፡፡ ስለዚህ፤ እስክናጣራ፤ ትግሬ ሁሉ ወያኔ ነው የምንል ሰዎች፤ ስለትግሬዎች ስንናገር፤ ስለራሳችንም እየተናገርን ነው፡፡ እስኪጣራ፤ አማራ ሁሉ፤ ትምክህተኛ ነው፡፡ እስኪጣራ፤ ኦሮሞ ሁሉ ጠባብ ነው፡፡ እስኪጣራ፤ እስላም ሁሉ ሽበርትኛ ነው አይነት ነገር፡፡ ያ ትክክል አይደለም፡፡ ገደል የሚከት አስተሳሰብ ነው፡፡

 

 • የትግራይ ህዝብ ግን አውቆና ነቅቶ ሕወሀትን ይደግፋል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ወይንም ሕወሀት በሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች (ወይ ጉድ፤ ሕዝቦች ማለት ለመድኩ እኔ ራሴ)፤ በተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የሚፈጸመውን ግፍና ጭቆና አውቆ፤ ወይም የተወሰነ አብላጫ ተጠቃሚነት ካገኘም፤ ያ ተጠቃሚነት የመጣው በሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጭቆናና በደል እንደሆነ ቢረዳ፤ አቅምና እውቀት አንሶት ካልሆን በስተቀር፤ የትግራይ ሕዝብ ከህወሀት ጎን ይሰለፋል ብዬ አልገምትም፡፡ ከደገፈም ሌላ ምርጫ ስላልተሰጠው ይመስለኛል፡፡ ልብ በሉ፤ የትግራይ ህዝብ ላይ የተለቀቀው የ43 ምናምን አመታት ፕሮፓጋንዳ አለ፡፡ ጥርነፋውስ፡፡ የትግራይ ህዝብ ከተቀረው ኢትዮጵያ ህዝብ በፊት ነው አስቀድሞ የተጠረነፈው፡፡ ሌላ እንዳይሰማ፤ ሌላ እንዳያውቅ ተደርጎ የታፈነና የተቀፈደደ ህዝብ ነው፡፡

 

 • ገብሩ አስራት እንደጻፈው፤ ብዙዎች ሕወሀትን ጠንቅቀው በሚያውቁ ሰዎች እንደተነገው፤ ሕወሀቶች በትግላቸውም ይሁን በአገዛዛቸው ዘመን፤ እንዴት አድርገው ከነሱ አመለካከት የተለየ አመለካከት ያላቸውን ትግሬዎች ሁሉ አጥፍተው እዚህ እንደደረሱ ገልጧል፡፡ በነገብሩ ላይ የደረሰው፤ የሕወሀትን አንድ ወጥ አመለካከት ለመቅረጽ የሚሄድበትን ርቀት የሚያሳይ ነው፡፡ ከነሱ የተለየውን ከማሰር፤ ከማሰቃየት፤ ከማደህየት፤ ከማግለል፤ ካስፈለገም ከመግደል ጭምር አይመለሱም፡፡ ሕወሀት የተቀረውን ኢትዮጵያ የሚያስተዳድርበትን መንግድ በደንብ ከተመለከትንም፤ ያ በሌሎች ክልሎች ያየነው፤ ሕወሀት እንዴት አድርጎ ትግራይን አፍኖ እንደሚስተዳድር ይነግረናል፡፡ ስለዚህ ይሄንን የታፈነ ህዝብ፤ በማያውቀውና በሌለበት፤ እንዴት ከተቀረው ህዝብ አይቆምም፤ ወይም ዝም ያለው ደግፎ ነው ብሎ መውቀስ ተገቢ አይደለም፡፡

 

 • እንደህዝብ፤ ጭቁን የትግራይ ህዝብ ከተቀረው ምስኪን የኢትዮጵያ ህዝብ የሚለየው ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡ አንዲት የትግራይ እናት፤ ልክ አንድ የኦሮሞ እናት፤ ወይም አንድ የአማራ እናት ወይም አንድ የጉራጌ እናት ያላት ደግነት አላት፡፡ የትግራም አባት እንደዚያው፡፡ ይሄንን መርሳትና፤ የተወሰኑ ትግሬዎች፤ ከተወሰኑ አማራዎችና ኦሮሞዎች ጋር ተባብረው ለሚሰሩት ወንጅል፤ የትግራይን ህዝብ ብቻ ወይንም ትግሬን በነቂስ መወንጀል ጤናማ ክስ አይደለም፡፡ ይሄ ኢትዮጵያዊ አስተሳሰብም አይደለም፡፡ የአማራ ህዝብ በስሙ ግፍ ከተሰራ፤ ግፍ ሰሪዎቹ እንጂ አማራው እንደማይጠየቀው ሁሉ፤ የትግራይ ህዝብም እንደዚያ በስሙ ለሚሰራ ግፍ ተጠያቂ ሊሆን አይችልም፡፡ መቼም ዛሬ አማራውንም፤ ኮንሶውንም፤ ኦሮሞውንም የሚገድሉት ጥይቶች ትግርኛ ይናራሉ ካላልን በስተቀር፤ አማራና ኦሮሞ፤ ወይም ጋምቤላና ሶማሌ ሰው ላለመግደሉ ማስረጃ የለንም፡፡ ስለዚህ፤ ይሄ ትግሬ ላይ ያነጣጠር ክስ በደንብ ይፈተሸ፡፡ በብሄር መጠየቅ ከመጣ፤ በአማራው ላይ የሚቀርበው ክስ ይገዝፋልና፡፡

 

 • ትግሬን ብቻ ነጥሎ የሚከስ አካሄድ፤ ጸረ-ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ በዘመናት ሂደት የተገመደ ኢትዮዊነታችን የምንለውን ነገር ባዶ ያስቀረዋል፡፡ አለበለዚያ የምንለው ኢትዮጵያዊነት ጎዶሎና ሰንካላ ነው፡፡ በውስጡ ዘረኝነት የተበረዘበት ወይንም ሀሳዊ ኢትዮጵያዊነትን ነው የምናራምደው ማለት ነው፡፡ ሰው በተገደለ ቁጥር ብድግ ብለን አንዱን ብሄር ተጠቂ አንዱን ብሄር ተጠያቂ የምናደርግበት ማንነት መሆን የለበትም፤ ኢትዮጵያዊነት፡፡ ኢትዮጵያዊነት፤ ከዚያ ይሰፋል፡፡ ኢትዮጵያዊነት ከዚያ ይጠልቃል፡፡ ኢትዮጵያዊነት ትንሽ ትግሬነት፤ ትንሽ አማራነት፤ ትንሽ ኦሮሞነት፤ ትንሽ ትንሽ ከየብሄሩ የተወጣጣ፤ ክፋትም ልማትም ያለበት ስሪት ነው፡፡ ባለፈው እንደጻፍኩት፤ ስልጣኔን ተጋርተን፤ ሰይጣንነትን ግን ላንድ ብሄር ብቻ የምንጭን ከሆነ፤ ያ ጸረ-ኢትዮጵያዊነት ነው፡፡

 

 • ኢትዮጵያዊነት ገና ያላለቀ ሂደት ነው፡፡ ሲጀመር ሲቋረጥ፤ ሲጀመር፤ ሲቋረጥ፤ አንዱ ሲጀምር ሌላው ሲያፈርስ፤ አሁን ደግሞ ኢህአዴግ የጀመረው ኢትዮጵያዊነት እነሆ እዚህ አደረሰን፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ፤ የአርከበ እቁባይ ሚና ይበዛ እንደሆን እነጂ፤ የሙክታር ከድርም አስተዋጽኦ አለበት፡፡ የጌታቸው አሰፋ ወንጀል ይገዝፍ እንደሆን እንጂ፤ የኩማ ደመቅሳ አድርባይነትም አለበት፡፡ እነአባይ ጸሀዬን ወንጅሎ፤ እነአባዱላ ገመዳን፤ እነገዱ አንዳርጋቸውን መተው ስህተት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ችግሮች፤ ሌሎች ኢትዮጵያዊያን ናቸው፡፡ ይሄ የጳውሎስ ነው፤ ይሄ የአጵሎስ አልልም፡፡ ስለዚህ የትግራይ ህዝብን ወይም ትግሬዎችን የጥቃት ዒላማ ያደረገ ፕሮፓጋንዳ መቆም አለበት፡፡

 

 • ይልቅስ፤ እንደሀሳብ፤ ትግሬዎችን ወይም የትግራይ ህዝብን፤ የጥቃት ዒላማ ሳይሆን፤ የንቃት ማእከል ያደረገ ፕሮፓጋንዳ ያስፈልጋል፡፡ አሁን አሁን ሳስበው፤ ኢሳት ከኦሮምኛ ይልቅ፤ ትግርኛ ፕሮግራም ቢጀምር የተሻለ ነበር፡፡ መጀመርም አለበት፡፡ ሕወሀት የጋተውን ለማስተፋት፤ ሕወሀት የሞላውን ለማጉደል፤ ሕወሀት ያሳሳተውን ለማስተካከል፤ ሕወሀት የጋረደውን ለመቅደድ ያለመ ፕሮፔጋንዳ ያስፈልጋል፡፡ ትግሬዎችን የሚያገልና የሚስደነግጥ ሳይሆን፤ ትግሬዎችን የሚያቅፍና የችግሩም የመፍትሄውም አካል ያደረገ ፕሮፔጋንዳ ነው የሚያስፈልገን፡፡ ጎበዝ፤ በሱ ላይ እንስራ፡፡ አሁን እየተከሄደበት ያለው የፕሮፓጋንዳ ስልት ግን፤ ከኢትዮጵያ ይልቅ፤ ለኢህአዴግ ያደላ ስልት ነው፡፡ ምክንያም፤ አንድም ጭፍንና የመንጋ ባህርይን የሚያበረታታ ነው፤ አንድም ትግሬዎችን ሁሉ በፍራቻ ከኢህአዴግ ጉያ የሚያስገባ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ፤ ትናንት በብሄራችን ተጠቃን ብለው እሪ ሲሉ በነበሩ አማሮች ሲቀጣጠል፤ አያምርም፡፡ ይሄ መታረም አለበት፡፡ ያበለዚያ፤ በ2009 እኔም ትግሬ ነኝ ብዬ አውጃለሁ፡፡ ለነገሩ፤ ኢትዮጵያዊ ብሄር የለውም፡፡ ብሄሬ በኢትዮጵያዊነት እሳት ቀልጧልና፡፡

 

ተክለሚካኤል አበበ፤ ቶሮንቶ፤ ካናዳ፤ መስከረም፤ 2009

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.