ክቡር ሚኒስትሩ ሾፌራቸው እያያቸው ቆዝመው መኪና ውስጥ ገቡ

abay-tshaye-and-syum-mesfin-satenaw-news-5

 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ምን ሆንክ?
 • በጣም ቆዝመዋል፡፡
 • እንዴት አልቆዝም?
 • ምን ሆኑ ክቡር ሚኒስትር?
 • አዲሱ ዓመት አስጠልቶኛል፡፡
 • እንዴ ለምን?
 • በቃ ሁሉ ነገር ያስጠላል፡፡
 • ኧረ እንዲህ አይሁኑ፡፡
 • ምን ላድርግ?
 • እስቲ ይኼን ሙዚቃ ይስሙት፡፡
 • አንተ አገሪቷ እንዲህ ሆና ትሞዝቅልኛለህ አይደል?
 • ከአገሪቷ ሁኔታ ጋር የሚሄድ ሙዚቃ ነው፡፡
 • እንዴት?
 • ያው ለእናንተ መልዕክት ነው፡፡
 • ማን ነው ዘፋኙ?
 • ይሁኔ በላይ ነው፡፡
 • ምን?
 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ፀረ ልማት የሆነ ዘፈን ዘፍኗል አሉ፡፡
 • ኧረ በጣም ልማታዊ ነው፡፡
 • ምንድን ነው ዘፈኑ?
 • ሰከን በል ይላል፡፡
 • ለቡና ነው እንዴ የዘፈነው?
 • ማለት ክቡር ሚኒስትር?
 • የሚሰክነው ቡና ነው ብዬ ነዋ፡፡
 • ኧረ ብዙ መስከን ያለበት ነገር አለ፡፡
 • ምንድን ነው የሚሰክነው?
 • መንግሥት…
 • እ…
 • ባለሥልጣናት…
 • እ…
 • የፀጥታ ኃይሉ…
 • ምን?
 • ብቻ ሁሉም፡፡
 • ለነገሩ እውነትህን ነው፡፡
 • እንዴት?
 • መስከን ሳያስፈልገን አልቀረም፡፡
 • ማለት?
 • ስማ አዲስ ዓመት እኔ ቤት እንዴት እንደሚከበር ታውቃለህ አይደል?
 • ክቡር ሚኒስትር ድል ባለ ድግስ ነዋ፡፡
 • በአሁኑ አዲስ ዓመት እንደዚያው ድል አድርጌ ደግሼ ነበር፡፡
 • እሺ፡፡
 • ግን ምን ያደርጋል?
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • ድግሱ ከንቱ ቀረ፡፡
 • ለምን ክቡር ሚኒስትር?
 • አንድ ብቅ ያለ ሰው የለም፡፡
 • ማለት ክቡር ሚኒስትር?
 • የጠራሁት ሰው በሙሉ ቀረ፡፡
 • ምን?
 • አንድ ብቅ ያለ ሰው የለም፡፡
 • በጣም ነው የሚገርመው፡፡
 • ምኑ ነው የሚገርመው?
 • የሕዝቡ አመፅ፡፡
 • ይኼም የአመፁ አካል ነው?
 • ታዲያስ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምንድን ነው የሚሻለው?
 • መስከን፡፡
 • እ…
 • ሰከን ብላችሁ ሕዝቡን ስሙት፡፡
 • ወይኔ፡፡
 • ለነገሩ ጥፋቱ የእርስዎ ነው፡፡
 • እንዴት?
 • አገሪቷ ላይ የነበሩት በርካታ ኮንሰርቶች እኮ ተሰርዘዋል፡፡
 • ለምን?
 • ሕዝብ ሐዘን ላይ ስለሆነ፡፡
 • እኔ ደግሞ ኮንሰርቶቹ የተሰረዙት በሌላ ምክንያት መስሎኝ ነበር፡፡
 • በሌላ በምን?
 • ፀረ ልማታዊ ስለሆኑ፡፡
 • ለማንኛውም እርስዎም መሰረዝ ነበረብዎት፡፡
 • ምኑን?
 • ድግሱን!

[ክቡር ሚኒስትሩ ቢሯቸው ሲንጐራደዱ አማካሪያቸው ገባ]

 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • እ…
 • የተጨነቁ ይመስላሉ፡፡
 • በጣም ተጨንቄያለሁ፡፡
 • ምን ያስጨንቅዎታል ክቡር ሚኒስትር?
 • ሁሉም ነገር፡፡
 • ማለት ክቡር ሚኒስትር?
 • የአገሪቷ ሁኔታ በጣም እያስጨነቀኝ ነው፡፡
 • እሱማ በጣም ያስጨንቃል፡፡
 • በጣም ነው የተናደድኩት፡፡
 • ለምን ክቡር ሚኒስትር?
 • አንድ ሰው ዝር አላለም፡፡
 • የት ክቡር ሚኒስትር?
 • ቤቴ ነዋ፡፡
 • ምንድን ነው የሚያወሩት ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ስማ ትልቅ ድግስ ደግሼ ነበር፡፡
 • የት ክቡር ሚኒስትር?
 • ቤቴ ነዋ ለአዲሱ ዓመት፡፡
 • እእእ…
 • አንተ ራስህ ጠርቼህ መቼ መጣህ?
 • ያው ከቤተሰብ ጋር ስላሳለፍኩ ነው፡፡
 • ሌላ ጊዜ ስጠራህ ከነቤተሰብህ እኔ ቤት አልነበር የምታሳልፈው?
 • እሱማ አዎ፡፡
 • እና ለምን አልመጣህም?
 • ያው እኛ ሰፈር ያለው ባለሥልጣንም ትልቅ ድግስ ቢደግስም፣ ሰው እንዳልመጣ ስሰማ እርስዎም ጋ ተመሳሳይ ነገር ይፈጠራል ብዬ ቀረሁ፡፡
 • እናንተ ሰፈር ያለው ባለሥልጣን ሰው ሲጠራ ስለቀረበት፣ እኔም ጋ ተመሳሳይ ነገር ይፈጠራል ብለህ ነው የቀረኸው?
 • አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • የእናንተ ሰፈር ሰውና የእኛ ሰፈር ሰው ማነው አንድ ያደረገው?
 • ክቡር ሚኒስትር አይሳሳቱ፡፡
 • እንዴት?
 • ሕዝቡ አንድ ነው፡፡
 • እያመፀብን ነው ማለት ነው?
 • እህሳ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • አንተም እያመፅክብኝ ነው?
 • እኔም ከሕዝብ ጋር ነው የምቆመው፡፡
 • ሕዝቡ ምንድን ነው የሚፈልገው?
 • መደመጥ፡፡
 • እኮ ምንድን ነው የሚያወራው?
 • ኪራይ ሰብሳቢነት ይጥፋ፣ ሰብዓዊ መብት ይከበር፣ የመናገር ነፃነት ይስፈን፣ ሙስና ይቀረፍ….
 • እና ድግሱ ላይ ለምን ሰው አልተገኘም?
 • ድግሱ ላይም እኮ እነዚህ ችግሮች ይንፀባረቃሉ፡፡
 • እንዴት?
 • ድግሱ የተደገሰው ከሕዝቡ በተወሰደ ገንዘብ ነው፡፡
 • እ…
 • ድግሱ ላይ ሰው እንደፈለገ ማውራት አይችልም፡፡
 • እኔ ጠፋሁ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር የሚያዋጣው ማዳመጥ ነው፡፡
 • ባላዳምጥስ?
 • እንደ ድግስዎት ባዶ ይቀራል፡፡
 • ምኔ ነው ባዶ የሚቀረው?
 • ሥልጣንዎ!

[ክቡር ሚኒስትሩ እንደ እሳቸው ኪራይ ሰብሳቢ የሆኑ ሚኒስትር ጋ ደወሉ]

 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ምነው?
 • ድምፅዎት ልክ አይደለም፡፡
 • እንዴት ልክ ይሆናል?
 • ምን ተገኘ?
 • በጣም እየፈራሁ ነው፡፡
 • ምንድን ነው የሚያስፈራዎት?
 • ሁሉም ነገር፡፡
 • ማለት?
 • ሊቀይሩን ነው እኮ፡፡
 • በምንድን ነው የሚቀይሩን?
 • በቴክኖሎጂ፡፡
 • ምን? እኛን በሮቦት ሊቀይሩን ነው?
 • ኧረ በተማሩ ሰዎች ልንቀየር ነው፡፡
 • እ… ቴክኖክራት ማለትዎ ነው?
 • ያው ነው፡፡
 • ኧረ ብዙ አይፍሩ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ለምን አልፈራ?
 • ይኼ እኮ የፓርቲያችን ፀባይ ነው፡፡
 • እንዴት ማለት?
 • ሁሌም አጣብቂኝ ውስጥ ስንገባ፣ የማንሰጠው ተስፋ የለም፡፡
 • እና ይኼ ተስፋ ነው?
 • አዎን፡፡ በቃ አጣብቂኙ እስኪያልፍ ለሕዝብ የሚሰጥ ተስፋ ነው፡፡
 • አይቀይሩንም ብለህ ታስባለህ?
 • ከዚህ በፊት ማን ሲቀየር አይተዋል?
 • እሱማ አልፎ አልፎ ነው ሰዎች የሚቀየሩት፡፡
 • በቃ ከእነዚያ ጥቂት ሰዎች መካከል ላለመሆን መጣር ነው፡፡
 • አይ በአሁኑ ግን በርካታ ሰው የሚቀየር ይመስለኛል፡፡
 • ብለው ነው?
 • አዎን ስለዚህ መፍትሔ መፈለግ ነው የሚበጀው?
 • ታዲያ ምንድን ነው መፍትሔው?
 • ራሳችንን ለውጠን መገኘት፡፡
 • ወደ ምን?
 • ወደ ቴክኖሎጂ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ቤታቸው ኮምፒዩተራቸውን ሲጐረጉሩ ሚስታቸው መጡ]

 • ምን ሆነሃል?
 • ምን ሆንኩ?
 • የተጨነቅክ ትመስላለህ?
 • እንዴት አልጨነቅ?
 • ራትህን አትበላም እንዴ?
 • ኧረ ይቅርብኝ ባክሽ፡፡
 • መሽቷል እኮ፡፡
 • አውቃለሁ፡፡
 • ምን እያደረክ ነው?
 • ሊቀይሩን ነው እኮ፡፡
 • ማለት?
 • በቴክኖሎጂ ሊቀይሩን ነው፡፡
 • የምን ቴክኖሎጂ ነው?
 • በተማሩ ሰዎች ሊተኩን አስበዋል አሉ፡፡
 • ቴክኖክራት ማለትህ ነው?
 • ያው ነው ባክሽ፡፡
 • እና ኮምፒዩተር ላይ ምን እያደረክ ነው?
 • እየፈለኩ ነው፡፡
 • ምንድን ነው የምትፈልገው?
 • የሚሸጥ ዲግሪ፡፡
 • ምን ያደርግልሃል?
 • ነገርኩሽ እኮ አሁን የተማረ ሰው ነው የሚፈለገው፡፡
 • ከዚህ በፊት የገዛሃቸው ዲግሪዎችስ?
 • እነሱ አሁን ኤክስፓየር ሊያደርጉ ነው፡፡
 • ለምን?
 • የአገር ውስጥ ናቸዋ፡፡
 • አሁን የምትፈልገው የውጭ ነው?
 • አዎን እሱ ነው የሚያዋጣው፡፡
 • ከመግዛት ግን ተምረህ ብታገኘው ሊሰጥህ ይችላል?
 • ምንድን ነው የሚሰጠኝ? ሥልጣን ይሰጠኛል?
 • እሱንም ጨምሮ ሌላ ነገር ይሰጥሃል፡፡
 • ሌላ ምን?
 • ብቃት!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.