የተቃዋሚ ፖለቲካ ጎራ የጋራ ትግል ውጤታማነት ላይ የተደረገ ግምገማና ዳሰሳ የፓርቲዎች ሪፖርት ጥንቅር

መስከረም 15/2007 ዓ.ም

1. መግቢያ፡-

የዚህ ሪፖርት መነሻዎችና ይዘት ለጥናቱ በቀረበው የመነሻ/አቅጣጫ ማመላከቻ ሰነድ/ቢጋር /TOR ላይ ተነጋግረን የደረስንበት አጠቃላይ ስምምነት፣ በሰነዱ ውስጥ የተመለከቱት ዓላማ፣አካሄድና የትኩረት ነጥቦች፣በሰነዱ ላይ በተነጋገርንበት ጊዜያት የተነሱት ኃሳቦችና የተጨበጠው የጋራ ግንዛቤ እና ተሳታፊ ፓርቲዎች በሰነዱ ላይ ተመስርተው ያቀረቡት የጥናት ሪፖርቶች ናቸው፡፡ ሪፖርቱ በተቻለው ሁሉ በውይይቱም ሆነ በሪፖርቶቹ የተመለከቱትን ችግሮችና የመፍትሄ ኃሳቦች ያካተተ እንዲሆን የተቻለው ጥረት ተደርጓል፡፡

በሪፖርቱ በዋነኛነት ማሳየት የተፈለገው በትናንት የተናጠልና የጋራ/ትብብር ትግል በአገራዊ ፖለቲካው መድረክ በተደረጉ ጥረቶች- ሂደቱንና ውጤቱን ተከትለው በተከሰቱ ችግሮች ላይ አድናቆታዊ መጠይቅ(Appreciative Inquiry) በማቅረብ ለቀጣዩ የጋራ ትግል ግልጽ ኃሳብ ለመጨበጥና ዘላቂ አቅጣጫ ለማስመር ነው፡፡ በዚህ መሰረት ጥናቱ የተለያዩ ፓርቲዎች በተናጠልም ሆነ በስብስብ/በጋራ ያደረጉትን ትግል ለመመርመር-መገምገምና መዳሰስ ሙከራ አላደረገም፤የየቱንም ፓርቲ ፕሮግራም፣ዓላማ፣ አደረጃጀት፣ርዕዮተ ዓለም/እምነት፣… እንቅስቃሴና ያስመዘገበውን ውጤት፣ ክፍተቶችንም ሆነ ያጋጠሙ ችግሮች … በአጠቃላይ አገራዊ ፖለቲካው ላይ ላለው አንድምታ እንደ ግብኣትና ማሳያ ከማቅረብ ያለፈ አካሄድ አልተከተለም፡፡

ጥናቱም ሆነ ይህ ሪፖርት በምንም መልኩ በተናጠልም ሆነ በጋራ የተደረጉ ጥረቶችን፣ የተገኙ ውጤቶችን ለማሳነስ ወይም ቦታ ለመንፈግ፣ የተከፈለውንና እየተከፈለ ያለውን ዋጋ ለማሳጣት እንዲሁም ለዚህም በግልና በጋራ የተሠጠውን አመራር ዕውቅናና ምሥጋና ለመንፈግ አይደለም፡፡ ይልቁንም ትግሉ የተደከመውንና የተከፈለውን መስዋዕትነት የሚመጠን ውጤት ያላስመዘገበበትን ምክንያት በጥቅል አውቆ፣ ባለፈው ድካምና መስዋዕትነት እንዲሁም ከተመዘገበው ውጤት ላይ በመነሳትና በመደመር/በመገንባት በተቻለው አጭር ጊዜ የሚፈለገው ውጤት ለማስመዝገብና ለጋራ አገራዊ ዓላማና ግብ አስተዋጽኦ ለማበርከት የተደረገ/የሚደረግ ጥረት ነው፡፡ በዚህ መሰረት እንኳን በነበረውና ባለው አስቸጋሪና ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ዋጋ ለከፈሉና እየከፈሉ ላሉ ዜጎች፣ተቃዋሚ ፓርቲዎችና መሪዎች ቀርቶ ለኢህአዴግ ተጋዳላዮችና ላስመዘገቡት ውጤት ዕውቅና መስጠት አለብን፡፡ በአጭር አገላለጽ እስካሁን የተደረገውንና እየተደረገም ላለው አስተዋጽኦ፣ለተከፈለውና እየተከፈለ ላለው መስዋዕትነትና ለተገኘው ውጤት ሁሉ ተገቢውን ክብርና ዋጋ የመስጠት አስፈላጊነት ሊሰመርበት ይገባል፤ የሚጠበቀው ድልም ካለፈው ጋር የተያያዘ/ቀጣይ/ የቀድሞው ትግልና የመጪው ድምር ውጤት መሆኑ ሊታወቅና ሊታመንበት ይገባል፡፡

ይህ ማለት በምንም መንገድ ‹‹ በተደጋጋሚ በወደቅንበት ተመሳሳይ መንገድ ተጉዘን የተለየ ውጤት ማምጣት አይቻልም›› የሚለውን የጋራ ግንዛቤና ለዚህም በኃሳብ ላይ የሚደረግ ግልጽና ዝርዝር ውይይት አዲስ የጠራ ኃሳብ ፍለጋችንና ግልጽ አቅጣጫ የማስመር አካሄዳችንን የሚገታ ወይም የሚያስር ሊሆን አይገባም፤ የሚያበረታታ እንጂ፡፡

በሪፖርቱ ላይ በየፓርቲም ሆነ በጋራ የሚደረገው ውይይት በጥናቱ ግኝቶች እና በመፍትሄ አቅጣጫዎች ላይ ትኩረት ማድረግ ለጥናቱ ዓላማ መሳካት ያለው ፋይዳ ግንዛቤ እንዲሰጠው ይጠበቃል፡፡

2. የጥናቱ ዓላማ፡-

በጥናት መነሻ/አቅጣጫ ማመላከቻ ሰነድ/ቢጋር/ እንደተመለከተው የግምገማውና ዳሰሳ ጥናቱ መድረሻ ለምን በተደጋጋሚ ወደቅን ? የሚለውን በመመርመር ‹‹ቅድሚያ ለአገርና ህዝብ›› በሚል ማዕቀፍ ከትናንቱ በመማር በተናጠልና በጋራ በየፓርቲያችንና በአገራዊ ፖለቲካው ሥር ነቀል ለውጥ በማድረግ ግንኙነታችንን በነጠረ ግልጽ ኃሳብና በተመጠነ የትኩረት አቅጣጫ በጠንካራ መሠረት ላይ ማሳረፍ ነው፡፡ በቀጣይ በተስማማንባቸው ውስን የጋራ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ዘላቂ ግንኙነት ለመመስረትና በተጠያቂነት መንፈስ የተናጠልና የጋራ ኃላፊነት ለመቀበልና ለተግባራዊነቱና ለምንጋራው አገራዊ የጋራ ውጤት ተባብረን ለመሥራት ነው፡፡ይህ ማለት የተለመደውን በፓርቲ አመራሮች ፍላጎትና ውሳኔ ላይ የተንጠለጠለ ተስፋ የመቁረጥና የማስቆረጥ አካሄድን በግልጽ በመታገል፣ በመቀልበስና በአዲስ አስተሳሰብ በመተካት፣ በገዢው ፓርቲ የመከፋፈል ፖሊሲ ሰለባ ሆነን በውጤት አልባ የተናጠል/የተበጣጠቀ ልፋት በአገርና ህዝብ ላይ የደረሰውንና እየደረሰ ያለውን ጥፋት በጋራ ለማቆም– የውስኗን ሃብት/ጊዜ ፣ጉልበት ፣ዕውቀት፣ ፋይናንስ/ ብክነትንና የመንፈስ ስብራትን/ተስፋ መቁረጥ፣ በመከላከል ለውጤት የሚያበቃ በእውነትና እውቀት ለዘላቂ አገራዊ መፍትሄ መሻት አቅምን ለማስተባበር፣ ግንኙነታችን ለማጠናከርና ጠንካራ አዎንታዊ ተጽዕኖ በኅብረት/በጋራ ለማሳረፍ የሚያስችል የጋራ መግባባት ላይ መድረስ ነው፡፡

3. የጥናት ዘዴዎች፡-

በጥናቱ ውስጥ የተለያዩ የንድፈ ኃሳብ ጽሁፎች፣ የፓርቲዎች መግለጫዎች፣ የፓርቲ መሪዎች መግለጫዎችና ቃለ ምልልሶች፤ የተናጠልና የጋራ ጥናት ውጤቶች /ሪፖርቶች/ ዳሰሳ፣ የፓርቲዎች ተግባራዊ እንቅስቃሴ ቅኝት፣ ከቀጥተኛ ተሳትፎ የተገኘ ግንዛቤ፣ ውይይት… ወዘተ እንደ ጥናት ዘዴዎች በጥቅም ላይ እንዲውሉ በተጨበጠው የጋራ ግንዛቤ መሠረት እንደተደረገ ይታመናል፡፡

ይህ ጥንቅር በጥናቱ መነሻ ሰነድ /ቢጋር/ላይ እንደተመለከተው እያንዳንዱ ተሳታፊ ፓርቲ ግብዓት እንዲሰጥ በተስማማነው መሠረት በየፓርቲው ከተደረጉ ውይይቶች የተገኙ ግብኣቶችና በጋራ ውይይት ወቅት የተነሱትን ጉዳዮች እንዲያካትት ተደርጎ የተዘጋጀ ነው፡፡ በዚህ ሰነድ ዝግጅት ሂደት አምስት ደረጃዎችን ማለትም ፡-

ቢጋሩ ለፓርቲዎች ከመሰራጨቱ በፊት በረቂቁ ላይ የተደረገ የጋራ ውይይት፣

በየፓርቲዎቹ በቢጋሩ መሰረት ግብኣት ለመስጠት የተደረገ ውይይትና ያቀረቡት ግብዓት፣

ከፓርቲዎች የተሰጠውን ግብኣት ማጠናቀር፣

በተጠናቀረው ሪፖርት ላይ በየፓርቲዎች የተደረገ ውይይት፣

በመጨረሻም በሪፖርት ጥንቅሩ ላይ ከየፓርቲዎች በቀረቡ አስተያየቶች በጋራ የተደረገውን ውይይት፣

አልፎ በነዚህ ሂደቶች ውስጥ የተነሱትን የጋራ ጉዳዮች በማካተት የተዘጋጀ በመሆኑ የጋራ መግባባት የተደረሰበት ሰነድ ነው ፡፡ ሆኖም ከጥናቱ ሽፋን፣ ለጥናቱ ከዋለው የማይለካ የጥናት ዘዴ (ኳልቴቲቭ) እና በውይይታችን ላይ በጥናቱ ላይ ሊወሰዱ ስለሚገባው የጥንቃቄ ማሳሰቢያዎች (ይህ ግንኙነታችን እየተጠናከረ፣ የበለጠ እየተቀራረብን ስንመጣ የሚሻሻል መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ) አንጻር ክፍተቶችና ውስንነቶች እንደሚኖሩት ይጠበቃል፡፡ ስለዚህ ይህ ሪፖርት በቀጣይ በቅርጽም ሆነ ይዘት በውይይት እየጠራና እየዳበረ የሚሄድ መሆኑ የተጠበቀ ሆኖ በአሁኑ ጊዜ ከባለፈው ትምህርት ወስዶ ለቀጣዩ አቅጣጫችንን በግልጽ ለማስቀመጥ በቂ እንደሆነ ይታመናል፡፡

4. የግምገማውና ዳሰሳው ግኝቶች፤

4.1. አጠቃላይ፡-

የአሸናፊ/ተሸናፊ(ጦርነት) የጠቅላይ ፖለቲካዊ ሥልጣን ታሪካችንና ልምዳችን፣በፖለቲካ ትንታኔኣችንና ግምገማችን ከዝርዝር በጥቅል ላይ የማተኮር ልምዳችን፣ በመከባበርና መቻቻል ሥም የመሸፋፈንና መሸካከም ተሞክሮኣችን፣ ሁሉንም የማኅበረሰብና ሙያ ዘርፍ የተጠናወተው በተቃውሞ ጎራው ላይ የሚቀርብ የትኛውም ትችት ትግሉን ‹‹ መጉዳት›› ነው የሚል ሥር የሰደደ አስተሳሰብ፣ ለችግራችንም ሆነ ለመፍትሄው ወደውስጥ ከማየት ችግራችን ወደውጪ መግፋት ፣ለዕርቅና ይቅርባይነት ያለን ጠባብ ቦታ፣ ለመመሰጋገን የተዘጋው በራችን ለመነቃቀፍና ለመጠላለፍ በእጅጉ ክፍት መሆኑ፣ለሥልጣንና ባለሥልጣን የምንሰጠው ቦታና ያለን አመለካከት … ወዘተ ላነሳነው ጥያቄ (ለምን ወደቅን) ለምንሰጠው ምላሽ አሉታዊያን ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ በሌላ አገላለጽ በዚህ ጥናት ላነሳናቸውም ሆነ ሌሎች የፖለቲካ ችግሮቻችን ለምንሰጠው ምላሽ የተቃውሞ ፖለቲካ ፓርቲ አባላትም ሆንን መሪዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት የወጣነው ከአንድ ዓይነት የፖለቲካ ማኅበረሰብ ጥንቅር/Social Fabric/ መሆኑና የምንጋራው ተመሳሳይ የፖለቲካ ባህልና ልምድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው፡፡

እስኪ በየወቅቱ ከተደረጉ የትብብር ጥረቶች የተወሰኑትን ለማስታወስ እንሞክር፡፡ በደርግ ጊዜ ኢማሌዲህ፣ ኢዲኃቅ፣ ከ1983 እስከ ምርጫ 97 ባለው ጊዜ ደግሞ – ደቡብ ኅብረት፣ኢሠዲአኃ ም/ቤት፣ ኢተፖዲኅ፣ ትዲኢ (ኢሠዲአኃ፣ኦብኮ፣መኢአድ፣)፣ ኢዴኃኅ፣ ቅንጅት፣ ከምርጫ 97 በኋላ ደግሞ መድረክ፣ ‹‹33ቱ/ትብብር››ንና በመድረክ አባላት መካከል፣ የመኢአድ/አንድነት፣ የአንድነት/ዐረና፣ የአንድነት/ትብብር፣ የውህደት ጥረቶች መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከነዚህ ውስጥ በህይወት ያሉ ስንት ናቸው፣ በምን ሁኔታ ላይ ይገኛሉ– ከውህደት ጥረቶች ውስጥ ስንቱ ተሳክተዋል? የሚሉትን ለመመለስ እያንዳንዱ ፓርቲ የየራሱን ግምገማ ያድርግና ጠቃሚ ግንዛቤ ይውሰድ፡፡

ባለንበት ተጨባጭ ሁኔታ በአገሪቱ ላይ ያንዣበበው አደጋና በህዝባችን ላይ እየደረሰ ያለው መጠነ ሰፊና ዘርፈ ብዙ በደል/ጭቆና ፣በአገራችን ከዕለት ወደ ዕለት እየተባባሱ የመጡ ፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮች የግፍ ጽዋው የሞላ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡ የገዢው ፓርቲ የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ ሂደትና ውጤት በህዝብ ላይ ያደረሰበትና እያደረሰበት ያለው ተጨባጭ አገራዊ ዕዳና መርገምት -ለዘመናት አብሮ በፍቅር፣ በመከባበርና በሠላም በኖሩ ህዝቦች መካከል የተዘራው ጥላቻ – አለመተማመን ፣አፍራሽ ፉክክር፣ ያልተመጣጠነ/አድሎኣዊ የሃብት ክፍፍል… ህዝቡ በሚገባ ምናልባትም ከፖለቲካ ፓርቲዎች ባልተናነሰ ሁኔታ ተረድቶታል፡፡ ይህ መረዳት በህዝብ ውስጥ የፈጠረው ከፍተኛ የለውጥ ፍላጎትና የትግል መነሳሳት ለዲሞክራቲክ ተቃዋሚ ፓርቲዎች መልካም አጋጣሚ ነው፡፡ በእውነት፣ዕውቀት ላይ ተመስርቶ በጥበብ ከተመራ ይህን የተዘጋጀ እምቅ ኃይል በዝቅተኛ ወጪ/ ጊዜ፣ዕውቀት፣ገንዘብ፣ጉልበት/ በቀላሉ ወደሚፈለገው ውጤትና ዘላቂ መፍትሄ- የሥርዓት ለውጥ ማድረስ ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ ተቃዋሚ የፖለቲካ ኃይሎች ዛሬም እንደትናንቱ ሁሉም በየፓርቲውና በመካከሉ ያለውን/የሌለውን ልዩነትና ችግር በግልጽ ሳያስረዳ ውኃ በማያነሳ የግለሰቦችና ‹‹ፓርቲዎች›› ፍላጎት እየተመራ ችግሩን በመሸፈንና ከህዝብ በመደበቅ በተለመደው መንገድ በመጓዝ ከውጤት እንደማይደርስ መቀበል ግድ ይላል፤ ይህም በፓርቲዎች የውስጥ ግንኙነትና በፓርቲዎች መካከል በሚደረግ ግንኙነት ሥር ነቀል የአስተሳሰብና የአመራር ለውጥ እንደሚያስፈልግ በግልጽ ያሳያል፡፡ስለዚህ በትናንት ግንኙነታችን የተፈጠሩ ችግሮችን በግልጽና ዝርዝር ለመወያየት መወሰን ይኖርብናል ማለት ነው– ከደቡብ ኅብረት በቅንጅትና ፣ኢዴኃህ፣ አልፎ እስከ ‹‹33ቱ›› የዘለቀው የጋራ ጥረት…ለምን ተበተነ/ፈረሰ፣ ፓርቲዎች ለምን ተከፋፈሉ፣ ለምን ይከፋፈላሉ… ለሚለው የማያሻማ መልስ ለመስጠት የምንችልበት ውይይት ያስፈልጋል ለማለት መድፈር አለብን፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በግልጽ ለመነጋገር ከፈለግን አሁን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ባለንበት እውነታ -‹‹በተያያዝነው
በእርስ በርስ ፍትጊያ የታገዘ የተበጣጠቀ የተናጠል ትግል›› በምኞትና ፍላጎት ብቻ ወደሚፈለገው ያለማድረሳቸው እውነት ነውና፡፡ ይህን ግምት ለመውሰድ ዝርዝር ጥናትም ሆነ ነቢይ ወይም ‹‹አዋቂ›› መፈለግ አያስፈልግም፡፡ ባለፉት 23 ዓመታት ለህዝብ ከጥርጣሬና ጥያቄ ውጪ በሙሉ ልብ የሚቀበለውና አስፈላጊውን መሥዋዕትነት ሊከፍልለት የሚችል መሪ ፓርቲ አላቀረብንለትም፣ በአንጻራዊነት ለ‹‹መንፈሱ›› ሽሚያ የተገባበት የ97 ቅንጅትም ቢሆን እምነት ቢጣልበትም በቃሉ አልተገኘም፡፡ ዛሬ ላይ ‹‹አለን›› የምንለውም እንኳን በተናጠል በጋራም ሆነን አሁን ባለንበት- ያልጠራ ኃሳብና የተለመደው ውጤት አልባ መንገድ (አስተሳሰብ፣አደረጃጀት፣ የአመራርና አሰራር ሥርዓት) የሥርዓት ለውጥ ማምጣት አይቻለንም፡፡ ገዢውን ፓርቲ ከሥልጣን ማስወገድ ቢቻለንም በዚህ የአስተሳሰብ ማዕቀፍ ውስጥ ሆነን የመንግስት ለውጥ የማምጣቱ በጥያቄ ውስጥ እንዳለ ሆኖም በአንድ ፓርቲ የተናጠል ጉዞ ዘላቂ የሥርዓት ለውጥ ማምጣት አይቻልም፡፡ ካለፈው ልምድና ተሞክሮ የተወለደ ጨለምተኝነት ሳይሆን፣ እውነቱ ይህና ይህ ብቻ ነው፡፡

በአንጻሩ ዛሬም በህዝብ ውስጥ ያለው የለውጥ ፍላጎት አጠያያቂ አይደለም፤ ይህ እምቅ የለውጥ ሃብት በአግባቡ ከትናንት ችግራችንና ውድቀታችን መማራችንንና ሥርነቀል ለውጥ ማድረጋችን በቃል ሳይሆን በተግባር ከተገለጸለት ዛሬም እምቅ አንጡራ ሃብታችን ነው፡፡ ግን እኛ ትናንት በምርጫ 97 ያደረስንበትን ስብራት ከመጠገን ይልቅ ጥፋታችንን ሸፍነን የሆነውንና የተደረገውን እንደ ታላቅ ጀብድ/ገድል እንዘክራለን፣ በባለቤትነት ይገባኛል ክርክር ውስጥ እንገባለን፡፡ ይህ አስተሳሰብ እኛ ለኢትዮጵያዊያን/ህዝቡ እውቀትና ንቃት፣አስተዋይነት …የሰጠነውና የምንሰጠው ግምት ዝቅተኛ መሆኑን ያመለክታል፡፡

በታሪካችን የተፈጸሙና ያለፍንባቸው አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ ድርጊቶችና ክስተቶች መኖራቸው አሌ የሚባል አይደለም፤ እንዲህ ዓይነቱ ክስተት የእኛ የብቻ ሳይሆን የዓለም አገሮችና ህዝብ ታሪክ አካል ነው፡፡ ዛሬ የሥልጣኔና የብልጽግና ፣የዘመናዊ አመራርና አስተዳደር አብነትና ምሳሌ እያደረግን የምንጠቅሳቸው ሁሉ በአገር ምስረታ ወቅት ያለፉት በተመሳሳይ መንገድ ነው፡፡ እነርሱ ያለፉበትን አፍራሽ መንገድ ተጸጽተውበት/ይቅር ተባብለው/ ለታሪክ መማሪያነት እየተጠቀሙ በገንቢው ላይ እየደመሩ ሲሰለጥኑና ሲበለጽጉ እኛ – በአንድ በኩል ‹‹ከኢትዮጵያዊነት ውጪ ››ሌላ ለምን ተጠርቶ የምንለው ባልነበርንበት ዘመን (ባላየነውና ባልዋልንበት ራሳችንን በባለቤትነት ሹመን) በታሪክ ፊት የተፈጠረውን ጥፋት/ስህተት – ክህደት ታሪክን ይቀይር ይመስል እየካድን፣ ይቅርታ ያጠፋ ይመስል በክህደት ጸንተን ለ‹‹ተበዳይ ›› የቂምና በቀል ማሳደጊያ/ማራቢያ እያመቻቸን፤ ፣በሌላ ተቃራኒው በኩል ደግሞ ‹‹ተበዳይ ›› ነን የምንል የትናንት ቁስልን ማመርቀዝ ለዛሬ ይጠቅመን ይመስል፣ ጥፋቶችን እያጎላን በጎውን እየሸፈንንና እየካድን በደሎች ሁሉ የተፈጸሙት በዕውቀት(ሆን ተብሎ) ነው ለሚል ድምዳሜ ያለፈውን የመቶዎቹን ዘመን በዛሬ የአስተሳሰብ፣ የዕውቀትና ስልጣኔ ደረጃ እየመዘንን ይቅር ማለት በደሉን ከመሻር አልፎ ታሪኩን ይፍቅ ይመስል ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ለቀጣይ ትውልድም የሚበቃ ለአገርና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት የማይጠቅም የልዩነት ዘር እንዘራለን፣ እንኮተኩታለን፡፡ ሁለቱም ጽንፎች በታሪክ ላይ ባላቸው የተንሸዋረረ አረዳድና በክህደት የታገዘ ቅራኔና እልህ በስፋት ሲታይ ለአገርቷና ለህዝቧ፣ ሲጠብም ለፓርቲያችን፣ ‹‹እንወክለዋለን›› ለምንለው ህዝብም ሆነ ለግል ፍላጎታችን ‹‹እጓምብሽን›› የማይጠቅም መሆኑን ለመቀበል (ለመማር) ዛሬም ያልተዘጋጀን መሆኑን የእስከዛሬው ድርጊታችንና የተጠናወተን- ያልተላቀቅነው ቆሞ-ቀር/የተቸነከረ አስተሳሰብ ይመሰክርብናል፡፡

ከላይ ያየናቸው ዛሬም ካለፈው ለመማር ብቻ ሣይሆን በህዝቡ ውስጥ ተዳፍኖ ያለውን የለውጥ ፍላጎት እንደ እምቅ ኃይል ለመጠቀም ዝግጁ ያለመሆናችንን በግልጽ ያሳያል፡፡ ዛሬም ከውድቀት/ክሽፈት ክብ አዙሪት ውስጥ አልወጣንም፡፡ ይህም በታሪክና ህዝብ እንደሚያስጠይቅ፣ቢያንስ ከራሳችን የኅሊና ፍርድ እንደማናመልጥ አልተቀበልንም፤ ወይም ወደ ውስጣችን ተመልክተን ድክመታችንና ጥፋታችን ለመቀበልና ከተጠያቂነት ራሳችንን ለማውጣትና የበደልነውን ህዝብ ለመካስ የተዘጋጀን መሆኑን ልናረጋግጥ አልተቻለንም፡፡ ሆኖም ይጥበብ እንጂ የዕድሉ በር ተዳፍኖ አልተዘጋብንም፣ ይዘግይ /ይርፈድ እንጂ ጨርሶ አልመሸብንም፡፡ከሁለቱ ጥንፈኛ አመለካከቶችና አካሄድ መካከል በብሄራዊ የመግባበት መድረክ ሊፈጠር የሚችል አማካይና አካታች የአመለካከትና የአካሄድ አማራጭ መፍትሄ አለ፡፡

በመሆኑም ይህ የጀመርነው ‹‹አዲስ›› ጥረት እንዳለፈው በጋራ የደከምንበትን በ ‹‹የእናቴ መቀነት ጠለፈኝ›› መንገድ ላይ ለመጣልና ወደየጎጆኣችን ለመመለስ ምክንያት የምንፈልግበትና በውጤት አልባው መንገድ ለመጓዝ ሣይሆን የሩቁን ትተን ካለፉት 23 ዓመትት ተደጋጋሚ ውድቀታችን ተምረን ሥርነቀል የአስተሳሰብና አመራር ለውጥ በማምጣት በኃላፊነት ስሜት ያለውን እምቅ ኃይል በጥበብ ለመጠቀም የሚያስችል ቁርጠኝነት ካሳየን ከሚፈለገው ግብ የማንደርስበት አንዳችም ምክንያት አይኖርም፡፡ በክሽፈት ድግግሞሽና የተጠያቂነት ያለመኖር ካልተጋረድን እና/ ወይም ክሽፈትን ስለተለማመድነው በውጤቱ ያደረስነውን ጥፋት ለመረዳት ራሳችንን ቸክለን -በነበርንበት ለመቀጠል ካልወስንን በቀር ዛሬም ዕድሉ ከኛው ጋር አለ፡፡ በሌላ አገላለጽ ከላይ እንደተጠቆመው እንደአገር ያለንበት እጅግ አሳሳቢ ሁኔታ፣እንደ ህዝብ እየደረሰብን ያለው አሰቃቂ ሥቃይና ምስቅልቅል እንደተጠበቀ ሆኖ ከጥናቱ የምንረዳው ማዕከላዊ ነጥብ ምንም እንኳ በጉዞኣችን ተደጋጋሚ ውድቀቶች ቢያጋጥሙንም አሁንም ረፈደ እንጂ አልመሸምና በጋራ ሁኔታውን የመቀልበስ ዕድሉ ተሟጦ አላለቀም፤ የሚፈለገው ለዘላቂ ውጤት በጋራ ለመስራት የእኛ ፍላጎት፣ዝግጅትና ቁርጠኝነት … ነው፡፡ ‹‹ይቻላል//››፡፡

ከላይ ያስቀመጥነውን የግምገማና ጥናት ውጤት ማጠቃለያ ኃሳብ ለመድረስ ያስቻሉንን የ23 ዓመታት ጉዞኣችን ግምገማና አጭር ዳሰሳ ግኝቶች ዘርዘር ተደርጎ ለውይይት መነሻ በሚያመች መልክ በአጭር አጭሩ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡ በቅድሚያ የፓርቲዎችን ውስጣዊ ሁኔታ (በፓርቲዎች አደረጃጀት፣ አመራር፣አሰራርና ተግባራዊ እንቅስቃሴ -በጥቅሉ በእነርሱ ቁጥጥር ሥር ባሉ ጉዳዮች–ጥንካሬዎችና ገንቢ ውጤቶች/4.2.1./ እንዲሁም ድክመትና ውስንነት/4.2.2./) የቀረቡ ሲሆን ፣ በቀጣይም ከፓርቲዎች ቁጥጥር ውጪ የሆኑ (መልካም አጋጣሚዎች/4.2.3./ና ሥጋቶች/4.2.4./) ውጪአዊ ጉዳዮች ቀርበዋል ፡፡

4.2. ውስጣዊ ጉዳዮች በሚመለከት፡-
4.2.1. የተቃውሞ ፖለቲካ ጎራው ጥንካሬዎችና ገንቢ ውጤቶች፡-

4.2.1.1. የፖለቲካ ኃይሎች በጋራ ለመሥራት ያደረጉት ጥረት በተደጋጋሚ ቢከሽፍም ተስፋ ባለመቁረጥ ጥረቱን መቀጠላቸው፤

ከደርግ ጊዜው ኢማሌዲህ ተነስተን እስከ ቅርብ ጊዜው የ‹‹33ቱ›› ሙከራ ድረስ ያለፍንባቸውን የትብብር ሂደቶችና የውድቀታቸውን ምክንያት ገምግመን/አጥንተን አይደለም ቆጥረን ለመጨረስ እንኳ አስቸጋሪ ነው፡፡ የእነዚህ ጥረቶች መደጋገም ‹‹ሽንፈትን/ክሽፈትን/ውድቀትን›› አለማምዶን ይሆን የሚለውን አሉታዊ ውጤት አቆይተን ወደሌላው ስናማትር ከዚህ ተደጋጋሚ ውድቀት በኋላም ተስፋ ሳይቆረጥበት ጥረቱ በተቃዋሚ ጎራው በተደጋጋሚ መደረጉ፣ ፍላጎቱና ጥረቱ (በጋራ ዓላማችን ላይ ያለን የጠራ ዕይታ ጥያቄ እንዳለ ቢሆንም) ዛሬ ድረስ መዝለቁ በራሱ እንደጥንካሬ ሊወሰድና በጥናትና ውይይት ለመታገዝና ብሄራዊ መግባባት ለመፍጠር ከተጋን ለቀጣዩ ትግል እንደ ግብኣት ሊያገለግለን ይችላል፡፡

4.2.1.2. በፓርቲዎች ውስጥ የወጣቶች በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ተሳትፎና የአመራር ብቃት እያደገ መምጣት፤

እርግጥ ነው የወጣቶች ተሳትፎ ገና ከትግሉ ጅማሮ ነበር፣ ወጣቱ የፖለቲካ ትግሉ ጠንሳሽና አንቀሳቃሽ ሞተርም ነበር፡፡ይሁን እንጂ በአብዛኛው ተሳትፎው ከዕድሜ/ከተፈጥሮኣዊው የለውጥ/አዲስ ነገር ፍላጎት ፣ በፖለቲካ፣ ፍልስፍናና በትግሉ ሂደትና ውጤት ዕውቀት በመመራት ጋር ሲነጻጸር ተፈጥርኣዊው ያመዘነ ነበር ማለት አስተዋጽኦውንና መስዋዕትነቱን አያሳንሰውም፡፡ ዛሬ ላይ ተሳትፎው እንደተጠበቀ ሆኖ በዕውቀት ላይ የመመስረቱ ጉዳይ እየተሻሻለ መምጣቱና የወጣቱ በአመራር ያለው ተሳትፎ እየሰፋ ብቻ ሳይሆን ብቃታቸውንም እየመሰከረ የመጣበት ሁኔታ ይታያል፡፡ይህ በፖለቲካው መድረክ የወጣቱ በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ተሳትፎና የአመራር ሚና እያደገ መምጣት በቀጣይ ያለውን ብሩህ ተስፋ አመላካች መሆኑን ብቻ ሣይሆን የኅብረተሰቡንም ንቃተ ኅሊና ዕድገት ጠቋሚ አድረጎ መውሰድ ይቻላል፡፡እዚህ ላይም የለውጡ ዓላማ በአዲስ አስተሳሰብ ላይ የመገንባት ጥያቄ መሆኑ ቀርቶ የትውልድ ልዩነትን የማስፋት (ትግሉ በትውልድ መካከል) እንዳይሆንና ይህንኑ ወደመፍታት እንዳይዞር የመፈተሸ አስፈላጊነት እንደተጠበቀ ሆኖ ለቀጣዩ ትግል ጠቃሚ ግብኣት አድርጎ መውሰድ ይቻላል ማለት ነው፡፡ አንጋፋዎቹ ፖለቲከኞች እነዚህን ወጣቶች ለመቀበል ልባችንና አዕምሮኣችንን ከፍተን መጠበቅ ይኖርብናል፣ ከዘጋንም ሰብረው መግባት መጀመራቸውን አለማጤን መጨረሻችንን አያሳምረውም፡፡

4.2.1.3. የተቃውሞ ጎራው ኢትዮጵያዊነት ስሜት እያደገ እንዲመጣ ያበረከተው አስተዋጽኦ፤

በገዢው ፓርቲ በህዝብ ውስጥ ያለመታከት ከተረጨው የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ ስልቶች -ህዝብን መነጣጠል
፣ከአንድነቱ ይልቅ ልዩነቱን ለጥጦ በማቅረብ አብሮነቱን መፈታተን፣አድሎኣዊ የሃብት ክፍፍልና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት በማድረግ የመለያየትና ጥርጣሬ የመፍጠር ጥረት… ፣ በተቃራኒ ህዝቡ በሂደቱና ውጤቱ ላይ ካገኘው ተጨባጭ እውነት በመነሳት የአንድነትና ኢትዮጵያዊነት ስሜቱ እየተጠናከረ መምጣቱን በምርጫ 97 ለዲሞክራቲክ የሰላማዊ ትግል ኃይሎች ከሰጠው ድጋፍ፤ ዛሬ ላይም የገዢውን ፓርቲ የመከፋፈል ስልት በግንባር እየተቃወመ ካለበት ሁኔታና ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ባጠቃላይ ፣በተለይም ለብሄር/ክልል ፓርቲዎች ከሚያቀርበው ጥያቄ በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡ በዚህ ረገድ ያልተሳኩና የፈጠሩት አሉታዊ ተጽዕኖ መኖሩ እውነት ቢሆንም የዲሞክራቲክ የተቃውሞ ፖለቲካ ኃይሎች ለትብብር ያደረጉት ጥረት የተጫወተው ሚናናና ያሳደሩት ገንቢ ተጽዕኖ ቀላል አይደለም፡፡ ከደቡብ ኅብረት/ኢሠዴአኃ ም/ቤት እስከ መድረክ ያሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡

4.2.1.4. የተቃውሞው ጎራው ህዝብ በሠላማዊ ትግል /የምርጫ ፖለቲካ / ላይ ያለው እምነት እንዲጨምር የተጫወተው ሚና፤

በአሸናፊ/ተሸናፊ የጦርነት ትግል መንግሥትን የመቀየር ታሪካችንና ልምዳችን በአገራችን በደረሰው ተደጋጋሚ ጥፋት ህዝቡ የተማረ መሆኑን አመላካች ሁኔታ ይታያል፡፡ በዚህ ረገድ ያለውን ለውጥ ሲያዳክም የሚታየውና የጦርነትን አማራጭ የግድ እያደረገ (ወደዚያ አማራጭ እየገፋ) ያለው ገዢው ፓርቲ ስለመሆኑ ምርጫ 97 ይመሰክራል፡፡ ሆኖም አሁንም እኛ የሠላማዊ ትግል በሩን ማስከፈት ከቻልን በህዝብ በኩል ያለው ፍላጎትና ተነሳሽነት አበረታች መሆኑና በድምጹ የሥልጣን ባለቤትነቱን ለማረጋገጥ ያለው ዝግጁነት እያደገ መምጣቱን በግልጽ ማየት ይቻላል፡፡

4.2.1.5. የተቀውሞ ጎራው አገራዊ ጥፋት በመከላከል በኩል ያበረከተው አስተዋጽኦ፤

የተቃውሞው ጎራ ገዢው ፓርቲ በየትኛውም ዋጋ ሥልጣኑን ለማቆየት በሚያደርገው ጥረት ከከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲው በተጨማሪ የሚያከናውናቸውን ለአገርና ህዝብ የማይበጁ ተግባራት በማጋለጥና እንዳይተገበሩም በመከላከል ረገድ ያበረከተው ድርሻ የሚናቅ አይደለም፡፡ ዛሬ ላይ ህዝቡ ከገዢው ፓርቲ በተጻራሪ እንዲቆም ፣ለገዢው ፓርቲ ማስፈራሪያዎችና መደለያዎች በቀላሉ እንዳይሸነፍ በማድረግ በኩል… በአንጻራዊ ሁኔታ ከፍርኃትና መሸማቀቅ እንዲላቀቅ ማብቃት የተቻለውና በውጤቱም አገሪቱን ከጥፋት ለመታደግ ተችሏልና ይህን ለቀጣዩ ትግል እንደ ስንቅ መጠቀም ይቻላል፡፡

ከነዚህ በተጨማሪ በርካታ የአብነት ተግባራትንና ውጤቶችን መጥቀስ ይቻላል፤ ነገር ግን ይህ የተደረገውን ትግል አስተዋጽኦ እንደማሳያ በማቅረብ ዕውቅና ለመስጠትና ለቀጣዩ ትግልም ግብኣት እንዲሆን ጠቀሜታውን ለማሳየት ነውና በዚህ ላይ ብንገታ ከጥናቱ ግብ ብዙ አያርቀንም፡፡

4.2.2. ድክመቶችና ውስንነቶች፤

4.2.2.1. የተቃውሞ ጎራ ፓርቲዎች በጥምረት ለሚያደረጉት ጥረት የጠራ የጋራ ኃሳብ ችግር፤
የጋራ ዓላማ ግልጽ አለማድረግ፣የጋራ ተግባራትን አለመመጠን፣ከአቅም በላይ ማቀድ/በፍላጎት መመራት፤

ወደ አብሮ መሥራት/ትብብር ከመሄድ በፊት ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን አስመልክቶ
ከፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች አንጻር በቂ ትንተናና ውይይት ሳያደርጉ በተቻኮለ መንገድ ወደ የጋራ ሥራ መግባት፤ ለሁለት ጽንፎች ትግል አመቺና አሳታፊ/አካታች የአማካይ ፖለቲካ ሜዳ አለማስፋት፣ ለአገሪቱ ችግሮች መፍትሄ ለመስጠት በምንሄድበት መንገድ የገዢውን ፓርቲ የትግል ስልትና መንገድ መከተል/ ጥላቻን በጥላቻ፣ ሴራን በሴራ…/፣ ካረጀውና ካፈጀው የፖለቲካ ሥልጣን ጥያቄና ለውጥ ታሪክና ልምድ የኃሳብ ልዩነቶችና በቅራኔዎች ላይ ኃሳብን አሟጦ/without Reservation/ በመወያየትና መከራከር ከመማማር ይልቅ መፈራረጅና መከፋፈል ወይም በይሉኝታ ታስሮ መቀመጥ፣ በጋራ የምንነሳበትንና የምንደርስበትን (መነሻና መድረሻችንን) በውል/በግልጽ ሳንለይ በፍላጎትና ጊዜያዊ ክስተቶች በመገፋት ወደ ትብብር መግባትና ከአቅም በላይ ማቀድ፣…. በማሳያነት አቅርበን የጠራ ኃሳብ ለመጨበጥ የሚከተሉትን መጠየቅ ይኖርብናል፡፡

የምንታገለውን በማወቃችን/በመለየታችን (እርሱም ላይ ግልጽ የጋራ ስምምነት የመኖሩ ጥያቄ እንዳለ ሆኖ ማለትም – ጭቆናን አጥፍቶ የሥርዓት ለውጥ ወይስ ገዢውን ፓርቲ አስወግዶ የመንግሥት ለውጥ፤ የ‹‹ጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው›› ወይስ በመርህና የጋራ ግብ ላይ የተመሰረተ ነው?) ላይ በደረስነው ስምምነት (ቢያንስ አምባገነኑን ገዢ ፓርቲ ለመለወጥ በሚለው ) መሰረት ‹‹እንተባበር›› እያልን ነው፤ ነገር ግን በትግላችን ማስመዝገብ በምንፈልገው ውጤት፣ ልንደርስበት በምንፈልገው ግብ (ልናመጣው በምንፈልገው ለውጥ እንዴትነት) ላይ ስምምነት አለን (የተለመደው የአሸናፊ/ ተሸናፊ- ወይስ የማንዴላ -መንገድ?)፣ ስምምነት በሌለበትስ ወደ የጋራ አገራዊ ግባችን መድረስ ይቻለናል?

ለተስማማንበት ትግል የጲላጦስ ( ከሃዲው)ን ወይስ የጴጥሮስ (ሰማዕቱ)ን መንገድ ነው እየተከተልን ያለነው? ማለትም እንደ ጴጥሮስ ላመንበትና ለቆምንለት ዓላማ እስከመጨረሻው በጽናት ለመቆምና የሚፈለገውን ዋጋ ሁሉ ለመክፈል ተዘጋጅተናል ወይስ እንደ ጲላጦስ ጥቅማችንና ሥልጣናችን ጥያቄ ውስጥ ከወደቀ ያመንበትን እንጥላለን ? ያላመኑበትን እያለቀሱ በማስፈጸም የኅሊና ፍርድ በሚደርሰው ጸጸት ውጤቱን ባንቀለብሰውም እንደ ጲላጦስ በጥፋታችን ለመጸጸት እንኳ ምን ያህል ተዘጋጅተናል– ድፍረቱ አለን?

የችግርና ቅራኔ አፈታታችን ምን ይመስላል ? በየፓርቲያችንም ሆነ በፓርቲዎች መካከል በሚደረግ ግንኙነት – ልዩነቶች፣ቅራኔዎች የመኖራቸውን ሃቅ ፣አብሮ በመሥራት ውስጥ የሚፈጠር ችግር የመኖሩን እውነት ተቀብለን ጊዜ ሰጥተን በመወያየት ልዩነቶችን ለማጥበብ፣ ቅራኔዎችን ለማስተናገድና
ችግሮችን ለመፍታት እንጥራለን ወይስ በመለያየት እንገላገላለን ? እስቲ በተቃውሞ ፖለቲካው ጎራ ካሉት ፓርቲዎች ለአጭር ጊዜ አብረው የሰሩትን አልፈን – በመዐህድ (ዛሬ ላይ በምርጫ ቦርድ ተመዝግበው ያሉ ከስድስት/6/ (@) በላይ ፓርቲዎች በተዘዋዋሪና በቀጥታ ከዚህ የወጡ ናቸው) ፣ደቡብ
ኅብረት/አማራጭ ኃይሎች (ዛሬ ላይ በምርጫ ቦርድ ተመዝግበው ያሉ ከሃያ/20/ (b) በላይ ፓርቲዎች/ኢራፓ እና አዲስ ራዕይን (c) ጨምሮ/ ከነዚህ የወጡ ናቸው) በኩል ያላለፉ ስንት እናገኝ ይሆን? በዚህ መሠረት ካሉት የተመዘገቡ ፓርቲዎች 40ዎቹ ነጻ ናቸው/የገዢው ፓርቲ አባላት፣አጋሮችና ሥሪቶች ውጪ/ ናቸው ብንል ከ65 በመቶ በላይ የሆኑት መነሻቸው መዐህድ/ደቡብ ኅብረት/አማራጭ/ ነው ማለት ነው፡፡

ለኦሮሞ ህዝብ የቆሙ ከ8 የማያንሱ ፓርቲዎች ለምን አስፈለጉ? ብለን እንጠይቅ፡፡ ከነዚህ ውስጥ አምስቱ/5/ ነጻ ናቸው ብንል መቶኛውን ከ77 ከመቶ በላይ ያደርገዋል ማለት ነው፡፡ ያለፍንበትና ያለንበት አያሳዝንም –አያሳፍርም፤ለቀጣይ ትግሉ ትምህርት ለመስጠት ከበቂ በላይ አይደለም ? ማዘንና ማፈር ወደ ቁጭት ካልተሸጋገረና ከጠብመንጃ ፍልሚያ በተቃራኒ በቆመው የሠላማዊ ትግል መሥመራችን በኃሳብ ላይ ወደ መወያየት/ዲያሎግ/ ካልተሸጋገርን ለምንፈልገው ለውጥ አንዳች ፋይዳ የለውም፡፡ የተለመደው መንገድ የትም አላደረሰንም፣አያደርሰንም፡፡

ከላይ የተነሱትን ጥያቄዎች መልስ ስንፈልግ ትግሉ የተደከመውንና የተከፈለውን መስዋዕትነት የሚመጥን ውጤት ያላስመዘገበበት ምክንያቶች፡-

ተገቢውንና ተፈላጊውን ዓላማ/ሃሳብ በግልጽ ለይተን ስላላስቀመጥን ( የምንሻውን አጥርተን ስላላወቅን) ሌላ የተለየ ውስብስብ/ውጥንቅጥ (አብስትራክት) መፍትሄ ፍላጋ ስንዋጅ እና በአብዛኛው በተከናወኑ ተግባራት – ድርጊቱንና ጊዜውን በአስፈላጊውና በተፈላጊው ጉዳይ/በተቀመጠው ዓላማ ላይ ስላላሳረፍንና ስላላሳለፍን፤

የሚጠበቅብንን ካለመገንዘብ አካባቢያችንን ገዢው ፓርቲ እንዳስቀመጠልን ብቻ ሣይሆን እንዲሆን እንደምንፈልገው አድርገን ለማየት ካለመቻልና እንደሚቻልና እንዲሆን እንደሚገባ ስላልተገነዘብን፤…ከመሆን የዘለሉ አይደሉም፡፡

እነዚህን ለማሳያ የተመለከቱ ጉዳዮችንና ለውይይት መነሻ በምሳሌነት የተነሱት ጥያቄዎች ላይ በግልጽ ለመነጋገር እምነት፣ፈቃደኝነት፣ ዝግጅት…. ከሌለን ዛሬም በተለመደው መንገድ ለመጓዝ እንጂ ለለውጥ አልተዘጋጀንምና ምርጫችን ከወዲሁ ማስተካከል ይኖርብናል፤ የ‹‹ሁለንተናዊ ለውጥ ኃይሎች›› እና ‹‹የተለመደው መንገድ ተጓዦች›› ከጅምሩ መለየት አለባቸው፡፡

4.2.2.2. የየተቃውሞ ጎራ ፓርቲዎች የአመራርና አሰራር ችግሮችና የፓርቲና የጥምረት አመራሮች ‹‹ ኢጓምብሽን›› እና የተጠያቂነት አለመኖር፤

የሰለጠነ ፖለቲካ ልምድ ማነስና የአሸናፊ/ተሸናፊ ትግል ውርስ/ልምድና ተሞክሮ የውስጠ ፓርቲ ዲሞክራሲ
አለመዳበር፣ (መከፋፈል፣መፈራረጅ፣ የትናንት ወዳጅንም ካላጠፉ ያለመተኛት…)፣ በተለመደው የአደረጃጀት መዋቅር፣የአመራርና የአሰራር ማዕቀፍ ለመቀጠል ያለው ፍላጎት( ለመሰረታዊ ለውጥ ያለው ፍላጎትና ዝግጁነት

—————————————————————————————————————————–
@- መዐህድ፣መኢአድ፣ኢዴፓ፣መኢዴፓ፣አንድነት፣ሰማያዊ፣
(b)-ደኢዴኃአ፣ጋዲኅ፣ወህዴግ፣ጋጎህዴአ/ኦሞቲክ፣ኢሶዴ-ደኅፓ፣የብዲን፣ጉህዴግ፣ሶጎህዴድ፣ ኦህዲኅ፣ ሲአን፣ ሀብአዴድ፣ ሀብዴድ፣ከህኮ፣ጌህዴድ፣መዐህድ፣ጠህዴኅ፣ኢዲኅ፣ኢፍዴኃግ፣
(c)- የኢራፓ መሥራችና መሪ የደቡብ ኅብረት የሰሜን አሜሪካ ድጋፍ ሰጪ የነበሩ፣ አዲስ ራዕይ ደግሞ የኢራፓ ግንጣይ መሆኑን ያጤኑኣል፡፡

ውስን መሆን)፣ የመሪዎች አዲስ አመራር የመፍጠር/ማሳደግና ማብቃት/ኃላፊነት ከመወጣት በተቃራኒ በራሳቸው የሚወጡትንም ለማጥፋት የሚደረግ ሴራና የበቀል እርምጃ፤ የራስን ፓርቲ አጉልቶ ለማሳየት የሚደረግ ፉክክርና
ለራስ በራስ ፕሮፖጋንዳ በመጋረድ ከእውነታው በላይ ግምት የመስጠት የታላቅነት በሽታና፤ የመሳሰሉትን
በየፓርቲውና በፓርቲዎች መካከል በሚደረጉ ግንኙነቶች ላይ የሚታዩ ድክመቶችን/ውስንነቶችን እዚህ ላይ
ማንሳት ለምናስቀምጠው መፍትሄ ተገቢ ግብኣት ይሆናል፡፡

በተጨማሪም ይህ ሁሉ በሚሆንበት ሁኔታ ውስጥም የፓርቲ አመራሮች የኃላፊነት ስሜት በበቂ ካለመታየቱም በፓርቲያቸው ህገ ደንብም ሆነ በህዝብ ፊት /በአደባባይ / በሚገቡት ቃል ተጠያቂነት ያለመኖሩ ለችግሩ አለመፈታት ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው፡፡

4.2.2.3. የተቃውሞ ጎራ ፓርቲዎች አቅም ውስንነት፣

ከገዢው ፓርቲ የመከፋፈል ሴራ በተጨማሪ በእኛ ከላይ በተጠቀሱት ድክመቶች የተነሳ አቅማችንን በመከፋፈሉ ከሚመጣው ውስንነት በተጨማሪ የህዝብን የተባበሩ ጥያቄ ባለመመለሳችንም በየጊዜው ከአገር ቤትም ሆነ ከውጪ /ዲያስፖራ/ በቂ ድጋፍ ለማግኘት አልተቻለም፣ የሚገኘውም ወጥነትና ቀጣይነት እንዳይኖረው ሆኗል፡፡ይህም በተናጠልም ሆነ በጋራ ያለንን የህዝብ ተደራሽነት አቅምና ከታች በ 4.3.1. ሥር የተጠቀሱትን መልካም አጋጣሚዎችና አመቺ ሁኔታዎች የመጠቀም አቅም በመገደብ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል፣ ያሳድራልም፡፡ በዚህ እውነታ የተቃውሞ ጎራው የአቅም ግንባታ ዕቅድ በችግር አዙሪት ውስጥ እንዲወድቅ ተገዶ በፋይናንስ፣ማቴሪያልም ሆነ የሰው ኃይል አቅም መጠናከር አልተቻለም፡፡

4.2.2.4. የተቃውሞ ጎራ ፓርቲዎች የገዢውን ፓርቲ የመከፋፈል ፖሊሲ ተግባራዊነትና ዘርፈ ብዙ ፖለቲካዊ ተጽዕኖ የሚመክት ‹‹ተመጣጣኝ ›› ዝግጅት አለማድረግ፣

ከላይ በተጠቀሱት ድክመቶች ውስጥ ሆኖ በቂ የመተማመን ፈጥሮ በጋራ ለመሥራት በጽናት መቆም አስቸጋሪ
በመሆኑ ለገዢው ፓርቲ ሰርጎ የመግባትና የመከፋፈል ዕድል ከማስፋቱም በተጨማሪ ትግላችንን በተበታተነ መልክ ማድረጋችን ለአጠቃላዩ ውጤትም ሆነ ለአገራዊው ዓላማ በገዢው ፓርቲ ላይ የምናሳድረው ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ተጽዕኖ ጎልቶ እንዳይወታ ከማድረጉም በተጨማሪ በህዝብ ያለንን ተቀባይነት ከጥያቄ ውስጥ ጥሎታል፣ ይጥለዋል፡፡

4.2.2.5. የተቃውሞ ጎራ ፓርቲዎች ካለፈው ለመማር ለድክመቶችና ውስንነቶች የተቀመጡ የመፍትሄ ኃሳቦችን ተግባራዊ አለማድረግ፣

ሁሌም ራስን ከድክመትና ስህተት ነጻ ለማድረግ የሚደረግ ጥረትና በተለመደው የክህደት መንገድ ለመቀጠል ያለው ፍላጎት እስከዛሬ ተጀምረው ብዙ ሳይራመዱ ለከሰሙ የጋራ ጥረቶችም ሆነ በቀጣይም ለሚታሰቡ በትብብር የአብሮ መሥራት ትልሞች እንቅፋት ናቸው፡፡ በየትኛውም እንቅስቃሴ ውስጥ ስህተትም ሆነ ድክመት የመኖሩን እውነት ለመቀበልና ከዚህም ለቀጣዩ ምዕራፍ ትምህርት የመውሰድ አስፈላጊነትና ዝግጅት የማይታለፍ ይሆናል ማለት ነው፡፡ የተለመደው የመሸፋፈንና የመሸካከም መንገድ የትም አላደረሰም፣አያደርስምና ሁላችንም በትግሉ ሂደት ለተከሰቱ ስህተቶች የየድርሻችንን አንስተን ትምህርት ወስደን ለወደፊቱ ትግል መዘጋጀት ይኖርብናል፡፡

በተናጠል ፓርቲዎችና በፓርቲዎች የጋራ ትግል መድረኮች የሚነሱ የልዩነት ኃሳቦችን ማስተናገድ ካለመቻል/ካለመፈለግ ወይም ልዩነቱን በመካድ ልዩነቱ በመከፋፈል/አንጃ ማጠናቀቅ ሊያበቃ ይገባል፡፡ ካለፈው የምንማርበትና ወደውስጥ ለመመልከት የሚረዳን የግጭት አፈታትና የክትትልና ግምገማ ሥርዓትና መዋቅር/አደረጃጀት መዘርጋትና ሥርዓቱም ተግባራዊ መደረግ ይኖርበታል፡፡

በተጨማሪም የሚከፋፍለን ገዢው ፓርቲ ወይስ የራሳችን መርህ አልባነት፣ለመርህ ተገዢ ለመሆንና የተደበቀ ፍላጎት ተገዢነት በመካከላችን የፈጠረው ጥርጣሬ እንዲሁም ለገዢው ፓርቲ ለገዚው ፓርቲ ከራሳችን ውስጣዊ እምነትና ማንነት በመነሳት የሰጠነው የተሳሳተ ግምት ነው? የሚለውን ማጤንና መመለስ ይኖርብናል፡፡

4.2.2.6. የተቃውሞው ጎራ ፓርቲዎች ለዲያስፖራ አሉታዊ ተጽዕኖ በሩን ክፍት ማድረግ፤

የዲያስፖራዎች በአገራቸው ጉዳይ የመሳተፍም ሆነ ተገቢውን አዎንታዊ ተጽእኖ ለማሳደር የሚደረግ ጥረት የማይካድ መብታቸው ነው፡፡ በአንጻሩ ሁለንተናዊ ድጋፍ የማድረግ ግዴታም ይኖርባቸዋል ማለት ነው፡፡ ነገር ግን በተሻለ ሁኔታ ላይ ባሉበት ሳይተባበሩ-በየጉዳዩ ተለያይተው እያሉ ተባበሩ፣ ራሳቸውን ላላሳመኑበትና ላላዘጋጁበት መስዋዕትነት የእንዲህ አድርጉ ትዕዛዝ የመስጠት ድፍረት … ዕድሉን የሰጣቸው የእኛ ድክመት መሆኑ መታወቅና በግልጽ መነገር ይኖርበታል፤ የጠንካራ ተቋማዊ አመራርና አሰራር ባለቤትን እጅ ለመጠምዘዝ ማንም አይደፍርም ፤ ደካማ ደግሞ ለማንም የጥምዘዛ ኃሳብ ሲያልፍም ድርጊት መጋለጡ ሃቅ ነው፡፡

4.3. ውጪአዊ ጉዳዮች በሚመለከት፡-
4.3.1. መልካም አጋጣሚዎችና አመቺ ሁኔታዎች
4.3.1.1. የአይ ሲቲ፣ የግንኙነትና መረጃ ሥርጭት ቴክኖሎጂ መስፋፋት፣
4.3.1.2. የዲያስፖራ ቁጥር፣ተሳትፎና ስርጭት እና ለሁለገብ ድጋፍ ያለው ተነሳሽነት ፣
4.3.1.3. የአመራር ጥበብ- ሣይንስ እያደገ መምጣት ፣
4.3.1.4. በዓለማችን የዲሞክራሲ አስተሳሰብ ገዢ እየሆነ መምጣት፣ መስፋፋትና የመድብለ ፓርቲ ፖለቲካ ሥርዓት/የሠላማዊ ትግል ተቀባይነት እያገኘ መምጣት፣
4.3.1.5. በአገሪቱ የሚታየው የከፋ ጭቆናና ውስብስብ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮችና የገዢው ፖርቲ ግትር አቋም፣
4.3.1.6. የህዝብ ንቃተ ኅሊና ዕድገት፣ የምርጫ 97 ተሞክሮ፣በህዝቡ ውስጥ ያለው ከፍተኛ የለውጥ ፍላጎትና ለተቃዋሚ ጎራው የሚያቀርበበው የተባባሩ ጥሪ (በተናጠል አንሰማችሁም) ፣
4.3.1.7. የትውልድ መዋቅር– ወጣትና የተማረ፣ኃሳብ አመንጪ፣አቅጣጫ ጠቋሚ፣ ለለውጥ የሚተጋ፣ኃላፊነት ለመቀበል ፍላጎትና ብቃት ያለው ወጣት ትውልድ ፣
4.3.1.8. የመንግሥት ከህገመንግስቱ አግባብ ውጪ በተለያዩ የሀገራችን እምነት ጉዳዮች ጣልቃ መግባትና የእምነቶችን ተከታዮች ለሠላማዊ የእምነት ነጻነት በቁርጠኝነት ለመታገል ማነሳሳት፣ ለምሳሌ የሙስሊሙ ማኅበረሰብ ሠላማዊ ትግል ተሞክሮ ፤

4.3.2. ሥጋቶችና ደንቃራዎች
4.3.2.1. የከፋ ድህነት፤
4.3.2.2. ከፖለቲካ ፓርቲ ውጪ ያሉ የዲሞክራሲና የፕሬስ ተቋማት እና ተጽዕኖ ፈጣሪ ዜጎች ተሳትፎ ውስንነት፣
4.3.2.3. የዲያስፖራ አሉታዊ ተጽዕኖ፤
4.3.2.4. የዓለም አቀፍ ፖለቲካ ሁኔታና ግሎባላይዜሺን፣
4.3.2.5. የአገራችን ጂኦ ፖለቲካና ታሪካዊ ጠላቶች፣
4.3.2.6. የገዢው ፓርቲና መንግስት አንድና ሁለትነት፣
4.3.2.7. አይሲቲና የደህንነት ቴክኖሎጂ በገዢው ፓርቲ ሙሉ ቁጥጥር ሥር መሆን፣
4.3.2.8. የፖለቲካ ባህላችን አለመዳበር፣አብሮ የመስራት ልማድ ውስንነትና ሥር የሰደደ የመጠላለፍና የአሸናፊ/ተሸናፊ ትግል ታሪክ ውርስ፣

5. ቀጣይ አቅጣጫ/ ስትራቴጂክና ስልታዊ መፍትሄ ፡-

5.1. አጠቃላይ፡-

5.1.1. ዘላቂው ስትራቴጂክ መፍትሄ ፡-

ችግራችን በግልጽ ማወቅ ወደመፍትሄው ግማሽ መንገድ የመጓዝ ያህል ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ከላይ በተገለጹትና በውይይታችን በሚዳብሩት ድክመቶቻችንና ውስንነቶቻችን ላይ በዝርዝር መነጋገር ይኖርብናል፡፡ በነባራዊውና ያለፍንበት ታሪክና ልምድ ስንነሳ ያለንበት ተጨባጭ ሁኔታ ለቀጣዩ ትግል ሁለት አማራጭ አቅጣጫዎችን የሚያመላክት ነው፡፡

አንድም በተለመደው መንገድ በመጓዝ የገዢውን ፓርቲ ዕድሜ ማራዘም- በአገሪቱ ላይ ተደቀነ ለምንለው አደጋ ተባባሪ የመሆንና በህዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን አሰቃቂ ሁኔታ እንዲራዘም ይሁንታ መስጠት ፤ ያሊያም ሁለተኛው መንገድ ራሳችንን ለሁለንተናዊ ለውጥ በማዘጋጀት ባለን ጥንካሬና አበረታች ውጤት ላይ በመደመር ወደሚፈለገው ግብ በጋራ ለመድረስ ከትናንት ስህተታችንና ድክመታችን ለመማር ራሳችንን ማዘጋጀት ነው፡፡

በዚህ መሠረት ዲሞክራቲክ የፖለቲካ ኃይሎች ከነዚህ አንዱን የመምረጥ ዕድል/ፈተና ከፊታችን ተቀምጧል፡፡ ይህ የጀመርነው ሂደትም ከነዚህ አማራጮች ማን የትኛውን እንደሚመርጥ ግልጽ እንዲያደርግ ይጠበቃል፡፡ይህ ሂደት ምን ያህል ጊዜ እንደሚወስድ ከላይ የገለጽናቸው ችግሮች- የፖለቲካ ባህል ውርሳችንና ሥር የሰደደውና የተለመደው የአመራርና አሰራር ልማዳችን … ቀላልና ቅርብ አያደርጉትም፡፡ በመሆኑም እነዚህን መለየት የማይታለፍ ግን ደግሞ ረጅም ጊዜ የሚፈልግ መሆኑ ታምኖበት እንደ ዘላቂ ግብ የምንወስደው ይሆናል፡፡

5.1.2. የአጣዳፊው የጋራ ተግባር ስልታዊ መፍትሄ፡-
5.1.3.
በሌላ በኩል ደግሞ ዛሬ ላይ ከፊታችን ላለው ምርጫ ተሳታፊ አባላት በምርጫና ከታች ስለዝርዝር አስፈላጊነት ለማብራራት ባነሳናቸው ጉዳዮች ዙሪያ በ2005 ዓ.ም በ‹‹33ቱ›› ከወሰድናቸው የጋራ አቋሞች አንጻር ልዩነት ስለሌለን (ሁላችንም የጥያቄው አቅራቢ በመሆናችን) በጋራ ጥያቄዎቻችንን የማቅረብ የአጭር ጊዜ የጋራ ተግባር ይኖረናል፡፡ ስለ ምርጫ 2007 የጋራ አቋም ለመውሰድ የጋራ ጥያቄዎቻችንን መለየት፣ ማቅረብ፣…፡፡

5.2. ዝርዝር

የዝርዝር አስፈላጊነት፡-

ጉዳያችንን በዝርዝር መመልከት አስፈላጊ የሚያደርገው በጥቅሉ ላይ ልዩነት ያለማሳየታችን ነው፡፡የችግራችን ምንጭም ሆነ መፍትሄ በጥቅሉ ውስጥ ሳይሆን በዝርዝሩ ውስጥ ነው ከሚል ነው፡፡
እስኪ በጥቅል ስናየው እስከዛሬ መተባበር አብሮ መሥራት ከተሳነን ወይም በተደጋጋሚ ሞክረን ፈተናውን ከወደቅን የተቃዋሚው ጎራ ፖለቲካ ፓርቲዎችና መሪዎች እነማን ነን ከወከልነው ህዝብ (አገራዊም ይሁን የብሄር) ከመብት መከበር፣ እኩልነት፣ከዲሞክራሲ ሥርኣት ግንባታ ፣ከህግ የበላይነት፣ ከመልካም አስተዳደር… ውጪ የምንሰብክ ወይም በዚህ ላይ ልዩነት ያለን? ፣ እነማንስ ነን ያለውን አምባገነን ሥርዓት በዚህ የማንከስ ወይም አበጀህ የምንል? የትኞቹስ ነን ለዚህ በጋራ መቆም አያስፈልግም ብለን የምንከራከር ወይም ስለትብብር አስፈላጊነትና ወቅታዊነት የማንሰብክ ? ግን ስንቶቻችን ነን ስለውድቀታችን ዝርዝር ጉዳዮችን አንስተን በዝርዝር የተወያየን ወይም እንድንወያይ ጥያቄ ያቀረብን ወይም ፍቃደኛ የሆንን?

ስንቶቻችን ነን በየፓርቲያችን ያለውን ችግር ምንጭ/መነሻና ዘላቂ መፍትሄውን፣ ከሌሎች ጋር አብሮ የመሥራት ግንኙነታችን ያጋጠመንን ችግርና መፍትሄውን በዝርዝር የተነጋገርን፣በየፓርቲያችንም በጥቅሉ ጉዳይ ላይ ልዩነት ሳይኖረን እየተከፋፈልን ስንት መሆናችንን ለመናገር ስንቶቻችን እንደፍራለን የሚለውን መመልከት ለዛሬ ጅምራችን ስኬት የግድ ነው፡፡

በጥቅል ሲታይ በየፓርቲያችንም ሆነ በጥምረት በምናደርገው ጥረት ልዩነቶቻችንን ማቻቻል/ለመሸካከሙ ችግሩ ተጠራቅሞ እስኪፈነዳ አልተቸገርንም/፣መለያየትን ለማስቀረት ቢቻል በውይይት ለመተማመን – ካልተማመንንም ‹‹ላለመግባባት መግባባት››ና ከነልዩነታችን ተባብረንና ተከባብረን ለመኖር( በልዩነታችንና ተቃርኖዎቻችን ለምን እንተራመሳለን፣ለምን እንፈራረጃለን/ ትናንት በአንድ አመራር ውስጥ እንዳላለፍን ስለምን ከሃዲ፣ሰርጎ ገብ፣የእገሌ ተላላኪና ጉዳይ ፈጻሚ… እንባባላለን/ ለምን በጋራ ባወጣነው ህግ ለመተዳደር -ለወሰነው ውሳኔ ለመገዛት፣ በየመግለጫውና መድረኩ በምንለው እና በአፈጻጸማችን (በቃልና በተግባራችን ) መካከል ያለውን ልዩነት ለማጥበብ ስለለምን ተሸነፍን፣እንደምን ሊሳካልን አልቻለም- ለምን ተደጋጋሚ ጥረታችን ደጋግሞ ከሸፈ? ብለን የመጠየቅ አስፈላጊነት ከጥያቄ አይገባም፡፡

የማይገናኘው የተቃዋሚዎች ቃልና ተግባር በተለመደው የክሽፈት መንገድ (ሳንኖር አለን ስንል፣የፈረንጅ ውሻ ሆነን ባለንበት አንበሳ መስለን ስንታይ፣ከውስጣችን ሳንተባበር ‹‹ፍቅር እስከ መቃብር›› ማለታችንን በአደባባይ ስንናገር፣ ተከባበርን/ተቻቻልን በሚል ስንሸካከም፣… ህዝብን እያታለልን ፣ ተስፋ እየመገብን ተስፋ ስናሳጣው ….) በተደጋጋሚና በየሙከራዎቹ ‹‹ከትናንቱ ተምረናል›› እያልን እየማልንና እየተገዘትን በተለመደው መንገድ ጉዞውን ከቀጠልን ከኢህአዴግን የአገዛዝ ዕድሜ የሚበልጥ ዘመን አስቆጥረናል፡፡ የህዝቡ ‹‹የተባበሩ ወይም ተሰባበሩ›› ጥሪ/ጥያቄም የዚህ የብዙ ዕድሜ ታናሽ አይደለም፡፡ በተቃዋሚ ጎራው ለጥያቄው ምላሽ ለመስጠት የተደረጉት ያልተሳኩ ሙከራዎች የጥያቄው የዕድሜ እኩያዎች ናቸው፡፡ ለበርካታ ጊዜ በተደጋጋሚ የተጀመሩ ጥረቶች ከሽፈዋል፣ጽንሶች ተጨናግፈዋል፣ ለህዝብ ተስፋ ሆነው የተወለዱ፣ ግን ያላደጉ በርካታ የ‹‹ ሾተላይ›› ሰለባዎች በአጭር ተቀጭተዋል…. ዛሬም ጥሪውም ‹‹ጥረቱም›› ቀጥሏል፡፡

ለዚህ የጥያቄ ብቻ ሣይሆን የሥጋትም ምንጭ የሚሆነውና ጉዳዩን በዝርዝር የማየት አስፈላጊነት የሚያጎላው – የዛሬው ሙከራስ ከትናንቱ የተለየ ነውን– ወይም ከትናንቱ (ከቅርቡና የሩቁ) ፣ከተሞክሮው ( ከራስና ከሌላው፣ከተናተሉና የጋራው፣እንደ ፓርቲና መሪ )… ትምህርት ተወስዷል ? የተለየ መንገድ ተቀይሷል? የተለየ ስልትና ዘዴ ተወጥኗል ወይስ ‹‹ አሮጌ ወይን በአዲስ መያዣ›› እንዲሉ ነው- ይህ ከሆነስ የት ያደርሰናል ወይም ሩቅ ለመጓዝና ከግቡ ለመድረስ ችግራችን ምን ነበር- ምንድንነው- ለመፍትሄው ምን ማድረግ አለብን? የሚሉትን ልምድ -ወለድ ሥጋት የተጣባቸው ጥያቄዎች መመለስና የመፍትሄ ኃሳብ ማቅረብ መታለፍ የለበትም፡፡

ስለሆነም ያለፈውን ተደጋጋሚ ስህተት ላለመድገም ጉዳዮችን በጥቅል ሳይሆን በዝርዝር እንድንመለከት ስለሚያስገድድ ፣በእኛ ዕይታ ለዝርዝር ውይይት መነሻ የሚሆኑ፣( በሚፈለገው መጠን በዝርዝር ቀርበዋል ማለታችን ባይሆንም) በየትኩረት ነጥቦቹ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

5.2.1. ካለንበት የተበጣጠሰ አደረጃጀትና የተነጣጠለ ትግል ወደ አንድ የጠራ አስተሳሰብና ድርጊት/ ‹‹ዘመናዊት›› ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት /መሸጋገር፤ በጋራ አብሮ የመስራት ችግራችን ማስወገድ፡፡

በአሁኑ ጊዜ በበቂ ለማስረዳት በማንችለው ልዩነት በአገራችን ከሰባ አራት/74/ የማያንሱ የተመዘገቡ ፓርቲዎች አሉ፡፡ በዚህ የተበጣጠሰ አደረጃጀትና እንደ አደረጃጀቱ ሁሉ በሚታየው የተናጠል ሩጫ የተፈለገውን ውጤት ማስመዝገብ አልተቻለም፣አይቻልም፡፡ በዚህ አገራዊ የፖለቲካ አመለካከት ማዕቀፍ ላይ የተመሰረተ አንድ የትግል ማዕከል ባልፈጠርንበት- የየፓርቲ መሪዎች በየራሳችን ፓርቲና የሥልጣን ፍላጎት ታጥረን ባለንበት እውነታ የእስከዛሬው የተናጠል ሩጫ የትም ያላደረሰን ውጤት አልባ መሆኑን ተቀብለን ለህዝባችን በምንነግረው ልክ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ቅድሚያ በመስጠት አንድ አገራዊ የነጠረ የትግል ኃሳብ ላይ ለመቆም መትጋት ይኖርብናል፡፡ ለዚህ ራሳችንን ከ‹‹ኢጓአምብሽን›› አላቀን ከገባንበት አዘቅት የሚያወጣንና ወደ ‹‹ዘመናዊት ኢትዮጵያ›› የሚመራን የጋራ መተክሎች እና ጠንካራ ዲሞክራቲክ አመራር የመፍጠር ታሪካዊና አገራዊ ኃላፊነት የወደቀብን መሆኑን ተረድተን ለዚህ በጋራ መንቀሳቀስ ይኖርብናል፡፡ ለዚህ የሚጠበቅብን እጅግ ቀላል ውሳኔ – ‹‹በቃል መገኘትና ራስን ከሥልጣን ፍላጎት በማላቀቅ ለአገርና ህዝብ ቅድሚያ መስጠት ›› ነው፤ የምንለውን ሆኖ ለመገኘት – ቁርጠኝነት፡፡

5.2.2.. በየፓርቲዎች ውስጥ እና በፓርቲዎች ግንኙነት የአስተሳሰብና የአቋም ሥርነቀል ለውጥ አስፈላጊነት ማመን፡-የተለመደው መንገድ ከተፈለገበት አላደረስም፣አያደርስም፡፡

ትግላችን የነጻነት ፣የእኩልነት፣የፍትሃዊነት … ነው እያልን በራሳችን ውስጥ ቦታ ሳንሰጣቸው ወይም መርህና እሴት ሳናደርጋቸው (በመተዳደሪያ ደንብ ውስጥ ሳይሆን በልቡና -ከአንገት ሳይሆን ከአንጀት) በመተዳደሪያ ደንብ ያስቀመጥናቸውንም ራሳችን እየረገጥናቸው/እየተረማመድንባቸው/ ከውስጣችን በሃቅ ልንታገልላቸው የምንችልበት የፖለቲካም ሆነ የሞራል መሠረት ሊኖረን አይችልም፡፡ ስለሆነም በእስከዛሬው የጥላቻ ፖለቲካና አፍራሽ መንገድ ለደረሰው ጥፋት ንስኃ አድርገን የመቻቻል፣አንድነትና የፍቅር አቅጣጫ ለመከተል ሱባኤ መግባት ይኖርብናል፡፡

ወደውስጥ ለመመልከት መዘጋጀት፣ካሳለፍነው ተሞክሮ በመማርና በመማማር እውነትን ለመቀበልና በዕውቀት ለመመራት ራስን ማዘጋጀት፣… ሥር ነቀል ለውጥና ውጤት ተኮር አመራር ( ያለፈውን ለታሪክ ባለሙያዎች እናቆይ ቢባል እንኳ በተለይ የተቃዋሚ ፖርቲ አመራሮች የየድርሻችንን ለማንሳት ድፍረቱ ይኑረን)፣ከጥላቻ ፖለቲካ መውጣት– የጠላቴ ጠላት ወዳጄ …ወጥተን በጋራ እሴቶች፣ዓላማ … ላይ ግንኙነታችንን መመስረት የግድ ይሆናል ፡፡ ለዚህ ደግሞ ፡-
—— አርቆ የሚያስብና የሚጸጸት ቀና ኅሊና፤
—— በፍቅር የሚያስተሳስር፣ ልዩነትን የማያሰፋና የማያስፋፋ ብልህ አመራር፤
—— በትዕግስትና ሚዛና የሚመራ የሰከነ መንፈስ፤
—— ተሸንፎ የሚያሸንፍ ጠቢብ ልቡና – ካለን በቂ ነው፡፡
ይህ ማለት እንደምንናገረው ከራሳችን የግል ፍላጎትና የ‹‹ህዝባችን››እና የ‹‹ፓርቲያችን›› ከምንለው አስተሳሰብ ለአገራችንና ለጠቅላላ ህዝቧ/ኢትዮጵያዊያን ቅድሚያ የሚሰጥ መተክል ላይ መቆም ነው፡፡በቃላችን መገኘት፡፡ ከትናንቱ ካልተላቀቅን ስጋቱ ይህን አስቸጋሪ ቢያደርገውም ለአይቻልም የሚውል አንድ የልዩነት ሰበዝ ከመንቀል በሚያግባቡንና አብረን እንዲንቆም በሚያስችሉን ዘጠና ዘጠኙ ላይ ትኩረት በመስጠት የሚቻል እናደርገዋለን በሚለው ላይ መስማማት ይኖርብናል፡፡

ይህ ሲሆን ‹‹ አይቻልም ከሚለን ወይም እንዳይቻል ከሚያስረን›› ልምድና ኃሳብ እስር ራሳችንን ነጻ እናወጣለን፣ የአስተሳሰብ ለውጥ/ሽግሽግ እናመጣለን፡፡
ከመጠላላት፣መናናቅ፣ መወነጃጀልና፣ክስ እና መለያየት ወደ ፍቅር፣መከባበር፣ መመሰጋገን፣ አንዱ ሌላውን መረዳትና መተባበር፣
ከመተማማት ወደ ፊትለፊት/ግልጽ ውይይትና መተቻቸት (እንዲህ አልኩት ለማለትና ቂማችንን ለመወጣት ሳይሆን ለጋራ ዓላማ መሳካት) በጎውን ለማማስገን፣ ጎዶሎውን ለመሙላትና ስህተቱን በማረም ለበለጠ ውጤታማነት፤
የአሸናፊ/ተሸናፊ የጥላቻ ፖለቲካ አስተሳሰብና ያለፈውን ሙሉ በሙሉ አጥፍተን ከዜሮ የመጀመር ልምድ ወደ የነበረውን አስተካክሎና አሻሽሎ በዚያ ላይ የመቀጠልና ተሸንፎ የማሸነፍ የአሸናፊ/አሸናፊ ፖለቲካ… ወዘተ እንለወጣለን፡፡
በተመሳሳይ የሌላውን መልካም ሥራ ለማጣጣል ወይም ለእኛ አደጋ አድርገን ከማየት ወደ አጋርና ተደጋጋፊ አድርጎ በማየት ዕውቅና ለመስጠት እንተጋለን፤ ለመማርና መማማር እንዘጋጃለን፡፡

ለምሳሌ- እስቲ መድረክ አማካዩን መንገድ በማሳየት የመቻቻል ፖለቲካ ትግል አንድ እርምጃ ወደፊት አስኪዷልና ሊመሰገን ይገባል፣ ሰማያዊ ፓርቲ ለ8 ዓመታት የተከረቸመውን የአደባባይ ትግል/ሰላማዊ ሠልፍ/ በር በመክፈት የዓላማ ጽናትንና ቁርጠኝነትን አስተምሯል፣ የሙስሊሙ ማኅበረሰብ ያነሳቸውን ጥያቄዎች የባለቤቱ/ የህዝብ በማድረግ የሠላማዊ ትግል ስልትን በቀጣይነትና በተከታታይ በማሳየቱና እንደሚቻል በማረጋገጡ ተምሳሌት/አርዓያ ሊሆነን ይገባል፣ የወጣቱ ወደ አመራር ለመምጣት (ኃላፊነት ለመቀበል) እያሳየ ያለው ፍላጎት እያደገ መምጣት ገንቢ በመሆኑ ሊበረታታ የሚገባ ነው፣በነጠረ ኃሳብ ላይ መቆም ያለውን ጥቅምና መንግስትን ምን ያህል እንደሚያስፈራ (ትክክለኛ በመሆኑ፣23 ዓመት ታገልን ከምንል ፓርቲዎች/ድርጅቶች በላይ የዞን 9 ጦማሪያንና ጋዜጠኛ 9 ወጣቶች ላይ የተደረገውን ክትትልና የተከፈተውን ጥቃት ያስተውሏል) ከዞን 9 ጦማሪን መማር ይቻላል … ማለት ማናችን ይጎዳል፣ያሳንሳል? የየቱን ፓርቲ ህልውና አደጋ ላይ ይጥላል? በየጊዜውና በየጥቃቅን ምክንያቱ የምንከፋፈልና የምንበጣበጥ ‹‹የተማርን›› እና አገር ለመምራት የተነሳን የፓርቲ አመራሮች በርካታ አሥርታትን ከዘለቁ ዕድሮችና የሰንበቴ ማኅበራት … ‹‹ያልተማሩ›› አመራሮች አድናቆት ቸረን ከእነርሱ መማር ማናችን ይጎዳል፣ ያሳንሳል? ይህ ማለት ለአብነት የተጠቀሱት ሁሉ ችግር የለባቸውም፣ ከእኛ ይበልጣሉ የሚል ትርጉም እንደምን ይሰጣል ? በተመሳሳይ በግለሰብ ደረጃስ ዕውቅና የሚሠጣቸው የሉምን የሚለውን ለመጠየቅ ስለምን ድፍረቱን እናጣለን?

በእርግጥ እስከዛሬ በታየው ልምዳችን የፓርቲንም ሆነ የአመራሩን ስህተት ፊት ለፊት/በግልጽ መናገር አንድም እንዳለመከባበርና እንደጥቃት/ማጥቃት- የጥላቻ ሆኖ ይቆጠራል ፣ያሊያም ‹‹ ትግሉን›› እንደመጉዳት፣ ሲያልፍም እንደ ገዢው ፓርቲ ተልዕኮ ፈጻሚነት ይወሰዳል። ስለሆነም በተነገረ ጊዜ (የቱንም ያህል ትክክልና ከፍተኛ ፋይዳው ቢኖረውና ለእርምት የሚጠቅም ቢሆን ) እንደ ስህተትና አስነዋሪ ድርጊት ይቆጠራል፡፡ እውነቱ ግን ድክመትንና ስህተትን እየሸፈኑ ጥንካሬን ብቻ ማጉላት በጣም ጎጂ መሆኑ ነው፡፡ ለግለሰብ ፓርቲ መሪዎችም ሆነ ለፓርቲዎች ግብዝነት፣አይጠየቄነት/አይነኬነትና የውስጠ ፓርቲ ዲሞክራሲ እጦት የዳረገንም ይሄው ነው፡፡ ይህ ልማድ ሥር የሰደደ በመሆኑ እስካሁን በተሞከረ ጊዜ የተጠናቀቀው በአብዛኛው በመከፋፈል/መለያየት ወይም በአፈና ነው፡፡ ሆኖም በጊዜ ሂደት በግልጽ መነጋገርና ትችቱ ለአዎንታዊ ጥቅም መዋሉ አይቀሬ ነውና የመጨረሻ ውጤቱ ለለውጥ ያለው አስተዋጽኦ ሊታመን ይገባልና ይህንን ልምድ ለማስቀረት መትጋት ይኖርብናል ፡፡

ከተከባበርን፣ከተደማመጥን፣ ከተስማማንና ከተባበርን…ማለትም ወደዚህ ለመለወጥ ፈቃደኝነቱ፣ ቆራጥነቱ… ካለን የጋራ ዓላማ በግልጽ እንቀርጻለን፣በጋራ እንቆምለታለን፣ በጋራ ከምንፈልገው ግብ አብረን እንደርሳለን- አገርን ከጥፋትና አደጋ፣ ህዝብን ከሥቃይና መከራ እንታደጋለን ፡፡ ለዚህ ደግሞ ቀጣይ ትግላችን በነጠረ ዓላማና በህዝባዊ መሰረት ላይ የቆመ/የተገነባ እንጂ በግለሰቦች ላይ የተንጠለጠለ ሊሆን አይገባም፡፡ መሪዎች የሚወጡት ከህዝብ ውስጥ እንደመሆኑ ህዝብን አደራጅቶ የትግሉ አካልና ንቁ ተዋናይ የማድረግና ለዚህም ወደ ህዝቡ ተደራሽነታችን የማስፋት ተግባራት ከፊታችን ይጠብቁናል ማለት ነው፡፡

5.2.3. በቀጣዩ ምርጫ መሳተፍ/አለመሳተፍ እና የጋራ ጥያቄዎች/ቅድመ ሁኔታዎችን መለየት፤

ከዚህ በፊት በ33ቱ የደረስንበት ድምዳሜና ያቀረብናቸው ጥያቄዎች ለዚህ መሰረት ይሆኑናል፡፡ ከነዚህ ጥያቄዎች መቅረብ በኋላ ምርጫ 2005 ተካሂዶ በርካታ መረጃዎችና ማስረጃዎችን በመንተራስ ያወጣነው መግለጫም አለን፡፡ በተጨማሪ ከዚያ በኋላ ከምርጫ ጋር የተገናኙ በገዢው ፓርቲ የተወሰዱ ኢዲሞክራሲያዊ እርምጃዎች በርካታ ናቸው- የፓርቲ አመራሮች እሥራት፣ የነጸው ፕሬስ መዘጋትና የጋዜጠኞች እስራትና ስደት፣…፡፡ ስለዚህ እነዚህን በማገነዘብና ማካተት የጋራ አቋም ለመውሰድና በጋራ ጥያቄ ለማቅረብ ይቻላል ማለት ነው፡፡

5.2.4. የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ባለድርሻነት የተቀበለ አሳታፊ የነጠረ አገራዊ የመግባቢያ ኃሳብ ማመንጫ ብሄራዊ የውይይት መድረክ፤

5.2.4.1. ኢህአዴግን ጨምሮ—–ላለንበት ተጨባጭ ሁኔታ የሚመጥን ዘላቂ መፍትሄ የሚሰጥና የሥርዓት ለውጥ ለማምጣት የሚችል አንድም ፓርቲ የለም፣ ከጥላቻና ጠቅላይ የዜሮ ድምር ፖለቲካ(አሸናፊ/ተሸናፊ) አዙሪት እንውጣ ካልን ከአግላይነት ለመራቅ ብቻ ሣይሆን ለገዢው ፓርቲ የማሰላሰያ ጊዜና ወደውስጥ የመመልከት ዕድል መስጠትም ስለሚያስፈልግ ሁሉን አቀፍ የብሄራዊ መግባባትና ዕርቅ ጉባኤ መጥራት ፣ማዘጋጀት፤
5.2.4.2. ኢህአዴግ እምቢተኛ ከሆነ– ሠላማዊ የፖለቲካ ኃይሎች፣ሲቪክ ማኅበራት፣የኃይማኖትና የማኅበረሰብ መሪዎች፣ተጽዕኖ ፈጣሪና ታዋቂ ግለሰቦች….. (እንደ 86 የሠላምና ዕርቅ ጉባኤ ሆኖ በነጠረ የሚተገበር ኃሳብ ላይ) የሚወያይ ብሄራዊ የሠላምና ዕርቅ ጉባኤ መጥራት፣ማዘጋጀት፡፡

6. ማጠቃለያ፡-

ይህ ሰነድ ከላይ ለተቀመተው ዓላማ የተዘጋጀና በተጠቀሱት ሂደቶች ያለፈ እንደመሆኑ ለቀጣይ የጋራ ትግላችን እንደ አቅጣጫ አመላካችና ማጣቀሻ ሰነድ ሆኖ ያገለግላል፡፡ከላይ ባስቀመጥናቸው ዘላቂ ስትራቴጂክ ሁለት አማራጮች ላይ የሚደረገው የማጥራት ተግባራትና ለወቅታዊው የምርጫ 2007 ያስቀመጥነው መፍትሄ የሚሄዱና የማይጋጩ/የማይጣረሱ በመሆናቸው የተጀመረው ሂደት ለሁለቱም ውጤቶችና ለዘላቂው ግብ ጎን ለጎን ይሰራል ማለት ነው፡፡ ለዚህም ለስትራቴጂክ ግቦች የሚሰራ አንድ ቋሚ ኮሚቴና በምርጫ ጉዳዮች ላይ የሚሰራ ሌላ ኮሚቴ በስምምነት ሰነዱ መሠረት ይዋቀራሉ፡፡

 

hands holding each other in unity

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.