አሜሪካ ስለ ህወሃት – “እጃችንን ብናነሳ በህይወት አይኖሩም”

በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ

woyane-3456-saytenaw-newsአሁን አሜሪካኖቹ እያመረሩ ነው” የሚለው ዜና አየሩን ወጥሮታል። በተለይም የኦባማ አስተዳደር ለኢህአዴግ/ህወሃት የጻፈው የከረረ ደብዳቤና ትዕዛዝ ለአገዛዙ የመቀመጫ ላይ ቁስል ሆኖበታል። ለዚህም ይመስላል ሃይለማርያም ሳይፈልጉ መለስን እንዲሆኑ ታዝዘው አሜሪካንን ወርፈዋል። ይኸው የሃይለማርያም ዘለፋ ያበሳጫቸው የስቴት ዲፓርትመንት ኃላፊዎች “ሰዎቹ ከማን ጋር እንደሚያወሩም አያውቁም። ደቡብ ሱዳን መሰልናቸው” ማለታቸውን የመሰክሩ ለጎልጉል ገልጸዋል። ይህንኑ ተከትሎ ሃይለማርያም ደሳለኝ ባስቸኳይ አሜሪካ እንዲመጡ ታዝዘዋል።

በወቅታዊው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ቀውስ ዙሪያ የአሜሪካ መንግስት ከህወሃት/ኢህአዴግ ጋር እያደረገ ያለውን ግንኙነት በቅርብ የሚከታተሉና በቂ መረጃ ያላቸውን በመጠቀስ የጎልጉል የአሜሪካ ዜና አቀባይ እንደዘገበው፣ የኦባማ አስተዳደር የጻፈው ደብዳቤ ሃይለማርያምን አደባባይ ወጥተው (“ፓርላማ” በተባለው የኢህአዴግ ም/ቤት) እንዲዘላብዱ አድርጓቸዋል።

“ግድያ አቁሙ፣ ማስተካከል የሚገባችሁን አስተካከሉ” የሚል ቁልፍ መልዕክት የያዘው ይህ የኦባማ አስተዳደር ደብዳቤ የአገዛዝ ለውጥ (regime change) እስከማድረግ የሚጠይቅ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል። ይህ ህወሃትን የጎመዘዘው ደብዳቤው ከመጻፉ በፊት በተለያየ ደረጃዎች ባሉ ባለሥልጣናትና አዲስ አበባ ባለው ኤምባሲ አማካይነት ህወሃት ከያዘው መንገድ እንዲታቀብ ሲጎተጎት እንደነበር የሚታወስ ነው።

በዚሁ መነሻ ሳይፈልጉ መለስን ሆነው መግለጫ እንዲሰጡ በህወሃት የታዘዙት ሃይለማርያም “ሪዢም ቼንጅ/አገዛዝ ለውጥ ይሉናል/” ሲሉ ስምና አገር ሳይጠቀሱ ተዛልፈዋል። የኢትዮጵያ ህዝብ ብቻ በራሱ በአገሩ ፖለቲካ ወሳኝ እንደሆነ ያወሱት ሃይለማርያም “በገንዘብ ድጋፍ” ዙሪያ ከደሰኮሩ በኋላ የገንዘብ ድጋፍ በመስጠት የአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ገብቶ መፈትፈት እንደማይቻል “መለስን ሆነህ ተናገር” በተባሉት መሰረት ተጽፎ የተሰጣቸውን የሚችሉት ያህል ስሜታዊ ሆነው ተናግረዋል።

ልክ መለስ በ97 ምርጫ ወቅት እንዳደረጉት፣ ሃይለማርያምም ኢህአዴግ አሁን  ካለበት በአፍሪካ የሰላም ማስከበር ተግባር ራሱ ሊያቅብ እንደሚችልና፣ ከሶማሊያ ዘመቻ ጦሩን እንደሚያስወጣ አስጠንቅቀዋል። ህወሃት ችግር ሲገጥመውና የአንጋሾቹ ፊት ሲጨማደድበት “የምስራቅ አፍሪካን ክልል ለአልሸባብ አሳልፌ እሰጣለሁ” እያለ ሲያስፈራራና ሲነግድ የኖረ ቢሆንም አሁን አሁን ግን ዛቻው የራሱን ገመድ የሚያሳጥር እየሆነ እንደሆነ ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት።

የሰላም ማስከበር “ዘመቻ እልል በቅምጤ” ለህወሃት አንድ የንግድ ኢምፓየሩ ነው። ብዙዎች እንደሚያውቁት በዚህ ዘመቻ የህወሃት ጄኔራሎች ዶላር ያፍሳሉ። በዶላር አበል ስለሚምነሸነሹ ምደባ ላይ እንኳን አይስማሙም። ቅሬታ የተፈጠረበት ጊዜም ጥቂት አይደለም። ለዚህም ሲባል ነው በየጊዜው ከፍተኛ መኮንኖች ቶሎ ቶሎ እየተፈራረቁ ከጸበሉ እንዲቋደሱ የሚደረገው።

እ.ኤ.አ. 2010 መጨረሻ ላይ በሰላም ማስከበር ላይቤሪያ ደርሰው የተመለሱ የሠራዊቱ አባላት “በውጭ ምንዛሬ ሲከፈለን የነበረው ገንዘባችን ሙሉ በሙሉ ይሰጠን” በማለት መሳሪያ በማንሳት ኮማንዶ የምትባል ከተማ ላይ የጎጃምን መንገድ ቆርጠው መደራደራቸውን የሚያስታውሱ ወገኖች፣ ከሰላም ማስከበሩ ስራ የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ ጥቅም ቀላል ባለመሆኑ “ተውት” ቢባሉ የህወሃት ጄኔራሎች እና የጥቅሙ ተቋዳሾች ለቅሶ እንደሚቀመጡ ብዙዎች ይስማማሉ። ከተራው ወታደር በስተቀር!!

ይህንን በመረዳት ይመስላል የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት /የስቴት ዲፓርትመንት/ ሰዎች “የአሜሪካንን ጥቅም ማስጠበቅ የሚችለው ህወሃት ብቻ አይደለም” ሲሉ የተደመጡት። አሁን አሜሪካ እየያዘች ያለውን አቋምና ከህወሃት ጋር እያደረገች ያለቸውን ግንኙነት በቅርብ የሚያውቁት መረጃ አቀባያችን “አሁን አሜሪካኖቹ የእኛን ጥቅም ማስጠበቅ የሚችሉ ሌሎች ኢትዮጵያዊያኖች አሉ” በማለት ከፍተኛ ባለስልጣናት መናገራቸውን ያስረዳሉ። ይህም ለዓመታት በተቃዋሚው ወገን ሲወተወት የነበረው ተፈጻሚነት የሚያገኝበት ደረጃ ላይ መድረሱን ያመላከተ ነው፡፡

መለስ በG-20 ስብሰባመለስ በG-20 ስብሰባ

አያይዘውም አንድ ከፍተኛ የስቴት ዲፓርትመንት ባለስልጣን በመገረም የተናገሩትን ይጠቅሳሉ። ህወሃት በሃይለማርያም አማካኝነት አሜሪካ እጇን ከኢትዮጵያ ላይ እንድታነሳ ይህ ካልሆነ ደግሞ ጠቅልሎ ከሶማሌ እንደሚወጣና በአፍሪካ የሰላም አስከባሪ ተግባሩን እንደሚያቆም ማስጠንቀቁን አስመልከቶ ባለስልጣኑ “እኛ የደቡብ ሱዳን ዓይነት መንግስት መሰልናቸው እንዴ?” ብለው ይጠይቁና አያይዘውም “እነሱ ከሶማሌ ቢወጡ እኛ አንሞትም። እኛ ግን እጃችንን ብናነሳ እነሱ ህይወታቸው አይኖርም፣ ሥልጣናቸውም በቀናት ውስጥ ታሪክ ይሆናል” ሲሉ የአሜሪካን ትዕግስት ወደ መገባደጃው መድረሱን የሚጠቁም አስተያየት ሰጥተዋል። ጉዳዩ የሸክላ ድስት ከብረት ድስት ጋር ያደረገውን አይነት ጸብ ተደርጎ ተወስዷል።

አንድ የመለስ የቅርብ ወዳጅ የሆኑ ከፍተኛ ዲፕሎማት “መለስ ይታዘዘና፤ መለስ አድርግ የተባለውን ያደርጋል፤ መለስ አያስቸግርም፤ መለስ ይሰማናል፤ እነዚህ አይሰሙም፤ ማድረግ ያለባቸውንም አያውቁም” ሲሉ ተማርረው ሲናገሩም ተደምጠዋል። እነዚህኞቹም ሆነ መለስ ተላላኪ ስለመሆናቸው ጥያቄ ባይነሳም፣ በመላላክ አንዳቸው ከሌላቸው የሚለዩበት ነገር ባይኖርም አሁን መካረሩ የመጣው “ልቀቁ” እስከማለት በመደረሱ እንደሆነ ለድርጅቱ ቅርበት ያላቸው ይናገራሉ።  ሌላ አንድ ጡረተኛ፣ ነገር ግን ተጽዕኖ ፈጣሪ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ዲፕሎማት “የወያኔ ነገር አሜሪካኖች ጉንጭ ውስጥ እየጎመዘዘ ሄዷል” ሲሉ ተደምጠዋል። እኚሁ ሰው በቅርቡ ወቅታዊውን የኢትዮጵያ ጉዳይ በተመለከተ ለአሜሪካ ምክርቤት የቀረበው ጠንካራ ረቂቅ ሕግ (H.Res.861) የሚጽድቅበት ጊዜም ሩቅ እንደማይሆን አመልክተዋል።

አሜሪካኖቹ ስራቸውን የሚሰራሉላቸው ሌሎች አካላት እንዳሉ መግለጻቸውን ተከትሎ ሃይለማርያም አሜሪካ መጥተዋል። ፋና የሚሰኘው የስርዓቱ አንደበት መስከረም 11 ቀን 2009 ግርማ ብሩን ጠቅሶ እንዳለው “ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ኃላፊ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድና ኧንደር ሴክሬተሪ ሻነን ስሚዝ ጋር መወያየታቸው” ይፋ አድርጓል።

smith3እንደ ፋና ወሬ የውይይቱ አንኳር ጉዳይ በምስራቅ አፍሪካ ዘላቂ ሰላም ለመፍጠር በሚቻልበትና የኢትዮጵያ ሚና በሚጠናከርበት ሁኔታ ላይ መሆኑን፣ በውይይቱ  በተለይ በሶማሊያም ሆነ በደቡብ ሱዳን አገሮች ውስጥ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ በኢህአዴግ ስም ሃይለማርያም ቃል ገብተዋል። “ጦራችንን ከሶማሊያ እናስወጣለን፣ ከሰላም ማስከበሩ ስራ ራሳችንን እናገላለን” ብለው በፎከሩ በቀናት ልዩነት ጌቶቻቸው ደጅ ደርሰው መሃላ መፈጸማቸው ከላይ የተባለውን ዜና የሚያጠናክር ሆኗል።

“በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረውን ግጭት” በማለት አሁን ሰላም እንዳለ በማስመሰል የፕሮፓጋንዳ ዜና የዘገበው ፋና፣ ችግሩን ለመፍታት እየተደረገ ስላለው ጥረትና የግጭቱን መንስኤ በመለየት የተለያዩ የመፍትሄ እርምጃዎች እየተወሰዱ እንደሆነ ስለመብራራቱ ችግሩን የእግረመንገድ አስመስሎ አቅርቦታል።

የጎልጉል የመረጃ ሰዎች እንዳሉት ግን ሃይለማርያም ደሳለኝ ታጋይ ጀኔራልና የህወሃት ሰዎች እየመሯቸው ወደ አሜሪካ ባስቸኳይ የመጡት እንደተባለው ለተባበሩት መንግሥታት ስብሰባ ብቻ ሳይሆን እንዲመጡም ታዝዘው ነው። ዋናው ጉዳይ “ከፓርላማው ፉከራ” ማግስት ቀደም ሲል በደብዳቤ የተገለጸላቸውን ጉዳይ እንዲቀበሉ ሲሆን በተደረገውም ውይይት አድርጉ የተባሉትን እንደሚያደርጉ ቃል መግባታቸው የግድ ይሆናል።

meles isayasህወሃትን የመሰለ የወንበዴ ቡድን እንደ ኢትዮጵያ ዓይነት አገር እንዲመራ ቀይ ምንጣፍ አንጥፈውና አበባ ጎዝጉዘው ከሥልጣን መንበር ላይ ያስቀመጡት ምዕራባውያን በተለየም አሜሪካኖች ናቸው፡፡ አሁን ደግሞ ከሕዝብ ጋር እንደወገኑ በማስመሰል ህወሃትን የማይሰማ፤ የማይታዘዝ እያሉት ይገኛል፡፡ እንደ ክሪስ ስሚዝ ዓይነት ጥቂት የአሜሪካ ፖለቲከኞች በስተቀር አብዛኛዎቹ በሹመት የመንግሥት ባለሥልጣናት የሆኑቱ የኢትዮጵያን ጉዳይ ለህወሃት ሙሉ በሙሉ አሳልፈው የሰጡ ናቸው፡፡ የአዛዥና ታዛዥ ግንኙነቱም ከበረሃ የጀመረ መሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ለኢትዮጵያውያን ሁሉ እያደር የእግር እሳት ሆኖ ያለፈውን የ1997 ምርጫ ተከትሎ ወደ ኢትዮጵያ በማምራት ከመለስ ጋር በርካታ ዲፕሎማቶችና የአሜሪካ ሕዝብ ተወካዮች ተነጋግረዋል። ከእነዚህ አንዱ አሁን ረቂቅ ሕግ (H.Res.861) በመጻፍ ቀዳሚ የሆኑት ከኒውጀርሲ ጠቅላይግዛት የአሜሪካ ም/ቤት ተወካይ ክሪስ ስሚዝ ናቸው። የዛሬ ሦስት ዓመት “ኢትዮጵያ ከመለስ በኋላ” በሚል የተዘጋጀ የምክክር ሸንጎ በመሪነት ሲከፍቱ መለስን “አሮጋንት /እብሪተኛ/፤ የፈለገውን ነገር በፈለገው ጊዜ የሚያደርግ ሰው …” በማለት ነበር የገለጹዋቸው። የርሳቸው ገለጻ ታዲያ ከ25 ዓመታት በፊት ኢህአዴግ እንዲነግስ ሲወሰን ከቃል በላይ እሳት እየተፉ ንግግር ያደረጉትን ኢትዮጵያዊ ያስታወሰ ነበር – የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኮ/ሎ ጎሹ ወልዴ!

goshu“… ሆን ተብሎ በተቀነባበረ ዕቅድ ህወሃት አዲስ አበባን እንዲቆጣጠር የተወሰነው ውሳኔ አሳዛኝና ከቶውንም ሊታመን የማይችል ነው። የሰከረ ርዕዮት ዓለም የሚከተሉ፣ በብሄርና በጎሳ ፖለቲካ ላይ የተተከሉ ጠባብ ቡድኖች፣ በስታሊናዊ መርህ የተጠመቁ፣ እንኳንስ 50 ሚሊዮን ህዝብ ያላትን አገር ቤተሰብን የመምራትና የማስተዳደር ተሞክሮ የሌላቸው፣ አገርን መምራትን የሚያክል ታላቅ ሃላፊነት ማሸከም ለኔ ከአእምሮ በላይ ነው …” ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ የትንቢት ያህል፤ ሳግ እየተናነቃቸው የኢትዮጵያን ተላልፎ መሰጠት የተናገሩት ታሪካዊ ንግግር ልዩ ሰነድ ሆኖ የተቀመጠላቸው ነው።

ከ25 ዓመታት በኋላ ብዙ ለውጦች ተካሂደዋል፡፡ በቢል ክሊንተን “የህዳሴ መሪዎች” ተብለው የተሞገሱት የምስራቅ አፍሪካ “ቆንጆዎች” ምርጥ አምባገነኖች ሆነዋል። መለስ ሞቷል፤ ኢሣያስ ነትቧል፤ ካጋሜና ሙሴቪኒ ቀናቸው ተቆጥሯል፡፡ የዛሬ 25ዓመት የነበረው ሙዚቃ “ሬዢም ቼንጅ” ነበር፡፡ ቅጂው ግን በካሴት ነበር፡፡ ዛሬም ሙዚቃው ያው ይመስላል፤ ያሁኑ ቅጂ ግን ዲጂታል ይሆናል፡፡