የተቋውሞ ሰልፎችና የሻማ ማብራት ዝግጅቶች በተለያዩ የጀርመን ከተሞች ተካሄዱ

ለተጠናከረው  ዘገባ ከጀርመን

angela-merkel-and-haile-mariam-desalegn-satenaw-newsበጀርመን አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዛሬ በቀን 14/ 1 / 2009 ( 24 September 2016) በተለያዩ ከተሞች የወያኔን መንግስት በመቃወምና በዚሁ  አገዛዝ የቅጥር  ወታደሮች በግፍ ህይወታቸውን ያጡትን ንጹሃን ኢትዮጵያውያን በማሰብ ሰላማዊ  ሰልፍና የሻማ ማብራት ፕሮግራሞችን አካሂደዋል። በቩዝበርግ ( Würzburg) በምትባል የጀርመን ከተማ ዛሬ ኢትዮጵያውያን ወደ አደባባይ በመውጣት ወያኔን አውግዘዋል።  ይህ ሰላማዊ ሰልፍ በአይነቱ ለየት የሚያደርገው  ጀርመናዊ የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ድርጅት  ተወካይ  እንዲሁም በጀርመን የአምንስቲ ኢንተርናሽናል ተወካይ ከኢትዮጵያውያን  ጎን በመቆም በሰልፉ መታደማቸው  ነበር። ከቩዝበርግ ዋና የባቡር ጣቢያ  መነሻውን ያደረገው  ይህ የተቋውሞ  ሰልፍ   በመዘጋጃ ቤቱ ፊት ለፊት የሻማ ማብራት ፕሮግራም በማድረግ አብቅቷል።

በሰላማዊ  ሰልፉ ላይ የተለያዩ መፈክሮች  በአማርኛ  በጀርመንኛ በኦሮምኛ እንዲሁም በእንግሊዘኛ ሲስተጋቡ ተደምጠዋል። ከነዚህም ውስጥ:

– እኛ  ኢትዮጵያኖች አንድ ነን

– የኦርሞ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ደም ያመናል

-አሽባሪ ወያኔ ኢህአዲግ እንጂ የኢትዮጵያ  ህዝብ አይደለም

-ህውሃት እና ዘረኝነት አብረው ይቀበራሉ

-ጠላታችን ህውሃት እንጂ የትግራይ ህዝብ አይደለም

-የሰውን መብት ከሚረግጥ መንግስት ጋር ትብብር  ይቁም

-ካንስለር አንጌላ መርክል ወደ ኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ይሰርዙ ወዘተ ይገኙበታል።

በዚሁ ከተማ የሰብአዊ መብት ተከራካሪ  የሆኑት (Mr Brukard Hose) ለሰልፈኞቹና  ሰልፉን በአግርሞት ሲከታተሉት ለነበሩት የጀርመን ዜጎች ባደረጉት  ንግግር  የወያኔ መንግስት ኢትዮጵያ ውስጥ  ከፍተኛ  የመብት ረገጣ  የነፍስ መግደል  ያለአግባብ  ንጹሃን  ሰዎችን የማሰር የማሰቃየት ወንጀል እየፈጸመ  እንደሆነ ገልጸዋል። በተጨማሪም  የፕሬስ ነጻነት በኢትዮጵያ  እንደሌለ እንዲሁም ጋዜጠኞች የፖለቲካ መሪዎች በእስር ላይ እንደሚገኙ  በጀርመንኛ  ባደረጉት ንግግራቸው  ገልጸዋል። የወያኔ መንግስት  በኢትዮጵያውያን ላይ እየፈጸመ  ያለውን ግፍ የጀርመን  ነዋሪዎች  ሚዲያዎች እንዲሁም የጀርመን መንግስት በአጽኖት መመልከት እንዳለባቸው  አሳስበዋል። “ኢትዮጵያ  ውስጥ የሚደረገው የመብት ረገጣ  እኔንም ስለሚነካኝና  ስለሚያገባኝ  ዛሬ በዚሁ የተቋውሞ ሰልፍ ላይ እናንተን  አጅቤ ታድሚያለሁ። ሰዎች መብታቸውን በመጠየቃቸው  ምክንያት በአምባገነኖች የሚገደሉ የሚታሰሩ ወይም ከአገራቸው የሚሰደዱ  ከሆነ በርግጥም  እንደ ግል ጉዳዬ በቀጥታ ሰለሚያገባኝ  ከእናነተ ጎን ቆሚያለሁ።”  (Mr Brukard Hose)

 

በጀርመን የአምንስቲ ኢንተርናሽናል ተወካይ የሆኑት (Frau Holthoff) በበኩላቸው ለታዳሚው  ይህንን  አምባገነናዊነትን የመቃወም እንቅስቃሴ  እንዳያቃርጥ አጥብቀው  መልክታቸውን አስተላልፈዋል። በንግግራቸውም  የጀርመን መንግስት በኢትዮጵያ ውስጥ እየተፈጸመ ያለውን የመብት ጥሰት እያየ እንዳላየ በማለፉ ታዳሚውን ይቅርታ  ጠይቀዋል። የሰውን ልጅ መብት በኢትዮጳያ ለማስከበር በሚደረገው ማንኛውም አይነት እንቅስቃሴ ሙሉ ድጋፋቸውን  እንደሚያደርጉም ቃል ገብተዋል። ነጻነታችሁን እስትጎናጸፉ ድረስ ትግላችሁን እንዳታቆሙ የሚል መልክት ድጋሜ ለታዳሚዎቹ በማስተላለፍ የአምንስቲ ኢንተርናሽናል ተወካይዋ ንግግራቸውን ፈጽመዋል።

 

ከሰልፉ አዘጋቾች አንዱ የሆኑት አቶ ግሩም ወርቁም  ወያኔን የመቃወም  እንቅስቃሴዎች ወደፊትም በሰፊውም እንደሚቀጥሉ  በማሳወቅ ለተመሳሳይ ጥሪዎች በጀርመን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ትብብርና አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ጥሪ አስተላልፈዋል። የዚህ  ፐሮግራም አስተባባሪ ከሆኑት መካከል አቶ አባይ ኪሮስ  በጀርመን የሚኖሩ  ኢትዮጵያውያን በወያኔ  አገዛዝ እየተፈጸመ  ያለውን  አረመናዊ ድርጊቶችን  በመቃወም ሊደረጉ በታሰቡ  ዝግጅቶች  ላይ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።  የጀርመን መርሃ መንግስት ካንስለር አንጌላ መርክል ወደ ኢትዮጵያ ሊያደርጉት ያቀዱትንም  የስራ ጉብኝት እንዲሰርዙ የፔትሽን ፊርማ በሃላፊነት ሲመሩ የነበሩት አቶ ሙሉጌታ  መርፌ ወያኔ ስልጣኑን  ለህዝብ እስከሚያስረክብበት ጌዜ ድረስ  ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ያለመሰልቸት ከፍተኛ ግፊት ማድረግ እንዳለባቸው  ገልጸዋል።

 

በተያያዘ ዜናም  በጀርመን ፍራንክፈርት ከተማ ኢትዮጵያውያን ወያኔ ያለ ርህራሄ የጨፈጨፋቸውን ኢትዮጵያውያንን በማሰብ የሻማ ማብራት ፕሮግራም በማዘጋጀት  አስበው  ውለዋል። በተጨማሪም  የጀርመን መርሃ መንግስት ካንስለር አንጌላ መርክል ወደ ኢትዮጵያ ሊያደርጉት ያቀዱትንም  የስራ ጉብኝት ተቃውመዋል። ተመሳሳይ የተቃውሞና  የሻማ ማብራት ፕሮግራሞች ኑረንበርግ በምትባል የጀርመን ከተማ ባለፈው ሳምንት ኢትዮጵያኖች አድርገዋል።

By Zerihun Shumete/ from Germany