ዘር ማጥፋት (genocide) ተጀምሯል [ታምሩ ፈይሳ]

መስከረም 2009 ዓም

ታምሩ ፈይሳ

tplf-satenaw-news-5667በነሐሴ መጨረሻ ላይ አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ባደረገው ንግግር፣ ኢህአዴግ ስህተት መፈጸሙን ይጠቅስና፣ የእርምት እርምጃ ሊያቀርብ ነው ተብሎ ሲጠበቅ፣ ‘የፀጥታ ኃይሎች ህግ እንዲያስከብሩ’ ሙሉ ትዕዛዝ ሰጥቻለሁ አለ። በጠቅላይ ሚንስቴሩ ትርጓሜ፣ ህግ ማስከበር ማለት፣ ዜጎች በህገ መንግስቱ የተሰጣቸውን መብት በስራ መተርጎም የሚችሉበትን ሁኔታ መገደብና መከልከል ማለት ነበር። ድምጻችን ይሰማ፣ መብታችን ይከበር ብለው የተነሱ ዜጎች እገሌ ከእገሌ ሳይል እንዲታሰሩ፣ እንዲገደሉ መፍቀድ ማለት ነበር። ይህ ትዕዛዝ በተለይ ትኩረት ያደረገውና ያነጣጠረው በአማራው ላይ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ለሶስተኛ ጊዜ ዘር የማጥፋትና የጅምላ ግድያ ፖሊሲ ተቀርጾ በስራ ላይ የሚውልበት ሁኔታ ተመቻቸ። የመጀመሪያው በኢጣሊያን ጊዜ ሲሆን፣ ሁለተኛው በደርግ ዘመን ነበር።

ዘር የማጥፋት ሕግ እአአ ታህሳስ 9 በ1948 ዓም ፀድቆ፣ ከጥር 12 ቀን 1951 ዓም ጀምሮ ተፈጻሚ ሆነ። Convention for the Prevention of the Crime of Genocide በመባል የሚታወቀው የዚህ ህግ አንቀጽ 2 የዘር ማጥፋት ወንጀል ትርጉም ምን እንደሆነ ይገልጻል። “Genocide is a crime of intentional destruction of a national, ethnic, and religious group, in whole or in part”.

(ትርጉም፡ ‘የዘር ማጥፋት ወንጀል’ (genocide) ይሁነኝ ተብሎ በብሄር፣ በዘር እና በሃይማኖት ቡድን ላይ በጅምላ ወይም በከፊል የሚደረግ የማጥፋት ወንጀል ነው።)

ከላይ የተጠቀሰው ሕግ ከመውጣቱ በፊት በቱርክ፣ በአሜሪካና ሌሎች አገሮች የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈጽሟል።

ዘር የማጥፋት ትዕዛዙ ትርጉምና እንድምታ

በኢትዮጵያ የዘር ማጥፋት ፖሊሲው እንዲወጣ ግድ ያለው፣ የ25 አመት የስልጣን ዘመኑ እያከተመለት መሄዱን ወያኔ መገንዘቡ ሲሆን፣ መርዶ ነጋሪ ሂደቱም በአማራና በኦሮሞዎች መሀል የመቀራረብ፣ ብሎም የትግል አጋርነት ይፋ መሆኑ ነበር። የወያኔ አገዛዝ መሰረት የሆነው የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ፣ በፖለቲካ ልሂቃን ወይም መሪዎች ሳይሆን፣ ለተቃውሞ አደባባይ በወጡ ወጣቶች ተናደ። ‘ለ25 አመታት ያህል ከፋፍለህ ገዝተኸናል፣ መከፋፈል ይብቃ’ አሉ ወጣቶች። አደባባይ የወጡ የጎንደር ወጣቶች። የሚፈሰው የኦሮሞ ደም ደማችን፣ በቀለ ገርባም መሪያችን ነው አሉ። ‘ለ25 አመታት ተደቁሰናል፣ ተዋርደናል፣ ተንቀናል፣ ማንነታችን መከበር አለበት፣ ያበጠው ይፈንዳ፣ ኦሮማይ!’ አሉ ወጣቶቹ። ስልጣን ለመልቀቅ አንዳችም ፍላጎት ሆነ ዝግጅት ያላደረገው ወያኔ ብርክ ያዘው፣ በመብረቅ የተመታ ያህል ደነገጠ። የፖለቲካ ድርጅቶቹ ለመተባበር እንኳን እያቅማሙ ባለበት በዚህ ወቅት፣ የጎንደር ወጣቶች ሲዘከር የሚኖር ታሪክ ሰሩ። ያን ታሪክ ለመስራት መሪም ሆነ መመራመርና መፈላሰፍ አላስፈለጋቸውም። ኑሮ አስተምሯቸዋልና!። የ25 አመት የህወሃት የግፍና የቅጥፈት ዘመን!

የኃይለ ማርያም ደሳለኝ ትዕዛዝ፣ በጎጃምና በጎንደር በሚገኘው የአማርኛ ተናጋሪው ሕዝብ፣ አለፍ ሲልም በአማራው፣ በአጠቃላይም በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ያነጣጠረ ነው። የጠ/ሚንስቴር ተብዬው ፖሊሲ ጽንፈኛ ባላቸው ግለሰቦች ላይ ያነጣጠረ ነው ቢባልም፣ ሕዝቡ በነቂስ በተነሳበትና ማን ከማን ሊለይ በማይችልበት ሁኔታ ትዕዛዙ ያታኮረው በመላ የአማራው ሕዝብ ላይ በመሆኑ፣ የዘር ማጥፋት ድርጊት እንጂ ከቶ ሌላ ነገር ሊሆን አይችልም።

የዚህ የዘር ማጥፋት ፖሊሲ መቀረጽ፣ በኢህአዴግ ዙሪያ አሉ ከሚባሉት ኃይሎች መሀል አንዱ፣ የመከላከያና የፀጥታው፣ አድራጊና ፈጠሪ ሆኖ ብቅ ማለቱንና የበላይነት መያዙን ያመላክታል። በሌላ አነጋገር፣ ኢህአዴግ እንዳበቃለት ኢትዮጵያም በእነ ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል እና በሳሞራ ዩኑስ እንደምትገዛና ወታደሩ ኮሽታ ሳያሰማ መፈንቅለ መንግስት ማካሄዱን ይጠቁማል። ኢህአዴግ ጭምብሉ ብቻ እንደቀረና ተገንዞ ሊቀበር እንደተሰናዳ ያሳያል። ይህ አዲስ ሁኔታ ውግዘት ስለሚያስከትልና የምዕራቡ ዓለም የእርዳታ ክንዱን እንዲሰበስብ ሊጋብዝ ስለሚችል ይፋ አይደረግም። ኢህአዴግም ፈረሰ አይባልም። ለማስመሰያ ሲባል ስብሰባ አደርጎ ውሳኔዎች ላይ ደረሰ ተብሎ ሊነገርና ሊዘገብ ይችላል። እነ ኃይለ ማርያም ደሳለኝም፣ አይናከሱምና ለማደናገሪያ ሲባል ስልጣናቸው ላይ ሊቆዩ ይችላሉ። ፓርላማውም አይፈርስም። እስካልተቀናቀነ ድረስ ለፖለቲካ ፍጆታና ‘ለልመና’ ሊያገለግል ስለሚችል እንዲቆይ ይደረጋል። በወታደሩና በፀጥታው፣ እንዲሁም ከበስተጀርባ ሆነው ለሚዘውሩት ለእነስብሃት ነጋ እስከታዘዘ ድረስ መመሪያ ተቀባይና አራጋቢ አካል ሆኖ ይቀጥላል። ማለቂያና ማቆሚያ የሌለው የወያኔ ማኪያቬላዊ አሰራርና አገዛዝ!

የወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ጉዳይ አዲስ አይደለም። ያ ሁኔታ ሊመጣ እንደሚችል እነ ጄነራል ፃድቃንን የመሳሰሉ የኢህአዴግ ውስጥ አወቆች ቀደም ሲል ጽፈዋል።

መፈንቅለ መንግስቱ ለምን መደረግ ነበረበት?

በተለያየ ጊዜ ይፋ እንደሆነው፣ የመከላከያ ኃይሉ እንደተቋምም ሆነ ከፍተኛ ሹማምንቶቹ ከፍተኛ ባለሀብቶች ናቸው። ስለሆነም፣ የዚህ ኃይልም ሆነ ከበስተጀርባው ያሉት ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች ዋና ፍላጎት እስከዛሬ ድረስ ያጋበሱትን ሀብትና ጥቅም አስጠብቆ መቆየት ነው። ለእነሱ ሀገር፣ ሕዝብ፣ ኢትዮጵያ ትርጉም የላቸውም። ኢትዮጵያ የምትኖረው የእነሱ ጥቅምና ፍላጎት እስከተሟላ ጊዜ ድረስ ብቻ ነው። ደም ማፈሰስን ኖረውበታል። ደም አፍሰውና ሬሳ ተረማምደው ነው አሁን ያሉበት ደረጃ የደረሱት። ሕዝብ ቢያልቅና ቢተላለቅ ደንታ አይሰጣቸውም። ጥቅማቸውና ፍላጎታቸው እስከተሟላ ድረስ በጀመሩት ለመቀጠል ይሞክራሉ። ካስፈለገም ሕዝቡን ለመከፋፈል፣ ትናንሽ ፍርፋሪ በመወርወር የተጀመረውን ትግልም ሆነ ትስስር ለመበጠስ ይጥራሉ። ሲሳካላቸው ያንን ፍርፋሪ እንኳን መልሶ ለመልቀምና ለመውሰድ ወደኋላ አይሉም።

የድምጽ አልባው መፈንቅለ መንግስት እንድምታ

ህወሃት ስልጣን ከያዘበት ወቅት ጀምሮ ትግርኛ ተናጋሪዎች ቁልፍ የሆኑ የመንግስትና የወታደር ክፍሎችን የያዙ ሲሆን፣ ዛሬ በትግርኛ ተናጋሪዎች የታጀለው ከፍተኛ የወታደር አካል ስልጣን ሙሉ በሙሉ እጁ አስገብቷል። ይህ አካል፣ ጉዳዮችንና ችግሮችን በወታደራዊ መነጽር ብቻ ስለሚመለከት የኢትዮጵያ ችግሮች እየተወሳሰቡ ይሄዳሉ። ይህ ወታደራዊ መንግስት፣

 • ሁለቱ ዋና ዋና የህብረተሰብ ክፍሎች አሁን የጀመሩት መቀራረብ እንዳይቀጥል በመሃላቸው ነፋስ እንዲገባ ያደርጋል። የኦሮሞ እንቅስቃሴ ሲነሳ ሲቀጠቅጠው እንዳልነበረ ሁሉ፣ አሁን አንዳንድ የማስመሰያና መታረቂያ እርምጃዎች እየወሰደ ነው። የኦሮሞ ክልል ከአዲስ አበባ ከሚገኘው ገቢ ተጠቃሚ ሊሆን ይችላል የሚል ሃሳብ እየተንሸራሸረ ነው። አማርኛ ተናጋሪው ሕዝብና ኦሮሞው አብረው የሚኖሩባቸውን ቦታዎች ለኦሮሞዎች በመስጠት የጥቅም ግጭት እንዲቀሰቀስ ያደርጋል። እኒህን መሰል ግጭቶች እንዲነሱ የሚደረጉት አማርኛ ተናጋሪውና ኦሮሞው አብረው በሚኖሩባቸው በቀድሞ የወሎና የሸዋ ክፍለሀገሮች ውስጥ ነው። ከዚህ ሌላ ግን፣ የኦሮሞ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ቦታዎች፣ የኦሮሞ ንብረት የሆኑ ንብረቶች (ባንኮችና የመሳሰሉ ተቋማት) ላይ ጉዳት በማድረስ በአማርኛ ተናጋሪዎች እንደተፈጸመ አስመስሎ ያቀርባል። እነዚህንና የመሳሰሉ ድርጊቶችን ማ እንደፈጸማቸው ውሎ አድሮ ሊደረስበት ቢችልም፣ መጀመሪያ ላይ ግን መደናገር እንዳውም መቃቃር ሊያስነሱ ይችላሉ።

 

በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የሕዝቦች መቃቃርንና መጋጨትን ፖሊሲ አድርጎ የተነሳ መንግስት ቢኖሩ የወያኔ መንግስት ነው። የተለያየ የህብረተሰብ ክፍል መቀራረብ ያስከፋው መንግስት ቢኖር ወያኔ ነው። ነሐሴ ውስጥ፣ የመንግስት ቃል አቀባይ ተብዬው በንዴትና በቁጭት ነበር ስለኦሮሞና አማራ መቀራረብ የተናገረው። ‘አክራሪ’ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮችና የሙስሊሙ ህብረተሰብ እንዴትና ለምን ሊደጋገፉ እንደቻሉም እንቆቅልሽ ሊሆንበት በመቻሉ፣ ችግሩ በቂ ‘የፖለቲካ ስራ ስላልተሰራ የተፈጸመ’ ነው በማለት ነበር የደመደመው። ማለትም፣ ‘በከፋፍለህ ግዛ’ ላይ የተመሰረተው የወያኔ ፖሊሲ በሚገባ ስራ ላይ አልዋለም ማለቱ ነው። የመፈንቅለ መንግስቱ መሪዎች ከሆኑት መሀል አንዱ ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል ባካሄደው ቃለ ምልልስ ተመሳሳይ ሃሳብ ሰንዝሯል። ምናልባትም፣ ቃል አቀባዩ የአለቃውንና የኃላፊውን ሃሳብ ነበር ያስተጋባው።

 • በሁለቱ ታላላቅ የህብረተሰብ ክፍሎች መሀል መፈጠር የጀመረው የመተባበር ሂደት እንዳይቀጥል ለማድረግ፣ ኦሮሞዎች ያነሷቸውን ጥያቄዎች የተቀበለ መስሎ ትግላቸውን ለማርገብ ይሞክራል። በአማርኛ ተናጋሪው ሕዝብ ላይ የጀመረውን የዘር ማጥፋት ሂደትን ግን ይቀጥልበታል።
 • አንቀጽ 39ን መሰረት በማድረግ ኢትዮጵያን ለመበታተን፣ ኢትዮጵያ ሌላው ዩጎዝላቪያ እንድትሆን የሚያስችለውን ዝግጅት ያደርጋል፣
 • የትግራይ ሕዝብ በፍርሃት ከጎኑ እንዲሰለፍ ያለመታከት ጥረት ያደርጋል፣
 • ሃይማኖት ላይ የተመሰረተ መከፋፈል ስር እንዲሰድና ገዝፎ እንዲወጣ የሚቻለውን ሁሉ ይፈጽማል፣
 • አንዳንድ ለራሳቸውና ለጥቅማቸው ብቻ ያደሩ ግለሰቦችን የይስሙላ ሹመት በመስጠት ሕዝብ አሳታፊ ፖሊሲ ያለው ለማስመሰል ይሞክራል፣

እነዚህ ሁኔታዎች፣

 • በፖለቲካ ሂደት እውነተኛ ለውጥ ለማምጣት የሚደረገው ጥረት ሙሉ በሙሉ እንዲያከትም ያደርጋል፣
 • ሁኔታዎች እየበረቱና ቀውሱ አልቆም እያለ ሲሄድ፣ ይህ የወታደር ክፍል፣ አለ የሚባለውን ሕገ መንግስት ሽሮ ሀገሪቱን እንደደርግ ዘመን በአዋጅ ማስተዳደር ይጀምራል፣
 • አሁን እንደሚደረገው ሁሉ፣ የትግራይ ሕዝብ ለመነገጃ ቀርቦ፣ ‘ልትፈጅ ነው’፣ ‘ሊጨርሱህ ነው’፣ ወዘተ እያለ በኢትዮጵያ ሕዝብ መሀል ያለው ግንኙነት እየደፈረሰና እየተበላሸ ይሄዳል። ውሎ አድሮም አብሮ መኖር ይቻላል ወይ የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። ከስርዓቱ ጋር በተሳሰረው የሕዝብ ክፍልና በተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ መሀል ያለው ድርና ማግ እየሰለለ ሄዶ ሊበጠስ ይችላል፣
 • የዘር ፍጅቱ ሳያባራ ይቀጥላል፣ ብዙ ሰው ያልቃል፣
 • ኢትዮጵያ እንደ አንድ አገር ፀንታ መቆየት ላይሆንላት ይችላል። እንደዩጎዝላቪያ ትናንሽ መንግስቶች ይበቅላሉ፤
 • እነዚህ ትናንሽ መንግስታትም ቢሆኑ ሰላም አያገኙም፤ ቀውሱ ሳያባራ ሊቀጥል ይችላል፣
 • በኢትዮጵያ የተነሳው ቀውስ ለጎረቤት አገሮችም ሆነ በአጠቃላይ በአፍርቃ ቀንድ አካባቢ ሊፈጠር ለሚችለው አለመረጋጋት ዋነኛ ምክንያት ይሆናል፣
 • የአክራሪ የሃይማኖት ቡድኖች የሚፈጠረውን አጋጣሚ በመጠቀም ትርምሱ እንዲቀጥል የሚችሉትን ያደርጋሉ፣
 • ሰላም ለመጠበቅ በሚል ሽፋን፣ በተባበሩት መንግስታት አማካይነት የምዕራቡ ኃይል ጣልቃ ይገባል።

የኢትዮጵያ መጻኢ ዕድል አስፈሪ ነው። ገናና የነበረች ይህች አገር፣ ለራሳቸውና ለጥቅማቸው ባደሩ ጥቂት ነውረኛ ግለሰቦች ልትደፈርና ልትዋረድ አይገባም። እነዚህ ግለሰቦች የኢትዮጵያን መቃብር ቆፍረው መቀመቅ ሊሰዷት ተዘጋጅተዋል። ያን ዕድል መስጠት የለብንም። ካደረግነውም ውርደት ነው። ስለሆነም፣ ሽማግሌ/ህፃን፣ ወንድ/ሴት፣ የተማረ/ያልተማረ፣ ሁላችንም ተረባርበን፣ የዘረኞቹን የደብረ ጽዬንን፣ የሳሞራ ዩኒስን፣ የስብሃት ነጋን፣ የዓባይ ፀሃዬን፣ የብርሃኔ ገ/ክርስቶስን፣ የአርከበ ዕቁባይንና ግብረ አበሮቻቸውን እኩይ ዓላማና ስራ ማምከን ይጠበቅብናል። ያን ሃላፊነት ለመወጣት የኢትዮጵያ ወጣቶች ፈር ቀዳጅ ስራ ጀምረዋል። ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችም የየበኩላችንን ማድረግ ይኖርባቸዋል።

ምን ይደረግ?

ዛሬ ኢትዮጵያን የገጠማት ችግር የአማርኛ ወይም የኦሮሚፋ ተናጋሪው ወይም የተወሰነ የህብረተሰቡ ክፍልን ብቻ የሚመለከት አይደለም። ዛሬ ኢትዮጵያን የገጠማት ችግር ከሀገሪቱ ህልውና ጋር የተሳሰረ ነው። በወያኔ ጉያ ተሸሽጎ ያደገው ወታደራዊ ቡድን ኢትዮጵያን እንደ አገር ሊያጠፋት ይችላል። ይህ ወታደራዊ ቡድን፣ ‘እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል’ እንዳለችው እንስሳ፣ ጥቅሙንና ስልጣኑን የሚያጣ ከመሰለው ኢትዮጵያ ብትበተን፣ ሕዝቦቿ ቢያልቁ ደንታ አይሰጠውም።

ወያኔም ሆነ አሁን ስልጣን የያዘው ወታደራዊ ቡድን፣ ባላሰለሰና በተባበረ የሕዝባዊ ትግል መንበርከክ አለበት። ይህ ቡድን ካልተንበረከከ ነገ አገር እንኳን ላይኖረን ይችላል።

ሕዝባዊ እምቢተኝነት

በሕዝባዊ እምቢተኛነት አማካይነት መብታችንን ለማስከበር የሚደረገው ጥረት ሳያሰልስ መቀጠል ይኖርበታል። ያ የትግል ዘርፍ ምን እንደሆነና ሊሆን እንደሚችል ከራሳችን ልምድ፣ በኦሮሞና በአማራ አካባቢ ከተደረጉ እንቅስቃሴዎች ተምረናል። ይህ ትግል ሌላ ሳይሆን ለግፈኛ አገዛዝ አለመገዛትና ነፃነትን መምረጥ ማለት ነው። ለነፃነታችን የጀመርነውን ትግል መቀጠል ይኖርብናል። ሌላ ምርጫ የለንም።

ትግላችን ዘዴ የተላበሰና የጠላትና የወዳጅን የኃይል ሚዛን ያገናዘበ ሊሆን ይገባል። በእርግጥ በተለያዩ የኦሮሚያና የአማራ ክልሎች አደባባይ ጭምር በመውጣት ድምጻችንን ከፍ አድርገን አሰምተናል። አላመች ሲልም ከቤት ባለመውጣት ተቃውሞ አድርገናል። ወገኖቻችን እየተገደሉ፣ በእሳት እየተለበበሉና በጥይት እየተቆሉ ባለበት በአሁኑ ሁኔታ አዲሱ አመት የፈንጠዝያና የደስታ በመሆን ፈንታ፣ ሰከን ብለን የምናስብበትና በስቃይ ላይ የሚገኙ ወገኖቻችንን የምንዘክረበት ሆኗል። ተገቢና ትክክለኛ የትግል አካሄድ ነው። ሌሎች እርምጃዎችም ወስደናል። ሕዝባዊ እምቢተኛነታችን ጉልበት እንዲኖረው፣ መልክ ባለው ሁኔታና ለረዥም ጊዜ እንዲቀጥል ከተፈለገ ብልሃትንና የሰከነ ስልት መጠቀምን ይጠይቃል። አደባባይ ወጥቶ ብሶት ማሰማት ተገቢና አስፈላጊ ቢሆንም፣ የወያኔ ህገ መንግስት ላይ የሰፈረው ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት ለይስሙላና ለማዘናጊያ ሆን ተብሎ የተካተተ በመሆኑ ያንን መሰረት አድርጎ መንቀሳቀስ ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን በተደጋጋሚ አይተናል። ስለሆነም፣ ደረታችንን ለጥይት፣ አንገታችንን ለካራ አሳልፈን መስጠት አይኖርብንም።

ወያኔን ተንተርሶ የተፈጠረው የሳሞራ ዩንስና የደብረ ጽዮን የአፋኝ ቡድን ነፍስ ከማጥፋት፣ ዘር ከመጨረስ፣ ብሎም ሀገር ከመበታተን ወደኋላ ሊል እንደማይችል መረዳት የነገሮች ሁሉ ቀዳሚ እርምጃ ነው። እንደ አበደ ውሻ በመቅነዝነዝ ላይ ያለው ይህ ቡድን፣ እስከዛሬ ያካበተው ሀብት በአንድ ቅጽበት ከእጁ አፈትልኮ ሲሄድ፣ እንኳን በእውኑ በህልሙም ያላሰበው ጉዳይ በመሆኑ፣ ያን ጥቅሙን ለማስጠበቅ ምንም ከማድረግ አይመለስም። አገር አጥፍቶ፣ ሕዝቦችን አተራምሶ፣ አፈራቅቆ፣ አጋጭቶም ቢሆን ሀብቱን እንደያዘ መቆየት ነው ዋና ዓላማው። ስለሆነም፣ ትግላችን ጉልበት እያገኘ እንዲሄድ ስልታዊ በሆነ መቀጠል ይኖርበታል።

ሕዝባዊ እምቢተኝነትና በዘር ማጥፋት ወንጀል ክስ መመስረት

ኢትዮጵያ እጅግ በርካታ የህግ ባለሙያዎች፣ በተለይ አለም አቀፍ ህግ ያጠኑ ምሁራን አላት ብዬ ገምታለሁ። እኒህ ዜጎች ኢትዮጵያንና ዜጎቿን ለመታደግ ከፈለጉ፣ ዋና ዋና የኢህአዴግ ሹመኞች ዘር የማጥፋት ወንጀል እየፈጸሙ በመሆናቸው ለአለም አቀፍ ፍርድ ቤቶች ክስ መመስረት መቻል አለባቸው። ምንም እንኳን የወያኔ ሹመኞቹ የምዕራቡ አለም፣ በተለይም የአሜሪካ ድጋፍ ስላላቸው ለጊዜው ሊነኩ የማይችሉ ሰዎች ቢሆኑም፣ ክስ መመስረቱ በራሱ ትልቅ እርምጃ ስለሆነ ለምናካሂደው ትግል ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል። ግፈኛ ግለሰቦቹ ይሸማቀቃልሉ፣ እንደልባቸው አይንቀሳቀሱም።

ሕዝባዊ እምቢተኝነትና ሕዝባዊ እርቅ

እርቅ ሲባል ሕዝባዊ እርቅ ማለት ነው። ሕዝባዊ እርቅ ከመቼውም ጊዜ በላይ አስፈላጊ የሆነበት ወቅት ቢኖር ዛሬ ነው። ወያኔ በ25 አመት አገዛዙ፣ ሕዝቡን ሲከፋፍል፣ ሲያጣላና ሲያጋጭ ኖሯል። ያ የወያኔ የአገዛዝ ዘይቤ አሁን ከፍተኛ ተግዳሮቶች እየገጠመው ቢሆንም አስተማማኝ በሆነ መንገድ ብሄራዊና አገራዊ እርቅ ይካሄድ ዘንድ፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖትና አንቱ የተባሉ የየህብረተሰቡ ‘መሪዎች’ በዘርም ሆነ በሃይማኖት ሰበብ በሕዝቡ መሀል የተቀረጸው የመጠላላትና የመፈራራት ስሜት እንዲያረብብ፣ ሰፊ የሽማግሌ ስራ ማከናወን ይጠበቅባቸዋል። ይህን መሰል ስራ ቢከናወን ወያኔ ኢትዮጵያን ለማጥፋት የሚያደርገውን ሩጫ በእጅጉ ሊገድብና ሊታደግ ይችላል።

የብሄራዊ እርቅ ጉዳይ ሲነሳ፣ የረባ ሕዝባዊ ድጋፍ የሌላቸው የፖለቲካ ድርጅቶች የስልጣን ተጋሪ እንዲሆኑ ማድረግ፣ ወይም የፖለቲካ ሥርዓቱ ሰፋ ብሎ ሌሎችን ሊያሳትፍ እንዲችል አድርጎ ማወቀር ማለት አይደለም። ያ ቢሆን መልካም ነበር። ይሁንና፣ ላለፉት 15 አመታት በተደጋጋሚ ተሞክሮ፣ በወያኔ ተቀባይነት ካለማግኘቱም ሌላ ሲያላግጥበት ቆይቷል። ዛሬ ትኩረቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የስልጣንና የጥቅም ተጋሪ እንዲሆኑ መታገል ሳይሆን ሀገር ማዳንና የተጀመረው የዘር ዕልቂት የሚመክንበትን መንገድ መሻት ነው።

ሕዝባዊ እምቢተኝነትና የመገናኛ ተቋማት

ብዙሐን የመገልገያ መሳሪያዎቹ በወያኔ እጅ ናቸውና ነጋ ጠባ ሊያስፈራሩን፣ እርስ በእርሳችን በጎሪጥ እንድንተያይና እንድንጣላ ሊያደርጉን ይሞክራሉ። ስለሆነም፣ የመጀመሪያውና ቀዳሚ እርምጃው የእነዚህ እኩይና አገር በታኝ ቡድኖችን ፍላጎትና ዓላማ መረዳትና በብዙሐን የመገልገያ ተቋማት አማካኝነት ለሚያስተላልፏቸው  ማናቸውም ጎጂ ሃሳቦችና በመርዝ የተለወሰ ቅስቀሳ ጆሮ አለመስጠት ነው። መርዙ ህዝብ መሀል በመግባት የበለጠ ብጥብጥና ሁከት እንዲሁም መለያየት እንዳይፈጥር፣ የሚመኩበት የመገናኚያ መሳሪያቸውን እናምክነው። ሰሚ እንዳያገኝ እናደርግ። ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ያለው ሕዝብ አናዳምጣችሁም፣ አንሰማችሁም ይበላቸው። የብዙሃን ድርጅቶቻችሁን ታቅፋችሁ ኑሩ፣ ስትፈልጉም ተጠቀሙባቸው ብሎ ሕዝቡ ሊያዳምጣቸው እንደማይሻ ያሳያቸው።

ሕዝባዊ እምቢተኝነትና የሕዝባዊ ሸንጎዎች ምስረታ

ባለፉት በርካታ ወራት፣ በተለይ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የተካሄዱት ትግሎች በታሪካችን ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ሲሆኑ፣ ትግሉ መሬት የረገጠና እንደ አለት ድንጋይ ጠንካራ እንዲሆን፣ በቀበሌ፣ በገበሬ ማህበር፣ በወረዳ፣ በአውራጃ፣ ወዘተ የሕዝቡን ትግል የሚያቀናጁ ስውር የሕዝባዊ ሸንጎዎች መመስረት ይኖርባቸዋል። መጀመሪያ ላይ በአንድ የቀበሌ ወይም የገበሬ ማህበር ከአንድ በላይ የሕዝባዊ ሸንጎዎች ሊፈጠሩ ቢችሉም፣ እነዚህ የተለያዩ አካላትን በውይይትና በመግባባት በጋራ እንዲሰሩና የጋራ አካል እንዲፈጥሩ ማድረግ ይቻላል። ያ ሊሆን ካልቻለም፣ በመመካከር ትግሉን እያቀናጁ ይቆዩና ሂደቱ ራሱ ወደ አንድ አቅጣጫ ይመራቸዋል።

ከቀበሌና ከገበሬ ማህበራት ጀምሮ የሚዋቀሩት እነዚህ አካላት፣ ወደፊት የምንፈጥረው የሽግግር መንግስታችን ዋልታና መሰረት ሊሆኑ ስለሚችሉ፣ ልዩ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል። የተጀመረው ትግል መቋጪያ ሊበጅለት የሚችለው በየአካባቢው ትግሉን የሚመሩ ሕዝባዊ ሸንጎዎች ሲመሰረቱ ብቻ ነው። ወያኔ በፍላጎቱ ከስልጣን አይወርድም። መገደድና መገፋት አለበት።

እነዚህ ሕዝባዊ ሸንጎዎች በመላ ኢትዮጵያ፣ በተለይም በኦሮሚያና በአማራ አካባቢ እንዲፈጠሩ ከተደረጉ በኋላ፣ በየአካባቢው የሚገኙ ሕዝባዊ ሸንጎዎች በጋራ የሚሰሩበት፣ መረጃ የሚለዋወጡበት፣ ትግሉን የሚያቀናጁበት፣ የጋራ የትግል ስልት የሚነድፉበት ሁኔታ ይፈጠራል። ይህ አካሄድ፣ በትግላችን ሂደት መሪዎቻችንን ለመውለድና ለመፍጠር የሚረዳን ሲሆን፣ ወያኔ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚያካሂዳቸውን ደባዎችና ተንኮሎች ያቅባል።

ሕዝባዊ እምቢተኝነትና የፖለቲካ ፓርቲዎች

ከ1997 ዓም ምርጫ በፊት፣ በኢትዮጵያ ለሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ መልዕክት አስተላለፈ፡ ‘ተባበሩ ወይም ተሰባበሩ’ አላቸው። ለመተባበር ሞክረው ስላልሆነላቸው ጥቂት ቆይተው ተሰባበሩ። ዛሬ፣ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነው ወገናችን አደባባይ ወጥቶ ሲፋለም፣ የፖለቲካ ድርጅቶቹ እንኳንስ አመራር ሊሰጡ፣ ከሕዝቡ ጎን አልተሰለፉም። አንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶች ዘጋቢዎች ሆነው አረፉ። እናም፣ ሕዝቡ በተነሳበት ጊዜ መምራት ካልቻሉ መቼ ሊደርሱለት ይችሉ ይሆን መጠየቅ አግባብ አለው? በአጭሩ፣ ድርጅቶቹ ከስም ባለፈ ምንም ድጋፍ እንደሌላቸው ግልጽ የሆነ ሲሆን፣ አቅም አለን የሚሉ ካሉ፣ ለመተባበር ጥረት ያድርጉ። ለስልጣንና ለግል
ጥቅም የሚያደርጉትን እሽቅድምድም ትተው፣ በሕዝቡ ላይ የሚደረገው ግፍ እንዲቆም ባላቸው አቅም ሁሉ ድምጻቸውን ያሰሙ። እንዲያ ማድረግ ካልቻሉ ጡረታ ይውጡ። ጡረታ መውጣት ደግሞ ክህደት ወይም ወንጀል አይደለም።

ሕዝባዊ እምቢተኝነትና የፖለቲካ እስረኞች

በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ወገኖቻችን፣ የአልገዛምና የእምቢታ ድምጻቸውን ስላሰሙ ብቻ ዛሬ በየወህኒ ቤቱ ይማቅቃሉ። ቤተሰቦቻቸውም ችግር ላይ ወድቀዋል። ልጆቻቸው ያለአባትና እናት በመቅረታቸው ትምህርታቸውን መከታተል አዳግቷቸዋል። ለእነዚህ ወገኖቻችን ልንደርስላቸው ይገባል። ስለሆነም፣ ሀ/ ዘር ሳንለይ፣ በየእስር ቤቱ የሚገኙ ወገኖቻችንን እየሄድን እንጠይቅ፣ እስር ቤቶቹን እናጨናንቅ፣ ለ/ የታሰሩ ወገኖቻችንን የሚታደግ፣ እርዳታ የሚሰበስብ፣ ሁኔታው በሚፈቅደው መሰረት ቤተሰቦቻቸውን ሊንከባከቡ የሚችሉ የመረዳጃ ማህበሮች እናቋቁም። የእስረኛ መረዳጃ ማህበሮች እንደእንጉዳይ በያለበት ፈልተው ያብቡ።

ሕዝባዊ እምቢተኝነትና የንግድ ማዕቀብ

የደቡብ አፍሪቃ ዘረኛ ሥርዓት ሊወገድ ከቻለባቸው አንዱ ምክንያት በዓለም ዙሪያ የተደረገው የኢኮኖሚ ማዕቀብ ሲሆን፣ በወያኔና በደጋፊዎቹ አማካይነት የሚካሄደው የገቢና የወጪ ንግድ ላይ ከፍተኛ ጫና ለማድረስ ሁለ-ገብ የንግድ ማዕቀብ ይደረግ ዘንድ በተለይ በዓለም ዙሪያ የፈሰሰው ኢትዮጵያዊ የማይናቅ ውለታ ሊያበረክት ይችላል።  የወያኔን የንግድ እንቅስቃሴ ነጥለን በማውጣት ማዕቀብ እንዲደረግበት፣ እንዲገለል፣ ብሎም እንዲከስር ማድረግ ይኖርብናል። የወያኔ ንግድ፣ በድርጅቱ ዙሪያ የተሰባሰቡት ከፍተኛ ሹመኞቹ ንብረት ነው። በዚህ ንግድ ባካበቱት ገንዘባቸው ነው በየአደባባዩ የሚቆሉን፣ የሚረሽኑን። በዚህ ንግድ ባካበቱት ገንዘባቸው ነው ሰላዮች አሰማርተው የሚያስጠቁሙብን። በዚህ ንግድ ባካበቱት ገንዘባቸው ነው ኢትዮጵያን ለመበተን ደፋ ቀና የሚሉት።

የንግድ ማዕቀቡ፣ በተለይ በወያኔና ተባባሪዎቹ የንግድ እንቅስቃሴ ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ ሸቀጣቸው ተቀባይና ገዢ እንዳያገኝ፣ እንዲሁም የገቢ ንግድ ማድረግ እንዳይችሉ ያላሰለሰ ጥረትና ትግል ማከናወን ያሻል። ስራው በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄድ፣ ሀ/ በተቀዳሚ የወያኔ የንግድ ተቋማት የሆኑትን ለይቶ በማወቅ ስማቸውን ይፋ ማድረግ፣ ለ/ ኢትዮጵያውያን በሚገኙበት ሁሉ፣ ከወያኔ የንግድ ተቋማት ጋር ንግድ (ቢዝነስ ) የሚያካሂዱ ድርጅቶችንና ኮርፖሬሽኖችን ለይቶ ማወቅ፣ ሐ/ እነዚህ ተቋማት ስለወያኔ እኩይ ስራና በዘር ማጥፋት ወንጀል ላይ መጠመዱን ያለመታከት ማስረዳት፣ ከወያኔ ጋር መስራት ማለት በዘር ወንጀል መተሳሰር መሆኑን አበክሮ ማስረዳት፣ መ/ ከወያኔ ተቋማት ጋር የሚካሄድ የገቢም ሆነ የወጪ ንግድ እንዲቆም ያለመታከት ማስረዳት፣ ሠ/ የወያኔ መንግስት ዘር በማጥፋት ተግባር ላይ መሰማራቱን ያገባኛሉ ለሚሉ ኢትዮጵያውያንም ሆኑ አፍቃሪ-ኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ማሳወቅ፣ ማስረዳት። ይህን የግፍ አሰራር በጽኑ እንዲቃወሙና እንዲታገሉ ማድረግ፣ ረ/ በምንገኝበት በየትኛውም ቦታ ቢሆን፣ ከአካባቢው የሕዝብ እንቅስቃሴ ጋር የጋራ ትብብር ፈጥረን እነሱ የእኛን፣ እኛ የእነሱን አጀንዳ እስተናግደን የወያኔን ኢኮኖሚ እናሽመድምድ።

ሕዝባዊ እምቢተኛነትና የወያኔ የንግድ ተቋማትን ማግለል

ወያኔ ሕዝብ የሚገድለው፣ አፋኞች የሚያሰማራው፣ የስለላ ስራና ሌሎች ግፎችን የሚያካሂደው እኛ ራሳችን በምንሰጠው ገንዘብ ተጠቅሞ መሆኑን በመረዳትና በመገንዘብ፣ ከህወሃት ሱቆች፣ የክፍለ ሀገራት አውቶቡሶችም ሆነ ከንግድ ተቋማት ጋር ያለንን ማናቸውንም ትስስር መቆራረጥ። ከህወሃት ሱቆችም ሆነ የንግድ ተቋማት ጋር አንዳችም የግዢም ሆነ የንግድ ልውውጥ ማድረጋችንን ማቆም። የወያኔ አውቶቡሶችን ጨርሶ አለመጠቀም። እነዚህ ተግባራትን በተሳካ ሁኔታ ለማካሄድ፣ በየክልሉ፣ በከተማዎች፣ በቀበሌና በገበሬ ማህበራት አካባቢ የሚገኙ የወያኔ የንግድ ተቋማት ማንነትን ለይቶ በማውጣት ለሕዝብ ይፋ ማድረግ። ላላወቀ ማሳወቅ። እዚህ ላይ አንድ ሊጤንና ተገቢ ትኩረት ሊደረግበት የሚገባ ጉዳይ፣ የሕዝብ የንግድ ተቋማት ዒላማ እንዳይሆኑ ልዩ ጥንቃቄ ማድረግ ያሻል።

ሕዝባዊ እምቢተኛነትና አማራው

ወያኔ ሥልጣን ከመያዙ በፊት አማራ ሳንሆን፣ ጎንደሬ፣ ጎጃሜ፣ ሸዌ፣ ወሎዬዎች ነበርን። በእነዚህ ቦታዎች አማርኛ ተናጋሪዎች ብቻ ሳንሆን ትግርኛ፣ ኦሮሚፋ፣ አገውኛ፣ አፋር፣ ቅማንትና ሌሎችም እንደኛው ራሳቸውን ጎንደሬ፣ ሸዌ፣ ጎጃሜና ወሎዬ ብለው ይጠሩ ነበሩ። የወያኔ ሥርዓት ያ አልፈን ወደሄድነው ማንነታችን መለሰን። ኢጣሊያን እንዳደረገው ሁሉ ዘር ቆጠራ ውስጥ ገብተን በቋንቋችን እንድንሰለፍ ገፋፋን። ያ ብቻ አይደለም። አጎራባች ወገኖቻችንን እንድንፈራና እንዳናምናቸው አደረገ። በበደኖ እና በሌሎች ቦታዎች እንደተደረገው፣ ወያኔ ከስልጣን ከተወገደ ኦሮሞ ይጨፈጭፍሃል፣ ኢትዮጵያም ትበታተናለች ብሎ ሰበከን። ፈራን። በብዙ ወገኖቻችን ላይ ግፍ ሲፈጸም ብናይም እንዳላየ ማየትን መረጥን።

እየዋለ እያደረ ግን፣ በብዙ ቦታዎች በአማራዎች ላይ ብዙ ግፍ በመፈጸሙ የተቆጩ አንዳንድ ወጣቶች የአማራ ማንነታቸው ላይ እንዲያተኩሩ ሁኔታዎች አስገደዷቸው። ተጎናጽፈነው የነበረውንና አባቶቻችን ያወረሱንን ኢትዮጵያዊ ክብራችንና ማንነታችንን ወያኔ ቀምቶን በዘር እንድንሰለፍና እንድናስብ አደረገ፣ ለወያኔ ድግስ እንድንታደም ተገደድን። ይሁንና፣ ግብዣው ይቅርብን አልተቀበልነውም ልንል ይገባል። ኢትዮጵያዊ ማንነታችንን በአማራ መነጽር ውስጥ አሻግሮ ማየት ነውርም ሆነ ክፋት የሌለው ቢሆንም፣ አባቶቻችንና እናቶቻችን ያወረሱንን ማንነታችንን ለልጆቻችን ለማሳለፍ እንብቃ። አባቶቻችን ለአማራ ሳይሆን ለኢትዮጵያዊ ማንነት በክብር የተዋደቁለትን ዓላማ አንስተን ፈለጋቸውን እንከተል። አባቶቻችን ኢትዮጵያ ብለው ኢትዮጵያን አቁመዋል። ባንዲራችን እንድትውለበለብ አድርገዋል። እኛም የአባቶቻችንን ዱካ እንከተል። ያ ሁኔታ ሊፈጠር የሚችለው ደግሞ የወያኔ ፖሊሲ ለአንዴና ለሁልጊዜ ሲንበረከክና ሲሸነፍ ብቻ ነው። ከዚህ ፖሊሲ በስተጀርባ ያለው የህወሃት ቡድን ተወግዶ አገሪቱ በሕዝቦቿ የበላይነት ስር ስትውል ብቻ ነው።

ሕዝባዊ እምቢተኛነትና የትግራይ ተወላጅ

የትግራይ ሕዝብ በአፋኙ በወያኔ ቡድን ስር መገዛት ከጀመረ ከሶስት አስርተ አመታት በላይ ሆኖታል። በተለይ የደርግ ጦር ትግራይን ለቆ ከወጣ ወቅት ጀምሮ፣ ወያኔ፣ ትግራይን በሶስት ዓይነት ዘዴ መግዛት ጀመረ። ሀ/ ከቀበሌና ከገበሬ ማህበር ጀምሮ ሕዝቡን የሚቆጣጠርበት ሰነሰለት ዘረጋ፣ ለ/ የትግራይ ሕዝብ ወያኔን ካልደገፈ ከፍተኛ ጥቃትና ጥፋት ሊደርስበት ይችላል የሚል ስር-ሰደድ ዘመቻ በማካሄድ ሕዝቡ በፍርሃት ቆፈን ውስጥ እንዲማቅቅ አደረገ፣ ሐ/ ወያኔ ስልጣን ሊይዝ በመቻሉ ተንቀው የቆዩት የትግራይ ተወላጆች አንገታቸውን ቀና አድርገው መሄድ ጀመሩ፤ ተከበሩ ብሎ ቀሰቀሰ።

‘አዛኝ ቅቤ እንጓች’ እንዲሉ፣ ወያኔና ግብረ በላዎቹ የትግራይን ሕዝብ እስረኛቸው በማድረግ በስሙ ይነግዳሉ። እኛ ብንወገድ የትግራይ ሕዝብ መከራና አሳር ይገጥመዋል፣ ለዕልቂት ይዳረጋል ይላሉ። ዓባይ ፀሃዬ ጳጉሜ ውስጥ ለአዲስ ፋና ሬድዮ በሰጠው መግለጫ እንደገለጸው፣ ሁኔታዎች አሁን ባሉበት ከቀጠሉ እንደ ሩዋንዳ ኢትዮጵያ ልትበታተንና የዘር ዕልቂት ሊከተል ይችላል በማለት ሊያሰፋራሩን፣ ሊያሸማቅቁን፣ እርስ በእርሳችን እንዳንተማመን ለማድረግ ይሞክራሉ። ወያኔ ለ25 አመታት በስልጣን ሊቆይ የቻለው፣ ሕዝባዊ ድጋፍ አግኝቶ ሳይሆን፣ በፍርሃታችን ላይ ተንተርሶ፣ ፍርሃታችንን ተንፍሶና ተመግቦ ነው። አንተ የትግራይ ተወላጅ የሆንከው ሕዝብ፣ ወያኔ ከስልጣን ከወረደ እንደ ሕዝብ እንኳን መኖር አትችልም፣ ከፍተኛ ዕልቂት ይደርስብሃል፣ ዘርህ ይጠፋል እያሉ እየሰበኩ ናቸው። ይህን መሰሉ ቅስቀሳ መለስ ዜናዊ በነበረበት ጊዜ፣ ከ1977 ዓም ምርጫ ጋር ተያይዞ የተነሳ ሲሆን፣ በመለስ ሳንባ የሚተነፍሱት ተከታዮቹ እነ ዓባይ ፀሃዬ ዛሬም ያንኑ ዘፈን ይዘፍናሉ። በሚኒልክ ጊዜ የደነቆረች፣ አሁንም ‘ምንሊክ ይሙት’ ትላለች እንዲሉ።

የትግራይ ሕዝብ የኢትዮጵያዊነት መሰረታችን ነው። ኢትዮጵያን ያለ ትግራይ፣ ትግራይን ያለኢትዮጵያ ማየት አይቻልም። ትግራይ ማለት የሃይማኖቶቻችንና የቋንቋዎቻችን መፈጠሪያ ቦታ ነው። ትግራይ ማለት ታሪካችን ነው። ትግራይና የተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለብዙ ሺህ አመታት አብረው ኖረዋል። ምንም እንኳን ታሪካችን እንደማንኛውም አገርና ሕዝብ አባጣና ጎርባጣ ቢሆንም አንተ ትብስ ወይስ እኔ በመባባል አብረን ዘልቀናል። ጣሊያን ወደቀዬህ ሁለት ጊዜ ሲዘልቅ አብረን መክተናል። እንደ ዥረት የፈሰሰው ደማችን ተቀላቅሏል። ያን ትስስራችንን ወያኔ እንዲበጥሰው ዕድሉን አትስጥ። የትግራይ ሕዝብ ታሪክ ስራ። በስምህ እየነገዱ ያወረዱህን አሳፍራቸው። እነሱ ነግደው በከበሩ አንተ እንደ በሊታ ትታያለህ። እነሱ በዘረፉ አንተም አብረህ ትወቀጣለህ። በወያኔ አገዛዝ ግፍ በሚዘንምበት በአሁኑ ወቅት፣ የትግራይ ምሁር ድምፁን ጨርሶ አለማሰማቱ አስተዛዛቢ ቢሆንም፣ ጊዜው አሁንም አልመሸም።

ሕዝባዊ እምቢተኛነትና ኦሮሞ ወገኖቼ

ትናንት እና ከትነንትና በስቲያ ታሪክ ጎድቶናል። ደረጃው ይለያይ እንጅ ሁላችንም ተጎድተናል። አባቶቻችንና እናቶቻችን ያሳለፉት መጥፎ ዘመን ለዛሬው ማንነታችን የሚጠቅመን፣ ትግላችንን አንድ እርምጃ ወደፊት ሊያራምድልን ከቻለ እንጠቀምበት። አለበለዚያ ግን፣ ዛሬ፣ ዛሬ መሆኑን አውቀን ለነገ የሚያገለግለንን የኑሮና የትግል ስንቅ፣ ቋጥረን ጉዞአችንን መቀጠለ ይኖርብናል።

በታሪካችን የተፈጸሙ ጉዳቶች ለወያኔ ስልጣን መቆየት መሳሪያ ሆነው ማገልገል የለባቸውም። የወያኔ ሥርዓት ስልጣን ላይ ለመቆየት ሁለት ዘዴዎች እንደሚጠቀም ልብ ልንል ይገባል። አንደኛው ፍርሃት፣ ሌላኛው ጉልበት ነው። አንተን ኦሮሞውን የአማራ ነፍጠኛዎች ያገኘሃትን መብት ሊቀሙህ አሰፍሰፈው እየጠበቁ ናቸው ይልሃል። ጥቂት የኦሮሞ ጀሌዎቹንና የስርዓቱ ተጠቃሚዎችን በየአቅጣጫው እያሰማራ፣ ያ ከቀዬው ያልወጣውን ደሀ አማራ ሊነሳብህ ነው እያለ ያስፈራራሃል። በፍርሃት ብቻ የወየኔ ሥርዓት ተገዢ ሆነህ እንድትኖር ፈርዶብሃል። አንዳንድ ምሁራን የዚህ የወያኔ የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ ሰለባ በመሆናቸው፣ ድርጅቱ እነሆ ከ25 አመት በላይ ሥልጣን ላይ ሊቆይ ቻለ። በመላ ኦሮሚያ የተንቀሳቀሰው ወጣቱ ትውልድ ያን የወያኔ ደባና ተንኮል በመረዳት እምቢኝ ለነፃነቴ በማለት ካለፈው ሕዳር ወር ጀምሮ ታሪክ ሰራ። የጎንደር ወጣት ተደራሽነቱን ሲገልጽ፣ በሁለቱ ታላላቅ ሕዝቦች መሀል ድልድዩ ተቀጠለ። እናም፣ የወያኔ አንደኛው የአገዛዝ መሳሪያ እንደ ብርጭቆ ተፈረካከሰ። ብዙ መፈላሰፍ ሳያሻቸው ወጣቶች አንድነታቸውን ሲገልጹልህ አንተም አጸፋውን መለስክ። ወያኔ አሁን አንድ ብልሃት ብቻ ቀርቶታል። በጉልበት መግዛት። በአማራው ላይ የዘር ማጥፋት ዕልቂት አውጆ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል። አንተን ደግሞ ትናንት እንዳደረገው ሁሉ ዛሬም በሸፍጥ እየገዛህ ሊኖር መላ ዘይዷል፡፡ ትናንት አብረን እንስራ ብሎ ካግባባህና የነበረህን ወታደር በአንድ ካምፕ ውስጥ እንድታጉር ካደረገ በኋላ ከበባ በማካሄድ በአንድ ሌሊት አጠፋህ፣ በተነህ። ዛሬም፣ አንዳንድ መለስተኛ የመሸንገያ እርምጃዎችን በመውሰድ ችግርህን ፈትቼአለሁ፣ ፌደራል አሰራሩ በትክክል እየሰራ ነው እያለህ ነው። ዳግመኛ አትታለል! ህገ መንግስቱ የፌደራል አሰራር ይፍቅዳል ቢልም፣ ዲሞክራሲ አልባ ፌዴሬሽን አይሰራም፣ ሰርቶም አያውቅም። ዜጋዊ መብትህን በመጠቀም አደባባይ በመውጣትህ በጥይት እየተቆላህና መሬትህን ለጥቂት ባለሀብቶች እየቸበቸበ ፌደራላዊ አሰራር ተከብሯል ማለት ቧልት ነው። ፌደራላዊ አሰራር ያለፖለቲካ ዴሞክራሲ ስጋ ሰጥቶ ቢላ መንሳት ማለት ነው። ስጋውን መብላት ብትፈልግ በጥርስህ ንጨው፣ ጥርስህንም ንቀለው ማለት ነው። በተጨማሪ፣ ዋነኛ የከባቢ ሀብት የሆነው መሬት በማዕከላዊ መንግስት ስር እንዲቆይ ተደርጎ ፌደራላዊ አሰራር ብሎ ነገር የለም። በመሬትህ የሚያዙበት በማዕከላዊ መንግሱቱ ውስጥ የተሰገሰጉት ባለሥልጣናት ናቸው።

ዛሬ አማራው ላይ የዘር ማጥፋት እርምጃ እየወሰደ ነው። አንተን ደግሞ በጥቃቅን እርምጃዎች ሸንግሎህ ሲያበቃ ነገ ሌላው ላይ የደረሰውን ዕጣ እንድትጎነጭ ያደርጋል።

የወያኔ ደባና ሴራ በተባበረ የሕዝባዊ የእምቢተኝነት ትግል ይናዳል!

የኦሮሞ፣ የአማራና የተቀሩት ወገኖች ትብብርና አንድነት ለዘለዓለም ይኑር!

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.