አቶ ገዱ ለምን አለቀሱ? ሀገር በደምና በአጥንት እንጅ በእምባ አልተገነባችም (ከይገርማል)

gedu-andargachew-satenaw-news-b-78

የሰው ልጅ እንባ በተለያየ ምክንያት ሊፈስ ይችላል:: የአይን ህመም ያለባቸው ሰዎች እንባ የመቋጠር ችግር ሊያጋጥማቸው ይችላል:: ጤነኛ አይን ያላቸውም ቢሆኑ በተለያየ ምክንያት እንባ ሊያፈሱ ይችላሉ:: በሀዘን የተነሳ ይለቀሳል: በእልህና በብስጭትም እንዲሁ እምባ ገደቡን አልፎ ሊፈስ ይችላል:: አንዳንድ ሰዎች የሆነ ነገር ላይ አትኩረው ሲያዩ አይናቸው እንባ ይቋጥራል:: ከልብ ፍርስ ብለው የሚስቁ ሰዎች አይናቸው እንባ የሚያቁርበት ጊዜ አለ:: እምባ በደስታም በመከራም: በጨዋታም በቁምነገርም በጉንጭ ኮለል እያለ ወርዶ ደረትን ያርሳል:: ተዋናያን የወከሉትን ገጸባህሪ ተላብሰው በሚያስቀው ሲስቁ በሚያስለቅሰው ስቅስቅ ብለው ሲያለቅሱ ስናይ እነርሱን ተከትለን በሳቃቸው ተደስተን የምንስቅ የውሸት ሀዘናቸው ተጋብቶብን በለቅሶ የምንንሰፈሰፍ ብዙወች እንኖራለን:: ልቅሶ ውስጣዊ ብሶትን ማስተንፈሻ: የደስታም ይሁን የሀዘን ስሜት መግለጫ: የውሸትም የእውነትም እምባ የሚፈስበት ሊሆን ይችላል::

በአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም (አብቁተ) የስብሰባ አዳራሽ የባሕርዳር ወጣቶችን ሰብስበው በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያነጋገሩት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከወጣቶች  በቀረቡላቸው ጥያቄወች ምክንያት እንዳለቀሱ ከተለያዩ ድረገጾች አነበብን:: የአቶ ገዱ ልቅሶ ከምን የመነጨ ነው?

የአማራ ወጣቶች የወያኔን አፈናና መከራ ከምንም ሳይቆጥሩ በድፍረት ያቀረቧቸው ጥያቄወችና የሰነዘሯቸው አስተያየቶች ከደርግ የቀይ ሽብር ጀምሮ በኢትዮጵያ ላይ የወረደውን አፍዝ አደንግዝ የሰበረውን ሕዝባዊ እምቢተኝነት የሚያጠናክር የዘመኑን ወጣት ቁርጠኛነት ያበሰረ የለውጥ ድምጽ ነው:: የአባቶችን ለጠላት ያለመንበርከክ ባህሪና የሀገር ፍቅሩን ተላብሰው ኢትዮጵያን ወደነበረችበት የክብር ማማ ለመመለስ በቁጭት የተነሱ መሆናቸውን የሚያሳይ የጽናት መገለጫ ነው:: ይህን በትግሬ ወያኔወች የከፋፍለህና የአደህይተህ ግዛ ዘረኛ ፖሊሲ የተማረረ ወጣት በተራ ሽንገላና በቃላት ጨዋታ አቋሙን እንዲቀይር ወይም እንዲያፈገፍግ ማድረግ የሚቻል አይደለም:: የአማራ ወጣቶች በወያኔ ጠላት ተብሎ ከተፈረጀው አብራክ የተገኙ በዘር ማጥፋት ፖሊሲ የግፍ ሰለባ የሆነው የመከረኛው የአማራ ልጆች ናቸው::

ወያኔ ስልጣን ላይ ከወጣ ጀምሮ በአማሮች ላይ የደረሰው መከራ በቃላት ሊገለጽ ከሚችለው በላይ ዘግናኝ ነው:: በአንድ ወቅት ጎበዛዝትና ቆነጃጅት ሆነው የሀገርን ዳርድንበርና የሕዝብን አንድነት በደምና በአጥንታቸው ያስከበሩ ያሁኑ አዛውንቶችና አሮጊቶች በጡረታ ጊዜያቸው “ኧሁ!” ብለው ሊያርፉ እድሉን አላገኙም:: ጡት ጠብተው ያልጠገቡ ሕጻናት ሳይቀሩ ከወላጆቻቸው እቅፍ ላይ አሸልበው በሰላም ለመነሳት አልታደሉም:: ወያኔ በፈጠረው ዘረኝነት የተነሳ ትንሽ ትልቅ ሳይል ለማየትም ሆነ ለመስማት በሚከብድ ግፍ አማራ በመሆናቸው ብቻ እጅግ ብዙ አማሮች ታርደዋል:: የዘር ምንጠራው አሁንም ቢሆን አልተገታም::

ወጣቶች:- ማየት ለተሳናቸው የአይን ብርሀን: ለደከሙት ምርኩዝ: ተስፋ ለራቃቸው ተስፋ: ለተጠቁት ደምመላሽ: ለወገንና ለሀገር አለኝታወች ናቸው:: የወገናቸው ሰቆቃ እረፍት  የነሳቸው የአማራ ወጣቶች ጸረ-ሕዝብና ጸረ-ሀገር የሆነውን ወያኔን ተፋልመው በማስወገድ ህዝባዊ ስርአት ሊያሰፍኑ በእልህ ተነስተዋል:: ለአቶ ገዱ ያቀረቧቸው ጥያቄወች የሚያመለክቱት ህዝባቸውንና ሀገራቸውን ለመታደግ ማንኛውንም መስዋእትነት ለመክፈል ግምባራቸውን የማያጥፉ ቁርጠኛ መሆናቸውን ነው:: አቶ ገዱና ድርጅታቸው ይህን የወጣቱን የቁጭት መነሳሳት የሚደግፉት እንዴት ነው?

በጎንደርና በጎጃም አካባቢ ጸረ-ትግሬ እንቅስቃሴ እየተቀጣጠለ ነው በማለት ትግሬ የሆኑት ሁሉ በወታደር ታጅበው በክብር በአውሮፕላንና በመኪና ሲጓጓዙ አይተናል:: ተፈናቀሉ ለተባሉት ትግሬወች የመቋቋሚያ ብር ከየክልሎች በገፍ እየፈሰሰ እንደሆነ እየሰማን ነው:: የአማራ ክልል ንብረታቸው ለወደመባቸው ካሳ ለመክፈል ቃል ገብቷል:: በየአካባቢው ወድቀው ለቀሩት አማራ  ወገኖቻችን የህሊና ጸሎት እንኳ ተደርጎላቸው ያውቃል? አማሮች ሰው አይደሉም? ሀብት ንብረት ለወደመባቸው ካሳ የከፈላቸው መቋቋሚያ የለገሳቸው አለ? ሌላው ቀርቶ አማራን እወክላለሁ የሚለው ብአዴን እንኳ የጥፋት ተባባሪና ሽፋን ሰጭ ሆኖ ከማገልገል ውጪ የአማሮችን ጩኸት ሲጮህ መከራቸውን ሲጋራ ታይቷል?

ግን አቶ ገዱ ለምን አለቀሱ? በፍርሀት ምክንያት ነው ያለቀሱት እንዳይባል አማራን የሚያህል ሕዝብ ይዞ መፍራት ትርጉም የሚሰጥ አይደለም:: አማራው ሲፈጥረው ወታደር ነው:: አባቶቻችን አለምን ጉድ ያሰኙ ገድሎች የፈጸሙት ዘመናዊ የውትድርና ትምህርት ስለነበራቸው ወይም ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቁ ስለነበሩ አይደለም:: የአማራው የአሸናፊነት ሚስጥር ልበ-ሙሉነቱ ነው: ጀግንነቱ ነው:: ይህን ህዝብ እየመራሁ ነኝ የሚል ሰው የህወሀትን ሀይል ፈርቶ የሚያለቅስ አይሆንም:: ልቅሷቸው የወጣቶችን የትግል ወኔ በመረዳት ከተሰማቸው ደስታ የመነጨ ከሆነ አማራን ከጥፋት ለመታደግ እየተሰሩ ባሉ ስራወች በሚያበርክቱት ድርሻ ወደፊት በተግባር የምናያቸው ይሆናል:: ብአዴን እስከቀበሌ ድረስ ያለውን አደረጃጀቱን ተጠቅሞ የአማራው ሕዝብ ተደራጅቶና ታጥቆ መብቱን እንዲያስከብር የበኩሉን እገዛ ሲያደርግ ያን ጊዜ የአቶ ደጉ እምባ የብሩህ ተስፋ አብሳሪ: የአንድነትና የመከባበር ቡቃያ አብቃይ ጠል (ዝናብ) ነው ማለት እንችላለን:: ከዚያ ውጭ የአማራ ክልል ፕሬዚደንት ነኝ ተብሎ ተቀምጦ እወክለዋለሁ የሚለው ሕዝብ በዘረኛ ቡድን ሲሰቃይ እያየ  እጅን አጣጥፎ ቁጭ ብሎ ሀዘንን በዘለላ እምባና በከንፈር መጠጣ መግለጽ የሕዝብ ልጅነትን: የወገን ተቆርቋሪነትን የሚያሳይ አይሆንም::

እንደሚሰማው ከሆነ አብዛኛው የብአዴን የታችኛውና የመካከለኛው አመራር በሕዝቡ ላይ የሚደርሰውን ግፍ ጠንቅቆ ስለሚያውቅ የስርአቱ አራማጅ የሆነውን ወያኔን እና አስከፊ አገዛዙን የሚጠላ እንደሆነ ነው:: ይህ ማለት ከሕዝቡ ጋር ተቀራርቦ የሚሰራው አመራር የወያኔ ስርአት እንዲያበቃ ከሚፈልጉት ወገኖች መሀል የሚደመር ነው ማለት ነው:: ታዲያ ይህን አመራር በአግባቡ ከተጠቀምንበት ህዝቡን የማንቃት: የማደራጀት: መሰረታዊ የወታደራዊ ስልጠና የመስጠት: የማስታጠቅና ራሱን ለመከላከል የሚያስችል የውጊያ ሞራሉን የመገንባት ስራው  በቀላሉ ሊሰራ ይችላል ማለት ነው:: ከላይ ያለው አመራር  ያለመካከለኛውና ያለታችኛው አመራር ሊሰራው የሚችል ምንም ነገር አይኖርም:: አማራውን ከፈጽሞ ጥፋት ለመታደግ ስንነሳ መስዋእትነት አይኖርም ማለት አይደለም:: የሚከፈለው መስዋእትነት እጅና እግርን አጥፈን ተቀምጠን ሞትን በጸጋ የምንቀበልበት ሳይሆን ገድለን የምንሞትበት ስለሚሆን ገዳያችን ከመናቅ ወደማክበር: ከመድፈር ወደመፍራት: ከትእቢት ወደአስቦ መስራት እንዲወርድ የምናስገድድበት ወሳኝ እርምጃ ነው::

ማንም እንደሚያውቀው ወያኔ የአማራ አካባቢወችን በማናለብኝነት ወደትግራይ ክልል ሲያጠቃልል የገጠመው ፈተና (resistance)ዝቅተኛ ነበር:: በዚህም የተነሳ ሌሎች ተጨማሪ መሬቶችን ለመውሰድ ቅድመ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል:: የራስዳሸን ተራራ በትግራይ ክልል እንደሚገኝ በተማሪወች መጽሀፍ ተጽፎ ለ10 አመታት ያህል ትምህርት የተሰጠው ለጨዋታ አልነበረም:: የላሊበላ ውቅር አብያተክርስቲያናት የሚገኙት በትግራይ ክልል እንደሆነ ለቱሪስቶች የማስተዋወቅ ስራ የተሰራው በስህተት አልነበረም:: ከዚህ በፊት ራያና ወልቃይት ያላግባብ ወደትግራይ ሲካለሉ “ለምን?” ብሎ የሞገታቸው ስላልነበረና በኋላም ቢሆን እንዲመለሱ የተደረገ ጫና ስላልነበረ ነው አማሮች ሞኞች ናቸው ብለው ሌላ ተጨማሪ መሬት ለመውሰድ ዕቅድ የነደፉትት:: የትግራይ ትልቁ ተራራ ራስ ዳሸን ነው ብለው በመጽሀፍ አውጥተው ከ10 አመታት በላይ ያስተማሩት አሁን እንደሚባለው በስህተት ሳይሆን የሕዝቡን ስሜት ለመለካት የተጠቀሙበት ዘዴ: ሁላችንም ቀስ በቀስ እየለመድነው እንድንሄድ የታሰበበት መላ ነበር:: የወልቃይት ወገኖቻችን ካለአጋር ብቻቸውን ለአመታት ጮኸው ከወደቅንበት የድብርት አለም ባያነቁን ኖሮ ራስ ዳሸን እና ላሊበላ አካባቢ የሚኖረውን የአማራ ሕዝብ ቀስ በቀስ አፈናቅለው ትግሬወችን ካሰፈሩ በኋላ በሂደት የትግራይ ክልል አካል አድርገው ሲያበቁ ሀፍረትና ይሉኝታ የሚባል ነገር ስለማያውቁ ደግሞ ሌላ መሬት ለመውሰድ መክጀላቸው አይቀርም ነበር::

ከወያኔ ጋር የሚደረገው ትግል ገና አልተጀመረም:: ወልቃይትና ራያን በፈቃዳቸው ይመልሱልናል የሚል ሀሳብ ማናችንም የለንም:: በተለያየ ስልት አማራውን ለማጥፋት የሚያደርጉትን ደባ ያቆማሉ የሚል እምነትም የለንም:: ወያኔ እስካለ ድረስ ሰላም: እኩልነት: ፍትህ እና  ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ ምድር የሚታሰቡ አይሆንም:: የኢትዮጵያ ሕዝብ ተከባብሮ በሰላምና በፍቅር እንዲኖር ከተፈለገ የክፋት ምንጭ የሆነው ወያኔ መጥፋት አለበት:: ወያኔ የሚጠፋው በእንባ ሳይሆን በትግል ነው:: ለትግል ከመነሳታችን በፊት ከመሀል የተሰገሰጉትን ወያኔወችና ማሰቢያ የሌላቸው ፍርፋሪ ቃራሚ (ተስፈኛ) አማራወችን ለይቶ በስልት እንዲገለሉ ማድረግ ያስፈልጋል:: መሰናክል ይፈጥራሉ የምንላቸውን በከፍተኛ አመራር ላይ የተቀመጡ የወያኔ ጉዳይ አስፈጻሚወችን በስብሰባ ወቅት እጅ ወደላይ ብሎ መሰወር ይቻላል:: የክልሉ የጸጥታ ሰራተኞች: የአካባቢ ሚሊሽያና የአማራ ፖሊስ የወያኔን ተልእኮ ለማስፈጸም የተሰለፉ ሀይሎችን ትጥቅ ማስፈታት አይከብዳቸውም:: በመከላከያና በፌደራል ደህንነት ውስጥ ለሚሰሩ ወሳኝ ሰዎች ከቤተሰቦቻቸው ጋር በመተባበር ሚሽን ቢሰጣቸው መልካም ነው:: በአማራ ክልል የሚደረገውን የነጻነት ትግል ዝግጅት ለማቀላጠፍ በአዲስአበባ ላይ አተኩሮ ውጥረት መፍጠር በክልሉ የሚሰሩ ስራወችን ለመሸፈን ይረዳል::  አላማው ለበጎ እስከሆነ ድረስ ብዙ ብዙ ሊደረግ ይችላል:: የሚያስፈልገው ቁርጠኝነት ብቻ ነው:: ትግሉ ቀላል የማይባል መስዋእትነት የሚጠይቅ ሊሆን ይችላል:: ቢሆንም ቀበቷችንን አጥብቀን መፋለም ግድ ይለናል:: ወያኔ የፈጠረው ችግር ይብዛም ይነስ በሁሉም ኢትዮጵያዊ ላይ የደረሰ በመሆኑ ከሌሎች ክልሎች ጋር የመናበብና የመደጋገፍ ስራ መስራት ተገቢ ነው:: ሁላችንም እጅ ለእጅ ተያይዘን ደፍረን መስዋእትነት ለመክፈል ስንቆም ያኔ ነጻነታችንን ማስመለስ እንችላለን:: እኛ ስንፈራ እነሱ ይጀግናሉ: እኛ ስንደፍር እነሱ በፍርሀት ይርበደበዳሉ:: ስለዚህ ባርነትን ለመሸከም የማንፈቅድ ሁሉ መስዋእትነት ለመክፈል አናመንታ::

አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በርሳቸው የስልጣን ዘመን በወያኔ ገዳይ ቡድኖች ተመተው ለወደቁት አማሮች አዝነው አልቅሰው ከሆነ ቢያንስ ለወገን ያላቸውን ተቆርቋሪነት ያሳዩ የመጀመሪያው የክልሉ ፕሬዚደንት ናቸው በሚል እናከብራቸዋለን:: አግባብ የማይሆነው ከእንግዲህ በኋላም እያስገደሉ ሀዘናቸውን በእንባ ለመግለጽ ቢሞክሩ ነው:: ከባለፈው ተምረው ለሕዝባቸው በጎ ነገር ያደርጋሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን:: እርስዎና ድርጅትወ የህዝብን ትግል መደገፍ ከቻላችሁ የሚከፈለውን መስዋእትነት ያለጥርጥር ይቀንስልናል:: እንጅ ለውጡ እንደሆነ በምንም ታምር አይቀርም:: ከህዝብ ጎን ለመቆም ብትቆርጡ እሰየው ነው:: ከህዝብ ጎን ለመቆም ፍላጎት ካላሳያችሁ የፈለገውን ያህል መስዋእትነት ተከፍሎም ቢሆን ነጻነታችንን አረጋግጠን ዴሞክራሲያዊት ሀገር መመስረታችን ስለማይቀር ከተጠያቂነት አታመልጡም::

የተከበሩ አቶ ገዱ:-

ለሕዝብና ለሀገር ቁምነገር ሊያበረክቱ: ስምወን በማይነጥፍ ቀለም በኢትዮጵያ ታሪክ ሊያሰፍሩ እድል ስልጣን ላይ አስቀምጣወታለች:: ይህን እድል ካመከኑት ለልጅ ልጆችወ መጥፎ ስም አውርሰው በሀፍረት አንገታቸውን ሰብረው እንዲኖሩ ያደርጋሉ:: ሕዝብወን አሰልፈው ጥሎ ለመውደቅ ከቆረጡ አይደለም ተወላጆችወ: አማራ ነኝ የሚል ሁሉ ስምወን እንደነ አጼ ቴወድሮስ: አጼ ሚኒሊክና እንደበላይ ዘለቀ ከልጅ ልጅ እያስተላለፈ በክብር ሲያነሳወ ይኖራል:: መጥፎ ሰው የሚኖረው ለራሱ ነው:: እሱ ካለፈ በኋላ ለተወላጆቹ ዕዳ ይሆናል:: መልካም ሰው ግን የሚኖረውም ሆነ የሚሞተው ለመልካም ተግባር ስለሚሆን በህይወት እያለም ይሁን ከማይቀረው ሞት በኋላም በስሙ የሚማልበት በስራው የሚከበሩበት ይሆናል:: ይወቁበት:: ካለፈ በኋላ ቢቆጩ ትርጉም የለውም:: ማን ማን እንደሆነ ይለዩ:: ለህዝብ ቆመዋል የሚሏቸውን አመራሮች ለማግኘት መስመር ይዘርጉ:: ለጠላት መሳሪያ ሆነው ሕዝብን ለጥቃት የሚያጋልጡትን ሰዎች ማስመከር በምክር ሊመለሱ ያልቻሉትን ደግሞ ማስወገድ የሚከፈለውን መስዋእትነት መቀነስ: የትግሉን አላማ ለማሳካት መሰናክሎችን መጥረግ ነው:: ትንፋሻችንን ውጠን ታግሰን አይተነዋል:: መከራውን ተቀብለን አልቅሰን አይተነዋል:: መከራችን ግን ቀን ከቀን አመት ከአመት እየባሰ ሄደ እንጅ አልተሻሻለም:: አባቶቻችን ፈተናን በትግል እንጅ በልቅሶ አላሸነፉም:: ሀገር በደምና በአጥንት እንጅ በእምባ አልተገነባችም:: የሕዝብ አንድነት በደምና በአጥንት እንጅ በእምባ አልተመሰረተም:: እኛም በተግባር እንዳየነው እምባችን የፈየደው ምንም ነገር የለም:: ከእንግዲህ ወዲያ የሚፈሰው እምባችን ሳይሆን ደማችን መሆን አለበት:: በደም የተከበረው ማንነታችን በደም ይጸናል::

ትንሳኤ ለኢትዮጵያ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.