ዳግማዊ  ዘመነ መሳፍንት በኢትዮጵያ [ሞት ቡሃላ]

EPRDFበጎንደር መቀመጫውን ያደረገው የማዕከላዊ መንግስት ንጉሰ ነገሰት የነበሩት ዳግማዊ ኢያሱ ባጋጠመቸው ያልተጠበቀ ሞት ምክንያት ልጃቸው ኢዮዋስ (የንግስና ስሙ አዲያም ሰገድ) በ1755 የማዕከላዊ መንግስቱ ንጉሰ ነገስት ሆነው በሰሎሞናዊው ስርዓት መሰረት እንዲሾሙ ምክኒያት ሆኖል፡፡ ይሁን እንጂ ልጅ አዲያም ሰገድ ከየጁ ኦሮሞ በሆኑት አያቱ ምንትዋብ እንደራሴነት እየታገዘ በጎንደር የሚገኘውን የማዕከላዊ መንግስት ማስቀጠል የቻለው እስከ 1969ዓም ለአስራ አራት አመታት ብቻ ነበር፡፡  ምን ተፈጠረ እንደምትሉኝ ተስፋ አደርጋለው፤ የአድያም ሰገድ ልጅ እግርነት እና የአባቱ ሞት ያስከተለውን የአስተዳደር ክፍተት በመጠቀም የትግራዩ ራስ ሚካኤል ስሁል ንጉሰ ነገስቱን  በ1769 በማስገደለል(በድጋሚ) የጎንደር ማዕከላዊ መንግስት ተደማጭነትን ለአንዴና ለመጨረሻ ግዤ እንዲያከትም በማድረግ ለዘመነ መሳፍንት መፈጠር ምክንያት( Immediate factor) ሆነ፡፡ በነገራችን ላይ ራስ ሚካኤል ስሁል እንደሟች መለስ ዜናዊ  አናታቸው መላጣ ነው( መቼስ የዘንድሮ ሰዎች ካላያቹ አታምኑም አይደል?  ፎቷቸውን  ከታች ማየት ትችላላችሁ)፡፡

በመሆኑም በሀገራችን ታሪክ ከ 1769 ዓም እስከ 1855ዓም ያሉት 86 አመታት ዘመነ መሳፍንት (“Age of Princes”) በመባል ይታወቃል፡፡  የዚህ ዘመን ዋነኛ መገለጫ ባህሪው የማዕከላዊ መንግስቱ ተፅኖ መፍጠር ያለመቻሉ(ጥርስ አልባ ውሻ መሆኑ)  እና ሀይ የሚላቸው ያጡ የአካባቢ መሳፍንት የእርስ በእርስ ጦርነቱን ያጧጧፉበት ግዜ መሆኑ ነው፡፡ በተለይ ሀገራችን ከምንግዤው በላይ አንድነቷ የተዳከመበት፣ በየአካባቢው የሚገኙት ገዢዎች እራሳቸውን ችለው የውጭ ግንኙነቶችን በድብቅ የሚያደርጉበት እና ፍትህ የሌለበት ግዜ መሆኑን ብዙ የታሪክ ፀሃፊዎች ይስማማሉ፡፡ በተጨማሪም መሳፍንታቱ በጎንደር በሚገኛው ማዕከላዊ መንግስት የአነሱን ፍላጎት የሚያራምድ ለይስሙላ የሚቀመጥ ንጉሰ ነገሰት ለማንገስ አስከመፋለም የደረሱበት ግዜ መሆኑን ከታሪክ ድርሳናት መመልከት ይቻላል (እንደ አሁኑ ሀይለማርያም(ሀይለ ህወሓት ) መሆኑ ነው፡፡

ወደ ሀገራችን የቅርብ ታሪክ ልመለስና ወታደራዊው የደረግ መነግስት በወደቀ ማግስት ሲጠሩ አቤት እንዲሁም ሲታዘዙ ወዴት የሚሉ እና ብሄርን የሚወክሉ የህዋሃት እንደራሴዎች ተፈጥረዋል፡፡ እኝህ የህወሓት እንደራሴዎችን/ የጭን ገረዶችን በበላይነት ለመምራት አንዲሁም የመጨረሻው ተደማጭ ግለሰብ ለመሆን በሚደረገው ስውር ግብግብ የትግራይ ህዝብ ተወካዮች ነን ባዮቹ በ1983ዓም ለሁለት ተሰንጥቀዋል፡፡ ከህወሓቱ የ1983 መሰንጠቅ የተረፈው አቶ መለስ ዜናዊ (አስተዋዩ መሪያቸው) የትግሉ አጋር የሆኑ ታጋዮችን በመብላት እንዲሁም አልፎ አልፎ ብቅ የሚሉ ስጋት የሚሆኑ የፓርቲ አባላትን ከጫወታ ውጪ በማድረግ ለህዋሃት እንዲሁም ለማዕከላዊ መንግስቱ መዳከም ጉልህ ሚና ተጫውቷል፡፡ አንድ ወዳጄ መለስና የማንችስተሩ ፈርጉሰን ተተኪ(ዘላለማዊ አጥቂ) አላፈሩም እያለ የሚቀልደደው ቀልድ ኪዚህ ጋራ የሚጣጣም ይመስለኛል፡፡ ያልተጠበቀ ሞት መኖሩን ያልተገነዘቡት ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ግለሰባቢ ሀያልነታቸውን አውን ለማድረግ ሙያዊ ብቃት የሌላቸውን እንዲሁም ግለሰባዊ ልዕልና የሚጎድላቸውን ሰዎች በዙሪያቸው በመሰብሰብ ፀሓይ ሆኖ ለመታይት ብዙ ጥረት አድርገዋል፡፡ በዙሪያቸው የሰበሰቧቻውን ግለሰቦች ዘለቄታ ያለው ታዓማኒነትና ታዛዥነት ለማግኘትም መንግስታዊ ሌብነትን እያዩ እንዳላዩ በማለፍ እንደመሳሪያነት ተጠቅመዋል፡፡ እንዲያዉም ሌብነት አስካልተያዝክ (መታዘዝና መታመን እስከቻልክ) ድረስ ስራ መሆኑን በይፋ አውጀዋል፡፡

በመሆኑም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ሞት ቡሃላ ያለው የሀገራችን ሁኔታ ከቀድሞ የዘመነ መሳፍንት ክስተቶች ጋራ የቀረበ ተመሳሳይነት ስላለው ዳግማዊ ዘመነ መሳፍንት ቢዬዋለው፡፡ ለዚህም እንደማሳያነት የሚከተሉት መግለፅ ይቻላል፡-

የመጀመሪያው ሀይለማሪያምን ከፊለፊት በማሰለፍ ሀገሪቷን የሚመራው የማዕከላዊ መንግስት ጊዤ በሄድ ቁጥር ተፅኖ ፈጣሪነቱ እና ህዝባዊ ተደማጭነቱ እየቀነሰ መሄዱ ተጠቃሽ ነው፡፡ ባለፉት አስር ወራት በኦሮሚያ እና በቅርቡ በአማራ ክልል በተከሰተው ህዝባዊ  ቁጣ  በሀይለማሪያም  ፊትአውራሪነት የሚመራው የማዕከላዊ መንግስት ህዝቡን ለማስፈራራት ቢሞክርም  ሰሚ ካለማግኘቱም በላይ ህዝቡ  በሶሻል ሚድያ የሚተላለፉ የትግል ስልቶችን አምኖ በመቀበል ህዝባዋዊ እምቢተኝነቱን አለማቋረጡን ለአብነት ማንሳት ይቻላል፡፡በተጨማሪም የማዕከላዊ መንግስቱ በተለያዩ ጊዚ ያወጣቸውን የፖሊሲ ማዕቀፎች እንዲሁም መንግስታዊ አቋሞች በህዝቡ እንቢተኝነት ለማዘግየት መገደዱ በአንድ በኩል የማስፈፀም አቅሙ መዳከሙን በሌላ በኩል ህዝባዊ አመኔታ ማጣቱን ያመላክታል፡፡  በቅርቡ እንኳ የአዲስ አበባ እና አጎራባች ከተሞች ማስተር ፕላን እንዲሁም የከተማ ታክሲ አሽከርካሪዎች አዋጅን  ይቅርታ በመጠየቅ ማራዘሙና እንዱሁም በወልቃየት ዙሪያ የተነሳውን የማንነት ጥያቄ አስመልክቶ የሚስተዋለውን ወጥነት የጎደለው  የመንግስት አቋም መመልከት ይቻላል፡፡

ዋናዎቹ የኢሐዲግ አባል ድርጅቶች ለይስሙላ የጠቀመጠውን የማዕከላዊ መንግስት ጠቅላይ ሚኒስቴር የሃላፊነት ቦታ ከተቻለ አጠቃሎ ለመያዝ አሊያም ተፅኖ ፈጣሪነታቸውን እውን ለማድረግ የሚያካሂዱት የውስጥ ሴራ ሌላው ከመጀመሪያው ዘመነ መሳፍንት የሚያመሳስለው ክስተት ነው፡፡  ከጠቅላይ ሚኒስተሩ ሞት ቡሃላ ባለችው ሀገራችን ህወሓት በማዕከላዊ መንግስቱ የነበረውን የበላይነት አስጠብቆ መሄድ የታሰነው ሲሆን ዋናዎቹ አባል ድርጅቶች( ኦህዴድ እና  ብአዴን) የታዛዥነት ሚናቸውን አምኖ ላለመቀበል ውስጥ ውስጡን ድብቅ ትግል በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ በተለይ ህወሓት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሞት ምክንያት ያጣውን ቦታ አሳልፎ ላለመስጠት የታለያዩ  የምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴር ክላስተሮችን በመፍፀጠር ተፅኖ ፈጣሪነቱን ለማስጠበቅ እንዲሁም ለወደፊቱ መደላድል ለመፍጠር ቢሞክርም መንገዱ ግን አልጋ በአልጋ አልሆነለትም፡፡

ሌላው ከምንጊዜው በበለጠ ሀገራዊ አንድነታችን አደጋ ላይ የወደቀበትና ፍትህ የተጓደለበት ወቅት  መሆኑ ነው፡፡ በአንድ ሀገር የሚኖሩ ህዝቦች ምንም እንኳ የተለያየ ቋንቋ እና ባህል ቢኖራቸው ደስታና ሀዘናቸው የጋራ ነው፡፡ አባቶቻችን ይህንን ሁኔታ አፍንጫ ሲመታ አይን ያለቅሳል ለካ እያሉ ይገሉፁታል፡፡  ይሁን እንጂ ላለፉት አስር ወራት ከ600 መቶ በላይ የሚሆኑ የኦሮሞ ወጣቶች በወገን ጥይት እየተመጡ ሲወድቁ  እንዲሁም በቅርቡ በአማራ ክልልና ኮንሶ እናቶች የወደፊት ተስፋ የሆኑ ልጆቻቸውን ከየመንገዱ እያነሱ ሲቀብሩ አይተን እንዳላየን መሆናችን አልፎም ጠባብና ትምከተኛ እያልን ስም ማውጣታችን ሀገራችን ከምንጊዜውም በላይ ውስጣዊ አንድነቷ መዳከሙን ያሳል፡፡ በተጨማሪም በጋምቤላ የሚኖሩ ንፅህን   ዜጎች በውጭ ወራሪ በጅምል ሲታረዱ እንዲሁም ሴቶቻችን በየ አረብ ሀገራት የሰብአዊ መብታቸው በተደጋጋሚ ሲገፈፍ መመልከታችን እነደ ሀገር ተፅኖ ፈፃሪነታችን አና ክብራችን መጉደፉን  እንዲሁም ፍትህ አለመኖሩን አመላካች ነው፡፡  እንዳንዶቻችሁ እንኳን  የአረብ ሀገራትን ታላቋን አሜሪካ እንኳ ሰሞኑን ሀይለማሪያም ሲያስፈራራ አላየህም እንደማትሉኝ ተስፍ አድረጋለው፡፡ ጅብ በሰው ሀገር ሄዶ ቁርበት አቅርቡልኝ አለ ….አሉ……..ይባላል፡፡

በመጨረሻም የእኔን ጥያቄ አንግባቹህ ሳትመለሱ ከመንገድ ለቀራችሁ ውድ ኢትዮጵያዊን ወንድሞቼ አፈሩ ይቅለላችሁ(Biyyoon isinitti haasalphatu )፡፡ ልጄ በሰላም ወደቤት ተመልሶ ይገባ ይሆን  ብላችሁ ለምትጨነቁ የሀገሬ ወላጆች እንዲሁም ታጋዮች  የኤቢሳ አዶኛን  “ሃቲ ዲራ ሂንቦሲ” የሚለውን ቀስቃሽ ዘፈን (https://www.youtube.com/watch?v=DOmV8RfsQ8k) እየጋበዝኩ ልሰናበታቹህ፡፡ የመፍትሄ ሃሳቡን ይዤ ብቅ እላለው በድጋሚ፡፡

የወይንሸት ልጅ ተወልደ!!!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.