ዓመተ ፍዳ ዘነገደ አማራ! [ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኩዳን]

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

ቤተክርስቲያን “ዓመተ ፍዳ” የሚለውን ቃል ዓለም ከተፈጠረ አንሥቶ ከክርስቶስ መወለድ በፊት ያለውን የሰው ልጆች በነፍስና በሥጋችን በአጋንንት አስከፊ የፍዳ፣ የመከራ፣ የሰቆቃ፣ ግዞት የነበርንበትን ዘመን ለማመልከት የምትጠቅሰው ቃል ነው፡፡

በቅርቡ “የጥፋት ዘመን” በሚል ርእስ በዋናነት በጋዜጠኛ ሙሉቀን ተስፋው የተዘጋጀ በ25 ዓመታቱ የወያኔ አገዛዝ ዘመን በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በአማራው ሕዝብ ላይ አጋንንት በተዋሐዷቸው በወያኔ ኦነግና ሌሎች የጥፋት ኃይሎች የተፈጸመውን የዘር ማጥፋትና ማፅዳት እልቂት የሚያትት ጥናታዊ መጽሐፍ ታትሞ ለአንባቢያን መቅረቡ ይታወቃል፡፡

አስቀድሜ ከጅማሬው አንሥቶ ይህ መጽሐፍ ታትሞ ለአንባቢያን እስኪደርስ ባለው ሒደት የተሳተፉ ወገኖችን በሙሉ በግሌ እጅግ አድርጌ ላመሰግን እወዳለሁ፡፡ ተባረኩ!

ከዓመታት በፊት ቀደም ሲል በዚህ ጉዳይ ላይ የጻፍኩትን “የዘር ማጥፋት ወንጀሎች በአማራ ሕዝብ ላይ በታሪክ ሒደት ውስጥ ከጥንት እስከ ዛሬ!” የሚለውን ረዘም ያለ ጽሑፍ በማካተት እንዲህ ዓይነት መጽሐፍ ለማዘጋጀት አስቤ ለዚህ እነ ጋዜጠኛ ሙሉቀን ላዘጋጁት መጽሐፍ መዘጋጀት እስፖንሰር (ደጋፊ) የሆነው ሞረሽ ወገኔ እንደተመሠረተ ሰሞን ለአንደኛቸው የድጋፍ (የስፖንሰር) ጥያቄ አቅርቤ ነበር፡፡ ሰውየው እንደሚያቀርበው ከነገረኝ በኋላ ምን ውሳኔ ላይ እንደተደረሰ ሳይነግረኝ በመቅረቱና በእኔም ላይ ታች አምና ኦነግ ያሳሳታቸው የጅማ ዩኒቨርስቲ (መካነ ትምህርት) ተማሪዎች ተገንብቶ ሊመረቅ በነበረው በአኖሌ ሐውልትና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ መጽሔት ላይ የጻፍኩትን ጽሑፍ ምክንያት በማድረግ ቁጥሩ ያልተወቀ ሰው የሞተበትን ዐመፅ አስነሥተው በእኔና በመጽሔቱ ላይ እርምጃ እንዲወሰድ ሲጠይቁ (በጥቂት ቀናት ውስጥም ዐመፁ ወደ ሌሎች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሲቀጣጠል የኦሕዴድ ሰዎች “አሃ! ሕዝባችን በዚህ ደረጃ መነሣሣት የሚችል ከሆነማ!” በማለት አጋጣሚውን ለመጠቀም በማሰብ እጃቸውን አስገቡበትና የተማሪዎቹን ጥያቄ የአዲስ አበባን ዐቢይ የማስፋፊያ አቅድ ወደ መቃወም እንዲዞር አደረጉት)

እናም በዚህ መልኩ በእኔና በመጽሔቱ ላይ እርምጃ እንዲወሰድ ሲጠይቁና በግልም የተለያየ ዛቻና ማስፈራሪያ ሲደርስብኝ ጊዜ ወያኔና ሌሎች የጥፋት ኃይሎች ኦሮሚያ ሲሉ በሚጠሩት የሀገራችን ክፍል በነጻነት ተዘዋውሬ በአማራ ኅብረተሰብ ላይ የተፈጸመውን አረመኔያዊ ኢሰብአዊ ዘር የማጥፋትና የማጽዳት ግፍ የማጥናት የማጣራትና የመዘገብ ዕድሌ እንደተበላሸብኝ ሲገባኝ ለሞረሽ ወገኔም ሆነ ለሌላ አካል ጥያቄውን ደግሜ ሳላቀርብ ቀረሁ፡፡

ይሁንና ይህ መሠራት መከወን የነበረበት ሥራ በእኔ ባይሠራም በእነ ሙሉቀን ተስፋው ተሠርቷልና ዋናው ጉዳይም መሠራቱ ነውና ምንም ዓይነት ቅሬታ አላደረብኝም፡፡ ከዚህ በፊት በዚህና ተያያዥ ጉዳይ ላይ በጻፍኳቸው ጽሑፎች ላይ ያነሣኋቸው ሐሰቦች እዚህ መጽሐፍ ላይ በመንጸባረቃቸውም አልተከፋሁም ጉዳዩ የሀገርና የወገን ነውና፡፡

እነ ጋዜጠኛ ሙሉቀን ሁኔታው የፈቀደላቸውንና መድረስ የቻሉትን ያህል በመድረስ ነፍሳቸውን ለአደጋ በማጋለጥ ጭምር በአማራ ሕዝብ ላይ የተፈጸመውን የዘር ማጥፋትና ማጽዳት በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸም የመጨረሻ ወንጀል ለመዘገብ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡ ያልደረሷቸው አካባቢዎችና የፍጅት ኩነቶች ቢኖሩም መጽሐፉ  ግን በሀገራችን በ21ኛው መቶ ክ/ዘ በፍጹም በፍጹም ይፈጸማል አይደለም ይታሰባል እንኳን የማይባል አረመኔያዊ ድርጊት ምናልባት አጋንንት ይሆናሉ እንጅ ሰው መሆናቸው በእጅጉ በሚያጠራጥሩ አራዊት የተፈጸመውንና አሁንም እየተፈጸመ ያለውን የግፍ ደረጃና ክብደት ለመረዳት ከበቂ በላይ መረጃና ግንዛቤ ሰጪ ነው፡፡

እነኝህን እጅግ ኢሰብአዊ የአውሬዎችን ድርጊቶች ድርጊቶቹ ለተፈጸመባቸው አካባቢዎች ሰዎች ካልሆነ በስተቀር ለብዙዎቻችን ጭምጭምታውን ካልሰማን ወገኖች መሀል ግን በሌላው የዓለም ክፍል በፍጹም ተሞክረው የማያውቁ ዘግናኝና አረመኔያዊ ግፎች በአማራ ብሔረሰብ ተወላጆች ላይ በብዛት መፈጸማቸውን የሚያውቅ እንደሌለ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡

የዚህ ምክንያቶቹ  ደግሞ አንደኛ፦ ጥቃቱ የተፈጸመባቸው ወገኖቻችን የተፈጸመባቸውንና እየተፈጸመባቸው ያለውን ግፍ ማውራታቸው ወይም መናገራቸው ለተጨማሪ ጥቃት የሚያጋልጣቸው መሆኑ ሲሆን፡፡ ሌላው ደግሞ “አማራ እንደ ሕዝብ የአጋንንቱ ኢላማ ሆኖ እየተጠቃ መሆኑ በይፋ ቢታወቅ ይህ ግፍ የዘነበበት ሕዝብ ተገዶ በሚወስደው የመከላከል እርምጃ እንዳለ ብሔረሰቡን ብሎም ሀገሪቱን ችግር ላይ መጣል ይሆናልና በእኛው ቢቀር ዋጥ አድርገነው ብንጠፋ ይሻላል!” ከሚል ከፍተኛ ኃላፊነት የተሞላበት አስተሳሰብ ነገር ግን የተሳሳተ አቋም የተነሣ ነው፡፡

ብዙዎቻችን በተለይም መረጃው የሌለን ወገኖች ለመረጃው ሩቅ ከመሆናችን የተነሣ ከፊሉ የተፈጸመው  የግፍ ዓይነት ለማመን እጅግ የምንቸገርበት ነገር ቢሆንም ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ በተለይም የአማራ ተወላጅ የሆነ ሁሉ ይሄንን መጽሐፍ ማንበብና ያለንበትን ሁኔታ መረዳት ይኖርበታል፡፡

ለሰብአዊ መብቶች መከበርና መጠበቅ የጸና አቋም ያለው ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሁሉ በተለይም የጥቃቱ ኢላማና ሰለባ የሆነው ዘር አባል የአማራ ተወላጅ  የሆነ ሁሉ ይሄንን መጽሐፍ አንብቦ ያ ግፍ የተፈጸመባቸው ወገኖች ሰቆቃና ሕመም አጥንቱ ድረስ ዘልቆ ካልተሰማው፣ ካልተንገበገበ፣ ቁጭት ካላቃጠለው፣ ይሄንን አረመኔያዊ ግፍ የፈጸሙና እየፈጸሙ ያሉ አራዊትን የመታገልና የመደምሰስ የትግል ስሜት ከውስጡ ካልተቀጣጠለበት ካልነደደበት እሱ በድን፣ እሬሳ፣ ጤና በእጅጉ የተጓደለው ወይም  የተሟላ የስሜት ሕዋሳት የሌለው መሆኑን እርግጠኛ ሊሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱም በዚህ የራሱ ጉዳይ በሆነ ነገር ያልተነሣሣ ያልተቀሰቀሰ ያልተቃጠለ በሌላ በምንም ሊቀሰቀስ አይችልምና፡፡

አርጀንቲኒያዊው ቸ ጉቬራ በዘርና በቀለም ለማይመስሉት ግፉአን ጥቁር አፍሪካውያን ሲል ለነጻነታቸው ለህልውናቸው አንዲት ነፍሱን መሥዋዕት እስከማድረግ ድረስ ቆርጦ መሰለፉን እያወቅን፣ የእኛም አባቶች በኮሪያ በሊቢያ በኮንጎ ወዘተርፈ ለሌሎች ሕልውና ነጻነትና ደኅንነት አንዲት መተኪያ የሌላት ነፍሳቸውን መሥዋዕት ለማድረግ ቆርጠው በመሰለፍ ዋጋ መክፈላቸውን እያወቅን፤ እኛ ይሄ ግፍ እየተፈጸመብን ለራሳችን ህልውና ነጻነትና ደኅንነት ዋጋ ለመክፈል ካመነታን ወደኋላ ካልን ይሄ በድን ሬሳ ካላስባለ ሌላ ምን ሊያስብል ይችላል? ለሆድህ ስትል ሆድህ አምላክህ ሆኖብህ የምትሸሽ ካለህ መብላት የምትችለው ስትኖር ነውና እንዳትኖርም ደግሞ አማራ በመሆንህ ምክንያት ብቻ እየታደንክ እንድትጠፋ ተፈርዶብሀልና ሆዳም ሆይ! እባክህን ሆድህን ምክንያት አታድርግ፡፡

ጥቂት የማንባል የአማራ ተወላጆች አጋንንቶቹ የጥፋት ኃይሎች በአማራ ተወላጆች ላይ የፈጸሙትንና እየፈጸሙት ያሉትን አረመኔያዊ ጥፋት አለመስማታችን አማራ በመሆን ብቻ እየተፈጸመ ካለው መጠነ ሰፊ አረመኔያዊ ጥቃት ሰለባነት ወይም ተጠቂ ከመሆን ያድነን ይታደገን ይመስል ጉዳዩ ሲወራ ላለመስማት እንሸሻለን እንጅ የራሳችኑ ጉዳይ እንደመሆኑ በንቃት ትኩረት ሰጥተን የት ቦታ ምን እየተደረገ እንዳለ በመከታተል ለመፍትሔው አንታትርም፡፡ ብዙዎቹም ይሄንን አደጋ ለመቀልበስ ከመታገል ይልቅ አማራነታቸውን መካድ መፍትሔ አድርገውታል፡፡ ይሁንና እነኝህ አማራነታቸውን የካዱ ወገኖች በአንድም በሌላም መንገድ አማራ ወይም የአማራ ደም ያለባቸው መሆኑ እየታወቀባቸው ለጥቃት ሲዳረጉ ዓየን እንጅ አማራነታቸውን መካዳቸው ከጥቃት ሲታደጋቸው ዓላየንም፡፡ ምንም ይምጣ ምን ማንነትን መካድ እራሱ እጅግ ወራዳና ነውረኛ የለፈስፋሶች ተግባር ነው፡፡

በመሆኑን መፍትሔው ወገብን አስሮ በቁርጠኝነት በጋለ ወኔና ጀግንነት አራዊቶቹን ታግሎ መጣልና መቅጣት ነው እንጅ ክህደት አይደለምና ለዚሁ ቆራጥ እርምጃ የበርካቶችን ነፍስ የሚያስበላ ሌላ ተጨማሪ ጊዜ ሳናባክን አጋንንቶቹን በተለያየ የትግል ስልት ለመታገል  በፍጥነት ቆርጠን እንነሣ!!!

ከዚህ ቀደም አነኚህ ሁሉ በ21ኛው መቶ ክ/ዘ ፈጽሞ የማይጠበቁ አረመኔያዊ ግፎች ሲፈጸሙ ፈተናው በሚጠይቀው ጥንካሬና ቁርጠኝነት በመነሣሣት ተገቢውን የተጠናከረ ተቃውሞ አለማሰማታችን የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በግድ እንዲያውቀው ዐውቆም እንዲያወግዘውና እርምጃ እንዲወስድበት አለማድረጋችን ይህ አረመኔያዊ ግፍ እስከአሁንም እንዲቀጥል ምቹ ዕድል ሰጥቷል፡፡

ወገን ሆይ! ስለ ዲሞክራሲ (መስፍነ ሕዝብ) ሥርዓት መመሥረት መታገሉን ምንንትስ እርሱት፡፡ በአሁኑ ሰዓት ይሄ ዓይነት ትግል ለአማራ ሕዝብ ሲበዛ ቅንጦት ነውና፡፡ መጀመሪያ በገዛ ሀገርህ አማራ በመሆንህ ብቻ እንደ አውሬ በየትም ቦታ እየታደንክ ከመታረድ ከመቃጠል ከመሳደድ ወጥተህ እንደሰው የመኖር መብትህን አረጋግጥ!!

በዚህ መጽሐፍ የተዘረዘሩ ግፎችን ስንመለከት ወያኔ ኦነግና ሌሎች የጥፋት ኃይሎች እንደ አኖሌ ያሉ የፈጠራ ስም የማጥፋት ክሶችን እውነት እያስመሰሉ ለምን እየፈጠሩ እንደሚያናፍሱና እንደሚያራግቡ በሚገባ ግልጽ ይሆንለታል፣ የጥፋት ኃይሎቹ እጅግ አስገራሚ በሆነ ሁኔታ በምን ያህል ደረጃ ደንቆሮዎች, የማሰብ ችሎታቸው እጅግ የተገደበና ኃላፊነት የሚባል ነገር ቅንጣት ታክል እንኳ የማይሰማቸው መሆናቸውን  ይረዳል፡፡ ምክንያቱም ይሄንን አረመኔያዊ ግፍ በዚህን ያህል ስፋትና ጥልቀት በደል በሌለባቸው ወገኖች ላይ አማራ መሆናቸውን ብቻ ወንጀል አድርገው ጥቃቱን ሲፈጽሙ ወደፊት እነሱን ምንም ዓይነት ዋጋ ሳያስከፍላቸው የአንድ ሰሞን ተራ ወሬ ሆኖ የሚቀር ተራ ነገር እንደሆነ አድርገው ያስባሉና ነው፡፡

ይሄንን ባለፉት 25 ዓመታት በአማራ ሕዝብ ላይ የተፈጸመውን በመጽሐፉም ውስጥ የተገለጸውን በታሪክ ጨካኝና አረመኔያዊ ግፍ በሕዝባችን ላይ ፈጽመዋል የተባሉት ፋሺስት ጣሊያን፣ ግራኝ አሕመድና ዮዲት ጉዲት እንኳን ፈጽሞ ያልሞከሩትን ሰው የአንድ ዘር አባል (አማራ) በመሆኑ ብቻ ሰብአዊና የዜግነት ክብሩን እጅግ ከተዳፈረው፣ ሥነልቡናን እጅግ ከሚያውከው፣ ጭንቅላትን እጅግ ከሚያደማው በርካታ የበደል ዓይነቶች አንሥቶ ፈጽሞ ለማመን በማይቻል ደረጃ እንደበግ ታርዶ ኩላሊቱና ጉበቱ በሚጥሚጣ እየተጠቀሰ እስከመበላት ድረስ በሰው ልጆች ታሪክ ታይተውና ተሰምተው የማያውቁ የግፍ ዓይነቶች መፈጸሙን ስመለከት እጅግ ግርም የሚሉኝ ሰባት ነገሮች አሉ፡፡

1ኛ. ይህ አማራን ከሀገር መንጥሮ የማጥፋት እርምጃ ወያኔ ክልል ብሎ በሚጠራቸው የሀገሪቱ የግዛት አሥተዳደሮች ሁሉ በሱ ትዕዛዝ ይህ ሁሉ ግፍ በአማራ ማኅበረሰብ ላይ ሲፈጸም በወያኔና ግብረ አበሮቹ ቀስቃሽነት አነሣሽነት ገፋፊነት አቀነባባሪነት አደራጅነት ካልሆነ በስተቀር በእየአካባቢው  ሕዝብ የራስ ተነሣሽነት የተፈጸመ አለመሆኑ፡፡

2ኛ. በእነዚያ ወያኔ ክልል በማለት በሚጠራቸው የሀገራችን ክፍሎች ያለቀው የአማራ ማኅበረሰብ ሊያርዱት፣ ገደል ሊወረውሩት፣ ሊረሽኑት፣ ሊያቃጥሉት እየወሰዱት ወይም እያጎሩት እንደሆነ እያወቀ ሦስትና አራት ቦታዎች ላይ ከተደረገው በስተቀር በአልሞት ባይ ተጋዳይነት መንፈስ ወይም “ሞቴ ካልቀረ ጠላቴን ይዠው ልሙት!” በሚል መንፈስ አንገቱን እያነቁም ይዘውት አብረው ገደል እየተወረወሩም መሞት ሲገባቸው ለመሥዋዕት እንደሚነዳ በግ ዝም ብለው መታረዳቸው፣ ገደል መወርወራቸው፣ መረሸናቸው፣ መቃጠላቸው፡፡

3ኛ. ይሄ ሁሉ ሕዝብ “አማራ ነህ!” ከሚለው ምክንያት በተጨማሪ በክርስቲያንነቱ ከነ አብያተክርስቲያናቱ እየተቃጠለ፣ እየታረደ፣ እየተሠየፈ ሲፈጅ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን እንደተጠቂነቷና ጉዳዩ በቀጥታ እንደሚመለከተው አካል ለአንድም ጊዜ እንኳ ጠንካራ የአቋምና የኃዘን መግለጫ አሰምታ አለማወቋ ጉዳዩንም አለመከታተሏ፡፡

እርግጥ ነው በዚህ 25 ዓመታት የቤተክርስቲያኗን የሥልጣን ቦታዎች በየእርከኑ የወያኔ የውሸት ካህናት ተቆጣጥረው እንደያዙት ግልጽ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ይህን ዓይነት እርምጃ ቤተክርስቲያን ትወስዳለች ብሎ ማሰብ ፈጽሞ የማይታሰብ የማይጠበቅም ነው፡፡ ይሁን እንጅ የወሳኝነት የሥልጣን ቦታ አይሁን እንጅ የአገልግሎት የሥልጣን ቦታ ላይ ከጵጵስና እስከ ዲቁና ያሉ በርካታ የአማራ ተወላጆች አሉ አይደለም ወይ? (ጉዳዩ በቀጥታ የአማራ ተወላጆችን ይመለከታል ለማለት ነው እንጅ ይሄንን አረመኔያዊ ግፍ ማውገዝስ የሁሉም ሰው ግዴታ ነበር፡፡)

እናም እነኝህ ሰዎች እንደእረኝነታቸው በግልም  ይሁን በቡድን ምን ያደረጉት ነገር ነበር? “ስለበጎችህ ቤዛ እራሴን አሳልፌ እሰጣለሁ!” ብለው በክርስቶስ ፊት ቃል ገብተው የእረኝነትን ሥልጣን ከተቀበሉ በተለይም “መነኮስኩ ነገንዠ ሞትኩ!” ካሉ በኋላ ምን የሚያስፈራቸውና ወደኋላ የሚስባቸው ነገር ኖሮ ነው ለክርስቶስ የገቡትን ቃልና ክርስቶስ የጣለባቸውን አደራ እየበሉ ጭጭ ያሉት?

“ምእመናን በአብያተክርስቲያናት ውስጥ እየታጎሩ ተቃጠሉ፣ ተመንጥረው በመጨፍጨፋቸው ይኖሩበት የነበረው ሀገር ወና ሆነ አብያተክርስቲያናቱንም አሕዛቡ አረማዊያኑ ከመዘበሯቸው በኋላ ጫት ማመንዠኪያቸው አደረጓቸው!” የሚለው ለሚሰማው ሁሉ ጆሮዎቹን ጭው የሚያደርግ የቤተክርስቲያን ታላቅ መርዶ ያልገደደው፣ ያልተሰማው፣ ኃላፊነቱንና ግዴታውንም ለመወጣት ያልቻለ እረኛ “እረኛ ነኝ!” ብሎ አፉን ሞልቶ ያወራል??? አደራቹህን! ሥራቹህ ቁልጭ አድርጎ እንደሚመሰክርባቹህ እናንተ ምንደኞች እንጅ እረኞች አይደላቹህምና ተሳስታቹህም እንኳ ቢሆን “የመንጋው እረኞች፣ የቤተክርስቲያን ጠባቂ ነን!” እንዳትሉ! የምታመልኩትም የምታገለግሉትም ሆዳቹህን እንጅ እግዚአብሔርን አይደለምና ይሄን ትሉ ዘንድ በፍጹም በፍጹም የተገባቹህ አይደላቹህም!

4ኛ. ምንም እንኳን ብአዴን ትግሬ ተሰግስጎ የሞላበት የወያኔ አሻንጉሊት ድርጅት ቢሆንም ያሉትንም ያህል ቢሆን የአማራ ተወላጅ የሆኑ ወይም ነን የሚሉም በሽዎች የሚቆጠሩ አሉና እነኝህ ሁሉ እያሉና ድርጅቱ “ለአማራ ሕዝብ መብት ነፃነት ህልውናና ጥቅም የቆምኩ ነኝ!” ብሎ እየለፈፈ እያለ በተባባሪነትና በቀጥታ ተሳታፊነት በአማራ ሕዝብ ላይ ሲፈጸም በቆየውና እየተፈጸመም ባለው የዘር ማጥፋትና ማጽዳት በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸም ከፍተኛ ወንጀል ውስጥ መገኘታቸው፡፡

መቸስ ትንግርት ነው! ሰው ራሱን ይበላል? እጅግ የሚያስገርመው ነገር ደግሞ ብአዴን ይሄንን እያደረገ ያለው ወያኔ ሌት ተቀን ለሚደክምለት ለትግሬ ሕዝብ ጥቅም መሆኑ ነው፡፡ “የብአዴን አማሮች የገዛ ሕዝባቸውን ለትግሬ ጥቅም ሲሉ ይፈጃሉ ያስፈጃሉ!” ሲባል እንዴት ሊሆን እንደቻለ በጣም ግራ አይገባቹህም? እጅግ አይደንቃቹህም? አሁን እነዚህ ብአዴን ውስጥ ያሉ አማሮች ሰው ነን ብለው ሳያፍሩ ከሰው ፊት ይቀርባሉ? እንደሚቀርቡማ ዕለት ዕለት ዕያየናቸውም አይደል! ግን ምን ጉድ ፍጥረቶች ቢሆኑ ነው? እውነት ግን እንደኛ ሰዎች ናቸው? ምንድን ነው እንደዚህ ተናጋሪ ዕቃ ወይም ተናጋሪ እንስሳ ሊያደርጋቸው የቻለው? ዕቃ ወይም እንስሳ ብቻ ነው ለምን? እንዴት? ሳይል እንዲያደርግ ያስደረጉትን ነገር ዝም ብሎ የሚያደርገው፡፡

ከዚህ ቀደም የብአዴኑ አቶ ታምራት ለዓይኔ ምን ብሎ ቀስቅሶ የአማራን ሕዝብ እንዳስፈጀው እናውቃለን፡፡ በዚህ መጽሐፍ ላይ ደግሞ ሌላኛው የብአዴን ባለሥልጣን የዛሬው ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ደመቀ መኮንን 1983/84ዓ.ም. ላይ መንታ ውኃ አካባቢ ሰዎችን አደራጅቶ በአብዛኞቹ የመተከል ሰፋፊ ጫካዎች ውስጥ ከ50 እስከ መቶ እርምጃ ልከ እምብርት (ራዲየስ) ርቀት ውስጥ ሲያንስ በአንድ ሲበዛ በበርካታ የአማራ ተወላጆች አስከሬን እንዲሞሉ ያደረገ፣ 1986ዓ.ም. ፓዊ በገበያ ቀን ሀገር ሰላም ብሎ በደራ ገበያ ሲገበያይ የነበረን በሽዎች የሚቆጠርን የአማራ ሕዝብ በድንገት ዙሪያውን አስከብቦ በመትረጊስ እርምት አድርጎ በማስፈጀት ገበያ የነበረውን ሜዳ ወደ የሰው ቄራነት በመቀየር በአስከሬን ቁልልና በሕዝብ ደም ኩሬ ማጥለቅለቁ በድፍን የመተከል የቻዌ ነዋሪ ይታወቃል፡፡

አቶ ደመቀ መኮንን አማራ ነው ይባላል፡፡ ከሆነ እሱና ያንን እልቂት የፈጸሙት ጓዶቹ እንዴት በገዛ ወገናቸው ላይ ምንም በደል ሳይኖርበት የእነሱን አማራነት የት ጥለውት ነው አማራነቱን ወንጀል አድርገው እንዲህ ሊፈጁት የቻሉት? ዘር ደም ከሆነ ብአዴኖች የአማራነት ደማቸውን እንዴት አድርገው ቀድተው ደፍተው ቀይረውት ነው አማራነትን ወንጀል አድርገው እንዲህ ሕዝብ ለመፍጀት የበቁት? በገዛ ወገናቸው ላይ እንዲህ ዓይነት ክሕደት ፈጽመው የፈጁ ሰዎች በደም ለማይዘመዳቸው ለማይመስላቸው ለራሱ ለወያኔ (ለትግሬ) እንዴት ነው ታማኝ ሊሆኑ የቻሉት??? ይሄ የሆነው በአንዳች መተት ወይም አጋንንታዊ ኃይል ካልሆነ በስተቀር አንድን ሰው ለራሱ ለሥጋው ለወገኑ ያለውንና ሊኖረውም የሚገባውን አግባብነት ያለው ተቆርቋሪነትን አጥፍቶ፣ ሚዛናዊ አመለካከቱን አዛብቶ እንደ ዕቃ ወይም ሮቦት (ምስለ ፍጡር) እንደፈለጉ እያሽከረከሩ “ለምን? እንዴት?” ሳይል እንዲህ ዓይነት አረመኔያዊ ድርጊት በገዛ ወገኑ ላይ በግፍ እንዲፈጽም ማድረግ እንዴት ነው የቻሉት???

ብዙዎቻቹህ “ኧረ ባክህ! የምን መተት ነው ደግሞ? ሰዎቹ ከልክ በላይ ራሳቸውን ስለሚወዱ ለግል ጥቅማቸው ብቻ ስለሚያስቡ ነው!” ትሉኝ ይሆናል፡፡ ለእኔ ግን ይሄ አሳማኝ ምክንያት አይደለም፡፡ ምክንያቱም ሀገርና ወገን በሌሉበት ሁኔታ እኮ “እኔ” ማለትና የግል ጥቅም የሚባል ነገር እኮ ሊኖር አይችልም! በእርግጥ ይሄው በሰዎቹ ላይ እያየን እንዳለነው ለጊዜው ሊመስል ይችላል፡፡ ስር መሠረትና ዘለቄታዊነት ግን አይኖረውም፡፡

“የሰው ልጅ ማኅበራዊ ፍጡር ነው!” ይባላል፡፡ ትክክልም ነው፡፡ የሰው ልጅ “እኛ” ማለት ካልቻለ “እኔ” ብሎ መኖር ፈጽሞ አይችልም! እኛ ሲል ደግሞ እኛ ሊል የሚገባው ሀገርንና ሕዝብን በፍትሐዊነት ተጠቃሚ ማድረግን መሠረት በማድረግ ካልሆነ በስተቀርና “እኛ” የሚለው ሰው የሱን ቢጤዎች አራዊት ሰብስቦ እነሱን እያሰበ ከሆነ ገና “እኛ” ማለት አልጀመረም፡፡ “እኛ” የሚሉ መሰላቸው እንጅ “እኔ” ነው እያሉ ያሉት፡፡

የሰው ልጅ “እኛ” ማለት ካልቻለ በስተቀር ለአንዲት ነፍሱ ሳይሳሳ የሚሠዋላት የጋራ ሀገር ሊኖረው አይችልም! የሰው ልጅ ራሱን ሲወድ ጥሩ ነው፡፡ ያኔ ነውና “እኛ” ማለት የሚችለው፡፡ “እኛ” ማለት ሳይችል ያለሥጋትና አደጋ የሚወደውን እራሱን ተጠቃሚ ማድረግ እንደማይችል ጠንቅቆ ያውቃልና ነው ማኅበራዊ ሰላሙ “እኔ” በሚሉ ከመታወኩ ነጻ ሆኖ ባያውቅም “እኛ” በማለት የጋራ ሀገር መሥርቶ አብሮ ለመኖር የቻለው፡፡

በመሆኑም ይህ የብአዴን ሰዎች ችግር የራስ ወዳድነት ችግር አይደለም፡፡ ምንድነው ታዲያ? ካላቹህኝ፦ ሌላ ምንም ሳይሆን በሆዳምነታቸው ላይ እጅግ ከባድ የሆነ  የአእምሮ፣ የአስተሳሰብ፣ የሥነ ልቡና መታወክና መዛባት ችግር (Mental & Psychological disorder) ያለባቸው ስለሆኑ ነው፡፡ ለዚህም ነው ባደረጉትና በሚያደርጉት ኢሰብአዊ ግፍ ሁሉ እንደ ሰው ቅንጣት ታክል እንኳ የማይሰማቸው፣ የማያሳስባቸው፣ የማይገዳቸው፣ ኃላፊነት የማይሰማቸው ሊሆኑ የቻሉት፡፡ ራሳቸው፣ የሚያገለግሉት ወያኔ፣ የኢትዮጵያም ሕዝብ ተጠቃሚ የማይሆኑበትን ተግባር ታጥቀው እየፈጸሙ ያሉት፡፡

5ኛ. ይህ ሁሉ አረመኔያዊ የዘር ማጥፋትና ማጽዳት በዚህ ክ/ዘ ይፈጸማል አይደለም ይታሰባል እንኳ የማይባል እጅግ አደገኛው በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸም ወንጀል እራሱን “የኢትዮጵያ መንግሥት ነኝ!” ባለ ኃይል አደራጅና አቀነባባሪነት ያለማሰለስ በስፋት ላለፉት 25 ዓመታት ያህል ሲፈጸም ምሁራኑ በተለይም የአማራ ምሁራን በግልም ይሁን በመደራጀት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማጋለጥንና ጉዳዩ የሚገባውን ትኩረት እንዲያገኝ ማድረግን ጨምሮ ሊያደርጉት የሚገባቸውን ሁሉ አለማድረጋቸው፡፡

እርግጥ ነው የቀድሞው ኢሰመጉ የአሁኑ ሰመጉና ሌሎች ተመሳሳይ ድርጅቶች ላስተማራቸው ሕዝብና ሀገር የሚጠበቅባቸውን ለማበርከት የሚጥሩ ምሁራን ፍሬዎች መሆናቸውን እረዳለሁ፡፡ ይሁንና ግን እነኝህ ድርጅቶች ያለብንን ፈተና በሚመጥን ጥንካሬ ትጋትና ቁርጠኝነት ነው ወይ እየሠሩ እየታገሉ ያሉት? እንዳልሆነ ሁላችንም እናውቃለን፡፡

አሁንም እርግጥ ነው መጽሐፍ በመጻፍ፣ ይህን የዘር ፍጅት የPHD (የሊቀ ጥብና) ትምህርታቸው የመመረቂያ ጽሑፍ ርእሰ ጉዳይ በማድረግና በሌሎችም መድረኮች ሦስት አራት የሚሆኑ ምሁራን ይሄንን የወያኔን አረመኔያዊ ተግባር ያጋለጡ አሉ፡፡ ሊመሰገኑም ይገባል፡፡

ነገር ግን ይሄ ሕዝብ ያስተማረውና ኃለፊነቱም ያለባቸው እነዚህ ብቻ ናቸው ወይ? የተቀረውስ? በእውነት በእውነት ምሁሩ ክፍል በዚህ ጊዜ የማይሰጥና አንገብጋቢ ጉዳይ ላይ የሚጠበቅበትን ርብርብ አለማድረጉና ዝም ጭጭ በማለቱ የወገኑ ደም ዕዳ አለበት! ለምንስ ጭጭ አላቹህ? እንዴት ነው ታዲያ እናንተ ያዳፈናቹህትን ያልተናገራቹህትን ባዕዳኑ እንዲጮሁት እንዲያስተጋቡት ልንጠብቅ የምንችለው? ከቶ እንዴትስ አስቻላቹህ? እንቅልፉስ እንዴት ተተኛላቹህ? እህልስ እንዴት ተበላላቹህ? ይሄ ድሀ ሕዝብ በድህነት አቅሙ ሳይማር እናንተን አስተምሮ ለዚህ ካበቃበት ዐበይት ምክንያቶች አንዱ ለእንደዚህ ዓይነቱ ክፉ ቀን እንድትደርሱለት ነበር እንጅ ወደ አደጉ ሀገራት ጣጥላቹህት እየሔዳቹህ እራሳቹህን በምቾት እያኖራቹህ እንድትረሱት ወይም ከንፈር እንድትመጡለት ነው ወይ???

6ኛ. የተባበሩት መንግሥታት፣ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችና ኃያላን መንግሥታት ይህ በዚህ ዘመን ይሆናል ተብሎ በፍጹም የማይታሰብ አረመኔያዊ የዘር ማጥፋትና ማጽዳት በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸም የመጨረሻ ወንጀል መንግሥት ነኝ በሚል አካልና አጋሮቹ በተለያዩ ቦታዎች ትናንትና እስከሸኘነው 2008ዓ.ም. ድረስ በአማራ ሕዝብ ላይ በስፋት ሲፈጸም እንደቆየና እየተፈጸመም እንዳለ እያወቁ መረጃዎች በሚገባ እያሏቸው ለእንዲት ጊዜም እንኳ ቢሆን መግለጫ አውጥተው አለማውገዛቸው፡፡

መረጃው ስለሌላቸው ስላልሰሙ እንዳይመስሏቹህ እንዳላዩና እንዳልሰሙ ሆነው ዝም ጭጭ ያሉት፡፡ እነኝህ ዓለም አቀፍ አካላት በወያኔና በሌሎቹ የጥፋት ኃይሎች በአማራ ዘር ላይ ለተፈጸመችው ለእያንዳንዷ የዘር ማጥፋትና ማጽዳት ወንጀል መረጃው በሚገባ እንዳላቸው መቶ በመቶ እርግጠኛ ነኝ፡፡ እነሱ እንኳንና በብዙኃን መገናኛዎች ሳይቀር በተደጋጋሚ የተዘገበባቸውን የአደባባይ ምሥጢሮች ይቅርና ወያኔ ተቃዋሚዎችን ለመወንጀል እያጠመደ ያፈነዳቸውንና ንጹሐንን የፈጀባቸውን የፈንጅ ጥቃቶች ሳይቀር ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ እኛ ዜጎች በሀገራችንና በራሳችን ላይ መፈጸሙን ፈጽሞ የማናውቀውን ስንት የተሠወረ ጉድ ሁሉ በሚገባ ያውቃሉ፡፡

እነሱ ሰሜን ኮሪያ፣ ኤርትራ፣ ሶሪያ፣ ቻይና፣ ኢራን ምንትስ እያሉ “በዓለማችን ላይ የሰብአዊ መብቶች እጅግ የሚጣስባቸው ሀገራት!” እያሉ ያብጠለጥላሉ እንጅ የሁሉም ግፍ ቢደመር ወያኔ የፈጸመውን ቅንጣት እንደማያክል በሚገባ ያውቃሉ፡፡ እነኝህ ከላይ የተጠቀሱት ሀገራት ፈጸሙ የተባሉት ወንጀል የሰብአዊ መብት ጥሰት ነው፡፡ ወያኔ ግን የፈጸመውና እየፈጸመው ያለው በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸመውን የመጨረሻ ወንጀል የዘር ማጥፋትና ማፅዳት ወንጀልን ነው፡፡ በመሆኑም በዚህች ዓለም ላይ ፍትሕና ርትዕ ቢኖር ኖሮ በዚህች ዓለም የወያኔን ያክል የሚወገዝና እርምጃ የሚወሰድበት አገዛዝ ከቶውንም ባልነበረ፡፡

“እና ታዲያ እነዚህ ምዕራባውያን መንግሥታት በተለይም የተባበሩት መንግሥታትና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ለሰብአዊ መብቶች መጠበቅ ቆመናል! እያሉ በዚህ ዘመን ፈጽሞ የማይጠበቀውን የወያኔን አረመኔያዊ ወንጀል ካወቁ ለምንድነው የማያወግዙትና እርምጃስ የማይወስዱበት?” ካላቹህኝ ኃያላኑ ሀገራት እስከዛሬ በወያኔና አጋሮቹ በይፋ የሚደረገውን የዘር ማጥፋትና ማጽዳት ወንጀል አለማውገዛቸውንና ለማውገዝም አለመፈለጋቸውን በምናይበት ጊዜና ወያኔም በአቶ አቦይ ስብሐት በኩል ያለአንዳች የተጠያቂነት ስሜትና ፍርሐት በአደባባይ “የአማራንና የኦርቶዶክስን አከርካሪ እንዳያንሰራራ አድርገን ሠብረናል!” ብሎ መናገሩን ስንመለከት ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየታተሙ በሚወጡ መጻሕፍት ላይ “ኃያላኑ ሀገራትና ወያኔ በአውሬው 666 የዲያብሎስ መንፈስ እየታዘዙና እየተመሩ ይሄንን ወንጀል በሀገራችንና በሃይማኖታችን ለመፈጸም በርትተው እየሠሩ ነው!” በማለት የሚያቀርቡትን ክስ እንድናምን ያስገድደናል፡፡

ይህ የመጻሕፍቱ ክስ እውነት ሆነም አልሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት የጀርባ አጥንት የሆነው የአማራ ሕዝብ ጉልበቱን እግዚአብሔርን አድርጎ ውጊያውን መዋጋት ግዱ መሆኑን ጠንቅቆ ሊያውቅ ይገባል፡፡ እዚህ ላይ ምንም ዓይነት መዘናጋት እንዳይኖር እጅግ ጥንቃቄ እንዲደረግ አጥብቄ ማሳሰብ እወዳለሁ፡፡ እርግጥ ነው በእርኩሰት ተዳድፈን ለይስሙላ በዘልማድ ካልሆነ በስተቀር እንደቀድሞው ከልብ በንጽሕናና ቅድስና በሚደረግ አገልግሎትና አምልኮ ከእግዚአብሔር በመራቃችን እግዚአብሔር ለዚህ ውርደት ስብራትና ጥፋት አጋልጦናል፡፡ እነኛ አብያተክርስቲያናት በአረማውያኑ ሲቃጠሉ ሲፈርሱና አሕዛብ አረማውያኑ የጫት ማመንዠኪያ ስፍራቸው ሲያደርጓቸው የተደፈረው ክብር የእሱም መሆኑን እግዚአብሔር አጥቶት አይደለም እንደማያይና እንደማይሰማ በዝምታ እየተመለከተ ያለው፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔርን አሕዛብ አረማውያኑን በደል እንደፈጸሙ እንዲቀስፍ እንዲበቀላቸው ወይም ደግሞ ምንም እንዳልተፈጠረ ዝም ብሎ እንዲመለከት የሚያደርገው የእኛው ሥራ ነው፡፡

የካህኑን የዔሊንና የልጆቹን የአፍኒንና የፊንሐስን ሥራ አስታውሱ፡፡ 1ኛ ሳሙ. ከም. 2-4 የእነሱ መበደል ታቦተ ጽዮን በአሕዛብ እጅ እንድትማረክ፤ ወስደውም እንደምናምንቴ በጣኦት ቤታቸው ከጣኦታቸው ስር እንዲወረውሯት፣ እስራኤላውያንም በጦርነቱ እንዲሸነፉና እንዲዋረዱ እንዲደቆሱም እንደዳረጋቸው አስታውሱ፡፡

እኛም በራሳችን ላይ እየደጋገምነው ያለነው ይሄንን ታሪክ ነው፡፡ እግዚአብሔር የሚፈልገው ንጹሕ እኛነታችን ነው እንጅ ከረከሱ እጆች የሚበረከት ገንዘባችንን አይደለም፡፡ እራሳችንን ሳንቀድስ እያሳመፅንና እያረከስን ሕንፃ ቤተክርስቲያኑን በግንብ አይደለም በዕንቁ እንኳ ብንሠራለት ለእሱ ምኑም አይደለም! አይደሰትበትምም፡፡ እንዲያውም አጥፊ ያዝበታል፡፡ ነገር ግን እንዳስቻለን መጠን እራሳችንን ቀድሰን ሕንፃ ቤተክርስቲያኑን ወይም የእግዚአብሔርን ቤት በጭራሮ እንኳን ብንሠራው ለእሱ በዕንቁ ከተሠራም በላይ ነው፡፡ ይሄንን ልብ ልንል ይገባል፡፡

ካልሆነ ግን እሱ ምንጊዜም ቢሆን የዐመፃን ዋጋ ከመክፈል ወደ ኋላ አይልም፡፡ ቃሉም እንደሚል “እሽ ብትሉ ለኔም ብትታዘዙ የምድርን በረከት ትበላላቹህ እንቢ ብትሉ ግን ብታምፁም ሰይፍ ይበላቹሀል” ትን.ኢሳ. 1፤19-20 እንዳለው ይህ ሁሉ ጉድ የመጣብንና የተሰበርነው እንቢ በማለታችን በማመፃችን መሆኑን መገንዘብ ይገባናል፡፡

መቀጣታችን ሌላም ዐቢይ ምክንያት አለው ቃሉ እንዲህ ይላል “ልጀ ሆይ የጌታን ቅጣት አታቃልል በሚገሥጽህም ጊዜ አትድከም ጌታ የሚወደውን ይቀጣዋልና የሚቀበለውንም ልጅ ሁሉ ይገርፈዋል፡፡ ብሎ የሚነጋገረውን ምክር ረስታቹሀል፡፡ ለመቀጣት ታገሡ እግዚአብሔር እንደ ልጆች ያደርጋቹሀልና፡፡ አባቱ የማይቀጣው ልጅ ማን ነው? ነገር ግን ሁሉ የቅጣት ተካፋይ ሆኗልና ያለ ቅጣት ብትኖሩ ዲቃሎች እንጅ ልጆች አይደላቹህም፡፡ ከዚህም በላይ የቀጡን የሥጋ አባቶች ነበሩን እናፍራቸውም ነበር እንዴትስ ይልቅ ለመናፍስት አባት አብልጠን ልንገዛና በሕይዎት ልንኖር በተገባን? እነሱ መልካም ሆኖ እንደታያቸው ለጥቂት ቀን ይቀጡን ነበርና እርሱ ግን ከቅድስናው እንድንካፈል ለጥቅማችን ይቀጣናል፡፡ ቅጣት ሁሉ ለጊዜው የሚያሳዝን እንጅ ደስ የሚያሰኝ አይመስልም ዳሩ ግን በኋላ ለለመዱት የሰላምን ፍሬ እርሱም ጽድቅን ያፈራላቸዋል” ይላል ቃሉ ዕብ. 12:5-11፡፡

“የእስራኤል ልጆች ሆይ! እናንተ ለእኔ እንደ ኢትዮጵያ ልጆች አይደላቹህምን? ይላል እግዚአብሔር” ትን. አሞ. 9፤7 በመሆኑም እኛ ኢትዮጵያዊያን ልጆች እንጅ ዲቃሎች አይደለንምና ምንም ቢበድሉ የቱንም ያህል ቢረክሱ ቢያምፁበትም ምንም እንደማይላቸው እንደ ሌሎች ሀገራትና ሕዝቦች ዝም አይለንም፡፡ እሽ እስክንልና እስክንመለስ ድረስ ይቀጣናል እንጅ፡፡ ስለሆነም ትቶ ላይተወን ነገር እሱን “እሽ!” ካለማለት በስተቀር ሌላ ምንም መፍትሔ የለንምና እሽ እንበል! ንስሐ እንግባ! ወደ እግዚአብሔር እንመለስ! ከዚያ እንደ እናት አባቶቻችን ለእግዚአብሔር ታምነን ስሙን ጋሻና ጦራችን አድርገን ያለብንን ውጊያ እንዋጋ በእኛና በጠላቶቻችን መሀከል ያለው የኃይል አሰላለፍ ልዩነት የሰማይና የምድር ያህል ርቀት ቢኖረውም እንኳ ያለጥርጥር እናሸንፋለን!!!

7ኛ. የወያኔ የኦነግና የሌሎች የጥፋት ኃይሎች ድንቁርና፡፡ እነኝህን ሰዎች ሳስብ ዓለም እንደዛሬው አንድ መንደር ሆና በአንደኛው የዓለም ጫፍ የተደረገው በሌላኛው የዓለም ጫፍ ላለው ምን እየተደረገ እንዳለ በዓይን ቅጽበት በሚታወቅበት ዘመን ሳይሆን ጥንት ሥልጣኔ ባልነበረበትና አንዱ ስለሌላው መረጃ በማያገኝበት ዘመን ላይ ይሄንን ሥልጣን የያዙ ሆነው ቢሆን ኖሮ ምን ሊያደርጉን ይችሉ እንደነበር ሳስብ በጣም ያስፈራኛል፡፡ እርግጥ ነው ወያኔ “መረጃ በዓይን ቅጽበት ከአንዱ የዓለም ጫፍ ወደሌላው በሚደርስበት ዘመን ላይ ነው ያለሁትና” ብሎ ምንም ነገር ከማድረግ አልተቆጠበም፡፡ ይሁንና ግን ይሄንን ሁሉ ጉድ ስናይ “በዚህ ዘመን ይሄንን ያደረገ በዚያ ዘመን ቢሆን ኖሮስ ምን ሊያደርግ ይችል ነበር?” ያሰኛል፡፡ አንድ ሰው ወይም ቡድን ኃላፊነት ተጠያቂነት ሰብአዊነት የማይሰማው፣ ነገን የማያስብ ሆኖ ካገኛቹህት ምንም ስለሆነ እንዳይመስላቹህ! ደንቆሮ ስለሆነ ብቻና ብቻ ነው፡፡ የድንቁርናቸው ድድርናና ጥልቀት እንደየሚሠሩት አውሬአዊ ተግባሮቻቸው ይወሰናል፡፡

ወያኔ ኦነግና ሌሎች የጥፋት ኃይሎች ይሄንን የዘር ማጥፋትና ማጽዳት ወንጀል በአማራ ሕዝብ ላይ ሲፈጽሙ በየቦታው የሚሰጡት ምክንያት የተለያየ ነው፡፡

ወያኔ ኦሮሚያ ብሎ በከለለው አካባቢ የሚጠቀሰው ምክንያት፦ “እናንተ የምኒልክ ዘሮች ናቹህ! ምኒልክ አሩሲ ሔጦሳ ላይ የወገኖቻችንን እጅና ጡት ቆርጧል!” የሚል ምንም ዓይነት መረጃ የሌለው ፋሽስት ጣሊያን “ልመሠርተው ያሰብኩትን ቅኝ አገዛዝ ያከሽፍብኛል!” ብሎ የፈራውን አማራን ለማስጠቃትና የሕዝቡን አንድነት ፈረካክሶ ለማዳከም ሆን ብሎ ፈጥኖ ያወራውን በጊዜውም ተሳክቶለት በአማራ ላይ ብዙ ግፍ እንዲፈጸምበት ለማድረግ አስችሎት የነበረውን የፈጠራ ወሬ ይዘው “እንበቀላቹሀለን!” በማለት እንደሆነ ይነገራል፡፡ ይሁንና አሁን አሁን እንኳ ይህ ወሬ ነጭ ውሸትና ፈጠራ መሆኑንና ወያኔና ኦነግ ለተመሳሳይ ዓላማ ከፋሺስት ጣሊያን ተውሰው ያመጡት የፈጠራ ወሬ መሆኑን እኛ ብቻ ሳንሆን የኦሮሞ ምሁራንም ሳይቀሩ ያረጋገጡት ሀቅ በመሆኑ ይሄንን ፈጠራ ምክንያት ማድረግ አይቻልም፡፡

ሌላኛው ወያኔ ኦሮሚያ ሲል በከለለው የሀገራችን አካባቢ የሚጠቀሰው ምክንያት ደሞ “አኛ የሀገሩ ሰዎች ደሀ ሆነን እያለ እናንተ ያለሀገራቹህ መጥታቹህ በእኛ ላይ ሀብታም ሆናቹህብን!” የሚል ነው፡፡ የገጠሩ ሰው ብዙ የሚያውቀው ነገር የለምና ወያኔና ኦነግ እውነት አስመስለው ለጥቃት ሲያነሳሡት የሚነግሩትን ነገር እንዳለች ይተፋታል፡፡ ሀቁ ግን ማን የመሬቱ ባለቤት፣ ማን ደግሞ በወረራና በመስፋፋት ይሄንን መሬት ከመቸ ጀምሮ ማንን አፈናቅሎ አሰድዶና አጥፍቶ ይሄንን መሬት እንደያዘ በግልጽ ይታወቃልና ወደ ሐተታ መግባት አያስፈልገኝም፡፡ ነገር ግን ወያኔ በገዛ ሕገመንግሥቱ ላይ “ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በሀገሪቱ በየትኛውም አካባቢ በነጻ የመዘዋወር፣ ኑሮን የመመሥረት፣ ሀብት የማፍራት መብቱ የተጠበቀ ነው!” እያለ በጎን ደግሞ ለየ ክልል ለሚለው አሥተዳደር የዚህን ተቃራኒ መልዕክት እየረጨ አማራን መጨፍጨፍ ማስጨፍጨፍ ማፈናቀሉ ደንቆሮነቱን፣ ኃላፊነት የማይሰማው የወሮበላ ቡድንነቱን፣ አርቆ ማሰብ አለመቻሉን እንጅ ሌላ የሚያረጋግጠው ነገር የለም፡፡

ወያኔ “የደቡብ ክልል” ሲል በሚጠራው የሀገሪቱ ክፍል የሚጠቀሱት ምክንያቶች ደግሞ፦ ደን ያቃጥላሉ!፣ ሕገወጥ ሰፋሪ ናቸው!፣ ከተወላጁ ጋር ተስማምተው መኖር አይችሉም! ፣ ሀገራቹህ አይደለም ከሀገራችን ውጡልን! የሚሉ ናቸው፡፡

እያንዳቸውን ዕንይ፦ ደን ያቃጥላሉ! ያ አካባቢ ከብት አርቢ ማኅበረሰብ ያለበት አካባቢ ነው፡፡ ደርግ በሰፈራ “ውጡልን!” የተባሉትን ወገኖች እዚያ ከማስፈሩም በፊት ከብት አርቢዎቹ ለከብቶቻቸው መሬቱ በየዓመቱ አዳዲስ ሳር እንዲያበቅልላቸው የግጦሽ መሬቱን የማቃጠል ልማድ እንዳላቸው እየታወቀ  ራሳቸው በሚለኩሱት እሳት ሁሌም ጠተያቂ የሚያደርጉት አማራውን ነው፡፡ መረጃ ተገኝቶ ደን ሲያቃጥል የተያዘ ሰው ኖሮ ያ ሰው በሕጋዊ መንገድ ቢቀጣ ምንም ባልነበረ ተገቢም ነው፡፡ የሚሆነው ይህ አይደለም፡፡ ቀድሞውንም ቢሆን ምክንያቱ የሚጠቀሰው ሆን ብሎ ለማጥቂያ ሰበብ ለመፍጠር ነው እንጅ በትክክል ስለተፈጸመ አይደለምና፡፡

ሕገወጥ ሰፋሪ ናቹህ! ወደሚሉት ምክንያት ስንሔድ እንዲህ እያሉ የሚያፈናቅሏቸው በሙሉ በደርግ መንግሥት የሰፈራ መርሐ ግብር የሠፈሩ ከዚያም በኋላ የገቡትም የእርሻ መሬት ተሰጥቷቸው ሕጋዊ የባለቤትነት ማረጋገጫ ሰነድ ተሰጥቷቸው ግብር ሲከፍሉ የኖሩ ስለሆኑ ይሄኛው ምክንያትም አይሠራም፡፡

ከተወለለጁ ጋር ተስማምተው መኖር አይችሉም፦ በዚህ የሚወነጀል ካለ ያልተስማማው በምን ጉዳይ ነው? እንደ ዜጋ መብትና ግዴታውን በመተላለፉ ነው ወይ እንዲህ ሊባል የቻለው? ከሆነም ወንጀል የሠራ ሰው በሚጠየቅበት ሕግ ተጠይቆ በአግባቡ ማስቀጣት ነው እንጅ ሕጋዊው አሠራር ዛሬ ዜጎች ባሕር ተሻግረው በባዕዳን ሀገራት በነጻነት ሠርተው መኖር ኑሮን መመሥረት በተቻለበት ዘመን በገዛ ሀገራቸው ወንጀላቸው ምን እንደሆነ ሳይጠቀስ “ከተወላጁ ጋር ተስማምታቹህ መኖር አትችሉምና!” ብሎ ዜጎችን በጅምላ ማፈናቀል፣ መዝረፍ፣ መፍጀት፣ ማቃጠል የትኛው የወንጀል ሕግ የደነገገው ድንጋጌ ነው?

እጅግ እጅግ የሚያሳዝነው የሚያስደነግጠውና የሚያስገርመው ደግሞ  “ከተወላጁ ጋር ተስማምታቹህ መኖር አትችሉም!” የሚለው ክስ ትርጉም አባዎራዎች ዋልጌና ውርጋጦች እቤታቹህ እደገቡ ባለቤቶቻቹህንና ልጆቻቹህን ሲደፍሩባቹህ፣ ከብቶቻችሁን ከበረትና ከመስክ እንደፈለጉ ነድተው ሲወስዱባቹህ፣ ከሱቆቻቹህ ያለክፍያ ዕቃ ያሻቸውን ያህል እያነሱ ሲወስዱባቹህ፣ በፀብ የሚተናኮላቹህ ጥጋበኛ ሲኖር ወዘተረፈ. ወዘተረፈ. ሲሆን ምንም እንዳልሆናቹህ ምናቹህም እንዳልተነካ በዝምታና በጸጋ ተቀበሉ! ማለት መሆኑን በደሉ ለተፈጸመባቸው ዜጎች ይህ ቃል የሚጠቀስላቸው እነኝህ በደሎች ተፈጽመውባቸው ፍትሕ ይሰጣቸው፣ የሚደርስባቸው ገደብ የለሽ ግፍ ይቆምላቸው ዘንድ ወደ ሕግ አካላት አቤት! ባሉ ጊዜ ሕግ ያስከብራሉ ከተባሉ ወንጀሉን ከሚፈጽሙት የባሱ እንስሳ ሕግ ያስከብራሉ ተብለው በኃላፊነት ከተቀመጡ ከሕግ አካላት ዘወትር የሚጠቀስላቸው ጉዳይ በመሆኑ ነው፡፡ መቸስ በጣም የሚገርምና እጅግም የሚያሳፍር ነገር ነው፡፡

ሀገራቹህ አይደለም ከሀገራችን ውጡልን! ወደሚለው ስንሔድ፦ ይሄንን ችግር የበለጠ ከባድና የተወሳሰበ የሚያደርገው ምን እንደሆነ ታውቃላቹህ? ጥቃት ፈጻሚዎቹ የበሰለ ንቃተ ኅሊና ደረጃ ላይ ያሉ አለመሆናቸው ነው፡፡ ጥቃት ፈጻሚዎቹ ሀገር ማለት ምን ማለት እንደሆነ፣ ይህች ሀገር እንደሌሎቹ ሀገራትና ሕዝቦች በቅኝ ተይዛ ሕዝቧ እንዴት በባርነት ተቀጥቅጦ እንዳልጠፋ፣ የሀገሪቱ የገጸ ምድርና የከርሰ ምድር ሀብቷ እንዴት ሳይቦጠቦጥ ሳይዘረፍ ሳይወሰድ እንደቀረ፣ ማን ምን ዓይነት መራራ መሥዋዕትነት ለሽዎች ዓመታት ሲከፍል ስለኖረ የሀገሪቱ መሬት እንደተፈጠረ ድንግል መሬት ሊሆን የቻለው፣ የተለያዩ ጎሳዎችም እንዳሉ ሳይበረዙ ሳይከለሱ እንደተፈጠሩ ለሥነ ሰብእ (ለአንትሮፖሎጂ) ጥናቶች  ምቹ መሆናቸው እስኪመሠከርላቸው ድረስ የተጠበቁ ሆነው ሊገኙ እንዴትና በምን ምክንያት እንደቻሉ ቢያውቁ ኖሮ አማራን “ሀገራቹህ አይደለም! ሀገራችንን ለቃቹህ ውጡልን!” ሊሉ አይደለም ለውለታው ምንም ቢያደርጉ ቢከፍሉት የማይጨርሱት እጅግ የበዛ ዕዳ እንዳለባቸው ተረድተው አክብረውት አድንቀውት አመስግነውት ወደውት ባልጠገቡት ባልረኩ ውለታው ባስጨነቃቸው ነበር፡፡

ግን ምን ያደርጋል ድንቁርናና አለማሰብ አለማስተዋል የሚባል አውሬ በወገኖቻችን ላይ ሠልጥኖ በባለውለታው በአማራ ሕዝብ ላይ በማነሣሣት እንዲህ ዓይነት ግፍ እያስፈጸመበት ይገኛል፡፡ ምን ማድረግ ይቻላል? ዕውቀት እንደ ክትባት በመርፌ አይሰጥ!

ለማንኛውም ወያኔ ደቡብ ሲል በከለለው የሀገራችን ክፍል ለሚፈጸመው የዘር ማጥፋትና ማጽዳት ወንጀል የሚጠቀሱ ምክንያቶች እነኝህን ይመስላሉ፡፡

ወያኔ ቤንሻንጉል ጉምዝ ሲል ወደሚጠራው የሀገራችን ክፍል ለጭፍጨፋው ወደሚጠቀሰው ምክንያት ስናልፍ ደግሞ የሚከተለውን እናገኛለን፦ “የክልላቹህ መንግሥት በማዳበሪያ ዕዳ ስለሚፈልጋቹህ ለቃቹህ ሒዱ!” የሚል ነው፡፡ የሚሉት እኮ ቢያጡ ነው! ለሚያይ ለሚሰማ “አማራ ስለሆኑና አማራ እንዲጠፋ ስለምንፈልግ ነው የምንጨፈጭፋቸው!” ላለማለት እኮ ነው እንጅ ሰዎቹ እዚያ ቦታ ላይ ያሠፈራቸው ደርግ በመላ ሀገሪቱ ይዞት በነበረው ሰፊ መርሐ ግብር ሳቢያ ነው፡፡

ስንት ችግርና ፈተናን አሳልፈው የሰፈሩባቸውን ቦታዎች ሁሉ ከአራዊቱ ከእባቡ ከጊንጡ ጋር ታግለው መሬቱን ሲያለሙትና ከዓመታት በኋላ የድካማቸውን ፍሬ መቅመስ ማጣጣም ሲጀምሩ “ብርቱና አርአያ አርሶ አደር!” እየተባሉ በየ የወያኔ ክልሉ የሚሸለሙት እነሱው ሲሆኑ ሰይጣን ያደረበት ሁሉ በቅናት ተቃጠለ “እኔ መጥፋቱን  እፈልጋለሁ እሱ ጭራሽ ይፋፋልኛል? በል በልልኝ!” እያለ ይፈጀው ያዘ፡፡ እንጅ እውነቱማ እዚያ ቦታ ላይ የሠፈሩት በደርግ ዘመን ሆኖ ወያኔ ገብቶ “የአማራ ክልል” ብሎ ከሠየመው አሥተዳደር ዕዳ ሊኖርባቸው የሚችልበት አንዳችም መንገድ ሊኖር እንደማይችል ሁሉም ሊረዳው የሚችለው ነገር ነው፡፡

ወልቃይት ላይ ለሚፈጸመው የዘር ማጥፋትና ማጽዳት ወንጀል የሚጠቀሰው ምክንያት ደግሞ፦ “ትግሬ ነን! ካላቹህ ተቀመጡ፡፡ አይደለንም! የምትሉ ከሆነ ግን መሬቱ የእኛ ነውና ለቃቹህ ውጡ!” የሚል ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ በተለያዩ ጽሑፎቸ ላይ በሚገባ የተነተንኩት ጉዳይ በመሆኑ ጽሑፌ በጣም ስለረዘመ በጣም ይቅርታ አድርጉልኝና ይሄን በዚህ ልለፈው፡፡ በአፋርና በሌሎች የወያኔ ክልሎች በአማራ ማኅበረሰብ ላይ ለሚፈጸመው የዘር መጥፋትና ማፅዳት ወንጀል የሚሰጠው ምክንያትም ከላይ ከተጠቀሱት ጋር ተመሳሳይ በመሆኑ እነሱንም አልፋቸዋለሁ፡፡

ጽሑፌን ላጠቃልለውና እንዳያቹህት ጅቡ ወያኔ ሳያመኻኝ ላለመብላት ዘጠና ዘጠኙን ይቀባጥራል፡፡ አንዴ ታስታውሳላቹህ አቶ ዓለምነው የተባሉ የብአዴን ባለሥልጣን የአማራን ሕዝብ እንዲህ ፈጅቶ ለመጨረስ ላበቃቸው ጉዳይ ምክንያት ለማበጀት ሲከጅሉ ምን ነበር ያሉት? “አማራ የትምክሕት ለኻጩን ካልጣለ ካላራገፈ በስተቀር ከሌሎች ሕዝቦች ጋር መኖር አይችልም!” ሲሉ ነበር በአራት ነጥብ የደመደሙት፡፡ “እንዲህ እያደረግን በስውርና በግልፅ በምንፈጽምብህ ጥቃት አጥፍተን ፈጅተን እንጨርስኻለን እንጅ!” ማለታቸው ነው፡፡

አቶ ዓለምነው ማየት የተሳናቸው ልበ ዕውር ደንቆሮ ሆነው ነው እንጅ ሥነሥርዓት አክብሮት ጨዋነት የሚባል ነገርን ከቶውንም የማያውቁትን በባሕርያቸው እንደ ፋብሪካ ዕቃ አንድ ዓይነት የሆኑትን ስድ፣ ዋልጌ፣ ባለጌ፣ ጭንጋፍ፣ ውርጋጥ፣ ቆሻሻ፣ ምናምንቴ፣ ጥጋበኛ የዕድሜ መግፋት እንኳ ከእነኝህ የሥነምግባር ጉድለቶቻቸው የማያርማቸውን የወያኔን መንጋ ከጎናቸው አስቀምጠው አክብሮቱና ሰላምታው ከሰው አልፎ ለእንስሳት የሚተርፈው ሥነሥርዓት ባሕሉ የሆነውን ታጋሽ አስተዋይ በሳል የአማራን ሕዝብ እንዲያ ብለው ለመዝለፍ ድፍረት ባላገኙም ነበር፡፡ ሲጀመር አእምሮውና ሥነልቡናው ከላይ አስቀድሜ  በጽኩላቹህ ሁኔት እንዲያ ሆኖ የተዛባና የታወከ በሽተኛ ይሄንን እንዴት ሊረዳ ይችላል?

የዚህ ሁሉ ሐተታ ቁልፍ መልእክት ፈጥነን እንንቃ! ይህ አሁን ሕዝባችን እያደረገ ያለው ዐመፅና ተቃውሞ ወያኔ አጋሮቹ ለ25 ዓመታት በመላ ሀገሪቱ በአማራ ሕዝብ ላይ በሥውርና በግልፅ ሲፈጽምብንና ሲያስፈጽምብን የኖረውን የዘር ማጥፋትና ማጽዳት አደገኛና ከባድ ወንጀል በዋናነት ታሳቢ ባደረገና አደጋውንም ለመቀልበስ በቆረጠ ዝግጅት መነቃቃት ወኔ ቁርጠኝነትና እልህ መሆን ይኖርበታል!! የሚለው ነው፡፡

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኩዳን

amsalugkidan@gmail.com

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.