አቡነ አብርሃም: ሕዝቡና ሠራዊቱ እንዲተዛዘኑ መከሩ፤ መንግሥትንና ሚዲያውን አሳሰቡ፤“በመሣርያ ሰላም አይገኝም፤ አይተነዋል፤ እያየነውም ነው፤ ሊኾንም አይችልም!”

ሐራ ዘተዋሕዶ

 • የመሣርያ ምላጭ ከመሳብ ይልቅ፣ የፍቅር መሳቢያን ተጠቀሙ፤ የፍቅር ማሰርያን ተጠቀሙ
 •  ጉልበታችን ሊያስመካን አይገባም፡፡ ሊያስመካን የሚችል ቢኖር መስቀሉ ብቻ ሊኾን ግድ ነው
 •  ሰላም፣ የሰዎችን ድምፅ ሰምቶ፣ መልስ በመስጠትና ችግርን በማስወገድ ነው የሚመሠረተው
 •  በኃይል ሰላምን አምጥተው በሰላም የኖሩ፣ በየትም ዓለም የሉም፤ የቀን ቆጠራ ካልኾነ በቀር!

*                *             *

 • ምንጊዜም ችግር የመሪው መንግሥት እንጂ የተመሪው ሕዝብ አይደለም፤ በቤተ ክህነትም!
 •  መንግሥት፣ እንደ ወላጅም እንደ መሪም፣ ችግሮችን በመፍታት መፍትሔ መስጠት አለበት
 •  በግድያ እና ሕዝቡን በማላቀስ፣ ነገ ሌላ የታሪክ ጠባሳ በስሙ እንዳያኖር ሊጠነቀቅ ይገባዋል!
 •  የጩኸቱን ድምፅ ሰምቶ ለጩኸቱ ካልመለሰ፣ ሕዝቡ ጩኸቴን አላቆምም ቢል የተለመደ ነው

*                *             *

 • ሚዲያዎች፣ ያሻችኹን እየቀጠላችኹ ከሕዝቡ አጋጫችኹን፤ ምን አባት አለን? አሰኛችኹ
 •  የቤተ ክርስቲያን፣ ድምፅዋ ይሰማ! ለማንም አትወግንም፣ የምንናገረውን በትክክል አድርሱ!
 •  ቤተ ክርስቲያንን የሚናፍቃት የውሸት ዕርቅና የምፀት ሰላም ሳይኾን የመስቀሉ ሰላም ነው
 •  እርስበሳችን በፈጠርነው መከራና ችግር መሣቂያና መሣለቂያ ከመኾን እግዚአብሔር አድነን!!

*                *             *

meskel-demera-celebration-in-bahirdar09

“ኹለችኁም ወደዚኽ መስቀል ተመልከቱ፤ በመሣርያ ሰላም አይገኝም፤ አይተነዋል፤ እያየነውም ነው፤ ሊኾንም አይችልም!”ብፁዕ አቡነ አብርሃም፤ የምዕ/ጎጃም፣ አዊ፣ መተከልና ባሕር ዳር አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ በመስቀል ደመራ በዓል አከባበር ላይ

በቤተ ክርስቲያን ቀኖና መሠረት፣ በትሩፋቱና በትምህርቱ ልቆ በአንብሮተ እድ የሚሾም ኤጲስ ቆጶስ፣ በቅዱስ ሲኖዶስ በተመደበበት ሀገረ ስብከት ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል፣ በበላይነት ለሚመራቸው ካህናትና ምእመናን ያለበትየኖላዊነትና የመግቦት ሓላፊነቱ ቀዳሚው ነው፡፡ ምእመናኑ፣ በተደራጀና በተሟላ ኹኔታ የትምህርተ ወንጌል አገልግሎት እንዲያገኙና ስለ ሃይማኖታቸው በሚገባ እንዲያውቁ፣ በመንፈሳዊ ሕይወት እንዲጸኑና በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን እንዲመሩ በትኩረት መሥራትና መከታተል ይኖርበታል፡፡ ከዚኽም ጋር ኤጲስ ቆጶሱ፡- የሀገር ፍቅር እና አንድነት በሰላም ተጠብቆ እንዲኖር በማድረግ፣ የቤተ ክርስቲያንን ጥንታዊና ታሪካዊ አገራዊ ሚና አጠናክሮ የማስቀጠል የመንፈሳዊ አባትነት ድርሻም አለበት፡፡

ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ የየጊዜውን ሥልጣኔ ተከትሎ እንዲሔድና ስለ ሀገር ፍቅር፣ ስለ ነፃነት ጥቅም፣ ስለ ዳር ድንበር መከበር፣ ስለ ብሔራዊ ምንነት ከምትሰጠው የተቀደሰ ትምህርት ሌላ፣ ለወገንና ለሀገር ትምክህት የሚኾኑ ጀግኖች ከታሪክ እንዲወለዱ ወቅቱ የሚፈቅደውን ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ትምህርት በማዘጋጀት ስታስተምር የኖረች የኢትዮጵያ ባለውለታ ቤተ ክርስቲያን ነች፡፡ የአኹኑ ትውልድም የአባቶቹን ታሪክ ተከትሎ ሀገሩን፣ ነፃነቱን፣ ክብሩንና ሃይማኖቱን ጠብቆ እንዲኖር ቤተ ክርስቲያን ከማስተማር የተገታችበት ጊዜ የለም፡፡

ከትላንት በስቲያ፣ መስከረም ፲፮ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም.፣ በባሕር ዳር መስቀል ዐደባባይ በተከበረው፣ የመስቀል ደመራ በዓል፣ የምዕራብ ጎጃም፣ አዊ፣ መተከል እና ባሕር ዳር አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም፣ ያስተላለፉት መልእክትም በዚኹ ዐይን የሚታይ ነው፡፡ ባሳለፍነው ፳፻፰ ዓ.ም. መገባደጃ በተቀሰቀሰው ሕዝባዊ ተቃውሞ፣ በርካታ ግድያዎች፣ የአካል መጉደልና የንብረት ውድመት በተፈጸመበት የሠቆቃ ድባብ ውስጥ፣ በተከናወነው በዚኹ ክብረ በዓል፣ ብፁዕነታቸው ባስተላለፉት መልእክት፣ በርካታ ኦርቶዶክሳውያንና ዜጎች ደስታቸውን እየገለጹ ነው፡፡

ብፁዕነታቸውን፣ ከሰማዕተ ጽድቅ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ሊቀ ጳጳስ እና ከብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ ጋር እያመሳሰሉ ያወደሱ ወገኖች፤ ኢሰብአዊነትንና ኢፍትሐዊነትን ያለአድልዎ በመቃወም፤ ያዘኑትን በማጽናናትና የተጨነቁትን በማረጋጋት፣ በተቃራኒዎች መካከል በአስታራቂነት የመቆም የቤተ ክርስቲያን ሞራላዊ ልዕልና እና የገለልተኛነት ሚና አኳያ፣ ሌሎችም አባቶች ሓላፊነታቸውን እንዲወጡ አርኣያነት ያለው ወቅታዊ መልእክት እንደኾነ በአጽንዖት ጠቅሰዋል፡፡

“ቤተ ክርስቲያን ከሕዝብዋ ጋር በመወገን፣ መንግሥት የሕዝብ እምባ ጠባቂ ግዴታ እንዳለበት የሚመክርና የሚያስጠነቅቅ ፈር ቀዳጅ አስተምህሮ በማድረጋቸው ሊመሰገኑ ይገባል፤” ብለዋል፣ አንድ ታዋቂ ፖሊቲከኛ በፌስቡክ ገጻቸው ባሰፈሩት አስተያየት፡፡ “ነዋ ብእሴ መስቀል – እነኾ የመስቀሉ ሰው” ሲሉ ብፁዕነታቸውን ያመሰገኑት ዲያቆን ኢንጅነር ዓባይነህ ካሴ በበኩላቸው፣ “ፍርሃት በራቀለት የጥብዓት አንደበት የተጌጠ ግሩም ቃል ከሊቀ ጳጳሱ ሰማን፡፡ ወሰኑን ሳያፋልስ፣ በዓለማዊ ፖለቲካ ውስጥ ዠቅ ሳይል፣ መንግሥት እና ሃይማኖት የተለያየ ነው የሚለውን ብሂል ሳይጋፋ ሓላፊነትን መወጣት፣ የመንፈሳዊ መሪ ድርሻ እንደኾነ የብፁዕነታቸው ቃል ያረጋግጣል፤ ዝም በማይባልበት ዝምታ ተገቢ አለመኾኑንም ያመለክታል፤” ብለዋል፡፡

“በሃይማኖት መሪነት ለብዙ ዓይነት አካላት ብዙ ዓይነት መልእክት ማስተላለፍ ይገባል፤” የሚሉት ዲያቆን ዓባይነህ፣ የብፁዕነታቸው ትምህርት በአድራሻው፣ ከሚዲያውና ከሕዝቡ ጋር በተለይም “ለባለጡንቻው” መንግሥት የተላለፈ መልእክት እንደኾነ በጭብጥ በመለየት አብራርተዋል፡፡ ለክብረ በዓሉ ምክንያት የኾነውን የመስቀሉን መገኘት ታሪክ፣ ከወቅቱ ኹኔታ ጋር በማገናዘብ ያስተማሩት ብፁዕ አቡነ አብርሃም፣ መንግሥት የሕዝቡን ብሶትና ጩኸት በቶሎ ሰምቶ ችግሮቹን በመፍታትና ጥያቄዎቹን በመመለስ የማስተዳደር፣ የመሪነትም የአባትነትም ድርሻ እንዳለበት አስታውቀዋል፡፡ ሰላምን የማስፈን ግዴታ ቢኖርበትም፣ በቀጠለው የሕዝቡ ጩኸት ሳቢያ በሚወስደው የጭካኔ ርምጃ፣ “ነገ ሌላ የታሪክ ጠባሳ በስሙ እንዳያኖር ሊጠነቀቅ ይገባዋል፤” ሲሉ አሳስበዋል፡፡

ዘላቂ ሰላም፡- በመግባባት፣ የሕዝብን ድምፅ በወቅቱ ሰምቶ ተገቢ ምላሽ በመስጠትና ችግርን በማስወገድ እንጂ፣ በመሣርያ ኃይል የሚመሠረት እንዳልኾነ፣ ይልቁንም የሀገርን አንድነትና ህልውና ለአደጋ በመዳረግ፣ ለታሪካዊ ጠላቶቻችን መሣቂያና መሣለቂያ እንደሚያደርገን አመልክተዋል – “ሰላምን በኃይል አምጥተው በሰላም የኖሩ በየትኛውም ዓለም የሉም፤ የቀን ቆጠራ ካልኾነ በስተቀር፤” ሲሉ አስጠንቅቀዋል – ብፁዕነታቸው፡፡ ከዚኽም አኳያ ፣ ዳር ድንበርንና የሀገርን ሰላምን ለሚጠብቅበት የመከላከል ትድግናው ቤተ ክርስቲያን ሌት ተቀን የምትጸልይለት ወታደሩና ሠራዊቱ፣ መሣርያውን ይያዝ እንጂ ምላጩን ከመሳብ ይልቅ የፍቅር መሳቢያን፣ የፍቅር ማሰርያን እንዲጠቀም፤ ሕዝቡም በአላስፈላጊ ጉልበትና ስሜታዊነት ከመተላለቅ፣ መስቀሉን መሣርያው አድርጎ ወደ እግዚአብሔር እንዲጮኽ በመንፈሳዊ መሪነታቸውና አባትነታቸው መክረዋል፡፡

ስለዚኽ ኹላችንም በያለንበት እንደ ወገንነት እንተዛዘን፡፡ እንደ ወገንነት እንተባበር፡፡ ስንቱ ወገን ነው በበረሓ ያለቀው፤ ስንቱ ወገን ነው እንጀራ ፍለጋ በየሀገሩ የተሰደደው፤ ስንቱ ወገን ነው ባሕር የሰጠመው፤ ስንቱ ወገን ነው ዘንዶ የዋጠው፤ እዚኽኮ ሰላማችን ቢበዛ፣ መደማመጥ ቢኖር፣ መቀባበል ቢኖር፣ መፍትሔ በየሰዓቱ ቢሰጥ ኖሮ ኹሉም ሰላም ይኾን ነበር፡፡ ሰላም ካለ ደግሞ ኹሉም ነገር አለ፡፡

እንደ ቅዱስ መጽሐፍ ቃል፣ ቤተ ክርስቲያን፣ የእምነት ነፃነትዋና ተቋማዊ ሉዓላዊነትዋ እስካልተጣሰ ድረስ፣ “ነፍስ ኹሉ፣ ለበላይ ባለሥልጣኖች እንድትገዛ” ብታስተምርም፣ ለማንም እንደማትወግን፣ ብፁዕነታቸው፣ በተለይ ለሚዲያ ሰዎች ተናግረዋል፡፡ የመንግሥት እና የሃይማኖት መለያየት፣ በኤፌዲሪ ሕገ መንግሥት ብቻ ሳይኾን፣ በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ ስምንት የተደነገገ የገለልተኛነት መርሖዋ ነው፡፡ በመኾኑም፣ ሚዲያዎች፣ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችንና አባቶችን ቃል እንዳሻቸው እየቀጣጠሉ፣ ከሕዝቡ ጋር ከማጋጨትና ሕዝቡን ተስፋ ከማስቆረጥ እንዲታቀቡ፣ ብፁዕ አቡነ አብርሃም ምክርና ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡

በዚኹ ክብረ በዓል፣ ብፁዕ አቡነ አብርሃም፣ ከወትሮው በተለየ፣ ተባርኮ የተለኮሰው ደመራ ተቃጥሎ እስኪያልቅ በዚያው በዐደባባዩ ከሚዘምሩት የሰንበት ት/ቤቶችና ማኅበረ ምእመናን ጋር በመቆየትና ሕዝቡን ወደየመጣበት አስቀድመው በመሸኘት ነበር፣ ወደ መንበረ ጵጵስናቸው ያመሩት፡፡ የበዓል አዘጋጅ ኮሚቴው፡- ከሀገረ ስብከቱ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት፣ ከአካባቢ የጽዋ ማኅበራት፣ ከማኅበረ ቅዱሳን የባሕር ዳር ማዕከል አባላት የተውጣጣ ሲኾን፣ ከብፁዕነታቸው ትምህርት አስቀድሞ ጸሎተ ምሕላ ደርሷል፤ በሊቃውንቱ፣ በሰንበት ት/ቤቶቹ ወጣቶችና በማኅበረ ቅዱሳን የተሰማው ያሬዳዊ ወረብም፣ ያለከበሮ በጽፋት ብቻ የቀረበ ነበር፡፡ ከበሮ የተመታውም ደመራው ከተለኮሰ በኋላ ተቃጥሎ እስኪያልቅ ብቻ ነበር፡፡

ምእመናኑና ካህናቱ፣ “ዘንድሮም መስቀል አለ እንዴ” እስኪሉ ድረስ ስጋት የነበረባቸው ቢኾንም፣ የኖላዊነትና የአባታዊነት ሓላፊነታቸውን በአግባቡ በተወጡት ብፁዕ አቡነ አብርሃም አጽናኝነት መንፈሳዊ ደስታውን ገልጧል፤ በእልልታና በጭብጨባም እግዚአብሔርን አመስግኗል፤ የቤተ ክርስቲያናችንን ቀጣይ አገራዊ ሚናን በተመለከተም ተስፋው ለምልሟል፡፡ በደመራው ምሽት፣ የብፁዕነታቸውን ከፊል ትምህርት የያዘ ቪድዮ፣ በማኅበራዊ ብዙኃን መገናኛ በስፋት ተሰራጭቷል፡፡ “በዝንቱ ትእምርተ መስቀል ትመውዕ ፀረከ” በሚል ርእስ፣ ለ25 ደቂቃ የዘለቀውና በጽሑፍ የተገለበጠው፣ የብፁዕ አቡነ አብርሃም፣ የባሕር ዳር መስቀል ዐደባባይ ትምህርት ሙሉ ይዘት ደግሞ እንደሚከተለው ተጠናቅሮ ቀርቧል፡፡


በዝንቱ ትእምርተ መስቀል ትመውዕ ፀረከ
በዚኽ የመስቀል ምልክት ጠላትኽን ድል ታደርጋለኽ!

/በብፁዕ አቡነ አብርሃም/

ኹላችኁም ወደዚኽ ወደ መስቀል ተመልከቱ(መስቀላቸውን ከፍ አድርገው እያሳዩ) ፡፡ መስቀል፣ ነፍስንና ሥጋን፣ ሕዝብንና አሕዛብን፣ ሰውንና መላእክትን ያገናኛል፡፡ መስቀል በአጠቃላይ፣ ሰውንና እግዚአብሔርን ያገናኛል፡፡ የክብር ባለቤት፣ የኹላችን ንጉሥ፣ የኹላችን ገዥ፣ በመስቀሉ ደሙን አፍስሶ፣ በደሙ ዋጅቶና ቀድሶ፣ አክብሮ፣ ልጆቹ አድርጎ፣ ነፃነትን ከማጎናጸፉ በፊት፣ እንደሚታወቀው ኹሉ፣ መስቀል የወንጀለኞች መቅጫ፣ የኃጢአተኞች መግደያ ኹኖ ኖሯል፡፡ በዚኽም የመጀመሪያዎቹ ፋርሳውያን እንደኾኑ ቤተ ክርስቲያናችን ትተርካለች፡፡ የምድር አምላክ የሚሉት ነበርና የምድር አምላካቸው እንዳይረክስ ወንጀለኞችን በመስቀል ላይ ይቀጡ ነበር፡፡ በታሪክም ብንሔድ ወንጀለኞች ሲገኙ የሚቀጡት በመስቀል ነበር፡፡ የክብር ባለቤት ግን የተዋረደውንና የተናቀውን ከፍ ማድረግ፣ ማንም ማን የለውም የተባለውን ያለው ማድረግ፣ የባከነውን የተቅበዘበዘውን፣ የጠፋውን፣ የተቸገረውን መርዳት፤ እርሱ የባሕርይው ነውና፣ የተዋረደውን መስቀል ለክብር ይኾን ዘንድ እነኾ በመስቀል ተሰቅሎ ደሙን አፍስሶ ስላዳነን፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን፡- መስቀል ነፃነታችን፣ መስቀል የነፃነታችን ዓርማ ብላ ታከብራለች፡፡

ዛሬ፣ ይህን በዓል ስታከብር፣ በዝንቱ ትእምርተ መስቀል ትመውዕ ፀረከ የተባለው ቆስጠንጢኖስ ነው፡፡ ምንጊዜም በዓሉን ስናከብር ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እና እናቱ እሌኒ ይጠቀሳሉ፡፡ የእሌኒን ታሪክ እንዳልተርክ ረዥም ሰዓት ይወስዳል፡፡ ባለፈው ዓመትም በሰፊው ተነጋግረንበታል፡፡ እሌኒ፣ የተቀበረውን መስቀል ፈልጋ በማግኘት፣ በደመራው፣ ቅድም መንፈሳውያን ወጣቶችም ሲዘምሩልን እንደነበረው፤ ‹‹ሰገደ ጢስ››(ጢሱ ወደ ላይ ወጥቶ ወደ ታች ወርዶ መስቀሉን ስላመለከተ) መስቀሉ የተቀበረበትን ያወጣችበትን ዕለት፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ታከብረዋለች፡፡

demera-celebration-at-bahirdar2009

፳፻፱ ዓ.ም. የመስቀል ደመራ በዓል አከባበር – በባሕር ዳር ሀ/ስብከት፣ ባሕር ዳር መስቀል ዐደባባይ

የመስቀሉ ነገር ሲነሣ ልጅዋ ቆስጠንጢኖስም አብሮ ይነሣል፤ በሥርዓት ያሳደገችው በመኾኑ፡፡ ቆስጠንጢኖስ በእናቱ አይሁዳዊ፣ በአባቱ አሕዛባዊ፣ እናቱ አምልኮተ እግዚአብሔር ያላት፣ እግዚአብሔርን የምትፈራ፣ በኋላም ክርስቲያን የነበረች ናት፡፡ አባቱ ደግሞ በጣዖት አምልኮ የሰከረ፣ ለማንም ለምንም ስሜት የሌለው፣ ደም አፍሳሽ ነፍሰ ገዳይ እንደነበረ የታወቀ፣ የተረጋገጠ ነው፡፡

እግዚአብሔር በኪነ ጥበቡ፣ እሌኒ ወደዚያ ሔዳ፣ የቆስጠንጢኖስን አባት ቁንስጣን አግብታ፣ ቆስጠንጢኖስን ወልዳ፣ በሥርዓት ስላሳደገችው፣ እነኾ በዚያ ዘመን አብያተ ክርስቲያናት ኹሉ ተዘግተው፣ አብያተ ጣዖታት ተከፍተው፣ ክርስቲያኖች ድምፃቸውን ከፍ አድርገው፣ ጩኸታቸውን ወደ እግዚአብሔር የሚያስተጋቡበት ዘመን ነበረና፣ ቆስጠንጢኖስን አሥነስቶ፣ ጠላቶቹን ኹሉ በመስቀሉ ኃይል ድል አድርጎ፣ የተዘጉ አብያተ ክርስቲያናትን ከፍቶ፣ የተከፈቱ አብያተ ጣዖታትን ከፍቶ፣ ለክርስቲያኖች ነፃነት የሰጠበት በዓል ስለኾነ፣ ይህን በዓል በዐደባባይ እንድናከብረው ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ከወሰነችበት ጊዜ ጀምሮ፣ በመከራም ይኹን በደስታ፣ ወደ ዐደባባይ ወጥታ፣ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ዘርግታ፣ ድምፅዋን ከፍ አድርጋ፣ በመስቀሉ ሰላምን ስጠን፤ በመስቀሉ ክብርን አጎናጽፈን፤ በመስቀሉ ጠላትን ድል አድርግልን፤ የሰው ልጅ ጠላት ሰው ሳይኾን ሰይጣን ነውና፣ እርስ በርስ እንድንጣላ፣ አንዱ የአንዱን ደም እንዲያፈስ፣ አንዱ አንዱን እንዲያሳድደው፣ አንዱ አንዱን እንዲያስጨንቀው፣ አንዱ አንዱን እንዲያስቸግረው የሚያደርግ ሰይጣን እንጂ ሰው ሲፈጠር በርኅራኄ፣ በቅድስና፣ በክብር ነውና፣ እነኾ ሰይጣንን ቅጣልን፤ አሳፍርልን፤ አንድነታችንን ሰላምን ስጠን፤ እያለች በዓሉን ታከብረዋለች፡፡

ዛሬም ይህን በዓል ለማክበር ዐደባባይ የተገኛችኹ በሙሉ፣ እንኳን ደስ አላችኹ፡፡ እግዚአብሔር ይባርካችኹ፡፡ በዝንቱ ትእምርተ መስቀል ትመውዕ ፀረከ፤ የክርስቲያኖች ድል ማደረጊያችን፣ የክርስቲያኖች አለኝታችን፣ የክርስቲያኖች ጋሻችን፤ ለዚኽም ነው፣መስቀል ኃይልነ – መስቀል ኃይላችን ነው፤ መስቀል ጽንዕነ – መስቀል መጽኛችን ነው፤ መስቀል ቤዛነ – መስቀል ቤዛችን ነው፤ መስቀል መድኃኒትነ፤ መስቀል መድኃኒታችን ነው፤ ብለን የምንሰመሰክረው፡፡

abune-abreham
በመስቀሉ እናማትባለን፤ በመስቀሉ ርኵሳን መናፍስትን እንገሥጻለን፤ በመስቀሉ ሰላምን እንዋጃለን፤ በመስቀሉ የራቁትን እናቀርባለን፤ በመስቀሉ የታመሙትን እንፈውሳለን፤ በመስቀሉ የተቸገሩትን እንረዳለን፤ በመስቀሉ የተጨነቁትን እንባርካለን፤ እናረጋጋለን፤ እያለች ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ መስቀል በእጆችዋ፤ መስቀል በልጆችዋ አንገት ላይ ጎልቶ ደምቆ የሚታይ እንደ መኾኑ፣ በዓለ መስቀሉን ስናከብር፣ ዛሬም ያጣነውን ሰላም እንዲሰጠን፤ የጥያቄዎቻችንን መልስ እንዲሰጠን፣ መግባባት የሚፈጠርበት፣ እንደ ኢትዮጵያዊ ስሜትና እንደ ኢትዮጵያዊ ባሕርይ፡- አንተ ትብስ፣ አንቺ ትብሽ ተባብለን የምንኖርበትን፣ አንዱ አንዱን የማያሳድድበትን፣ የማያስጨንቅበትን፣ ንጹሕ ደም የማይፈስበትን፣ ሰዎች ያለአግባብ የማይታሰሩበትን፣ በነፃነት በሀገራቸው በፍቅርና በሰላም ሠርተው፣ ጥረው ግረው እግዚአብሔርን እያመለኩ፣ የሚኖሩበትን በዓለ መስቀሉን ስናከብር፣ ይህን እንዲያደርግልን ነው፣ ጸሎቱም ልመናውም፡፡ እግዚአብሔር ጸሎታችንን ይስማ፡፡(ሕዝቡ፣ አሜን እለ ይከተላል)

ምንጊዜም መስቀልን መሣርያ እናድርግ፡፡ በዝንቱ ትእምርተ መስቀል ትመውዕ ፀረከ፤ አንዳንድ ጊዜ ሰዎች መሣርያ ስለያዙ፣ በመሣርያ ድል የሚያደርጉ ይመስላቸዋል፡፡ ብዙ ጊዜ በመሣርያ ድል አድርጎ ማንም ማን አልኖረም፡፡ የዕለቱን በዓል ስናስታውስ፣ ቆስጠንጢኖስ እና መክስምያኖስ፣ ትልቅ ምስክሮች ናቸው፡፡ መክስምያኖስ እጅግ ጦረኛ የኾነ፣ ክርስቲያኖችን ያስጨነቀ፣ አብያተ ጣዖታትን የከፈተ፣ ብዙና ብዙ መከራ ያደረሰ ነበር፡፡ ለዚኽ ነበር ክርስቲያኖች ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ወደ እግዚአብሔር እየጮኹ፣ በክርስትና ሕይወቱ የታወቀውን፣ በምግባር ያደገውን፣ በትሩፋት የበለጸገውን፣ በርኅራኄ የተሞላውን ቆስጠንጢኖስን፣ እባክኽ ርዳን፤ ክርስቲያኖች በዋልንበት ማደር አልቻልንም፤ ባደርንበት መዋል አልቻልንም፤ ብለው ለመኑት፡፡ እርሱም ነገሩን መረመረ፤ ችግሩን ተረዳ፣ ግፉንም አየ፡፡ ‹‹የተቃጠሉትን አልባሳት፣ ቅዱሳት መጻሕፍት፣ የተሠባበሩትን መስቀሎች፣ ጽዋዎች በአጠቃላይ የቤተ ክርስቲያን ንዋያተ ቅድሳትን አሳዩት፤›› ይላል የቤተ ክርስቲያናችን ታሪክ፡፡

ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ያን ከተመለከተ በኋላ፣ መሣርያ አለኝ፤ ኃይል አለኝ፤ ወታደር አለኝ፤ ጉልበት አለኝ ብሎ በጉልበቱ ተመክቶ፣ በመሣርያው ራሱን ከፍ ከፍ አድርጎ ወደ ጦር ሜዳ አልሔደም፡፡ የመጀመሪያ መሣርያው ያደረገው መስቀሉን ነው፡፡ በጸሎት እግዚአብሔርን ጠየቀ፤ ከዚያም በጸፍጸፈ ሰማይ፣ በዝንቱ ትእምርተ መስቀል ትመውዕ ፀረከ፤ በዚኽ የመስቀል ምልክት ጠላትኽን ድል ታደርጋለኽ፤ ተብሎ ተጽፎ አነበበ፡፡ ቋንቋውንም የሚተረጉሙ ተረጎሙለት፤ ከዚኽ በኋላ ውጊያውን ገጠመ፤ እርሱም ቻለ፤ ትእምርተ መስቀሉን ትምክሕት፣ መሪ አድርጓልና፡፡ ጠላትን ድል አድርጎ ለክርስቲያኖች የእምነት ነፃነትን አጎናጸፈ፡፡ አኹንም ለሀገራችን ነፃነትን ያጎናጽፍልን፡፡ መተሳሰብን ይስጥልን፡፡ መተዛዘንን ይስጥልን፡፡ አንተ ትብስ፣ አንቺ ትብሽ መባባልን ይስጥልን፡፡ ጠላታችንን ያርቅልን፡፡(ሕዝቡ፣ አሜን እያለ ይከተላል)

በመስቀሉ ጥላቻንም አስወግዷል፡፡ በኤፌ. ምዕ. 2 ቁ. 16 ላይ ስናነብ፣ ‹‹ጥላቻን ያስወገደ፤ ኹለቱን አንድ ያደረገ በመስቀሉ ነው፤ ገብረ ሰላመ በመስቀሉ››፤ ሰላምን ያጡ ኹሉ በመስቀሉ ነው ሰላምን ያገኙት፡፡ በመሣርያ ሰላም አይገኝም፤ አይተነዋል፡፡ እያየነውም ነው፡፡ ሊኾንም አይችልም፡፡ ሰላም በፍቅር የሚመሠረት ነው፤ ሰላም በመስቀሉ ነው የሚመሠረተው፡፡ ሰላም በሃይማኖት ነው የሚመሠረተው፡፡ ሰላም በመግባባት ነው የሚመሠረተው፡፡ ሰላም የሰዎችን ድምፅ በመስማትና መልስ በመስጠት ነው የሚመሠረተው፡፡ ሰላም ችግርን በማስወገድ ነው የሚመሠረተው፡፡ በኃይል ሰላምን አምጥተው በሰላም የኖሩ በየትኛውም ዓለም የሉም፤ የቀን ቆጠራ ካልኾነ በስተቀር፡፡

ስለዚኽ ማንኛውም ባንኖ፣ ከችግሩ ነቅቶ፣ ሰላምን አስፍኖ፣ ኹሉም የሰላምን አየር እንዲተነፍስ፣ በመግባባት እና ሰላም፣ ችግርን ፈትቶ፣ እነኾ አገራችንን የነፃነት አገር፣ ለማንም ያልተገዛች፣ ለማንም ያልተንበረከከች፣ ለማንም እጅዋን ያልሰጠች፣ በሃይማኖትም በጀግንነትም የጀግኖች አገር፡፡ ያች የጀግና አገር፣ ዛሬ እርስ በእርሳችን በመጠላላት፣ ባለመደማመጥ፣ ለችግር መፍትሔ ባለመስጠት፣ እንዲኹ ዝም ብሎ በስጋት ላይ የተመሠረተ አኗኗር፤ ነጋዴው ነግዶ የማይበላበት፣ ገበሬው ሠርቶ አምርቶ የማያፍስበት፣ የማይቆፍርበት፣ ራሱን የማይረዳበት፣ ተማሪው ተምሮ ተምሮ በትምህርቱ ነገ ለሀገር ደራሽ የማይኾንበት አኗኗር፣ አኗኗር ሊኾን ስለማይችል፣ እነኾ ማንም የሚመለከተው ኹሉ ችግሩን ለመፍታት እንደየሃይማኖቱ(ከአቅራቢያው መስጊድ አዛን ይሰማ ነበር)፣ ክርስቲያኑም ወደ መስቀሉ በመመልከት፣ በመስቀሉ ጥላ ሥር ሰላም መኖሩንና ንጹሕ አየር ያለ መኾኑን በማመን፣ የተጣሉ በመስቀሉ የሚገናኙ መኾኑን በማመን፤ ቅድም እንዳልነው አሕዛብና ሕዝብኮ ተገናኝተው አያውቁም፤ ሕዝብ የሚባለው በእግዚአብሔር የሚያምን ነው፤ አሕዛብ ደግሞ እግዚአብሔርን የማያምን፣ በዘፈቀደ የሚመላለስ ነው፡፡ ሕዝብ እና አሕዛብ የተገናኙ በመስቀሉ ነው፡፡ ነፍስና ሥጋ እንኳ የተዋሐዱት፣ የተገናኙትና የእግዚአብሔርን ክብር ለመውረስ የበቁት በመስቀሉ ነው፡፡

ዛሬም በዓለ መስቀሉን ስናከብር፣ መስቀሉን እንመልከት፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ተናግሮታል – ‹‹ከጌታዬ ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ››፤ ጉልበታችን ሊያስመካን አይገባም፡፡ ሊያስመካን የሚችል ቢኖር መስቀሉ ብቻ ሊኾን ግድ ነው፡፡ መስቀሉን የመረጠ ሰው ደግሞ ሰላም አለው፡፡ መስቀሉ ስንል፣ መስቀል የሰላም ዓርማ ስለኾነ ነው፡፡ ከመስቀል ጋር ጥላቻ አይስማማም፡፡ ከመስቀል ጋር እሰጥ አገባ አይስማማም፡፡ ከመስቀል ጋር አንዱ አሳዳጅ ሌላው ተሳዳጅ፤ አንዱ ገዳይ ሌላው ተገዳይ እንዲኾን አይስማማም፡፡ መስቀሉ ኹሉንም እኩል ይዋጃል፤ በመስቀሉ ድነናልና፡፡ በዚኽ መስቀል ላይ ነው፣ መድኃኒታችን ተሰቅሎ የነፃነትን ዐዋጅ ሲያውጅ፣ ይህ መስቀል የክርስቶስ ዙፋን ነው፤ ይህ መስቀል የነፃነት ዐዋጅ ማወጃ ነው፡፡ ለዚኽ ነው፤ አማናዊትዋ፣ ጥንታዊትዋ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ መስቀሉን የምታከብረው፡፡ እግዚአብሔር ያከበረው ስለኾነ ነው፡፡

ቅድም የዕለቱ ወንጌል(ዮሐ. ምዕ.19 ቁ.25) ሲነበብ ሰምታችኋል፤ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ፣ አላዋቂዎች ሲዘባበቱበት፣ ሲቀልዱበት፣ ሲተፉበት፣ ራስኽን አድን እያሉ የምፀት ቃል ሲናገሩበት፣ ከመስቀሉ ላይ እንዳለ ለቅዱስ ዮሐንስ፣ ‹‹እነኋት እናትኽ››፤ ለቅድስተ ቅዱሳን ለድንግል ማርያም ደግሞ፣ ‹‹እነኾ ልጅሽ›› በሚል ቃል ኪዳኑ የጸናበትእኛ ልጆቹ፣ የቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም ልጆች፣ ቅድስተ ቅዱሳን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የእኛ እናት ትኾን ዘንድ በመስቀሉ ቃል ኪዳን የገባበትም ስለኾነ፣ የተዋሕዶ እናት ቤተ ክርስቲያናችን መስቀሉን በዚኽ ዓይነት ታከብረዋለች፡፡

ስለዚኽ ባለንበት ሰዓት ብዙ አይተናል፡፡ የዘመኑን የማኅበራዊ መገናኛ መሥመሮችን ብዙ ተመልክተናል፡፡ እጅግ የሚያሳዝንም፣ የሚዘገንንም ድርጊት ሲፈጸም፣ ሲደረግ፤ ኢትዮጵያዊ በኢትዮጵያዊ፣ ወገን በወገኑ ላይ ያደርጋል ተብሎ በማይታሰብ መልኩ እያየን ነው፡፡ ይህ ይበቃል ልንል ይገባል፡፡ በቃ! ወደ ሰላማችን እንመለስ፤ ችግሮች ይፈቱ፤ መግባባት ይስፈን፤ ኹሉም ሥራውን እየሠራ ለጥያቄው በሰላም መልስ እያገኘ መኖር አለበት፤ ወደሚለው ኹሉም ማዝመም አለበት፡፡ እንደ ፖሊቲካ አይደለም የምናገረው፤ እንደ ሃይማኖት ግን መናገር ያለብኝ ነገር አለ ብዬ አምናለኹ፣ መንግሥትንም በተመለከተ፡፡ በፖሊቲካ ከመነዘረው የእርሱ ጉዳይ ነው የሚኾነው፤ የእኔ አይደለም፤ እንደ ሃይማኖት ግን በነፃነት፣ በድፍረት ነው የምናገረው፡፡

ትላንትና መንግሥት፣ የሞቱትን ዐፅም በማውጣት፣ በመሰብሰብ፡- ‹‹አረመኔው እና ጨካኙ፣ ይኸው ልጆቻችኹን ገደለላችኹ›› ብሎ፣ ማላቀሱ የትላንትና ትዝታ ነው፡፡ ይህ ታሪክ ደግሞ ዛሬም በውስጣችን ተፈጽሞ፣ ነገ ሌላ የታሪክ ጠባሳ በስሙ እንዳይኖር ሊጠነቀቅ ይገባዋል፡፡ ነገሮችን ኹሉ በመወያየትና ችግሮችን በመፍታት፣ ሰላምን ለማስፈን መንግሥትም ግዴታ አለበት – ከላይ እስከ ታች፡፡ ያ እስከ ኾነ ድረስ ሰላምን የተጠማ ሕዝብ ነው፡፡

ማንኛውም እንደሚናገረው፣ በርግጠኝነት፣ ምንጊዜም ችግር የመሪው እንጂ የተመሪው ሕዝብ አይደለም፡፡ በቤተ ክህነትም፣ ኹልጊዜም ችግር የመሪው እንጂ የሕዝብ አይደለም፡፡ የምለውን ካላደረግኽልኝ፣ ጩኸቴን ካልሰማኸኝ…(የምእመናን እልልታና ጭብጨባ ይሰማል፤ ብፁነታቸውም …ግዴለም፣ ግዴለም አጨብጭቡልኝ እያልኩ አይደለም፤ ዝም ብላችኹ ስሙ፤ በማለት ይቀጥላሉ) የጩኸቱን ድምፅ ሰምቶ ለጩኸቱ ካልመለሰ፣ ማስተባበያ ካልሰጠ፣ አዎንታዊነቱን፣ እውነቱን እውነት፣ ሐሰቱን ሐሰት ብሎ ካላረጋገጠ፣ መልስ እስካልሰጠኸኝ ድረስ ጩኸቴን አላቆምም ማለት የተለመደ ነው፡፡

አንድ ሕፃን ልጅ ወደ ወላጆቹ ያለቅሳል፤ እናት ይኑረውም አይኑረውም ጡትዋን ስትሰጠው ጸጥ ይላል፡፡ ማግኘት አለማግኘት፣ ያ ሌላ ጉዳይ ነው፡፡ እንደ እርሷ አመጋገብ ነው፡፡ ለምግብም የደረሰ እንደ ኾነ እርጥብም ይኹን ብስል እንደ አኗኗሯ፣ የተወሰነ ነገር ስትሰጠው ያን ይዞ ዝም ነው፡፡ አለበለዚያ ሕፃኑ ማልቀሱን አይተውም፡፡ መንግሥት፣ እንደ ወላጅም እንደ መሪም እንደ ሀገር ጠባቂም ኹለንተናዊ ሓላፊነት እጁ ላይ የተጣለበት እንደ መኾኑ፣ ችግሮችን በመፍታት መፍትሔ መስጠት አለበት፡፡

በአንፃሩ፣ የሚዲያ ሰዎችም እዚኽ አያችኋለኹ፡፡ ወደፊት በዚኽ ዓይነት እንድትቀርጹ የምንፈቅድ አይመስለኝም፤ ከይቅርታ ጋር፡፡ ዛሬ፣ እዚኽ ነፃ ስለኾነ መልካም ነው፡፡ ለምን ቢባል፣ አንዳንድ ጊዜ እኛን ትጠይቃላችኹ፤ ታናግሩናላችኹ፤ እኛ ከሕዝቡ ጋር የምንጋጭበትን የፈለጋችኹትን ቃል ቀጥላችኹ ታስተላልፋችኹ፤ ሕዝቡ ያን ይሰማና፣ ምን አባት አለን? ይላል (ጭብጨባ ይሰማል)፡፡ የምንናገረውን በትክክል አድርሱ፡፡

ቤተ ክርስቲያን፣ ለማንም ለማን አትወግንም፡፡ ጥላቻን አትሰብክም፤ መገዛትን ታምናለች፤ ተገዙም ትላለች፡፡ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃል ነውና አትገዙ አትልም፡፡ ቤተ ክርስቲያን፣ አልገዛም የምትልበት ጊዜ ቢኖር፣ በሃይማኖትዋ ሲመጣ፤ ሃይማኖትን ካድ፤ ማዕተብን በጥስ፤ ቤተ ክርስቲያን የሚዘጋ ካለ፣ አዎ፣ አልገዛም ብላ አንገትዋን ትሰጣለች፡፡ ግደል ግን አትልም፡፡ ሞትን ተማርን እንጂ መግደልን አልተማርንም፡፡ መሰደድን ተማርን እንጂ ማሳደድን አልተማርንም፡፡ ክርስቲያን ይህ ነው – ይሰደዳል እንጂ አያሳድድም፡፡ ይሞታል እንጂ አይገድልም፡፡ ይወቀሳል፤ ይሰደባል እንጂ አይወቅስም፣ አይሰድብም፡፡ እውነትን ግን በዐደባባይ ይናገራል፡፡

ለዚኽ ነው ዛሬ፣ ከትንሽ እስከ አዛውንቱ በአማናዊት ቤተ ክርስቲያን ተሰብስቦ፣ ለሀገር ሰላም የቆመው፤ ለሀገር አንድነት የሚጸልየው፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የሀገርን ሰላም ትፈልጋለች፤ ባለታሪክ ስለኾነች፡፡ ከጥንትምኮ ለዚኽች ሀገር ነፃነት ማን ነው አንድዋና ተጠቃሹዋ ባለታሪክ? ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ታቦትዋን መስቀልዋን አዝማች፣ መሪ አድርጋ፡፡ እስከዛሬ ድረስኮ ቋንቋችን፣ ባህላችን፣ ሥርዓታችን ተደበላልቆ የባዕዳን አገር ትኾን ነበርኮ፣ እንደሌላው፡፡

ይህች አማናዊት ቤተ ክርስቲያን ግን ኹልጊዜ በመስቀል እየባረከች፣ በመስቀል እያቀረበች፣ በመስቀል እየሳበች፣ በመስቀል እያስታረቀች፣ የተለያየውን በመስቀል እያገናኘች፣ በመስቀል ነፃነት ያላትን አገር ለትውልድ አውርሳለች፡፡ ዛሬም ምኞትዋም ዓላማዋም ይኸው ነው፤ ሌላ ዓላማ የላትም፡፡ ሌላ የሚናፍቃት ነገር የለም፡፡ ቤተ ክርስቲያን የሚናፍቃት ሰላም ነው – የመስቀሉ ሰላም፡፡ የምፀት ሰላም አይደለም፡፡ የመስቀሉ ሰላም፣ ‹ለማግባቢያ› የሚነገር ሰላም አይደለም፡፡ ለማጥመጃ የሚነገር ሰላም አይደለም፡፡ የውሸት ዕርቅም አይደለም፡፡ በመስቀሉ የተፈጸመው አማናዊ ሰላም፣ ዛሬም፣ ነገም ከነገ ወዲያም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ይናፍቃታል፡፡ ሥራዋም፣ ልመናዋም፣ ጸሎትዋም ይኸው ነው፡፡ (ጭብጨባ)

ለዚኽም ነው፣ ሌትም ቀንም፣ አይደለም ስለ ሰው ልጆች ስለ ሀገር ጠባቂዎች፣ ስለ ወታደሩ፣ በሀገሩ በድንበሩ፣ ‹‹ዕቀብ ሕዝባሃ ወሠራዊታሃ ለሀገሪትነ ኢትዮጵያ፤ ዳር ድንበሯን፣ ሕዝብን የሚጠብቀውን ሠራዊት በአጠቃላይ ከላይ እስከ ታች ከጠላት ከወራሪ ጠብቅ፤ ታደግ›› እያለች በመስቀሉ የምትጸልይ ይህች ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ስለዚኽ የቤተ ክርስቲያን ድምፅዋ ሊሰማ ይገባል፡፡

ዐዋጅዋ፣ ማንኛውም ነገር፣ የታሰሩት እንዲፈቱ፣ ያዘኑት እንዲጽናኑ ነው፡፡ በማወቅም ባለማወቅም፣ የሚገርመው ነገር፣ እያንዳንዱ የየግሉን ጥላቻ ምክንያት አድርጎ፣ የመስቀሉን ቃል ኪዳን ረስቶና ዘንግቶ፣ አጋጣሚውን ተጠቅሞ ጠላትን ለመበቀል፣ ባልሠራው፣ ባልዋለበት፣ ሰውዬው ያለ፣ ሌላ አገር ነው፣ እንዳለ እየተደረገ ታስሯል፡፡ ይኼ በደል ነው፡፡ አንድ ሰው ባልሠራው ከታሰረ፣ ባላደረገው ከተወነጀለ እግዚአብሔርስ እንዴት ዝም ይላል? ሰላምን ያሳጣል፡፡

eth-demera09
ስለዚኽ ማንኛችንም ለሰላም፣ ለሀገር ፍቅር፣ ለሀገር ነፃነት፣ ለሀገር ዕድገት፣ ለኹለንተና፣ ከልመና ለምንላቀቅበት ነገር ኹሉ፣ በአንድ ድምፅ ቤትን ዘግቶ ጠላት ሳይሰማ፣ በእልክ፣ በአላስፈላጊ ነገር፣ እኔ እበልጥ፣ እኔ እበልጥ፣ እስኪ የታባትኽንስ ምን ታመጣለኽ ብሎ፣ ዘመን የፈጠረውን መሣርያ አንግቦ ከመሮጥና፤ ሌላውም የመጣው ይምጣ ልሙት ብሎ ከመጋፈጥ ይልቅ፣ ወደ መስቀሉ ተመልክተን፣ ወደ እግዚአብሔር ነግረን፣ እውነተኛ ፍርድ ሰጪው እግዚአብሔር፣ ፍርዱን ሰጥቶ፣ ሰላሙን አብዝቶ፣ በቃችኹ ብሎ ኹላችንም በሰላም እንድንኖር የቅድስት ቤተ ክርስቲያን መልእክት ነውና፣ ኹላችን ይህን ገንዘብ ልናደርግ ይገባል፡፡(ጭብጨባ እና እልልታ)

ለክርስቲያኑ፣ ለሠራዊቱ – ወታደራዊው ትእዛዝ፣ ከዚያው ካላችኹበት ኹኖ፣ ለክርስቲያኖች፣ እንደ መንፈሳዊ መሪነቴ የማዝዘው፣ ለሠራዊቱ፣ ለወታደሩ፣ ለኹሉም፤ መሣርያው ይያዝ እንጂ ምላጩን ከመሳብ ይልቅ የፍቅር መሳቢያን ተጠቀሙ፡፡ የፍቅር ማሰርያን ተጠቀሙ፡፡(እልልታ እና ጭብጨባ) አዎ፣ ሌላውም ደግሞ እስኪ ምን ታደርገኛለኽ ብለን፣ እሳት ይዞ እሳት በሚተፋ ፊት፣ በአላስፈላጊ ጉልበትና ስሜታዊነት አትተላለቁ፡፡ ወደ እግዚእብሔር ቀርበን እንጩኽ፤ እግዚአብሔር መልስ ይሰጣል፣ ከዚያ በላይ ከኾነ፡፡(እልልታ እና ጭብጨባ)

ስለዚኽ ኹላችንም በያለንበት እንደ ወገንነት እንተዛዘን፡፡ እንደ ወገንነት እንተባበር፡፡ ስንቱ ወገን ነው በበረሓ ያለቀው፤ ስንቱ ወገን ነው እንጀራ ፍለጋ በየሀገሩ የተሰደደው፤ ስንቱ ወገን ነው ባሕር የሰጠመው፤ ስንቱ ወገን ነው ዘንዶ የዋጠው፤ እዚኽኮ ሰላማችን ቢበዛ፣ መደማመጥ ቢኖር፣ መቀባበል ቢኖር፣ መፍትሔ በየሰዓቱ ቢሰጥ ኖሮ ኹሉም ሰላም ይኾን ነበር፡፡ ሰላም ካለ ደግሞ ኹሉም ነገር አለ፡፡

ስለዚኽ ዛሬ ስጋት ነው፤ መስቀል እናክብር አናክብር፤ እንዲኽ ቢኾንስ እንዲኽ ቢደረግስ፣ ብዙ ተብሏል፡፡ ይህ የምታዩት ሕዝብ፣‹ሃይማኖቴ ነው፤ የመጣው ይምጣ› ብሎ ለሃይማኖቱ ቆርጦ የመጣ እንጂ፣ አኹን እገሌ ይጠብቀኛል እገሌ ያስጠብቀኛል ብሎ አይደለም፡፡

ሃይማኖት ከኹሉም በላይ ስለኾነ፣ ተደብቆ መዋልን ትታችኹ፣ በዚኽ ሃይማኖት፣ በዚኽ መስቀል ዐደባባይ፣ የእናት ቤተ ክርስቲያንን ጥሪ ሰምታችኹና ተቀብላችኹ፣ መስቀሉን መሪና ሠሪ፣ በመስቀሉ ሰይጣንን ድል አድርጋችኹ፣ በአንድነት በፍቅር መስቀሉን እንድናከብር፣ ጥሪውን ሰምታችኹ በዚኽ የተገኛችኹ ኹሉ፣ እግዚአብሔር በኃይለ መስቀሉ ይባርካችኹ፤ እግዚአብሔር ይጠብቃችኹ፤ ኹሉንም እግዚአብሔር ይጠብቅልን፡፡

ዛሬ ለጠላት መሣቂያና መሣለቂያ የኾነችውን አገራችንን፤ በሩቅ ኹነው እየተመለከቱ፡- አለቀላቸው፣ አበቃላቸው ለሚሉት ባዕዳን፤ ትላንት፡- በሰማይ በራሪ፣ በምድር ተሽከርካሪና ተወንጫፊ ኾነው መጥተው በኀፍረት ለተመለሱ፣ የሀገራችንን ጀግንነትና ወኔ ለቀመሱ፣ ካህናቱ በመስቀላቸው በታቦታቸው፣ ጀግናው በጀግንነቱ ተከላክሎ ማንነታቸውን አሳፍሮ ለሰደዳቸው፤ ዛሬ እርስ በርሳችን በፈጠርነው መከራና ችግር መሣቂያና መሣለቂያ ከመኾን እግዚአብሔር አድነን፤ ምኞታቸውን ኹሉ አርቅልን፤ ተማምነን ተደማምጠን፣ መንግሥትም የሕዝቡን ጩኸትና ብሶት ሰምቶ፣ ችግሩን ፈትቶ፣ በሰላማዊ መንገድ እንኖር ዘንድ የእግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃዱ ይኹንልን፡፡

እንደ ዛሬው ኹሉ ለሚመጣው ዓመትም ያድርሰን፡፡ አሜን፡፡ ጸሎት፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.