በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የመምህራን ውይይት በተቃውሞ ተቋረጠ [ አለማየሁ አንበሴ]

የትምህርት መጀመሪያ ቀን እስካሁን አልታወቀም
gonder-university

ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ዘግይቶ ከትላንት በስቲያ የተጀመረውና ለ5 ቀናት እንደሚካሄድ የተጠበቀው የጎንደር ዩኒቨርስቲ የመምህራን ውይይት፤ ትላንት ሐሙስ ጠዋት በተቃውሞ የተቋረጠ ሲሆን ከሰዓት በኋላ በዩኒቨርሲቲው የውስጥ ጉዳይ መምህራኑ ውይይት አድርገዋል፡፡

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ቀደም ሲል ከመስከረም 9 ጀምሮ ይካሄዳል ተብሎ የነበረው ውይይት፤ መምህራኑ በውይይቱ ሥፍራ ሳይገኙ በመቅረታቸው አለመካሄዱ የሚታወስ ሲሆን በድጋሚ በዩኒቨርሲቲው በወጣ ማስታወቂያ መሰረት ውይይቱ ከመስከረም 19 እስከ መስከረም 24 እንደሚካሄድ ተገልፆ ነበር፡፡ ሁሙስ እለት የቀድሞ የትምህርት ሚኒስትርና የዩኒቨርሲቲው የቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር ስንታየሁ ወ/ሚካኤል፤ “የሰላማዊ መማር ማስተማር ሂደት” በሚል ርዕስ ለውይይት መነሻ የሚሆን ፅሁፍ ያቀረቡ ሲሆን፤ የመድረክ መሪውን የመነሻ ፅሁፍ ተከትሎ መምህራን በሶስት አዳራሽ ተከፋፍለው በቡድን ውይይት  እንዲያደርጉ ቢሞከርም፣ በሁለቱ አዳራሾች የነበሩ መምህራን ራሳቸውን ከንግግር በማቀባቸው ውይይቱ ተበትኗል፡፡ በሌላኛው አዳራሽ ከነበሩ መምህራን አንደኛው ድንገት ተነስቶ፤ ‹‹ሰው እየተገደለ፣ ንብረት እየተቃጠለ ምን እንድንል ነው የምትፈልጉት?›› የሚል ዱብ ዕዳ ጥያቄ የቀረበ ሲሆን የመድረኩ መሪ ንግግሩን ውይይቱ መበተኑ የዩኒቨርሲቲው መምህራን ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል።

በበነጋታው አርብ አወያዩ ዶ/ር ስንታየሁ፤ ለመምህራን ደሞዝ መጨመሩን ጠቅሰው፤ ጭማሪው የመምህሩን ጥያቄ ለመመለስ ተብሎ የተደረገ መሆኑን በመግለፅ፤ ንግግራቸውን ሊቀጥሉ ሲሉ፤ የውይይቱ ተሳታፊች በማጨብጨብና “እሽሽሽ…ሽ” የሚል ድምፅ በማሰማት አወያዩን ከመናገር የገቷቸው ሲሆን ውይይቱ በተጀመረ በ15 ደቂቃ ውስጥ በዚህ ተቃውሞ ተበትኗል፡፡
በሌላ በኩል የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ ‹‹በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መነጋገር እንኳ ባንፈልግ ከሰዓት ተገናኝተን፣ የዩኒቨርሲቲውን የባለፈው ዓመት እቅድ አፈፃፀም ገምግመን ቀጣዩ እቅድ ላይ ውይይት እናደርጋለን፤ በራሳችን ተቋም ጉዳይ ብቻ እንወያያለን›› ባሉት መሰረት መምህራኑ ከሰአት በኋላ ከፕሬዚዳንቱ ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

በተያያዘ የአማራ ክልል የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የትምህርት መጀመሪያ ቀናቸውን ያስተላለፉ ሲሆን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች የመግቢያ ቀን ለሁለተኛ ጊዜ ቢቀየርም እስካሁን የመግቢያ ቀኑም በግልፅ አልታወቀም፡፡

አዲስ አድማስ

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.