በኢሬቻ በዓል ላይ ስለደረሰው ጭፍጨፋ የጎጃም ዓለም አቀፍ ትብብር መግለጫ [ጎጃም ዓለምአቀፍ ትብብር]

የለመደ ልማድ ያሰርቃል ከማዕድ!”

gojam-alliance-satenaw-newsዛሬ የኢሬቻን በዓል ለማክበር በደብረ ዘይት (ቢሾፍቱ) በተሰበሰበ የኦሮሞ ሕዝብ እና ሌሎች ኢትዮጵያውያን ላይ ወያኔ-ኢህአዴግ ያደረሰውን የጅምላ ጭፍጨፋ የጎጃም ዓለም አቀፍ ትብብር በጽኑ ያወግዛል። ወያኔ-ኢህአዴግ የፈረማቸውን ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎችን ሁሉ ወደ ጎን በመተው ሰላማዊ ዜጎችን በጅምላ የመጨፍጨፍ አባዜውን ዛሬም አጠናቅሮ በመቀጠል የኦሮሞ ሕዝብ የመፈቃቀርና የምስጋና በዓል ላይ ርህራሄ አልባ የሆኑ የአጋዚ ወታደሮቹን በመላክ የጅምላ ጭፍጨፋ አካሂዷል። የኢሬቻ በዓል እንዳይካሄድ በየቀበሌው ማስፍራሪያ ቃላትን በታጠቁ የእንግዴ ልጁ ኦህዴድ ካድሬዎች አማካኝነት ሲቀሰቅስ የሰነበተው ወያኔ-ኢህአዴግ ያ አልሳካ ሲለው በዓሉ እንደተለመደው በአባ ገዳ ሽማግሌዎች ሳይሆን አልባሳቱን አጎናጽፎ ባመጣቸው ካድሬዎቹ እንዲመራ ወሰነ። ይህንንም ዓይን ያወጣ የወያኔ ሴራ የኦሮሞ ሕዝብ ሲያከሽፍበት የለመደ ልማድ ያሰርቃል ከማዕድ እንዲሉ ወደ ተጠናወተው ግብሩ ወደ ጅምላ ጭፍጨፋ ተዛውሯል።

“ጅራፍ እራሱ ገርፎ እራሱ ይጮሃል” እንዲሉ ዛሬ ለፈጸመው ጭፍጨፋ ቅድመ ዝግጅት ሲያደርግ እንዳልነበር ሁሉ ጭፍጨፋውን ባደረገ በሰዓታት ልዩነት ተሽቀዳድሞ ሁከቱን የፈጠሩት “ፀረ-ሰላም ኃይሎች” እንደሆኑ በመግለጽ የሃዘን ቀን አወጇል። ለወያኔ-ኢህአዴግ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሙሉ በሥርዓቱ ላይ ጥያቄ ካለው “ፀረ-ሰላም ኃይል” ነው። ይህንንም በተግባር ላለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ያሳዬ ሲሆን በዚሁ በኦሮሚያ ለአስር ወራት እንዲሁም በአማራ ላለፉት ሁለት ወራት በሰላማዊ መንገድ ተቃዉሟቸዉን ለማሰማት አደባባይ የወጡ ንፁሃን ዜጎችን በቅልብ ወታደሮቹ በቀጥታ ተኩሶ በመግደል፤ ሰልፍ ስለወጡ ብቻ በግፍ በሺዎች በማሰርና ኢሰብአዊ በሆነ ሁኔታ በማሰቃየት አስመስክሯል። ይህ አሳፋሪ ድርጊቱም ለሰዉ ልጆች ሰብዓዊ መብቶች በሚከራከሩ እንደ ሂውማን ራይትስ ዋች፣ አምነስቲ ኢንተርናሽል፤ የአፍሪካ ቀንድ የሰብዓዊ መብቶች ሊግ የመሳሰሉ ድርጅቶች የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን በመዘርዘር ያጋለጡትና ያስጠነቀቁት ሲሆን እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ በስፋት ተደማጭና ተነባቢ የሆኑት እንደ ቢቢሲ፤ ሲኤንኤን፤ አልጀዚራ፤ ዋሽንግተን ፖሰት፤ ዘጋርዲያን የመሰሳሰሉት ሚዲያዎች በተከታታይ ዘገባዎቻቸዉ ለአለም ሕብረተሰብ ይፋ ያደረጉት ጉዳይ ነዉ።

በባህልና በሃይማኖት በመቻቻል ለበርካታ ክፍለ ዘመናት በሰላምና በመከባበር ሲኖሩ የቆዩትን ኢትዮጵያውያንን ከፈፍሎ ለመግዛት ያመቸው ዘንድ በርካታ የመከፋፈያ ስልቶቹን ነድፎ እየሰራ ያለ ቢሆንም ኢትዮጵያውያን ግን ክፍፍሉን በአደባባይ ተቃውመውታል። ለወያኔ-ኢህአዴግ ይህ ህዝቡን በመግደል፣ በማሰር፣ በመግረፍና በማሰቃየት ዝም ለማሰኘት መሞከር አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ከዚህ በፊት በኦጋዴን፡ በጋምቤላ፡ በኦሮምያ እንዲሁም ባለፉት ጥቂት ወራት ብቻ ከጎጃምና ከጎንደር ከሞት የተረፉትን  በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችን በለሊት በማደን በብር ሸለንቆና ባልታዎቁ ስውር ቦታዎች አፍኖ እያሰቃያቸው ይገኛል። ይህም ብዙሃን ወገኖቻችንን በመጨፍጨፍ ሌላዉ ወገናችን እንዲሸማቀቅና አርፎ እንዲቀመጥ ከማድረግ አልፎ “ጥቂት ህገ-ወጦች ህገ-መንግስቱን በሃይል ለመናድ” የሚል ቅፅል ስም በመስጠትና በመከፋፈል የስልጣን ዘመኑን ሲያራዝም ቆይቷል፡፡ ይህ የወያኔ ዘረኛና አሳፋሪ ድርጊትም ታሪክ ይቅር የማይልው ሃቅ ሆኗል።

ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን ሕዝብን ከሕዝብ ለማቃቃር ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ እስከ ምስራቅ እየሰራ ስለሚገኝ የኢትዮጵያ ሕዝብ  በተለይ ሰፊው የአማራና የኦሮሞ ህዝብ በዓላማው በመጽናት የወያኔ-ኢህአዴግ  የመከፋፈያ ስልቶችን ለማክሸፍ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል  የጎጃም ዓለም አቀፍ ትብብር ጥሪውን ያቀርባል። ዛሬ በኦሮሞ ወገናችን ላይ ወያኔ የፈጸመው የጅምላ ጭፍጨፋን የጎጃም ዓለም አቀፍ ትብብር አምርሮ ከማውገዙም በተጨማሪ ዳግም እንደዚህ ዓይነት ኢሰብአዊ ድርጊት በኢትዮጵያውያን ላይ እንዳይከሰት ሁሉም የፖለቲካም ሆነ የሲቪክ ተቋማት በጋራ ከሕዝቡ ጋር በመቆም የወያኔን ሴራ እንዲያከሽፉ ጥሪውን በድጋሚ ያቀርባል።

በመጨረሻም በብር ሸለቆና ባልታዎቁ ስውር ቦታዎች እየተሰቃዩ ያሉትን የአማራ ልጆቸን አገዛዙ ባስቸኳይ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲለቅ ጎጃም ዓለም አቀፍ ትብብር ይጠይቃል።

ፈጣሪ በግፍ የተገደሉ ወገኖቻችንን ነፍስ በሰላም ያሳርፍልን!!!

ሕዝብ ያሸንፋል!!!

የጎጃም ዓለም አቀፍ ትብብር

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.