አለባብሰው ቢያርሱ ባረም ይመለሱ  {ይሄይስ አእምሮ}

erecha-satenaw-newsማለባበስ በጣም ጎጂ ነው፡፡ አሁን የምንገኝበት ማኅበራዊና ፖለቲካዊ አጣብቂኝ እንደእስከዛሬው ዓይነት የሽፍንፍንና የጥግንግን አካሄድን የሚያስተናግድ አይደለም – አምርሯል፡፡ አካፋን አካፋ ማለት የሚገባበት ትክክለኛ ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡ አንድን እውነት ሺህ ጊዜ ብንሸፋፍነው መገለጡ አይቀርም፡፡ ሲገለጥ ደግሞ የሚያስቀይም ስዕል ጎልቶ የሚታይበት አጋጣሚ እየበዛ ይመጣና ከመገናኘት ይልቅ መለያየት የማያመልጡት አሳዛኝ ክስተት ይሆናል፡፡

በሰሞኑ የእሬቻ በዓል የተከሰተውን ከወያኔ በቀር ሁላችንም እናውቃለን፤ ወያኔዎች ግን “ጥቂት ሰዎች (ኦሮሞዎች) በተፈጠረው መጨናነቅ ተረጋግጠው” እንደሞቱ እንጂ (በውጪዎቹ stampede ሲሉ ሰምተዋልና) በነሱው ታዛዥ “ኢትዮጵያውያን” አልሞ ተኳሽ ወያኔያዊ አልቃኢዳዎች በመትረየስና በጭስ ጋዝ እንደተረፈረፉ ሊያምኑ አይፈልጉም፡፡
ከዚህ የእሬቻ ዕልቂት ሌሎቻችን ምን እንማራለን?

ከዚህ ዕልቂት የምንማረው ነገር እጅግ ብዙ ነው፡፡ በመሠረቱ ይህ ዕልቂት በጎሣ ላይ ያነጣጠረ እንዳልሆነ ማመን እፈልጋለሁ፡፡ ኢትዮጵያውያን ለወያኔ ከፋፋይ ሥርዓት እጅ ሰጥተን ሁሉንም ነገር ወደዘር እንመነዝረዋለን እንጂ በአንዱ ሰው ውስጥ ብዙ ዘር በሚገኝበት እንደኢትዮጵያ ባለ ሀገር ውስጥ ሙከራው የለም ማለት ባይቻልም አንድን ዘር ለይቶ የማጥቃት ሙከራ እምብዝም አይሳካም፡፡ ምክንያቱም በሕዝብ የዘመናት ማኅበረሰብኣዊ ሽመና የተነሣ ማኅበረሰቡ አንዱን ሲሉት ሌላውን ነው – ኦሮሞ ሲሉት ትግሬ ነው፤ ትግሬ ሲሉት ደግሞ አማራ ነው፤ ጎንደሬ ሲሉት አርሲ ነው – ወለጋ ሲሉት ደግሞ ሲዳሞ ነው፡፡ ሁሉም ተቀያይጦ አንዱን ስትገድለው በውስጡ ሌላውም አብሮ ይሞታል፡፡ ከዐማራና ትግሬ ወላጆች የተገኙ ልጆችን ብትፈጅ ላንተ አንዱን ወይ ሌላውን የገደልክ ይመስልሃል እንጂ ሁለቱንም ነው ባንድ ጥይት የፈጀሃቸው፡፡ እንደፍቅሬ ቶሎሳ አንድ ቀደም ያለ መጣጥፍ ከሆነ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ በመዋሃዱ አንዱን ከሌላው ለመለየት የሚቻል አይደለም – ወያኔዎች ውኃና ዘይት ሊያደርጉን ቀን ከሌት ቢማስኑም ፈጣሪ በፀጋው ወተትና ውኃ አድርጎ አንዳችንን በአንዳችን ውስጥ እንደሰም አቅልጦ ውሁድ ሻማና ጧፍ አድርጎናል፤ ጊዜ ይፍጅ እንጂ ደግሞ ወያኔ ያዞረብንን ትብታብ በአንድነት በጣጥሰን አንዲት ታሪካዊት ሀገራችንን በጋሪዮሽ የብርሃን ፀዳላችን የምናደምቅበት የነፃነት ዘመን በቅርቡ መምጣቱ አይቀርም፡፡

ቋንቋ እንደሆነ በመልመድ ወይም በመማር እንጂ በባሕርያዊ የደም ትልልፍና በሀብት ውርስ የፍርድ ሂደት ስለማይገኝ ዐማርኛ የማይችል “ዐማራ” በኦሮሞ ውስጥ ብታገኝ ወይም ትግርኛ የማይችል “ትግሬ” በኦሮሞ ውስጥ ብታገኝ ይህ ክስተት ከፍ ሲል የሰው ልጅ ዝቅ ሲል ደግሞ የኢትዮጵያውያን ልዩ መገለጫ በመሆኑ የሚያስደንቅ አይደለም፡፡ ለዚህም ነው የወያኔ የዘር ቀመር ወንዝ የማያሻግር ወፍ ዘራሽ የታሪክ አራሙቻ መሆኑ የሚነገረውና ሀገር አጥፊነቱ ዘወትር የሚገለጸው፡፡ ሰሚ በመጥፋቱ ግን ሀገርና ሕዝብ ላይ በቀላሉ ሊቀለበስ የማይችል ጉዳት እየደረሰ ነው፡፡ ደጋግ ሰዎች እየጠፉ በክፉዎች ተከበናልና አንድዬ ይሁነን፡፡

ለማለት የፈለግሁት በዚህ የእሬቻ በዓል የሞቱት ሁሉም ኢትዮጵያውያን እንጂ አንዱ ዘር ማለትም ኦሮሞ ተመርጦ እንዳልሆነ ለማስታወስ ነው፤ ይህንንም ስል የማንንም ወንጀል ለመደበቅ ሣይሆን እውነቱን ለመግለጽ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ወያኔ በዚህ ዕልቂት የፈረደብን በሁላችንም ላይ እንደሆነ መረዳት አለብን፡፡ ለነገሩ በዓሉን ለማክበር ከሁሉም ሥፍራዎችና ከሁሉም ጎሣዎች የተሰባሰቡ ኢትዮጵያውያን በሥፍራው በመገኘታቸው የኦሮሞ ሟች ቁጥር ሊበዛ እንደሚችል ቢገመትም ሁሉም ሞቷል ማለት እንችላለን፡፡ ማንም ይሙት ማን ግን የሞተው ሰው በመሆኑ፣ በዚያም ላይ ምናልባት ሁሉም ኢትዮጵያውያን መሆናቸው ስለሚገመት የሀዘኑን ምንጭ ወያኔን ሳይጨምር ሀዘኑ የሁላችንና የመላዋ ሀገራችን ነው፡፡ ነፍስ ይማር፡፡

ፍርዱ በሁላችንም ላይ ከሆነ ዘንዳ በወያኔ ላይ መነሳት ያለብን ሁላችንም በጋራ ሆነን ነው፡፡ የያዝነው መንገድ ግን እንደዚህ አይደለም ወይም አይመስለኝም፡፡ ጥቃቱ በሁላችንም ላይ የሚደርስ ሆኖ ሳለ የትግላችን አቅጣጫ ግን የተፈናጅራ (የተለያዬና ርስ በርስ የሚቃረን) ሆኖ ለኛ ተጨማሪ ዕልቂትን የሚያስከትል ለጠላቶቻችንና ለገዳዮቻችን ደግሞ ሠርግና ምላሽ ሆኖ ጮቤ የሚያስረግጣቸው ነው፡፡ በቢሊዮን ዶላሮች በሚገመት የበጀት ምደባ የማያገኙትን ከፋፋይ የትግል ሥልት በመከተላችን ወያኔዎች እኛን በጅልነታችን እንደሚያመሰግኑን አልጠራጠርም፤ በዚህ ረገድ ያጠመዱት ወጥመድ ተሳክቶላቸዋልና በጣም ዕድለኞች ናቸው፡፡
እውነቱን ለመናገር ብዙ አክራሪነት ይታየኛል፡፡ አክራሪነት ደግሞ ያለያያል እንጂ ወደ አንድ የጋራ መድረክ አያመጣም፡፡ ሕዝቡ በተለይም ወጣቱ ሰከን ማለት አለበት፡፡ አንድን የዘር ሐረግ ብቻ እየነቀሱ በዚያ ላይ ማጠንጠን መጨረሻ ጥፋት መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ ከወያኔ ካልተማርን ፈጣሪ ራሱ ወርዶ ወንበር ዘርግቶ አያስተምረንም፡፡ “ኦሮሞና ዐማራ አንድ ሆኑ፤ ሌሎች ጎሣዎችንም በኅብረት አስተሳስረውና አማክለው ለሀገራዊ ነፃነት ፈር ቀዳጅ የጋራ ትግል ጀመሩ” ተብሎ ከመነገሩና በብዙዎች ዘንድ ከመወደሱ በሰሞኑ የእሬቻ በዓል አከባበር ላይ የታዘብነው ሁሉንም የማያካትትና ብዙኃንን ትቶ የአንድን ንቅናቄ ዓላማ ብቻ የሚያቀነቅን የትግል አቅጣጫ ትኩረት ሳቢ ነበር ማለት አይቻልም፡፡ ከስሜት ካልወጣን፣ ከጎጠኝነት ወይም ከክልላዊ የተናጠል ሩጫ ካልታቀብንና ለወል ማንነታችን ካልተጋን የጠላቶቻችን መሣሪያ እንደሆንን እንዘልቃለን፡፡
የማየው አክራሪነት ዘር ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ብዙ ወጣቶች ኦሮሞን ከኢትዮጵያ ገንጥለው የወያኔን አጀንዳ ለማራመድ ሲሞክሩ ይታያል፤ የፈረደበትን ወያኔ ልጥቀስ እንጂ ከወያኔ በማይተናነስ የዘውገኝነት አረንቋ ገብተን ዳግም እንድንዳክር የሚያስገድድ በዘረኝነት አባዜ የተለወሰ ድግስ የሚደግሱልን ወገኖች ሊኖሩ እንደሚችሉ በዚህ አጋጣሚ ባስታውስ ነውር ያለበት አይመስለኝም፡፡ እንደነዚህ ዓይነት ወገኖች ሃሳባቸው በተለያዩ ከፋፋይ ድርጊቶች ይገለጻል፡፡ ወልጋዳው አካሄድ ተጠናክሮ የሚታየው በውጪ ሀገራት በተለይም እንደልብ በሚፈነጩበት በዲያስፖራው አካባቢ ቢሆንም በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ይህ ወረርሽኝ ወደ ሀገር ውስጥም ገብቶ ስሜት ቆንጣጭ በሆነ ሁኔታ እያቃቃረን ይገኛል፡፡ ልብ ልንገዛና ወደኅሊናችን ልንመለስ ባለመቻላችን ሌላው ሁሉ ቀርቶ የእግዚአብሔርን ቤት እንኳን በዘርና በጎሣ እየከፋፈልን “የአቡነ አረጋዊ ቤተ ክርስቲያን”፣ “የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ደብር” ወዘተ. በሚል የመንግሥተ ሰማይንና የገሃነመ እሳትን ነዋሪዎች ሳይቀር በሣቅ የሚያፈነዳ ከንቱ የማይም ትያትር የምናሳይ “ኢትዮጵያውያን” ሞልተናል፡፡ እዚህ በሀገር ቤት መቼም ከመኪና ታርጋ ጀምሮ እስከ ባንክና ሌሎች የንግድ ተቋማት ድረስ በዘር ልምሻና በፆታና ሃይማኖት ድልድል ተኮድኩደን “ወጋገን ባንክ”፣”አንበሣ ባንክ”፣ “አዋሽ ባንክ”፣ “ዳሸን ባንክ”፣ “ንብ ባንክ”፣ “ብርሃን ባንክ”፣ “እናት ባንክ” … እያልን ስንጃጃል የሚታዘበን ቢኖር የአሣራችን ብዛትና የቂልነታን መጠን ዳር ድንበር የሌለው መሆኑን በግልጽ ይረዳል፡፡ ዘመን ሲያልፍ የምናወራው ስንትና ስንት የነውር ሥራ አለን መሰላችሁ፡፡

ሰሞኑን ከታዘብኳቸው እንከኖቻችን ጥቂቶቹ፡-
ትዝብት አንድ – አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ የኢትዮጵያ ባንዴራ የዐማራ (ብቻ) አይደለችም፡፡ ይህች ባንዴራ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኦሮሞዎችና ዐማራዎች እንዲሁም ትግሬዎችና ሌሎች ጎሣዎች በመላዋ ሀገራችን ከውጭ ወራሪዎችና ከውስጥ ምንደኞቻቸው ጋር በተካሄዱ ጦርነቶች ያለቁላት የቀስተ ደመና ምሳሌ ናት፡፡ ይህች ባንዴራ ለተንኮል ሲባል ቤተ ሙከራ ውስጥ ተፈልስፎ እንደሚሰጥ ዘመን ወለድ የጠላት ፍብርክ ባንዴራ ሳትሆን እነአባመላ ዲነግዴ፣ እነጄኔራል ደምሴ ቡልቶ፣ እነቀ.ኃ.ሥላሴ፣ እነመንግሥቱ ኃ.ማርያም፣ እነደጃች ገረሱ፣ እነጄኔራል ጃጋማኬሎ፣ እነአብዲሣ አጋ፣ እነ ስንቱን የኦሮሞ ጀግና አንስቼ ልዝለቀው – እነዚህ ሁሉ የኦሮሞ የጦር አበጋዞችና የሀገር መሪ ነገሥታት የተዋደቁላት ባንዴራ ዛሬ ለአንድ ጎሣ – ለዐማራ – በችሮታ ተሰጥታ በዚህ የተገፋ ሕዝብ ስም ስትጎሳቆል ማየት ከማሳዘኑም በላይ የታሪክን ፍርድ የሚጋብዝ ከፍተኛ ጥፋት እንደመፈጸምም ይቆጠራል፡፡ የሕዝብን የጋራ አንጡራ ሀብት ቀምቶ ለአንድ ነገድ ብቻ ማስታቀፍ ነውርና ታሪክን አለማወቅ ወይም ጨርሶ መካድ ነው፡፡ ይህ በዘመን የሾመጠረ ጠላ ሰክሮ እምቡር እምቡር ማለት ደግሞ የትም እንደማያደርስና ውሉን የማይስተው ታሪክ ትክክለኛ መስመሩን ሲይዝ ለትዝብት እንደሚዳረግ መረዳት ተገቢ ነው፡፡ ሸረኛ ሰዎች በዘረጉት የወጥመድ ጉድጓድ ውስጥ ገብቶ በስሜት ስካር ከመጨፈር ይልቅ ወደ እውነተኛው ታሪካችን በመመለስ በወያኔ ሤራ የላሉና የተበጣጠሱ የአብሮነታችንን ገመዶች ማጠባበቅ ይሻለናል፡፡ ስሜትና እውነት እንደሚለያዩ ካልተገነዘብን ዘመን ወለድ ስካራችን በቀላሉ አይለቀንም፡፡

ስለሆነም ወደኅሊናችን በመመለስ የጥንት የጧትን አእምሯዊና ባህላዊ የጋራ ሀብትና ንብረት አክብሮ መያዝ ይኖርብናል፡፡ ንፋስ ወደነፈሰበት ሁሉ እየዞርን አንገታችንን ማጣት አይገባንም፡፡ በአንድ በኩል ኅብረትና አንድነት ፈጠርን እያልን በሌላ በኩል የጋራ ሀብታችንን መጥላትና ወደ አንድ ጎሣ መለጠፍ ተገቢም ወቅታዊም አይደለም፡፡ በአንድ ጊዜ ሁለት መሆን አይቻልም፡፡ ለመሠሪዎች ተንኮል መንበርከክም ለተራዘመ የግፍ አገዛዝ ከመዳረግ ውጪ አንዳችም ፋይዳ የለውም፡፡ ከጎጂ መሠረት አልባ እልህ ወጥቶ ምክንያታዊና ሰብኣዊ ፍጡር መሆን ይገባል፡፡ በኦሮምኛ ትውፊት “ትናንት አልፏልና አያስጨንቅህ፤ ነገም ያንተ ላይሆን ይችላልና እጅግም አያሳስብህ፤ ዛሬ ግን በእጅህ ያለ በመሆኑ በጥበብና በማስተዋል ተጠቀምበት” የሚል በሳል ብሂል አለ፡፡ ብልኆች ይህን ብሂል አጢነው በአግባቡ ይጠቀሙበታል፤ ዝንጉዎች ግን በሰው አልባሌ ምክር እየተወሰዱ ጊዜያቸውንና አቅማቸውን በሞላ ለአሉታዊ ዓላማና ግብ ያውሉታል፤ በመጨረሻው ግን ለፀፀት መዳረጋቸው አይቀርም፡፡
በደብረ ዘይት ዕልቂት የኢትዮጵያን ንጹሕ ባንዴራ ብመለከት ኖሮ ደስታየ ወሰን ባልነበረው፡፡ የወያኔን ባንዴራና ከፋፋይ ወገኖች የደረቱልንን ቡትቶ አስወግደን በመጣል ከፍ ሲል የጠቃቀስኳቸውና ሌሎች ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን የተሰውላትን ንጹሕ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ ዓላማ ብንሰቅል ኖሮ ትግላችንን በሰማንያው የኢትዮጵያ ነገድና ጎሣ ሁሉ ልናስደግፈው በቻልን ነበር፡፡ ሰይጣን ይሁን ወይም ወያኔዊ የዓመታት መርዘኛ ፕሮፓጋንዳ ያን ብልኃትና ጥበብ ሰውሮብን ለሕዝብና ለመሬቱ ባዕድ የሆነ ሌላ ባንዴራ በማሳየታችን ትግላችንን አሳነስነው፤ የሌሎችንም ድጋፍ አቀዘቀዝነው፡፡ ተገቢ አይደለም፡፡ በውጭ ሀገር በሚደረጉ ሰልፎችም ይሄው አዲስ ክስተት ይታያል፡፡ በስመ “እነእንትናን ላለማስቀየም” ሲባል እርጥብን ከደረቅ፣ ነጭን ከጥቁር መሞጀር አግባብ አይደለም – እውነቱን ልቦናችን እያወቀው – የልቦናችንን ማወቅም ሁሉም ወገን እየተረዳው አጉል መሸዋወድ ተገቢ አይደለም፡፡ ያለህን የጋራ ንብረት በመጣል አይደለም ማንነትህን የምታስጠብቀው፤ ያልነበረህን በነበረህ በመለወጥና አዲስ ማንነት በመደረት አይደለም ፍቅርና አንድነት የምታዳብረው፡፡ “ያልወለድኩት ልጅ ቢለኝ አባባ፤ አለው አፌን ዳባ፣ ዳባ” ይባላል፡፡ “የራስህ ጉዳይ ነው” እንዳትሉኝ እንጂ ለምንድን ነው እኔ የብኣዴን ተብዬውን ባንዴራ ከነቀለሙ እንኳን እስካሁን ላውቀው ያልቻልኩት? ማንም እየተነሣ የላዩ ላይ በል ባለው ቁጥር ባንዴራ እየጠፈጠፈ በየአምሳና መቶ ዓመቱ የሚያሸክመኝ ነፈዝ ከሆንኩ ምኑን ሰብኣዊ ፍጡር ሆንኩት! እንደዚያማ ከሆንኩ የኔን ነፃነት፣ የማሰብና የማገናዘብ ችሎታየን ምን ወሰደብኝ ሊባል ነው? አሜሪካውያንን ተመልከት፣ እንግሊዛውያንን ልብ በል፡፡ ማንም ሞቅ ያለው የጨረቃ ሌሊት ዕብድ ሁሉ እየመጣ ባንዴራን አይለውጥም፤ ሀገር እንደማይለወጥ ሁሉ የጥንት አባቶችና እናቶች የሞቱለት ሰንደቅ ዓላማም ግርግር በተፈጠረ ቁጥር አይቀየርም፡፡ ለዚህም ነው በባንዴራ የሚደረግ ድርድር ቅጥ ያጣ ድርድር የሚሆነውና ሰውን አስደሰትኩ ብለህ የጋራ ማንነት መገለጫህን ዋጋ ማውረድ የማይገባህ፡፡ ይታሰብበት፡፡
ማለባበስ ይቅር የምለው እንግዲህ ከነዚህ መሠረታዊ ነጥቦች በመነሳት ነው፡፡ ይህን ጉዳይ በሚመለከት ከብዙዎች ኦሮሞዎችና ሌሎች ጓደኞቼ ጋር ስንጨዋወት የተረዳሁት ሃቅም ይሄው ነው፡፡ ትግላችን እንዲሰምር ከታይታዊ የይስሙላ መተባበር ይልቅ ለእውነተኛ የመተማመንና የመዋደድ ስሜት መገዛት አለብን፡፡ ትብብራችን የስትራቴጂ ወይም የሥልት ከሆነ ቀደም ሲል እንደተናገርኩት አለባብሶ ማረስና ለዐረም ሲመለሱ መቸገር ነው፤ ማኅበራዊ ዕርቅና ስምምነት ግልብ ሳይሆን ልባዊ መሆን አለበት፤ የሚያስተማማና እየቆዬ የሚያመረቅዝ ነገር መኖር የለበትም፤ የሚያሸምቁበት ሸፍጥም ሊኖር አይገባም፤ ፍጹማዊ መግባባትና ግልጽነት በተስማሚዎች መካከል ሊሠፍን ይገባል፡፡ የዛሬ ዐርባና ሃምሳ ዓመት ያልነበረ ነገር ዛሬ መጥቶ የዛሬ ዐርባና ሃምሳ ዓመታት የነበሩ ፍጡራንን ሊከፋፍልና የሚደርስባቸው በደልና ጭቆና ላይ ልብ ለልብ ተገናኝተው እንዳይታገሉ ደንቃራ ሊፈጥርባቸው አይገባም፡፡

“ከትናንት በስቲያ እገሌ ገዝቷል፤ ከትናንት እስከዛሬ እነእገሌ እየገዙ ነው፤ ከዛሬ ጀምሮ ደግሞ የእኛ የመግዛት ተራ ነው” የሚሉት አስቂኝ ፈሊጥ ደግሞ በጭራሽ አያዛልቅም – ይህ ሥልት በዚህ በምንገኝበት የዴሞክራሲ ዘመን ለመታገያና ለማታገያነት ቀርቶ ሊሰሙት የሚያሰጠላ ያረጀ ያፈጀ ሥልት ነው፡፡ በመሠረቱ ማንም ቢገዛ ለዘመዶቹና ለጥቂት ወገኖቹ የሀብት መንገድ ይከፍት እንደሆነ እንጂ በቋንቋና በዘር ምክንያት ሁሉም አያልፍለትም፡፡ ይህ ቢሆን ኖሮ እንደትግሬ ወያኔ ዘረኛ እንዳለመኖሩ አዲስ አበባ ላይ የሚለምን አንድም የትግሬ ጎሣ አባል ባልነበረ፡፡ የአዲስ አበባን መንገዶች ሁሉ ተመልከቱ – ከትግራይ የመጡ የኔ ቢጤዎች እንደማንኛውም ጎሣ አባላት እየለመኑ ታገኟቸዋላችሁ፤ ከጠቅላላው የተጋሩ ብዛት አኳያ ያለፈለት ትግሬ ጥቂት ነው፡፡ ያላለፈለትና እንደኛው እንደብዙዎቹ መከራውን የሚበላው ትግሬ ብዙ ነው፡፡ እርግጥ ነው – እንደዬግለሰቡ አእምሯዊ ጥንካሬ የሚታይ ሆኖ አብዛኛው ወይም በጨዋ አነጋገር ጥቂት የማይባለው ትግሬ ችግሩን በሥነ ልቦናዊ ኩራት ሊያስታምምበት የሚያስችለው ብዙዎቻችን በወቅቱ በግልፅ ይታያል ብለን የምናምነው ትግሬያዊ የበላይነት የሚፈጥርለትን ባዶ ተስፋ ሊሰንቅ ይችል ይሆናል፡፡ ተስፋ ግን ሆድን አይሞላምና የመንደሬን ነዋሪ ወይዘሮ አብረኸትን ከአምባሻ ሻጭነት ወይም ወጣት ግደይን ከቁራሌነት አውጥቶ ባለፎቅ ያደረገ ትግሬ ወያኔ እስካሁን አላገኙም – እውነቴን ነው፤ ረጋ ብለን ከታዘብን ስሜትና እውነት እንደሚለያዩ ማጤን እንችላለን፡፡ ስለሆነም ይህ በዘር ላይ የተመሠረተ የአገዛዝ እሳቤ ልቦለዳዊ እንጂ እውናዊ አይደለም፡፡ እናም ወደ አቅላችን እንመለስ፡፡ ደግሞም የአሁኑን የወያኔ አገዛዝ ለታሪክ ፍርድ ትተን ለጊዜው እንርሳውና የዱሮዎቹን አገዛዞች ብናይ ያን ያህል በዘርና በጎሣ የተመሠረቱ ናቸው ብለን የምንወቅሳቸው እንዳልነበሩ ጤናማ ኅሊና ያለን በዕድሜ አንጋፋ ሰዎች የምንፈርደው ጥሬ እውነት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የለየለት ዘረኝነት የታየው አሁን እንጂ የቀድሞዎቹ እኩል ይገድሉን፣ እኩል ይቀጠቅጡን፣ እኩል ይጨቁኑንና ያንላቱን ነበር እንጂ ለአበበና ለደቻሳ ወይም ለዘበርጋና ለሐጎስ በሚል የተለዬ ሕግ አውጥተው ከፈሪሃ እግዚአብሔር መንገድ የሚያፈነግጡ አልነበሩም፡፡ ባልነበረ ነገር አንኮነን – ቢያንስ ገሃድ የወጣና በመርህ ደረጃ የጸደቀ የአሁኑን መሰል አድልዖዊ የአገዛዝ ሥልት አልነበረም፡፡

ትዝብት ሁለት ፡- ቋንቋን በሚመለከት ደግሞ ጥቂት የምጨምረው ነገር አለኝ፡፡ ዐማርኛ መናገር የሚችል ኦሮሞ ዐማርኛን መናገር ለምን ይጠየፋል? የቋንቋና የሰው ግንኙነት እኮ የመራጃና (tool) የሰው ግንኙነት እንደማለት ነው፡፡ ቋንቋ ማለት እንግሊዝኛም በለው ቻይንኛ ወይም ዐማርኛም በለው ኦሮምኛ ከአንድ ዶማ ወይም ከአንድ ማረሻ አይለዩም፡፡ በቃ፡፡ ልዩነቱ – ልዩነት ከተባለ – ዶማው ለመቆፈሪያነት ሲውል ቋንቋው ደግሞ ለመግባቢያነት ማገለልገሉ ብቻ ነው – አንዱ ይታያል ሌላው አይታይም፤ አንዱ ቁሣዊ ነው ሌላኛው ረቂቅ የአእምሮ ሥሪት ነው፡፡ ከዚያ ውጪ “ያንተ ቋንቋ፣ የኔ ቋንቋ” በሚል ይህን ያህል ልንወራከብበትና በሥነ ልቦና ልክፍት ተጠምደን ልንፋጅበት የሚገባን አይደለም – በዚህ ረገድ ብዙ አለማወቅና ብዙ የስሜት መነዳት ይታያል፡፡ እንደኔ ቢቻል ሁላችንም ኦሮምኛ ብንችልና በርሱ ብንጠቀም ደስ ባለኝ፡፡ እንደታሪክ አጋጣሚ ሆኖ ግን ሰማንያው የኢትዮጵያ ጎሣ የሚግባባው በዐማርኛ ሆነና ቋንቋው ለራሱም ዐማርኛ ቋንቋ ተናጋሪ ለሚባሉትም ጥላቻን አትርፎ ቁጭ አለ – ምሥጋናና ወሮታ ማስገኘት ሲገባው፡፡ አንዳንድ ዕቃ ሳትወድ በግድ ዕዳ ያመጣብሃል፤ አንዳንድ ዕቃ ደግሞ ሸጠኸውም ሆነ አከራይተኸው ወይም አውሰኸው ጥቅም ታገኝበታለህ፡፡ ዐማርኛ ግን ለዐማሮች ያስገኘላቸው የዕልቂት ዐዋጅ ሆነ፡፡ የበሉበትን ወጪት መስበር መቼም እንደኢትዮጵያውን የሚያውቅበት የለም፡፡ …

ዐማርኛን በጋራ መግባቢያነት መጠቀም ካልፈለግን ደግሞ ከሌሎቹ አንዱን እንምረጥና እንጠቀምበት፡፡ በጎች እንኳን ሲቀላቀሉ “እምባ” ይላሉ፡፡ እኛ ደግሞ ሰዎች ስለሆንን ስንገናኝ አንድ ወይ ሁለት እንዳስፈላጊነቱም ከዚያ በላይ የወል መግባቢያ ያስፈልገናል፡፡ ዐማርኛ በታሪክ አጋጣሚ ይህን ቦታ ሊያገኝ ቻለ እንጂ ቀደምት ተናጋሪዎቹ ወረፋ ይዘውና ከንጉሥ ደጅ ጠንተው ይህን የመከራ ዕጣ ፋንታ የተቀበሉ አይመስለኝም፡፡ ታዲያ ለምን እንጠየፈዋለን? ሰዎቹንስ ባልሠሩት ሥራ ለምን እንጠላቸዋለን? ሌላ የተሻለ አማራጭ እስክናገኝ ብንጠቀምበት ምን እንጎዳለን?

አስፈላጊ ሆኖ ካገኘነው ቋንቋውን ይናገሩታል የሚባሉ ሰዎችን ግዴለም እንራቃቸው – ይህም ስህተት መሆኑ እንዳለ ሆኖ፡፡ እነሱን መጥላትና የነሱ ስለመሆኑ እንኳን በወጉ የማይታወቀውን ዐማርኛን መጥላት ግን ስህተት ነው ብቻ ሣይሆን ጤናማነት የሚጎድለው የተዛባ አመለካከት ነው፡፡ ባሏን የጎዳች መስሏት ስስ የሰውነቷን ክፍል በጋሬጣ እንደቧጨረችው ሴት መሆን ይቅርብን፡፡ ለምሳሌ ኦሮሞና ዐማራ ተባበሩ በተባለበት ማግስት እንኳን “በእናቴ ዐማራ ነኝ” የሚለው ሣተናው የባህር ማዶ ታጋይ ዐማርኛን ሲጠየፍ ይስተዋላል፡፡ ለምን? ዐማርኛ ቋንቋ ሁሉንም የኢትዮጵያ ነገዶችና ጎሣዎች አስተባብሮ ባንድ ግዛት ውስጥ ተቻችለው እንዲኖሩ ማድረጉ ስህተት ይሆን? ይህ ዓይነቱ ጠባይ በቅጡ ካልተያዘ ጠባብነት የሚመነጭ ሲሆን በሌላም ወገን የቋንቋን ተፈጥሯዊ የኢ-ባሕርያዊነት ጠባዩን በውል ካለመገንዘብ የሚመጣ በሽታ ነው፡፡ ቋንቋና ሸሚዝ አንድ መሆናቸውን ለሚረዳ ለእንደኔ ዓይነቱ ሰው ግን ሰዎች እንኳንስ በሰዎች ቋንቋ በዝንጀሮ “ቋንቋ”ም ቢግባቡ ድንቅ ነገር እንጂ አያስከፋም፡፡… ይህቺ በቋንቋ ምክንያት ቱፍ ቱፍ የሚሉ ሰዎች በስስ ሰብኣዊ ጠባይ በመግባት መሰሎቻቸውን ወይም ቢጤዎቻቸውን በቀላሉ በማስቆጣት ለሚፈልጉት ዓላማ ለማነሳሳት እንጂ በርግጥም የቋንቋ ጉዳይ ያን ያህል ሚዛን የሚደፋ ሆኖ እንዳልሆነ ሳይገባቸው ቀርቶ አይመስለኝም፡፡

በነገራችን ላይ አንድ ቋንቋ ለብዙኃን የወል መግባቢያነት እንዲውል ሲደረግ ቋንቋውን በአፍ መፍቻነት የሚጠቀሙት ሰዎች ቁጥር ከቁብ አይጣፍም፡፡ እንደዚያ ቢሆን ኖሮ በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያ የጋራ ቋንቋ ከምኞት ባለፈ ትግርኛ ሊሆን በቻለ ነበር፡፡ የዓለም ቋንቋ ደግሞ መንደሪን የሚባለውና ከአንድ ቢሊዮን ሕዝብ በላይ የሚገመት ቻይናዊ የሚናገረው ቋንቋ በሆነ ነበር፡፡ ምሥጢሩ ያለው ቋንቋው በድልድይነት ስንቶችን ያገናኛል? የሚለው ነው እንጂ “ስንቶች በአፍ መፍቻነት ይናገሩታል?” የሚለው አይደለም፤ ይህን እውነት አለማወቅ ለቋንቋ አርበኝነት በማጋለጥ ላልተፈለገ ኩርፊያና ላልተጠበቀ ጉዳት ይዳርጋል፡፡ ኅብረ ብሔራዊ በሆኑ የኛን መሰል ሀገራት ውስጥ አንድ ቋንቋ ለጋራ ቋንቋነት የሚመረጠው “ከራሴው ውጪ የማንንም ቋንቋ አልጠቀምም” በሚል በርህን በመጠርቀም ሣይሆን “የትኛው ቋንቋ በየትኞቹ ማሕበረሰቦች ዘንድ በስፋት ይነገራል?” የሚል ጥናት በመመርኮዝ ነው፡፡

ዐማርኛን ለመግደል ብለው ወያኔ ትግሬዎች ብዙ ሠሩ፤ በሥልጣን ቆይታቸው የዐማርኛን ጥቅም በሂደት ሲረዱ ግን ዐማሮችን የማጥፋት ዋና ተልእኳቸውን ለአፍታም ሳይዘነጉ ቋንቋውን ነጥለው ለልጆቻቸውና ለካድሬዎቻቸው በደንብ ማስተማሩን ተያያዙት፡፡ እነሱ አካሄዳቸውን ሲለውጡ ሌላው የነሱን የቀደመ ፈለግ ተከትሎ ዐማርኛን ሲጠየፍና ሲያንቋሽሽ ቆይቶ በመጨረሻው ሲያጤነው አዲስ አበባ የገቡት ልጆቹ የዘበኝነትና የጽዳት ሥራ ለመያዝ እንኳን መቸገራቸውን ተገነዘበ፤ በዲግሪ ተመርቀውም አዲስ አበባ ሲመጡ ወይ እንግሊዝኛ አልቻሉ ወይ ዐማርኛ አልቻሉ ከሁለት ያጣ ጎመን እየሆኑ መቸገራቸውን ሲገነዘቡ በወያኔ የመበለጥ ሞኝነታቸውን በማሰብ አምርረው አዘኑ፡፡ ይህ ነው እንግዲህ አንዱ የወል ቋንቋ ዕንቆቅልሽ – ቋንቋውንና ተናጋሪዎቹን የመጥላትና የመውደድ ጉዳይ አይደለም ወንድሜ፡፡ ስለዚህ በምናውቀው ልሣን ሁሉ እንግባባ እንጂ የኩራት ድንበር አናብጅ፤ አንተ በዐማርኛ ላይ አፍንጫህን ብትነፋ ዐማርኛ አይጎዳም፤ አንቺ በትግርኛ ወይም በኦሮምኛ ላይ ፊትሽን ብታዞሪ እነሱ ግዑዛን ናቸውና አይጎዱም፡፡ ቋንቋ የትም ብትሄድ ወስፋትህን የምትሸነግልበት የእስትንፋስህ መሠረት የሆነ የመግባቢያ መሣሪያ እንጂ ጠላትህ ሊሆን አይችልም፡፡ ያን ቋንቋ በአፍ መፍቻነት ማንም ይናገረው ማን ላንተ ያለው ጠቀሜታ ግን ከምንም በላይ ነው፡፡ ዓለም ወደ አንድ መንደርነት እየተለወጠችና አንድነቷን እያጠናከረች በምትገኝበት የግሎባላይዜሽን ዘመን በራስህ ጠባብ ዓለም ውስጥ በምትፈጥረው ምክንያት የተነሣ ለዚህና ለዚያ ቋንቋ ያለህ አተያይ ቢንሻፈፍ ተጎጂው አንተው ብቻ ነህ፤ ኩራት እራት መሆኑ ቀርቷል ወዳጄ ልቤ – (እንደቃና ቲቪ ‹ወዳጄ ታየር› ልበልህ ይሆን?)፡፡ በወያኔ የቋንቋ ፌዴሬሽን ሳቢያ ስንቶች እንደተጎዱ እኔ ነኝ የማውቀው – መምህር ነበርኩና፡፡
ስለዚህ ግዴላችሁም ሌላ የምንተካው እስክናገኝ ድረስ ለጊዜው በዚሁ ቋንቋ – ባማርኛ – እንጠቀም፡፡ በማይጨበጥ ምክንያት በጠላቶቻችን ተገፋፍተን ልንሰባብረው የሞከርነውን ማኅበረሰብኣዊ ድልድይ በአፋጣኝ እንጠግን፡፡ አለበለዚያ እየሞትን ነው፤ እግዜር አይበለውና በጠላቶቻችን ምክርና ሰይጣናዊ አስተምህሮ ከቀጠልን የሁላችንም ወረደ መቃብር በአጭር ጊዜ ውስጥ ይፈጸማል፡፡ የመከፋፈላችን ብሥራት ለጠላቶቻችን የደስታ ምንጭ ነው፡፡

“አገባሻለሁ ያለ ሁሉ ላያገባሽ ከባልሽ ጋር ሆድ አትባባሽ” የሚለውን የዐማርኛ ብሂልና “ይበጃል ቢሉን አህያ አረድን፤ አይበጅም ቢሉን ጠራርገን ጣልን፤ ‹(የአህያው ሥጋ) ይበጃችሁ ነበር እኮ› ቢሉንና ሄደን ብንፈልገው አጣነው” የሚለውን የኦሮምኛ ብሂል እንድታጣጥሟቸው በመጋበዝ ልለያችሁ፡፡ ለሁላችን መልካም ክራሞት፤ ለሀገራችንም ሰላምንና በአዲስ ሕዝባዊ ኢትዮጵያዊ መንግሥት ሥር መረጋጋትን ተመኘሁ፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.