ወጣቶች ለምን አክራሪ ሙስሊም አማፂ ቡድኖችን ይቀላቀላሉ

ልደት አበበ

5208d5c4550ddአክራሪ ሙስሊም አማፂ ቡድኖችን የሚቀላቀሉት በብዛት ወንድ ወጣቶች ሲሆኑ ፤ ከቅርብ ጊዜ አንስቶ የሴቶቹም ቁጥር እየጨመረ መጥቷል። ወጣቶች ለምን የሳላፊቾች ቡድንን እንደሚቀላቀሉ እና ያላቸውን ሚና በዛሬው የወጣቶች ዓለም እንቃኛለን።ቤተሰቦቼ «እስላማዊ ቅዱስ ጦርነትን»የሚቃወሙ ከሆነ ፤ እነሱንም ለመግደል ዝግጁ ነኝ ሲል ነው ኤርሀን በቅርቡ ለጀርመን «ዙድ ዶይቸ» ጋዜጣ የመለሰው። የ22 ዓመቱ ወጣት ታዋቂ ሳላፊስት እና ራሱን እስላማዊ መንግሥት እያለ የሚጠራው የአይ ኤስ ቡድን አባል ነው። የቱርክ ተወላጁ እና የኮምፒውተር ሳይንስ ተማሪ የነበረው ወጣት ፤ የባየርን ፌደራል ግዛት የሀገር ውስጥ ሚኒስትር «ጀርመንን አደጋ ላይ የሚጥል ሰው ነው » ሲሉ የገለፁት ይህ ወጣት ጀርመንን ለቆ እንዲወጣ ተወስኗል። ከዚህ ወር አንስቶ ወጣቱ የሚኖረው ወላጆቹ ሀገር ቱርክ ነው።

እንደ ኤርሀን ተመሳሳይ ርዕዮተ ዓለም የሚከተሉ ቁጥራቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ ሳላፊስቶች አሁንም ጀርመን ውስጥ ይገኛሉ። በተለይ ወጣቶች በዚህ አክራሪ ቡድን ክፉኛ ይሳባሉ። በጀርመን የአክራሪ እና ወግ አጥባቂ ሙስሊሙ ቁጥር በጥቂት ዓመታት ውስጥ በሶስት እጥፍ ገደማ ከፍ ማለቱን እና በአሁን ሰዓትም 6300 የሚደርሱ ሳላፊስቶች ጀርመን ውስጥ እንደሚገኙ፤ የጀርመን የህገ መንግሥት አስከባሪ መሥሪያ ቤት ኃላፊ ሀንስ ጊዮርግ ማስን በቅርቡ ገልፀዋል። እንደ ማስን 450 የሚሆኑ ወጣቶች እስካሁን ከጀርመን ወደ ሶርያ እና ኢራቅ ለውጊያ ሄደዋል። ቁጥራቸው የማይታወቁት እንዳለ ሆኖ ማለት ነው። ከነዚህም ከ 7-10 የሚሆኑት አጥፍተው ጠፍተዋል። «ፍራንክፈርተር አልገማይነ » ጋዜጣ ዋቢውን ጠቅሶ እንደዘገበው ከሆነ ደግሞ 1800 የሚሆኑ በዚሁ ጦርነት ለመሳተፍ ጀርመንን ለቀው ተጉዘዋል። በለንደን ኪንግስ ኮሌጅ የሽብር ተግባራት ተመራማሪ የሆኑት ካተሪነ ብራውን ወጣቶቹ በዚህ ቡድን የሚሳቡበትን ምክንያት ያስረዳሉ። « የመጀመሪያው ምክንያት ምንም እንኳን የእስላማዊ መንግሥትን ፖለቲካ ባንቀበለውም ለእስልምና መስፋፋት ፖለቲካዊ ተስፋ የጨበጠ ነው። ይህ ማራኪ ያደርገዋል። በአሁኑ ሰዓት አውሮፓ ውስጥ በሚካሄዱት በርካታ ክርክሮች ወጣት ሙስሊሞች ባዕድነት በሚሰማቸው ሰዓት ይህ ሚና ይጫወታል። ሌላው ምክንያት ሁሉም ወጣቶች ጋር ያለ ያላዩትን ነገር ለማየት መጓጓት እና መናፈቅ አለ። ይህንን ከፍራንኮ እና ከስፔን የርስ በርስ ጦርነት ጋር ማመሳሰል ይቻላል። አስገራሚ ነበር። እና በርካታ ወጣቶች የሚሆነውን ሁሉ አድርገዋል። አሁን ያለውም ተመሳሳይ ነገር ነው።»

ከ 75 ዓመታት በፊት ስፓኝ ውስጥ ከተካሄደው የርስ በርስ ጦርነት ጋር የዛሬውን ጃሀዲስቶች አካሄድ ያመሳሰሉት ብራውን በዚህ የእስላማዊ ቅዱስ ጦርነት ወደ ሶርያ እና ኢራቅ የሚዘምቱት ልጃገረጆችም ቁጥር ክፉኛ ከፍ ማለቱን ይናገራሉ። እንደ ብራውን 200 የሚሆኑ ሴቶች እስካሁን ከአውሮፓ ተነስተው ሶርያ ገብተዋል።« ለበርካታ ሴት ወጣቶች አጓጊ የሚያደርግበት ምክንያት የአንድ አዲስ የሚመሰረት ሀገር አካል መሆን ሊሆን ይችላል። ሴቶቹ የአዲስ ነገር አካል እና የሀገሪቷ እናት እንዲሁም የተፋላሚዎች ሚስት መሆን ይፈልጋሉ። ይህ ከፖለቲካዊ አመለካከት እንጂ፤ ገና ለገና ማግባት እፈልጋለው የሚል አስሳሰብን ተመርኩዞ አይደለም።»

ከሶስት ሳምንት በፊት ከዩናይትድ ስቴትስ ተነስተው ይህንኑ ጦርነት ሊቀላቀሉ በጉዞ ላይ የነበሩ ሶስት እድሜያቸው ከ 15-17 የሆኑት ልጃገረዶችን የጀርመን ብሔራዊ የድንበር ፖሊስ ፍራንክፈርት የአይሮፕላን ማረፊያ ላይ በቁጥጥር ስር አውሏቸው ወደ መጡበት ዩናይትድ ስቴትስ መልሷቸዋል። ሌሎች ወጣቶች ግን እንዲሁ ከዩናይትድ እስቴትስ እና ከአውሮፓ ጎዞዋቸው ቀንቷቸው ሶርያ ገብተዋል። ለዚህ ጦርነት ራሳቸውን ከሰው በሺ የሚቆጠሩ በጎ ፍቃደኞች መካከል ምንም እንኳን አብዛኞቹ ወንዶች ቢሆንም፤ የሴቶቹ ቁጥር ቀን ከቀን እየጨመረ ይገኛል። ከጥቂት ወራት በፊት ጀርመንን ያነጋገረው የአንዲት ወጣት ጉዳይ ነበር። የ 16 ዓመቷ ወጣት በቱርክ በኩል አድርጋ የሶርያ የማሰልጠኛ ካምፕ ገብታለች። የጀርመን ኖርድ ራይን ቬስትፋልን ግዛት የህገ መንግሥት አስከባሪ ቢሮ ኃላፊ ቡርክሀርድ ፍራየር ከዚች ግዛት ብቻ 25 የሚሆኑ ልጃገረዶች ለውጊያ ጀርመንን ለቀው መውጣታቸውን ይናገራሉ። ከወንዶቹ ጋር ሲነፃፀር አብዛኞቹ ሴቶች በእድሜያቸውም ይሁን በቁጥር ትንሽ ናቸው።« እድሜያቸው ከ 16-20 ክልል ውስጥ ነው። በዛ ላይ ሁሉም ማለት ይቻላል ጀርመን ከሚኖሩ የውጭ ሀገር ቤተሰቦች ተወላጆች ናቸው። ወደ እስልምና የተቀየሩት ጥቂት ብቻ ናቸው። አመጣጣቸው በሰላማዊ ሁኔታ ከሚኖር ቤተሰብ ነው። ነገር ግን በህይወታቸው የሆነ ነገር የጎደላቸው ይመስላል። ልክ እንደ ወንዶቹ እውቅና ማግኘት እና የህይወት መንገዱ ጠፍቷቸዋል ። ትንሽ ደግሞ የአመጽ አካሄድም አለበት ።ቤተሰቦቻቸው መካከል የማያደርጉት አዲስ ነገርም ነው። ጀብደኝነትም አለ።ከወላጆች ቤት ለቆ መውጣት የመሳሰሉት። አንዳንድ ሶርያ ገብቼ እምነቴን በሚገባ መከታተል እፈልጋለሁ ያሉም አልጠፉም። ቡርካ ለብሼ እንደ ጀርመን ሳንሆን በነፃ መንቀሳቀስ እችላለሁ ያሉም አሉ።»

ከዚህም በተጨማሪ የጀግና ባለቤት መባልን የሚፈልጉ ሴት ሙስሊሞች አሉ። እንደዛም ሆኖ ራሳቸው ተሰልፈው የሚታገሉም አልጠፉም። የሽብር ተግባራት ተመራማሪ ብራውን ስለተወሰኑት ሴቶች ይናገራሉ።« ከጥቂት ወራት በፊት በድረ ገፅ ላይ « የልብ እና የአተነፋፈስ ማዳመጫ እንዲሁም ክላሺንኮቭ አለኝ። ከዚህ ሌላ ሰው ምን ያስፈልገዋል?» ስትል የፃፈች አንድ ማሌዢያዊ ሀኪም አለች ። አንዲት ብሪታንያዊ ደግሞ አመፅ የሚያሳዩ በርካታ ምስሎችን እና ፁሁፎችን አውጥታለች። ባለፈው ሳምንት ደግሞ ለምሳሌ አንዲት ፈረንሳያዊ የአጥፍቶ ጠፊዎችን ቀበቶ አድርጋ ፎቶ ለጥፋ ነበር። ስለዚህ ሴቶችም ጦርነት ውስጥ በቀጥታ እንደተሰለፉ እናያለን ማለት ይቻላል ወይም ቢያንስ ፕሮፖጋንዳው ይካሄዳል። በተመሳሳይ መልኩ ደግሞ ቤት ይዘው ትዳር መስርተው እና ልጆች ወልደው እንደሚሰሩ ያሳያሉ።»

አብዛኞቹ ወጣት የአይ ኤስ ተዋጊዎች ጂሀዲስቶችን የተቀላቀሉት በኢንተርኔት ነው። በኢንተርኔት በተሰራጩ ቪዲዮዎች፣ ብሎጎች እና ፌስ ቡክ ላይ በቦታው የሚገኙ ሌሎች ተፋላሚዎች በሚለጠፉት ይሰበካሉ። ከዚህም ሌላ ተፋላሚውን ቡድን እንዴት በተግባር መቀላቀል እንደሚችሉ ምክር እና የፕሮፖጋንዳ ድጋፍ ያገኛሉ። እንደ ፍላየር በዚህ ጦርነት የሴቶቹ ሚና የተወሰነ ነው። የአንድ ተዋጊ ታማኝ ባለቤት እና እናት መሆን። « ሴቶች ለውጊያ ሳይሆን ወንዶቹን እንዲረዱ እና እንዲንከባከቡ ነው የሚያገለግሉት። ሆኖም እንደሚመስላቸውም ነፃ አይደሉም፤ አብዛኛውን ጊዜም በፈለጉበት ሰዓት ወደ መጡበት መመለስ አይችሉም።»

ይህ ነው ከኦስትሪያ የመጡ ሁለት ልጃገረዶች የገጠማቸው። ኦስትሪያን ከለቀቁ ከ 6 ወራት በኋላ ለጓደኞቻቸው የ ይድረሱልኝ ጥሪ አሰሙ። ከአይ ኤስ ተፋላሚዎች ጋር ትዳር የመሰረቱ ወጣቶች በስፍራው የታዘቡትን ደም መፋሰስ እንደከበዳቸው የገለፁት የ 16 እና የ 17 ዓመት ልጃገረዶች ይህ ከመሆኑ ጥቂት ወራት አስቀድመው ግን ሙሉ በሙሉ ተሸፋፍነው እና ጠመንጃ አንግበው የተነሷቸው ምስሎች በኢንተርኔት ተሰራጭተዋል። በወቅቱ «ለአላህ ስንል እንሞታለን» ይል ነበር መልዕክታቸው።

ብራውንም ይሁኑ ፍራየር የአክራሪ ሙስሊሞቹን ርምጃ ከፖለቲካ እና ከሽብር ጋር እንጂ ከሐይማኖት ጋር አያይዙትም። ምክንያቱም አንዳንዶች ስለ እስልምና በቂ ግንዛቤ እንደሌላቸው ነው የሽብር ተመራማሪዋ ብራውን የታዘቡት።«በጣም የሚያስገርመው፤ ምን ያህል የተወሰነ እውቀት ሴቶቹ እና ወንዶቹ እንዳላቸው ሲታይ ነው ። ያው የተለመደው አባባል እና ጥቁሩ ባንዲራ፣ በቪዲዮ በሚሰራጩት ዜማዎች ብቻ ናቸው ያሉት። ነገር ግን ስለ ሐይማኖታዊ ትምህርቱ ስለ ጂሀድ እና በአኗኗራቸው ላይ ስለሚኖረው ለውጥ ጠልቀው አያጤኑም። »

ጀርመን በሀገሪቷ የሚገኙትን ጀሀዲስቶች ምን ታድርግ በሚል የተነሱት ክርክሮች እንደቀጠሉ ናቸው። ለጦርነት እንዲጓዙ በሩን መክፈት? ፓስፖርታቸውን እየቀሙ መንገዱን መዝጋት? ወይስ የውጭ ሀገር ተወላጆቹን ወደ ትውልድ ሀገራቸው ማባረር? ሁሉም አማራጮች አነጋግረዋል።
የጀርመን ሰላም አስከባሪ መስሪያ ቤቶች በአሁኑ ሰዓት ከ 200 የሚበልጡ እና ከአይ ኤስ ቡድን ጋር ግንኙነት ይኖራቸዋል የሚሏቸውን ተጠርጣሪዎች እየመረመሩ ይገኛሉ።የጀርመን የፍትህ ሚኒስትር ሀይኮ ማስ ፤ እኢአ እስከዚህ ዓመት መጨረሻ የኃይል ርምጃ ለማካሄድ ሀገር ለቀው ለመሄድ ሲሞክሩ ለሚያዙት ስለሚጠብቃቸው ቅጣት ሚኒስቴሩ መፍትሄ ያቀርባል ብለዋል። ባለፈው ዓመት ከፍራንክፈርት በቱርክ በኩል አድርጎ ወደ ሶርያ በመግባት የአማፂውን ቡድን የተቀላቀለው ክሬሽኒክ ያደገው ፍራንክፈርት አቅራቢያ በምትገኘው የባድ ሆምቡርግ ከተማ ነው። የ 20 ዓመቱ ወጣት ስልጠና ከወሰደ እና ለአይ ኤስ ቡድን ከተዋጋ ከተወሰኑ ወራት በኋላ ጦርነቱ ከአቅሙ በላይ ስለሆነበት ተመልሶ ጀርመን ሊገባ ሲል ፍራንክፈርት የአይሮፕላን ማረፊያ በፖሊሶች እጅ ገብቷል። መስከረም ወር አጋማሽ ክስ የተመሰረተበት ወጣት ትውልዱ ከኮሶቮ ነው።በአቃቢ ህግ መሰረት ወጣቱን የ 4 ዓመት እስራት ይጠብቀዋል። ከሶርያ እና ከኢራቅ የተመለሱ የታዋጊው ቡድን አባላት ላይ ክስ ሲመሰረት የክሬሽኒክ የመጀመሪያው ነው። ይሁንና ባለፉት ሳምንታት በርካታ ተመሳሳይ የክስ ሂደቶች ተጀምረዋል።

በጀርመን ህግ መሰረት የሽብርተኛ ቡድንን የሚቀላቅል፣ የሚደግፍም ሆነ የሚያስተዋውቅ በአንቀፅ 129 ንኡስ አንቀፅ ሀ መሰረት ቅጣት ይጠብቀዋል። እንደ እኢአ መስከረም 11, 2001 ዓ ም ዩናይትድ ስቴትስ ላይ አልቃይዳ ጥቃት ከጣለ በኋላ ደግሞ ጀርመን በ 2002 ዓም ለውጭ ሀገር በአንቀፅ 129 ስር ንዑስ አንቀፅ ለ አክላለች። በዚህም መሰረት አሸባሪዎችን እስከ 10 ዓመት እስራት ይጠብቃቸዋል።

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.