ክቡር ሚኒስትር – [የክቡር ሚኒስትሩ ልጅ ፌስቡክ እያየች ታለቅሳለች]

ምን ሆነሽ ነው የምታለቅሽው?
እህ… እህ… እህ…
አንቺ ምን ሆነሻል?
በጣም ነው የከፋኝ?
ማን አባቱ ነው አንቺን ልጄን የሚያስከፋው?
አንተ ራስህ፡፡
ምን?
አንተ ነህ የምታስለቅሰኝ፡፡
እኔ ደግሞ ምን አደረኩሽ?
ምን ያላደረከው ነገር አለ?
አሜሪካ ሄደሽ እንድትዝናኚ አይደል እንዴ ያደረኩት?
እሱማ አድርገሃል፡፡
ከዛም ስትመለሺ አውሮፓ ሾፕ እንድታደርጊ አድርጌያለሁ አይደል እንዴ?
ልክ ነው፡፡
ይኸው ቻይና ራሴ ይዤ ሄጄ አይደል እንዴ ዩኒቨርሲቲ አስገብቼሽ የመጣሁት?
እሱንም አድርገሃል፡፡
ታዲያ እኔ ምን አድርጌ ነው ያስከፋሁሽ?
ሕዝቤን አስከፍተሃል፡፡
ምን?
ሕዝቡ ሲከፋው፣ እኔም ይከፋኛል፡፡
እኔ ጠፋሁ?
ምነው ዳዲ?
የእኔ ኪራይ ሰብሳቢ፡፡
ኤጭ ዳዲ፡፡
ፀረ ልማት ሆነሽልኛላ?
ዳዲ በጣም ነው የሚሰለቸው፡፡
ምኑ?
ሁልጊዜ ፀረ ልማትና ኪራይ ሰብሳቢ እያላችሁ ትዘልቁታላችሁ?
እ…
በጣም ትሰለቻላችሁ፡፡
አንዴ ቆይ ይኼን ወሳኝ ስልክ ላንሳ?
እኔ ስለአገር እያወራውህ ከዚህ በላይ ምን ወሳኝ ነገር አለ?
ይኼም ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ የደወለላቸውን ጉዳይ አስፈጻሚ ማናገር ጀመሩ]

ሄሎ ክቡር ሚኒስትር፡፡
አቤት፡፡
ዕቃዎቹ ጂቡቲ ደርሰዋል፡፡
ሁለቱም ኮንቴይነሮች ጂቡቲ ደረሱ?
አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
ታዲያ ምን ፈልገህ ነው?
አይ ያው ላሳውቅዎት ብዬ ነው፡፡
ስማ እኔ ዲመሬጅ መክፈል ሰልችቶኛል፡፡
በአፋጣኝ እንዲነሱ አደርጋለሁ፡፡
በጣም ደስ የሚል ዜና ነው የነገርከኝ፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ ከልጃቸው ጋር ማውራት ቀጠሉ]

ምንድን ነው ዳዲ?
እ…
ስለምንድን ነው ያወራኸው?
አይ የላክናቸው የልዑካን ቡድን ጂቡቲ ደረሱ እያሉኝ ነው፡፡
አትቀልድ እንጂ?
ምነው?
የልዑካን ቡድኑን በኮንቴይነር ነው እንዴ የላካችኋቸው?
እ…
ለካ ሕዝቡ ወዶ አይደለም፡፡
እንዴት?
በጣም ነው የተማረረው፡፡
በምኑ?
በውሸታችሁ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚስታቸው ጋር እያወሩ ነው]

አንቺ ይቺ ልጅ እንዴት ተበላሽታለች?
ምን አደረገች?
ከመቼ ጀምሮ ነው ለአገር የምትቆረቆረው?
ምን ማለት?
ለሕዝብ ቆሜያለሁ ምናምን ትላለች፡፡
መብቷ እኮ ነው፡፡
ምኑ?
ለሕዝብ መቆምና መቆርቆር ነዋ፡፡
እንዴ እናትና ልጅ ኪራይ ሰብሳቢ ሆናችሁልኛል ለካ?
ምን?
ሁለታችሁም ፀረ ልማት ሆናችኋል፡፡
ኧረ በፈጠረህ፣ ይኼን ቃል የማልሰማበት ቦታ የት ልሂድ?
ፀረ ልማት የሆነ አገር ነዋ፡፡
ስማ ለመሆኑ ሶሻል ሚዲያ ትከታተላለህ?
ምንድን ነው እሱ?
እሱንም አታውቅም?
ምን ኢቢሲ ላይ ያለ ፕሮግራም ነው?
ኧረ እኔ የምልህ ፌስቡክ ምናምን ነው፡፡
ይኼ የኒዮሊብራሎቹ ሚዲያ?
ይኼ እኮ ነው ችግራችሁ?
እሱ አይደል እንዴ አገር እያፈራረሰ ያለው?
አገር የምታፈርሱትማ እናንተ ናችሁ፡፡
ምን?
እናንተ ናችሁ፡፡
[ለክቡር ሚኒስትሩ ሕንፃቸውን የሚሠራላቸው ኮንትራክተር ደወለላቸው]

እሺ ክቡር ሚኒስትር፡፡
አለቀ?
ሁሉም ነገር አልቋል፡፡
መመረቅ ይችላል?
በሚገባ ክቡር ሚኒስትር፡፡
በቃ ዘመድ አዝማድና ወዳጆቻችንን ጠርተን እናስመርቀዋለን፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ ስልኩን ዘግተው ከሚስታቸው ጋር ማውራት ቀጠሉ]

ማን ነው የደወለልህ?
የሥራ ጉዳይ ነው?
እኮ ምንድን ነው የሚመረቀው?
ኮንዶሚኒየም ቤቶች ናቸው፡፡
አጭበርባሪ፡፡
ምን?
ኮንዶሚኒየም ቤት ስታስመርቅ ነው ዘመድ አዝማድና ወዳጆችህን የምትጠራው?
አንቺ ሴትዮ ምነው ጠመድሽኝ?
ለምን አልጠምድህ?
እኔ ከአንድ አይሉ ሁለት ሦስት ቤቶች አልሠራሁልሽም?
እሱማ ሠርተሃል፡፡
እሺ ፎቅስ ቢሆን አልገነባሁልሽም?
አዎ ገንብተህልኛል፡፡
መጋዘንስ ቢሆን አልገነባሁም?
ገንብተሃል፡፡
ታዲያ ምን አደረኩሽ?
ለራስህማ ታውቅበታለህ፡፡
ከራስ በላይ ነፋስ አይደል እንዴ ተረቱ?
እሱ ተረት አሁን ተቀይሯል፡፡
ምን ተብሎ?
ከራስ በላይ ሕዝብ!
[ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸውን ቢሮ አገኙት]

ምን ሆነሃል አንተ?
ምን ሆንኩ?
ከሚስትህ ጋር ተጣላህ እንዴ?
ከእሷ ጋር ተጣልቼ አላውቅም፡፡
ታዲያ ምን ሆነህ ነው የከፋህ ትመስላለህ?
እሱማ በጣም ከፍቶኛል፡፡
ለምን?
አገሪቷ ላይ ምን እየሠራችሁ ነው?
ምን ሠራን?
እኔ ውጭ ተምሬ የያዝኳትን ዶላር ለአገሬ ሳመጣ፣ እርስዎ ከዚህ ወደ ውጭ ገንዘብ ያሸሻሉ፡፡
እ…
እኔ አገር ለማገልገል ደፋ ቀና እላለሁ፣ እርስዎ ራስዎትን ለማበልፀግ ደፋ ቀና ይላሉ፡፡
በጣም ተናንቀናል፡፡
ቆየን ከተናናቅን፡፡
[ለክቡር ሚኒስትሩ የመጋዘናቸው ኃላፊ ደወለላቸው]

አቤት፡፡
ኧረ ጉድ ጉድ ጉድ፡፡
የምን ጉድ ነው?
አቃጠሉት ክቡር ሚኒስትር፡፡
ደመራውን ነው?
ደመራው ከተቃጠለ ቆየ እኮ፡፡
ምንድን ነው የተቃጠለው ታዲያ?
መጋዘኑ፡፡
ምን?
ከነሙሉ ንብረቱ ነው የወደመው፡፡
መጋዘኔን አቃጠሉት?
አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
ለነገሩ ችግር የለውም፡፡
እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
ካሳ እጠይቃለሁ፡፡
ከማን?
ከመንግሥት!
[ስልኩ ሲዘጋ ከአማካሪያቸው ጋር ወሬያቸውን ቀጠሉ]

ክቡር ሚኒስትር ግን ትንሽ አይስማዎትም፡፡
ምኑ ነው የሚሰማኝ?
የሕዝብ ብሶት፡፡
የምን ብሶት?
የሕዝቡን ገንዘብ በካሳ መልክ ጭራሽ ሊወስዱ?
መጋዘኔ እኮ ነው የተቃጠለው፡፡
ክቡር ሚኒስትር የሚሻለው ምን እንደሆነ ያውቃሉ?
ምንድን ነው?
ሕዝቡ እግር ላይ ወድቀው…
ምን?
ይቅርታ መጠየቅ!
[ክቡር ሚኒስትሩ መኪናቸው ጋ ሄደው ሲያንኳኩ ሾፌሩ አልሰማቸውም፡፡ ከዛም ስልኩ ላይ ሲደውሉለት አይቷቸው በሩን ከፈተላቸው]

ምን እያደረግክ ነው አንተ?
አዲስ ስልክ እኮ ገዝቼ ቪዲዮ እያየሁ ተመስጬ ነው፡፡
ስልክ ብርቅ ነው እንዴ?
እኔማ የስድስት ወር እቁብ ገብቼ ነው ይህቺን ቴክኖ ሞባይል የገዛሁት፡፡
ለስልክ ነው የስድስት ወር እቁብ?
እርስዎማ በስድስት ወር መጋዘን ነው የሚገነቡት፡፡
ምን ብንገነባም እያቃጠሉት አስቸገሩን?
በፌስቡክ ሲቃጠል ያየሁት የእርስዎ ነው እንዴ?
አንተ ይኼን ፌስቡክ ተው አላልኩህም?
ሕዝቡ የሚከታተለው ፌስቡክን ነው እኮ፡፡
ኢቢሲን ትቶ?
ታዲያስ ክቡር ሚኒስትር፡፡
ተናንቀናል ማለት ነው፡፡
ሕዝቡ ከናቃችሁ ቆየ እኮ፡፡
ምን?
ሕዝቡ ከነቃ ቆየ፡፡
ለመሆኑ ምንድን ነው የምታየው?
አንዷ ሠርጓ ላይ የይሁኔን ዘፈን አስከፍታ መንግሥትን ተቃወመች፡፡
የትኛው የየሁኔን ዘፈን?
መንግሥትን የመከረበት፡፡
ምን ብሎ?
ሰከን በል!
እውነትም ተናንቀናል፡፡
ቆየን ስልዎት፡፡
ምን ይደረግ ነው የሚሉት?
ክቡር ሚኒስትር ኢሬቻ ላይ የተፈጸመው ምንድን ነው?
ይኸው ለዩኔስኮ ልናቀርበው የነበረውን በዓል አበላሹብን እኮ፡፡
ለነገሩ በዓሉማ መቅረቡ አይቀርም፡፡
ለማን ነው የሚቀርበው?
ለዩኤን ሴኩዩሪቲ ካውንስል!

ምንጭ – ሪፖርተር

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.