አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ:- የወያኔ ሰራዊት ቀኝ ሁዋላ ወደ ደደቢት [ታሪኩ አባዳማ]

መስከረም 2009

woyane-satenaw-news-5
ህወሀት ተልዕኮው በከፊል ሰምሯል ፤ ለብሔር ብሔረሰቦች መብት እስከ መገንጠል ቆሜያለሁ ብሎ ነበር ፣ ዲሞክረሲ ሳይሽራረፍ አረጋግጣለሁ ፣ ሰብአዊ መብት አሰፍናለሁ ብሎ ነበር ፣ ያለፍርድ አንድም ዜጋ ህይወቱን ቀርቶ መታሰር አይደርስበትም ብሎ ነበር ፣ ከጎረቤት አገሮች ጋር በማይናወጥ ሰላም እንኖራለን ብሎም ነበር… ከፖለቲካ ስርአት ምህዳር እና ሰማይ በታች ሁሉንም በጎ ነገሮች በኔ አገዛዝ ስር ትጎናፀፋላችሁ ሲል ቃል ገብቶ ነበር። ቃሉን በሰነድ ላይ አስፍሮ ህገ መንግስት አድርጎ – እሰከዚህ ድረስ ተጉዞ ነበር።

ራዕዩ ቃል ፣ ቃሉም ሰነድ ሆኖ ነበር… በቃ ፣ ከዚያ ማለፍ አልቻለም። ሰነዱ ሳይነበብ ብል በላው ፣ ምስጥ መዘመዘው ፣ አረም ዋጠው። ቃሉ ስጋ ወ ደም ሳይዋሀድ ጨነገፈ… በመጨረሻም እነሆ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አወጀ። የተባባሰ ግድያ አዋጅ ፣ የላቀ ጅምላ መብት ጥሰት አዋጅ ፣ የጫካ አዋጅ ፣ የአራዊት አዋጅ ፣ የደደቢት አዋጅ አወጀ። ህወሀት ከሀያ አምስት አመታት የግፍ አገዛዝ በሁዋላ ቀኝ ሁዋላ ወደ ደደቢት አለ ፤ ጫካውን ናፈቀ። ተጠያቂነት እና ግልፅነት የማያውቀው የደደቢት ፖለቲካ ህይወት እጅጉን ናፈቀው።

መጀመሪያ ያኔ ወደ ደደቢት ሲጓዝ የህዝብ ብሶት ሰንቆ ለጋ ወጣት ሳለ የተመኘውን ሊከውን ነበር – ይብዛም ይነስ ብሩህ አይምሮ ፣ ያልተልከሰከሰ መንፈስ እና ምኞት ነበረው። አሁን ወደ ደደቢት ለመጓዝ የተነሳው ደግሞ በህዝብ ልጆች ደም የጨቀየ እጆቹን ፣ በሙስና የበከተ ህሊናውን ፣ በውሸት እና ቅጥፈት የተባ ምላሱን አንዘላዝሎ ፣ ታሪክ ይቅር የማይለው ፣ ትውልድ አሳፋሪ ታሪኩን አንግቦ ነው። ህወሀት ቀኝ ሁዋላ ወደ ደደቢት አለ – አስቸኳይ ጊዜ አወጀ። ገድለው በህግ የማይጠየቁበት ፣ ዘርፈው የማይጠግቡበት ፣ ባሻቸው ውለው የሚያድሩበት ደደቢት ናፈቀው። ወንድም ወንድሙን ገድሎ የሚፎክርበት ፣ ሀውልት የሚገትርበት ፤ ድልድይ አፍርሶ ፣ ባንክ ዘርፎ ፣ ድሀ አስለቅሶ እለት ጉርሱን ሳይቀር ቀምቶ ወደሚያድርበት ደደቢት ቀኝ ሁዋላ ዙር አለ – አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አወጀ። ህወሀት እንደገና ኢትዮጵያ ለምኔ አለ ፣ ኢትዮጵያዊ ገድሎ ፣ ክብሯን አዋርዶ ፣ ባንዲራዋን እንደ ጨርቅ በሶ እየቋጠረ ወደማይጠየቅበት ደደቢት ፊቱን አዞረ።

ትናንት በቃሉ መሰረት የሰጣቸውን ሰነድ የተማመኑ ፣ ተማምነውም መብታቸውን የጠየቁ አሸባሪ ተብለው አደባባይ በጥይት እሩምታ ታጨዱ ፣ በየወህኒው ታጎሩ ፣ ተሰደዱ። ያልተሸራረፈው ዲሞክረሲ ቀርቶ መሰረታዊ እና ተፈጥሯዊ መብታችን ይከበር ያሉ በወንጀል ተከሰው ወህኒ ተወረወሩ። በታጎሩበት ወህኒ እሳት ነደደባቸው። እሱም አልበቃ ብሎ ዛሬ ለሌላ ጅምላ ፍጅት አዋጅ ታወጀባቸው – አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ።

ህወሀት ትግራይን ነፃ ለማውጣት ተልሞ ድፍን ኢትዮጵያን ተቆጣጥሯል – ህዝቧን በከፋፍለህ ግዛ መርህ በጎጥ ሸንሽኖ አንድነቷን አናግቷል። አንድነቱ በተናጋ እና በተከፋፈለ ህዝብ ትከሻ ላይ ተደላድሎ እጅግ መጠነ ሰፊ የሆነ ሀብት መዝብሮ ቢጠሩት የማይሰማ ቱጃር ሆኗል። በጎጥ የከፋፈለውን ህዝብ በወረፋ አንዱን ዛሬ ሌላውን ነገ እየነጠለ ሲገድል ፣ ወህኒ ሲያግዝ ፣ ለስደት ሲዳርግ ፣ ንብረት ሲቀማ ሀያ አምስት አመታት አስቆጥሯል።

ግን ዛሬ ህዝብ በቃ አለ – አለም ይህን ጅምላ ፍጅት መርምሮ ተጠያቂውን ለፍርድ ማቅረብ ግድ ይላል ሲል ሰምቶ ህወሀት ደነበረ ፣ ፊቱን ወደ ደደቢት አዞረ። አንዳችም ተጠያቂነት ወይንም ግልፅነት ወደሌለበት ወደ ደደቢት አለም ለመጓዝ ተጣደፈ። ኢትዮጵያን በታትኜ ፣ እንደ ሩዋንዳ የዘር ፍጅት አቀጣጥዬ ደደቢት ገባለሁ አለ። ይህም አይሆንም ሲል ህዝብ አንድነቱን አጥብቆ ከዳር እስከ ዳር ተሰለፈ – ህወሀት ግን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አወጀ – ደደቢትን ከነ አተላው እግታችሁዋለሁ አለ፤ ህዝብን ምን ያህል እንደ ናቀ ለማሳየት አዋጅ አወጀ። የአንዲት አገር ልጆችን በጎጥ ሸንሽኖ ፣ በክልል በረት አጉሮ እንኳ መግዛት ተሳነው።

የትግራይን ሪፐብሊክ ለማወጅ የረቀቀው ሰነድ ከተቀበረት ዋሻ አቧራው ተራግፎ ወደ አደባባይ ብቅ እያለ ነው። ወያኔ/ህወሀት ‘በብረት አስገብረን ፣ ደም አፍሰን ፣ እንደ ገል ቀጥቅጠን እንደ ብረት አቅልጠን መግዛት ካልቻልን እናንተን በታትነን እኛ ሪፐብሊካችንን እናውጃለን’ በሚል እየተጋበዘ ቆይቷል። ህዝቡ አንተ እንደፍጥርጥርህ ለእኛ ግን አንድነታችን ፣ ሰብአዊ መብታችን ዋስትናችን ነው በሚል ፅኑ ተቃውሞ ማድረጉን ቀጠለ። ህወሀት ደደቢት ላይ ሲያደርግ እንደ ነበረው ጭፍን ጥላቻን በህዝብ ለመርጨት ሲል ሀውልት እስከ ማቆም ደረሰ። ህዝብ ግን ህወሀት ሰራሽ የሆነ አንዳችም ነገር እንደማይበጀው ይፋ አደረገ። Down down woyane እያለ መልካው እስኪናጋ ድረስ አስተጋባ። ህወሀት ግን ፊቱን ወደ ደደቢት አዞረ ፣ ተጠያቂነት ፣ ግልፅነት የሌለበትን ስርአት ናፈቀ – አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አወጀ።

አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ይፋ ሆኗል – የደደቢት ስርዓት በመላው አገር በይፋ ይረጋገጣል ብለዋል። ከቶውንም ህግ ባልነበረበት አገር ፣ ስርአት ባልተጠበቀበት ምድር አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚያመጣው ምን አዲስ ነገር አለ? እስከ ዛሬ እንደ ጅረት ስላፈሰሱት ደም ፤ እስከ ዛሬ ከአፅመ ርስቱ ስላፈናቀሉት ዜጋ ፤ እስከ ዛሬ ህልውናውን ፣ ስብእናውን ክደው ስላዋረዱት ህዝብ ጉዳይ መልስ እየጠየቅን እንጂ መቸ ሌላ ዙር ፍጅት ጠየቅን።

ሳይውል ሳያድር ለጥያቄአችን መልስ እንፈልጋለን። እስከ ደደቢት ድረስ እናንተን የምንሸኝበት አቅም ፣ ዝግጅትም ሆነ ፍላጎት የለንም ፤ አስቸኳይ ጊዜ አዋጃችሁን የምንሸከምበት ዕዳ ፣ በዚያም የምንገዛበት ትከሻ የለንም። ደደቢትን ወደ እኛ እንዳመጣችሁ ሁሉ መልሳችሁ እንድትረከቡ ህዝብ ድምፁን ከፍ አድርጎ ይጮሀል። Down down woyane ይላል።

 

Comments are closed.