ማኅበራዊ የብዙኃን መገናኛ እና ወያኔ! [ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው]

ወያኔ ሕዝብ በነጻነት ሐሳቡን የሚገልጽበት የማኅበራዊ የብዙኃን መገናኛው መድረክ (Social media platform) መቅሰፍት እንደሆነበትና ሊያግደው ሊገታው እንደሚፈልግም በተለያየ መንገድ ሲገልጽ ቆይቶ አሁን በመጨረሻ ደግሞ ያለ አንዳች ሐፍረትና መሸማቀቅ በአሻንጉሊት ሹሙ በአቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በኩል በተባበሩት መንግሥታት የመሪዎች ስብሰባ ላይ ግልጽ አድርጓል፡፡

social-media-tplf-satenaw-news

ወደዚህ ዝርዝር ከመግባቴ በፊት ግን ትንሽ እስኪ ስለ ማኅበራዊ የብዙኃን መገናኛ ምንነትና ጠባይ ልግለጽ፦

ማኅበራዊ የብዙኃን መገናኛ (Social media) ማለት ምን ማለት ነው? ማኅበራዊ የብዙኃን መገናኛ ማለት፦ ዐውደ መረብን (Internet) በመጠቀም የሚከወን ያለ አንዳች ቅድመ ምርመራና ገደብ በሙሉ ነጻነት እንደ ድረ ገጾች (Websites, Webpages) እና ሌሎች ተመሳሳይ ሐሳብና መረጃ የመለዋወጫ መድረኮች ማለት ነው፡፡ በማኅበራዊ የብዙኃን መገናኛ አጠቃቀም ዙሪያ ገዳቢ ሕግ አለ ከተባለ እሱ የሞራል (የቅስም) ሕግ ብቻና ብቻ ነው፡፡

ማኅበራዊ የብዙኃን መገናኛ ከስሙ መረዳት እንደሚቻለው የማኅበረሰቡ ማኅበራዊ ሕይዎት እንዳለ እንደወረደ የሚስተጋባበት የሚገለጽበት የሚስተናገድበት ወይም የገሐዱ ዓለም ነጸብራቅ ማለት ነው፡፡ ይህም ማለት በገሐዱ ዓለም ያለ ውሸት ሌላ የማያውቅ ወስላታና በሌላ በኩል ደግሞ ሐቀኛ እውነተኛ እንዳለ ሁሉ፣ በገሐዱ ዓለም ባለጌ ስድ ዋልጌና ነውረኛ ተግባሩ እንዲሁም ጨዋ የተባረከና የሚያንጽ ተግባሩ እንዳለ ሁሉ፣ በገሐዱ ዓለም ተሳዳቢ ተራጋሚ ደካማ ጎን ብቻ እንጅ ጠንካራ ጎን ጨርሶ የማይታየው ጨለምተኛ እንዲሁም ደግሞ መራቂ አመስጋኝ ነገሮችን በትክክል በሚዛናዊነት ተመልካች እንዳለ ሁሉ፣ በገሐዱ ዓለም ያለራሱ ጥቅም ሌላ የማያውቅና የማይታየው አስመሳይ አድር ባይ ኅሊና ቢስ ሆዳም እንዲሁም ማንንም ሳይፈራና ሳያፍር ሊከፍለው የሚችለው ዋጋ ሳያሳስበው ስለ እውነት ስለ ሀገር ስለ ሕዝብ ጥቅም ህልውናና ደኅንነት ፊት ለፊት የሚጋፈጥ ሐቀኛ እንዳለ ሁሉ፣ በገሐዱ ዓለም የሰው ልጅ ስቃይና ችግር የሚያስደስተው ዘወትር ይሄንን በማድረግ የሚተጋ እንዲሁም የሰው ልጆች በዚህች የመከራ ምድር ሲኖሩ የሚገጥማቸውን ችግርና መከራ ለማቅለል ሰው በመሆኑ ብቻ ኃላፊነት ተሰምቶት በተቻለው አቅም ሁሉ የሚኳትን የሚታትር እንዳለ ሁሉ ሌላም የተቀረው በማኅበረሰቡ ያለው መጥፎና መልካም ነገር ሁሉ የሚንጸባረቅበት የሚስተናገድበት የሚውካካበት የብዙኃን መገናኛ ዓይነት ማለት ነው ማኅበራዊ የብዙኃን መገናኛ ማለት፡፡

ከላይ ከጠቀስናቸው ውስጥ የማይፈለጉ ምግባሮች ቢኖሩም የሰው ልጆች ሰው ከመሆናቸው ጋር በተያያዘ ካለባቸው ደካማ ጎን የተነሣ ሊፈጽሟቸው የሚገደዷቸው ተጨባጭ ነባራዊ ሐቆች እንደመሆናቸው እነኝህን ድርጊቶች ሕግ በመቅረጽ ለመቆጣጠርና አደባባይ እንዳይወጡ ለማድረግ  ይሞከራል እንጅ በየትም ቦታ ቢሆን ከቶውንም ለማጥፋት አይሞከርም አይቻልምም፡፡

ውሸታም አለብህና ተብሎ አንድን ማኅበረሰብ ማጥፋት እንደማይቻለውና ፈጽሞ እንደማይገባም ሁሉ በፌስ ቡክ (በመጽሐፈ ገጽ) የሚዋሽ ሰው አለና ተብሎም መጽሐፈ ገጽ (ፌስ ቡክ) ይጥፋ ማለት ፈጽሞ አይቻልም፡፡ ከተባለም ፍጹም ፍጹም አግባብነት የጎደለው ተግባር ነው፡፡ አይደለምና ከአንድ ማኅበረሰብ ከአንድ ግለሰብ እንኳ ፍጹምነት ፈጽሞ እንደማይጠበቀው ሁሉ የዚሁ ማኅበረሰብና ግለሰብ ሕይዎት ማንነትና መስተጋብር መንጸባረቂያ መድረክ ከሆነው መጽሐፈ ማኅበራዊ የብዙኃን መገናኛም ፍጹምነትን መጠበቅ በፍጹም አይቻልም ሲበዛም ቂልነት ነው፡፡

ውሸትን አሉባልታን መከላከል የሚቻለው የብዙኃን መገናኛውን በማገድ ወይም በማጥፋት ሳይሆን የመረጃ ፍሰትንና የመወያያ መድረኮችን ይበልጥ ነጻና ተደራሽ በማድረግ ብቻና ብቻ ነው፡፡ ይሄ ነው የዲሞክራሲያዊና (መስፍነ ሕዝባዊና) ኃላፊነት ተጠያቂነት የሚሰማው መንግሥት አሠራር፡፡ ይሄም በመሆኑ ነው የምዕራቡ ዓለም በዚህ መርሕ መሠረት እየተመራና ሀገርና ሕዝብም በእጅጉ ተጠቃሚ ሆኖ ሊገኝ የቻለው፡፡ ዕውነት የሌለውና ወንጀለኛ አካል ብቻ ነው ግልጽነትንና ተጠያቂነትን የሚጠላው፡፡ ምክንያቱም ነጻ የመረጃ ፍሰት ቢኖር የበለጠ ጉዱ ወንጀሉ ይገለጥበታል ተጠያቂም ይሆናል እንጅ እውነት ኖሮት ይሄንን እውነት አቅርቦ ሊያስተባብልና ከተጠያቂነትም ነጻ ሊወጣ አይችልምና ነው፡፡

ለነገሩ እንዲያው ነገሩን አልኩ እንጅ የወያኔ ችግር በማኅበራዊ የብዙኃን መገናኛ ሐሰት መነገሩ አይደለም፡፡ ወያኔ ላይ በማንኛውም ሰው የፈለገውን ያክል ሐሰት ወይም ውሸት ቢወራ ከሁኔታዎች አስቸጋሪነት የተነሣ መረጃ ካለመያዙ አንጻር ያ ወሬ ውሸት ሊመስል ይችል ይሆናል እንጅ ከወያኔ ማንነት አንጻር ወያኔ አያደርገውም! ወይም ሊያደርገው አይችልም! የሚባልና ያላደረገው የነውር፣ የክህደት፣ የጥፋት፣ የወንጀል ዓይነት ፈጽሞ ካለመኖሩ አንጻር የተወራ ቢወራ ሐሰት ወይም ውሸት አይደለም፡፡  በዚህም ምክንያት ነው አቶ ኃይለ ማርያም በተባበሩት መንግሥታት የመሪዎች ስብሰባ ላይ “በማኅበራዊ የብዙኃን መገናኛ ውሸት ተወራብን፣ ስም ማጥፋት ተኪያሔደብን!” ሳይሆን “ማኅበራዊ የብዙኃን መገናኛው ቡድኖችና ግለሰቦች የተፈጸሙ እውነተኛ ድርጊቶችን እያነሡ በማራገብ ለራሳቸው ዓላማ መጠቀሚያ መድረክ ሆኖብን ተቸግረናል!” በማለት የተወራውና እየተወራ ያለው እውነት እንጅ ሐሰት ወይም ስምማጥፋት እንዳልሆነ በማረጋገጥ ትንሽም እንኳ ብትሆን ሐፍረት ሳይሰማቸው በ “የሌባ ዓይነደረቅ መልሶ ልብ ያወልቅ” አቀራረብ የወለፊንድ ክሳቸውን ያቀረቡት፡፡

ቆይ! ቆይ! አቶ ኃይለ ማርያም የተራገበው ነገር በትክክል የተፈጸመ ወይም ያለ ችግር ከሆነ መፍትሔ የሚሆነው የተራገበው እውነተኛ የተፈጸመ ችግር እንዳይፈጠር እንዳይፈጸም ማድረግና ተጠያቂነት እንዲሰፍን ማድረግ ነው እንጅ እንዴት ሆኖ ነው “ይህ ችግር ለምን ይፈጸማል? ፈጻሚዎቹ በሕግ ይጠየቁ!” በማለት የሚጮሁትን እርስዎ “የተፈጸሙ እውነተኛ ችግሮቹን ለራሳቸው ዓላማ የሚያራግቡ!” ሲሉ የጠሯቸውን የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችንና ለሕዝብ ለሀገር መብት ህልውና ደኅንነት የሚታገሉትንና የመታገያ መድረኩን ማለትም ማኅበራዊ የብዙኃን መገናኛውን ማጥፋት ማገድ ወይም መከልከል የሚሆነው???

ይሄ እኮ ዓይን ያወጣ አፋኝነት ነው፡፡ ይሄ እኮ ተጠያቂ ለመሆን ፍጹም አለመፈለግና አለመፍቀድ ነው፡፡ ይሄ እኮ ሌላ ብዙ ጉድ አለብኝ ይሄ ጉዴ እንዲወጣና ተጠያቂ እንድሆንም አልፈልግም! ጉዴን የሚያወጣና ተጠያቂ ሊያደርገኝ የሚሞክርን ጋዜጠኛን፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋችንም ሆነ ፖለቲከኛን (እምነተ አስተዳደራዊን) አልምርም! አጠፋሁ! ማለት እኮነው፡፡

አቶ ኃይለማርያም ይሄንን የተናገሩትን ነገር በዓለም መሪዎች ፊት እንደተናገሩ ስሰማ “ኧረ እነዚህ ሰዎች ዛሬስ ጭራሽ የት ቦታ ለማን ምን እንደሚባልም ጠፋባቸው እንዴ!” ነበር ያልኩት፡፡ ዓይነ አውጣነታቸው፣ ዓይነ ደረቅነታቸው ልክና ገደብ የለሽ መሆኑ ነው እንግዲህ እዚህ ድረስ ሊያዋርዳቸው የቻለው፡፡ ለእኛማ እንዴት ጥሩ መሰላቹህ! ዓለም አወቀልና፡፡ በእንዲህ ዓይነት ፀረ ሰብአዊ መብት፣ ፀረ ተፈጥሯዊ መብት፣ ፀረ ሐቅ፣ ፀረ ሐሳብን የመግለጥ ነጻነት፣ ዓይን ያወጣ አፋኝ አንባገነን አገዛዝ ታፍነን ተረግጠን ተጨቁነን እየተገዛን እንዳለን በገዛ አንደበታቸው ለዓለም ተነገረልን፡፡ ያውም እኮ በጣም የሚገርማቹህ 4% በማይሞላ የዐውደ መረብ (የኢንተርኔት) ሽፋን ወይም ተደራሽነት እኮነው ይሄንን ያህል ጭንቀትና ሁከት ውስጥ የወደቁት፡፡ በ50% እና 60% ሽፋን ሕዝባቸውን ዘመኑ ከሚጠይቀው ዘመናዊ አገልግሎት ጋር አገናኝተው ተጠቃሚ ያደረጉት ጎረቤት ሀገራት እነ ኬንያ ምን ይበሉ?

አየ ወያኔ! በሆነ ተአምር ዓለም ባልሠለጠነበት ዘመን የነበረን አረመኔያዊ የደነቆረ አስታሳሰብ ይዘህ በ21ኛው መቶ ክ/ዘ ላይ ተገኘህና ከ21ኛው መቶ ክ/ዘ አስተሳሰብ ጋር ፍጹም አልጣጣም ብለህ እጅግ ተቸገርክብን እኮ! አንተ ተቸግረህ እኛንም አሳራችንን አበላኸን እኮ! እባክህን? እባክህን? ነጻነት መሠረታዊ ፍላጎት የሆነበትን፣ ነጻ የዐውደ መረብ (የኢንተርኔት) ግንኙነትና የመረጃ ፍሰት የሁለንተናው መሠረት የሆነበትንና የግድ አስፈላጊ የሆነበትን የሠለጠነውን 21ኛውን መቶ ክ/ዘ በፍጹም በፍጹም አትመጥንምና እባክህ? እባክህ? እባክህ? ልቀቀንና ወደምትሔድበት ሒድልን???

በሉ እንግዲህ ወገኖቸ ፈላጭ ቆራጩ አንባገነኑ አፋኙ ወያኔ ዐውደ መረቡን (ኢንተርኔትን) በመዝጋት ከማኅበራዊ የብዙኃን መገናኛ እድምተኝነት ሊለያየን እንደሆነ አስታውቋልና ፕሲፎንም ሊሠራልን አልቻለምና ሳልሰናበታቹህ ከመለያየታችን በፊት ከወዲሁ ልሰናበታቹህ፡፡ ነገር ግን በእርግጠኝነት  ወያኔን ደምስሰን በቅርቡ መልሰን እንደምንገናኝ ባለሙሉ ተስፋ ነኝ፡፡ እርግጥ ነው በመሀሉ የምናልፍ እንኖር ይሆናል፡፡ ይሁን እንጅ ከዚያ ቀን የምንደርስ መኖራችን ግን የማያጠራጥር ጉዳይ ነው፡፡ ከዚያም ከዚያማ አፋኙን አገዛዝ ቀብረነዋልና ያለምንም አፈናና ያለ አንዳች የዐውደ መረብ አገልግሎት መስተጓጎልና መቆራረጥ በፍጹም ነጻነት እንደፈለግን የፈለግነውን ጉዳይ ያለ ፍርሐት የምንወያይበት የምንመክርበት ሐሳቦቻችንን በነጻነት የምንገልጽበት የምንለዋወጥበት ጊዜ ይሆናል ማለት ነዋ! ይህ ቀን እውን እንዲሆን በሁሉም ረገድ እንድንተጋ አደራ እያልኩ እስከዚያው ደኅና ሁኑ!!!

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

amsalugkidan@gmail.com

 

 

 

 

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.