ሰማያዊና መኢአድ የኢትዮጵያዉያን ሁሉ ቤት ናቸው [ግርማ ካሳ]

 

13259998_1026870737397860_7809576735746440482_nየሰማያዊ ፓርቲ ካለፈው ምርጫ ጀመሮ ለአንድ አመት ከአራት ወራት ይሄ ነው የሚባል እንቅስቃሴ አለማድረጉ ይታወቃል። ይሄም የሆነበት ዋና ምክንያት በሊቀመንበሩ ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት እና በሌሎች አመራሮች መካከል አለመስማማቶች በመፈጠራቸው ነበር።

በፓርቲው ድርጅታዊ ደንብ መሰረት የድርጅቱ የበላይ አካል ጠቅላላ ጉብዬው ነው። የድርጅቱን ሊቀመንበር ፣ የድርጅቱን ብሄራዊ ምክር ቤት አባላት እና የደርጅቱን ኦዲት ኮሚሽን አባላት የሚመርጠው ይሄው ጉብዬ ነው። ሊቀመንበሩ አብረዉት የሚሰሩ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት መርጦ በብሄራዊ ምክር ቤቱ ያጸድቃል። እንግዲህ እነዚህ ሶስቱ አካላት አንዱ ሌላውን እንዳያዝ ተደርገው ነው የተዋቀሩት። ይሄ ተጠያቂነት እንዲኖር ሆን ተብሎ የተደረገ ነው። ፈረንጆች check and balance የሚሉት አይነት ነው።

በፓርቲው ዉስጥ አለመስማማቱ ነገሮችን ሁሉ አስሮ ባለበት ወቅት፣ ለሁለት አመት በወህኒ ሽብርተኛ ተብሎ ከነሃብታሙ አያሌው ጋር ሲሰቃይ የነበረውና የድርጅቱ ምክር ቤት ም/ሰብሳቢው የሺዋስ አሰፋ ከወህኒ ይወጣል። ሁሉም አመራሮች በማሰባሰብ የፓርቲው ችግር በዉይይት እንዲፈታ ለማድረግ ይጥራል። በዚህ ወቅት ነው ከአምስት ወራት በፊት፣ ከዚህ በታች የምታይዋት ፎቶ ለሕዝብ የተለቀቀችው። የብሄራዊ ምክር ቤት ሰብሳቢውና የሕግ ባለሞያው አቶ ይድነቃቸው ከበደ፣ የምክር ቤት ም/ሰብሳቢ አቶ የሺዋስ አሰፋ፣ የድርጅቱ ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት፣ ም/ሊቀመነበሩ አቶ ነገሰ ተፈረደኝ፣ የኦዲት ኮሚሽን መሪ አቶ አበራ ገብሩ እና የህግ ባለሞያ የሆኑት አቶ ሳምሶን ገረመውን ነው በፎቶ የምናያቸው።እነዚህ ስድስት ወገኖች በሰማያዊ ፓርቲ ዉስጥ ያሉ ሶስት ተቋማት መሪዎች ነበሩ። ከኢንጂነር ይልቃ በስተቀር ሁሉም አሁንም መሪዎች ናቸው።

የሰማያዊ ፓርቲ መስከረም 28 ቀን ጠቅላላ ጉብዬ አድርጓል። በዚህ ፎቶ ላይ ካሉት ዉስጥ አምስቱ በጠቅላላ ጉብዬው ተሳታፊ የነበሩ ሲሆን፣ ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት በአባላት ፊት ቀርበው በድጋሚ ለመመረጥም ሆነ ሌሎች ጉዳዮች ላይ ያላቸዉን አቋም ለመግለጽ ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል። ጠቃላላ ጉባዬው የተጠራው ሕግ ወጥ በሆነ መንገድ ነው ይላሉ። ሆኖም ግን የድርጅቱ ኦዲት ኮሚሽን ጉባዬ መጠራት እንደሚችል በደንቡ ላይ በማያሻማ መልኩ በገልጽ ተቀምቷል። እርግጥ ነው እርሳቸውም ባሉበት ጉብዬው ተደርጎ ቢጠናቀቅ ኖሮ በጣም ጥሩ ይሆን ነበር። ግን በተለያዩ ምክንያቶች ለመገኘት ፍቃደኛ ካልሆኑ ፣ መቼም የሰማያዊ ፓርቲ የአንድ ሰው ፓርቲ ስላልሆነ፣ “እርሳቸው በተመቻቸው ጊዜ ሲመጡ ይመጡ” ብሎ ትግሉን ከመቀጠል ዉጭ ሌላ አማራጭ አይኖርም። (በዚህ አጋጣሚ ለወንድም ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት በትግል ዉስጥ አለመስማማትና ግጭት እንዳለ ተረድተው፣ ከአዲሱ የሰማያዊ አመራር ጋር አብሮ በመስራት የድርሻቸዉን እንዲወጡ በአክብሮት እጠይቃለሁ። ብዙ ሊሰሩና ሊያገለግሉ እንደሚችሉ አወቃለሁ። የሚያስፈልገው ፍቅርና ቅንነት ነው። ለመታግል፤ የግድ ሊቀመንበር መሆን የለብንም)

በመጨረሻ አንድ በጣም ትንሽ የሚመስል ግን በጣም ጠቃሚ የሆነ ነጥብ ማስቀመጥ እፈልጋለሁ። የሰማያዊ ፓርቲ ጠቅላላ ጉብዬዉን ያደረገው በመኢአድ ጽ/ቤት ነው። ባለኝ መረጃ በዶር በዛብህ ደምሴ የሚመራው የመኢአድ አመራር “እኛና እናንተ እኮ አንድ ነን። ጽ/ቤታችን የናንተም ጽ/ቤት ነው። በፈለጋችሁበት ጊዜ ጽ/ቤቱን መጠቀም ትችላላችሁ። እኛ በፊትም መለያየት አልነበረብንም፤ አንድ ነን” በሚል ሰማያዊዎች ምን ነገር ሳይከፍሉ ጉባዬያቸውን በመኢአድ ጽ/ቤት እንዲያደረጉ በመፍቀዳቸው ነው ጉብዬው ሊደረግ የቻለው። ይህ የአንድነትና የሶሊዳሪቲ መንፈስ በአንድነት የለዉጥ ሃይሉ መካከል ፣ ያልነበረ በጣም መበረታታት ያለበት መንፈስ ነው። በዚህ አጋጣሚ ለመኢአድ አመራር አድናቆቴን እና ምስጋናዬን እንዳቀርብ ይፈቀድልኝ።

አሁን በአገራችን ባለው ሁኔታ የአገዛዙ የግፍ ቀንበር ከመብዛቱ የተነሳ ዜጎች ወደ አመጽ እየሄዱ ነው። ፖለቲካው እጅግ በጣም ሲበዛ ከሯል። ሆኖም ግን መቼም ቢሆን ሰላማዊ እንቅስቃሴ በተባበረ መንገድ፣ በእውቀት ከተመራ የተሻለ አማራጭ ሊሆን እንደሚችል ጥርጥሬ የለኝም።
ሌላው ደግሞ አሁን እያየን ያለነው እንቅስቃሴ ዘር ተኮር የሆነ ብዙ ወገኖች ያላቀፈ እንቅስቃሴ ነው። ኢትዮጵያዊያንን ሁሉ ያቀፈ፣ ለዘርና ለጎሳ ቦታ የማይሰጥ ድርጅት ያስፈልጋል። እንግዲህ እንደ መኢአድ ሰማያዊ ያሉ ደርጅቶች አሉ። መኢአድም ሰማያዊ አዲስ አመራር ነው ያላቸው። አብሮ የመስራት ፍላጎታቸው በጣም ጠንካራ ነው። እነዚህን ድርጅቶች በማጠናከርና በማገዝ በኢትዮጵያ ብሄረተኝነት ሥር እንታገል። ብሶት የምናሰማ ሳይሆን የምንታገል እንሁን። ትግል ደግሞ ከአልጋ ወደ አላጋ መዝለል አይደለም። የተሰበረዉን ጠግኖ፣ የደከመዉን አጠናክሮ መዉጣት ነው።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.