የህወሀትን መሰሪ አላማዎች ለማክሸፍ ባንድነታችን እንጽና!!!

G7 hይህወሀት ኢሕአዴግ መንግስት ባለፈው እሁድ ባሻንጉሊቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አማካይነት የተገለጸውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መላ ሀገሪቱ ላይ አውጇል። ያስቸኩዋይ ጊዜ አዋጅ የሚያውጁ መንግስታት በመሰረቱ ህገመንግስትን እንደመንግስት ልጓም የሚያዩና የሚያከብሩ መንግስታት ሲሆኑ አዋጁ ልዩነትም ትርጉምም ይኖረዋል። እንደወያኔ አይነት ለህግና ሕገ መንግስት ግድ የሌለው ሕገወጥና ለሕግ ክብር የሌለው መንግስት ፣ ራሱ ያወጣውን ህግ አልመች ባለው ቁጥር ሁሉ እንደልቡ የሚሽር መንግስት የሚያውጀው አዋጅ የህዝብ መብት ገፈፋውን ለማፋፋም ቅልጥፍና ይጨምርለት እንደሆን እንጂ በመሰረቱ አዋጁ የሚፈጥረው እንዳች ለውጥ የለም። ወያኔ አትዮጵያን በሀይል እንጂ በህግ አስተዳድሮ አያውቅም። የወያኔ አላማ ግልጽ ከሆነ ሰንብቷል። በግፍና በግፍ መንገድ ብቻ የህዝቡን ጥያቄ ለማስቆም ቆርጦ መነሳቱን አረጋግጦልናል። ሕዝባችን የጀመረው የነጻነት ትግልም በዚህ ምክንያት ወደኋላ ይሄድልኛል ብሎ ገምቷል። ለወያኔ ጨካኝ ገዥዎች ያልተገለጸላቸው ነገር የግፍ ብዛት ትግል የሚያስቆም ቢሆን ኖሮ ትግሉ አሁን በደረሰበት ደረጃ ፈጽሞ የሚደርስ እንዳልነበር ነው። እሁን የግፉ የበደሉና የዝርፊያው ጽዋ ሞልቶ ከፈሰሰ በሁዋላ የኢትዮጵያ ህዝብ መብቱን ሳይጎናጸፍ ተመልሶ ቤቱ ይገባልኛል ብሎ ማሰብ የታሪክን አካሄድ ከማይረዱ ጭፍን እምባ ገነኖች የሚጠበቅ ነው።

ሀገራችንን የሚገዛው የወሮበሎች መንግስት ካፈና የተለየ የፖለቲካ አማራጭ ማሰብም ስራ ላይ ማዋልም ከቶ እንደማይችል ማረጋገጫው አንዱ ይህ ያስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ነው። ይህንን ያስቸኩዋይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ ይልቁንም የህዝቡን ተገቢና ሰላማዊ አመጽ በደም የመበከል አባዜውን ለማርካት ብዙ ደም ለማፍሰስ እየተዘጋጀ ያለ መሆኑን የሚያሳዩ ብዙ ምልክቶችም መረጃዎችም እየታዩ ነው።

በቅርቡ በሶማሌ ክልል እንዳደረገው የግዴታ ሰላማዊ ሰልፎችን በማዘጋጀት በህዝብ ላይ ህዝብ የማነሳሳት አሳፋሪ ጸረ ህዝብና ጸረ ሀገር ፕሮፓጋንዳ ጀምሯል። ከዚህ አልፎም ትልልቆቹ የኦሮሞና የአማራ ብሔሮች በትንንሹቹ ላይ የተነሱ ለማስመሰል ወገኖቻችን በፍርሀት ተይዘው ከጎኑ እንዲሰለፉ ለማድረግ ጥረት እያደረገ መሆኑ ታውቋል። አልፎ አልፎም አንድ ብሔረሰብ በሌላው ላይ ጥቃት እንዲያደርስ የማደራጀትና የመቀስቀስ ስራ እንደሚሰራ መራጃዎች ያሳያሉ። ባንዳንድ አካባቢዎችም በወያኔ ካድሬዎች ቅስቀሳ የርስ በርሰ ግጭቶች ተከስተውም ተመልክተናል። ወያኔ ይህን የሚያደርገው ህዝቡ ከራሱ ከወያኔ ጋር ያለውን የመብት ጥያቄ ትግል ወደ እርስ በርስ ጦርነት ለመቀየር ነው። ይህ የቁም ቅዠት ከተሳካለት ገላጋይ በመምሰል ትንሽ እድሜ እቀጥላለሁ ብሎ ስላመነ የሚያደርገው ነው። ሰሞኑን በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች በተለይም በነገሌና ሌሎች የሀገራችን ማዕከላዊ ደቡብ አካባቢዎች የዚህ አይነት ወያኔ ሰራሽ ግጭቶችን ተመልክተናል። የወያኔ መሪዎች እንደማንኛውም ሕዝብ ላይ እንደሚፈጽሙት ወንጀል ሁሉ ለዚህም ወንጀል ሙሉ በሙሉ ተጠያቂዎች መሆናቸውን ሊያውቁ ይገባል።

እንደወያኔ አይነት ለስልጣኑ ሲል የፈለገውን ነገር ለማድረግ ወደሁዋላ ለማይልና የሞራል ለከት ለሌለው መንግስት የሚፈስ የህዝብ ደምም ይሁን የርስ በርስ ደም መፋሰስ ከቁም ነገር አይገባም። ወያኔ ይህን በተግባር አሳይቶናል። እንደዚህ ያለ ትንሽም ሀላፊነት የማይሰማው መንግስት ተብዬ ነገር ባለበት ሀገር ውስጥ የርስ በርስ ሰላማችንን ለመጠበቅና ግጭቶችን ለማስወገድ ብሎም የወያኔ መሳሪያ አለመሆን በራሳችን በዜጎቹ ትከሻ ላይ የወደቀ ነገር ነው። በመሆኑም ወያኔን ለማስወገድ ከምናደርገው ትግል ጎን ለጎን ወያኔ የሰራልንን ወጥመድ አየበጣጠስን ርስ በርሳችን እየተጠባበቅንና እየተናበብን ትግሉን ማፋፋም ይኖርብናል።

ወያኔን ከትከሻችን ላይ አሽቀንጥረን እስካልጣልን ድረስ የሰላም፣ይህይወትና የደህንነት ዋስትና የለንም። ወያኔ መኖር የሚችለው ህዝብን በስጋት ውስጥ በመክተት በመከፋፈልና በማጋጨት መሆኑን ማወቅና ይህንን ወጥመድ ማክሸፍ መቻል አለብን። በየአካባቢያችን ርስበርስ ለማጋጨት የሚደረጉ ሙከራዎችን፣ ቅስቀሳዎችንና እንቅስቃሴዎችን ነቅተን መጠበቅ አስቀድሞ ህዝብ እንዲያውቀው በማድረግ መካላከል ይሆርብናል። የዚህ አይነት እኩይ ተግባሮችን ለወያኔ መሳሪያ በመሆን ለመስራት የሚፈልጉ ዜጎችን አስቀድሞ ማጋለጥ ማግለልና የህዝቡን ሀይል ፈርተው ከእኩይ ተግባራቸው እንዲቆጠቡ ማድረግ ያስፈልጋል።

ንቅናቄያችን አርበኞች ግንቦት 7 ወያኔ ዛሬ ከመቼውም የበለጠ የተሽመደመደበትና እስከዛሬ የተጠቀመባቸው የመግዣ ዘዴዎች ሁሉ አልሰራ ብለውት የተጨነቀበት ወቅት ላይ ነው ብሎ ያምናል። ስለዚህ የኛ ተግባር መሆን ያለበት፤ ይህ ያምባገነንና የዘራፊ ቡድን ሰማይ መሬት እንዲዞርበትና ብዙ ጥፋት ሳያደርስ የሚወድቅበትን መንገድ ማፋጠን ነው ። ፍትህ ፤ እኩልነትና ነጻነት በአገራችን እንዲሰፍን የሚንሻ ቅን ዜጋ ሁሉ በያለንበት ሀይላችንን አስተባብረን እንነሳ ።

የንቅናቄያችን ሊቀመንበር ፕሮፈሰር ብርሃኑ ነጋ በቅርቡ ባስተላለፈው መልዕክት እንዳለው ዘንድሮ ሞተንም ሆነ ገለን ነጻነታችንን የምንቀዳጅበት ዘመን ነው።

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !!!