ሽማግሌዎች ነን ካሉ መጀመሪያ ወያኔን ያግባቡ – #ግርማ_ካሳ

ራሳቸውን የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ብለው የጠሩ ሰዎች፣ በኢቢሲ ቀርበው አንዳንድ ነገር ብለዉናል። ስለሰላም፣ ስለመግባባት…ወዘተረፈ ነግረዉናል። በግሌ በመርህ ደረጃ በተናገሩት ነገር ምንም ችግር የለኝም። ለአመታት ስጽፈዉና ስናገረው የነበረ ነገር ነው።

ሆኖም ግን እነዚህ ሽማግሌ ነን ባዮች መኖር አለበት ብለው እየጠየቁት ያለው ሰላም ሊኖር ያልቻለው ሕወሃቶች የሰላም በሮችን በሙሉ ስለዘጉ መሆኑን መዘንጋት የለባቸው።በሰላም የሚንቀሳቀሱትን አስረዋል። በሰላም ብእርና ቦርድ ይዘው የጻፉትን አስረዋል። ብዙዎች ከመሬታቸው አፈናቅለዋል። ጠንካራ የሚባሉ የፖለቲካ ደርጅቶችን ዘግተዋል። ምንም አይነት የመናገር፣ የመጻፍ፣ ሀሳብን በነጻነት የመገልጽ መብት ዜጎች የላቸው፡ የኢኮኖሚክ መብት የላቸውም። የገዢው ፓርቲ አባል ካልሆኑና በገዢው ፓርቲ ዉስጥ የሚሰጡ ደርቲ (ቁሻሻ) መመሪያዎችን ተግባራዊ ካላደረጉ ስራ መቀጠር አይችሉም። በአጠቃላይ የዜጎችን ሕልወና ነው ወያኔዎች አደጋ ዉስጥ የከተቱት።

በመሆኑም ዜጎች የሰላሙ በር ስለተዘጋ፣ አማራጭ ስላጡ ወደ ጫካ ገቡ። ወደ አመጽ ሄዱ። ይሄ ደግሞ ተፈጥሯዊ ነው።

እነዚህ ሽማግሌ ነን ባዮች፣ በርግጥ ለአገርና ለሕዝብም ለሰላም ቆመናል የሚሉ ከሆነ ፣ በኢቢሲ ቀርበው ህዝቡን ከሚያሰለቹትና ለግፈኞች የፖለቲካ ፍጆታ መጠቀሚያ ከሚሆኑ፣ ግፈኞቹን ፊት ለፊት በድፍረት መግጠም ነው ያለባቸው።

አመጹ አሥር ሺህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቢኖር አይቆምም። የተጀመረዉም መለስተኛ ጦርነት ይባባሳል እንጂ አይበርድም። አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እንዳሉት በመከላከያ፣ ወይም በፖሊስ ወይም በደህንነት ሃይል ህዝብን ማረጋጋት፣ ሰላምንም ማምጣት አይቻልም። ሕዝብን በመስማትም ህዝብን በማክበርና የሕዝብን ጥያቄዎች በመመለስ ነው አስተማማኝ ሰለም የሚመጣው።

ሰላም ከተፈለገ፣ እነ ጌታቸው ረዳ፣ አንዴ እነ አትሌት ሃይሌን፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ሌላውን እያቀረቡ አይመናቸኩብን። በርግጥ ለሰላም ፍላጎት ካላቸው፣ ጥቂት ቀላል ነገሮች ቢያደረጉ ብዙ ነገሮችን ማርገብ ይችላሉ፡

1. የሕሊና እስረኞች ( አንዱዋለም አራጌ፣ እስክንደር ነጋ፣ በቀለ ቀርባ፣ ኮሎኔል ደመቀ ዘዉዱ፣ አስቴር ስዩም ፣ ንግስት …….) በሙሉ መፈታት አለባቸው።

2. ከአማራው ክልል እና ከኦሮሚያ ክልል የአጋዚ ፌደራል ጦር ለቆ መዉጣት አለበት። ህዝቡና የክልሉ ፖሊሶች ራሳቸው ህግና ስርዓትን ማስጠበቅ ይችላሉ። ዜጎች አጋዚዎችን ሲያዩ ነው የሚቆጡት፣ ወደ አመጽም የሚሄዱት። አጋዚዎች እንደ ወራሪ ጠላት ስለሚታዩ።

3. አገር ዉስጥ ካሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ጥገናዊ ሳይሆን መሰረታዊ የዴሞክራሲ ተቋማት (ምርጫ ቦርድ፣ ፍርድ ቤት፣ ፖሊስ፣ መከላከያ ፣ ሜዲያ..) ገለልተኛ የሚሆኑበትን መንገድ የሚያመቻች ኮሚሽን በማቋቋም ከዚህ በኋላ የምርጫ ሰላማዊ ፖለቲካ የሚያዋጣ እንደሆነ ማሳየት አለባቸው።

ሌሎች ጥያቄዎችም አሉ። ግን ቢያንስ እነዚህን ሶስቱን እንኳን ማድረግ ቢችሉ፣ ወይንም እንደሚያደርጉ በሜዲያ ቢያወጁ ፣ በ እጅጉ ነገሮች ይረግቡ ነበር።

ኳሷ ያለችው ገዢውች ሜዳ ላይ ናት። እነ ሃይሌ እንሸምግል ካሉ ጋሪዉን ከፈረሱ አያስቀድሙ። ፈረሱ ይቅደም። ሰላምን በተመለከተ ተቃዋሚዎች ጋር፣ ህዝቡ ጋር ቅንጣት ያህል ችግር የለም። ሰላም አደፍራሹ፣ ጸረ-ሰላሙ ወያኔ ራሱ ነዉና ፣ ከቻሉ ወያኔን ለማግባባት ይሞክሩ።ካልሆነ ደግሞ አርፈው ይቀመጡ። አያደንቁሩን።

ሽማግሌዎች ነን ካሉ መጀመሪያ ወያኔን ያግባቡ – #ግርማ_ካሳ

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.