ውይይቱ ስለሚመለከተኝ በተነሱት ጭብጦች ላይ እኔም የምለው አለኝ  (ከይገርማል)

bereket-and-lidetuወቅታዊውን የኢትዮጵያ ሁናቴ አስመልክቶ የፖለቲካ ፓርቲወችና ታዋቂ ሰዎች ያካሄዱትን ውይይት በከፊል ተከታትያለሁ:: በዚህ ውይይት ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡ ሰዎች የኢትዮጵያን ፖለቲካ በተለይም ኢሕአዴግ ኢትዮጵያን ከተቆጣጠረበት ጊዜ ጀምሮ ያለውን በመዳሰስ ጥሩና ጥሩ ያልሆኑ ጎኖች ናቸው ያሏቸውን ጉዳዮች በማንሳት ከወቅታዊ ችግሮች ጋር አያይዘው ለማሳየት ሞክረዋል:: ሀገራችን ለገጠሟት ችግሮች ምክንያት ናቸው ያሏቸውን ነጥቦች  ዘርዝረው ለነዚህ ችግሮች መፍትሄ ለማስገኘት ያሳዩትን ተሳትፎ በበኩሌ ከልብ አደንቃለሁ:: የትኛውም የሀገሬ ጉዳይ ይመለከተኛል የሚል ለሀገሩና ለሕዝቡ ፍቅርና ክብር ያለው ማንኛውም ዜጋ የተገኘውን አጋጣሚ ሁሉ ተጠቅሞ ይበጃል የሚለውን ሀሳብ መተንፈሱ ተገቢ ነው:: ይህንን መሰረት በማድረግ እኔም እንደ አንድ ሀገር ወዳድ ዜጋ በውይይቱ ላይ በተነሱት ጭብጦች ላይ ተመርኩዤ የግል አስተያየቴን ለማቅረብ እፈልጋለሁ::

የኢሕአዴግ ሰዎች የተናገሩትን በተመለከት ምንም ባልል እመርጣለሁ:: በተለይ በአመራር ላይ የተቀመጡት ሰዎች ስለሀገር አንድነትና ስለሕዝብ ፍቅር የሚጨነቁ አለመሆናቸውን ብዙ ጊዜ በተግባር አሳይተውናል:: እነርሱ የሚነግሩን ኢትዮጵያን ከኢኮኖሚ ኋለቀርነትና ከዴሞክራሲ እጦት አላቀው አለምን ጉድ ያሰኘ ልማት እንዳስመዘገቡ ነው:: የኢትዮጵያን ሕዝብ በተለይ የገጠር ኗሪውን ከድህነት አረንቋ ስበው ማውጣት በመቻላቸው በአርሶ አደሩ ልብ ውስጥ ተደላድለው መተኛት እንደቻሉ ነው:: በዚህም ምክንያት የትኛውም ተቃዋሚ በገጠር ውስጥ የፖለቲካ ዘር ዘርቶ ለማምረት እንደሚቸገር ነው:: ከእነዚህ ሰዎች ጋር በምንም መንገድ ተወያይቶ መተማመን የሚቻል አይደለም:: ልማት እንዳላስመዘገቡ: የትኛውም ሕዝብ እንደማይወዳቸውም ያውቃሉ:: ነገር ግን ይፋ ያላወጡት ድብቅ ጸረ-ኢትዮጵያ አጀንዳ ያላቸው ስለሆኑ እስካስሄዳቸው ድረስ የትኛውንም የማጭበርበሪያና የማዘናጊያ መንገድ ከመጠቀም ወደኋላ አይሉም::  ስለዚህ እነርሱ ያሉትን ቢሉ ሰምቶ ከማለፍ በስተቀር ክርክር መግጠሙ ትርጉም አልባ ነው ብየ ስለማምን የነሱን ንግግር ወደጎን ትቼ ሌሎች ሰዎች በተናገሯቸው በተለይም በአቶ ልደቱ ንግግሮች ላይ አስተያየት ላቀርብ ወደድሁ::

አቶ ልደቱን ከወጣትነታቸው ጀምረው ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ህይወት ባበረከቱት ጉልህ ድርሻ ከልብ አደንቃለሁ:: ለሀገርና ለሕዝብ ይጠቅማል ብለው ያመኑትን የፖለቲካ አደረጃጀት ተጠቅመው የዴሞክራሲና የምጣኔ-ሀብት እድገት አማራጭ በማቅረብ ለተግባራዊነቱ ብዙ መስዋእትነት እንደከፈሉ እረዳለሁ::  አቶ ልደቱ በየሄዱበት እየተከታተሉ የዛቻና የማስፈራራት ድርጊት በገዥው ፓርቲ ቅጥረኞች ተፈጽሞባቸዋል: በተጠና መንገድ የመገለል ሰለባ ሆነዋል: ታስረዋል: ተገርፈዋል:: ይህን ሁሉ ተቋቁመው እስካሁን በፖለቲካው አለም መቀጠላቸው በራሱ ያላቸውን የአላማ ጽናትና ቁርጠኝነት በግልጽ የሚያሳይ ነው:: የ1997ቱ ዓ.ም ምርጫ አቶ ልደቱ ገናና ሆነው የታዩበት ወቅት ነበር:: በድፍረታቸው: የሰውን ቀልብ ለመሳብ ባላቸው የድምጽ ውበት (Tone) በሚያነሷቸው ቁምነገሮችና ጭብጦች መላውን ሕዝብ ከቅንጅት ጎን እንዲቆም ካደረጉት ጥቂት ሰዎች መሀል አንዱ ነበሩ::  መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይ ወጣቱ ስሜታቸውን እየተጋራ ሲያዝኑ አዝኖ ሲስቁ ስቋል:: ከቢሯቸው እንዳይወጡ በታገቱበት ጊዜ ብዙወች ሱባዔ ገብተው በቁራጭ ምንጣፍ ከወለል ላይ እስከመተኛት ደርሰው ነበር:: ዛሬ ያ ሁሉ ተቀይሮ ትንሽ ትልቁ አይንህ ላፈር ይላቸው ይዟል:: አቶ ልደቱ በሕዝብ ከመከበር ወደመጠላት ያወረዳቸው የኢሕአዴግና የትግል አጋሮቻቸው የክፋት ሴራ ነበር:: ሁሉም በተበለጥን ስሜት ተረብሸው ነበር:: ሁሉም ከፊት ለመታየት ከፊት ያለውን ወርውሮ ከኋላ መጣልን መርጦ ነበር:: ያ ባይሆን ኖሮ ለምን የአቶ ልደቱን ጥፋት አንድ ሁለት ብሎ ማስቀመጥ አልተቻለም: በተነሱት ነጥቦች ላይስ እርሳቸው መልስ እንዲሰጡ አድርጎ ከግራ ቀኝ የተሰነዘሩትን ነጥቦች ይዞ ለመፍረድ ለምን አልተሞከረም? ከአቶ ልደቱ ጋር በዝምድናም ይሁን በአካባቢ አንገናኝም:: ግን ምን ብየ ልጥላቸው? ሌሎችን ተከትየ? ፕሮፌሰር መስፍንን ጨምሮ ሌሎች ትላልቅ የቅንጅት አመራሮችን ልደቱ ከሀዲ የተባለበትንና ለመጠላት ያበቃውን ምክንያት እንዲነግሩን ከዚህ በፊት በጻፍኋቸው ጽሁፎች ጠይቄ ምንም ያገኘሁት መልስ የለም:: እኔም እኮ እንደሌሎች ብጠላቸው ግድ የለኝም:: ግን ምን አየሁ ብየ ልጥላቸው? ቅንጅትን ያፈረሰው እሱ ነው ምናምን የሚለው ጉግ ማንጉግ ወሬ እንደሆነ ትርጉም የሚሰጥ አይሆንም:: እርግጠኛ ነኝ ልደቱ “ቅንጅትን ያፈረስሁት እኔ ነኝ” ብለው ደፍረው ቢናገሩ “ጉረኛ! ቅንጅትን ለማፍረስ የሚያስችል ምን አቅም ኖሮህ ነው?” የሚሉ ድምፆች ከዚህም ከዚያም ሊደመጡ በቻሉ ነበር:: ለማንኛውም ይህን በዚህ ገትቸ ውይይቱን በተመለከተ ወደአቀረቡት ሀሳብ ላይ አተኩሬ ጥቂት አስተያየቶችን ልበል::

አቶ ልደቱ አሁን የሚከተሉት የፖለቲካ ዘይቤ ከስልጣን ተፎካካሪነት ይልቅ ኢሕአዴግን ወደማባበል ያዘነበለ ይመስላል::   እንደሚታወቀው የወያኔ ህግ የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት የወያኔ ውሳኔ የኢሕአዴግ ውሳኔ ነው:: ሕወሀት ያጸደቀው ሰነድ የኢሕአዴግ ሰነድ ነው: ኢሕአዴግ ያጸደቀው ደግሞ የመንግሥት ሰነድ ነው::

ወያኔ ሀገራዊ ፍቅርና ሀገራዊ አጀንዳ የለውም ለማለት የሚያበቃን  የሚሰራቸው ስራወች ናቸው:: ከሀገራዊ ፍቅር ይልቅ ጎሳዊ ፍቅር እንዲያብብ ሲገፋፋ: ከአንድነት ይልቅ ልዩነት እንዲያብብ ሲያደርግ ነው እዚህ የደረሰው:: ስለሀገርና ስለህዝብ አንድነት የሚከራከሩ ወገኖች ትምክህተኛ እየተባሉ ሲንቋሸሹ ነው ዘወትር የምንሰማው:: የአሰብን ወደብ እኛ ካልተጠቀምንበት የግመል ማጠጫ ከመሆን ያለፈ ፋይዳ የለውም በሚል ከወያኔ የድብቅ አላማ አንዱ የሆነው የአሰብ ጉዳይ እንደቀልድ ተገፍቶ ወደብ-አልባ እንድንሆን  መደረጉን ነው የምናውቀው:: አቶ ልደቱ ራሳቸው ለነበሩበት ፓርላማ ይዞታቸውን በሱዳኖች ተነጥቀው ለስደት የተዳረጉ በአዋሳኝ ይኖሩ የነበሩ ወገኖቻችን አቤቱታ ማቅረባቸውንና አምባገነኑ መለስ “አንድም ሰው አልተፈናቀለም” በማለት ሙልጭ አድርጎ ሲዋሽና ዳርድንበራችንን ሲያስደፍርና መሬት አሳልፎ ሲሰጥ ነው ያየነው:: ሰው በሀገሩ ላይ ለመኖር አልፈቀድለት ብሎ በትዕዛዝ ከክልላችሁ ውጪ የመጣችሁ ናችሁ ተብለው በአሥር ሺወች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲፈናቀሉ ነው ያየነው:: ዜጎች በብሔር ተደራጅተው እንዲተላለቁ ሲቀሰቀሱ ነው የምናውቀው:: ስንቱ ይወራል! ታዲያ ወያኔ-መሩ ኢህአዴግ ጠላት ነው: ኢትዮጵያዊም አይደለም ቢባል ስህተቱ ከምኑ ላይ ነው?

“ተቃዋሚወች ለኢሕአዴግ ያላቸው አመለካከት የተሳሳተ ነው:: ይህን ሁሉ ልማት እየሰራ እያለ ሀገር ለማፍረስ እንደመጣ ውጫዊ ኃይል አድርጎ መመልከቱ አብሮ ለመስራትና ለመካከር ትልቅ እንቅፋት ፈጥሯል” ይላሉ አቶ ልደቱ:: ኢህአዴግን እንደ ኢትዮጵያዊ ድርጅት እንዲታይ የማያደርጉት ምክንያቶች ብዙ ቢሆኑም ከላይ በመጠኑ ያነሳኋቸው ምክንያቶች ብቻቸውን ለአስረጅነት ከበቂ በላይ ናቸው:: ይህን እውነታ አቶ ልደቱ ያጡታል የሚል ግምት የለኝም:: ኢሕአዴግ መንገዶችን ሁሉ ጥርቅም አድርጎ ዘግቶ ያሻውን እየተናገረ የሚፈልገውን እያደረገ ያለ መሆኑን አልተገነዘቡም ለማለት አይቻልም:: አቶ ልደቱ እየተጣጣሩ ያሉት ኢትዮጵያዊ አጀንዳ የሌለውን ወያኔ በመለማመጥ ኢትዮጵያዊ ለማድረግ እንደሆነ  ነው:: በውጭ ያሉት ተቃዋሚወች ኦነግንና ኦብነግን ኢትዮጵያዊ ለማድረግ ጎንበስ ቀና እንድሚሉት ሁሉ አቶ ልደቱም ወያኔ በረሀ  በነበረበት ጊዜ ያስቀመጠውን ኢትዮጵያን የመበተንና ትግራይን የመገንጠል ግብ ሰርዞ ኢትዮጵያዊነት እንዲላበስ ነው እያባበሉት ያሉት:: ይህ በፍጹም የሚቻል አይመስለኝም:: እየተሰራ ያለው ስራ ኢትዮጵያን እያዋዛ ቀስ በቀስ የሚንድ እንጅ አንድነቷን የሚያጠብቅ: በሕዝብ መሀል አብሮነትን የሚያጠናክር አይደለም::

አቶ ልደቱ ወያኔ የሰራው ትልቅ ልማት እንዳለ ሲናገሩ ስሰማ ከት ከት ብዬ እየሳቅሁ ነበር:: እንግሊዝ ሀገር ድረስ ሄደው በልማት ኢኮኖሚ (Development Economy) ሁለተኛ ዲግሪያቸውን እንደተማሩ ሰምቻለሁ:: በምጣኔ ሀብት ትርጉም ልማት ማለት ሁለንተናዊ ዕድገት ከሚለው ጋር የሚቀራረብ ትርጉም የሚሰጠው ቃል ነው:: ልማት የኢኮኖሚ እድገትና ፍትሀዊ ክፍፍልን: የማህበራዊ እድገትን:  የዴሞክራሲና የአሳታፊነት እድገትን: ሞራላዊና ስነልቦናዊ እርካታን- – –  የሚያጠቃልል የሁሉም ዕድገቶች ድምር ውጤት ነው:: ታዲያ እንዴት ሆኖ ነው ልማት አለ ማለት የሚቻለው? ሚልዮኖች ከቀን አንድ ጊዜ በልተው ማደር በማይችሉበት: የኑሮ ውድነቱ ጣሪያ በነካበት: ሰው በዘረኝነትና በኢፍትሀዊ አሰራር ተስፋ በቆረጠበት በአሁኑ ወቅት እንዴት ልማት አለ ብሎ ደፍሮ መናገር ይቻላል? ሁሉም በግላጭ ማየት የሚችለው የማህበራዊ አገልግሎት ዘርፉን ዕድገት ነው:: ይኸ ዕድገት የተገኘው ግን በራስ ገቢ ነው ወይ?

 

እንደሚታወቀው ባለፉት 25 አመታት ከውጪ ሀገር የተገኘው እርዳታና ብድር እጅግ ከፍተኛ ነው:: ይህ ገንዘብ እንደኮንዶሚኒየም ቤቶች 40/60 በሚለው ስሌት የተመደበ ሆኖ 40 ለሀገሪቱ 60ው ለወያኔ የሚውል ነው:: የኮንዶሚንየም 20 በ80 እና 40 በ 60 የሚለው ስያሜ የመጣው ምናልባት ከዚህ ሊሆን ይችላል::  11 ቁጥር ከግምባር ላይ ምልክትነት አልፋ ወያኔ የተመሰረተበትን የካቲት 11ን ብአዴን ተመሰረተ የተባለበትን ሕዳር 11ን ሌላው ቀርቶ ሀገራችን በየአመቱ 11 በመቶ እያደገች ነው የሚባልለትን የ11 ቁጥር ፍቅር አይነት መልዕክት ያለው ሊሆን ይችላል:: ያም ሆነ ይህ በማምረት ተግባር ያልተገኘ ከውጭ በመጣ ብድርና እርዳታ የሚገነባ መንገድና ህንጻ ሀገሪቱ እንዳስመዘገበችው ዕድገት የሚታይ አይሆንም:: አንዳንዴ የሚገርመኝ ነገር ደግሞ አለ:: የኢኮኖሚውን ዕድገት ብቻ ነጥለን  ብንወስድ በዚህ አመት 11% አድገናል ሲባል ከየትኛው አመት ጋር አወዳድረውት እንደሆነ ማወቅ እያስቸገረኝ ነው:: እንደሚታወቀው እድገትን በሁለት መንገድ መግለጽ ይቻላል:: አንደኛ ካንድ ቋሚ አመት ጋር በማነጻጸር ሲሆን ሌላው ደግሞ ያምናውን እና የዘንድሮን በማወዳደር የሚገለጽ ነው:: ለምሳሌ 1983 ዓመተ ምህረትን መነሻ አመት (Base year) አድርጎ በመውሰድ የሁሉንም አመት ዕድገት ከ1983ቱ ጋር በማወዳደር ማስላት አንደኛው መንገድ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከአመት አመት የሚኖረው እድገት የሚሰላበት መንገድ ነው:: በሁለተኛው የእድገት አሰላል አምና 10% ያደገ ኢኮኖሚ ዘንድሮ ም 10% ቢያድግ ከአምናው ይልቅ ዘንድሮ የበለጠ አድጓል ማለት ነው:: የዋጋ ግሽበትን ከግምት ሳናስገባ ለውጡን ብቻ ብንወስድ ታችአምና 100 ብር ያስገኘ ኢኮኖሚ አምና በ10% አድገ ብንል የአምናው ኢኮኖሚ 110 ብር የተገኘበት ነበር ማለት  ነው:: በያዝነው አመት ኢኮኖሚው በ10% አደገ ስንል ደግሞ  ኢኮኖሚው 110*10% = 11 ብር ለውጥ አሳይቷል ማለት ነው:: ይህም ማለት አምና ከተገኘው ገቢ የ 11 ብር ብልጫ ተገኝቷል ማለት ነው:: ይህንን ለውጥ ከመቶ ሳይሆን ከብዙ ቢሊዮኖች ተነስተን ስናሰላው በጣም ብዙ ነው:: በአጭሩ በየአመቱ ከዜሮ በላይ የሆነ እድገት እያስመዘገብን ነው ሲባል አምና ከነበረው ምርት የበለጠ ምርት ዘንድሮ አፍሰናል ማለት ነው:: እንዲህ አይነት ዕድገት ለማስመዝገብ ሀገሪቱ በየአመቱ ከነበሩት በተጨማሪ ሌሎች የዕድገት ፕሮጀክቶችን ወደሥራ ማስገባት ይኖርባታል:: ይህ ማለት በአምናው አመት የተጠናቀቁትን ስራወች መተካት ብቻ ሳይሆን ሌሎች ተጨማሪ የኢኮኖሚ ዕድገት አምጪ ሥራወችም መፈጠር አለባቸው ማለት ነው:: በእርግጥ እንዲህ አይነት ሁኔታ በየአመቱ ተፈጥሮ ነበር ወይ? ለሚለው የመከራከሪያ ሀሳብ ፍርዱን ለአንባቢ ትቼ የኢኮኖሚ ዕድገቱን የተመለከተ የላይ ላይ ዳሰሳየን ልቋጭና ወደሌሎች ጉዳዮች ልግባ::

አቶ ልደቱ ኢሕአዴግ በሽግግርሩ ጊዜ ይበልጥ ዴሞክራሲያዊ እንደነበረ ይናገራሉ:: ሀገራዊ አደረጃጀት ያላቸው ፓርቲወች ተገፍተው የጎሣ ድርጅቶችና ተወካዮች ያውም ከኦሮሞ ቀጥሎ በብዛቱ በሀገሪቱ በሁለተኛ ደረጃ የሚገኘው የአማራ ሕዝብ ባልተወከለበት ሁኔታ የተመሰረተው የሽግግር መንግሥት እንዴት ሆኖ ‘ዴሞክራሲያዊ ነበር’ ለማለት እንደሚቻል ግልጽ አይደለም:: ኢህአዴግ እንዲጠላ ተቃዋሚወች ብዙ ሰርተናል: ነገር ግን ከእኛ ይልቅ የመንግሥት ሜዲያ አሰልችና መንቻካ አቀራረብ ነው የበለጠ እንዲጠላ ያደረገው ይላሉ አቶ ልደቱ:: ይኸው እኛም ጥፋታችንን አምነናል በሚል ቅላጼ ለዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ግንባታ በጎ ርምጃ ለመውሰድ በቅድሚያ ኢሕአዴግም እንደርሳቸው ጥፋቱን አምኖ እንዲቀበል ለማበረታታት ሲጥሩ ታይተዋል:: አሁን የተደቀኑብንን ፈተናወች ለመሻገር ኢሕአዴግን ማግለል ሳይሆን የመፍትሔው አካል ማድረግ ያስፈልጋል በማለት ከመንግሥት: ከሕዝብና ከተቃዋሚወች የሚጠበቁ ናቸው ያሏቸውን አስተዋጽዖወች ዳስሰዋል:: ተቃዋሚው አንድን ሕዝብ ተጠቃሚ ሌላውን ተጎጅ እንደሆነ አድርጎ መቀስቀስ ተገቢ እንዳልሆነ ገልጸው በመግባባትና በብሔራዊ እርቅ ላይ ያነጣጠረ የሚያቀራርብ ፖለቲካ እንዲሰራ መክረዋል:: እንዲህ እንዲህ እያሉ የወያኔን አንጀት ለመብላት ሲጥሩ ይታያሉ::

ኢሕአዴግ የተጠላው ተቃዋሚው እንዲጠላ ስለቀሰቀሰበት ወይም ሜዲያው የኢሕአዴግ ልሳን ስለሆነ ብቻ አይደለም:: ኢሕአዴግ  የተጠላው በሚሰራቸው ጸረ-ሕዝብ እና ጸረ-ሀገር ተግባሮቹ ነው:: ለወያኔ መራሹ መንግሥት መጠላት ዋናው ምክንያት የሀገራችንን አንድነት ለመናድ እና በሕዝቦች መሀል ልዩነትን ፈጥሮ በጥላቻ እንዲጠፋፉ አቅዶ በሚሰራው እኩይ ሥራው ነው:: ሌላው ሌላው ተጨማሪ ነው:: የትግራይን ሕዝብ ከሌሎች የተለዩ ወርቆች ናቸው ያለው ተቃዋሚው አይደለም:: የኢኮኖሚና የፖለቲካ ልዩነት በጎሣወች መሀል የፈጠረው ተቃዋሚው አይደለም::

እኔ በበኩሌ የአቶ ልደቱን አካሄድ በአድርባይነት ሳይሆን በአስታራቂነት መንፈሱ ነው የምረዳው:: ሕዝቡም ሆነ ተቃዋሚው ያልዋለበትን እንደዋለበት ያልሰራውን ስህተት እንደሰራው አድርጎ በማቅረብ የችግሩ ምንጭ አንተ ወያኔ ብቻ አይደለህም: ሁላችንም አጥፍተናል ለማለት ነው:: የወያኔን ልብ በፍቅር አሸንፎ ከሚከተለው አፈንጋጭ ሀሳብ ለማናጠብ: አካባቢያዊ ስሜቱን ፍቆ ለኢትዮጵያዊነት እጁን እንዲሰጥ እና ወደሰላም ወረዳ እንዲመለስ ለማድረግ ነው:: ይህ ግን በፍጹም ሊሆን የማይችል ነገር ነው::

የወያኔ ዕቅድ እንዲህ በቀላሉ በቃላት ሽንገላ የሚታጠፍ አይሆንም:: ትልቅ አላማ ለታላቋ ትግራይ ይዘው ነው የተነሱት:: በኢትዮጵያ ውስጥ መቀጠላቸው አላማቸውን ለማስፈጸም ረድቷቸዋል:: አላማቸውን ለማስፈጸም ደግሞ ማንኛውንም ስልት ይጠቀማሉ:: እና በኢትዮጵያ ስም ይበደራሉ: እርዳታ ይቀበላሉ:: የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ተቆጣጥረው ገቢና ወጭ ንግዱ ላይ ነግሰዋል:: የገንዘብና የባንኪንግ አገልግሎት በነርሱ ስር የወደቀ ነው:: የኢትዮጵያ የሆነውና ለኢትዮጵያ የመጣው ሁሉ ለታላቋ ትግራይ ምስረታ በእርሾነት እየዋለ ነው:: አንድ ቀን ሁላችንንም አናክሰው ወደትግራይ ማቅናታቸው አይቀርም:: ይህን አያደርጉም የሚሉ ብዙ ኢትዮጵያውያኖች ይኖራሉ:: አካሄዳቸው የሚያሳየን ግን ይህንን ነው:: ሳይመረጡ ተመረጥን: ሳይወደዱ ተወደድን: ሳያደርጉ አደረግን የሚሉት ለመዋሸት ብቻ አይደለም:: እነዚህ ሰዎች ያየነውን እና የምናውቀውን ሳይቀር የሚዋሹን ድክመታችንን አይተው ምንም አታመጡም ደግ አደረግን ለማለት ነው:: የሚሻለው ጎሰኞችን መለማመጥ ሳይሆን ራስን አጠንክሮ መገኘት ነው::

ከአቶ ልደቱ አነጋገር ውስጥ “ብቃት ያለው ተቃዋሚ ልንፈጥር አልቻልንም” የሚለው ቁምነገር ሊሰመርበት የሚገባ ነው:: ተቃዋሚው መሰባሰብ ያለበት በጋራ እሴቶች ዙሪያ እንጅ ኢሕአዴግን በመጣልና በመደገፍ ዙሪያ መሆን የለበትም:: የአንድነት ኃይሎች የሚባሉት ለዘላቂ አላማ በአንድ ላይ መቆም ሲያቅታቸው “ሥራ ከመፍታት ልጀን ላፋታት” በሚል አይነት ዘይቤ ከጎሳ ድርጅቶች ጋር ጊዜያዊ ትብብር ለመፍጠር በየፊናቸው ሲደክሙ ይታያሉ:: የጎሣ ድርጅቶች ከአንድነት ይልቅ ልዩነትን መሰረት አድርገው የተደራጁ ናቸው:: የሚናገሩትም ሆነ የሚያደርጉት ለጎሣቸው እንጅ ለኢትዮጵያ አይደለም:: ወያኔን ጨምሮ ሁሉም የጎጥ ድርጅቶች ከአንድነት ኃይሎች የበለጠ በመሀከላቸው መቀራረብና መተሳሰብ አለ:: በዚህም ምክንያት ከታላቋ ትግራይ ምስረታ በኋላም ቢሆን ሌሎቹ የጎሣ ድርጅቶች የሀገራችን የማይፈቱ እንቆቅልሾች ሆነው ኢትዮጵያን ማዳከማቸውን እንዲቀጥሉ የወያኔ ድጋፍ ሳይለያቸው ይቀጥላሉ::

ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ እያሉ የሚያለቅሱ ብዙ ድርጅቶች እንዳሉ ይታወቃል:: እነዚህ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ስም የሚጮሁት ጩኸት የዕውነት ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊነትን ከመውደድ የተነሳ ከሆነ ከዚህ የበለጠ የጋራ አጀንዳ ምን ሊኖር ይችላል? በሀገር ውስጥ ያሉት ሰላማዊ የአንድነት ታጋዮች በአንድነት መቆም ቢችሉ: በውጭ ሀገር የሚኖሩት የአንድነት ኃይሎች እንዲሁ በአንድነት ቢሰለፉ: ሕዝቡ ዳር እስከዳር ሊደግፋቸው እንደሚችል በርግጠኝነት መናገር ይቻላል:: ኢትዮጵያን ማእከል አድርጎ በሀገር ውስጥና በውጪ የሚፈጠረው ግምባር ከማንም የበለጠ ጠንካራ አመራር እንደሚኖረው አያጠራጥርም:: በጠንካራ አመራር ተብላልተውና ታሽተው የሚወጡ  የትግል ስልቶች ጎሰኞችን መሰረት እንደሚያሳጣቸው መገመት አይከብድም:: የአዲስ አበባ ሕዝብ በኢትዮጵያዊነቱ የሚደራደር እንዳልሆነ በግልጽ ይታወቃል:: ከአዲስ አበባ ውጪ የሚኖረው ሕዝብ የአዲስ አበባን ትንፋሽ የሚያዳምጥ መሆኑን ማስታወስ ተገቢ ነው:: አንድ ሳንሆን ስለአንድነት መደስኰሩ ትርጉም የለውም:: ስለዚህ ያለፈውን ሁሉ ስለኢትዮጵያና ስለሕዝባችን ስንል ይቅር እንባባልና በአንድነት እንሰለፍ:: ያን ጊዜ ለውጡን እናያለን::

ትንሳኤ ለኢትዮጵያ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.