ለወያኔ እድሜ ማራዘሚያ በተዘጋጀ መድረክ  ተቀዋሚዎች ምን ይሰራሉ?   {ይገረም አለሙ}

ethiopian opposition partyየፖለቲካ ድርጅት  የመገናኛ ብዙሀን ባለቤት አንዳይሆን የመከለክለውን  ህግ በመተላለፍ ወያኔ ያቋቋመው  ፋና  ሰሞኑን አንድ  የውይይት መድረክ አዘጋጅቶ ነበር፡፡ ውይይቱን  በቀጥታ ስርጭት ሳይሆን ለእኛ ይገባቸዋል ብለው የመጠኑልንን አቀናብረው አስተላልፈውልን ተመልክተነዋል፡፡ ጽሁፍ አቅራቢዎቹ ተወክለው ይሁን ወክለው ባይታወቅም ከምሁራን ከባለሀብት ከተቀዋሚና ከኢህአዴግ ተብለው ነው የቀረቡት፡፡ ከኢህአዴግ አቶ በረከት ከተቀዋሚ አቶ ልደቱ፡፡ ዶ/ር መረራንና ኢ/ር ይልቃልን ጨምሮም ጥቂት የፓርቲ ሰዎችንም በአዳራሹ ተመልክተናል፡፡ የባለሀብቶች ተወካይ የተባሉት ጽሁፍ አቅራቢ   ለመድረኩ መዘጋጀት ምክንያት በሆነው ህዝባዊ አመጽ ለተገደሉት ሀዘናቸውን በመግለጽ ብቸኛ ሰው ሆነዋል፡፡ ከዚህም ሌላ  ኢህአዴጎች መታደስ ሳይሆን ፈርሶ መሰራት ነው ያለባችሁ በማለት ፖለቲከኞቹ ያልደፈሩትን ተናግረዋል፡፡ አቦ እግዜአብሄር ይባርክዎት፡፡

ተቀዋሚ ፖለቲከኞች በሀገራዊ ጉዳይ ላይ ምክክር በሚደረግበት በማናቸውም መድረክ ተጋብዘው አይደለም ራሳቸው ጠይቀው ሊገኙ አንደሚገባ አምናለሁ፡፡ ነገር ግን በተለያየ ግዜ የወያኔን ግብዣ ፋይዳ ቢስ እያሉ አለመቀበላቸውን ሲነገሩን  የነበሩ ሰዎች  የህውኃትን  ህልውና ለመታደግ በተዘጋጀ በዚህ መድረክ ላይ መታየታቸው ለምን አሰኝቷል፡፡

በዚህ መድረክ  መገኘት ያለባቸው ሰዎች ወያኔ  በጥገናዊ ለውጥና በጥልቅ ተሀድሶ ራሱን አርሞ  በሥልጣኑ አንዲቀጥል የሚሹና ምክር ሰምቶ  የሚታዘዝለትንም መድሀኒት ወስዶ ለህዝብ ጥያቄ ተገቢና ትክክለኛ መልስ መስጠት ይችላል ብለው የሚያምኑና  ምክር ለመለገስና መድሀኒት ለማዘዝ የተዘጋጁ መሆን አለባቸው፡፡

ከዚህ አንጻር  የተቀዋሚ ተወካይ በሚል ሽፋን ጽሁፍ ለማቅረብ የበቃው አቶ ልደቱ  ተገቢ ቦታው ላይ ነው የተገኘው እላለሁ፡፡ ከተሰብሳቢው በኩል ሆነው ሲናገሩ ያየናቸው  ዶ/ር መረራና ኢ/ር ይልቃል ግን ያለቦታቸው ነው የተገኙት ብየ ስላመንኩ ለምን የሚል ጥያቄ አነሳለሁ፡፡ ከስሜት ሳይሆን ከምክንያት ተነስተን መድረኩ የሚገባቸውንና ያለ ቦታቸው የተገኙትን ለይቶ ማወቅና የመገኘታቸውን አንዴትነት መረዳት የህዝቡን ትግል ቀጣይ ተግዳሮቶች ለመለየት የሚያስችል  ይሆናል፡፡

አቶ ልደቶ ፤

አቶ ልደቱ ከተቀዋሚ ፓርቲ ተብሎ ከመነገሩ በቀር ተቃዋሚዎችን አይደለም አባል የሆነበትን ኢዴፓን ስለመወከሉ አልተገለጸምና አነጋጋሪ ሆኖ የሰነበተው ንግግሩ የግል አቋሙ ይሁን   የኢዴፓ አልታወቀም፡፡ ፓርቲውም አላስተባበለም፡፡ የተገኘው በግሉም ይሁን በኢዴፓ መድረኩ የሚመጥነው ነውና  በተገቢው ቦታ ነው የተገኘው ፡፡ይህን ደግሞ ከተመደበለት  በላይ 10 ደቂቃ አስጨምሮ ለ40 ደቂቃ ባሰማው ንግግሩ  ያረጋገጠው ነው፡፡  አቶ ልደቶ በብዙ መንገድ ወያኔን አድንቆና አጀግኖ የህዝቡን ትግል አናንቆና ወያኔን በሚገባው ቋንቋ ማነጋገር የሚሉ ወገኖችን አክራሪዎች እያለ በዘለፈበት ንግግሩ አስቀድሞ ለሚያውቁተ የበለጠ ማረጋገጫ ሰጥቷል፡፡ እስካሁን ላላወቁትና በተለይ ከምርጫ 97 ወዲህ ለአቅመ ፖለቲካ ለደረሱት ወጣቶች ደግሞ ራሱን በግልጽ አሳይቷል፡፡ ወያኔዎች በዛ መድረክ ሲያቀርቡት ማንነቱን ተረድተውና ፍላጎቱን አጢነው ይሁን ወይም ለመድረኩ እንዲስማማ አዘጋጅተውት ባይታወቅም የልደቱ አድራጎት ግን ለእነርሱም ሆነ ለራሱ የሚጠቅም አይመስለኝም፡፡ የእነርሱ ፍላጎት ሊጠቅሙትና ሊጠቀሙበት ሳይሆን ለመጨረሻ ሊገሉት ከሆነ ግን የሚሳካላቸው ይመስለኛል፡፡

ትናንት ዛሬ አይደለም በሚል እሳቤ ልደቱ ካደረሰውም ከደረሰበትም ተምሮ ይሆናል የሚል እንጥፍጣፊ አዘኔታና ተስፋ  የነበራቸው ሰዎች ሁሉ አንቅረው እንዲተፉት ያደረገ መድረክ በመሆኑ ፤ለምን በተቀዋሚ ካባ ቀረብክ እንጂ ለምን እዛ  መድረክ ተገኘህ አንዴትስ አንዲህ ለመናገር ደፈርክ ልንለው አይቻለንም፡፡ ወያኔ የራሱ ሰዎች እየጠሉትና እየከዱት ባለበት ሰአት ህዝብ የጠላኝ እውነቱን ሳያውቅ ነው የሚለው አቶ ልደቱ ከወያኔ ጋር ይበልጥ ለመጣበቅ ይህን ያህል መሄዱ ምን ለማግኘት አስቦ ወይንም ምን ቃል ተገብቶለት አንደሆነ ወደ ፊት የሚታይ ይሆናል፡፡

ዶ/ር መረራ

ዶር መረራ የኦፌኮና የመድረክ መሪ ቢሆኑም በዛ መድረክ የተገኙት በየትኛው ፓርቲ ውክልና አንደሆነ ግን አልተነገረም፡፡ በተለይ አንደ ኦፌኮ ሊቀመንበርነታቸው በዛ መድረክ ላይ መገኘት ቦታቸው ነው ወይ የሚል ጥያቄ አንስቶ በቂ ምክንያት ካላቸው እንዲነግሩን አለበለዛም የተገኙት አለቦታቸው እንደነበር አምነው ለወደፊቱ አንዲታረሙ መንገር ያስፈልጋል፡፡ የወዳጅን ስህተት እየሸፋፈኑ ማለፍ ወይንም አትንኩት ብሎ በተከላካይነት መሰለፍ ሰውየውን ጭምር ነው የሚጎዳው፡፡

ከገዳይ አስገዳዮች ጋር በአንድ መድረክ፤

ባሳለፍነው አንድ አመት በኦሮምያ ከአንድ ሺ በላይ ሰላማዊ ዜጎች መገደላቸውን  በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ መታሰራቸውንና ለአካል ጉዳት መዳረጋቸውን ከራሳቸው ፓርቲ ሲወጡ ከነበሩ መግለጫዎች ሰምተናል፡፡ ያ አልበቃ ብሎ ሌላ ግድያ ሌላ አስር ሌላ ማሰቃየት ለመፈጸም የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ታውጇል፡፡  ለዶ/ር መረራ በአንዲህ አይነቱ መድረክ መገኘት  ግድያና እስራቱ መቆምና ያለፈው በገለልተኛ አንዲጣራ ስምምነት ላይ መደረስ ነበረበት፡፡ ነገር ግን ይህ ሊሆን ቀርቶ  የተ.መ.ደ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ጉዳዩን ለማጣራት ላቀረበው ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ ተነፍጎት ባለበት ወቅት ያውም ለህውኃት ትንሳኤ  ሊመክር በተጠራ መድረክ የዶ/ር መረራ መገኘት ምን ለመፈየድ ነው?  ሺዎች ኦሮሞዎችን ከገደሉና ካስገደሉ ሰዎች ጋርስ ምሳ አብረው መብላታቸውን   በመገናኛ ብዙሀን መናገራቸውስ ምግቡ እንዴት ቢዋጠላቸው ነው?  ይሄ መቼም ዲፕሎማሲም ዴሞክራሲም ሊባል የሚችል አይመስለኝም፡፡

ጥያቄአችን የሥርዓት ለውጥ ነው፡፡

የሥርዓት ለውጥ እየጠየቀ ያለውን  የህዝብ ትግል የዶ/ር መረራ ፓርቲ  ባይመራውም  እወክለዋለሁ የሚለው ሕዝብ ጥያቄ ነውና መደገፉ ግድ ነው፡፡ የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ ወያኔ በሥልጣን ላይ እያለ የሥርዓት ለውጥ ተግባራዊ የሚሆንበት መንገድም ዘዴም አለ ካላሉ በስተቀር  ከሥልጣን መልቀቅ የሚጠይቅ ነው፡፡ ታዲያ የሥርዓት ለውጥ እየጠየቁ ለወያኔ እድሜ ማራዘሚያ መድሀኒት ፍለጋ በተጠራ መድረክ ላይ መገኘት ምን ይሉታል ?

ወያኔ አፍ አንጂ ጆሮ የለውም

ዶ/ር መረራ ከሚታወቁባቸው ንግግሮች አንዱ ወያኔ አፍ አንጂ ጆሮ የለውም የሚለው ነው፡፡ ታዲያ ወያኔ የሚናገር አንጂ የሚሰማ ካልሆነ ርሳቸው በዛ መድረክ የተገኙት ወያኔን ለመስማት ነው? ወይንስ በራሱ መድረክ ሲሆን ጆሮ ይኖረዋል ብለው ወይንም የህዝቡ ቁጣ ጆሮ እንዲኖረው አድርጎታል ብለው አምነው ለጥገናዊ ለውጡ ሀሳብ ለመለገስ፡፡ ከላይ ባነሳኋቸውም ሆነ በሌሎች ምክንያቶች የዶ/ር መረራ በፋና መድረክ መገኘትን  ተገቢ የሚያደርግ ምክንያት አላገኘሁምና  አለቦታቸው ነው የተገኙት እላለሁ፡፡ ምክንያት ካላቸው ማስረዳት ከሌላቸው ደግሞ ነገም ሚሆነው አይታወቅምና ተመሳሳይ ነገር በመስራት ለወያኔ ምርኩዝ የሚሆንና ትግሉን የሚጎዳ ተግባር ከመፈጸም ሊታቀቡ ይገባል፡፡ አናለባብስ!

ኢ/ር ይልቃል ጌትነት

ሰማያዊ ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤ አካሂጄ የሊቀመንበር ለውጥ አደርጌአለሁ ማለቱን ሰምተናልና ኢ/ር ይልቃልን በሚመለከት የሚነሳው  የመጀመሪያ ጥያቄ ማንን ወክሎ ነው የተገኘው የሚለው ነው፡፡ ሁለተኛው ብዙ መድረኮችን አልገኝም እያለ መሰረዙን እናውቃለንና ዛሬ ምን ተገኘ የሚል ሲሆን ሶስተኛው በዛ ቦታ መገኘነቱ በተለያየ ግዜና መድረክ ሲናገራቸው ከነበሩትና የፓርቲው አቋሞች ናቸው ብለን ከተቀበልናቸው ጉዳዮች ጋር የሚቃረን መሆኑ ነው፡፡ ጥቂቶቹን አንይ፡፡

ትግሉ የነጻነት ነው፤

በምርጫ 2007 ሰሞን ትግሉ የነጻነት ነው እያለ ሲናገር ሰምተናል፡፡ ይህንኑ አቋሙን በማጠናከርም ካናዳ በሄደበት ወቅት የምርጫ ፖለቲካ አብቅቶለታል ሲል ተናግሯል፡፡ እነዚህም ሆኑ  ሌሎች  ንግግሮቹ የሚያሳዩት የሥርዓት ለውጥ ያስፈልጋል የሚል እምነት አንዳለው ነው፡፡ ወያኔ በስልጣን ላይ እያለ ነጻነትን የሚያቀዳጅ የሥርዓት ለውጥ የሚገኝበትን ዘዴም ሆነ መንገድ  የነገረንም ሆነ ያሳየን የለምና በእስካሁን ግንዛቤአችን የምንረዳው እነ ይልቃል የሥርዓት ለውጥ ሲሉ ወያኔ ስልጣን መልቀቅ/ መወገድ አለበት እያሉ አንደሆነ ነው፡፡  ታዲያ ኢ/ር ይልቃል ለመገናኛ ብዙኃን ፍጆታ የሚናገረውና የሚያምነው የተለያየ ካልሆነ በስተቀር  የወያኔን እድሜ ለማራዘም መድሀኒት ፍለጋ በተጠራ መድረክ ላይ መገኘቱ ምን ለማትረፍ አንደሆነ ግልጽ አይደለምና ምክንያት ካለው ማስረዳት ካልሆነም ዳግም መሰል ድርጊት አንዳይፈጽም በተለይ ወዳጁ አድናቂው ተከታዩ ወዘተ ነን የምትሉ ልትመክሩትም ልትገስጹትም ይገባል፡፡ህዝብ አንዴ አንቅሮ ከተፋ መመለሻ የለም፡፡

ወያኔ የሥልጣን እድሜውን ለማራዘም ይጠቅማል እስካለ ድረስ መድረክ መጋበዝ አይደለም ትንሽ ትንሽ ሥልጣን እስከመስጠት ሊሄድ ይችላል፡፡ በዚህ ወቅት እየተንገዳገደ ያለውን ወያኔ ተጋግዞ ከመግፋት ይልቅ በየግል ፍላጎት ምክንያት በወያኔ ድርጊት እየተታለሉም ሆነ እየማለሉ ጥያቄውን በመመለስም ሆነ ስጦታውን በመቀበል ምርኩዝ መሆን የኢትዮጵያ  ህዝብ በባርነት አንዲኖር ተባባሪ መሆን ነውና ያስጠይቃል፡፡ ስለሆነም ወያኔ ከዚህ በኋላም ብዙ ነገር ሊያደርግ መቻሉን ታሳቢ በማድረግ  ህዝብ በደሙ ያቀለመውን ትግል ማገዙ ቢቀር አንዲኮላሽ ተባባሪ ከመሆን መቆጠብ ይገባል፡፡  ላለፈው ክረምት ቤት ባይሰራም ለመጪው ማሰብ ግን ተገቢ ነው፡፡

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.