የጀግኖች አባቶችህን ደም አርክሰህ ኢትዮጵያዊነትክን ክደህ ነጻነት የለም [ሰርጸ ደስታ]

ethiopia-675-satenaw-newsብዙ በኢትዮጵያ ምድር ዛሬ እየኖራው ያለው ሕዝብ በወያኔና አጋሮቹ ሞገሱና ክብሩ ኃይሉም የሆነውን ኢትዮጵያዊነቱን ስለዘነጋ ወይም ከሙሉው ስላጎደለው አቅመ ቢስ ሆኖ የባንዳ ልጆች መጫወቻ ሆኗል፡፡ በተለይም ደግሞ የኦሮምኛ ተናጋሪው ሕዝብ የራሱን አኩሪ የኢትዮጵያዊነቱን ክብሩን በባንዳ ልጆች ጥሎ እንደባዘነና አቅም የለሽ እንደሆነ ብዙ ጊዜ በቁጭት አንስቼዋለሁ፡፡ አሁንም ገና ብዙ ይቀረዋል፡፡ ማንም ማንን ዛሬ አይለማመጥም፡፡ በሌላ በኩል እስከዛሬ በኢትዮጵያዊነት ብቻ ይታወቅ የነበረው አማራ የተባለውም ሕዝብ አሁን ላይ በአማራ ብሔረተኝነት እየተቀየረ መሁኑን እናያለን፡፡ በእርግጥም አማራ የተባለው ሕዝብ ያለ ሐጥያቱ በሁሉም ማለት ይቻላል ሐጥያተኛ እንዲሆንና ሁሉም አይንህ ላፈር ሲለው 25 ዓመት ታግሶ አሁን ያመረረ ይመስላል፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ ነጻነት በሚል ለዘመናት እየታገለ ቢመስልም ውጤቱ ግን የኋልዮሽ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ ይህን ታላቅ ሕዝብ ከማንነቱ ለማምከን ብዙዎች ከየአቅጣጫው በጥንቃቄ ነበር የዘመቱበት፡፡ ከኃይለስላሴ ዘመን ጀምሮ ይህ ሕዝብ ኢላማ ቢሆንም በወያኔና የኦሮሞ ነን በሚሉ እንደነ ኦነግና የመሳሰሉት ድርጅቶች ለአለፉት 25 ዓመታት ፍጹም ከኢትዮጵያዊነቱ እንዲመክንና አቅመቢስ ሆኖ እነሱ እነዳሰኛቸው እንዲዘውሩት በሰፊው ሲሰራበት ኖሯል፡፡ ዓለም ሳይቀር በአድናቆት የሚያነበውን የጀግኖች አባቶቹን ታሪክና ደም አርክሶ አእምሮውን ለማምከንና ከአባቶቹ ታሪክ ለመነጠል በጥንቃቄ ጠላቶቹ የጻፉለትን እንደነ የቡርቃው ዝምታ የመሳሰሉ አፈታሪኮችን አሜን ብሎ ተቀብሏል፡፡ ዝናቸው አለምን ያስደመሙ ጀግኖች አባቶቹ ትዝ አይሉትም፡፡ ማንነታቸውን በጭላንጭል የሚነገር አንዳነዶቹም ከነጭርሱ ምናባዊ በሆኖ ራሱ የፈጠራቸው “ጀግኖች” በሚል ያመልካቸዋል፡፡ በጀግንት ማማ ላይ ያሉ አባቶቻችንን ለአንድ አፍታ እናስታውስ፡፡ እስኪ ጀግና ከሌላ ብሔር ይዋጣ ኢትዮጵያ ጀግኖቼ ብላ የምትዘክራቸው አብዛኞቹ ከየት ናቸው? የኦሮሞ ሕዝብ ይህንን በደንብ እንዳይረዳ ነው ትልቁ የወያኔና አጋሮቹ ጥንቃቄ፡፡ ይህ ለኦሮሞ ሕዝብ ግልጽ ከሆነለት ማንም ሊያቆመው የማይችል ኃይል አለው፡፡ ኢትዮጵያም የኔ ታሪኳም የኔ ብሎ ካመነ ማንም ሊያዎመው እንደማይችል ጠላቶቹ ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡ ለዛም ነው የኦሮሞ ጀግኖች ማንነታቸውን በክቡር ደማቸው የጻፉትን የታላቁን የሚኒሊክን ታሪክ ከታሪክ ሁሉ ነጥሎ ልዩ በጥላቻ ስብከት ያንን ታሪክ የኦሮሞ ሕዝብ እንዲጠላው የተደረገው፡፡ ወያኔም ኦነግም ሌሎችም ልዩ ሴራ ያላቸው ኦሮሞ ነን በሚል የሚንቀሳቀሱ ብዙዎች ያ ታሪክ የኦሮሞ ሆኖ ከቀጠለ አደጋ እንደሆነ ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡

ታላቁን ጎበናን ማንም አፍ ማሟሻ ሲያደርገው ይሄንኑ አው ብሎ ህዝብም ሲቀበለው ነው የኦሮሞ ሕዝብ ማንነቱን ያጣው፡፡ ሚኒሊክ አማራ የተባለው ብሔር ቢባልም በዘመኑ ሁሉ ዋና ተባባሪዎቹና የመንግስቱም ዋና ተዋናይ የኦሮሞ ልጆች የሆኑበትን አገሪቱ በአኩሪነቱ ልዩ የጀግንነትና የልማት ስኬት ዘመን የራሱ መሆኑን ክዶ ይህን ታላቅ የክብሩን ዘመን በረገመ ጊዜ ነው የኦሮሞ ሕዝብ የተዋረደው፡፡ አስተዋይ አእምሮ ይኑረን፡፡ ለመሆኑ ወያኔን የሚኒሊክ ታሪክ ለምን ያሰበረግገዋል? እነ ኦነግስ ለምን ያንን ታሪክ ከኦሮሞ ሕዝብ ታሪክ እነዳይሆን ዘመቱበት?  አኖሌ፣ ጨለንቆ ሌላም ጦርነት? አይደለም!! የዚህ ታሪክ ኢላማ መደረግ ዋናው ምክነያት የኦሮሞን ሕዝብ ከኢትዮጵያ የታሪክ ባለቤትነት ለማምከን፣  ወያኔና አጋሮቹ እንደ ጦር ከሚያስፈራቸው አማራ ከሚባለው ሕዝብ ጋር የኦሮሞን ሕዝብ ለማለያየት እንደሆነ አስተውለናል? እናማ እስኪ የሚኒሊክን ታሪክና የስልጣን ባለቤቶች እንይ፡፡ ነጻነት ሁሉ ለሚፈልጉ ምሳሌ የሆነው የአደዋው ድል የማን ነው?የትግሬ ነው የኦሮሞ? ከትግሬ እሱም ከተንቤን የሆነው ከአሉላ በቀር ማን እዛ ቦታ ተሰለፈ ራስ መነገሻ ቢሰለፍ የሚያስተዳድረው ስለሆነ ነው፡፡ ይልቁንም በብዛት የምናውቀው ብዙ ትግሬዎች በባንዳነት ተቀጥረው ለጠላት ያገለግሉ እንደነበር ነው፡፡ በመሪነት ቦታ የነበሩ እንደነ ኃይለስላሴ ጉግሳ የመሳሰሉ ትግሬዎች ሳይቀሩ ጣሊያነን በባንዳነት ሲያገለግሉ የነበሩ ናቸው፡፡እስኪ ከኦሮሞ ልጆች እንቁጠር፡- ራስ ጎበና ዳጬ(ተዋጠልህ አልተዋጠልህ እውነታው ማንም እንደጎበና ጀግና የለም)፣ የሚኒሊክ የጦር አበጋዝ ፊትአውራሪ ገበየሁ ጎራ፣ ደጃዝማች ባልቻ አባነብሶ፣ ራስ አሊ(ሚካኤል-የጁ)፣ የሚኒሊክ አጎት ራስ መኮንን ወልደሚካኤል ጉዲና፣ ፊታውራሪ ሐበተጊዮረጊስ ዲነግዴ፣ ከኋለኞቹ ደጃዝማች ገረሱ ዱኬ፣ ዛሬም በሕየወት ያሉት ጀነራል ጃጋማ ኬሎ፣ በጠላት አገር አለምን ጉድ ያሰኘ ታሪክ የፈጸማ የነጆው አብዲሳ አጋ….. ወዘተ፡፡  ዛሬ የባንዳ ልጆች እንደፈለጋቸው እንደቦይ ውሃ እንዲነዱት የሆነው የአባቶቹን አኩሪ ታሪክ የረገመው የቁቤ ትውልድ ወደራሱ ካልተመለሰ ወደፊትም ነጻነትን የሚያያት አይመስለኝም፡፡ አጠቃላይ የታላቁ የኦሮሞ ሕዝብ ማንነት በወያኔና ልዩ ሴራ ባላቸው ኦሮሞ ነን በሚሉ የተለያዩ ድርጅቶች ማንነቱን አጥቶ ባዝኖ ለዘመናት ቆይቷል፡፡ ሰሞኑን ትንሽ ትንሽ አባቶቹን የሚያስታውሰው ብቅብቅ እያለ ቢሆንም አሁንም ገና ብዙ መንገድ ይቀረዋል፡፡ መሪዎቹን በውል ለይቶ አላወቀም፡፡ እንደ እምነቱ የሚያየው ኦነግ ለወያኔ ለእርድ እየዳረገው ያለው እሱ እንደሆነ አልተረዳም፡፡ ኦነግና ወያኔ አላማቸው አንድ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ማፈራረስ፡፡ የኦነግን ፖለቲካ መሪዎች ስናይ አብዛኛውዎቹ ከሕዝብ ጋር ሳይሆን ሀይማኖታዊ ሴራቸውን በሐበሻ ምድር ለማሳካት እንቅልፍ ያጡ ናቸው፡፡ ወያኔ ይሄንን ቡድን ይፈልገዋል፡፡ ምን አልባትም ለኦነግ መሪዎች ከወያኔ ገንዘብ እንደሚሰጥ አንዳንድ ምልክቶች ይጠቁማሉ፡፡ የኦሮሞን ልጅ ለመግደል ኦነግ የሚል ታርጋ ይለጠፍበታል፡፡ የኦነግ መሪዎች ግን ከኢትዮጵያ በተዘረፈ የወያኔ ገንዘብ በአውሮፓና አሜሪካ ይኖራሉ፡፡ ኦሮሞን ከኢትዮጵያዊነቱና ከታሪኩ ለመለየት ምን የላደረጉት አላቸው?

ሌላው ከታሪኩም ጋር በተያያዘ የኦሮሞን ሕዝብ እንዲሁም ሌሎችን አማራ ከሚባለውና  የትግሬው ዘር ለመለየት ሐበሻና ሌላ ተብሏል፡፡ ለመሆኑ ሐበሻ ማን ነው? ያልሆነውስ? ኢትዮጵያ ከመሠረቱም የሐበሻ አገር ነች፡፡ ለመሆኑ ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ አሮምኛ የሚናገረው ሕዝብ መሠረቱ የት ነበር? መዳ ወላቡ? መዳ ወላቡን መሠረቴ ነው የሚል ትወልድ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ዘመናትን ከኖረው ሕዝብ ጋር እኩል ሊሆን አይችልም፡፡ የኦሮሞን ሕዝብ ከመዳወላቡ መጣ የሚሉ አሁንም ለሴራቸው እንዲያመች እንጂ ዛሬ ኦሮምኛ የሚናገረው ሕዝብ በአብዛኛው ከነጭርሱ አሮምኛም ተናጋሪ እንዳልነበረ ጠንቅቀን እናውቀዋለን፡፡ በሸዋና ከፊል ምዕራብ ኢትዮጵያ የሚኖረው ኦሮምኛ ተናጋሪ ከነጭርሱ የነገስታት ዘር ከሚባሉት ቀደምት የአቢሲኒያ መሪዎች ነው፡፡ ማስተዋል የጠፋው ትውልድ ሆኖ እንጂ ዛሬም ድረስ የሚታይ እውነተኛ ምስክር ነው፡፡ ኢትዮጵያ እስከ ኬንያ ድንበር ያለው ሕዝቧ ሀበሻ ነው፡፡ በቀደምት ታሪክ አካባቢውን ከሚያስተዳድሩ የአቢሲኒያውያን ልጆች እንጂ ሌላ አይደለም፡፡  በተዛባ መልኩ ከመዳ ወላቡ ወደ ሰሜን መጣ የተባለው የአሮምኛ ተናጋሪ ሕዝብም ቢሆን መሠረቱ ሰሜን እንጂ መዳወላቡም ማዳጋስካርም አደለም፡፡ ዛሬ በወሎና ትግራይ ኦሮምኛ የሚናገረው ሕዝብ ከመዳወላቡ ወደ ሰሜን የሄደው አደለም፡፡ ይልቁንም ከሰሜን ወደ ደቡብ በሚንቀሳቀስበት ወቅት በዛው የቀረ እንጂ፡፡  የባንዳዎቹ ልጆች የሄንን እውነት እንዳይረዳው ነበር ጥንቃቄ አድርገው በኦሮሞ ሕዝብ ላይ የዘመቱት፡፡ ሚኒሊክ ኢትዮጵያን የከለሉበት ድንበር በዘፈቀደ ያደረሳቸው ድረስ ለመከለል ሳይሆን በትክክልም ከጥንታዊቷ አቢሲኒያ ሕዝቦች ጋር የተያያዘውን ብቻ ነው፡፡

አሁንም እላለሁ የኦሮሞ ሕዝብ ወደማንነት ክብሩ ለመመለስ ቆም ብሎ ማሰብን ይጠይቀዋል፡፡ ኦሮምያ የሚባል አገር የለም፡፡ ትኩረቴ በዚህ ሕዝብ ላይ የሆነው ለአገሪቱ ነጻ መውጣት የዚህ ሕዝብ ወደ ትክክለኛ ማንነቱ መመለስና የታሪኩም የአገሩም ባለቤት መሆን ቁልፍ ጉዳይ እንደሆነ ስለምረዳ ነው፡፡ ወያኔንና አጋሮቹን ከምንም በላይ ይሄ ያስፈራቸዋል፡፡ ዛሬ በሥሙ የሚንቀሳቀሱት ግን ዓላማቸው ኦሮምያ የሚባልን አገር መመሥረት እንደሆነ አውቀናል፡፡ ብዙ ጊዜ ሲያምታቱ አንዴ ወዴት እንገነጠላለን ግንድ ወዴት ይሄዳል ሌላ ጊዜ ደግሞ አሮምያ ለኦሮመዎች ምናምን ሲሉ ቆይተዋል፡፡ ኦሮሞም ሆነ ሌላው ያለ ኢትዮጵያዊ ማንነቱ መኖር የሚችል ሕዝብ አይደለም፡፡ አንድ ያደረገው ኢትዮጵያዊነቱ እንጂ ባነዳዎቹና ጠላቶቹ እንደሚያወሩለት አደለም፡፡ ሲጀምር ዛሬ ኦሮሞ የሆነው ሕዝብ አብዛኛው ሌላ ሕዝብ ነበር፡፡ ዛሬ ኦሮምያ የሚባለው የአገሪቱ ክፍልም ቀድመው ይኖሩበት የነበሩ የአገሩ ባለቤቶች ኦሮምኛ ተናጋሪ አልነበሩም፡፡ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ሱማሌን ጨምሮ በቋንቋ እንጂ በደም አንድ ሕዝብ እንደሆነ ከታች ባስቀመጥኩት ሊነክ ላይ የሚገኘውን የሳይንስ ጥናት መረዳት ከቻላችሁ አንብቡ፡፡ ሐበሻ ማን ነው? ሐበሻስ ያልሆነስ? ዛሬ ማንንም ማን አይለማመጥም ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ ነው፡፡ ለባነዳዎች ሴራ የተመችን ታሪክ እያራገቡ ሕዝብን ከማንነቱ ለማምከንና አቅም እንዳይኖረው ለሚያሴሩ መልሳችን ኢትዮጵያዊቴ ከምንም በላይ ማንነቴ ነው ልንል ይገባል፡፡ ይህ ባልሆነበት ብዙ ሌላ ፈተና አለብን፡፡ የኦሮሞን ፖለቲካ የአረብና የጣሊያን ባንዳዎች ሊመሩት አይገባም፡፡ ለሁሉም ከኢትዮጵያዊነቱ ውጭ አማራጩ ምንድነው?

እስከዛሬ አማራ የሚባለው የኢትዮጵያ አንድነት አቀንቃኝ ነበር፡፡ ዛሬ እሱም አማራነቴን ብቻ እያለ ነው፡፡ ሌሎችስ ትንንሾቹ ያለ ኢትዮጵያ ሕልውና ወደፊት እንዴት ልትኖሩ ታስባላችሁ፡፡ አሁን ኢትዮጵያዊነትን ማጥበቅ የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ እንጂ በዘፈቀደ እንዳለፍንበት ዘመን በየጎጣችን የምናቅራራበት ጉዳይ አይደለም፡፡ ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ ነው፡፡ የበጎ የታሪክ ባለውለታዎቻችንን እረግመናልና ብዙ እዳ እንዳይሆንብን፡፡ በቅርብ በዲላ በጎራጌ ማሕበረሰብ ላይ የተፈጸመው አደጋ ያለ ኢትዮጵያ ምን ሊሆን እንደሚችል አስቡት፡፡  ያለ ኢትዮጵያ እንኳንስ ትንንሾቹ ክልሎች ትልልቆቹም አመት ሳይሞላ ብትንትናቸው እንድሚወጣ ግልጽ ነው፡፡ በመገፋት ብዛት ሊሆን ይችላል፣ አሁን ያለው በአማራ ብሔረተኝነት የተጀመረው እንቅስቃሴ አደገኛ እንደሆነ ብዙዎች አላስተዋሉም፡፡ በኢትዮጵያ አንድነት አቀነቃኝነት አይንህ ላፈር እንዳለተባለ አሁን እኔም እራሴን ላድን ከዚያም በላይ ራሴን ችይ አገር እሆናለሁ እያለ የተነሳ ትውልድ አለ፡፡  ለብዙዎች የዚህ ቡድን እንቅስቃሴ የተገለጸላቸው አይደለም፡፡ በዚህ ሕዝብ ያልተለመደ አዲስ የሆነ ነው፡፡ ቡድኑ ሕዝብን ለማሳመን በሰፊው እየሰራ መሆኑ ብቻም ሳይሆን በእርግጥም ብዙ ሕዝብ ለዚህ አስተሳሰብ እየተገዛ ነው፡፡ በኢትዮጵያዊነት ላይ ያን ያህል ጥላቻ አለው ባልልም እየቆየ እቅዶቹን ማሳካት ሲጀምር መገንጠልን ዓላማዬ ማለቱ አይቀሬ ነው፡፡ የአማራ ሕዝብ ለኢትዮጵያ አንድነት መሪ ተዋናይ እንዳልሆነ አሁን በዚህ ቡድን ፍልስፍና እንደሚጠለፍ ሁኔታዎች ግልጽ ሆነው ይታያሉ፡፡ የቡድኑም አካሂድ እስከዛሬ ከምናውቃቸው ሁሉ ለየት ያለና ሚስጢራዊ መረቡ ብዙ ጫፍን በአንድ ጊዜ ያዳረሰ ነው፡፡ ሳይቃጠል በቅጠል የሚባለው አሁን ነው፡፡ ሁላችሁም ማንነታችሁን ከዚህ ሊንክ ላይ እንብቡት http://www.cell.com/ajhg/abstract/S0002-9297(12)00271-6

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!

አሜን!

ሰርጸ ደስታ

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.