ወያኔን በመቃወም ኢትዮጵያውያን በጀርመን ጎዳናዎች ለሰልፍ ወጡ [ዘርይሁን ሹመቴ]

ለተጠናከረው  ዘገባ ዘርይሁን ሹመቴ ከጀርመን

german-demoወያኔንን  በምእራብያውያን  ዘንድ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ጫና ውስጥ እንዲገባ እያደረጉ የሚገኙ በጀርመን አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አምባገነናዊውን የወያኔን ስርአት በመቃወም ቩዝበርግ (Würzburg) በምትባል የጀርመን ከተማ በ12 ጥቅምት 2009ዓም(22 October 2016) ዳግም ወደ አደባባይ ወጥተዋል። ለአርንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራችን ብለው በየቀኑ በአጋዚ ጦር በሚሰቀጥጥና ግፍ በተሞላበት አረመናዊ  ግድያ  ውድ ህይወታቸው እየተሰዋ  የሚገኙትን ኢትዮጵያውያን በማሰብ በአንጻሩ ከፋፋይ ወያኔን በማውገዝ ይህንን የተቋውሞ ሰልፍ አካሂደዋል። አባቶቻችን ለጦርነት የተከለከለ ኬሚካልና  መርዝ ከአውሮፕላን  እየተደፋባቸው ፣ እነርሱ ከያዙት መሳሪያ እጅግ  የረቀቀ ጦር  ከታጠቀ ቀኝ  ገዢ ጋር ተፋልመው  በነጻነት ያወረሱንን  ኢትዮጵያ አገራችንን ወያኔ ከቀኝ  ገዢ በባሰ  ሁኔታ   በመዝረፍ፣ በህዝባችን ላይ  የባርነት ቀምበር በመጣል ከዛም አልፎ በአሰቃቂ መንገድ እየገደለ ለ25 ዓመታት ቆይቷል። በነጻነት እንድኖር  በተሰጠኝ አገሬ ላይ ለባርነት አልገዛም በማለት ውድ የኢትዮጵያ ህዝብ ለወያኔ  አምባገነኖች አምቢ  በማለት እየተዋደቀ ይገኛል። ኢትዮጵያን  ከወያኔ  የባርነት ግዞት ነጻ ለማውጣት በሚደረገው ትግል  በጀርመን  የሚገኙ ኢትዮጵያውያን  ወያኔ አጋሬ ብሎ ከሚመካባችው አውሮፓውያን ጋር ያለውን ግንኙነት እንዲሻክር እንዲሁም ጫና ውስጥ በማስገባት ከአውሮፓውያኑ  የሚለገሰውን የገንዘብና የቁሳቁስ ምጽዋት እንዲቋረጥበት በማድረግ የትግሉ አካል መሆናቸውን  በተደጋጋሚ እያሳዩ  ይገኛሉ።

በጀርመን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ የተቋውሞ እንቅስቃሴዎች የጀርመን መንግስት ከወያኔ ጋር ያለውን ፖለቲካዊ ሆነ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶችን ድጋሜ እንዲያጤነው ለማስደረግ እየጣሩ ይገኛሉ። ካንስለር  አንጌላ መርክል (Chancellor Dr. Angela  Merkel)  በጀርመን መንግስት  ወጪ በአዲስ አበባ የተገነባውን አዲሱን የሰላምና የደህንነት ህንጻ  ለማስመረቅ ባደረጉት የኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ወያኔን ከመወረፍ አልፈው ለተቃዋሚዎች ድጋፋቸውን መስጠታቸው በዚሁ በጀርመን አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ንቁ ተሳትፎና  የተቋውሞ  እንቅስቃሴዎች  ውጤት ነው። በተጨማሪም ካንስለር አንጌላ መርክል በወያኔ ባለስልጣናት የቀረበላቸውን በፓርላማ ውስጥ ንግግር የማድረግ ግብዣን በመናቅ  ተቃዋሚ በሌለበትና አምባገነንነት በሰፈነበት በእንደዚህ ባለው ፓርላማ ውስጥ  ንግግር አላደርግም በማለት ወያኔን ያሳፈሩት ኢትዮጵያውያን በበርሊን በፍራንክፈርት በሙኒክ በቩዝቡርግ በኑረንበርግ እና  በተለያዩ  ከተሞች ወደ አደባባይ በመውጣት ወያኔን በማሳጣታቸውና  የሚፈጽመውን የመብት ጥሰት ለማጋለጥ በመቻላቸው ነው። በዚህ አገር የሚገኙ የኢትዮጵያ የሲቪክ ማህበራት የእምነት ተቋውማት የሰብአዊ መብት ተከራካሪዎች እንዲሁም የፖለቲካ  ድርጅቶች በሃይለማርያም ቁንጮነት የሚመራው የወያኔ ስርአት  የሚፈጽማቸውን የዘር ማጥፋት፣ እስራት፣ አፈና ፣ ጭቆናና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በማጠናቀርና በመረጃ በማስደገፍ የጀርመን መንግስት ለወያኔ የሚያደርገውን ማንኛውንም አይነት ድጋፍ እንዲያጤነው በይበልጥም  እንዲያቋርጥ ያላሰለሰ  ጥረቶች እያደረጉ ይገኛሉ። በ12 ጥቅምት 2009ዓም የተደረገው ወያኔን የመቃወም ስልፍ የተዘጋጀውና የተጠራው በነዚሁ ተቁዋማት እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል።

ወልቃይት የአማራ እንጂ የወያኔ ሆኖ አያውቅም፣ ሞት ለወያኔ ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ፣  አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ፣ ኮሎኔል ደመቀ ፣ አቶ በቀለ ገርባ ይፈቱ ፣ በአማራ በጋምቤላ በኦሮምያ በኮንሶ የሚፈሰው  ደም የኛው  ደም ነው እንዲሁም ሌሎች መፈክሮችን ሰልፈኞቹ ሲያሰሙ አርፍደውል። በተጨማሪም በጀርመንኛና በእንግሊዘኛ ወያኔ ገዳይ ፣ አምባገነን እንዲሁም አሸባሪ እንደሆነ ሰልፉን  በቩዝበርግ ከተማ ጎዳናዎች በትእይንት ለሚመለከቱት የጀርመንና የውጭ ዜጎች በራሪ ወረቀቶችን በማደልና  መፈክሮችን በማሰማት ለማስረዳትና ለማሳወቅ ተችሏል።  የጀርመን መንግስት  ከወያኔ ጋር ምንም አይነት ትብብር ማድረግ አቁሞ ከተጨቆኑት ነገር ግን በነጻነት ተጠብቃ የቆየችውን ኢትዮጵያን ከ25 ዓመታት የወያኔ የባርነት  አገዛዝ ለማላቀቅ እየተጋደሉና እየተዋደቁ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጎን እንዲቆም ሰልፈኞቹ አጽንኦ በመስጠት ጠይቀዋል። ክቡር የነጻነታችን አርማ የሆነችውን አርንጋዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራችንን በአገራችን  ኢትዮጵያ ዳግም ከፍ ብላ እንድትውለበለብ በየቀኑ ከጎጠኛው ወያኔ ጋር አንገት ለአንገት ተናንቀው እየተፋለሙ የሚገኙትን  ጀግና ኢትዮጵያውያንን እስከ ድል ድረስ ለመደገፍ በተለያዩ የጀርመንና  የአውሮፓ ከተሞች ተመሳሳይ ጥሪዎችና የተቋውሞ  እንቅስቃሴዎች እንደሚደረጉም በሰልፉ ማጠናቀቂያ  ላይ ተገልጿል።

By Zerihun Shumete/ from Germany

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.