አንድነት የ2007 ዓ.ም ምርጫን እንደሚሳተፍ አሳወቀ

• ከህዳር 14 -20/2007 የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ ጠርቷል

አንድነት ለዴሞክራሲያዊና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) መጭውን 5ኛ ሀገራዊ ምርጫ እንደሚሳተፍ አሳወቀ፡፡ ፓርቲው ዛሬ ህዳር 11/2007 ዓ.ም በዋናው ጽፈት ቤቱ ‹‹ምርጫ ሲባል አማራጭ ሳያሳጡ መሆን አለበት›› በሚል በሰጠው መግለጫ ገዥው ፓርቲ ቀጣዩን ምርጫ በስፋት ለፕሮፖጋንዳ መጠቀሚያነት እያዋለው እንደሆነ፣ ከአሁን ቀደም የተካሄዱት ምርጫዎች ለመድብለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታ አስተዋጽኦ አለማድረጋቸውን፣ ከዚህ ይልቅ ገዥው ፓርቲና መንግስት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች በመሆናቸው አንድ አውራ ፓርቲ ለመመስረት እየጣሩ በመሆኑ ምርጫን አማራጭ አልባ ማድረጋቸውን አትቷል፡፡

በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች የአንድነት አባላት ላይ ዘመቻ በሚባል መልኩ አፈና እና እስር እየተፈጸመባቸው መሆኑን ያስታወሰው መግለጫው ይህ የገዥው ፓርቲ ተግባር ተቃዋሚዎችን በማዳከም ከምርጫው ውጭ ለማድረግ ያለመና ዴሞክራሲያዊ የሆነ ስርዓት እንዲመሰረት ፍላጎት እንደሌለው የሚያሳይ ነው ሲል ወቅሷል፡፡

‹‹በስርዓቱ በኩል ነጻና ፍትሐዊ ምርጫ እንዳይካሄድ የተለያዩ ጫናዎች እየተደረጉ የሚካሄዱ ምርጫዎች ሁሉ ትርጉም አልባ እየሆኑ ይገኛሉ›› ያለው መግለጫው ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም የሚደረገው ምርጫም በመንግስት በኩል የመድብለ ፓርቲን ስርዓት ለማጎልበት ምንም አይነት ምቹ ሁኔታ እንዳይፈጠር ከአሁኑ የተለያዩ እንቅፋቶችን በመደርደር ላይ ነው ብሏል፡፡ የአንድነት አመራሮችና አባላትን በገፍ በማሰር ፓርቲው ከፍተኛ ጫና እየተደረገበት ነው ያለው መግለጫው፣ ሆኖም አንድነት ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ሆኖ ህዝብን በመቀስቀስና በማበረታታት የተዘጋውን በር ለማስከፈት እንደሚሰራ እምነቱን ገልጾአል፡፡

‹‹በእኛ በኩል ደጋፊዎቻችን በመራጭነት እዲመዘገቡ ከማበረታታት ጀምሮ የህዝብና የፓርቲ ታዛቢ በመሆን የምርጫ ሂደቱን በሙሉ በንቃት እንዲከታተልና እንዲሳተፍ የበኩላችን ጥረት በማድረግ የ2007 ዓ.ም ሀገራዊ ምርጫ ህዝባዊ እንዲሆን ትግላችን እንቀጥላለን›› ሲል ምርጫውን ለመሳተፍ መወሰኑን ገልጾአል፡፡

በመግለጫው ገዥው ፓርቲ ለመድብለ ፓርቲ ግንባታ ዝግጁ እንዳልሆነ እና አፈናው እንደተባባሰ እየገለጻችሁ እንዴት ከአሁኑ ምርጫውን ለመሳተፍ ወሰናችሁ በሚል ለቀረበው ጥያቄ የፓርቲው ምክትል ፕሬዝደንት አቶ ግርማ ሰይፉ ‹‹የተዘጋውን ምህዳር ማስከፈት የሚቻለው የኢትዮጵያን ህዝብ በሰላማዊ ትግል በማሳተፍ ነው፡፡ ምርጫ ደግሞ አንዱ የሰላማዊ ትግል ስልት ነው፡፡ ይህን ስለምናምን ነው በምርጫው ለመሳተፍ የወሰንነው፡፡ ይህን ስንል ግን የፖለቲካ ምህዳሩ ምቹ ነው እያልን አይደለም›› ብሏል፡፡

አቶ ግርማ የ9ኙ ፓርቲዎችን ትብብር ለምን እንዳልፈረሙ ለተነሳላቸው ጥያቄም ‹‹ከመድረክ የወጣነው በቅርቡ ነው፡፡ በመሆኑም ከመድረክ ጋር ከነበረን ትብብር ወጥተን ከሌላ ትብብር ዘለን መግባት የለብንም በሚል ጥናት እየተደረገበት ነው፡፡ በጥናቱ ከታመነበት እንፈርማለን፡፡ ባንፈርምም አብረን አንሰራም ማለት አይደለም›› ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል አንድነት ‹‹የሚሊዮኖች ድምጽ ለህሊና እስረኞች›› በሚል ከህዳር 14 እስከ ህዳር 20 2007 ዓ.ም በማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ ማዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡ ዘመቻው ‹‹ለመንግስት ባለስልጣናት፣ ለታዋቂ ግለሰቦች፣ ለዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተቋማትና ለልዩ ልዩ የሚዲያ ድርጅቶች በኢንተርኔትና በሶሻል ሚዲያ በኩል መልክዕት በመላክ በሀገራችን ያሉትን የፖለቲካ እስረኞች ሁኔታና አያያዝ በተመለከተ መረጃ በመስጠት ተገቢ የሆነ አያያዝ እንዲኖራቸው፣ ከእስር እንዲፈቱ፣ በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉትን ማሰርና ማዋከብ እንዲቆም በመንግስት ላይ አወንታዊ ተፅዕኖ ለመፍጠር›› ያለመ እንደሆነ ተገልጾአል፡፡

UDJ-SEAL-300x296

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.