ኢትዮጵያዊ ማንነት አለ – ለኔ ኢትዮጵያዊነት ማንነቴ ነው – #ግርማ_ካሳ

ይህ ሰው ነዋሪነቱ በአዉስትራሊያ ነው። ዶክተር ነው። በኦሮሞ እንቅስቃሴ ዙሪያ ብዙ ከሚጽፉና በቀዳሚነት ከሚጠቀሱ ከነጃዋር መሐመድ፣ ፕርሮፌሰር ሕዝቄል፣ ገረሱ ቱፋ ከመሳሰሉ ምህራን መካከል የሚመደብ ነው።

ኢትዮጵያዊ ማንነት አለ – ለኔ ኢትዮጵያዊነት ማንነቴ ነው – #ግርማ_ካሳጋዜጠኛው “አሜሪካዊ፣ አዉስትራሊያዊ ሲባል ..ኢትዮጵያዊ የማይባልበት ምክንያት ምንድን ነው?” ይጠይቃል። ዶር ጸጋዬ ” የአማራ ማንነት ፣ የትግሬ ማንነት በኢትዮጵያዊ ማንነት ሥር ይንቀሳቀሳል እንጂ ። የኢትዮጵያ ማንነት ብሎ ነገር የለም” የሚል አስቂኝና ደካማ ምላሽ ይሰጣል። ከአንድ ምሁር የማይጠበቅ።

እኔ የአዲስ አበባ ልጅ ነኝ። የሽገር፣ የአዱ ገነት ….አያቶቼና ቅድመ አያቶቼን ከወሰድኩ ወደ ቦረና፣ ወደ ጂማ፣ ወደ አዳ (ወለንጪቲ) ፣ ወደ ጎጃም፣ ወደ መንዝ ..እሄዳለሁ። ቢያንስ 5/8ኛ ኦሮሞነት ዉስጤ አለ። ግን ራሴን እንደ ኦሮሞ አላይም። ራሴን እንደ አማራ አላይም። ኢትዮጵያዊነት ነው የኔ ማንነት። አቦ ተዉኛ ….. እኔ አማራ አይደለሁም። ትግሬ አይደለሁም። አማራ ሆኜ ወይም ትግሬ ሆኜ በኢትዮጵያዊነት ማንነት ሥር አልተደበኩም።

ዶር ጸጋዬ “ለኔ ኢትዮጵያዊነት ማንነቴ አይደለም” ብሎ የመናገር ሙሉ መብት አለው። ሆኖም ግን በጅምላ የኢትዮጵያዊነት ማንነት የለም ብሎ ያውም በራዲዮና በአደባባይ መናገር ጠባብነት ብቻ ሳይሆን arrogance ነው። እነ ዶር ጸጋዬና ሌሎች የፈለጉትን ይበሉ፤ እኔ ዘሬ ኢትዮጵያዊነት ነው !!!!!!አራት ነጥብ።

ሌላ ዶክተሩ ከተናገራቸው ዉስጥ አንድ ሌላ ነጥብ ላንሳ። ከሁለት ሳምንታት በኋላ በአትላንታ አንድ ኮንፍራስን እንደሚደረግ፣ ኮንፍራንሱ እንደ ሞዴል የወሰደው ደግሞ በ1955 በደቡብ አፍሪካ ኤ.ኤን.ሲ ያወጣውን ፍሪደም ቻርተር የተባለው እንደሆነ ይናገራል። በቻርተሩ ላይ የተጠቀሰ አንድ አርፍተ ነገር ይጠቅሳል። “South Africa belongs to everyone who lives in it” የሚል።

እንግዲህ ለዶር ጸጋዬና ለጓዶቹ አንድ ጥያቄ አለኝ። ታዲያ “ኦሮሚያ የኦሮሞዎች ናት” በሚል ሌላውን ማህበረሰብ በኦሮሚያ ዉስጥ እንደ እንግዳ መቁጠር ( ኬንያ እንደሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን ማለት ነው) በምን መልኩ ነው ከደቡብ አፍሪካ ፍሪደም ቻርተር ጋር ሊገናኝ የሚችለው ?የደቡብ አፍሪካ ፍሪደም ቻርተር አፓርታይድን፣ ዘረኝነት ለመታገል ነው የተጻፈው። ሆኖም ግን በአትላንታ ኮንፍራንስ አዘጋጆች ከሚባሉ መካከል ምንሰማው በኦሮሚያ ሌላውን ያገለለ፣ የገፈተረ፣ አፋን ኦሮሞ ብቻ የሚነገርበት፣ ኦሮሞዎች በኦሮሞነታቸው የክልሉ ብቸኛ ባለቤት ሆነው እንዲቀጥሉ የሚያደረግ አመለካከት እንዳላቸው ነው። ለምን ዶር ጸጋዬና የኦሮሞ አክቲቪስቶች “South Africa belongs to everyone who lives in it” እንደተባለው “The Oromia region belongs to everyone who lives in it” የሚል አቋም መያዝ ከበዳቸው ? በኦሮሚያ ከአፋን ኦሮሞ ጋር አማርኛም የሥራ ቋንቋ እንዳይሆን ለምን ይከራከራሉ ? እነርሱ ከዚህ በፊት አማርኛ ተጫነበን እያሉ ያማረሩትን፣ ለምን በሌላው ላይ ኦፋን ኦሮሞን በግድ ለመጫን ይሞክራሉ ? ( reverse discrimination) በአዳማ ናዝሬት ለምሳሌ ከ85% በላይ ነዋሪዎች ኦሮምኛ ተናጋሪ አይደሉም ። በጂማ ከ60% በላይ። ግን ዜጎች ፖሊስ ጣቢያ፣ ማዘጋጃ ቤት የመሳሰሉ የክልሉ ሆነ የከተማው መስተዳደር ጋር ሲሄድ ግን፣ በግድ በቁቤ ማመልከቻ እንዲያስገቡ ይደረጋሉ ? አፋን ኦሮሞ የማይናገር ሰው የመንግስት ሥራ ተቀጥሮ መስራት አይችልም። ይሄ ታዲያ ዘረኝነትና ጸረ-ዴሞክራሲያዊነት አፓርታይዳዊ አሰራር አይደለምን ? ለምን ይሄንን እነ ዶር ጸጋዬ አይቃወሙም ?

ምን ችግር አለው አማርኛም አፋን ኦሮሞ ሁለቱም በትምህርት ቤት ቢሰጡ ፣ ሁለቱም የሥራ ቋንቋ ቢሆኑ ? ምን ችግር አለው ሁሉም እኩል ሆኖ፣ የሁሉም መብት ተከበሮ፣ ሁሉም ባህሉ፣ ቋንቋ ተከበሮለት በሰላም ቢኖር ?ምን ችግር አለው ሁሉም የአገሩ ባለቤት ቢሆን ?

ዾር ጸጋዬ ፣ ፕርሮፌሰር ሕዝቄል እንዲሁም ሌሎች አሁን ያለው ሕገ መንግስት መነካት የለበትም የሚል አቋም ነው ያላቸው። የአሁኑ በሕወሃትና በኦነግ በሕዝብ ላይ የተጫነው ሕገ መንግስት እኮ “Ethiopia belongs to nations, nationalities and peoples ” ነው የሚለው። ኢትዮጵያ የነዋሪዎቿ ሳይሆን የጎሳዎች፣ የብሄር ብሄረሰብና ሕዝቦች የሚሏቸው ናት። ” South Africa belongs to everyone who lives in it” እንደተባለው Ethiopia belongs to everyone who lives in it” ቢባልና ከዘር አወቃቀር ፣ ከዘር ፖለቲካ ቢወጣ ምን ችግር አለው ?

እነ ዶር ጸጋዬ የዘር ፖለቲክ ላይ ሙጭጭ ካሉ የደቡብ አፍሪካን ምሳሌ ባይጠቅሱ ይሻላል። አፋቸውን አያበላሹ። ጥሩ ምሳሌ ከፈለጉ ፍራንኮ ቱጅማን እና ስሎቦዳን ሚሎሶቪች ይገዟቸው የነበሩ ግዛቶችን መጥቀስ ይችላሉ።

ዶር ጸጋዬ ያደረገዉን ቃለ ምልልስ ለማዳመጥ ከፈለጋችሁ ሊንኩ እንሆ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.