የሙታን ድምፅ ይጣራል? [ዴሬ አይሣ፤ አርባ ምንጭ ፤ኢትዮጵያ]

 

Unity - satenaw Newsየመቶ አለቃ ጳዉሎስ ቦጋለ “የሕዝብ ምጥ” በሚል ካናዳ ሆነ የጻፈውን  Ethiomedia ላይ አነበበኩ። ጽሁፉ ረዥም ነው። መዝጊያው ላይ “የዘበዘብኩት” ይላል። እውነትነው! ስለምንና ስለማን  እንደጻፈ እንኳን እኔ ራሱም የተረዳው አይመስለኝም።ጳዎሎስ ቦጋለ መዘብዘቡ ሳይሆን ደፍሮ መጻፉ ገረመኝ! ተርቱ “ ጅብ የማያውቁት አገር ሄዶ ቁርበት አንጥፉልኝ አለ!” ነበር። የዛሬ ጅብ የሚያውቁት አገርም ሄዶ ቁርበት አንጥፉልኝ ማለት ቻለ። በዛሬ መገናኛ ካናዳ ከኢትዮጵያ የአንድ ቀን መንገድ ነው። በማህበራዊ ገጽ (Social Media,Internet) የደቂቃ መንገድ ነው። ስለዚህ ጳዉሎስ ቦጋለ የሚኖርበት ካናዳ  “የማያውቁት አገር” አይደለም።

የጳውሎስ ቦጋለ “ደፍሮ መጽፉ ገርመኝ!” ያልኩት ሌላ ተረት አስታወሰኝ። “የአቦን ስለት የበላ ያስለፈልፈዋል!” ሲባል “የት አለ እኔ የለፈለፍኩት!”አለ የሚባለውን። ድፍረቱ ገረመኝ ያልኩትን በሁለት ማስረጃ ለማስረዳት እሞክራለሁ። አንደኛው ከራሱ ከጳውሎስ አንደበት የስማሁትና ሁለተኛው በዚሁ በEthio Media  ላይ የያዛሬ ሁለት አመት ገደማ (February 18, 2015 ) ሽመልስ አበበ የጻፈውን በከፊል እዚህ በመለጠፍ ነው።

                                                  *

1.በዘመን ደርግ ፤በ1960ዎቹ ውስጥ ጳውሎስ ቦጋለ የጋሞ ጎፋ ክፍለ ሐገር ምክትል ዋና አስተዳዳሪ ነበር።። ሰው- በላው የደርግ አባል ሻለቃ ለአሊ ሙሳ አርባ ምንጭ መጣ።  በመቶ አለቃ ጳዎሎስ አዘጋጅነት የ11 የጎፋና የገለብና ሐመር ባኮ አውርጃ ነፍጠኞች ስም  በወቅቱ “አብዮታዊ እርምጃ!” ለሚባለው  ለአሊ ሙሳ ቀርበለት። ዋና አስተዳዳሪው የኦሮሞ ነጻ አውጭ ድርጅት አባል የሆነው መኮንን ገላን ነበር። ጳውሎስ  አቀረበ ያልኩት መኮንን ክፍለ ሐገሩንና ማን ምን እንደሆነ አያውቅምና  ተባባሪ እንጅ ጠንሳሽ ሊሆን አይችልም በሚል ነው። ከነዚህ 11 ስዎች ውስጥ አንዱ ዳኛቸው ከጥቂት አመታት በፊት በወ ቅቱ ለነበረው  የንጉሱ ፓርላማ ከጳውሎስ ጋር የተወዳደር ሰው ነበር። የግል ቂም በቀል ነበራቸው ይባላል።

በቀረበው መሠረት ሻለቃ አሊ ሙሳ “አብዮታዊ ውሳኔ!” አሳለፈ። “አብዮታዊ እርምጃ!” ማለት ይረሸኑ ማለት ነዉ።ብዙ ባለስልጣናት የነበርቡት ስብሰባ ስለነበር ውስኔው ወዲያውን አርባ ምንጭ ናኜ። ትልቅ ድንጋጤና መሸበረም ፈጠረ። “ማነው ተረኛው?” የሚለው በሁሉም ዘንድ ጭንቀትን ፈጠረ። ከተሰበሰቡት ባለስልጣናት አንዱ “እኔ እዚህ ውስጥ የለሁበትም!” ብሎ ስብሰባውን ረገጦ እንደወጣም ተወራ። ሒሊናውን እንጅ 11ዱን ሰዎች አላዳነም።የግለስቡን ስም እዚህ ማንሳት ለጊዜው አስፈላጊ አልመስለኝም።

11 “አብዮታዊ እርምጃ!” የተወሰነባቸው ሰዎች ሰዎች ጎፋ አውራጃ ዋና ከተማ የላ-ሳውላ በእስራት ላይ ነበሩ። በነጋታው ማታ ተረሸኑ። መረሽናቸው ሳይሆን ግድያው እንዴትና ማን አንደፈጸመው መስማቱ የበለጠ የሚዘገንን ነበር። 11ንም ግድያውን( መረሸኑን) የፈጸመው የመቶ አለቃ ጳውሎስ ቦጋለ ነበር። ይህንን የሰማሁት ከራሱ ከጳውሎስ አንደበት ነበር።

“አብዮታዊዊ  ውሳኔ!” በአሊ ሙሳ በተሰጠ ማግስት የመቶ አለቃ ጳውሎስ ቦጋለ በአውሮፕላን ወደየላ-ሳውላ በረረ ።ይህን የሚነግረን ጳውሎስ ነበር። ድርጊቱ ከተፈጸመ በኋላ በሁለተናኛው ቀን አርባ ምንጭ በቀለ ሞላ ሆቴል ጀርባ ፤ወደሐይቆቹና የእግዜር ድልድይ ፊቱን ያዞረው  ጉብታ ላይ ከጓደኞቼ ጋር ቢራ ስንጠጣ የመቶ አለቃ ጳውሎስ መቶ ተቀላቅለን። ወሬውን ማን እንዳነሳው በደንብ አላስታውስም ። ጳውሎስ ሳውላ ግድያው እንዴት እንደተፈጸመ ያወጋን ጀመርን። ያምስታውሰው  “ ሳውላ  ቀን ደርስኩ.. ከማውቃቸው ሰዎች ጋር ሆነን ስንቀመቀም ሞቅ ብሎኝ አመሸን። ከምሸቱ  ሁለት ሰአት ገደማ ወደወህኒ ቤት ሔድን። እስረኞቹ የፍጥኝ ታስረው መጡ። ግርግዳ አስደግፏቸው አለኩ። ከዚያ ኡዚያን አውጥቼ ተራ በትራ አርከፍኩባቸው። ግማሹን በደርቱ፤ሌላው ጭንቅላቱን ፤..የልፍለፋሉ ..ይናዘዛሉ ..ልጆቼን ሳላስድግ … ሳልናዘዘ.. ቤተሰቤን ሳልስናበት ። የደሙ ፍንጣሪ ልብሴን አበላሸው …”  የጦር ሜዳ ፊልም የሚያወራ ነበር የሚመስለው። ዜማ አይኑረው እንጅ ፉከራና ቀረርቶ ይመስል ነበር። የዚያን ቀን የደነገጥኩትን ያክል  ከዚያ በፊትም ከዚያ ወዲህም ደንግጨ አላውቅም።

                                                  *

  1. አሁን ደግሞ ሽመልስ አበበ በ Ethiomedia ላይ February 18, 2015 ከጻፈው ከዚህ ጋር ተዛማጅነት አለው ብዬ ያሰብኩትን ከዚህ በታች አቀርባለህ

“…..እ. ኢ. አ. በ1969 ዓ. ም. በአንድ ወቅት የአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መማሪያ ክፍሎች ዴስኮች ላይ ለእያንዳንዱ ተማሪ ተብሎ በእጅ የተጻፉ የኢሕአፓ ወረቀቶች ተበትነዉ ነበር። ክፍል ስገባ ወረቀቱን አነበብኩ። ወረቀቱ የተሞላዉ በኢህአፓ መፈክሮች ነዉ። እያንዳንዱም ተማሪ አንብቦት ዝም ብሏል። ትምህርትም ተጀምሮ ሳለ የአርባ ምንጭ ወረዳ ፖሊስ ጣቢአ አዛዥ የነበረ ሻምበል ተስፋዬ የሚባል ከጠቋሚ ተማሪዎች ጋር በመሆን በየክፍሉ እየዞረ ማን ነዉ ወረቀት የበተነዉ እያለ ይጮህ ነበር።እኔ የነበርኩበት ክፍልም መጥቶ ጮኸብን። ብዙ ተማሪዎች ክፍል ለቅቀዉ ሲወጡ እኛም ወጣን። ብዙ ጠቋሚ ተማሪዎች በቦክስ ተመቱ። ቁጥሩ አንድ መቶ የሚሆን ማስ የሚባል (ፈረንሳይ የተሰራ አስር ጥይት ጎራሽ) ግማሽ አዉቶማቲክ ጠብመንጃ የታጠቀ የፈጥኖ ደራሽ ሀይል ትምህርት ቤቱን ከበበ። በዚህን ጊዜ ነበር አቶ አሰፋ ጫቦ ወደ ትምህርት ቤታችን የመጡት።

አቶ አሰፋ በጉርድ ላንድሮቨር ሲመጡ ተማሪዎች አሰገቧቸዉ ብለዉ ሲጮሁ ዋና መግቢያዉን በር ይጠብቁ የነበሩት ተማሪዎች አስገቧቸዉ። ከዚያም ሰንደቅ አላማ የሚከበርበት ቦታ መኪናዉን አቁመዉ ከመኪና ሲወጡ ተማሪዎች ከበቧቸዉ። ከዚያም ተማሪዎች ጪኸታቸዉን ማሰማት ጀመሩ። አቶ አሰፋ የላንድሮቨሩ ሞተር ኮፈን ላይ ቆመዉ ሳለ የድምጽ ማጉያ ተሰጥቶአቸዉ ከተማሪዎች ጥያቄ መቀበል ጀመሩ። ከዚያም መልስ መስጠት ጀመሩ። ተማሪዎች በጥሞና አዳመጧቸዉ። እርሳቸዉም “…ይህቺ የዴሞ ቅስቀሳ ነች። ትምህርታችሁን ብትከታተሉ ይበልጥ ትጠቀማላችሁ…” ብለዉ ተናገሩ። ሌሎች መልሶችም ባያረኩን እንኳ እሳቸዉ ምልስ ሊሰጡ እንደማይችሉ ተማሪዎች የተረዱትም ይመስለኛል። በቦክስ የተመቱና የደሙ ተማሪዎች በአምቡላንስ ወደ ሆሲፒታል ተላኩ። ጥቃቱን የፈጸሙ ተማሪዎች ከተጠያቂነት እንደማይድኑ አቶ አሰፋ ማሳሰቢያ ሰጡ። ይህ እየሆነ ሳለ የመቶ አለቃ ጳዉሎስ ቦጋለ መጥቶ አቶ አሰፋ እንዲናገር እድል ሲሰጠዉ ድምጽ ማጉያዉን ተቀበሎ መደንፋት ጀመረ። “…የአድሀሪያን ልጆች የሬሳ ሳጥን በሚያክል አገልግል ፍትፍትና ጭኮ እየተላከላቸዉ ተንደላቅቀዉ እየተማሩ የጭቁን ልጆች እንዳይማሩ ለማድረግ የተጠነሰሰ ሴራ ነዉ…” እያለ ደነፋ። ብዙ ዛቻዎችንም ዛተ። ከዚያም አቶ አሰፋ ከመቶ አለቃ ጳዉሎስ ጋር ለጥቂት ደቂቃዎች ተነጋገረ። የመቶ አለቃ ጳዉሎስ እየተቆጨ ሲናገር እንደነበር ታዘብኩ። ኮሎኔል ተስፋዬ የሚባል የፈጥኖ ደራሽ ሀይሉን መርቶ የመጣዉ ወደነርሱ ጠጋ ብሎ የነገሩትን ሰምቶ ሄደ። ከዚያም አቶ አሰፋ ለዚያኑ ቀን ትምህርት እንደሌለና ወደ ቤታችን እንድንሄድ ነገሩን። እኛም ወደ ቤት ስንሄድ የታዘብኩት ነገር ቢኖር የመቶ አለቃ ጳዉሎስ ቦጋለ ከአቶ አሰፋ ጋር ሲጨቃጨቅ እንደነበር ነዉ። በወቅቱ ከጓደኞቼ ጋር ስንነጋገር የደረስንበት መደምደሚያ ቢኖር የመቶ አለቃ ጳዉሎስ እርምጃ ለመዉሰድ ፈልጎ በአቶ አሰፋ እምቢተኝነትና ተጽእኖ ደም ላይፈስ እንዳልቻለ ነዉ። በወቅቱ ቁጥሩ አንድ መቶ የሚሆነዉ የፈጥኖ ደራሽ ሀይል የግድያ ትእዛዝ ቢሰጠዉ ኖሮ ምን ያህል ተማሪ እንደሚሞት መገመት አያዳግትም. በተማሪዎችም ዘንድ አቶ አሰፋ ክብር ሊያገኙም ችለዋል ይህችን ዉለታ ለተማሪዎች ስለዋሉ።

ከአቶ አሰፋ ጋር በርእዮተ አለም አመለካከት ብለያይም አንኳ በእርሳቸዉ ብርታት ከሞት ልድን ችያለሁ። በወቅቱ ከከበቡን ፈጥኖ ደራሾች ቢያንስ ወደ አስር የሚሆኑትን አዉቃቸዋለሁ። ተማሪዎች የነበሩ ናቸዉ። በሌላ ወቅት አግኝቼ ስጠይቃቸዉ በአቶ አሰፋ እምቢተኝነት የመቶ አለቃ ጳዉሎስ ቦጋለ ትእዛዝ ለመስጠት እንዳልፈለገ አዛዣቸዉ የነበረዉ ኮሎኔል ተስፋዬ እንደነገራቸዉ አጫወቱኝ። ትእዛዝ ቢሰጣቸዉ ኖሮ እኔንም ሊገድሉ እንደሚችሉ ነገሩኝ። እኔም የህችን የአቶ አሰፋን ዉለታ ሁል ጊዜ እንዳስታዉስ አደረገኝ። አቶ አሰፋን ወድጄ አላዉቅም። ግን ይህ ዉለታቸዉ እንዳከብራቸዉ አድሮጎኛል።

ብዙ ሰዎችን አስገድለዋል የሚል ክስና ስሞታ በተደረጉት ትችቶች ዉስጥ ተካትተዋል። አርባ ምንጭ ዉስጥ የተደረጉት ግርፊያዎች ናቸዉ የኢሕአፓን አባላትና ደጋፊዎች ለማጋለጥ ተብሎ። ፋሺስቱ አሊ ሙሳ በገዛ እጁ የገደላቸዉ አተ ተፈሪ (የእኔ ዘመድ የሆነችዉ አየለች ማመጫ ባለቤት)፣ ክፈተዉ (የአጎቴ ባለቤት ወንድም)፣ እና ኑሩ (አቶ አሰፋ ሲታሰሩ በእርሳቸዉ ምትክ የተመደበዉ) ሲሆኑ አርባ ምንጭ ዉስጥ ምንም የፖለቲካ ግድያ አልተካሄደም። አንድም የኢሕአፓ አባል አልተገደለም። ግርፋት ግን ተካሂዷል። በጎፋ አዉራጃ ዋና ከተማ ሳዉላ ከተማ የመቶ አለቃ ጳዉሎስ ቦጋለ ፊዉዳሎች ናቸዉ ብሎ የረሸናቸዉ ጥቂት ግለሰቦች ናቸዉ። የገለብና ሀመር ባኮ አዉራጃ ዋና ከተማ ዉስጥ አንድ የጊዶሌ ተወላጅ የሆነ ካድሬ አንድ ነጋዴ ገድሏል። እ. ኢ. አ. በነሐሴ ወር 1976 ዓ. ም. (August 1984 G. C.) ለትምህርት ኢትዮጵያን ለቅቄ እስከምወጣ ድረስ እዚያዉ ጋሞ ጎፋ የኖርኩ ስለሆነ ሁኔታዎችን ጠንቅቄ አዉቃለሁ። በአቶ አሰፋ ላይ የተደረገዉ አሳዛኝ ትችት ከእዉነት የራቀ መሆኑ በጣም አሳዘነኝ። ጸሀፊዎቹና ተቺዎቹ ከተባራሪ ወሬ የቀሰሙትን ነገር እንደ እዉነታ አድርገዉ ማቅረባቸዉ ዋጋ ቢስነቱን ከማጋለጥ በስተቀር የሚያመጣዉ ነገር ያለ አይመስለኝም። አቶ አሰፋ ቢጠየቁም እንኳ በኢሕአፓነት ተጠርጥረዉና ታስረዉ ለተገረፉት እንጂ በአስገዳይነት አይደለም። ብዙ ተማሪዎች በኢሕአፓነት ተጠርጥረዉ በተለያዩ ቦታዎች ታስረዉና ተገርፈዉ ወደ ሰላማዊ ኑሮና ትምህርት እንዲመለሱ ተደርጓል። ግድያ እንዳይካሄድ ካድሬዎች እንኳ አቶ አሰፋን ያሙ የነበረ ለመሆኑ ሲነገር ሰምቻለሁ። አቶ አሰፋ ኢሕአፓዎች እንዳይገደሉ አድርገዋል። ጋሞ ጎፋ ዉስጥ ባጠቃላይ እስራትና ግርፊያ ተካሄደ እንጂ የፖለቲካ ግድያ አልተካሄደም። ይህ ደግሞ በአዲሰ አበባና ሌሎች ከተሞች አንዳንድ የቀበሌ ሊቀመናብርት በቀይ ሽብር ወቅት ወጣቶች እንዳይገደሉባቸዉ ያስሯቸዉና ይገርፏቸዉ ከነበረዉ በምንም ተአምር አይለይም።

ኢሕአፓዎች ያደረጉትስ የከተማ ቃፊር የግድያ ዘመቻ እና በመካከላቸዉ በነበረዉ የፖለቲካ መከፋፈል እርስ በእርስ የተጋደሉት፤ እንዲሁም ወጣቱን ያስጨረሱት ተረሳና የአቶ አሰፋ ድርጊት ጎልቶ ታይቶ ነዉ ወይ እንዲህ አይነቱ ትችት የተደረገዉ? ትችት በትክክል መረጃ ተይዞ ሲቀርብ ያምራል። ያለበለዚያ ቂም መወጣጫ ወይም ለፖለቲካ ፍጆታ ይዉላል። ደርግም፣ ኢሕአፓም፣ መኢሶንም፣ ወያኔም ሆን ማንም ድርጅትም ሆነ ግለሰብ ከተጠያቂነት አይድንም።

ኢትዮጵያ ለሁላችንም እኩል እናት አገር ነች። ማንም ከማንም አይበልጥም። የበደሏት፣ የገደሏትና የሞቱላትም እንዲሁ አሉ። እያንዳንዱ ትዉልድ የራሱ የሆነ ባህርይ እንዳለዉ ሁሉ ለቀጣዩ ትዉልድ የሚያስተላልፈዉ ትምህርት ገንቢ ሀሳብና ራእይ ያለዉ ቢሆን ይመረጣል። ካልሆነም ደግሞ የታሪክ ተወቃሽ ሆኖ ይቀራል። አገር በቂም በቀል የሚመራ መሆን የለበትም። ታሪክም ቢሆን የሚጻፈዉ በቂም በቀል አይደለም። ወቀሳ፣ ትችትና ሂስ ገንቢ የሚሆኑት አግባብ ባለዉ ሁኔታ ሲፈጸሙ ነዉ። ታሪክም እንዳይወቅሰን ደግሞ ብናስብበት የበለጠ ጠቃሚነት አለዉ ብዬ አምናለሁ።

ሺመልስ አበበ shimelisabebe@gmail.com

*

ይህ በሆነ በሶስተኛው ወር ይሁን ጳውሎስ ቦጋለ ከምክትል አስተዳዳሪነቱ ተነሳ። ድርጊቱ ተደርሶበት በቁጥጥር ስር ውሏል የሚል ወሬ ናኝቶ ነበር። በቁጥጥር ስር ሳይሆን ንግድ ሚኒስቴር መዝገብ ቤት መደቡት። ከዚያም ዛሬ ነገ ቁጥጥር ስር ይውላል የሚል ወሬ ነበር። ጳውሎስም አመኖበት  በቁሙ የሚቃዥ ሁኖ ነበር ተብሎ ሲወራ እስማለሁ። ከዚያ ለማምለጥ አንድ የሚያውቀውን ሰው ተማጽኖ ለፖለቲካ ትምህርት ኩባ ተላከ። ለዚያ ለመሔድ የነበረው ቀዳዳ በወቅቱ ከነበሩት የፖለቲካ ድርጅቶች የአንዱ አባል መሆን ነበር። ኩባ  አንድ አመት ተኩል ቆይቶ ወደኢትዮጵያ ሲመለስ የሰደድ አባል ሁኖ ተመለሰ።  ይህ ደግሞ አዲስ አበባ እንደገባ  ሌላ ችግር ፈጠረበት። የሁለት ድርጅት አባል ሆኖ መገኘት በወቅቱ ሲበዛ ለሞት ሲያንስ ለእስራት የሚያበቃ ነበር። ሰደደ የነመንግስቱ ኃይለ ማርያም ፓርቲ መሆኑ ነው። በፖሊስነቱ የሚያውቀው፤የሰደድ አመራር አባል የነበረው  ሻለቃ ጌታቸው አግዴ ከዚህ ማጥ ውስጥ አስወጣው ሲባል ሰመቻለሁ።

ይህ ነው የሚባል  ስራም  ሳያገኝ ወያኔ ገባ። ወያኔ እንደገባ ሊጠጋቸው መንገድ በመፈላለግ ላይ እንዳለ ይህንን ኢሰብዐዊ ድርጊቱን ደርሱበትና በቁጥጥር ስር ሊያውሉት ሲፈልጉ በጅቡቲ በኩል ሾልኮ ካናዳ ገባ ተባለ። የሰማሁት ይህንን ያክል ነው እንጅ በተለየ ያጣራሁት አልነበረም። አሁን ካናዳ ሁኖ ለኢትዮጵያ ሕዝብ  ተቆርቋሪ ሁኖ “የሕዝብ ድምጽ” ብሎ  ጻፈ።እኒዚያ የረፈራፋቸው  ሰዎች የህዝብ አካል አልነበሩም? አርባ  ምንጭ ሁለተኛና ደርጃ ሊያስፈጃቸው የነበሩት   ተማሪዎች ሕዝብ ቁጥር ውስጥ አይገቡም? የሕዝብ ትርጉም ትላንት፤ተትላንት ወዲያ፤ ዛሬ፤ ነገ፤ ኢትዮጵያ ይሁን ካናዳ እንደ አመችነቱ የሚለዋወጥ ተለዋዋጭ ትርጉም አለው?  ፀፀት የሚሉት፤መሰቅጠጥ የሚሉት አንዳንዱ ቤት፤ጳውሎስ ቦጋለ ቤት  ሞቶ ቀበረ?አንድ ልዩነቱ ቢኖር፣ጳውሎስ ቦጋለ ሲያመልጥ  ሻለቃ አሊ ሙሳ ግን “የቁርጡ ቀን ሲመጣ” የገዛ ሹጉጡን ጠጥቶ ሞተ ! ይገርመኛል!

የመቶ አለቃ ጳውሎስ ቦጋለ “የሕዝብ ምጥ” በሚለው ጽሁፉ መግቢያ አካባቢ “አስጨናቂው ምጥ አገርንና ሕዝብን ከገጠማቸው አስከፊ አስተዳደር ለመገላገል ..”ይላል። ወደማጠቃለያው ላይ ደግሞ “እንግዲህ ለብዙ አመታት አምቄው የኖረውን እንዳለ ዘረገፍኩት” ይላል ። ጳውሎስ ንዳለ ዘርገፍኩት ማለቱን እንኳን እኔ ራሱም የሚያምነው አልመስለኝም።ጎፋ የላ-ሳውላ በኡዚ ያጨዳቸው 11 ሰዎች ጉዳይ አላነሳም። ይህ በአደባባይ፤ሳውላ ወህኒ ቤት፤ አገር ሲያየው የፈጸመው ነበር። ጳውሎስ ቢረሳው፤ቢዘነጋው፤ ወይም ሊረሳው ሊዘነጋው ቢፈልግም እኒያ  አይን ምስክር የነበሩ ሊረሱትና ሊዘነጉት የሚችሉት አይመስለኝም። እነዚህ 11 ስዎች እንደማንኛችንም ባል፤አባት፤ ወንድም፤ አጎት፤አክስት፣ጎሮቤት፣ዘመድ-አዝማድ አገር የሚያውቃቸው ዘመድ አዝማድ ፣ከሁሉም በላይ ልጆች ያላቸው ነበሩና ትላንትም፤ዛሬም ነገም ሊረሱ የሚችሉ አይመስለኝም።

የጳውሎስ ቦጋለ “የሕዝም ምጥ” ጽሁፍ መደመደሚያው “በቅርቡ የምለው አለኝ!” ይላል። ይህንን ወድጀዋለሁ! በቅርቡ ይህንን አስቃቂ ግፍ ታሪክ ይነገራናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። እኔም ሆንኩ ሌላው ከጳውሎስ ቦጋለ መስማት የምንፈልገው አንዳች ነገር ቢኖር የዚህን የየላ-ሳውላ ወህኒወኔ ቤት ግድያ ታሪክ ብቻ ነው።

ወይም አማራጭም አለ።ካናዳ የወንጀለኛና ፤የነፍሰ ገዳይ መሽሸጊያ፤መታጎሪያ ፤መሸፈቻ ጫካ አይደለችም። የአለም አቀፍ ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ማቋቋሚያ ስምምነት(International Court of Criminal Justice,ICC )December 18,1998 በ  ፈርማ ተቀብላ  አጽድቃለች። በዚሁ መሠረት በየአገሩ የተሽሸጉ የሰው ዘር አጥፊዎች እየተፈረደባቸው ወህኒ ወረደዋል።  ለሰው  ዘር መዳን የሚሟገቱ ድርጀቶችና ግለሰቦች ተባብረው ማስረጃውን ለካናዳ መንግስት የማቅረብ ጉዳይ እንጅ ጳውሎስ ቦጋለን  ፍትሕ አደባባይ ማድረስ ዛሬ በጣም  ውስብስብ አይመስለኝም።

ጳውሎስ ቦጋለ “በቅርቡ የምለው አለኝ!” የሚለውን ለዚያ ፍርድ ቤት ይንገርና ከዚያ ብንስማው እምርጣለሁ!

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.