በወያኔ እርሾ አንዲት ኢትዮጵያን ማሰብ አይቻልም! ማስጠንቀቂያ ለአዲሱ ንቅናቄ! [ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው]

dc-meeingዛሬ ምሽት 21,2,2009ዓ.ም. በዶቸቨሌና በቪኦኤ (ሌላ መረጃ የምናገኝበት መንገድና ዕድል ዝግ በመሆኑ ነው) ትናንትና አሜሪካ ውስጥ 9 ወራት ከፈጀ ውይይት ድርድርና ድካም በኋላ ሀገር አቀፍ እና ጎሳ ወይም ጎጥ ተኮር አምስት ድርጅቶችን ያቀፈ “የኢትዮጵያ ሀገራዊ ንቅናቄ!” የተባለ የጥምረት ንቅናቄ መመሥረቱ ይፋ መደረጉን ከመጠነኛ ማብራሪያ ጋር ሰማን፡፡ እውነቴን ነው የምላቹህ ዛሬ ከመቸውም ጊዜ በባሰ በሀገራችን ፖለቲካ (እምነተ አሥተዳደር) ጉዳይ ላይ ተስፋ የቆረጥኩበት ዕለት ነው፡፡ በዚህ ቅጽበት አንድ መፍትሔ የምለውን ነገር ለማሰብ ተገድጃለሁ ወደመጨረሻ እገልጽላቹሀለሁ፡፡

ይህ የጥምረት ንቅናቄ ግልጽ ካደረገው ዐቢይ ጉዳይ አንዱና ዋነኛው የሀገራችን ፖለቲካ (እምነተ አሥተዳደር) ምን ያህል በወያኔአዊ አስተሳሰብ የተመረዘ መሆኑንና አስቀድሞ ይሄንን አሳሳቢ ችግር መቅረፍ ምን ያህል አንገብጋቢ መሆኑን ነው፡፡

ለዚህ አባባሌ ሁለት ምክንያቶች አሉ፡፡ አንደኛው ይህ የሀገራዊ ንቅናቄ ጥምረት ወደፊት ልንመሠርተው ለምንፈልገው መንግሥታዊ አሥተዳደር በወያኔ በኩል ተጭነነው ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እንዳመዘነ ያየንበት ጎሳ ተኮር የፖለቲካ ድርጅት እንቅስቃሴዎች ቦታ እንዳላቸው ግልጽ ማድረጉ ሲሆን፡፡

ሌላው ደግሞ ጥምረቱ በተበሰረበት መድረክ ላይ ከነኝሁ ጥምረቱን ከፈጸሙት ድርጅቶች የተነገሩ ወያኔአዊ የፖለቲካ አስተሳሰብና መርሖዎች ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ይህ ጥምረት ቢሳካለትና ሀገር ቢቆጣጠር በሁለቱ በጠቀስኳቸው ወያኔአዊ ችግሮች ምክንያት ዛሬ ውጥንቅጧ ወጥቶ እየታመሰች ካለችው ኢትዮጵያ የተለየች ኢትዮጵያን መፍጠር እንደማይችል እንዲያውም በአንዳንድ ሁኔታ የባሰ ችግር ላይ የምትሆን ሀገርን ሊፈጥር እንደሚችል ግልጽ ሆኗል፡፡

ይህ የሀገራዊ ንቅናቄ ጥምረት በጥምረት የተመሠረተ ሳይሆን የተጣመሩት ድርጅቶች እራሳቸውን አፍርሰው አንድ የተዋሐደ ድርጅት መሥርተው ቢሆን ኖሮ ይህ የጠቀስኩት ሥጋት ባልተፈጠረ ነበር፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ከድርጅቶቹ ፖለቲካዊ ብስለት ማነስና ከጠባብነት ችግር የተነሣ ድርጅቶቹ ይሄንን ሊያደርጉ አልቻሉም፡፡ በዚህ ሁኔታ እነሱ እንዳሉት እንዴት አንድ ዓይነት መግባባት ላይ እንደደረሱ ግልጽ አይደለም የማይመስል ነገርም ነው፡፡ ምክንያቱም አንድ ዓይነት መግባባት ላይ ቢደርሱ ኖሮ ከመዋሐድ የሚያግዳቸው ነገር አይኖርም ነበርና፡

ከላይ የጠቀስኩትን ሥጋት ከፈጠሩ ሁለት ዐበይት ጉዳዮች ሁለተኛው ማለትም “ጥምረቱ በተበሰረበት መድረክ ላይ በተጣማሪ ድርጅቶች የተነገሩ ወያኔአዊ የፖለቲካ መርሖዎች” ስል የጠቀስኩት መብራራት ይኖርበታልና አንድ ምሳሌ በማንሣት እሱን ላብራራ፡፡

በዚያ መድረክ ላይ ከተጣማሪ ድርጅቶች አንደበት አንድ በተደጋጋሚ የተገለፀ አባባል አለ “በሕዝቦቿ መፈቃቀድ ላይ የተመሠረተች አዲስ ኢትዮጵያ!” የሚል፡፡ ድርጅቶቹ ይህ ቃል ምን ማለት እንደሆነ ሳይገባቸው ሳይረዱትና ሳያምኑበት እንዳልተናገሩት እገምታለሁ፡፡ አደጋው ያለውም እዚህ ላይ ነው፡፡ የሚገርመው ይሄንን ብለው ሲያበቁ እዛው ላይ ደግሞ የወያኔ ሕገመንግሥት ለሀገር ህልውና አደጋ ስለሆነ አፍርሰን ወይም ውድቅ አድርገን ሌላ አዲስ ሕገመንግሥት አርቅቀን እናፀድቃለን ማለታቸው ነው፡፡ “በሕዝቦቿ መፈቃቀድ ላይ የተመሠረተች አዲስ ኢትዮጵያ!” ብለው ሲሉ “የወያኔ ሕገመንግሥት ለኢትዮጵያ አንድነት አደጋ ነው መጣል ውድቅ መሆን አለበት!” ከሚሉበት ምክንያት አንዱ የሆነውን አንቀጽ “የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት እስከ መገንጠል!” የሚለውን እንደገና ሕይዎት እየዘሩበት እንደሆነ አልገባቸውም ወይም ሸፍጠዋል፡፡

“በሕዝቦቿ መፈቃቀድ” ማለት ምን ማለት ነው??? እንዴትና ለምንስ ነው ላይፈቃቀዱ የሚችሉት? ግለሰቦች ወይም ቡድኖች የሚያደርሱት በደል ሀገር እንዳደረሰችው ተቆጥሮ እሷ ላይ ሊፈረድባት ይገባል ወይ??? እሽ እንደእነሱ አባባል “ያልፈቀደ አለ” እንበልና ያልተፈቃቀዱ እንደሆነስ ምን ሊያደርጉ ነው??? ያው ግልጽ ነው እንገነጠላለን ነው መልዕክቱ፡፡ ስለሆነም “ጥምረቱ የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት የማስቀጠልን ጉዳይ መሠረቱ ወይም ዋነኛ ጉዳዩ አድርጓል!” መባሉ ሐሰት ወይም የማስመሰል ነው ማለት ነው፡፡ ታዲያ እንዲህ ዓይነት ሸፍጦችን ያዘለ ጥምረት እንዴት ሆኖ ነው ለዚህች ሀገር መፍትሔና ከወያኔ/ኢሕአዴግ የተሻለ አማራጭ ሊሆን የሚችለው??? ወያኔ በቀደደው ቦይ እየፈሰሱ፣ ወያኔአዊ አስተሳሰብ እያራመዱ ከወያኔ የተለዩ ሌላ አማራጭ መሆን ይቻላል ወይ? በዚህስ ሁኔታ እንዴት ሆኖ ነው ይህ ንቅናቄ እንደተገለጸው “ከ9 ወራት ውይይትና ድርድር በኋላ አንድ አግባቢ ሐሳብ ላይ የተደረሰበት የጥምረት ንቅናቄ ነው!” ሊባል የሚችለው?

ይህ “በሕዝቦቿ መፈቃቀድ” የሚል ወያኔአዊ አባባል በዕውቀትና በእምነት ላይ ተመሥርቶ ከአንድ አካል ከወጣ ይህ ቃል የሚወጣው እንደወያኔ ሁሉ ፀረ ኢትዮጵያ አቋም ዓላማና ሸፍጥ ከሚውጠነጠንበት አካል ልብ ውስጥ እንደሆነ ማንም ሊጠራጠር አይገባም፡፡ ፈቀድንም አልፈቀድን እኮ ይህች ሀገር የግዛት አካሏ ሲሰፋ ሲጠብ ቆይቶ መጨረሻ ላይ አሁን የያዘችውን ቅርጽ የያዘች መሆኗ እንዳለ ሆኖ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ከተመሠረተች እኮ ሽዎች ዓመታት አልፈዋል፡፡ ሽዎች ዓመታት ወደኋላ ተመልሰን መደራደር ነው እንዴ የምንፈልገው? ንኮች ካልሆንን በስተቀር ይሄ በእውን የሚቻል ነገር ነው ወይ? ያለቀለት ጉዳይ ከሆነ ሽዎች ዓመታት ባለፉት ነገር ላይ ጊዜን በከንቱ ማጥፋት ለምን አስፈለገ? ችግራችን ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር መኖሯ ነው ማለት ነው? ካልሆነ በስተቀር የህልውናዋን ጉዳይ ለምን እንዲያጠያይቅና ቅድመ ሁኔታ እንዲሆን እንፈልጋለን???

ማንም ሰው እንደሚረዳው ችግራችን የሆነውና ልናስተካክለው፣ ልንቀርፈው፣ ልናቀናው፣ ለዜጎች በሙሉ ምቹና አስደሳች ልናደርገው የሚገባን ጉዳይ አሥተዳደራዊው ችግር እንጅ በየትኛውም አማራጭ ይሁን በየት ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ተመሥርታ መኖሯ አይደለም ችግራችን የሆነው፡፡ ሊሆንም አይችልም፡፡ ይህ አጀንዳ ኢፍትሐዊ ጥቅማቸውን ማስጠበቅ የሚፈልጉት የዚህች ሀገር ጠላቶች የባዕዳን እንጅ የዜጎች አይደለም፡፡ እንዲህ ብሎ የሚያስብ ሀገራዊ አካል ካለ በባዕዳን መርዘኛ የጥፋት አስተሳሰብ የተመረዘ ነውና ከእንዲህ ዓይነት አካል ጋራ ጥምረትም በሉት ምን አድርጌ ለሀገር የሚበጅ ነገር እፈይዳለሁ ብሎ ማሰብ እጅግ ሲበዛ ጅልነትና አለማስተዋልም ነው፡፡

በመተባበር በመመካከር በመደራደርና በመወያየት ቀናና በፍትሐዊነትና በእኩልነት  ለዜጎች ሁሉ የሚመች መንግሥታዊ አሥተዳደር መመሥረት ከፈለግንና ይሄንንም ማድረግ የሚቻል ከሆነ በዚህም ችግራችንን ሁሉ መቅረፍ የምንችል ከሆነ ይህ እንዲሆንም በርትተን መታገል እንዳለብን ካመንን “በሕዝቦቿ መፈቃቀድ” ምንንትስ በማለት የኢትዮጵያን ህልውና አጠያያቂና ቅድመ ሁኔታ አድርጎ ማቅረብ ለምን አስፈለገ??? ሲጀመር በኢትዮጵያ ህልውና ላይ እንድንወስን መብቱን ማን ሰጠን?እንዴትስ አገኘነው? በተለይ ደግሞ አሁን ኢትዮጵያ ብለን ከምናውቃት ሀገር ድንበር ማዶ ፈልሶ ከገባ ረጅም የሚባል ዓመት ያላሳለፈ ጎሳ በሉት ብሔረሰብ እንዴት ሆኖ ነው በአሁኗ ኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ “ወሳኝ ነኝ!” ሊል የሚችለው??? ዝም ብሎ በመድረቅ የሚሆን ይመስላቸዋል ወይ? ይሄን ባይ ወገኖች የሞራል (የቅስም) ጥያቄን ለራሳቸው ሊያነሡ አይገባም ወይ? በዚህ አስተሳሰባቸው ሊያጎሉ እንጂ መቸም ቢሆን ሊያተርፉ እንደማይችሉ፣ ዕድሜ ዘለዓለማችንን ስንተራመስ እንኖር እንደሆነ ነው እንጅ ይሄንን አድርገን እንደማንረጋጋ እንዴት መገንዘብ ተሳናቸው? ምን ያህልስ ለፖለቲካ (ለእምነተ አሥተዳደር) ፣ ለኢኮኖሚ (ለምጣኔ ሀብት) ፣ ለማኅበራዊ ጉዳዮች፣ ለነባራዊና መጻኢ ዓለማቀፋዊ ኩነቶች ጥሬ ወይም አንዳችም ነገር የማያውቁ መሀይም ቢሆኑ ነው “ተገንጥለን እንደ ሀገር ልንቆም እንችላለን!” ብለው ሊያስቡና ሊያምኑ የቻሉት??? እነዚህ ናቸው አሁን በሀገርና በሕዝብ እጣ ፋንታ ላይ የሚወስኑት???

የዚህን ያህል የሞራል (የቅስም) እና የእውነታ (ፋክት) ተጠያቂነትና ተገዥነት  ከማይሰማቸውና ከሌላቸው አካላት ጋርስ የእነሱን ጥፋት ያዘለ ትግል አግዞ ለእነሱ ድጋፍ ሆኖ ዓላማቸውን ለማሳካትና ለመበላት ካልሆነ በስተቀር እንዴት ሆኖ ነው ተግባብቶ ለአንድ ዓላማ አብሮ መሥራትና ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ተጠቃሚ ማድረግ የሚቻለው???

በዚህ አንገብጋቢ ነጥብ ምክንያት በግሌ እስከዛሬ ስደግፈው የነበረውን አርበኞች ግንቦት 7ን ብሔራዊ (ሀገር አቀፍ) ንቅናቄ ከዚህ በኋላ ለእነኝህ የጥፋት ዓላማን ለሸመቁ የጥፋት አካላት መጠቀሚያ መሆኑ ስለሆነ ከዚህ ቀደምም ይህ ድርጅት ከጎሳ ተኮር ድርጅቶች ጋር ጎሳ ተኮርነታቸውን እንደያዙ አስተሳሰባቸው ከጎሳ ተኮርነት ወደ ሀገር አቀፍነት ሳያድግ ሳይለወጥ ከነሱ ጋር ተጣምሮ ቢሠራ የጥፋት ዓላማቸውን ደግፎ አግዞ ለስኬት በማብቃት ሀገርን ሌላ ዙር ምስቅልቅል ውስጥ እንድትገባ ከማድረግ ባለፈ ሊፈጥር የሚችለው ሀገርንና ሕዝብን የሚጠቅም በጎ ነገር ሊኖር እንደማይችል በመግለጽ ደጋግሜ ሳስጠነቅቅ የቆየሁት  ጉዳይ በመሆኑ ከዛሬ ጀምሮ የአርበኞች ግንቦት 7 ደጋፊነቴን ማቋረጤን በይፋ መግለጽ እወዳለሁ፡፡

ይህ የጥምረት ንቅናቄ ኩነት ማለትም የሀገራችን ፖለቲካ በወያኔአዊ ጠባብ አስተሳሰብ ተመርዞ የመቅረቱ አሳሳቢ ችግር ጉዳይ ከሌሎች አሳሳቢ ምክንያቶች በተጨማሪ ይህንን ጠባብ ጎጅና ኋላ ቀር አስተሳሰብ የሚያቀና የሚያስተካክል ማለትም በሠለጠነው የምዕራቡ ዓለም ጎሳ ተኮር የፖለቲካ ንቅናቄ ሕገወጥና ክልክል እንደሆነ ሁሉ በሀገራችንም እንዲህ ዓይነት ኋላ ቀር ያልሠለጠነ ጎጂ የፖለቲካ ንቅናቄን ሕገ ወጥ አድርጎ ዜጎችን በእኩል ዓይን በመመልከት የሀገራችን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ በማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ሰብአዊ መብቶች ላይ ብቻ አትኩሮ እንዲዘወርና በእነዚህ የአስተሳሰብ ልዩነቶች ብቻ እንዲዳኝ ማድረግ የሚቻልበትን ምኅዳር የሚፈጥርና የአጠቃላይ ሕዝቡ ማለትም የግለሰብን መብትና ከጎሳ ተኮር ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ውጭ የሆኑ የቡድን መብት የተጠበቁባት ፍጹም ዲሞክራሲያዊት (መስፍነ ሕዝባዊት) ኢትዮጵያን ለመመሥረት የሚታገል አንድ ይሄንን ከባድ ኃላፊነት መውሰድና መወጣት  የሚችል ጠንካራ የአማራ ፖለቲካዊ ድርጅት የግድ አስፈላጊ መሆኑን ከመቸውም ጊዜ በበለጠ ግልጽ አድርጓል፡፡

እዚህ ላይ “ኋላ ቀር ያልሠለጠነ ጎጂ ጠባብ ጎሳ ተኮር ፖለቲካዊ አስተሳሰብን ለማስወገድ…” እያልክ ቆይተህ እንዴት አንተው ራስህ መልሰህ ደሞ “የአማራ” ትላለህ? የሚል ጥያቄ ይነሣ ይሆናል፡፡ በቂ አሳማኝና አጥጋቢ መልስ አለው በሌላ ጊዜ በሚገባ ከአደረጃጀት አቅዱ ጋር እመለስበታለሁ ጠብቁኝ፡፡

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

amsalugkidan@gmail.com

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.