በዘረኞች በምትታመስ ያልታደለች ሀገር ውስጥ አንድ መሆን ያቃታቸው ሙና የአንድነት ኃይሎች (ከይገርማል)

dc-meeingሀገር እናትም አባትም ናት:: ሀገር ዘመድ አዝማድ ናት:: ሀገር ዘር ቋንቋ ናት:: ከሀገር በላይ ምን ወላጅ: ምን ዘር: ምን ቋንቋ አለ? ከሀገር በላይ ምን ገመና ከታች ወገን: ምን በሰላም የሚያርፉበት ጎጆ አለ? ከሀገር በላይ ምን ሀብት ምን ተስፋ ምን ህይወት አለ? አባት እናቶቻችን ክፉውንም ደጉንም ተጋርተው: በደምና በአጥንታቸው አስከብረው ያስረከቡንን ሀገር እንዴት አድርገን ልንጠላ እንችላለን:: ሚሊዮኖች ሞተው ሚልዮኖች ቆስለው አስከብረው ያቆዩንን ሀገር እንዴት ለማፍረስ እንነሳለን?

የጎሣ ድርጅቶች በተለይ ሕወሀት: ኦነግና ኦብነግ በኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ላይ ጥልቅ ጥላቻ እንዳላቸው በግልጽ ነግረውናል: በተግባር አሳይተውናል:: ግን ለምን?

ወያኔወች ኢትዮጵያን የሚጠሉት አማራውን ስለሚጠሉ ነው:: አማራውን የጠሉት ‘የትግራይ የበላይነት በአማራው የበላይነት በመተካቱ ስልጣን ስላጣን ነው: አማራው ስለጨቆነን ነው’ በሚል ነው:: የኦሮሞ ድርጅቶች ደግሞ አጼ ሚኒሊክ በወረራ ብዙ ሚሊዮኖችን ገድሎ ሳንወድ በግድ ኢትዮጵያዊ አድርጎናል ይላሉ:: ኦብነጎች በበኩላቸው የእንግሊዝ መንግስትና የኢትዮጵያ መንግሥት ባደረጉት ስምምነት ካለፍላጎታችን ወደኢትዮጵያ እንድንካለል ተደርገናል በሚል ኢትዮጵያን ይጠላሉ:: የኦሮሞ ድርጅቶችና ሕወሀት የሚናገሩት ኢትዮጵያ የተመሰረተችው በአጼ ሚኒሊክ ዘመነ-መንግሥት በሀይል እንደሆነ ነው:: ምናልባት ኦብነግ የኦጋዴን ክልል ከእንግሊዝ ወደኢትዮጵያ የተመለሰው በአጼ ኃይለሥላሴ ጊዜ ስለነበር ኢትዮጵያ የተመሰረተችው በአጼ ኃ/ሥላሴ ጊዜ ነው ሊል ይችላል::

ከአጼ ሚኒሊክ ዘመን በፊት በነበሩ የሀገር ውስጥና የውጪ የታሪክ ጸሀፊወች እንደተረጋገጠው ኢትዮጵያ አሁን ከነበራት የግዛት ክልል እጅግ የሰፋ ይዞታ እንደነበራት ነው:: ጅቡቲን እና ሶማሊያን አጠቃላ የያዘች: ከፊል ሱዳንን እና ከፊል ግብጽን ያቀፈች: ቀይ ባሕርን ተሻግራ የመንን ጭምር በግዛቷ ያጠቃለለች: በደቡብም እንዲሁ አሁን ላይ በሌሎች ሀገሮች የሚታወቁ ክልሎችን ሁሉ የያዘች እንደነበረች የታሪክ መጽሀፍት ያወሳሉ:: ያ ሰፊ የግዛት ክልል በጊዜ ሂደት የማዕከላዊ መንግሥቱን ብርታትና ድካም ተከትሎ ሲሰፋና ሲጠብ ኖሮ በቅርቡ እንኳ ባሕረ-ነጋሽ ትባል የነበረችዋ ኤርትራ ተከልታ ኢትዮጵያ አሁን ያላትን ቅርጽ ይዛ ትገኛለች::

የግራኝ መሀመድን ወረራ ተከትሎ የማዕከላዊ መንግሥቱ ፈርሶ አካባቢያዊ ጉልበተኞች ተፈጥረው ነበር:: ግራኝ መሀመድ ከሞተ በኋላም ቢሆን የማዕከላዊ መንግሥቱ ጥንካሬ አግኝቶ ሁሉንም የኢትዮጵያ ክልል ለማሰባሰብ አቅም አንሶት ለብዙ ጊዜ ቆይቷል:: በዚህም የተነሳ አብዛኛው የደቡብና የምስራቅ የሀገሪቱ ክፍል በየሰፈር አውራወች ይመሩ ነበር:: ከዳግማዊ ሚኒሊክ ዘመነ-መንግሥት በፊት ባለው ጊዜ የሶማሌና የኦሮሞ ጎሣወችን ለይተን ብናይ እያንዳንዳቸው በንዑስ ጎሣወች የተከፋፈሉ መሆናቸውን እንረዳለን:: የሀረር: የባሌ: የአርሲ:: የሸዋ: የሲዳሞ: የወለጋ: የከፋ: የኢሉባቦር: የሲዳሞ ኦሮሞወች የማይገናኙ የየራሳቸው ንዑስ ጎሣ ያላቸው ነበሩ:: ንዑስ ጎሣወቹ በተለያየ ምክንያት ይዋጉ ነበር:: ሶማሌወችም እንዲሁ በንዑስ ጎሣወች የተከፋፈሉና በጠላትነት የሚተላለቁ ነበሩ:: ኦሮሞወችም ሆኑ የኢትዮጵያ ሶማሌወች ሌላ ወገን አደረሰብን ከሚሉት በላይ በእርስ በርስ ጦርነት ተጨፋጭፈዋል:: በማዕከላዊ መንግሥቱ ስር የነበሩት የአብዛኛው የሰሜን እና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ግዛቶች ለይቶላቸው ወደመሳፍንታዊ የየአካባቢ አስተዳደር የተከፋፈሉት በትግራዩ ራስ ስሁል ሚካኤል (ቀዳማዊ መለስ ዜናዊ) አጥፊ ርምጃ ነበር:: ከዚያ በኋላ የየአካባቢ መንግሥታት ተፈጥረው ለስልጣን እና ለመሬት መተላለቅ ተጀመረ:: አማራ በመሳፍንት ግዛቶች የተከፋፈለ ነበር:: ትግራይም እንዲህ አሁን እንደሚወራው አንድ አልነበረችም:: አድዋ: ሽሬ: አክሱም: እንደርታ: ተምቤን: ክልተአውላሎ: አዲግራት: ራያና አዘቦ የየራሳቸው መሪወች ነበራቸው:: ከላይ ሰራየን: ሀማሴንን እና አከለጉዛይን ጨምሮ ሁሉም ትግርኛ ተናጋሪወች በእርስ በርስ ጦርነት የተጠመዱ ነበሩ::

የማዕከላዊ መንግሥቱን አቅም አጠናክረው በየአካባቢው ጉልበተኞች የሚተዳደሩ ክልሎችን ለማሰባሰብ ሙከራ ያደረጉት የመጀመሪያው ንጉሥ አጼ ቴወድሮስ ሲሆኑ ለውጤት የበቃው ግን በአጼ ሚኒሊክ ዘመነ መንግሥት ነበር::

አጼ ሚኒሊክ ሀገር ላቀና እንጅ ላጠፋ አልመጣሁም በማለት ሕዝባቸውን ለማሰባሰብ የቻሉ ታላቅ የሀገር መሪ ነበሩ:: እምቢ ብሎ የወጋቸውን የጎሣሃይል መክረውና ገስጸው ከምንም በላይ በፍቅር አሸንፈው እምዬ ምኒሊክ ተብለው ያስተዳደሩ የተለዩ መሪ ነበሩ:: እንዲህ እንዳሁኑ በሕዝብ ላይ በግድ ገዥወችን የሚጭኑ ሳይሆኑ በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር በመረጠው እንዲተዳደር የተማረከውን በምህረት ለቀው ሕዝቡ የሚወደውን መልሰው የሚሾሙ እጅግ ብልህና ዴሞክራት መሪ ነበሩ:: ንጉሡ አሁን ያለችውን ኢትዮጵያ ከመሰረቱ በኋላ የጎሣወች ፍትጊያ እየከሰመ: በጦርነት ምክንያት የሚሞተው የሕዝብ ቁጥርም እየቀነሰ ሄደ:: በሰው ልጅ መነገድ (የባሪያ ንግድ) ወንጀል ነው ተብሎ በመታወጁ ሮጠው እንዳያመልጡ በሚል ጅማታቸው እየተቆረጠ በግላጭ በገበያ ይሸጡ የነበሩ ወገኖቻችን እፎይታን አገኙ::  የትምህርትና የጤና አገግሎቶች መሰረት ተጣለ:: የህዝብን ሰላም የሚያስከብር ፖሊስ: የሀገርን ዳርድንበር የሚጠብቅ ወታደር በየቦታው ማስቀመጥ ተጀመረ:: የፖስታ: የስልክ: የመንገድ ግንባታወች መካሄድ ጀመሩ:: በፊት ያልነበሩ የስልጣኔ አሻራወች በምድር ላይ ያረፉት በሚኒሊክ ዘመን ነበር:: የማህበራዊ አገልግሎቶች የተስፋፉት: ሰው በሰላም ወጥቶ በሰላም መግባት የጀመረው በሚኒሊክ ዘመን ነበር:: የንዑስ ጎሣወች መተላለቅ: የመሳፍንቶች መሻኮት: የባሪያ ፍንገላው የተገታው በአጼ ሚኒሊክ ዘመነ-መንግሥት ነበር:: የዘመነ መሣፍንት እና ዘመነ ንዑስ ጎሣ ጊዜ አልፎ ዘመነ አንድነት ሲመሰረት በሁሉም ሕዝብ ተጋድሎ ነጻነታችንን ከጣሊያን ወራሪ ኃይል ለመከላከል በቃን:: የጣሊያንን ወረራ ለመመከት መላው ኢትዮጵያዊ ሆ ብሎ ተነስቶ በፈጸመው ገድል አድዋ ላይ በማይነጥፍ ደም የጥቁር ዘር አኩሪ የነጻነት ታሪክ ጻፍን:: ታዲያ ለምንድን ነው አጼ ሚኒሊክ የሚጠሉት?

አጼ ሚኒሊክን የሚጠሉ ቡድኖች የዱሮውን ሥርአት መልሰው ሕዝቡን በጎሣና በአካባቢ ለማጫረስ የሚፈልጉ እርኩስ መንፈስ የሰፈረባቸው ሰዎች ናቸው:: ኢትዮጵያችን እንደሀገር እንዳትቀጥል የሚፈልጉ ታሪካዊ ጠላቶቻችን በገንዘብ የሚገዟቸው ለሀገርና ለሕዝብ ደንታ የሌላቸው የባንዳና በሰው ሲነግዱ የነበሩ የባሪያ ፈንጋይ ልጆች ናቸው:: የኢትዮጵያን አንድነትና ዕድገት የማይወዱ: ደም የጠማቸው ሰው መሰል አጋንንቶች ናቸው:: ለመፍጠር በሚፈልጓቸው ትናንሽ ሀገሮች ለመንገስ የሚያልሙ የስልጣን ጥመኞች ናቸው::

ለንደን ላይ ተሰባስበው ኦሮሚያ ነጻነቷን የምታገኘው ኢትዮጵያ ስትፈራርስ እንደሆነ የተናገሩት ዶክተሮች የአንድነትና የሰላም ነቀርሳወች ናቸው:: አንዳንድ ፕሮግራሙን ያዘጋጁ ናቸው የሚባሉ ሰዎች የሚናገሩት ሊዋጥ የማይችል ነገር አለ:: እኒህ ሰዎች የሚሉት የኦሮሞ ድርጅቶች በሙሉ ተሰባስበው ወደአንድ የሚያስማማ ነገር እንዲመጡ ከተደረገ በኋላ ያን የተስማሙበትን የጋራ አቋም ይዘው ከሌሎች ድርጅቶች ጋር ለመወያየት እንዲያስችላቸው ነው ስብሰባው ያስፈለገው:: “መጀመሪያ ኦሮሞወች አንድ መሆን አለብን:: ከዚያ በኋላ ከሌላው ኢትዮጵያ ጋር እንወያያለን” ነው የሚሉን:: “የተለያየ አመለካከት ያላቸው ሰዎች ሀሳባቸውን ያለገደብ እንዲያቀርቡ የተደረገው ችግሮቹን ሁሉ አውጥቶ ለመወያየት እንዲያስችለን ነው:: ጉባዔው ላይ የተነገረው ማህበሩንም ጉባዔተኛውንም አይወክልም። የመገንጠል ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ያቀረቡትን ሀሳብ ብቻ ነጥሎ በማውጣት የፖለቲካ ሥራ ተሰርቶብናል” ሲሉም ይደመጣሉ:: እሽ ተናጋሪወችን እንተዋቸውና አጨብጫቢወቹን ምን እንበላቸው:: ሁላችንም የተረዳነው ያ ሁሉ ሰው ያጨበጨበው ተናጋሪወቹን ለመቃወም ሳይሆን ለመደገፍ ነበር: የተናገራችሁት ነገር የእኛም ፍላጎት ነው ለማለት ነበር:: አይደለም እንዴ? ማን ያላጨበጨበ አለ? “ተጨበጨበ ማለት ተስማማ ማለት አይደለም” የሚሉን ጭብጨባው የተቃውሞ ነበር ለማለት ነው? የሚገርም ጊዜ! አንድ ጠንካራ የኦሮሞ ድርጅት ፈጥሮ የመገንጠል ህልምን ለማሳካት የሚደረገው ዘመናዊ አካሄድ የተቃዋሚውን ኃይል በመበተን ወያኔን ከመጥቀም ውጪ የቀን ህልማችሁን የሚያሳካ አይሆንም:: ምክንያቱም አንደኛ ድርጅቶቹ የቀድሞው ንዑስ ጎሣ ስሜት የተጠናወታቸው በመሆናቸው በምንም አይነት ውይይት በአንድነት ሊቆሙ የማይችሉ መሆናቸው ሲሆን ሌላውና ዋናው ግን የኦሮሞ አባቶች ደምና አጥንት የከፈሉላትን ሀገር በጥቂት ወስላቶች ቅስቀሳ ተታለው የኦሮሞ ልጆች ሊያፈርሷት ስለማይነሱ ነው:: በደም የተጻፈውን የጋራ ታሪካችንን ሊያጠፉ ስለማይፈቅዱ ነው:: አንድነታችን አይደለም እንዲበጠስ እንዲላላም ስለማይፈልጉ ነው::

በሌላ በኩል በአራት የፖለቲካ ድርጅቶች የኢትዮጵያ ሃገራዊ ንቅናቄ ከሦስት ቀናት በፊት ተመስርቷል:: ንቅናቄውን ከመሰረቱት ድርጅቶች መሀል የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዴፍ)፣ የአፋር ህዝብ ፓርቲ፣ እና የሲዳማ ህዝቦች ዴሞክራሲያው ንቅናቄ የጎሣ ድርጅቶች ሲሆኑ አርበኞች ግንቦት 7 ጎሣ-አልባ የሆነ ማለትም የትኛውንም ጎሣ ደግፎ ያልቆመ ኢትዮጵያዊ ድርጅት እንደሆነ ነው የሚታወቀው:: በሜሪላንድ ሲልቨር ስፕሪንግ ከተማ በተካሄድው ስነስርዓት የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ሊቀመንበር አቶ ሌንጮ ለታ፣ የአርበኞች ግንቦት ሰባት ሊቀመንበር ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ የአፋር ህዝብ ፓርቲ ሊቀመንበር ዶ/ር ኮንቴ ሙሳ እና የሲዳማ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ሊቀመንበር አቶ በቀለ ዋዮ ፊርማቸውን በማስቀመጥ ንግግር አድርገዋል። ፕሮፌሰር ብርሃኑ በትግል ሜዳ ላይ ናቸው በሚል ንግግር ያደረጉትና ፊርማቸውን ያስቀመጡት በተቀረጸ ምስል ሲሆን ሌሎች የንቅናቄው አባላት በአካል ተገኝተዋል። በሕዝብ ብዛት ከኢትዮጵያ ሁለተኛ ደረጃን የያዘው አማራ እንደድርጅት ንቅናቄውን እንዲቀላቀል ጥሪ ያልተደረገለት አማራውን የሚወክል አንድ ጠንካራ ድርጅት ባለመፈጠሩ መሆኑ ተነግሯል:: ከተለያዩ የኦሮሞ ድርጅቶች ጋር ድርድር ሲያደርግ የነበረው አስተባባሪ ኮሚቴ የአማራ ድርጅቶች እንዴት ሊበዙበት እንደቻለ ግልጽ አይደለም:: ያም ሆኖ በኢሕአዴግ ጊዜ ከነበረው የሽግግር መንግሥት በተሻለ ሁኔታ አማራው በአንድ ሰውም ቢሆን ተወክሏል:: ለነገሩ ያህል ነው እንጅ የአማራ ድርጅትም ሆነ የአማራ ተወካይ በእንደዚህ አይነት መድረክ መገኘቱ ተገቢ ነበር ለማለት አይደለም:: ምክንያቱም ይህ ንቅናቄ ኢትዮጵያዊነት ስለሚጎድለው የትም አይደርስም ብለን ስለምናስብ ነው:: እስቲ አስቡት! የአፋርና የሲዳማ ድርጅቶች የትግል አርማ ይኖራቸዋል ብለን እናምናለን:: በዚህ ስብሰባ ላይ ግን በኢትዮጵያዊነታቸው የሚኮሩ በመሆናቸው በሀገራቸውን ሰንደቅ ስር ሆነው ነው ስብሰባውን ያካሄዱት:: ኦዴፍ ያደረገው ምንድን ነው? የኦነግ ሰንደቃላማ ምን መልዕክት አለው? በምስረታው ላይ የታዩት የኢትዮጵያና የኦነግ ሁለት ሰንደቅአላማወች ልዩነትን እንጅ በምንም አይነት ትርጉም አንድነትን አያሳዩም:: ፉክክርን እንጅ ትብብርን አያመለክቱም:: ሁለቱን ሰንደቃላማወች አትዩ ብለው ሊያሳምኑን ቢፈልጉም አይዋጥልንም:: ንግግራቸውም አይጥመንም:: በተግባርም እነማን እንደሆኑ እናውቃቸዋለን:: የአንድነት ኃይሎች ከሚባሉት ውስጥ ኢትዮጵያ የሚለውን ስም ያላካተተ ድርጅት ግንቦት 7 ብቻ ሳይሆን ይቀራል? የአንድነት ድርጅቱ አርበኞች ግንቦት 7 ለምን ከጎሣ ድርጅቶች ላይ መጣበቅ ፈለገ? ከአንድነት ኃይሎች ጋር ተባብሮ ለመስራት ቢል ቢል አልሳካለት ብሎ ደክሞት ትቶት ነው? በልዩነትና በአንድነት መሀል ምን አይነት የሚያስማማ ስራ መስራት ይቻላል? የኦሮሞ ሕዝብ በኦነግ በኩል ካልመጣችሁ አንሰማችሁም ብሏል?

አማሮች በአማራነታቸው መደራጀታቸውን ለአፍታም እንኳ እንደስጋት የሚያይ ካለ እርሱ ያልተገለጠ ድብቅ ፍላጎት ያለው መሆን አለበት:: ኦሮሞው: ሶማሌው: አፋሩ: ሲዳማው:  ቤንሻንጉሉ- – – በዘሩ ሲደራጅ ቃል ያልተነፈሰው ሁሉ አማራው በዘሩ መደራጀት ሲጀምር መጮህ መጀመሩ ለምን እንደሆነ ግልጽ አይደለም:: አማራው በአማራነቱ  የተደራጀው የዘረኝነት አባዜ ስለተጠናወተው ሳይሆን ጠላት ነው ተብሎ ስለተፈረጀ ነው:: ዘሩ መጥፋት አለበት ተብሎ የተወሰነበት በመሆኑ ነው:: በተለያየ መንገድ የዘር ፍጅት እየተፈጸመበት ስለሆነ ነው:: እንዲደራጅ ያስፈለገው በአንድነት ተሰልፎ ራሱን ከጥቃት መከላከል እንዲችል ነው::

በሚሊዮን የሚቆጠር አማራ ዳብዛው ሲጠፋ: በአስር ሽወች የሚቆጠሩ ሲገደሉ ማን ደረሰላቸው? በሀገራቸው ባይታወር ሆነው ለዘመናት ከኖሩበት ቦታ ምንም ነገር ሳያንጠለጥሉ ሲባረሩ ማን ዞር ብሎ አያቸው:: አንጀታቸው በርሀብ ታጥፎ የሳምንታት የእግር መንገድ ሲጓዙ ማን አይዟችሁ አላቸው:: ተፈናቃይ ናቸው የተባሉት ትግሬወች ውሀ ሳይጠማቸው መንገድ ሳይመታቸው እየበሉ እየጠጡ በመኪናና በአውሮፕላን ነው የተጓጓዙት:: የመቋቋሚያ ተብሎ ከየክልሎች ሳይቀር በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ነው የፈሰሰላቸው:: አማራማ ምን ያልሆነው አለ! ነገሥታቱ ፈጽመውታል ለተባለው በደል የአማራ ሕዝብ ቀጥተኛ ተጠያቂ ሆኖ ባልሰራው ስራ ባልዋለበት ሀጢያት መታረድ መሳደዱ ሳያንሰው ይባስ ብሎ የአማራውን ሕዝብ ይወክላሉ የተባሉ አማሮች መጀመሪያ ኤርትራ ድረስ ሄደው ሻእቢያን ይቅርታ እንዲጠይቁ: አሁን ደግሞ ጥቂት የትግራይ ሰዎች ከአማራ ክልል ተፈናቅለዋል በሚል ትግራይ ድረስ ሄደው “ለጠፋው ጥፋት ሁሉ በደሉ የእኛ መሆኑን እናምናለን: ማሩን!” ብለው ከአባይ ወልዱ እግር ላይ ወድቀው እንዲለምኑ አልተደረገም? ከዚህ የበለጠ መረን የለቀቀ ግፍ ምን አለ?

ከምንም በላይ ችግር አስተማሪ ነው:: አማሮች በአንድነት መቆም ካልቻላችሁ በየቦታው እንደጨው ዘር ተበትናችሁ ማለቃችሁ አይቀርም:: ከየአካባቢው የሚሰማው ደወል አማራው ከተኛበት እንዲነሳ የሚጠራ “ንቃ!” የሚል የአደጋ ጊዜ ጥሪ ነው:: ስለዚህ ወደ አንድ የአማራ ድርጅት ተጠቃላችሁ የሕዝቡን ሁለንተናዊ አቅም አስተባብራችሁ ለነጻነታችሁ መስዋእትነት ክፈሉ:: ሌሎች የአንድነት ኃይሎችም ብትሆኑ የአማሮችን እንቅስቃሴ እንደከፋፋይነት አትዩት:: እንዲያውም ሙሉ ድጋፋችሁን ስጧቸው:: አማሮች አያት ቅድመአያቶአቸው የሞቱላትን ሀገር ለምንም ነገር አሳልፈው ሊሰጡ የማይፈቅዱ የሀገር ማተቦች ናቸው:: የአማራ ልጆች የአንድነት ኃይሎች ነበሩ: አሁንም ናቸው: ወደፊትም ከኢትዮጵያዊነት ደረጃቸው የሚያወርዳቸው ምንም ነገር አይኖርም:: አማራነት እኮ ፍጹም ኢትዮጵያዊነት ነው:: አማራን መደገፍ ኢትዮጵያን ማጽናት ነው:: ይህ ሲባል ሌላው ሕዝብ በኢትዮጵያዊነቱ ይታማል ማለት አይደለም:: ሀገሩን የማይወድ ሕዝብ የለም:: ነገር ግን ሀገራቸውን እንዲጠሉና በሀገራቸው እንዲያፍሩ የሚቀሰቅሱ ኢትዮጵያን የማይወዱ  በትግራይ: በኦሮሞና በሶማሌ ሕዝብ ስም የተደራጁ ድርጅቶች አሉ:: የትኛው የአማራ ድርጅት ኢትዮጵያዊነትን ተጻርሮ ቆሞ ያውቃል? የአማራ ድርጅት መመስረት የሚያሳስብ አይሆንም:: የሚያሳስበው የተለያዩ የአማራ ድርጅቶች መፈጠራቸው ነው:: ይህ አደገኛ አዝማሚያ ታርሞ ወደአንድ የአማራ ፋኖ ድርጅት መጠቃለል ያስፈልጋል:: አንድ የአማራ ጠንካራ ድርጅት መመስረት የአማሮችን ጥቃት ለመከላከል ብቸኛ አማራጭ ነው:: ከየአቅጣጫው የሚወረወርበትን ጦር መመከት የሚችለው በአንድነት መቆም ሲችል ነው:: ማደራጀት: ማንቃት: መሰረታዊ የውጊያ ትምህርት መስጠት: ማስታጠቅ: የውጊያ ሞራልን መገንባት አሁኑኑ መጀመር ያለባቸው አቢይ ሥራወች ናቸው:: ጠንካራ ሆኖ ሲገኙ ብቻ ነው ራስንና ሀገርን ከጥቃት ለመታደግ የሚቻለው:: ከጥቂት ጊዜ ወዲህ በክልሉ እየተደረጉ ያሉት ንቅናቄወች የአማራውን አንገት ቀና ያደረጉ ናቸው ብንል ከእውነቱ መራቅ አይሆንም::

የአንድነት ኃይሎችም ብትሆኑ ከእድሜና ከተሞክሮ ተምራችሁ ስህተታችሁን አርሙ:: ለጎሣ ድርጅቶች የምታደርጉትን ልምምጥ አቁሙ:: በአንድነት መቆም የማይችሉ ቡድኖች ላይ ጊዜ ከማባከን ወጥታችሁ ራሳችሁ በአንድነት ለመቆም ጣሩ:: ዋና አጀንዳችን ኢትዮጵያ ናት የሚለው አርበኞች ግንቦት 7 ከኢሕአፓ እና ከሌሎች የአንድነት ኃይሎች ይልቅ እንዴት ኦነግ ሊቀርበው ይችላል? የሻእቢያ ተጽእኖ ይኖር ይሆን!

የጎሣ ድርጅቶች ይጐዷችኋል እንጅ ለምንም ነገር አይጠቅሟችሁም:: ወያኔ የአንድነት ኃይሎችን የሚያስፈራራው በእነዚህ የጎሣ ድርጅቶች ተማምኖ ነው:: ሁኔታወች እየጠነከሩ ሲመጡ ጥሪ የሚያደርገው ለማንም ሳይሆን ለእነዚህ የጎሣ ድርጅቶች ነው:: “የራሴን ክልል ልገነጥል ስለሆነ ኑና የናንተን ድርሻ ተረከቡኝ:: የአንድነት ኃይል ነኝ እያለ የሚረብሸውን ወገን ለመከላከል እጅ ለእጅ እንያያዝ” የሚል ጥሪ ቢያደርግ ብታምኑም ባታምኑም መሀል ሜዳ ላይ ገትረዋችሁ ይሄዳሉ:: ጊዜ ካለፈ በኋላ ቢንደፋደፉት ዋጋው ይከብዳል:: ከጎጠኞች ጋር የምታደርጉት የወረት ፍቅር በፍጹም ዘላቂ አይሆንም:: በአላስፈላጊ ጉዳይ ጊዜ በማባከን ተጎጅወች የሚሆኑት ትናንሽ መንግሥታት መስርተው ሕዝቡን ለማለብ የሚያልሙት የጎሣ ድርጅት አመራሮች ሳይሆኑ ሀገርና ሕዝብ ናቸው:: ለእነርሱማ መኖራቸው እንኳ አይታወቅ ለነበረው ሳይቀር የፕሮሞሽን ሥራ እየሰራችሁላቸው ነው:: ከኢትዮጵያ የበለጠ የጋራ አጀንዳ የለንም የምትሉ ሁሉ ልዩነታችሁን በሕዝብ እንዲዳኝ ለይደር ትታችሁ ሀገር በማዳን ተግባር ላይ በአንድነት ቁሙ:: ከአንድነት ይልቅ ልዩነትን ከሚያቀነቅኑ የጎሣ ድርጅቶች ጋር ግንባር ለመፍጠር በሚል ጊዜ ማባከን ሙና መሆን ነው:: ሙና ማለት የዋህ: ሞኝ: ሁልጊዜ የሚበለጥ: ተላላ: አድሮ ቃሪያ እንደማለት ነው:: በዋናው አጀንዳ ላይ ልዩነት የለንም የምትሉ ቡድኖች አንድ ሳትሆኑ በዋናው አጀንዳ ላይ ከማይስማሙት ጋር ግምባር ለመፍጠር መሯሯጥ ትርጉም አይሰጥም:: እባካችሁ እባካችሁ የጐጥ ድርጅቶችን ከነመፈጠራቸው እርሷቸውና እናንተው አንድ ለመሆን ስሩ:: እባካችሁ እባካችሁ በልዩነት ላይ የቆሙትን ቡድኖች እርሷቸውና ፊታችሁ ወደሕዝብ አዙሩ:: እባካችሁ እባካችሁ ለኢትዮጵያ አንድነት ያላችሁን የማይናወጥ አቋም በአፋችሁ ሳይሆን በተግባራችሁም አስመስክሩ::

ትንሳኤ ለኢትዮጵያ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.