የቀበና ችግኝ ጣቢያ ቦታ ለወ/ሮ አዜብ መስፍን ቤት መስሪያ ተሰጠ

azeb-satenaw-newsጥቅምት ፳፭ (ሃያ አምስት) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከ10 ሺ ካሬ መሬት በላይ ስፋት ያለው የቀበና ችግኝ ጣቢያ ተነስቶ ፣ ቦታው ለወ/ሮ አዜብ መስፍን መኖሪያ ቤት መስሪያ ተሰጥቷል። ግንባታው የሚካሄደው በመንግስት ወጪ ሲሆን፣ ወ/ሮ አዜብ ቦታውን በስማቸው አዙረዋል።የጠ/ሚኒስትር ጽ/ቤት ለአዲስ አበባ ከንቲባ ጽ/ቤት ቦታውን ለቤተመንግስት ሰዎች እንዲያስረክብ የተጠየቀበት፣እንዲሁም የከንቲባ ጽ/ቤት ለቦሌ ክፍለ ከተማ መስተዳደር የጻፉዋቸው ደብዳቤዎች እና ሌሎችም መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ የችግኝ ማፍያ ጣቢያው በያመቱ ከ100 ሺ በላይ ችግኞችን ለክፍለከተማው ያቀርባል።

የቀበና ችግኝ ጣቢያ በቦሌ ክ/ከተማ ከአትላስ ወደ ደሳለኝ ሆቴል በሚወስደው መንገድ ከአውሮፓ ህብረት ልኡክ ጽ/ቤት አጠገብ ባለው መንገድ ወደ ውስጥ ገባ ብሎ ይገኛል። ድርጅቱ  20 ቋሚ ሰራተኞችና ከ20 እስከ 30 የሚደርሱ ጊዜያዊ ሰራተኞች አሉት። 5 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎለት ከተሰራ በሁዋላ፣ በውስጡ ግሪን ሃውስ፣ የሰራተኛ መታጠቢያና ባኞ ቤት፣ የጥበቃ ቤት፣ አፍረና ኮፕስት መቀላቀያ ቤት፣ ሴፕቲክ ታንክ፣ እና የተለያዩ ትላልቅ ታንከሮች ያሉበት እንዲሁም ቦታው ለችግኝ ማፍያነት እንዲያመች ተደርጎ የተሰራ ነው። ይህ ዘመናዊ የችግኝ ማፍያ ቦታ ተነስቶ ቦታው በትእዛዝ ለቤተመንግስት ሰዎች እንዲሰጥ የጠ/ሚኒስትር መ/ቤት ጥር 12 ቀን 2008 ዓም በቁጥር መ30/7/851/1.5 የአዲስ አበባ ከንቲባ ለሆኑት አቶ ድሪባ ኩማ ሄይ ትእዛዝ ጽፏል።

አቶ ድሪባ ኩማ ለአዲስ አበባ ዋና ስራ አስኪያጅ የካቲት 21 ቀን 2008 ዓም በጻፉት ደብዳቤ በአዋጅ 653/2001 መሰረት ለሚገነባው የመኖሪያ ቤት አግልገሎት የሚውል 3ሺ 500 ካሬ ሜትር መሬት በቦሌ ክ/ከተማ ወረዳ 03 የቀድሞ ቀበሌ 10 የአዲስ አበባ ችግኝ ጣቢያ ያለበት በታ ተዘጋጅቶ ለቤተመንግስት አስተዳደር እንዲረከብ የጠ/ሚኒስትር መ/ቤት በቀን 12 ጥር 2008 በጻፈው ደብዳቤ መሰረት ያሳወቀን በመሆኑ፣ በዚሁ መሰረት ጣቢአውን ማስነሳት የግድ ስለሚል ችግኝ ጣቢያው የሚያስተዳደረው ተቋም አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት በማድረግና ለችግኝ ጣቢያው የሚያስፈልገውን ምትክ ቦታ በመረከብ በቦታው ያለውን ንብረት እንዲያነሳ እንዲደረግና በአስቸኳይ ቦታውን ለመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ እንዲያስረክብ እያሳወቀኩኝ የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ እና የቤተ መንግስት አስተዳደርም ለተፈጻሚነቱ ክትትል እንዲያደርጉ ግልባጭ ተደርጎላቸዋል።” የሚል ደብዳቤ ጽፈዋል።

ምንም እንኳ አቶ ድሪባ የጻፉት 3 ሺ 500 ካሬ ሜትር መሬት እንዲሰጥ ቢሆንም፣ ከፒኮክ መናፈሻ ጋር የተያያዘው የችግኝ ማፍያ ጣቢያ ስፋት ከ10 ሺ ካሬ ሜትር በላይ መሆኑንና ችግኞችን በማውደም የግንባታው ስራ መጀመሩ ታውቋል። በውስጥ የሚገኙ ችግኞች እየወደሙ ሲሆን፣ ተቆርቋሪ ወገኖች “ ህዝቡ ወጥቶ የህዝብና የመንግስት ንብረትና ሃብት እንዲጠበቅ፣ ሰራተኞች ወደ ስራቸው እንዲመለሱና የተሰጠው መሬትም በአፋጣኝ እንዲመለስ ጠይቀዋል።

ጉዳዩን በቅርብ የሚከተታሉ ወገኖች ፣ወ/ሮ አዜብ የመኖሪያ ቤት መስሪያ በግለሰቧ ስም የተመዘገበ ቤትና ንብረት የላትም በሚል መሬቱ የተሰጣቸው መሆኑን ጠቅሰው፣ በአለማቀፍ ደረጃ አረንጓዴ ኢኮኖሚ እንፍጠር በሚባልበት ፣ የህዝብና የመንግስት ሃብት እንዲጠበቅ በሚለፈፍበት ወቅት ፣ ገዢው ፓርቲ ሰራተኞችን በመበተን የህዝብን ሃብትና ንብረት ለግለሰብ መስጠቱ ህገወጥ ነው ይላሉ።

በአዲስ አበባ ውስጥ በአሁኑ ሰአት አንድ ተራ ግለሰብ ለቤት መስሪያ የሚሆነውን 91 ካሬ ሜትር ቦታ ባጣበት ሁኔታ፣ 109 አባወራ ሊያኖር የሚችልን ቦታ ለአንድ ግለሰብ መስጠት ግልጽ ዝርፊያና ኢፍትሃዊነት ነው በማለት ተቆርቋሪ ወገኖች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። የህወሃት ኢህአዴግ ባለስልጣናት በአዲስ አበባና አካባቢዋ እጅግ ሰፋፊ መሬቶችን መያዛቸው ይታወቃል። ወ/ሮ አዜብ መስፍን በእርሳቸውና በዘመዶቻቸው በቢሊዮን የሚቆጠሩ የግልና የህወሃት የንግድ ድርጅቶችን ያንቀሳቅሳሉ። የሙስና እናት የሚል ስያሜ ያገኙት ወ/ሮ አዜብ፣ መንግስታዊ ስልጣን ባይኖራቸውም በኢፈርት ስምና በግል ከሚያንቀሳቅሱት ሃብት ጋር በተያያዘ አሁንም ድረስ በህወሃት ፖለቲካ ውስጥ የማይናቅ ተጽኖ አላቸው።

በሌላ በኩል በለገጣፎ፣ ለገዳዴና ሌሎችም አካባቢዎች አሁንም የቤት ማፍረስ  ዘመቻው አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተገን አድርጎ በመካሄድ ላይ ሲሆን፣ ትናንት በገዎሳ፣ በአቆርጫና በማዞሪያ ከ50 በላይ ሰዎች ተይዘው ታስረዋል።

ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የፌደራል ፖሊስ አባላትና የአጋዚ ወታደሮች አካባቢውን ከበው ቤቶችን እያስፈረሱ ሲሆን፣ ትናንት ምሽትና ዛሬ ወደ አካባቢው የሚንቀሳቀሰውን እንዲሁም ከምሽቱ 12 ሰአት በሁዋላ ሲዘዋወር የተገኘውን ወጣት ሁሉ እየደበደቡ በማሰር ላይ ናቸው።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.