ለአዋጁ አዋጅ ፤ [ይገረም አለሙ]

stateofemeኢትዮጵያውያን  ለሀያ አምስት ኣመታት ባካሄድነው ትግል  ከወያኔ አገዛዝ መላቀቅ አልቻልንም ፡፡ በዚሁ መንገድና ስልት ቀጥሎም ከወያኔ አገዛዝ መላቀቅ እንደማይቻል ከመቼውም ግዜ አሁን ግልጽ ሆኗል፡፡ ህዝቡ በራሱ ተነሳሽነትና መንገድ ባካሄደው ትግልና እሱን ተከትሎ ወያኔ የወሰደው የአስቸኳይ ግዜ ርምጃ በግልጽ ያሳየንም ይህንኑ ነው፡፡ ስለሆነም እስካሁን በተከተልነው አሰራርና በተጓዝንበት መንገድ  ከወያኔ አገዛዝ ለመገላገል  አንደማይቻል በመረጋገጡ ባለተሄደበት መንገድ ለመሄድ ይቻል ዘንድ ከህዝቡም በኩል የአስቸኳይ ግዜ ማወጅ አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡በዚህ የምትስማሙ ከዚህ በታች በቀረበው  መነሻ ሀሳብ ላይ አስተያየት ስጡበት፡፡

አንቀጽ 1- የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ አስፈላጊነት፤

ወያኔ የሥልጣን እድሜውን ለማራዘም ያስችለኛል ያለውን ግድያ እስራትን ሽብር ህጋዊ አድርጎ ለመቀጠል የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ አውጥቷል፡፡  በዚህ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ሽፋን በህዝብ ላይ እየፈጸማቸው ያለውን እኩይ ድርጊቶች ማስቆምና  ወደ ፊትም ሊፈጽማቸው ያሰባቸውን ማክሸፍ መቻል  ለዘላቂው ድል መንገድ ጠራጊ ርምጃ በመሆኑ ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ይቻል  ዘንድ  የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ መውጣት አስፈላጊ ሆኗል፡፡

አንቀጽ 2-የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ዓላማ፣

የዚህ አዋጅ ዋና ዓላማ በኢትዮጵያ ሀገራዊ ሉአላዊነትና በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባት የሚያምኑ ነገር ግን ተበታትነው የሚገኙ ኃይሎችን በመለየት በመካከላቸው ያለውን   የዓላማ ሳይሆን ከመሪዎች  ግላዊ ፍላጎት የሚመነጭ ልዩነት    በማስታረቅ የተባበረ ጠንካራ ኃይል ፈጥሮ የህዝቡንም ትግል አቀናጅቶ   የወያኔን የአገዛዝ ዘመን የሚያሳጥር ትግል ማድረግ ማስቻል ነው ፡፡

አንቀጽ 3 በአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ወቅት  የሚከናወኑ ተግባራት

 1. የአደረጃጀት እንዴትነትም ሆነ የትግል ስልት ምንነት ትብብር ለመፍጠርም ሆነ ተደጋግፎ ወደ ድል ለማምራት አንቅፋት ሊሆን አይችልም፡፡ ስለሆነም ድርጅቶች ሁሉ በመሪዎቻቸው ኪስ ውስጥ የሚገኘውን የግል አጀንዳ አስቀምጠው ወያኔን ማስወገድን መነሻው፣ ዴሞክራሲያዊት ሀገር መመስረትን  መድረሻ ግቡ ያደረገ ትብብር መስርተው  በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የተጠና የተቀናጀና የተጠናከረ ትግል ማቀጣጠል፡፡
 2. የየድርጅት ደጋፊዎች ከጠባብ የድርጅት ፍቅርና ከግለሰብ አምልኮ በመላቀቅ ትግላቸውንም ሆነ ድጋፋቸውን  ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባት ለሚደረገው ትግል በጋራ ማዋል፤
 3. ምሁራን እንደ እውቀት ዝንባሌያቸው በመሰባሰብ ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የሚያሸጋገር መንገድ ማዘጋጀት፣
 4. ሁሉም ድርጅቶች ከወያኔ በኋላ ምን አይነት ኢትዮጵያን እንደሚሹ እንዴትስ እውን እንደሚሆን መክረውና ዘክረው በሰነድ የተዘጋጀ አቋማቸውን በግልጽ ማሳወቅ፡፡
 5. በሀገራዊም ሆነ በብሄር ከተደራጁት መካከል ከምር ወያኔን ለማስወገድ የሚታገሉ አለመኖራቸው ከፍሬአቸው እየታየ በመሆኑ  እነዚህን መለየት አንዲስተካከሉ መምከር ሳይሆን ሲቀር ትግሉ በእነርሱ አንዳይደናቀፍ ማጋለጥ፡
 6. ግልጽ ዓላማና የትግል ቁርጠኝነት አንግበው ከምር ለለውጥ የሚታገሉትን ለይቶ ማወቅና መርዳት፤
 7. ትግሉ በትብብርና በመደጋገፍ አንዳይካሄድ የሚያደርጉ የየድርጅት አመራሮችን  በመምከርም ሆነ በማስገደድ ከእስከዛሬው ድል አልባ መንገዳቸው አንዲወጡ መስራት እምቢ ካሉ ያለ ድጋፍ ህልውና ሊኖራቸው ስለማይችልና አጥፊዎችን መደገፍ ደግሞ የጥፋት ተባባሪ ስለሚያደርግ ድጋፍ መንሳት፣በግልጽ ማውገዝ፤
 8. በየሀገራቱ የነጻነት ትግሉ የዲፕሎማሲ ቡድን በማቋቋም ተከታታይነት ያለው ስራ መስራት፤
 9. ሁሉም ኢትዮጵያዊ በጋራና በየግል ሊዘምረው የሚችል አንድ የትግል መዝሙር ማዘጋጀት፤
 10. ነጻነት ናፋቂ ኢትዮጵያዊ ሁሉ በያለበት በወያኔ ጎራ የተሰለፉ ወገኖቹ የጥፋት ስራ ተባባሪ እንዳይሆኑ መስራት፤

 

አንቀጽ 4  በዚህ አዋጅ የተከለከሉ ተግባራት፤

 1. ህዝቡ በደሙ ባቀለመው የነጻነት ትግል መደራደር፤
 2. ህዝቡ የፈጠረውን አንድነት የሚቃረንና ልዩነትን የሚያንጸባርቅ የዘር ጥላቻ ቅስቀሳ ማካሄድ፤
 3. በጽሁፍ በንግግር በሌላም መንገድ የነጻነት ትግሉን ሊጎዳ የሚችል ተግባር መፈጸም
 4. የተፈጠሩ ትብብሮች ተጠናክረው አንዳይቀጥሉ ለማሰናክል መሞከር፤
 5. ያለበቂ ምክንያት የትብብር አባል አለመሆን ወይንም ድርጅቶች ወደ ትብብር እንዳይመጡ ማድረግ
 6. አንዱ ድርጅት ወይንም የድርጅት አባልና ደጋፊ በሌላው ድርጅት ላይ የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ ማሰራጨት የጎንዮሽ ትግል ማካሄድ
 7. ጸረ ኢትዮጵያ አቋም ለሚያራምዱ ድርጅቶችም ሆኑ ግለሰቦች ተባባሪ መሆን፣ ድጋፍ መስጠት፤
 8. የወያኔን እድሜ ሊያራዝም የሚችል ተግባር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መፈጸም

 

አንቀጽ 5  የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ተፈጻሚ የሚሆንባቸው ቦታዎች

አዋጁ ኢትዮጵያውያን በሚገኙበት ቦታ ሁሉ ተፈጻሚ ይሆናል፡፡

አንቀጽ ስድስት የአዋጁ አፈጻጸም

ይህን አዋጅ ከሀገር ቤት ሆኖ ማስፈጽም የማይቻል በመሆኑ  አስፈጻሚው አካል በውጪ ሀገር ይሆናል፤

አዋጁን የሚያስፈጽመው በዚህ አዋጅ መሰረት የሚፈጠረው የፓርቲዎች ህብረት አመራር ይሆናል፤

አስፈጻሚው አካል ዝርዝር የተግባር አፈጻጸም መመሪያ ያወጣል፤

አንቀጽ ሰባት የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ቆይታ፣

የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ እስከ ሽግግር ወቅት ድረስ ተግባራዊ ይሆናል፤

አንቀጽ ስምንት የአዋጁ ተፈጻሚነት ፤

ይህ አዋጅ   ከ    ጀምሮ      የጸና ይሆናል፡፡

 

ይህ አዋጅ የህዝቡን የነጻነት ትግል ከግብ ለማድረስ የሚያስችል ከነበረው የተለየ ዘዴም መንገድም ለመከተል አንዲያስችል በህዝቡ ስም የሚወጣና  ኢትዮያውያን ባሉበት ሁሉ ተግባራዊ የሚሆን እንደመሆኑ አፈጻጸሙ ነጻነቴን በሚልና ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን በሚናፍቅ ዜጋ በጎ ፈቃድ ተግባራዊ የሚሆን ነው፡፡

አስፈጻሚው ሀይል ከማስተባበር አቅጣጫ ከማሳየትና ከማቀናጀት ባለፈ አዋጁን ተፈጻሚ ለማድረግ የሚያስችለው አቅምም መንገድም አይኖረውም፡፡

አዳብሩት ወይንም ጣሉት

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.