በአማራ ስም ከተደራጁ ነጻ አውጭ ድርጅቶች ጀርባ ያለው ማንነው? [ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው]

ዓላማውስ ምንድን ነው?

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

የማኅበራዊ የብዙኃን መገናኛዎችን  በአንክሮ የምትከታተሉ ወገኖች  እንደምታስታውሱት ይህ ለአማራ ሕዝብ ተቆርቋሪ መስሎ ኢትዮጵያንና አንድነትን የጣለ ተገንጣይ “የአማራነት” አስተሳሰብ መራገብ ከጀመረ ይሄው ሦስተኛ ዓመት መያዙን ታውቃላቹህ፡፡ በወቅቱ ይህ አስተሳሰብ በድንገት ከየአቅጣጫው በዘመቻ መልክ በአንዴ ሲነዛ ከነበረኝ መረጃ ተነሥቸ በዚህ አስመሳይና ዕኩይ የወያኔ ሸፍጠኛ አስተሳሰብ ወገን እንዳይሰናከል በማሰብ ወዲያውኑ “አዲሱ የወያኔ ዘመቻ!” በሚል ርእስ አንድ ጽሑፍ መልቀቄ ይታወሳል፡፡ ከወያኔ ሰፊ ድካምና ጥረት በኋላ እያደር ይህ የወያኔ መሠሪ አስተሳሰብ መሬት ሊረግጥ የሚችልበት ሁኔታ እየተፈጠረ መሆኑን የሚጠቁሙ አንዳንድ ነገሮችን በመታየታቸው  እንደገና ልመለስበት ተገደድኩ፡፡

ይሄም ምንድን ነው፦ መጀመሪያ ይህ አጥፊ ሐሳብ ይራገብ የነበረው የቤት ሥራው በተሰጣቸው  በወያኔ ካድሬዎች በሐሰተኛ የመጽሐፈ ገጽ መዝገብ (የፌስ ቡክ አካውንት) ነበር፡፡ ከጊዜ በኋላ ግን ይህ ለአማራ ሕዝብ ህልውና ተቆርቋሪ መስሎ የተቀመረ ነገር ግን አማራን ከስረ መሠረቱ የሚያጠፋ አስተሳሰብ ጥቂት የማይባሉ ምኑንም የማያውቁ ስሜት ብቻ የሚጋልባቸውን ጮርቃ ወገኖቻችንን አሳስቶ አስተሳሰቡ በእነኝህ ወያኔ ባልሆኑ የዋሀን ወገኖቻችንም ይራገብ ጀመረ ከዚያም አልፎ ድርጅቶች እየተቋቋሙ አባላትና ደጋፊ እስከማሰባሰብ ተደረሰ፡፡ ይህ ሁኔታም ይህ የወያኔ መሠሪ አስተሳሰብ መሬት እየረገጠ መሆኑን ጠቋሚ ነው፡፡

ለመሆኑ ወያኔ ይሄንን የሚያደርገው ለምንድን ነው? ካልን ስለሁለት ምክንያቶች ነው አንደኛ ከብሔረሰቦች ባለአደራነት ተሰምቶት ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ የሚለው ብቸኛው አማራ ኢትዮጵያን ከጣለ ኢትዮጵያ ባለቤት ተቆርቋሪ ታጣለች ማለት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ባለቤት ተቆርቋሪ አጣች ማለት ደግሞ ወያኔ ሊገዛት የማይችላት ኢትዮጵያ በምትመጣበት ጊዜ ህልውናውንና ደኅንነቱን ለማስጠበቅ፣ ጠያቂ አካል እንዳይኖርበት የኢትዮጵያ መጥፋት ወይም መፈራረስ የግድ አስፈላጊ ነው ብሎ በማመኑ ሲሆን፡፡ ሌላው ደግሞ አማራን ጠብቆት ከኖረው ታማኝ የዚህች ሀገር ባለአደራነት ለማንጠብ ለማስፎረሽና  አማራ በሚጠፋበት ወጥወድ ውስጥ ለመጣል ነው፡፡

ለመሆኑ እንዴትና ለምን ይህ የወያኔ አስተሳሰብ ጥቂት በማንላቸው የዋሀን ወገኖች ተቀባይነት ሊያገኝ ቻለ? ብለን መጠየቅ ያለብንም ይመስለኛል፡፡ ምክንያቶቹ የሚከተሉት ናቸው፦

1ኛ. አማራ ኢትዮጵያን ከጣለ እራሱንም እንደሚያጣ ያልገባቸው ወገኖች አዛኝ መስለው ማንነታቸውን ደብቀው በቀረቡ የወያኔ/ብአዴን ካድሬዎች “አማራ እስከመቸ ድካሙንና መሥዋዕትነቱን ማንም ዋጋ ላይሰጥለት ብቻውን ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ እያለ ልጆቹን መሥዋዕት እያደረገ ሲያስፈጅ ይኖራል? እንደጠላት ከመቆጠር በስተቀር ምን አተረፈለት? ይሄው ህልውናው ሳይቀር አደጋ ላይ ወደቀ፡፡ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ አንድነት አንድነት ከማለት ያተረፈው ይሄንን ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ግን መሞኘት የለበትም! የአማራን ደም የምትጠጣ ኢትዮጵያ ገደል ትግባ! አማራ ለራሱ ህልውና ማሰብ ራሱን ማዳን አለበት!” ወዘተረፈ. የሚለው የወያኔ የጥፋት ስብከት አስመሳይ የአዛኝነት የተቆርቋሪነት ስሜት የታጀለ ስለሆነ በዚህ በመታለል፡፡

2ኛ. ወያኔ ትውልዱ ባለአደራነቱን ሊያውቅ ሊረዳ የሚችልበትን፣ የሀገር ፍቅርና የአርበኝነት ስሜት ሊሞላ የሚችልበትን፣ ታሪካዊና የዜግነት ግዴታውን ሊገነዘብ የሚችልበትን የታሪክ ትምህርት ከመጀመሪያ ደረጃ እስከ ዩኒቨርስቲ (መካነ ትምህርት) ባጠቃላይ ከሀገሪቱ የትምህርት ሥርዓት ጨርሶ እንዲጠፋ በማድረጉና የሀገር ፍቅርን የባለአደራነትን የአርበኝነትን ስሜትና ኃላፊነት በትውልዱ ላይ ስትሞላ የነበረችውን የኢትዮጵያን ቤተክርስቲያን አንደበትም ከላይ እስከታች በመቆጣጠር ይሄንን ታሪካዊ ተግባሯንና ኃላፊነቷን እንዳትወጣ አንደበቷን ስለዘጋው ትውልዱ እየተሞላ ያለው የወያኔን ጠባብነትና ፀረ አንድነት የጥፋት ስብከት ብቻ በመሆኑ፡፡

3ኛ. አስቀድሞ ፋሺስት ጣሊያን በዘመናችን ደግሞ ወያኔና ሌሎች የጥፋት ኃይሎች ለጥፋት ዓላማቸው የአማራን ሕዝብ ስም ለማጥፋትና አማራን ለማስጠቃት በአማራ ሕዝብ ላይ ለበቀል የሚያነሣሣ በሰፊው ሲያስወሩት የኖሩትና እያስወሩት ያሉት የፈጠራ ወንጀል ወሬዎች እውነት ስለመሰላቸው ወሬው የበቀል እርምጃን እንዲፈሩ ስለሚያደርጋቸው ፍርሐቱ የመሰብሰብ ስሜትን ስለሚፈጥርባቸው “ሌላውን ትተን የራሳችንን እንያዝ!” እንዲሉ ስለሚያደርጋቸው፡፡

4ኛ. እነኝህም እንደሌሎቹ ተገንጣይ ክፍሎች ከእውቀት ብስለትና ልምድ ማነስ “እኛም ገንጥለን የራሳችንን ሀገር እንመሠርታለን!” የሚሉት የሀገሪቱ ክፍል ከተገነጠለ በኋላ እንደሀገር ለመቆም የሚያስችል ሁኔታና አቅም የሌለው መሆኑን ካለማወቅ፡፡ የመሳሰሉት ናቸው፡፡

እነኝህን እያንዳንዳቸውን በዝርዝር ማየት ይኖርብናል፦

በተራ ቁጥር አንድ ለተነሣው፦ እነዚህ የዚህ የወያኔ አስመሳይ ፀረ ኢትዮጵያ መርዘኛ አስተሳሰብ ሰለባ የሆኑ የዋሀን ጮርቃ ወገኖቻችን ሊያስተውሉት ያልቻሉት ቁምነገር ቢኖር ምንድን ነው መሰላቹህ ለኢትዮጵያ ጠላት ሆኖ የመጣ የጥፋት ኃይል ለአማራም የማይመለስ መሆኑንና የመጨረሻ ግቡም አማራን ከሀገሪቱ ማጥፋት መሆኑን አያውቁም፡፡ አርቆ የማየትና የማስተዋል ችሎታቸው በእጅጉ የተገየበ ነው፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያን እና አንድነት ማለትን መተው አማራን ከጥፋት የሚታደገው ይመስላቸዋል፡፡ ነገር ግን የጥፋት ኃይሎች ዓላማ ኢትዮጵያንና አንድነትን ከአማራ እጅ ማስጣል ብቻ ሳይሆን እራሱን አማራንም ከመሬቱ አጥፍቶ ሀገሩንና አጠቃላይ እሴቶቹን መውረስ በመሆኑ አማራ ኢትዮጵያንና አንድነትን ጥሎ በጎጥ መሰብሰቡ ለጥፋቱ የተመቸ ቀለበት ወይም ወጥመድ ውስጥ እንዲሆን ያደርገዋል እንጅ አማራን ከጥፋት  አይታደገውም፡፡

እነኝህ ሰዎች የተሸነፉ፣ እጅ የሰጡ፣ ሥነ ልቡናቸው የተሠበረ፣ ምንም እርባና የሌላቸው ልፍስፍሶች ናቸው፡፡ የሚገርመው ከአንዳንዶቹ ወያኔ ለዚህ ዓላማ ከገዛቸው በስተቀር ሁሉም ሊባል በሚያስችል ደረጃ ወጣቶች መሆናቸው ነው፡፡ ወጣትነታቸው ብስለት፣ ልምድ፣ አርቆ ማሰብ፣ ማስተዋል፣ እንዳይኖራቸው አድርጎ ለዚህ ውድቀት ቢያጋልጣቸውም ወጣትነት ልበሙሉነትና የጀብደኝነት ስሜት የሚጎላበት የዕድሜ ዘመን ሆኖ እያለ እንዴት እንዲህ ዓይነት የመሠበርና የተሸናፊነት ሥነልቡናና ስሜት ሊነግሥባቸው እንደቻለ እጅግ በጣም ነው የሚገርመኝ፡፡ ከዚህም በላይ ደግሞ በዚህ ድውይ ወያኔአዊ  አመለካከታቸው ከአማራነት የነጠቡ የጨነገፉ ሽሎች ሆነው እያለ በዚህ ጭንጋፍነታቸው ለጭንጋፍ ዓላማቸው የዚህን ጀግና፣ ቆራጥ፣ በሳል፣ ብልህ፣ አስተዋይ፣ አርቆ አሳሳቢ፣ ባለታሪክ ሕዝብ የአማራን ስም ለመጠቀም እንዴት ድፍረት እንዳገኙ ብቻ ነው እጅግ የሚገርመኝ ነገር፡፡

በሁለተኛ ላይ ለተነሣው ምክንያት፦ ወያኔ የታሪክ ትምህርትን ከትምህርት ገበታ ያጠፋበት ምክንያት ግልጽ ነው፡፡ ማንነቱን የማያውቅ፣ በማንነቱ ኩራት የማይሰማው፣ የሀገር ፍቅር ስሜት የሌለው፣ ኃላፊነቱን ባለአደራነቱን የማይረዳ አልጫ ትውልድ እንዲፈራ እንዲወጣ እንዲፈጠር ነው፡፡ ትውልዱ እንዲህ ካልሆነ በስተቀር ወያኔ የጥፋት አስተሳሰቡን በትውልዱ ላይ ማስረጽ እንደምይችል አሳምሮ ያውቀዋልና ነው፡፡ በመሆኑም ነው ከዓመታት በፊት በአማራ ስም ነጻ አውጪ ወይም ተገንጣይ ድርጅት መመሥረቱ ፈጽሞ የማይታሰብ የነበረው ነገር ዛሬ ወያኔ የሰለበው ስልብ ትውልድ በመውጣቱ እውን ሆኖ በማኅበራዊ የብዙኃን መገናኛ እየተራገበ ያለው፡፡ እነኝህ ተገንጣይ ድርጅቶችን አቋቋምን የሚሉ ወጣቶች ከፊሎቹ በወያኔ ዘመን የተወለዱ ከፊሎቹ ደግሞ በደርግ ቢወለዱም በወያኔ ዘመን ነፍስ ያወቁ በወያኔ ትውልድ ገዳይ የትምህርት ሥርዓት ተኮላሽተው የወጡ ናቸው፡፡ ሥራቸውም እያሳየን ያለው ይሄንኑ ነው፡፡ እዚህ ላይ አንድ ሳላስገነዝብ ማለፍ የማልፈልገው ነገር ቢኖር አንዳንድ ይህ ክሴ የማይመለከታቸው ምስጉን ቤተሰቦች መኖራቸው ሳይረሳ ለዚህ የትውልድ ውድቀት ኪሳራ ኅብረተሰቡም ተጠያቂ መሆኑን ነው፡፡ አንደኛ ትውልዱ እንዲህ ሆኖ እንዲወጣ የሚያደርግ ትውልድ ገዳይ ትውልድ መራዥ የትምህርት ሥርዓት ሥራ ላይ ሲውል በጽኑ መቃወምና ውድቅ እንዲሆን ማድረግ ሲኖርበት አለማድረጉ ሲሆን ሌላው ክፍተቱን በግሉ ለመሙላት ማለትም ልጆቹ የሀገር ፍቅር የሌላቸው አልጫና የመከኑ እንዳይሆኑ የተቻለውን ያህል እቤቱ በራሱ ጥረት በማድረግ ክፍተቱን ለመሙላት ጥረት አለማድረጉና ወያኔ የሚያጠጣቸውን ብቻ እንደያዙ እንዲቀሩ በመተው እንዲህ ዓይነት የከሰረ ትውልድ እንድንታቀፍ አድርጎናልና ለዚህ ኪሳራ ኅብረተሰቡም ተጠያቂ ነው፡፡ ያለፈውን መማሪያ በማድረግ ስሕተታችንን አርመን ትውልዱን ለማዳን ለሀገርና ለሕዝብ ጠቃሚ ሆኖ እንዲወጣ ማድረግ የሚጠበቅብንን ሁሉ ማድረግ ይኖርብናል፡፡

ወደ ሦስተኛው ምክንያት ስናልፍ፦ ወያኔና ሌሎች የጥፋት ኃይሎች ሆን ብለው በአማራ ላይ በርካታ የተቀነባበሩ የፈጠራ ወንጀሎች እንዲወሩ እንዲናፈሱ ማድረጋቸው ጥቂት በማይባሉ አማሮች ላይ በተለይም ወያኔና ሌሎች የጥፋት ኃይሎች የሚያስወሩት ለምሳሌ እንደ የአኖሌው የጡት ቆረጣ ያለው የፈጠራ ወሬ ሐሰት መሆኑን የሚረዱበት የሚያረጋግጡበት የታሪክ ዕውቀት የሌላቸው ወገኖች ይህና ሌሎች መሰል የፈጠራ ወሬዎች የጥፋተኝነት ስሜት እንዲጫጫናቸው አድርጎ በወያኔና በሌሎች የጥፋት ኃይሎች የሚፈጸምባቸውን ኢሰብአዊ ግፎች በጸጋ እንዲቀበሉ፣ “ኧረ የታባቷ ደሞ የምን ኢትዮጵያ ነው!” ብለው በታሪካዊ አደራቸው ላይ ክህደት እንዲፈጽሙና ይሄንን እያደረጉት ያለውን ፀረ ኢትዮጵያ የመገንጠል እንቅስቃሴን እንዲያደርጉ አድርጓቸዋል፡፡ ወያኔና ሌሎች የጥፋት ኃይሎችም ይሄንንና መሰል የፈጠራ ውንጀላዎችን በትጋት የሚያደርጉበት ምክንያትም በአማራ ሕዝብ ላይ የፈጸሙትንና ሊፈጽሙት የፈለጉትን ኢሰብአዊ ግፍ በምክንያት ያደረጉት ለማስመሰል ወንጀላቸውን ለመሸፈንና አማራ ኢትዮጵያንና አንድነትን እንዲጥል እንዲተው ለማድረግ ነው፡፡ ይሄንን ካላደረጉ በስተቀር የጥፋት ዓላማቸውን ፈጽሞ ማሳካት አይችሉምና፡፡

እውነታው ግን ከዚህ በእጅጉ የተለየ ነው፡፡ አማራ ለዚህች ሀገር ህልውና እራሱን እንደሻማ ያቀለጠ ሕዝብ ነው፡፡

በተደጋጋሚ መጽሔቶችና ድረ ገጾች ላይ እንደገለጽኩት እርግጥ ነው የሀገሪቱ ማዕከላዊ መንግሥት በውጭና በውስጥ ችግሮች ምክንያት በተዳከመበት ጊዜ የራቀውንና ተረስቶ የቆየውን የሀገሪቱን ክፍሎች የመሰብሰብና ሀገሪቱን በተቻለ መጠን መልሶ አንድ የማድረጉን በዐፄ ቴዎድሮስ የተጀመረውን የተቀደሰ ዓላማና ዘመቻ ዐፄ ምኒልክ ከፍጻሜ ለማድረስ ጥረት በሚያደርጉበት ጊዜ በሰላማዊ መንገድ እንዲመለሱ በተደጋጋሚ ጥረት ተደርጎ በፍጹም ሰሚ በታጣባቸው ቦታዎች የአንድ መንግሥት ተቀዳሚ ኃላፊነት ሀገርንና ሕዝቧን ከውጭና ከውስጥ አጥቂዎች ወይም ጠላቶች መጠበቅ ነውና እርምጃ ከመውሰድ ውጪ ሌላ የቀረ ምንም ዓይነት አማራጭ አልነበረምና ይሄንን በማድረግ ዐፄ ምኒልክ የድርሻቸውን የቤት ሥራ ሀገርን መልሶ አንድ የማድረጉን ተልዕኮ እሳቸውም የቻሉትን ያህል ሰብስበው ባለው መልኩ አጠናቀዋል፡፡ በዚህ  ወቅት ዐፄ ምኒልክ የላኳቸው ከጦሩ ውስጥ ከዘጠና በመቶ በላዩ ኦሮሞ የሆነበት የጦሩ ዋና ኃላፊ ራስ ጎበና ዳጬ ኦሮሞ የሆኑበትን ሠራዊት “በዘመቻው ወቅት ጡት ቆርጧል!” ብሎ መጀመሪያ ፋሺስት ጣሊያን በኋላም ለተመሳሳይ ዓላማ ወያኔ እና ሸአቢያ ያስወሩት ወሬ ፈጠራና ምንም ዓይነት መረጃ የሌለው መሆኑ በተለይ አሁን ላይ በጣም ግልጽ የሆነና በእኔ ብቻም ሳይሆን በሌሎችም ብዙ የተባለበት ሐሰትነቱ የተረጋገጠ ጉዳይ በመሆኑ በጥፋት ኃይሎች የፈጠራ ክስ ዐፄ ምኒልክም ሆኑ አማራ ሊወነጀል አይችልም አይገባምም፡፡

ይህ የወያኔና የሌሎች የጥፋት ኃይሎች የፈጠራ ወሬ የተለየ የጥፋት ዓላማ ያነገበ በመሆኑ ነው እንጅ ሀገርን መልሶ በማዋሐዱ ወይም አንድ በማድረጉ ዘመቻ ወቅት ሁኔታው ግድ ብሎ ያውም ከሰላማዊው ሕዝብ ሕፃን አዋቂ ሴት ወንድ ሳይባል በበርካታ ቤቶች እየታጎረ እንዲቃጠል ከተደረገው በሽዎች ከሚቆጠረው ጎንደሬ አማራ እጣ የከፋ ጉዳት የደረሰበት ማንም የትም የለምና ፈጠራ እየተወራ ለመክሰስ ማንም የሞራል (የቅስም) ብቃት ባልኖረው ነበር፡፡ ወያኔና ሌሎች የጥፋት ኃይሎች ግን ከላይ ለገለጽኩት ዕኩይ ዓላማ ሆን ብለው በማውራት እያየነው ያለውን ስኬት ለማስመዝገብ ችለዋል፡፡ በመሆኑም ወያኔና ሌሎች የጥፋት ኃይሎች የሚያወሩት የፈጠራ ወሬ እውነት መስሏቸው የሚሸማቀቁትን እጅግ የጥፋተኝነት ስሜት የሚሰማቸውንና ከዚህም የተነሣ ኢትዮጵያን አንድነትና አደራን የጣሉትን ወገኖች እውነቱን በመንገር ሥነልቡናቸውን አክሞ በራስ መተማመን እንዲኖራቸው ማድረግና ይህንን የጥፋት ኃይሎች ጥረት በመቀልበስ ረገድም ከባድ ሥራ እንደሚጠይቅ ታውቆ ፈጥኖ መንቀሳቀስ ይገባናል፡፡

በአራተኛ ደረጃ ወደተጠቀሰው ምክንያት ስናልፍ፦ በጣም የሚገርመው ነገር ተገንጣይ ነን የሚሉ የየብሔረሰቡ ቡድን አንድን አካባቢ የራስ አድርጎ መከለል ከተቻለ በቃ ሀገር መሆን የሚቻል እንደ ሀገር ሕዝብን ቀጥ አድርጎ ይዞ መቀጠል የሚቻል ይመስላቸዋል፡፡ የእነኝህ ወገኖች የማሰብ የማስተዋል የማገናዘብ ችሎታ አልባነት ከሚታይበት ጉዳይ አንዱና ዋነኛው ይሄ ጉዳይ ነው፡፡ ለአንድ ሀገር ህልውና እጅግ ወሳኝ የሆነው የባሕር በር ወይም ወደብ ይዛ በመገንጠል ካልተሳካላት ባሕረምድር (ኤርትራ) አይማሩም፡፡ “እሷ ወደብ ኖሯት ያልተሳካላት እኛ ደሞ ሳይኖረን!” ብለው ሐሳባቸው አዋጪ አለመሆኑን አያስቡም፡፡ አንደኛ ጭንቅላታቸው ይሄንን ያህል ርቆና ጠልቆ ማሰብ የሚችል ስላልሆነ ሲሆን ሌላው በሥልጣን ጥማት የሰከሩ በመሆናቸው እከሌ የተባለው አዲሱ ሀገር ምንትስ የሚባል ሥልጣን ለማግኘት ይብቁ እንጅ ሌላው ችግር ግድ የሚሰጣቸው ኃላፊነት የሚሰማቸው ባለመናቸው ነው፡፡ ወይም ደግሞ ኢትዮጵያ ያልቻለችውን የወደብ ኪራይ ተበጣጥሰው የሚመሠረቱት ሀገሮች የሚችሉት ሆነው አይደለም፡፡ ይሄ አንድ ምሳሌ ነው

ያ ሀገር ሲመሠረትስ ዙሪያውን ካሉት ከሌሎች እንደሱ ከተገነጠሉት ጋር ዘላቂ የሆነ ሰላምና መረጋጋት ይኖረዋል ወይ? በድንበር ወሰን ተሻጋሪ በሆኑ በወንዞች አጠቃቀም ዙሪያ በመሳሰሉት ሳይጋጭ ሳይፋጅ በሰላም ነው የሚኖረው ወይስ እንኳን ተገነጣጥሎ “የራሴን ሀገር መሠረትኩ!” ብሎ ይቅርና አብሮ እየኖረ እንኳን “የኔ ድንበር ነው አይደለም የኔ ነው! የኔ መሬት ነው አይደለም የኔ ነው!” በመባባል ሲቆራቆስ እንደመኖሩ ዕድሜ ዘለዓለሙን ዙሪያውን ከየአቅጣጫው ሲፋጅ ሲተላለቅ ለመኖር ነው? እንዲህ ሆኖስ እንዴት ነው እንደሀገር ሊኖር እንደ ሀገር ሊቆም የሚችለው? ፣ ሕዝብን መግቦ ከዚያም አልፎ ከሚቆራቆሳቸው ጎረቤቶቹ ወደ ወደብ መሻገሪያ መድረሻ መንገድ አግኝቶ ወደውጭ ተሸጦ መሠረተ ልማትን ገንብቶ ዘላቂነት ያለውን እድገት ሊያስመዘግብ የሚችል  የተፈጥሮ ሀብትና ተጓዳኝ ፍላጎቶችን ሊያሟሉበት የሚያስችል የተፈጥሮ ሀብት አሉት ወይ?፣ ልዩ ልዩ ፍላጎቶችን መሠረት ያደረገው የባዕዳን ሀገራት ጣልቃ ገብነት ጉዳይ ሌላ ብዙ ብዙ የተወሳሰበ ጣጣ የሚጠይቅ ጉዳይ መሆኑን የሚያውቁ የሚረዱ አይደሉም፡፡ ሀገር የመመሥረት ጉዳይ ልክ በቃ እንደገበሬ ማሳ በመከለል የሚያበቃ ይመስላቸዋል፡፡

እነዚህን የአማራ ነን የሚሉትን ለመሆኑ የቱን ነው እንገነጥላለን የምትሉት? የጥንቱን የአማራ ሀገር ዛሬ ወያኔ ኦሮሚያ የሚለውንና ትግራይን ጨምራቹህ ነው ወይስ ሳትጨምሩ ነው? የአማራ ሀገር ያልሆነው የቱ ነው? የሆነውስ የቱ ነው? ስትሏቸው ምን ይላሉ መሰላቹህ ያው የወያኔ ቅፍቅፎችም አይደሉ? “የአማራን ክልል ነዋ!” ይሏቹሀል፡፡ የአማራ ክልል በሚሉት ውስጥም አገው፣ ቅማንት፣ ወይጦ ወዘተረፈ. እንዳለ እንኳን አይታሰባቸውም፡፡ ባጠቃላይ ድንቁርና ነድቶ ድንቁርና የሚጋልባቸው ደናቁርት በመሆናቸው እንዲህ ያለ ከበድ ከበድ ያለ ሐሳብ አይታሰባቸውም፡፡ እንዲያው በእውር ድንብሱ ሕዝብን ነድተው ገደል መክተት ነው የሚፈልጉት ቢታሰባቸውማ ሁሉም ተገንጣይ ነን የሚሉ ድርጅቶች በፍጹም እርስ በእርስ ተባልቶ ለማለቅ ካልሆነ በስተቀር የሚሆን ነገር እንዳልሆነ፣ እጣ ፋንታቸውና ተስፋቸው የተሳሰረ የተጋመደ፣ የማደግ የመበልፀግ ዕድላቸው ያለው በአንድነት ውስጥ ብቻ እንደሆነ ተረድተው አርፈው በተቀመጡ ነበር፡፡ ወይ አዋቂ ሆነው የሚበጀውን አያስቡ ወይ ደግሞ አናውቅም ብለው አርፈው አይቀመጡ እንዲሁ ብቻ ማወክ ነው ሥራቸው፡፡

ለመሆኑ የጥፋት ኃይሎች አማራንና ሀገሪቱን ማጥፋት ማፍረስ የሚፈልጉት ለምንድን ነው? ሦስት ምክንያቶች አሉ 1ኛ. አማራን ካላጠፋነው በስተቀር ሥልጣን ይዘን ለዘለቄታው ልንገዛ አንችልም ከሚል፡፡ 2ኛ. መሬቱንና ሀብቱን አጠቃላይ እሴቶቹን ለመውረስ 3ኛ. “አማራን በኢትዮጵያዊነት ስሜቱ፣ በተቆርቋሪነቱ፣ በሀገር ፍቅሩ፣ ለሀገሩ ባለው ነገር ሁሉ ምንም ብናደርግ ልንስተካከለው ሌንደርስበት አንችልምና!” ከሚል ሰይጣናዊ ቅናት የተሞላ ቀቢጸ ተስፋ፡፡

ስለሆነም በተለያየ ምክንያት አማራን ጠላት ያደረጉ ባዕዳንን ድጋፍና ምርኩዝ በማድረግ እንደምንም ብለው አማራን ማጥፋትን መረጡ፡፡ በእርግጥ ጥቃቱ ሲፈጸም ከቆየ የሰነባበተ ቢሆንም በዚህ ወቅት ግን የአማራ ህልውና አደጋ ላይ እንደሆነ ለሁሉም ግልጽ መሆን ይኖርበታል፡፡ አማራ ህልውናውን ለማስጠበቅ ራሱን ለመታደግ በአማራ ብሔርተኝነት ስሜት መነሣሣትና መታገል ግዴታ የሆነበት ወቅት ላይ ደርሷል፡፡ ብሔርተኝነት በተፈጥሮው ከፍትሕ ከዕኩልነት ባጠቃላይ ከዲሞክራሲያዊ (ከመስፍነ ሕዝባዊ) መርሖዎች ጋር ይቃረናል ወይም አይስማማም፡፡ ይሁንና የአማራ ብሔርተኝነት የተወለደው እንደሌሎቹ ጎሳንና ኢፍትሐዊ የሆነን የጎሳን ጥቅም መሠረት በማድረግ ሳይሆን ኢትዮጵያን ለመታደግ በመሆኑ ተፈጥሯዊ የብሔርተኝነት ወይም የዘውገኝነት ችግሮች አያሰጉትም፡፡ ለጊዜው አቅም ይገድበዋልና የራሱን ህልውናና ደኅንነት ማስጠበቁ ላይ ለማተኮር ይገደድ ይሆናል፡፡ የራሱን የቤት ሥራ ሊሠራለት የሚችል ሌላ አካል የለምና፡፡ ኢትዮጵያን ከጥፋት በመጠበቅ ታሪካዊ አደራውንና ግዴታውን መወጣት የሚችለው መጀመሪያ እራሱ ሲኖር ነውና፡፡ ሩቅ ባልሆነ ጊዜ ግን በትግሉ በሚፈጥረው ዕድል አቅሙን በበቂ ገንብቶ ኢትዮጵያን ያካልላል፡፡ ከጥፋትም ይታደጋታል፡፡ ፍጹም ዲሞክራሲያዊት (መስፍነ ሕዝባዊት) የሆነች ኢትዮጵያንም ይመሠርታል፡፡ አማራ የራሱን ህልውና ለማስጠበቅ ሲታገል በተመሳሳይ ሰዓት የዚህች ሀገር ህልውና ይጠበቃል፡፡ አማራ ሲኖር ኢትዮጵያ ትኖራለች፡፡ አማራ ከሌለ ኢትዮጵያም አትኖርም፡፡ የጥፋት ኃይሎች አማራን ለማጥፋት የሚጥሩት ወንጀል ኖሮበት ሳይሆን ይሄንን ቁርኝት ስለሚያውቁ ነው፡፡

በመሆኑም እነኝህን በወያኔ/ብአዴን ወላጅነት ወይም አደራጅነት ተመሥርተው አማራን ከኢትዮጵያ ስለመገንጠል ይሚያወሩ የወያኔን ቅፍቅፎችንና ከአማራነት የጨነገፉ ሽሎችን ከወያኔ ለይተን ልናያቸው አይገባም፡፡ የአማራ ህልውና መጠበቅ ካለበት አማራን ወደገደል ወደ ወጥመድ ወደ ድንቁርና እየመሩ ያሉትን የወያኔ ቅጥረኞች የግድ ማቆም ያስፈልጋል፡፡ መሬት ላይ ከጠፉ ማለትም ተግባራቸው ፍጹም ስሕተት መሆኑን ተረድተው መመለስ የሚችሉትን በማስተማር ለወያኔ ቅጥረኝነታቸው ታማኝ ሆነው እምቢ የሚሉትን እንቅፋቶች ደግሞ በመምታት መሬት ላይ እንዲጠፉ ካደረግን ሊኖሩ የሚችሉት አየር ላይ ብቻ ማለትም ነጻ መሆኑ ምቹ መስክ በሆነላቸው ማኅበራዊ የብዙኃን መገናኛው ላይ ብቻ ይሆናል፡፡

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

amsalugkidan@gmail.com

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.