“ጦር አምጣ!” – አሰፋ እንደሻው (ዶ/ር፣ የህግ)*

ethiopia-satenaw-news-1በታሪክ እንደተመዘገበው ከ1500-33 የነገሱት አጼ ልብነ ድንግል ሸዋ ውስጥ ቦካን በሚባል ቦታ ከትመው በያቅጣጫው ተቀናቃኞቻቸውን ሁሉ በማሸነፋቸው ሰላም ሰፍኖ፣ እርሻም ተስፋፍቶ ሲገዙ ሰራዊታቸው ስራ ስለፈታ የገዛ ግንባቸውን በጦራቸው እየወጉና እያፈረሱ፣ በየቤተክርስቲያኑ ጧፍና እጣን እየላኩ ጦር እንዲያወርድላቸው ይሳሉ ነበር፡፡ በለጋ ወጣትነት ዘመናቸው (በ12 አመታቸው) በመንገሳቸው ይመስላል ጉብዝናቸውን ለማስመስከር የሚችሉበትን አጋጣሚ በመሻት “ጦር አምጣ!” ያሰኙት፡፡ ቢታመንም ባይታመንም የአህመድ ኢብራሂም (“ግራኝ”) ጦር ሰራዊት ተነስቶባቸው ለመመከት እስኪሳናቸውና ካገር አገር እየሸሹ እስኪሞቱ ደረሱ፡፡

ታሪክ እራሱን ይደግማል መጀመሪያ በአሳዛኝ ሁኔታ ቀጥሎ ግን በፌዝ እንዲሉ፣ ከ450 አመታት በኋላ በ1983 አም የመንግስት ስልጣን የተረከቡት የህወሃት/ኢህአዴግ መሪዎች ገና በወጉ መቆናጠጥ ሳይጀምሩ በትጥቅ ትግል ይፈታተኑናል ብለው ለገመቷቸው “መንገዱን ጨርቅ ያድርግላችሁ”፣ “ኢህአዴግ ጦርነት መስራት የሚችል ድርጅት ነው” የሚሉ የንቀትና የማስፈራሪያ ቃላት ይወረውሩባቸው ነበር፡፡ ትርጓሜው ባታስቡት ይሻላችኋል፣ እኛን በጦር ሜዳ ማሸነፍ ቀርቶ ላጭር ጊዜም ቢሆን መቋቋም አትችሉም የሚል ነበር፡፡

በዘመናችን የፖለቲካ ትግል ታሪክ ውስጥ ላንድ ድርጅት/ፓርቲ በሃሳብ የሚቀርቡትን ወደራስ ለመመለስና ለማስጠጋት፣ ተቃራኒዎችን ወደባሰ ትንቅንቅ ውስጥ እንዳይገቡ መጣር ቋሚ ስልት ሆኖ ሳለ በህወሃት በኩል ግን ሁሉም ወገኖች ተንበርክከው በነሱ መዳፍ ስር ያውም በግለሰብ ደረጃ ተበታትነው በአባልነት ካልገቡ ቦታ የላቸውም፡፡ ገና ስልጣን ላይ ሳይወጡ ጀምሮ ከሚጠጓቸው ድርጅቶች ሁሉ የሚያገኙት ምላሽ በእኩልነት አብሮ መስራት እንጅ በናንተ ስር አንሆንም የሚል ስለነበር ርቃናቸውን ቆይተው ደርግ በህዝባዊ እምቢታና ተጋድሎ ተገዝግዞ ሊወድቅ ሲል እዚህ ግቡ የማይባሉ አናሳ ቡድኖችን አሰባስበው ለራሳቸው ተጨማሪ ስም ፈጥረው ኢህአዴግ ብለው ስልጣን ላይ ወጡ፡፡ በአሜሪካና እንግሊዝ መንግስታት ተጽእኖ እንዲሁም በይሉኝታ ብቻቸውን ስልጣን ላይ ፊጥጥ ከሚሉ ከሌሎች ጋር አብረው ቢታዩ የሚሻል መሆኑ መጨረሻ ላይ ገብቷቸው የሽግግር መንግስት ከየትም ከየትም ከተሰባሰቡ ጋር አብረው አቋቋሙ፡፡

የሽግግሩ ዘመን ፖለቲካዊ  መድረክ ለዘመናት ተጠራቅመው የቆዩትን የህብረተሰቡን ቅራኔዎችና ችግሮች ላንዴም ለመጨረሻም ለመጋፈጥና ስር ነቀል መፍትሄዎችን ለማብጀት መሆኑን ለመረዳት አቅቷቸው (ወይም ብዙ ሰው ሳያቋርጥ እንደሚከሳቸው አሻፈረኝ ብለው) ህዝብን የሚወክሉ ወይም በህዝብ ውስጥ ተደማጭነት አላቸው የሚባሉትን ሁሉ መጋበዝ እጅግ ተገቢው አሰራር ሆኖ ሳለ እነሱ ግን ስልጣኑን የማይጋሯቸው፣ ድክመታቸውን የማያጋልጧቸው ለይስሙላ ሽግግር እንዳካሄዱ የሚመሰክሩላቸውና የሚያራግቡላቸው ግለሰቦችንና ቡድኖችን ሰበሰቡ፡፡ የአገዛዙን አውታሮች (የርእሰ ብሄሩን ቦታ፣ መከላከያ፣ ጸጥታ፣ የውጭ ጉዳይ፣ የገቢዎች አስተዳደር) በራሳቸው ጠባብ ቡድን እጅ ጠፍንገው አጫፋሪ ቡድኖችንና ግለሰቦችን ተራ በተራ ከመድረኩ ላይ እያባረሩ በራሳቸው ምስል የተቋቋሙትንና ምንም የተለየ ድምጽና አስተሳሰብ  የሌላቸውን “ኢህአዴግና አጋር ድርጅቶቹ” በሚለው ስር ቆልፈው አገሪቱን ባሻቸው መንገድ፣ ባልተገደበ ጉልበትና እብሪት እየገዙ ግን ችግሮቿን ሳይፈቱ ለአመታት ተቀመጡ፡፡

የፖለቲካው አሰላለፍ ከቀን ወደቀን ስልጣን ላይ የወጡትን የሚሞግት፣ የሚተችና የሚፋለም እየበዛ እንጅ ገዥዎችን የሚወግናና ተሰሚነታቸውን የሚጨምር አልሆነም፡፡ በመጀመሪያ የስልጣን ወራት ከደርግ ስላላቀቁን ሰርተን ለመብላት እስከቻልን ድረስ ያሻቸውን ይሁኑ ባዩ በርካታ ነበር፡፡ ከቀለም ቀመሱ አንስቶ እስከወዛደሩ፣ ከአስተማሪውና የቢሮ ሰራተኛው አንስቶ እስከእንጀራ ሻጩ፡፡ ነገር ግን ከህወሃት/ኢህአዴግ ውጭ ማንም በፖለቲካው መድረክ መፈናጠጥ እንደሌለበት በይፋ እየሰበኩ (“ደማችንን አፍስሰን ያገኘነውን ለማንም አንሰጥም” በሚል ፈሊጥ እያጀቡ)፣ አንድም ተቀናቃኝ በድርጅት መልክ ብሎም ባንድነት እንዳይቀናጅ የተለያዩ ማነቆዎችን በህግ መልክ አስቀርጸው፣ በሰላዮቻቸው አማካይነትም በተደራጁት ሃይሎች ውስጥ ከፋፋዮችን እያሰረጉ ለመበታተን በሚያደርጉት ጥረት እየተሳካላቸው አንድም በቅጡ የሚጋፈጣቸው ሃይል የሌለ አስመስለው ለ14 አመታት (እስከ 1997) ናጠጡበት፡፡

የህዝቡን ቅሬታዎች፣ አቤቱታዎችና ተቃውሞዎች መስሚያ ጆሮ አብጅተው ስለማያውቁ በተለይ ደግሞ በትንሹ በትልቁ ሰበብ እያግበሰበሱ ስለሚያስሩና ከመንግስት ስራ ስለሚያባርሩ፣ ለግል መፍጨርጨርም በር ስለሚዘጉ አስቀድሞ በ1993 ከዚያም በ1997 ግልጽ ጥላቻንና ተስፋ መቁረጥን የተንተራሰ የህዝብ መነሳሳት ታየ፡፡ እነዚህን ስሜቶች በቅጡ አንጠርጥሮ የለውጥ አስተሳሰቦችን ይዞ በሰፊ አሰባሳቢ ድርጅት ዙሪያ ተፎካካሪ ንቅናቄዎች እንዳይገነቡ ገዥዎቹ እየቀደሙ በልዩ ልዩ መልኮች ስለሚወናጨፉ የኢህአዴግ ጥናካሬ ተደርጎ ተዘመረለት፡፡ ሌሎችን የፖለቲካ ዝንባሌዎችና ተቃዋሚዎች በሃሳብ ሞግቶና ህዝብን አሳምኖ የራስ ደጋፊ አድርጎ፣ አሸንፎ ከመገኘት ይልቅ በተንኮል፣ በማምታታትና በማስፈራራት እንዲቀጭጩ በመጉዳት ድል ተጎናጽፈናል እየተባለ 25 አመታት ተቆጠሩ፡፡ በርግጥም ሁሉም ተመልካች ይህ ሂደት መቸ እንደሚቆም ለመናገር እያቃተው አንድ ቀን ይፈነዳል በሚል አጠቃላይ አነጋገር ብቻ ራሱን እየሸነገለ ቆየ፡፡ የ1997 የለውጥ ትንቅንቅ እንደጤዛ ከረገፈ በኋላማ ህዝቡን እንደ”ደደብ” “ሰላማዊ ትግል” የሚሉትን ወገኖችም እንደገዢው መደብ መሳሪያ አድርጎ መመልከትና ለማናቸውም የከተማ ትግሎች ንቀትና መዛበት ተስፋፋ፡፡ በውጭ አገሮች የተደራጁ የሰላማዊ ትግል አራጋቢዎች ሁሉ ድምጻቸው እየሰለለ፣ ላገር ውስጡ ንቅናቄዎች የሚሰነዝሩትን ድጋፍ እያቀዘቀዙና እየተው ሄዱ፡፡

ህወሃት/ኢህአዴግ ባንድ በኩል እሰኪ የምትችሉ ወደጫካ ገብታችሁ ሞክሩን እያሉ በእብሪት “ጦር አውርድልን” ሲሉ ያለ የሌለ አቅማቸውንና የውጭ አገሮች ድጋፋቸውን እያሟጠጡ የአመጽ አሰላለፋቸውን ለደቀኑባቸው ወገኖች ግን የውግዘት ናዳ መወርወራቸውን ተያያዙት፡፡ የፖለቲካ ምህዳሩ ጠበበ፣ ጋዜጠኛውንና ማንንም ተቃዋሚ ወገን እየለቀማችሁ ማሰር፣ ካገር እንዲጠፋ መገፋፋት ወዘተ ውሎ አድሮ መዘዝ ይኖረዋል ተዉ የሚሏቸውን መስማት ደካማ እንደሚያሰኛቸው ቆጠሩት፡፡ (ደራሲው ራሱ በለንደን ኢትዮጵያ ኤምባሲ እግር ጥሎት አንድ ስብሰባ ላይ ከ8 አመት በፊት ገደማ ተገኝቶ “የኦነግ መሪዎች ሳይቀሩ አገር ቤት ገብተው መታገል እንደሚፈልጉ እየጮሁ ነው፤ ጋዜጠኞችን በማሰር አገሪቱ ተወዳዳሪ እያጣች ነው፣ ስለዚህ የፖለቲካውን ምህዳር አስፉት” ብሎ በወቅቱ በነበሩት አምባሳደር ብርሃኑ አማካይነት ለመንግስቱ እንዲተላለፍለት ማሳሰቡ ትዝ ይለዋል፡፡) ቻይና በተቃዋሚዎች ላይ የገነባችውን በቀላሉ የማይገረሰስ ማነቆና የጭፍን አምባገነንነት ስርአት በተለየያዩ ምክንያቶች ሊሳካላት በመቻሉ በማህበራዊ ስርአቷ፣ በአገዛዝ አወቃቀሯ የተለየችውን ኢትዮጵያን በዚያው መልክ ለ50 አመታት ያለተቀናቃኝ እንገዛለን ተብሎ ተዘፈነ፤ ህልሙ ተዘረጋ፡፡ ሌላው ሁሉ ቀርቶ በ1997 ምርጫ ወቅት አዲስ አበባ ላይ የራሳቸው የጦር ባልደረቦች በመከላከለያ መኪናዎች እየተጫኑ ሄደው የድምጽ ካርዳቸውን የሰጡት ለተቃዋሚዎች መሆኑ ራሱ ምንም ትምህርት አልሰጣቸው፡፡

ከሁሉም በይበልጥ አስገራሚው ባገሪቱ ምንም አይነት ተቀናቃኝ እንዳይኖር በምርጫ አማካይነትም አንድም ድምጽ ለተቃዋሚዎች እንዳይሰጥ አስተዳደራዊ፤ ህጋዊና ኢኮኖሚያዊ ስልቶች ተቀየሱ፡፡ አላማቸው በህብረተሰቡ ውስጥ “አብዮት” ቀርቶ (በመግለጫዎቻቸው ይህን ቃል እየጠሉ በፊት በፊት “የቀለም አብዮት” በኋላ ደግሞ “ነውጥ” በሚል ተክተውታል) አንዳችም ሰልፍ፣ አንዳችም ያደባባይ ግርግር እንዳይኖር ማድረግ ነበር፡፡ ስለሆነም ህገመንግስቱን በመሻር ያለፖሊስ ፈቃድ ምንም ህዝባዊ ስብሰባ ማድረግ እማይታሰብበት ደረጃ ደረሰ፡፡ በዋቤ ሸበሌ ሆቴል ገንዘብ ማሰባሰቢያ እራት ለመብላት የተሰበሰቡ የሰማያዊ ፓርቲ እድምተኞች ባስቸኳይ ለቀው እንዲወጡ ሲያስደርጉ ያገሪቱ የፖለቲካ አየር ምንም ልዩነት እማይሰማበት ጨለማ እንዲሆን አቅደው (አልመው) እንደነበር ይጠቁማል፡፡

የማናቸውም ህዝባዊ ተቃውሞ አንቀሳቃሽ ክፍሎች በይበልጥ ወጣቶች መሆናቸውን መሰረት አድርገው ገዥዎቹ ለነዚያ ክፍሎች ሁለት መድሃኒቶች አዘዙ፡፡ ባንድ በኩል የገዥው ፓርቲዎች ተቀጥላዎች እንዲሆኑ የወጣቶችና የሴቶች ስብስቦች በትእዛዝና በጉልበት ተደራጅተው ከቻይናው መሪ ፓርቲ በላቀ አኳኋን (ከህዝብ ብዛት ንጽጽር አኳያ) አገሪቱን በአባሎች ሞሏት፡፡ በፊት በፊት በየዩኒቨርስቲው የሚመረቀው ሁሉ አባል እንዲሆን ይገደድ ነበር፤ በኋላ በኋላ ገና ሲገባም መመዝገቡን እንዲያፋጥን መገፋፉት ስራቸው ሆነ፡፡ ሁሉም የገዥው ፓርቲዎች አባል ከሆነ ለተቃውሞ ማን አለሁ ሊል ይችላል; “አዬ ብልጠታችን!” ሳይሉ አይቀሩም ይህንን የቀየሱት፡፡ በዚህ አድራጎታቸው ከደርግ ኢሰፓ ፓርቲ ምንም እንዳልተለዩ ማን ይነግራቸዋል!

ሁለተኛው መደሃኒታቸው  በስራቸው ለተደራጁት ሁሉ ድርጎ (ጥቅማ ጥቅም) መስጠት፤ የቀን አበልና ምግባ ምግብ ማደል ሆነ፡፡ ናፖሊዮን ወታደሮች በሆዳቸው ነው የሚጓዙት እንዳለው! በአነስተኛና ጥቃቅን ድርጅቶች ወዘተ የሚሰለፈው ሁሉ ቅምሻውን ከተካፈለ በኋላ ከመንግስት የሚቀርብለትን ማናቸውም ጥያቄ ሳያቅማማ (በደስታ ሆነ በሌላ) እንዲቀበል ያነጣጠረ እቅድ ነበር ይህ ኢኮኖሚያዊ አሰራር፡፡ ያገሪቱን ሃብት ያለምንም ማስተዋል ወጣቱን፣ ሴቱን፤ ገበሬውንና ሌላውን አባላቸውን ለማጥመድ ሲጠቀሙበት የፖለቲካ ተሳትፎ ለትርፍ ማስገኛ የመዋሉን አስነዋሪ መልእክት አጥተውት አይመስልንም፡፡ ስርአቱ ከላይ  በሙስናና በዝርፊያ እየተጨማለቀ መሆኑን ለመሸፋፈን ሽርፍራፊ ጥቅማጥቅም በህብረተሰቡ ውስጥ እስከታች ድረስ ቢወርድ “ጤነኛ” ገጽታ ይላበሳል በሚል ግምት ነበር፡፡ ሁሉም አብሮ ከባለገ ማን በማን ላይ ጣቱን ሊቀስር ይችላል; የህዝብን ሃብት በዚህ መልክ የመቀራመቱ መርሃ ግብር ከሌሎች ተዛማጅ ኢኮኖሚያዊ ብልግናዎች (ህገወጥ መሬት፣ የኪራይ ቤት፣ ቦታና የባንክ “ብድር” ለስርአቱ አገልጋዮች ማርከፈከፍ) ጋር እንዲተሳሰር ግፊቱ እየጨመረ በመሄዱ የእለት ተእለት የህዝብ አስተዳደር ጉዳይ እየተረሳ፣ ጭራሹኑም ብሶት የሚያነሱና አቤቱታ የሚያቀርቡ “ጸረ-ሰላም” ብሎም “ጸረ-ልማት” እየተሰኙ አገሪቱን ድቅድቅ ጨለማ ወረራት፡፡

ባገሪቱ የፖለቲካ መድረክ ላይ በሸቀጥ ግዥና ሽያጭ መልክ ታዛዥነት፣ አጎብዳጅነትና የህዝብን እንባ አሳልፎ መስጠት ሲነግሱ የተቃዋሚውን ጎራ ሳይነኩ አላለፉም፡፡ የተቃዋሚ መሪዎችን ወደገዥው ፓርቲዎች ለማዞር የሚቀርብላቸው የገንዘብ፣ የቤትና ቦታ እንድሁም የሹመት ድለላ ከመድራቱ ውጭ የተቃዋሚ እንቅስቃሴዎች በተበከለው አዲስ የድርጎ ፖለቲካዊ ባህል ተመተዋል፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲዎች አባላት ልክ እንደመንግስታዊ አቻዎቻቸው ከአመራሮቻቸው ተመሳሳይ ጉርሻ ካልሰጣቸሁን፣ ልዩ ልዩ ወጭዎችን ካልሸፈናችሁልን ወደሚል እንዲወርዱ ከፍተኛ ተጽእኖ ነበረባቸው፡፡ የፖለቲካ ተሳትፎዋቸው አገራቸውንና እንቆምለታለን የሚሉትን ህዝብ በፈቃደኝነትና በነጻ ለማገልገል መሆኑ እንዲደበዝዘና የቅጥረኛነት መንፈስ እንዲሰልባቸው ሆነዋል፡፡

በምርጫ ፖለቲካው አቅጣጫ በየደረጃው ያሉ የገዥው ፓርቲዎች ሰራተኞችና መሪዎች አንድም ድምጽ ለተቀናቃኝ እንዳይሰጥ የሚለውን የውስጥ መመሪያቸውን በተቻላቸውና ባመቻቸው ሁሉ እንዲያስፈጽሙ ግዴታና ሃላፊነት ስለተጣለባቸው ሁሉም ደጁን ማጽዳት ከቻለ የትኛውም ከተማ ይጸዳል ከሚለው አባባል ጋር ተያይዞ ውጤቱ በ2002 አም 98፤ በ2007 ደግሞ 100 በመቶ “አሸናፊዎች” ሆኑና አረፉት፡፡ ታዲያ ማን ሞኝ ሆኖ የየራሱን እንጀራ ለየቅሉ ባላንጣ አይኑ እያየ ያስረክባል; ማስፈራራት፣ ማሰር ብሎም መግደል፣ ኮረጆ መስረቅ፣ እንዲሁም ስፍር ቁጥር የሌላቸው የማጭበርበር አይነቶች ለ”ቅዱስ አላማቸው” ሲባል የሚከናወኑ ደርጊቶች ሆነው በተግባር ዋሉ፡፡ ተመልካቾች ከዳር ቆመን ስንጠባበቅ ቢያንስ ቢያንስ በመራጩ ህዝብ ዘንድ ብቻ ሳይሆን ባገሪቱ ባጠቃላይ ስም ያበጁትና በምንም ሚዛን የማይወድቁትን ተቃዋሚዎችን የመንግስቱ መሪዎች ጣልቃ ገብተው ቆጠራዎቹን በትክክል አስኪደው አንድ 30 ያህል ወደፓርላማው ያስገባሉ ብለን እንጠብቅ ነበር፡፡ ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ! ነገር ግን በአለም በሞላ ፊት ሁለት ጊዜ እንዲዋረዱና ከመሪነት ተርታ ውስጥ የማይገቡ መሆናቸው እንዲጋለጡ ሆነዋል፡፡ (ብዙ ሚሊየን ዶላር የለገሳቸው የባንድ ኤይዱ ቦብ ጌልዶፍ ራሱ “ማደግ ያልቻሉ ጨቅላዎች” ነበር ያላቸው፡፡) በምርጫ አፈጻጸም በኩል የሙጋቤ አድራጎት እንኳን ከነሱ ምንኛ የተሻለ እንደነበር ተነግሯል፡፡

የህዝብ እንቅስቃሴን ደብዛውን ለማጥፋት በህግ በኩል እየወታተፉ የደነገጉትን ባጭሩ እናንሳ፡፡ በህገ መንግስቱ ላይ የሰፈሩት የዴሞክራሲና ሰብኣዊ መብቶች የተባሉት ከመነሻውም የፖለቲካ (መዋቅራዊ) ዋስትናና ማህበራዊ መሰረት ስላላገኙ በሁሉም አቅጣጫ ቢጎነተሉ፣ ቢዘጉ፣ እንደሌሉ ቢቆጠሩ በተሟጋችነት የሚሰለፍ ማንም ወገን በፖሊስና ሌላም አስተዳደራዊ መሳሪያ ስለሚገደብ ብዙም ሊጨነቁበት አያሻም ነበር፡፡ ለነገሩ በርካታ የቀድሞ አባሎቻቸው እንዳሳወቁት በታሪካቸው ነጻ ሃሳብ በመካከላቸው ተስተናግዶ፣ በውይይት አብላጫ ድምጽ አሸናፊ ሆኖ ስለማያውቅ በድርጅቶች ቁንጮ ላይ የተቀመጡት ርስበርስ አውርተው ብቻ ሁሉንም ሰለሚጨርሱትና ውሳኔያቸውን በትእዛዝ መልክ ወደታች ስለሚልኩት  ህዝቡ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ አሰራር መስፈን እንደሚያስገልገው ትዝ አይላቸውም፡፡ ያም ሆኖ ግን በተለያዩ የህግ ማሻሻያዎችና አዳዲስ አዋጆች (በጸረ-አሸባሪ ህግና የማህበራዊ መደራጀትን ከውጭ ጣልቃ ገብነት ለማጽዳት በሚል ባወጡት) አማካይነት ተደማሪ የፈሪ ብትሮች ፈጥረዋል፡፡ እነዚህ ህግጋት ተፈጻሚነታቸው የነሱን ደጋፊዎች እንዲያሞላቅቁ፣ ተቀናቃኞቻቸውን ግን እያዋከቡ ለመበታተን ነው፡፡ ለምሳሌ የፓርቲዎች ምዝገባ አሰራር በዚህ መልክ የተዋቀረ ነው፡፡ ቤተሰቦች ሳይቀሩ ተሰባስበው ያለምንም ደፋ ቀና የገዥዎች ወዳጅ ፓርቲዎች ሲመሰርቱ እግራቸው እስኪቀጥን ድረስ ዞረው ዞረው ስንት ሰው አስፈርመው ይኸ ቀረ ያ ጎደለ በሚል የሚንገላቱት ጥቂት አይደሉም፡፡ የህግ መሳሪያነት በዚህ መልክ መንሻበቡ ተደጋጋሚ እንጅ ልዩ ሁኔታም አንዳይመስላችሁ፡፡

ሄዶ ሄዶ እስከቅርቡ ዘርፈ-ብዙ ህዝባዊ ንቅናቄ ድረስ ገዥዎቹን ሁሌም ሲያሳስባቸውና ሲያስጨነቃቸው የቆየው ከተቃዋሚዎች መብዛት ጋር ሃይል አብጅቶ ሰውነቱን አግዝፎ የሚተናነቃቸውን ክፍል ከተቻለ በእንጭጩ አጥፍተው ካልሆነም አኮስሰው ለማቆየት የተያያዙትን የማያቋርጥ ትንቅንቅ የማሳካት ጉዳይ ነበር፡፡ ከ1983 ጀምሮ እስከ ከ1997 ድረስ በሙሉ ሃይላቸው የሚከታተሉት የፖለቲካ መድረኩን ከሌሎች አሻራ አጥርተው ብቻቸውን ያለተቀናቃኝ ለማንገስ ነበር፡፡ ይህ ጠባብ ድርጅታዊ ተልእኳቸው ከሁሉም ተግባር በላይ ተደርጎ በመሳሉ የገብረ ህይወት ባይከዳኝ “የመንግስት አስተዳደር” ስራዎች ተንቀው “መንግስት-አልባ” ስርአት ሰፍኖ ነበር፡፡ ሳር ቅጠሉን በስለላ ስራ ማሰማራት፣ ተቀናቃኞችን መከታተልና መከፋፈል፣ ማጋዝና ማጥፋት የግቢ ነፍስ ውጭ ነፍስ ደረጃ ደርሰው፣ የህዝቡን እሮሮ የሚሰማ  አካል እየጠፋ ያካባቢ “ዱርየ” ሁሉን ነገር ሊቆጣጠር እየቃጣው፤ የንግዱም ማህበረሰብ እንዳሻው ህዝቡ ላይ እየፏለለ “መንግስት” የህወሃት/ኢህአዴግ ተጨማሪ ክንድ ወይም ተቀጥላ ሆነ፡፡ የፖለቲካው መስክ ከሌላው ወገን ሁሉ ተነጥቆና ተከልሎ በነሱና ለነሱ ብቻ የመጫወቻ ሜዳ ተደረገ፡፡ በጦር ሜዳ ላይ ሙሉ ድልና የበላይነት ነበረን በሚለው ትረካቸው ትይዩ የፖለቲካው ዘርፍም ያንኑ መለኪያ እንዲላበስ ያለ የሌለ ሃይላቸውንና ጥረታቸውን ከመመደብ አልተገቱም፡፡ ፖለቲካውን ጦርነት ሲያካሂዱ በነበረው መልክ ስለተያያዙትም በነሱ አይን የዜሮ ድምር ጫወታ ከመሆን አላለፈም፡፡ ሁሌም አሸናፊ፣ ሁሌም አዛዥ፣ ሁሌም አነሳሽና ጠንሳሽ ብሎም ፈጻሚና አሳራጊ የመሆን ድርሻ ከነሱ ህልውና ጋር የተጣበቀ አደረጉት፡፡

በዚህም ምክንያት የ1997 ምርጫ ፉክክር እንኳን ለነሱ ለተቀናቃኞቻቸውም ውጤቱ አስቀድሞ ያለቀ ተደርጎ ይታይ ነበር፡፡ ማሸነፍ የዘወትር ልምዳቸው፣ በህዝብ ዘንድ ተቀባይነታቸውም የማይገሰስ አድርገው ስለሚያስቡት የምርጫው መልክ በየትኛውም አቅጣጫ ቢቀናጅ (ያገር ውስጥም ሆነ የውጭ ታዛቢዎች ኖሩ አልኖሩ) አንዳንድ ከተሞች ያጠራጥራቸው እንጅ ገበሬውን በሙሉ ከጎናቸው የሚነጥለው ሃይል እንደሌለ ይፎክሩ ነበር፡፡ አገሪቱ የገበሬ ህብረተሰብ በመሆኗም ሰማይ ዝቅ ምድር ከፍ ቢል እነሱን ከስልጣን የሚያወርድ ውጤት አይኖርም ብለው ነበር፡፡ ገበሬው የነሱን ድርጅት በነጻ አውጭነትና የህይወቱ አለኝታ አድርጎ በመሳል ልቡ ውስጥ አስገብቶናል ብለው በተደጋጋሚ እንደሚወተውቱት! ይልቁንም በፖለቲካው መድረክ ላይ ፍጹም የበላይነታቸውን እላይ በተገለጸው አካኋን ስላበጃጁት፣ ተቀናቃኞቻቸውን የመደራጃና ህዝብ የመሳቢያ ስራ እንዳይሰሩ ኮድኩደው በማኖራቸው ከስልጣናቸው ንቅንቅ የሚያደርጋቸው ሃይል ጭራሽ አይኖርም ብለው ደምድመው ነበር፡፡ ለዚህ ነበር በምርጫው ወቅት የመገናኛ ብዙሃኑን ለቀቅ አድርገዋቸው የሃሳብ ፍጭቶች በመጠኑም ቢሆን ሊደመጡና ህዝቡ ያልተለመደውን የሃሳብ ገበያ ሊቋደስ የቻለው፡፡ ያችው መጠነኛ ፉክክር በህዝቡ ውስጥ ሲብላላ የቆየውን የብሶትና የተቃውሞ ስሜት ስላከከችለትም ነበር በምርጫው ወቅት ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ ገዥዎችን አይናችሁን ላፈር ያላቸው፡፡ ገዥው ወገን ሙሉ በሙሉ ባይሸነፍም የቆጠራ ማጭበርበርና ሌላም የብተና ስራዎች ካልታከሉበት በአማካይ የብዙሃን ድምጽ ሊያጣ እንደሚችል ብዙዎች ገምተው ነበር፡፡ ይህም በኋላ በቆጠራው ወቅት ተረጋግጧል፡፡

የ1997 ምርጫ አካሄድ ጠንከር ያለ የተቃውሞ ፖለቲካ አስቀድሞ በስሎና ተደራጅቶ ቢሆን ኖሮ ሊደርስ ይችል የነበረውን መለካም ውጤት ከማመልከቱ በላይ በገዥዎቹ ውስጥ ሽብር ለቀቀባቸው፡፡ ለ14 አመት ሲያካሂዱት የነበረው ሁሉንም የፖለቲካ ሃይሎች የማፈንና የጸጥታ ግንባታ ስራ ብቻውን የህዝቡን የፍትህና የአስተዳደር ጥያቄዎች መመለስ እንደማይችል አረጋገጠ፡፡ መንግስቱ ላይ የተሰቀሉት ወገኖች በተለይ የህዝቡን የእለት ተእለት ኑሮ ማሻሻያ ተግባሮች ላይ ካልተሰማሩ የማይገሰሰው የፖለቲካ የበላይነታቸውና የጸጥታውና የፍርሃቱ ውጥንቅር ባንዴ በነው እንደሚጠፉ ጠቆመ፡፡ የፖለቲካ ስልጣን ፋይዳ በህዝቡ ዘንድ ድህነትን፣ ርሃብን፣ በሽታን፣ ስራ አጥነትን፣ ማይምነትን ለመዋጋት ካልሆነ ገዥዎቹ እንዳሻቸው ቢፈነጩበት በፍራቻ ጫና ስር ለጊዜው በትዝብት እየመዘገበ ቢቆይም አመቺ ወቅት ጠብቆ እንደሚነሳ አሳየ፡፡

ይህንኑ አስፈሪ መልእክት በመረዳት ህወሃት/ኢህአዴግ መፈራገጥ ተያይዞ ከ1997 ወዲህ እስከ2008 ድረስ መጠነኛ ኢኮኖሚያዊ ለውጦች ላይ ተሳፈረ፡፡ በተለይ የመንገድ አውታሮችን፣ በድሃ አገሮች ከተሞች የለውጥ ምልክት ብለው የሚደረደሩና የሚታዩትን ህንጻዎችን፣ የጤናና ትምህርት አቅርቦቶችን መዘርጋት ተያያዙ፡፡ አገሪቱ ከግብርና ወጥታ ወደኢንዱስትሪ እንድትገባ የሚለውና ባለም ዙሪያ በማንም ወገን ተቀባይነት ያገኘውን ተራ መመሪያ ግን እስካሁን ከለበጣ ንግግር የላቀ ቦታ አልሰጡትም፡፡ ለምሳሌ በከፍተኛ የሹሞች ጋገታ፣ ያጎብጓቢና የጥሩምባ አጀብ አልፎ አልፎ ከሚናፈሱት “ትንግርተኛ” ምርቃቶች የሃዋሳው “ኢንዱስትሪ ፓርክ” ጥንታዊ (የመጀመሪያው ያውሮፓም የእስያም የኢንዱስትሪ ዘርፍ!) የሆነውንና ሌሎች አገሮች እየዘጉት ያለውን የጨርቃጨርቅ ስራ መልሶ ኢትዮጵያ ላይ የሚተክል ነበር፡፡ በተጨማሪም የፖለቲካ መድረኩን ሙሉ በሙሉ በጃችን ተቆጣጥረነዋል በሚል የኢኮኖሚውን ዘርፍ ለመለዋወጥ ያስቸለናል ብለው ካወጡዋቸው እቅዶች ጀምሮ እስከ ተግባራዊ አሰራሮቻቸው ድረስ ያለህዝባዊ ተሳትፎ፣ ሙያዊ ብቃት ያላቸውን ክፍሎች ሳይጨምሩ ስለሚደናበሩ ይኸውና አገሪቱን ለምስቅልቅል ችግሮች ዳርገዋታል፡፡

ከሁሉ አስቀድሞ መሬት የህዝብ ከሆነበት ከ1967 ጀምሮ በገጠሩ ህዝብ ዘንድ የተፈጠሩትን በርካታ ችግሮች (መሬት መጣበብ፣ ምርታማነት መቀነስ፤ የህዝብ ብዛት መጋሸብ) መፍትሄ እንደማብጀት (የመስኖ ስራን ማስፋፋት፣ የግብርናውን ገጽታ የሚያስለውጥ የጥበብ አጠቃቀም መያዝ) መሬቱን እየነጠቁ መሸጥና መለወጥ ከፍ ተኛውን የጥፋት ድርሻ ይዟል፡፡ በገጠር ከተሞች ሳይቀር የቦታዎች መቀራመትና ዝርፊያ በየትኛውም ደረጃ ያሉት የመንግስቱ ሹማምንት ስምሪት ሆኗል፡፡ ዱሮ በፖለቲካው መስክ ማንንም ወገን አናስደርስም ይሉ የነበሩት ሃላፊዎችና መሪዎች በሃብት ዝርፊያና ጥቅም ማካባትም እኛ ብቻ ነን ብለው ጥቂት ቆርቆሮዎች አሰባስበው በጭቃ የተመረገ ግድግዳ ውስጥ ጎጆ የሚቀልሱትን ሳይቀር በአፍራሽ መኪናዎች ጠራርገው የመጣል እብሪት ውስጥ ገብተዋል፡፡ ይህ ዘርን ያልለየ የጥፋት ስራ አገሪቱን ከዳር እስከዳር በሚያነቃንቅ እሮሮና ትንቅንቅ ከተታት፡፡

በመሬት አጠቃቀምና ባለቤትነት ዙሪያ በያቅጣጫው የተጀመረው የተቃውሞ እንቅስቃሴ እያደገ ሌላ ሌላም ገጽታ እየተጨመረበት ዛሬ መንግስቱን ከነጭራሹ አንቅሮ ወደመትፋት ደረጃ ከፍ ብሏል፡፡ የኦሮሞዎች አዲስ አበባን ተነጠቅን ስሜት እየተስፋፋና እየተጋጋለ ማንነትን ከማረጋገጥ፣ ከነጻነትና ራስን ሙሉ በሙሉ ከማስተዳደር ጋር ተቆራኝቷል፡፡ ህጻናትና አሮጊቶች ሳይቀሩ ከሊቅ እስከደቂቅ እየተሰለፉ መሳሪያም አንፈራም፣ የተነጠቅነውን ኩሩነታችንን፣ ማንነታችንን፣ መሬታችንን፣ ባህላችንን እናስመልሳለን፤ አሊያም መሞትን እንመርጣለን ብለው የመንግስቱን ያስተዳደር መዋቅሮችን አፍርሰዋል፡፡ በሰላሙ ጊዜ መደማመጥና መስማማት ያልሞከረው እንዲያውም በማናለብኝነት ትእዛዝ ሲያስተላልፍ የኖረው የህወሃት/ኢህአዴግ መንግስት ዛሬ አንድም ሰሚ የኦሮሞ ህብረተሰብ ክፍል እስኪያጣ ደርሷል፡፡

በአማራው፣ በኮንሶው፣ በካፋው፣ በቤኒ ሻንጉል ወዘተ የተቀሰቀሰውም ተቃውሞና ጥያቄም ከመንግስት በኩል ሲወረወር ከቆየው መሰላቸትና ንቀት የተወለደ ነው፡፡ መሬትና አጠቃቀሙ፤ ማንነትና ተደማጫነት፣ የራስን ድምጽ የተንተራሰ አገዛዝ የመሻት ጥያቄዎች እየተደራረቡ ተነስተዋል፡፡ ዱሮም የማይሰማውና የማይገባው በየእርከኑ የተሰገሰገው የስልጣን ባለቤት ሁሉ እየተገረሰሰ፣ ሹማምንቱ ከስራቸው እየተባረሩ በፖለቲካው አግጣጫ መፈታት የሚኖርበት መንገድ ዱሮም እንዳልተቀየሰ ዛሬም የጦር ሃይልን የማሰማራት  እርምጃ እየተጠናከረ ከድጡ ወደማጡ እየገቡ ነው፡፡ ህወሃት/ኢህአዴግ ከጧት የለመዱትንና ሊለቃቸው ያልቻለውን እያንዳንዱን የህዝብ እሮሮና ቁርሾ በመንግስታዊ ጦር መሳሪያ መጋፈጣቸው እንደቀጠለ ሆኖ የህዝብ አመጽን እየጎለበተ እንዲሄድ ረዱት እንጅ አልበተኑትም፡፡ ዱሮም የመንግስት የሃይል እርምጃዎች ምን ጊዜም ተቃውሞን እንደሚወልዱ፣ የበለጠ ሃይል የባሰ ተቃውሞና አመጽን እንደሚቀሰቅሱ የታወቀ ነውና ዛሬ አገሪቱ ለደረሰችበት ማለቂያ የሌለው አዙሪት መብቃቷ ሊየስደንቅ አይገባም፡፡

መንግስት ለልማት ተነሳሳሁ ስላለ፣ በተከታታይ አመቶች ብዙ ድሎች አስመዘገበኩ ብሎ ስለፎከረ ባገሪቱ እያደር ስር እየሰደደና እየሰፋ የሄደውን ምስቅልቅል ሁኔታ ከውጭ ጠላቶች በተሰነዘረ ጣልቃ ገብነት የተፈጠረ አድርጎ ማቅረቡ ምንም የሚያስኬድ አለሆነለትም፡፡ ምስቅልቅሉ የተጠበቀም ባይሆን በገዥዎች በኩል በቆየው ድፍንነትና በተወጠሩበት እብሪት ምክንያት እየተፈጠረና እየዳበረ የመጣ እንጅ የውጭ ሃይሎች የተከሉትና ያፋፉት አይደለም፡፡

እንዲያውም የህዝቡ ተቃውሞ አነሳስና መራባት ካሁን በፊት ባገሪቱም ሆነ በሌሎች ተመሳሳይ ሁኔታዎች የተከሰተ አይደለም፡፡ የህዝብ ብሶት ስር እየሰደደ የመንግስት ደንታቢስነትና አፈና ሲጨመርበት ከምንም የማይቆጠር ሰበብ ሁሉ እንደምክንያት መቆጠሩና ለትግል መነሳሳት መሰረት መጣሉ ባይቀርም በኢትዮጵያ የታየው ግን እጹብ ድንቅ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ የህዝብ ሮሮና ቁጣ ተደራጅቶ በስልጣን ላይ ከተፈናጠጠው መንግስታዊ ሃይል ጋር የሚላተመው በአደባባይ ወጥተው የመደበኛ ተቃውሞ ትግል ላይ ነን ከሚሉት ፓርቲዎች ጋር በተቆራኘ መልክ ሲንቀሳቀስ ቆይቶና አድጎ ነው፡፡ ይህን መሰል ንቅናቄ እየመሩና እያደራጁ በመቆየታቸው ህጋዊ ፓርቲዎቹ የህዝቡን መበደልና ጥያቆዎች አንግበው የፖለቲካውን መድረክ ለመያዝ ሲጥሩ በህዝቡ ድጋፍና ርካታ ላይ ስለሚገነቡ በድንገት ካመራራቸው የሚያወርዳቸው ሃይል አይገጥማቸውም፡፡ ያልታሰበና ያልታየ የትግል አመራር ዘው ብሎ ወደጎን አይገፋቸውም፡፡

በኢትዮጵያ እላይ በገለጽነው ምክንያት የህዝብ ብሶቶችና ችግሮች በነጻ መንግድ ለመንግስቱ የሚቀርቡበት አግባብና መድረክ እየተዳከመና እየጠበበ መጥቷል፡፡ የመገናኛ ብዙሃን ተሸብበው ተሸብበው ስለእንግሊዝ እግር ኳስና የማያቋርጥ ዘፈን ለማስተላለፍ (ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የውጭ ባህልና አኗኗር ብቻ የሚያስተጋቡ የተተረጎሙ ፊልሞች 24 ሰአት የሚረጩበት አሰራር በመስፈኑ) ከዚያም አልፎ አሰልቺ በመሆኑ አደማጭ የሌለው የገዥውን ፓርቲ ልፈፋ ብቻ ለማራገብ ስለሚውሉ ለመንግስቱም ለህዝቡም በሚያገለግል መልክ መፍትሄዎችን ማቅረቢያ አልሆኑም፡፡ በዚህ ላይ ህዝቡ በቀጥታ በራሱ ጉዳዮች ዙሪያ እንዳይመካከር ታግዶ ኖሯል፡፡ ተማሪዎች፣ ወጣቶች፣ ሰራተኞች፣ ሴቶች፣ ገበሬዎችና የከተማ ነዋሪዎች እንዲሁም የሙያና የንግድ ማህበራት በነጻ ተደራጅተው ችግሮቻቸውን ባሻቸው መልክ እየተገናኙ መነጋገር ከተከለከሉ ቆይቷል፡፡ ገዥው ፓርቲ በትእዛዝና በጥቅም እየደለለ የድርጅት አቋም ሰጥቷቸው የህግ አውቅና ችሯቸው የሚንቀሳቀሱት ከፓርቲው መሳሪያነት ስለማይዘሉ የህዝቡን የልብ ትርታ ማዳመጫና የሚሹዋቸውን መፍትሄዎች ማብጃ ስለማይሆኑ ተቀባይነታቸው ውሱን እንዲያውም ሰዉ የሚሸሻቸው ሆነዋል፡፡

በሌላ በኩል ገዥው ወገን ህጋዊ (ማለትም የተመዘገቡ) ፓርቲዎች ብቻ እንዲንቀሳቀሱ ስለቀየሰው ለመመዝገብ የሚቻልባቸውን መመዘኛዎች በመቀያየርና በመጠምዘዝ በርካታ ዜጎች “ህገ-ወጥ”ና “አሸባሪ” እየተባሉ ከሰላማዊ ፖለቲካው መድረክ ተባረው ሌላ አቅጣጫ እንዲቀይሱ ተገደዋል፡፡ ገዥው ፓርቲና መንግስት ለነሱ በሚያመች መልክ በየጊዜው እየለዋወጡ በሚያወጧቸው አሰራሮች የሰላማዊ ትግል መድረኩንና መንገዱን እያጣበቡ የተመዘገቡ ፓርቲዎችም ቢሆኑ እግር ከወርች ተቀፍድደው እንዳይንቀሳቀሱ ተደርገዋል፡፡ ገዥዎቹ በቻይና ቅድ ከፍተኛ የአባላት ቁጥር ሲያካብቱ ተቃዋሚ የሚባሉት ክፍሎች ግን ባንድ ላይ ተዳምረው እንኳን ሊስተካከሏቸው ሲሶም ደረጃ አልደረሱም፡፡

ነገር ገን ወሳኙ የብዛት ጉዳይ ሳይሆን በአስተሳሰብም፣ በልምድና በታማኝነትም ገዥዎቹን የሚከተለው የህብረተሰብ ክፍል በቅርቡ በታየው ህዝባዊ ንቅናቄ ላይ መንግስቱን ደግፎና አቅፎት አልታየም፡፡ ከሚኒስትሮቹ አንስቶ እስከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች፣ ከሰራተኛው፣ ወታደሩና ገበሬው አንስቶ እስከ ወጣቱና ሴቶች፣ ከተማ ነዋሪዎች ድረስ አንድ ላምስት በሚሉት የመጠርነፊያ አደረጃጀት ያስተሳሰሩት ሁሉ እንደእንቧይ ካብ ሆነዋል፡፡ የስለላ መዋቅሩ ሲቀር የህዝብ አመጽ በተቀሰቀሰሰባቸው አካባቢዎች ሁሉ የመንግስቱ አስተዳደራዊና የፖሊስ መዋቅሮች አንድ ባንድ ፈርሰዋል፡፡ ያ የተዘመረለት የአባል ብዛትና የአንድ ላምስት መዋቅር የት እንደደረሰ እስካሁን የሚያነሳም አልሰማንም፡፡

የገዥው ፓርቲ መዋቅሮችና የአደረጃጀት ስልቶች በያቅጣጫው ሲንከረባበቱ፣ በህግ የተመዘገቡት ፓርቲዎች በህዝቡ ዘንድ ተሰሚነታቸው ጭራሽ ጠፍቶና ለህዝባዊ አመጾች አመራር ጠፍቶ ባለበት ሰኣት እንደሚገመተው ምንም እንቅስቃሴ አይኖርም ብለው ያሰቡ ቁጥራቸው ትንሽ አልነበረም፡፡ የህዝቡን ድንቁርናና ፈሪነት በየወቅቱ እየጠቀሱና እየመነዘሩ ለህወሃት/ኢህአዴግ መሳሪያ ሆነ ብለው ሲያወግዙት የቆዩት ሁሉ ጉድ እስኪሉ ድረስ በትቢያው ላይ የተጋደመው የህዝብ ወገን ሳይታሰብ ብድግ አለ፡፡ ገዥውም ተቃዋሚውም ፓርቲዎች ባልጠበቁት መንገድ አፋቸውን ከፍተው እንዲመለከቱት ተገደዱ፡፡ ለካስ የፖለቲካው መድረክ መጣበብ፣ የህወሃት/ኢህአዴግ የማይገሰስና ፍጹም የበላይነት የሰፈነበት ስርአት የመገንባት እቅድ ያልተጠበቀውንና የተረሳውን ተራ ህዝቡን ወደመድረኩ እንዲጠጋ በቻ ሳይሆን መድረኩን ቀምቶ እንዲይዘው አዘጋጅቶታል!

ከሁሉም በላይ የተቃውሞውን አቅጣጫ ማንም ሊተነብየው የማይችል ነበር፡፡ ህዝቡ በእለት ተእለት በደሎች ዙሪያ መነሳሳቱ ከፍተኛው ጉዳይ ነበር፡፡ ወጣቱም ክፍል ከህዝቡ ጋር ገጥሞ ትግሉን ሲያቀጣጥለው የመጠቀ አስተሳሰብና ቲዎሪ ይዞ አልነበረም፡፡ በወጣቱ ውስጥ ምንም የተቃዋሚ ፖለቲካ አስተሳሰብ እንዳይሰፋፋ ገዥው ፓርቲ ስላሰነካከለው በባዶውና በስሜት እንዲነዳ አድርጎት ስለቆየ እንኳን ትግል ሊመራ ከህዝቡ ጋር የሚቆም መስሎ አልታያቸው ይሆናል፡፡ ነገር ግን ምንም የማይፈይድና የትም የማያደርስ “ልማታዊ ግንዛቤ” ከመጨበጥ ባዶ መሆን ይበልጥ ጠቅሞት ከህዝቡ ጋር ለመግጠም አስችሎታል፡፡ ወጣቱ ክፍል መጀመሪያ ላይ በያካባቢው ሁሉ “ህወሃት ሌባ” እያለ መጮሁን ምን ያህል ያስተሳሰብ ድርቅ እንደመታው ለተመለከተ ከህዝቡ ውስጥ ቦታ ያገኛል አያሰኝም ነበር፡

በኦሮሞው ገበሬና ትንንሽ ከተማ ኗሪ ውስጥ መጀመሪያ ላይ (ህዳር/ታህሳስ 2008) የተነሳው ጥያቄ ማህበራዊ ሳይንስን ማጥናትና መራቀቅ ሳይጠይቅ “እንደሰው አልተቆጠርንም፣ መሬታችንን እየነጠቁ እንድንፈናቀልና እንድንራብ ተደርገናል፣ አዲስ አበባንም (ፊንፊኔን) ቀምተውና አስፋፍተው ኦሮምያን ለሁለት ሊሰነጥቋት ነው” የሚል አይነት የውስጥ ለውስጥ መልክት ተላለፈ፡፡ በዚህም የየኮሌጁ፣ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃዎች የኦሮሞ ተማሪዎች፣ ወጣቱ ባጠቃላይ፣ አሮጊቶችና ሽማግሌዎች ከዳር እስከዳር ተነቃነቁ፡፡ በጥይትና በዱላ መመታት ለህልውናና ክብር ሲባል ከመሰለፍና ከመተናነቅ የሚገቱ አልሆን አሉ፡፡ በተቀሰቀሰው የህዝብ ቁጣ ውስጥ ለመግባት ክብራችን ተነካ፣ ማንነታችን ተናቀ ከሚል ስሜት ውጭ ምንም እውቀትና ያስተሳሰብ ብስለት የሚጠይቅ ስላልነበር በማእበሉ ውስጥ ያልተካተተ አልነበረም፡፡ የወጣቱ ክፍል ለዚህ ማእበል መፈጠርና ማደግ አንዳንድ መፈክሮችን እያበጃጀ ቢጨምርም ባይጭምርም ገዥዎች ለሚያስፈልገው ግለት የሚመጥን በትር፣ ዱላ፣ ደምና ሞት ወዲያውኑ አቅርበዋል፡፡ ያንን የጠቀስነውን በአለም ዙሪያ የተረጋገጠውን የጭቆና፣ አመጽ፣ ጭቆና ሰንሰለት ለኦሮሞው ህዝብ ዘርግተውለታል፡፡ ከዚያማ የመንግስቱ የጸጥታ ሃይሎችና የፓርቲና ያስተዳደር ሰራተኞች በኦሮሚያ በጠቅላላው መውጫ መግቢያ እንዲያጡ ከቦታ ቦታ ለመዘዋወርም የህዝብን ርህራሄ እንዲሹ ሆኑ፡፡ መነሻው ምን ሊሆን እንደሚችል ለማወቅ የቸገረውን ያህል ማቆሚያው የት እንደሚሆን ለመገመት የሚያቀት የህዝባዊ ተጋድሎ መሰላል ከምድር ወደሰማይ ተዘረጋ፡፡

በአማራውም አካባቢ የተፈጠረው የህዝብ መነቃነቅ አጀማመር በተመሳሳይ ሁኔታ ነበር፡፡ ባዲሱ የህወሃት/ኢህአዴግ መንግስት ውስጥ አማራው ውክልና አልነበረውም፣ አማራው ካገሪቱ ባጠቃይ እየተፈናቀለና እየተገደለ ተቆርቋሪ የለውም ከሚሉ አቤቱታዎችና ክሶች ያላለፈ ስሜት ለአመታት እየተገላበጡ ቢቆዩም ህዝቡ በእምቢታ ወደመነቃነቅ የሚደርስ አይመስልም ነበር፡፡ በተለይ ደግሞ በአማራነት የተሳለ መፈክር ሆነ ቃል አንግቦ ከማእከላዊው መንግስት ጋር ይላተማል ለማለት የሚያስደፍር ፍንጭ አልነበረም፡፡ የኦሮሞ ህዝብ ህዳር 2008 ላይ አንስቶ በይፋ ሲንቀሳቀስ አማራው እከሃምሌ 2008 ድረስ ምንም ድጋፍ ሳያሰማ ቆይቷል፡፡ የኦሮሞው ትግል አማራውን ጎትቶ ከጎኑ የሚያስቆምበት ምንም በግልጽ የሚታይ ምክንያት ስላልነበረው የፖለቲካ ታዛቢዎች ሳይቀሩ ይህን ያማራውን ዝምታና አለመቆርቆር መረዳት ተስኗቸው ነበር፡፡የኦሮሞው ጥያቄ በብዙዎች ዘንድ የነጻነት ብሎም የመገንጠል ተደርጎ ከተሳለ ረዥም ጊዜ ስላለፈው አማራው አገሪቱን ለመቆራረስ ለሚነሳ ሃይል እንዴት አድርጎ ድጋፍ ይሰጣል ተብሎ በመፈረጁ ኦሮሞው ብቻውን ያወጣ ያውጣው እንኳን አልተባለም ነበር፡፡ ቢያንስ ቢያንስ በመንግስት ሃይሎች በኦሮሞዎች ላይ በደረሰው ግድያ፣ ድብደባና እስራት ሳቢያ አማራው (በተለይ ፊደል ቀመሱ ክፍል) መቆርቆሩንና ሃዘኔታውን ይገልጻል ተብሎ ሲጠበቅ አጠቃላይና አሳፋሪ ዝምታ ሰፍኖ እስከ ጎንደሩ የሃምሌ 2008 ሰልፍ ዘለቀ፡፡

የጎንደር ህዝባዊ ሰልፍ አነሳስ ልክ እንደኦሮሞው ከታላላቅ መርሆዎችና አስተሳሰቦች የመነጨ፣ በምሁራኑና በተቃዋሚ ፓርቲዎች የተቋጠረ አልነበረም፡፡ ባገሪቱ ታሪክ የህዝብ መተራመስ፣ መነቃነቅና መሸጋሸግ ያለ ቢሆንም ጥንቃቄ በተሞላው መልክ የማንነትን ጥያቄ ማስተናገድ በተሳነው የህወሃት/ኢህአዴግ መንግስት ትንኮሳ የተጠነሰሰ፣ እየጎለበተ የሄደና በኋላም የፈነዳ ነው፡፡ “ወልቃይት አማራ ነው” የሚለውን መፈክር አንግቦ በሰልፍ የተጓዘው ህዝብ ማንነታችን ተናቀ፣ ከቁም ነገር አልተቆጠርንማና በቁም ከመዋረድ መሞት እንመርጣለን ብሎ ነው፡፡ ዴሞክራሲን እንገነባለን፣ ስርአቱን እንለውጣለን የሚለው አስተሳሰብ ከጧት ትዝ ያላቸው ቢኖሩ እንኳን ቁጥራቸው አነስተኛ ሳይሆን አልቀረም፡፡ እያደር ግን ከመንግስቱ ግትርነትና የሃይል እርምጃዎች መበራከትና የከፋ በደል መፈጸም ጋር ልክ እንደኦሮሞው ትግል የአማራውም ንቅናቄ የስርሰት ለውጥን ጥያቄ አንግቦ መንግስታዊ ድርጅቶችን እያፈረሰ የውስጥ አስተዳደር ማቆም ጀመረ፡፡

የጎንደሩ ህዝብ ጥያቄዎች በማንነት ለይ የተቆናጠጡ በመሆናቸው አማራው ወዲያውኑ ከኦሮሞው ትንቅንቅ ጎን ተሰልፏል፡፡  በገሃድ አውቆት ተናገረም አልተናገረም ኦሮሞው ለሚታገልለት አላማ ቆሟል፡፡ እንዲያውም የአማራው ትግል አቀንቃኞች ባወጣቿው የድጋፍ መልእክቶች ይህንን አስተጋብተዋል፡፡ “የፈሰሰው የኦሮሞ ደም የአማራ ደም ነው”፣ “የታሰሩት የኦሮሞ መሪዎች የአማራም መሪዎች ናቸው” ወዘተ. የሚሉት መፈክሮች በጎንደር ከዚያም በባህርዳር፣ አልፎም በደብረማርቆስና ሌላም አካባቢዎች በሰልፍ ሲሰሙ ለኦሮሞ አቀንቃኞች ብርቱ ድጋፍ ሆነዋል፡፡ የሁለቱን ህዝቦች በደሎች ባቀናጀ መልክ ትግሉን የመቀጠል ፍላጎትም ወዲያው ተዥጎደጎደ፡፡ በይበልጥ የኦሮሞው ትግል አቅጣጫ በውል ያልተሰመረ ስለነበር ኢትዮጵያን በስርአት ለውጥ አማካይነት ወዳዲስ አስተዳደር የማስገባት ህልም መገለጽ ጀመረ፡፡

እንደተባለው የኦሮሞውና የአማራው ትግሎች ባነሳሳቸው የማንነትን ጥያቄ አንግበው በህዝባቸው ላይ ደረሰ የሚሉትን የመናቅና የመዋረድ በደሎች ለማስቀረት ነበር፡፡ ነገር ግን የማንነት ጥያቄያቸው መልስ አጥቶ እንዲያውም በፖሊስና በጦር ሃይል እንዲመቱ በመደረጉ ህይወታቸውንና አካባቢያቸውን ራሳቸው ብቻ በሚያዙበት ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ስር ለማስገባትና ለመገንባት እንዲራመዱ ወሰወሳቸው፡፡ በታዩት ታቃውሞዎችና ትንቅንቆች (ስራ የማስቆም እንዲሁም በቤት የመዋልና መንገድ የመዝጋት አድማዎች) እንደተመለከተው ማእከላዊው መንግስት ከህወሃት/ኢህአዴግ ቁጥጥር ስር ወጥቶ በሌላ እንዲተካ የቆረጡ ይመስላሉ፡፡ ግብግቡ በቀላሉ ወደፍጻሜ ይደርሳል ላለማለት ትልቁ ማስረጃ በየወቅቱና በያቅጣጫው መስፋፋቱና ስር እየሰደደ መሄዱ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የግብግቡን አስቸጋሪ ገጽታ ይጠቁማል፡፡

የህወሃት/ኢህአዴግ መንግስት ቦግ ድርግም የሚል፣ የተበታተነ ያውም “ህገ-ወጥ”ና “ጸረ-ሰላም” ተቃውሞ እንደገጠመውና በቀላሉ እንደሚበትነው ይግለጽ እንጅ በራሱ መገናኛ ብዙሃንና በወዳጆቹ ሳይቀር ስር እየሰደደ፣ ስፋት እያበጀ መሆኑ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ ምን አልባት ብዙ አነጋጋሪ ከሆኑት የግብግቡ ገጽታዎች ውስጥ መፍትሄዎች ከማቅረቡ አቅጣጫ የሚሰነዘሩት ናቸው፡፡ ብዙዎቹ መፍትሄ ተብየዎች ወደሰላም የሚመልሱ ሳይሆኑ ግብግቡን የሚያባብሱ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ይወሰዱ ከሚባሉት እርምጃዎች መካከል ለሰው ህይወትና ለንብረት ውድመቶች ተጠያቂ በሚባሉት ላይ የሚወረወሩት በቃል ደረጃ የሚመስሉ ሆነው ተግባራዊነታቸው ግን አጠራጣሪ ነው፡፡ እንዲያውም ባንድ በኩል በተቀናቃኝነት የተሰለፉት ጭራሽ ወደለየለት አመጸኛነት እንዲገፋፉ ይጋብዛሉ፡፡ በሌላም በኩል እስር ቤቶች ሞልተው እየፈሰሱ ያውም አንዳንዶች በአመጸኞች እየተከፈቱ ተጨማሪ እሰረኞች ማጋበስ ስርአቱን መሳቂያ ያደርጉታል፡፡ ለዚህ አይነት “አደጋ” የሚጨነቅ ባይኖርም፡፡

ለህወሃት/ኢህአዴግ እጅግ አስቸጋሪው ግብግቡን ከተለመደው “ጦር አምጣ” አስተሳሰባቸው ውጭ ማሰብ ነው፡፡ ከሁሉ አስቀድሞ ግብግቡ ከህግ ማስከበር ንትርክ የዘለለ ነው፡፡ የስርአቱን አሰራር የመጣስ ወይም የማረም ሳይሆን ህልውናውን የመተናነቅ ነው፡፡ ባጭሩ ህወሃት/ኢህአዴግ በሚሰፍረው ልክ መኖር አይሆንልንም፤ በቃን የሚል ነው፡፡ በስርአቱ ስር ተቀፈደድን፣ ታፈን፣ ተመዘበርን፣ ተጨፈጨፍን ለሚሉ ወገኖች መልሱ ህጉን አክብሩ፣ ሰላም ፍጠሩ ሊሆን አይችልም፡፡ ፍየል እዚህ ቅዝምዝም ወዲያ እንደሚሉት፡፡

ህወሃት/ኢህአዴግ ይህነን መሰረታዊ ጉዳይ መጨበጥ ተስኖት እያደር በጦር ስልት ያለውን ሃይል እያሰማራ በሁሉም ረገድ እየተዋረደና እየተናቀ ነው፡፡ ተራው ህዝብ ከሚችለው በታች ስለሚያስብና የቡጢና የዱላ፣ የጥይትና የእስራት ጋጋታ ስለሚያካሂድና ስለሚያከታተልም አመጹ አለመገታቱን ከራሱ ድክመት ጋር ኣያይዘውም፡፡ አስተዳደሩ ሲበክት ተጠያቂ የሆኑትን አባሎቹን ቢያንስ ማባረር እቅቶት በህዝብ ዘንድ አንድም ቅንጣት ተሰሚነት እንዳልቀረው ሁሉ ዛሬም ለተቀሰቀሰው አመጽ “ጦር” መስበቅ ብቻ የሚታያቸውን ማስወገድ አልተቻለውም፡፡ ከሁሉ አስቀድሞ “መርከቢቱ” እንዳትሰጥም በክብደታቸው የሚጫኗትን ማራገፍ የመጀመሪያው የሲቃ እርምጃ መሆን ሲገባው ሁሉንም እንዳዘለ አይናቸው እያየ ገደል ሊገቡ ነው፡፡

ህወሃት/ኢህአዴግን የጎዳቸውና የተለመደውን የጦርነት ፖለቲካ እየሰበቁ እንዲዘልቁ ያደረጋቸው ምናልባት የተቃዋሚዎቻቸው አለመታወቅ ሊሆን ይችላል፡፡ የአማራውንም የኦሮሞውንም ትግል የሚመሩት እገሌና እገሊት ተብሎ ተዘርዝሮ ማንነታቸው የማይታወቅ በጥቅሉ ግን የወጣቱ ክፍል (“ጎበዝ አለቃ” ባማራው፣ “ቄሮ” በኦሮሞው) መሆናቸው ከኢምንትነት ቆጥሯቸው ይሆናል፡፡ በሁለቱም በኩል ዱሮ ከሚታወቁትና ስም ካበጁት ፓርቲዎችና ድርጅቶች ጋር በመነጠልና እነሱን በመናቅ የትግል ጎዳና ስለገቡ ለገዥዎቹ ቀርቶ ለህዝቡ ግራ የሚያጋባ ሆኗል፡፡ የተለመዱትን ድርጅታዊ አሰራሮችና የፖለቲካ ስልቶች ወደጎን ጥለው፣ ህጉን ሳይከተሉና በህጉ ሳይታወቁ በመንቀሳቀሳቸው በተቀላጠፈ አኳኋን ውጤት ለማስመዝገብና ከመንግስቱ ስለላና ቁጥጥር መዋቅሮች ውጭ ህልውናቸውን ለማረጋገጥ ችለዋል፡፡ መንግስቱ ራሱ ባገሪቱ የዘረጋውን የስለላና የአንድ ለአምስት መዋቅሮች አምልጠውና ተቋቁመው መኖራቸው ለብቻው አስደናቂ ነው፡፡

በዘመናችን የፖለቲካ ትግል ታሪክ ስም ያበጁትንና ቀደም ብሎ የተቋቋሙትን (ኦነግ፣ መላ ኢትዮጵያ፣ መድረክ፣ ኢዴፓ) በግልጽም ሆነ በተዘዋዋሪ መልክ ነቀፎና ወደ”ጡረታ” አስገብቶ ህልውናውን በድርጊቱ ብቻ እያሳወቀ መገኘቱ ጭራሽ አዲስ ምእራፍ ነው፡፡ የቀድሞው የተማሪዎች ንቅናቄ ህዝቡን ለመቀስቀስ ብቻ ሲጠቀምበት የነበረውን ዘዴ ሁሉ እነዚህኞቹ አስር ክንድ ያህል አስረዝመውና ለዋውጠው አገዛዙ ጋር ግብግብ ወደመፍጠር አሻግረውታል፡፡ ቅስቀሳ፣ መግለጫ፣ ፕሮፓጋንዳ የሚባለውን የትግል መጸነሻና መገንቢያ እጅግ አስፈላጊ የመጀመሪያ ምእራፍ “ዘለው” ከድርጊታቸው ጋር ባንድ ላይ አዋህደው ለመንግስቱ ማስጠንቀቂያ እንኳን ሳይሰጡ በፈለጉበትና ባቀዱት መንገድ ትንቅንቅ ይገጥማሉ፡፡ ፊርማ አሰባስቦ ብሶታችን ይኸ ነውና ይስተካከል የሚል ነገር የለም፡፡ በራሪ ወረቀት አሰራጭቶ ይኸ ይሁን ያ የሚል ማስጠንቀቂያ አልተሰማም፡፡ ለዚህም ትልቁ ምክንያት ያነገቡት አላማና ጥያቄያቸው ከላይ እንዳነሳነው ለማይማንም ማስረዳት የማያስቸግር ስለሆነ ነው፡፡ ያካባቢያቸውንና ያስተዳደራቸውን ሁኔታ አስተውለው “ተንቀናል ክብራችን ይመለስልን” ብለው ከደመደሙ በኋላ በተቃውሞ ለመነሳት ብዙ ትንታኔና መግለጫ ለምን ያሻቸዋል; በዚህ ረገድ አድራጎታቸውና አቋማቸው የዱሮውን በተለይ በላቲን አሜሪካ የተከናወነውን የፎኮ (በቡድን ሆኖ ትጥቅ አንግቦ የሚያነቃና የሚታገል) እንቅሰቃሴ ይመስላል፡፡ የኛዎቹ የታጠቁ ባይሆኑም፡፡ ለጊዜው፡፡

በርግጥ በህዝቡ መሃል የተፈጠረውና የተስፋፋው የማንነት ጥያቄ ባንድ ጀንበር አልተቀጣጠለም፡፡ ከዚህ በፊት ባቀረብነው አንድ ጽሁፋችን ላይ ከህወሃት/ኢህአዴግ ህገመንግስት እጅግ የተጠቀመው አማራውና ኦሮሞው ነው ብለን ነበር፡፡ ባንጻሩ የትግራይ-ትግርኝት ህዝብ፣ አፋሮች፣ ኩናማዎች፣ ሳሆዎች በሁለትም በሶስትም ተቆራርጠው ከፊል አካላቸውን አጥተዋል፡፡ በቲዎሪ ደረጃ አማራና ኦሮሞ ግን ያካባቢ የተፈጥሮ ካርታቸውን ከሞላ ጎደል ተከትለው የራሳቸውን አገዛዝ ለማቋቋም በሩ ተከፍቶላቸው ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ክፍለ ሃገርነታቸው የሚጠበቅባቸውን እስካሟሉ ድረስ ባንድ አጠቃላይ (“ፌዴራል”) መንግስት ስር ተገቢውን ሚናቸውን ሊያገኙ የሚችሉ መስሎ ነበር፡፡

የህወሃት/ኢህአዴግ ህገመንግስት ለህዝቡ የሰጠውን መብት እየሸራረፉና እያጠፉ አገሪቱን እንደግል ንብረታቸው፣ ህዝቡን እንዳገልጋያቸው ያደረጉት ገዥዎች ህገመንግስቱ ሊያጎናጽፈው ያለመውን የማንነት ጉዳይ ደብዛውን ሲያጠፉት ቆይተዋል፡፡ በማናለብኝነት፡፡ በጣም በቅርቡ እንኳን የኮንሶ ህዝብ፣ ከነሱም በፊት በትግራይ ውስጥ የእምባስነይቲ አካባቢ ህዝብ መንግስቱ የጫነባቸውን አስተዳደራዊ መዋቅር አንቀበልም፣ አንፈልግም በማለታቸው ማን ጆሮውን ሰጣቸው; ጭራሽ የተለመደውን የገዥዎች እርምጃ ማለትም የፖሊስና ጦር ሰራዊት ድብደባና ግድያ አልፎም እስራት አዠጎድጉደውባቸዋል፡፡ በዚህ አይነት በያካባቢው ህዝብ ላይ በገዥዎቹ የተፈጸሙት የንቀት፣ የማዋረድ ተግባሮች ህዝቡ አጻፋውን እንዲመልስ ሲገፋፉት ኖረዋል፡፡ “ጦርነት መስራት” ሙያችን ነው ባዩ ገዥ ክፍል ተቃዋሚ ድርጅቶች በይበልጥ በከተማ የሚውተረተሩባቸውን ተግባራት በጋዜጣ ላይ መግለጫ በመስጠት እንዲወሰኑ በማስገደዳቸውና መፈናፈኛ በማሳጣታቸው፣ በገጠር የሚንቀሳቀሱባቸውም ጥንካሬ ስላላበጁ ለማናለብኛቸው ማስተንፈሻ አጥተው ቆይተዋል፡፡

ሳይደግስ አይጣላም እንዲሉ መነጋገርና መደራደርን የማያውቅ በህዝብ ውስጥ ግን እንደለቡ የሚዘዋወር የበደል ስንክሳር እየደረደረ ከሊቅ እስከደቂቅ አስተባብሮ የሚያስነሳ ተፎካካሪ ፈጠረባቸው፡፡ ይህ ክስተት የነሱው ፍጡር መሆኑን ማወቅ ቢሳናቸው አያስገርምም፡፡ ራሳቸው ያወጡትን ህግ እየጣሱ፣ ከ1967 ወዲህ የህዝብ ሃብት የተደረገውን መሬት እየነጠቁ የግል ሃብት ሲያካብቱበት፣ ተራው ሰው መጠለያ ለመስራት ደፋ ቀና ሲል በጉልበታቸው ሲደመስሱበት፣ የገዠው ፓርቲ አባል ካልሆኑ የመኖርና የመስራት እድል ሲነፍጉ፣ በነሱው ቀጭን ውሳኔ መኖር ወይም መሞት ለማንኛውም መብት ተፋላሚ ሲታደል ምድሪቱ ራሷ አፍ አብጅታ አለመጮኋ ያስገርማል! (መጥኔ ለኤርትራ ህዝብ፣ የኛ እንኳን ሌላው ሌላው ቢቀር በብዛታችን ምክንያት ያፈናና የድፍጠጣው መጠን ከጌቶቻችን ቁጥጥር ውጭ እንድንሆን “ረድቶናል”!)

በመንግስቱ መገናኛ ብዙሃን የሚወተወተውን ላዳመጠ አገሪቱ በልማት ጎዳና እየገሰገሰች፣ ምቀኞች በክፋት ተነሳስተውና ለውጭ ሃይሎች መሳሪያ ሆነው ህዝቡንና ያገሪቱን የእድገት እድል እንደሚጎዱት ተደርጎ ነው፡፡ ራሳቸውን ለመሸንገል የሚከለክላቸው ነገር ስለሌለና እውነተኛውን ገጸታ መሳል ከቶ የሚተናነቃቸው ጉዳይ ስለሆነ ገዥዎቹ ገድል እየገቡ እንኳን ከአደጋው እንዲድኑ አይመክሩም፡፡ በመፍትሄ ረገድ ማቅረብ ያለባቸውንማ በጨረፍታም አይነኩት፡፡

ባንድ አገር ውስጥ የህዝብ አመጽ ቀርቶ ጎልቶ የሚታይ አቤቱታ ሲታይ አይነተኛ ምላሹና ማስተንፈሻው አቤቱታውን በሃቅና በፍጥነት መርምሮና እውነተኛውን ተቀብሎ በከፊልም ሆነ በሙሉ ማስተካከያ ማብጀት፣ እርምት መፈጸም ነው፡፡ እንደአቤቱታው አይነትና በህዝቡ ውስጥ ያለውን ስሜት በውይይት ለመለወጥ ከመቻሉ ወይም አለመቻሉ ጋር ተገናዝቦ፡፡ የአዲስ አበባው የከተማ ማሰፋፊያ እቅድ ለአካባቢው ኦሮሞ ህዝብ ጎጂነት አለው ሲባል ወዲያውኑ እቅዱን መሰረዝ ሲቻል በማናለብኝነት ተግባራዊ እንዲደረግ መታዘዙ የገዥዎቹን እብሪትና ለህዝቡ ያላቸውን ንቀት ገልጾዋል፡፡ ህዝቡ በንቀት ታየን ሲልና ማስረጃዎቹና ተጓዳኝ ብሶቶችም እየተደራረቡ ሲቀርቡ ለተቃውሞው ስር መስደድ ምክንያት እንዳይሆኑ አፋጥኝ ውሳኔ ብልጥ ከሆነ መንግስት ይሰነዘር ነበር፡፡ ያም ቢቀር በተለያዩ ጊዜዎች የይቅርታና ለቅሶ ቀረሽ ልመናዎች ከማጉረፍ አልፈው ተግባራዊ ምላሾች መስጠት ይችሉ ነበር፡፡

የመጀመሪያዎቹ የመለሳለስና የመፈጋፈግ ደረጃዎች ካለፉና ህዝቡ ጆሮውን በፍጹም ለመንግስት መስጠት ከተወ በኋላ (የቅርቦቹን ብቻ ለመዘርዘር በኦሮሚያም፣ በአማራም፤ በኮንሶም) የሚጠበቁት መፍትሄዎች ተደራራቢ ሆነዋል፡፡ ዛሬ በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት የገጠመው ነጠላ ችግሮችን እየዘረዘሩ እነዚህን ፈጽምልን ከማለት ያለፈ መሆኑን መገንዘብ ያሻል፡፡ ህወሃት/ኢህአዴግ በምንም መልክ አይድረሱበን፤ እራሳችን በምናስበውና በተመቸን አኳኋን ችግሮቻችንን እንፈታለን የሚለው አስተሳሰብ በተጠቀሱት አካባቢዎች ሰፍኗል፡፡ ባጭሩ መንግስቱን እያቅማሙም ቢሆን የመቀበልና በሱም የመታዘዝ ጊዜ አብቅቶለታል፡፡ “ጦር አምጣ” ተብሎ ነበር፤ “ጦሩ” መጥቶ ሜዳው ላይ ፈሷል፡፡ ይህ “ጦር” ግን ህዝቡን ከዳር እስከዳር ማነቃነቅ የሚችል ሆኖ ገዥውን በጉልበት አሸንፎ ስልጣን ለመቀማት ጉልበት የለውም፡፡ ባሁኑ ወቅት ሁለቱም  (ገዥዎችም ሆነ ተቃዋሚ) ተፋላሚ ወገኖች መሸናነፍ ደረጃ ላይ አልደረሱም፡፡ ከጊዜ ብዛት አሸናፊው ይለያል ቢባል እንኳን በመካከል የሚፈሰው ደም፣ የሚጠፋው ንብረትና ባገሪቱ ኢኮኖሚና አጠቃላይ የወደፊት እድል ላይ የሚያንዣብቡት አደጋዎች የመሸናነፉን አቅጣጫ ማንም እንዳይከጅለው ያደርጉታል፡፡ ከዚህም በላይ የገዥዎች ይዞታ እያደር እያሽቆለቆለ፣ እስካሁን ያልተነሱበት ያገሪቱ ሌሎች ክፍሎችም ከተቃዋሚው ጎራ የመጨመራቸው እጣ እየጎላ እንጅ እየቀነሰ ሊሄድ አይችልም፡፡ ስለሆነም ያገሪቱን ይህንን ተጨባጭ ሁኔታ በጥሞና ለተከታተለና ላጤነ የሚጠበቀው ያልተለመደ፣ ፍጹም አዲስ መፍትሄ መሻት ነው፡፡

አንደኛ ህወሃት/ኢህአዴግ በ”ጦር አምጣ” ፖለቲካውና እብሪቱ ያመረታቸውን ተቀናቃኞቹን በመብራት እየለቀመ ከምድር ገጽ ለማጥፋት እንደማይቻለው ማመን አለበት፡፡ ማናቸውም የጉልበት እርምጃዎች ሁኔታዎችን እያባባሱ መምጣታቸውንም አብሮ ሊቀበል ይገባዋል፡፡ እስካሁን የተከሰቱ ድርጊቶችን የሚገልጹ አሃዞችን በመቀመር ሆነ ባገሪቱ ላይ የሰፈነውን የግጭት ስጋት ስሜት መስፋፋት በማሰባሰብ ይህንን እውነታ አለመጨበጡ አስተዛዛቢ ነው፡፡ ያገሪቱን ሃብት የሚከሰክስበት ግዙፉ የስለላ መዋቅርም ቢሆን የገለጽነውን እይታ ሳያቀርብለት ይቀራል ብሎ መገመት ያስቸግራል፡፡ በቁጥጥሩ ስር ባሉ የዜና አውታሮቹና በመንግስቱ ሹማምንት አፍ ራሱን በመደለል የሚያራግባቸው ትእይንቶች ምን ያህል ከእውነት እንደራቁ ህዝቡ ታዝቦ ታዝቦ የጨረሰው፣ በፌዝና በቀልድ የሚቀባበለው ሆኗል፡፡

ሁለተኛ ከ20ኛው ክፍለዘመን ጀምሮ በሽምቅነት መልክ የሚነቃነቁ ትግሎችን ለመቋቋም ብሎም ለመግታት አይነተኛ መፍትሄው “አሳውን ለመያዝ ውሃውን ማድረቅ” የሚባለው በኢትዮጵያ ወቅታዊ ትንቅንቅ ውስጥ የሚሰራ አይመስለንም፡፡ አሳው ከውሃው ሊለይ አይችልምና! ባንድ በኩል ያስተሳሰብና የቲዎሪ ምጥቀት የታጋይነትና አታጋይነት መለኪያ ባልሆኑበት ትንቅንቅ ውስጥ ሁሉም መሪ ሁሉም ተመሪ ይሆናል፡፡ ንቅናቄውን የሚመራው አስተሳሰብ (ለገዥዎቹ በሚጥመው ቃል “ራእይ”!) ወለሉ ላይ የተኛ ወይም የተጋደመ ስለሆነ ሁሉም የብሄረሰቡ አባሎች በእኩልነት የሚጋሩት ነውና፡፡ የትግሉን አድማስና የደጋፊ አይነት የሚወስኑት አስተሳሰቦች ወለሉ ላይ አስከተነጠፉ ድረስ ከሚመለከታቸው ብሄረሰቦች መሃል ግለሰቦችን እየነቀሱ የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰድ ለትግላቸው መሳኪያ ተጨማሪ ግለት ከመስጠት አይዘልም፡፡ (እስር ቤቶችም የአመጹ ማሰራጫና ማደራጃ ትምህርት ቤቶች ሆነው ቆይታዋል፡፡ ስየ አብርሃ ምስክርነቱን ከመስጠቱ በፊት ጀምሮ!) ማንም ከሜዳው በየትኛውም አኳኋን ቢገለል የማይተካ አይደለም፡፡ ልዩ ስልትና አስተዋጽኦ ያለው ሰው ብቻውን እያራገበ የሚያሳድገው ወይም በድክመቱ ምክንያት የሚያኮስሰው ተቃውሞ ስላልሆነ ለገዥዎቹ ያለው ብቸኛ “ምርጫ” ለህዝቡ ጥያቄዎች ተገቢዎቹን ምላሾች መስጠት ነው፡፡

ሶስተኛ ከላይ እንደተጠቀሰው የህዝቡ ጥያቄዎች ከነጠላ ይቺን አድርጉልን ያቺን አግዱልን አልፎ ባንድነት በአገዛዙ ላይ ህዝባዊ ውክልና ይኑረን ሆኗል፡፡ ህዝቡ ባሻው መልክ አገዛዙን እንደገና ሙሉ በሙሉ የማዋቀርም ባይሆን ከላይ እስከታች እየፈተሸ ጉድለቱን የማረምና የማስተካከል ፍላጎት ገልጾዋል፡፡ ገዥው ክፍል ከላይ እንዳተትነው ተቀናቃኞቹን ሙሉ በሙሉ ማስወገድም በቁጥጥሩ ስር ማስገባትም ስለማይችል የሚቀረው አማራጭ በድርደር የጋራ መፍትሄ መሻት ነው፡፡ ተጋጣሚ ሃይሎች አንዱ ከሌላው ተሸሎና አይሎ የተነሳበትን አላማ ማሳካት ካልቻለ ባለም ዙሪያ የታየውና በተግባር ላይ የዋለው ጤነኛ አማራጭ የድርድር መፍትሄ መሻት ነው፡፡ የኛዎቹ ገዥዎች በተደጋጋሚ “ጦርነት መስራት” ልማዳቸው መሆኑን መግለጽ ስለማይታክታቸው ይህንን አማራጭ የሽንፈት ምልክት ያደርጉት ይሆናለ፡፡ ነገር ግን ዛሬም እንደዱሮው ገዥዎቹ እውነት ከኛ ጋር ነው እስካሉ ነገር ግን የነሱን እውነት እንደበፊቱ ያለተቀናቃኝ በተግባር ለማሳየት እስካልቻሉ ድረስ እብሪታቸውን አምቀውና ዋጥ አድርገው ወደድርድር መቅረብ አለባቸው፡፡ ቢያንስ አገሪቱ ላይ የጀመሩትን የኢኮኖሚ መሻሻል እድል ከአደጋ ለማዳን የድርድሩን አስፈላጊነትና ወቅታዊነት ተቀብለው ወዳዲስ ምእራፍ ፈጥነው ለመግባት መዘጋጀት አለባቸው፡፡ ይህን ባያደርጉ በታሪክ ፊት ከፍተኛ ተጠያቂነታቸው እንደተመዘገበ ለዘላለም ይኖራል፡፡

አራተኛ ገዥዎቹ ከተቀናቃኞቻቸው ጋር ለመደራደር ከተነሱ የመጀመሪያው አርምጃቸው ነጻ የመነጋገሪያ መድረክ ለመፍጠር የመገናኛ ብዙሃኑን ከቆየው መንግስታዊ ተጽእኖና ስውር ክልከላዎች ማላቀቅ ነው፡፡ ይህን ለማረጋገጥም በፖለቲካ ምክንያት የተያዙ እስረኞችን መፍታት፣ የመገናኛ ብዙሃኑን ከመንግስት ባለቤትነትና ቁጥጥር ስር ማውጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የዚህ እርምጃ ዋና አላማ ነጻ የፖለቲካ ውይይት መድረክ በመፍጠር ላገሪቱ የሚበጁትን ሃሳቦችና መመሪያዎች ከሁሉም ወገኖችና አቅጣጫዎች እንዲቀርቡ ማስቻልና ይበልጥ ተቀባይነት ያለውን አንጥሮ ለማውጣት ነው፡፡ በተጨማሪም ባገሪቱ ጉዳዮች ላይ ያገባናል የሚሉ ሃይሎች ሁሉ  በግልጽ እንዲወጡ፣ ማንነታቸውም እንዲረጋገጥ ይረዳል፡፡

አምስተኛ የድርድሩን ይዘትና አቅጣጫ በተመለከተ ተደራዳሪዎቹ መንግስት ላይ ካሉት በተጨማሪ ተቃዋሚ የሚባሉትን ሁሉ (ከነጠብመንጃ ያዥዎቹ) ማጠቃለል ይገባዋል፡፡ በተሰብሳቢዎቹ ማንነትና በተግባሮቹ አንጻር ከዱሮው በተሻለ መንገድ ሁሉን አቀፍ በመሆን የማያዳግም የፖለቲካ መፍትሄ ለማብጀት እመርታ ማሳየት ይኖርበታል፡፡በርግጥ ባለጠብመንጃዎች በድርድሩ ለመካፈል የተኩስ ማቆም ቃል ኪዳን እንዲፈጽሙና በተግባር እንዲያውሉ ይገደዳሉ፡፡ ሄዶ ሄዶ የድርድሩ አላማና ተግባር ባገሪቱ ላይ ለሰፈኑ ችግሮች መፍትሄዎችን አውጥቶና ተስማምቶ ለህዝብ ውሳኔና ድርጊት ማዘጋጀትና ማቅረብ ይሆናል፡፡ በዚህ መንፈስ የተደራዳሪዎች ድርሻ እጅግ ጊዜ የማይሰጡትን ከዘላቂ ተግባራት ለይተው ውሳኔዎችን ማብጀት ይሆናል፡፡ ከሁሉ አስቀድሞም ላገሪቱ አዲስና ጊዜያዊ መንግስታዊ አመራር በመፍጠር የህዝቡን የእለት ተእለት ኑሮ በሰላም እንዲካሄድ ያደርጋሉ፡፡ ከሱ በተጨማሪ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችን (የሰዎችን መዘዋወር ጭምር) የሚያስተጓጉሉ ድርጊቶችን ያስቆማሉ፡፡ የጦር ሃይሉ ወደመደበኛ ተልእኮው እንዲመለስና ህገመንግስታዊ የስራ ወሰኑን እንዲያከብር ያደርጋሉ፡፡

የድርደሩ አስፈላጊነትና መነሻ ማንም ሃይል ለብቻው ወይም በቡድን መልክ ያገሪቱን ወቅታዊና ዘላቂ አኗኗር ለመወሰንና በተግባር ለማረጋገጥ አለመቻሉ ስለሆነ ሁሉም ሃይሎች የህዝብ ውክልና አለን፣ ለህዝቡም እንቆማለን እስካሉ ድረስ አበክረው ሊቀበሉትና በተግባር ሊተረጉሙት መነሳሳት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ በታሪክ አልፎ አልፎ የሚከሰት ድንቅ ግዳጅ መሆኑን  ተረድተው የየድርሻቸውን መፈጸም የማይችሉ ወይም በእንቅፋትነት የሚግተረተሩ ሁሉ ፊት ለፊት ፈጦ የሚጠብቃቸው እድል ወደአቧራነት መለወጥ ብቻ ይሆናል፡፡

 

* Ê/` ›có ›”Åh¨< ቦረና ት/ቤት’ Î’@^M ©”Ñ@ƒ’ k. ኃ.Y.“ K”Å” ¿’>y`e+ }Ua c=”Òþ`“ ›=”ÓL”É ¿’>y`e+­‹ uýaôc`’ƒ IÓ ›e}UbM:: ›e}Á¾ƒ “K:- a_endeshaw@yahoo.co.uk

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.