ዉይይት ባለ ወደ ወህኒ – #ግርማ_ካሳ

yidnekahew-kebede-satenawnews
ይድነቃቸው ከበደ

ወንድም ይድነቃቸው ከበደ በአሁኑ ወቅት በወህኒ ነው የሚገኘው። ታፍኖ ከመወሰዱ በፊት በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ የሚከተለዉን ጽፎ ነበር። ለአገርና ለሰላም ይበጅ ዘንድ እንወያይ ነበር ያለው።

ይድነቃቸው ከበደ የሰማያዊ ፓርቲ የምክር ቤት ሰብሳቢና የሕግ ባለሞያ ነው። ወያኔዎች ወደ ወህኒ ሲወስዱት አንዱ የከሰሱበት ምክንያት ከ”ግርማ ካሳ” ጋር ቻት አድርገሃል በሚል እንደሆነ ሰምቻለሁ።

ወያኔዎች በክሳቸው ላይ “ግርማ ካሳ”ን ሲጠቅሱ ይድነቃቸው የመጀመሪያቸው አይደለም። ሃብታሙ አያሌው እና ጌታቸው ሸፍራውን ” የጥፋት ሃይል ከሆነው፣ የግንቦት ሰባት አመራር ግርማ ካሳ ጋር ትገናኛላችሁ” ብለውም ከሰዋቸዋል።

እንግዲህ አለም ይፍረድ ፣ ላለፉት 11 አመታት የሰላማዊ ትግልን በመደገፍ፣ እንደ ግንቦት ስባት ያሉ ድርጅቶችን በመተቸት፣ ከገዢው ፓረቲ ጋር እርቅና መግባባት ያስፈለጋል በማለት፣ አገዛዙ የሚፈጽማቸውን ጠቃሚ ፕሮጅክቶች በመደገፍ የሚታወቀው ግርማ ካሳ “የጥፋት ሃይል፣ የግንቦት ሰባት ያዉም አመራር አባል” አድርገው ከወሰዱት ፣ ታዲያ ማን ነው በነርሱ አይን “ሰላማዊ” የሚባለው ?

“ሁሉን አቀፍ ውይይት ያስፈልጋል”
አቶ ይድነቃቸው ከበደ (የሰማያዊ ፓርቲ ብሔራዊ ምክር ቤት ሰብሳቢ)

በአገራችን የተቀሰቀሰው ህዝባዊ ተቃውሞ ህዝብ በአገዛዙ ሥርዓት ላይ በከፋ ደረጃ ቅሬታ እንዳለው የሚያመላክት ነው፡፡ ገዢዉ መንግሥት በአገራችን የተቀሰቀሰው ህዝባዊ ተቃውሞ፣ ከዚህ ቀደም እንደሚያደርገው ሸፋፍኖ ለማለፍ ያልተቻለው ከመሆኑም በላይ፣ ተቃውሞ መኖሩን አምኖ ተቀብሎአል፡፡ ነገር ግን የተቃውሞው ምክንያት አገዛዙ እንደሚለው፤ “የኢኮኖሚ እድገት ያመጣው የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ነው፡፡” ለማለት በግሌ እቸገራለሁ፡፡ እኔ ለህዝባዊ የተቃውሞ እንቅስቀሴው ትክክለኛው ምክንያት፣ህዝባዊ ቅቡልነት ያለው የመንግሥት አስተዳደር እጦት ያመጣው ነው! ብዬ አምናለሁ፡፡ በመሆኑም ዋናው ምክንያት ለህዝብ የቆመ፣ ከህዝብ የተመረጠ የመንግሥት አስተዳደር መሻት እንደሆነ በግሌ ለመገንዘብ ችያለሁ፡፡ የኑሮ ሸክሙ የከበደው፣የእለት እንጀራ ከስንት አንዴ በእድል የሚመገብ ህዝብ በበዛበት አገር፣ የኢኮኖሚ እድገት ያመጣው ጥያቄ ነው፤ ማለት ግራ ያጋባል። ዛሬ ላይ ከጫፍ እስከ ጫፍ የተነሳው ተቃውሞ እዚህ ደረጃ ከመድረሱ በፊት፣የተረጋጋ የፖለቲካ ሽግግር በማድረግ፣ የዜጎች ጥያቄ እንዲመለስ በተለያየ መልኩ ጥረት ሲደረግ ነበር፡፡ ለሚደረጉ ጥረቶች ሁሉ በአገዛዙ በኩል ይሰጥ የነበረው ምላሽ ተገቢ ባለመሆኑ ችግሩ ሊከሰት ችሎአል፡፡ ይህም እንደሚሆን ይጠበቅ ነበር፡፡

ዛሬ ማን ምን መስማትና ማየት እንዳለበት በአዋጅ የሚደነገግበት ደረጃ ላይ ተደርሷል። ህዝባዊ ተቃውሞ መኖሩን አምኖ የተቃውሞ ምክንያቱ ደግሞ “የኢኮኖሚ እድገት ያመጣው የመልካም አስተዳደር ጥያቄ” ነው፡፡ በማለት ያመነ መንግስት፣ በአስቸኳይ አዋጅ አማካኝነት ምላሽ ለመስጠት መሞከሩ አስገራሚ ያደርገዋል፡፡ የአገዛዙ ስርዓት አሁንም ቢሆን እየሄደበት ያለው መንገድ ነገሮችን ይበልጥ የሚያወሳስብ እንጂ ወደ-መፍትሔ የሚያመራ አይደለም፡፡ የመንግሥት ምላሽ ከህዝቡ ጥያቄ ጋር ፈጽሞ የሚገናኝ አይደለም፡፡ ነገሩን ይበልጥ አስገራሚ የሚያደርገው ችግሩን ለመፍታት ጥረት እያደረግሁ ነው የሚለው መንግሥት፣ እንደ መፍትሔ የተጠቀመው የዜጎች መሰረታዊ መብት በአዋጅ መገደብ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ በፍፁም ለህዝብ ጥያቄ ምላሽ ሊሆን አይችልም ፡፡

አሁን በአገራችን የሚታየው ችግር ከስርዓት አቅም በላይ ነው፡፡ “ላልተካደ ጉዳይ” ማስረጃ ማቅረብ በህግ አስገዳጅ አይደለም እንደሚባለው፣ገዢው መንግሥት ተቃውሞውን ለመቋቋም ከመደበኛ ህግ አልፎ የተለየ አዋጅ ለማውጣት ተገድዷል። ይህም የችግሩን አሳሳቢነት አመላካች ነው፡፡ ለችግሩ መፍትሔ የሚገኘው ግን በችግሩ ዙሪያ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ በቅድሚያ የጋራ ግንዛቤ ሲኖራቸው ብቻ ነው፡፡ ለዚህም እንዲረዳ ሁሉን አቀፍ ውይይት ሊካሄድ ይገባል፡፡ መፍትሔው ህዝብ ላነሳው መሰረታዊ ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ መሆን አለበት፡፡ ይህ እንዲሆን ሁሉን አሳታፊ ውይይት በአስቸኳይ መካሄድ አለበት፡፡ አሁን ሥልጣን ይዞ የሚገኘው አካል ከማንም በላይ ለዚህ ጉዳይ ተባባሪ ሊሆን ይገባል፡፡ በተለይ ዘላቂ የሆነ መፍትሔ ለማምጣት እንዲረዳ፣ በአገር ውስጥና ከአገር ውጪ የሚገኙ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን፣ የሰብአዊና የዲሞክራሲ መብት ተሟጋቾች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣በትጥቅ ትግል ተሳታፊ የሆኑ (የተኩስ አቁም ስምምነት በማድረግ)፣ምሁራን፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የህዝብ እንደራሴዎችና ሌሎች የሚመለከታቸው በሙሉ የሚገኙበት አስቸኳይ የመፍትሔ ሃሳብ የሚመነጭበትና ስምምነት ላይ የሚደረስበት ውይይት መካሄድ አለበት፡፡ የውይይቱ ቅድመ ሁኔታና የመወያያ ነጥቦች እንዲሁም ተዛማች ነገሮች የዚሁ አካል ሊሆን ይገባል የሚል የግል አስተያየት አለኝ፡፡
(ይህ አስተያየት በግል የቀረበ እንጂ የፓርቲ አቋም የሚመለከት አይደለም)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.