የትግራይ ክልል በአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚፈለጉትን አቶ ወልዱ ወልደአረጋይ አሳልፌ አልሰጥም አለ

gihon-hotelበባህርዳር ከተማ የጊዮን ሆቴልን ያለጨረታ ተከራይተው ለ20 አመታት ሲጠቀሙበት የነበሩት አቶ ወልዱ ወልደአረጋይ በአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ቢታዘዙም የትግራይ ክልል አሳልፌ አልሰጥም ማለቱ ተነገረ።
የአቶ መለስ ዜናዊ ዘመድ እንደሆኑ የሚታወቁት አቶ ወልዱ ወልደ አረጋይ ከ1987 ዓም ጀምሮ ለ 20 አመታት የመንግስት የነበረው የባህርዳር ጊዮን ሆቴል ያለጨረታ ተከራይተው ሲገለገሉ ቆይተዋል። ይሁንና አቶ መለስ ከሞቱ በኋላ የባህርዳር ነዋሪዎች ባደረጉት ጫና ሆቴሉ በ 2007 መጨረሻ ላይ ለመልቀቅ ተገደዋል።

በዚሁ ጊዜም ከግብር ማጭበርበር ጋር በተያያዘ በፌዴራል ገቢዎች ቢሮ ባህርዳር ቅርንጫፍ ተከሰው በመጨረሻ የ7 አመታት እስር ቢፈረድባቸውም ይግባኝ ጠይቀው እነ አቶ ስብሃት ነጋ ባደረጉት ጫና በዋስትና ከእስር መለቀቃቸው ይታወሳል።

ጉዳያቸው ከታችኛው ፍርድ ቤት ጀምሮ ይገባኝ እየተጠየቀበት ወደ አማራ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ደርሶ ውሳኔያቸው ቢፀናባቸውም አቶ ወልዱ ከባህር ዳር ወደ አድዋ በመሄድ ለጊዜው መሸሻቸው ይነገራል።

ይህንኑ ተከትሎ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በጋዜጣ ተጠርተው ሊገኙ ባለመቻላቸው በፖሊስ ተይዘው እንዲቀርቡ በመታዘዙ ይህንን ለማስፈጸም የክልሉ ፖሊሶች ፍለጋ ላይ ቆይተዋል።

gihion-hotel-2በዚሁ መሰረት የአማራ ክልል ፖሊስ አባላት ወደ አድዋ በማምራት በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ መሰረት አቶ ወልዱን በቁጥጥር ስር ለማዋል ቢሞክሩም የትግራይ ክልል አሳልፌ አልሰጥም ማለቱ ተነግሯል።

በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ግዳጅ የተሰጣቸው የአማራ ክልል ፖሊሶች በትግራይ የጸጥታ ሃይሎች ታስረው ከቆዩ በኋላ ማክሰኞ ተፈተው ተደብድበው መባረራቸውንም ምንጮቻችን ለኢሳት አስታውቀዋል።

የባህርዳር ጊዮን ሆቴልን ሲያስተዳድር የነበረው ልጃቸው ብስራት ወልዱ በጣና ዳር የሚገኘውን በ 1999 ዓም ይህን ድርጅት በሊዝ ጨረታ ለመግዛት ሞክሮ ሳይችል በመቅረቱ ከትግራይ ጄኔራሎች ጋር በመመሳጠር በከተማው ከንቲባ ላይ ዛቻና ማስፈራራት ሲያካሄድ እንደነበር ምንጮቻችን አክለው ጠቁመዋል።

በታክስ ማጭበርበር በአማራ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚፈለጉት አቶ ወልዱ አረጋይ በአድዋ ከተማ በከፈቱት የብረታብረት ቶርኖ ቤት ከፍተው እየሰሩ ቢገኙም የትግራይ አስተዳደር ግለሰቡ የክልሌ ተወላጅ በመሆናቸው አሳልፌ አልሰጥም በማለቱ ሊሳካ አለመቻሉን የኢሳት ምንጮች አስታውቀዋል።

የትግራይ የጸጥታ ሃይሎች በተለያዩ ጊዜያት ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ ከአማራ ክልል የሚፈልጉትን ሰው እያፈኑ ሲወስዱ መቆየታቸው ይታወሳል። በቅርቡም ምንም የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሳይኖራቸው ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱን አፍነው ለመውሰድ ሲሞክሩ የጎንደር ነዋሪዎች ባደረጉት ትግል የአማራ ህዝብ ተቃውሞ ለመነሳት ምክንያት መሆኑ ይታወሳል። በአሁኑ ጊዜ ግን የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት አቶ ወልዱ ሙላት ከአድዋ በፖሊስ ተይዘው እንዲመጡ ትዕዛዝ ቢያስተላልፍም የትግራይ መንግስት የፍ/ቤቱን ውሳኔ ሳያከብር የአማራ ፖሊሶችን አስሮ ማባረሩ ብዙዎችን እያነጋገረ ነው።

ኢሳት (ህዳር 8 ፥ 2009)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.