ርዮት አረንጓዴ፣ ቢጫ ቀይ ሰንድቅ አላማ በላይዋ ላይ ለብሳ በክብር ከቃሊቲ ትወጣለች – ግርማ ካሳ

በሃይ ስኩል የእንግሊዘኛ አስተማሪ ነበረች። በሕገ መንግስቱ ላይ የተደነገገዉን መብት በመጠቀም፣ በተለያዩ አገር ውስጥ በሚታተሙ ሜዲያዎች ትጽፋለች። «እነርሱ እንዲጻፍ ከሚፈልጉት ዉጭ እንዲጻፍ የማይፈልጉ ባለስልጣናት፣ የሃሰት ክስ መሰርተዉ፣ ዳኛ ለተብዬዎች መመሪያ ሰጠዉ፣ መሰረተ ልማቶችን ለማፍረስ አሴራለች፣ ሽብርተኛ ናት» ብለዉ ፈረዱባት።

ryotይች እህት ርዮት አለሙ ትባላለች። ጡቷ አካባቢ ችግር ስላለበት ክትትል እንደሚያሰልጋት እየታወቅም ክትትል እንድታገኝ አልተደረገም። ወደ ሶስት አመት ገደማ ባላጠፋችዉ ጥፋት፣ ኢሕአዴግን ስለተቃወመች ብቻ፣ እየማቀቀች ነዉ። የርዮት ወንጀል አገሯ፣ ሕዝቧን መዉደዷ ነዉ።

ርዮት አለሙ፣ ከጋዜጣኛ ነብዩ ሃይሉ ጋር በአዲስ ፕሬስ፣ ከጋዜጣኛ ስለሺ ሃጎስ ጋር በ ቼንጅ መጽሄት ላይ ሰርታለች። ነብዩና ስለሺ፣ በአንድነት ራዲዮ አንድ ወቅት ስለርዮት አለሙ፣ ከሚያወቁት ያጋሩንን ጥቂቱን ላካፍላችሁ።

ያዉ በአገራችን ባለዉ የዘር ፖለቲካ ምክንያት «የትግራይ ልማት ማህበር»፣ «የአማራ ልማት ማህበር» የሚባሉ አሉ። እነዚህ ማህበራት በየቦታዉ ለልማት ሥራ በሚል ገንዘብ ያሰባስባሉ። የአማራዉ ልማት አማራ የሚላቸዉን ነዉ የሚያነጋግረዉ፣ የትግሬዉ ደግሞ ትግሬዎችን።

አንድ ጊዜ የትግራይ ልማት ማሕበር፣ ርዮት በምታስትምረበት ትምህርት ቤት የገንዘብ ማሰባሰቢያ ትኬቶችን ይሸጣል። አንዱ ትኬት 30 ብር ነበር። በትግራይ፣ መቀመጫ አጥተዉ በመሬት ላይ ተቀምጠዉ የሚማሩ ተማሪዎችን የሚያሳይ ቪዲዮ አሳዩ። እነርሱ ትግሬ፣ አማራ. ኦሮሞ ይላሉ። እርስዎ ግን ሁሉንም ዘር ሳትለይ “ወንድሞቼ፣ እህቶቼ” ትላቸዋለች” ። «ይሄማ መሆን የለበትም» ብላ በቪዴዎ የታዩ ተማሪዎችን ለመርዳት ወሰነች። እርሷ ብቻ 300 ብር አውጥታ አሥር ትኬቶች ገዛች። ሌሎች ጓደኞቿም እንዲገዙ ግፊት አደረገች። ምንም እንኳን ትግሬ ባትሆንም፣ የትግራይ ልማት ማህበሩ ያነጣጠረው ትግሬዎች ላይ የነበረም ቢሆን፣ እርሷ ግን ያየቸው የተማሪዎችን ዘር ሳይሆን፣ ስብእናቸዉን እና ኢትዮጵያዊነታቸውን ነበር።

ርዮትን ያሰሩ ሰዎች፣ «መሰረተ ልማትን ለማፍረስ ፣ በሰዎች ላዩ ጉዳት ለማድረግ የምትፈልግ ፣ አሸባሪ ናት» ነዉ የሚሉን። እንግዲህ በትግራይ ያሉ ተማሪዎች ይመስክሩ።

በአገራችን ትልቅ የኢኮኖሚ ችግር እንዳለ የሚታወቅ ነዉ። ጥቂቶች እላይ ሲመጠቁ፣ አብዛኛዉ ኑሮ ከብዶት፣ በቀን አንዴ እየተመገበ ነዉ የሚኖረዉ። ርዮት አስተማሪ እንደመሆኗ በተማሪዎቿ አካባቢ ያለዉን ችግር ታዉቃለች። ብዙ ጊዜ በጠኔ ሲወድቁ አይታለች። ብዙዎችም እንደ ታላቅ እህት ችግራቸውን ያጫዉቷታል። አቅሟ በፈቀደ መጠን ከማስተማር በተጨማሪ ተማሪዎቿን የምትረዳ ፣ የተከበረችና የተወደደች ምህሩ ነበረች። በጣም ችግረኛ ለሆኑ፣ አሥራ ሁለት ተማሪዎች፣ የሚለብሱት ዩኒፎርም በየአመቱ የምታሰፋ ነበረች።

ርዮትን ያሰሩ ሰዎች፣ «መሰረተ ልማትን ለማፍረስ ፣ በሰዎች ላዩ ጉዳት ለማድረግ የምትፈልግ አሸባሪ ናት » ነዉ የሚሉን። እንግዲህ በአዲስ አበባ ያሉ፣ ርዮት እንደ ታልቅ እህት የረዳቸቸዉና የደገፈቻቸው ተማሪዎች ይመስክሩ።
አንድ ጊዜ ደግሞ እንዲህ ሆነ። አንድ በጣም ጎበዝ የሆነ፣ ተማሪዎ፣ የማትሪክ ዉጤት እንደጠበቀዉ አልመጣለትም። የመንግስት ተቋማት መመደብ አልቻለም። በዚህም ምክንያት በጣም ተስፋ ቆርጦ እራሱን ወደ ማጥፋት ደረጃ ደረሰ። ይሄንን ስትሰማ ቤተሰቦቹን አነጋገረች። ያለዉን ነገር አስረዷት። በጣም ድሃዎች እንደመሆናቸው፣ ልጃቸውን የግል ትምህርት ቤት ከፍለው ሊያስተምሩት እንደማይችሉ ነገሯት። ይህን ወጣት፣ ወጭዉን በሙሉ ሸፍና፣ ዩኒቲ ኮሌጅ ገብቶ እንዲማር አደረግቸው።

እንግዲህ አስቡት ወገኖቼ፣ እንደ ርዮት አለሙ አይነት የተከበሩ፣ አገር ወዳድ፣ ለሰው የሚያዝኑ ኢትዮጵያዉያንን ነዉ ሕወሃት/ኢሕአዴግ ሽብርተኞች እያለ ወደ ቃሊቲ የሚወረወረው። ዜጎች መልካም በሰሩ፣ የአገርንና የወገንን ጥቅም ባስቀደሙ፣ ለሕዝብ ክብርና ነጻነት በቆሙ፣ ፍትህን በሰበኩ፣ የአገሪቷ ባለስልጣናት የሚሰሩትን ስህተቶችን በደሎች ባጋለጡ ለምንድን ነዉ የሚታሰሩት ? ኢትዮጵያስ እስከምቼ ለልጆቿ ሲኦል ትሆናለች ?

አንዳንድ ሰዎች በጣም ክፉ ከመሆናቸው የተነሳ ሌሎች ሲሰቃዩ የሚደስቱ አሉ። እነዚህ በዉስጣቸው ያለው የሕሊና ድምጽ የማይቃጭልባቸዉ ፣ ርህራሄና ሃዘኔታ የሚባል ነገር የሌላቸው፣ ለስብእና ክብር የማይሰጡ ናቸው። ኢሕአዴግ እየተመራ ያለ በእንደነዚህ አይነት ሰዎች ነዉ። እነዚህ ሰዎች የራሳቸዉን የጥላቻ እርካታ ለማጥገብ ሲሉ በሚሰሩት ግፍ፣ ኢሕአዴግን ወደ ገደል እየወሰዱት ነዉ።

የርዮት አለሙ መታሰር እንደ ፓርቲ ኢሕአዴግ ለሚያደርጋቸው የልማት እንቅስቃሴዎች ምንም አይጠቅምም። በፖለቲካም የበለጠ እንዲጠላ ነዉ እያደረገው ያለዉ። የኢሕአዴግ አባላትና ደጋፊዎች የሚመሯቸውን አክራሪዎች ገፍተዉ እንዲያስወጡ እመክራቸዋለሁ። በአስቸኳይ ርዮት አለሙ እንዲሁም ሌሎች የሕሊና እስረኞችን መፍታት አለባቸው። ቀናት እየጨመሩ በሄዱ ቁጥር ነገሮች እየተወሳሰቡ ነዉ የሚመጡት። ኢሕአዴግ እየመነመነ፣ እነርዮት አለሙ ደግሞ ተወዳችነታቸው እየጨመረ ነዉ የሚመጣዉ።

ርዮት አለሙ፣ አሁን ብትታሰርም፣ ሚሊዮኖች የርዮት አፍ ሆነዉ ድምጻቸዉን ያስተጋባሉ። የሚሊዮኖች የፍትህ ድምጽ የአራት ኪሎ ቤተ መንግስት ግድግዳን እያለፈ፣ ባለስልጣናቱ በተኙበት ይሰሙታል። ያለ ምንም ጥርጥር ርዮት አለሙ፣ እንደ ደራርቱ ቱሉ የኢትዮጵያን አረንጓዴ፣ ቢጫ ቀይ ሰንድቅ አላማ በላይዋ ላይ ለብሳ በክብር ከቃሊቲ ትወጣለች።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.