አሉቧልታ ይብቃ! [በላይነህ አባተ ]

በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com

gossip1ለፍትህ፣ ለሕዝባቸውና ላገራቸው ሲሉ በመቶ ሺዎች እሚቆጠሩ ዜጎች ተሰውተዋል፤ ተጠብሰዋል፤ እግር ተወርቺ ታስርዋል፤ ንብረታቸውን ተቀምተዋል፡፡ እኛ ህሊና ቢሶች ግን ጠቢባን ለበጎ ጉዳይ የፈጠሯቸውን ራዲዮ፣ ቴሌቪዥን፣ ኢንተርኔት፣ ፌስቡክን፣ ትዊተርና ሌሌችንም መገናኛዎች በውሸትና ትክክለኛ ማስረጃ በሌላቸው ጩኸቶችና ጫጫታዎች ሞልተናቸዋል፡፡ ያሳዝናል! በትክክለኛ መረጃ ሳይደገፉ ግለሰብን፣ ቡድንና ሕዝብን መቦጨቁን ቁርስ፣ ራትና ምሳ አርገነዋል፡፡ አሉቧልታ ሰፈር ለሰፈር ትዳር ሲያፈርስ፣ ጎረቢት ሲያጋጭ፣ እድር ሲበትንና እቁብ ሲንድ ኖሯል፡፡ ጎጆ ሲያፈርስ የኖረው ይህ ጥጃ አሏቧልታ ዛሬ ወይፈን ሆኖ አገር ሲያፈርስ ይውላል፡፡ አሉቧልታ ሰውን ከሰው፣ ቡድን ከቡድን፣ ሕዝብን ከሕዝብ እያጋጨ ከአንድነት ይልቅ መለያዬትን፣ ከመዋደድ ይልቅ መጣላትን ሲያዛምት ጀምበር ወጥቶ ይጠልቃል፡፡ በአሉቧልታ ስብቀት መንፈሳዊም ሆነ አካላዊ ኃይላችን እያለቀ መራመድ ስላቃተን በተለያዩ የሕብረተሰብ እድገት መስፈርቶች የአለም ጭራ ሆነናል፡፡ ዘለሰኛ የጣለን አሉቧልታ ልንነሳ አንገታችንን ስናቀና መልሶ ይረፉቀናል፡፡ ለመነሳት እውነትን መመርኮዝ ይኖርብናል፡፡

የሃይማኖት ፈላስፋዎች እውነት እግዚአብሔር ወይም የሚያምኑት አካል አለዚያም መንፈስ ብቻ እንደሆነ ያስተምራሉ፡፡ ሃይምኖት አልባ የሆኑ ፈላስፎችም በእውነት ሐያልነት ያምናሉ፤ የእውነትን መንገድ ለመከተልም እንደ ሶቅራጥስ እስከ ሞት የሚያደርስ መከራን ይቀበላሉ፡፡ እውነት በሰው አቅም ወይም በሰውኛ ስናያት ግን አይነኬ ሆና እናገኛታለን፡፡ ሰው መቶ በመቶ እውነተኛ ይሆናል የሚል እምነት የለኝም። መቶ በመቶ እውነተኛ የሆነ ሰው ካለ ከሰው ከፍ ያለ ፍጡር በመሆኑ ለማምለክ ዝግጁ ነኝ፡፡ መቶ በመቶ እውነተኛ መሆን ባይችልም ሰው ወደ እውነት ሊጠጋ ይችላል፡፡ ሰው ወደ እውነት ለመጠጋት የሚችለውም በመርጃ በተመሰረተ ግብሩ ነው፡፡ በምርምር የተመሰረተ ትክክለኛ መርጃ እውነትን እንድንመረኮዝና የሚረፉቀንን ቧልታና አሉቧልታ ፈንቅለን እንድንወጣ ይረዳናል፡፡

ለመሆኑ ቧልትና አሉቧልታና ምንድን ናቸው? ቧልትና ቧልተኛ፤ ወይንም አሉቧልታና አሉቧልተኛ የሚሉትን ቃላት ቢያንስ ባንዱ አይነት ያገራችን ቋንቋ ያልሰማ ወገን አይኖርም ብዬ አስባለሁ፡፡ ቧልት ነገርን ወይም ወሬን ከአንዱ ተቀብሎ ወደሌላው የመቀባባት ሂደት ነው፡፡ ነገርን ወይም ወሬን እንደ መሸጋገሪያ እቃ (transmission vehicle) ሆኖ የሚያመላልሰው ሰው ቧልተኛ ይባላል፡፡ አሉባልታ ደግሞ ከቧልትም የከፋ ነው፡፡ ቃሉ ከተሰራባቸው ፊደሎች መገንዘብ እንደሚቻለው አሉቧልታ ከ”አሉ”ና “ቧልት” ጥምረት የተፈጠረ ነው፡፡ እንደ ቧልት ሁሉ አሉቧልታ ከቧልተኛ የተቀበሉትን ነገር ወይም ወሬ ሥረ-መሰረቱን  ሳያረጋግጡ ወደ ሌላው የማሰራጨት ሂደት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር አሉቧልታ መሰረት የሌለው  ሁለተኛ ደረጃ ወሬ (baseless second hand information) ማናፈስ ማለት ነው፡፡ አሉቧልታን በማከናወን ስራ ላይ የተሰማራ ሰው አሉቧልተኛ ይባላል፡፡

 

መለስተኛ ሁለተኛ ደርጃ ትምህርት ቤት እያለሁ አንድ የአማርኛ መምህራችን በቡድን እየከፈሉ ድራማ እንድናዘጋጅ ያዝዙን ነበር፡፡ ባንድ ወቅት የኛ ቡድን “ዋይታና አሉቧልታ አንድን ቤት ሲፈታ” በሚል ርእስ ድራማ ማዘጋጀቱ ትዝ ይለኛል፡፡  በዚያ እድሚያችን አሉቧልታ ቤትን ሲፈታ ወይም ሲያፈርስ ይታየን ነበር፡፡ ዛሬ እሚታዬኝ ግን አሉቧልታ ከቤትም አልፎ አገርን፣ ከዚያም አልፎ ተከታታይ ትውልድን ሲፈታ ነው፡፡ አሉቧልታ አገርን መፍታት ከጀመረ ዓመታት አልፈዋል፡፡ የተለያችሁ ፍጡሮች ናችሁ በሚል አልቧልታ በሰሜን የሚገኙ ወንድምና እህቶቻችን ተለይተዉናል፡፡  በአሉቧልታ በዘርና በቋንቋ ተከፋፍለን አላስፈላጊ እንካ-ስላንቲያ ውስጥ ገብተናል፡፡ በአሉቧልታ በሚፈጥረው ጦስ ስንቱ እሚበላው አጥቷል፤ ታስሯል፤ ተገርፏል፡፡ በአሉቧልታ ስንቱ ተሰዷል፤ ህይወቱን አጥቷል፡፡ በአሉቧልታ ምክንያት አንድ መሆን አንቀጥ ሆኗል፡፡  ለዚህ ሁሉ መረጃ ማቅረብ የሚያስፈልግ አይመስለኝም፡፡ ሁላችንም በጆሮአችን እያዳመጥነው፤ ባይናችን በብረቷም እየተመለከትነው ነው፡፡ አሉቧልታ ያላደረሰብን በደል የለም፡፡  ካላወቅንበት ወደፊትም ሊያደርገን የማይችለው ነገር አይኖርም፡፡

እንደ ክህደት ሁሉ አሉቧልታም አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ምናልባት ለየት የሚል ነገር ቢኖር የከሀዲውም ሆነ የአሉቧልተኛው ቁጥር (prevalence) በከፍተኛ የስሌት ፍጥነት(Geometric progression) እያሻቀበ መሄዱ ነው፡፡ በመላው አገራችን ዉስጥ ተሰግስገው የነበሩ አገራቸውን የከዱ ወገኖቻችን በሆዳቸው ተገዝተው ጣሊያንን መንገድ እያሳዩ በአሉቧልታ አያት ቅደመ አያቶቻንን አስገድለዋል፡፡ የዛሬ አገር ከሐዲዎች ደግሞ ሌላ ሳይመጣብን አሉቧልታ እያናፈሱ እርስ በራሳችንን አናክሰውናል፡፡ የቧልት መጸሕፍትን ሞነጫጭረውና የቧልት ሐውልትን ጠርበው አሉቧልታን በማናፈስ ሕዝብን እንደ እሳትና ጪድ በማያያዝ ሸር ተጠምደዋል፡፡

ቧልትና አሉቧልታ እንዴት ይሰራጫል? ስርጭቱንስ እንዴ መግታት ይቻላል? ቧልት እንዲኖር ቢያንስ ሶስት፤ ለአሉቧልታ ህልውና ደግሞ ቢያንስ አራት ሰዎች ያስፈልጋሉ፡፡ መረጃ-፩ን ይመልከቱ፡፡

መረጃ-፩

ታሚ                 ቧልተኛ             አሉቧልተኛ            ሰሚ ….

ቧልት ወይም አሉቧልታ የሚታማ ሰው ወይም ቡድን ከሌለ ቧልት አይኖርም፡፡ በተመሳሳይ መንገድ ቧልተኛ ወይም አሉቧልተኛ ከሌለም አሉቧልታ አይኖርም፡፡ አሉቧልተኛን የሚሰማ ሰው ወይም ሕዝብ ከሌለም አሉቧልታ ቦታ አያገኝም፡፡  ስለዚህ መፍትሄው ቢቻል ሁሉም ጋ ካልተቻለም ቢያንስ አንዱ ጋ ማነጣጠር አለበት ማለት ነው፡ቧልተኛና አሉቧልተኛ ላይ ጊዜንና ኃይልን ማባከን ፈጣንና አጥጋቢ ውጤት የሚያመጣ አይመስለኝም፡፡  በቧልትና በአሉቧልታ የሚሰማሩ ሰዎች ልባዊት(ሐሳቢ) የሆነችው የአእምሯቸው ክፍል በጥቅም፣ በቅናት፣ በክፋት፣ በተንኮል፣ በሸርና በበታችነት ስሜት የታወረችባቸው ሰዎች ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ ጥቅም እንደ ህጻን በቃላት ሙከሻ ከመደለል የሳጥናኤል ፍቱን መሳሪዎች እስከሆኑት ገንዘብና ስልጣን ይደርሳል፡፡ ስለዚህ ከቧልተኛና አሉቧልተኛ ይልቅ ለጉዳዩ መስንኤ ከሆነው ታሚ ግለሰብ ወይም ቡድንና ወሬው ከአሉቧልተኛ ከሚደርሰው ሰሚ ግለሰብ ወይም ሕዝብ ላይ ማተኮር እሚሻል ይመስለኛል፡፡

ስስትና ሆድ፤ ገንዘብና ስልጣን እስካሉ ድረስ አሉቧልታ ሙሉ በሙሉ ይጠፋል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ነገር ግን ካወቅንበትና በቁርጠኝነት ተነስተን ከዘመትንበት እንደመሶሎኒ ሰራዊት መቀመጫ በማሳጣት የቧልተኛንና አሉቧልተኛን ቁጥር መቀነስ እንደዚሁም የቧልትና አሉቧልታን ስርጭት መቆጣጠር ይቻላል፡፡ ትኩረታችን ከቧልተኛና ከአሉቧልተኛ ሳይሆን ከታሚና ከሰሚ ላይ ቢሆን መልካም ነው፡፡ ወላጆቻችን ያሳድጉን ካልሆነ ሰው ጋር እንዳንዉል እያስጠነቀቁ ነው፡፡ “የገሌ ልጅ ወስላታ ስለሆነ ከርሱ ጋር እንዳትዉል!” ይላሉ፡፡ ውለው ከተገኙም ከተግሳፅ አልፈው ለኩርኩም፣ ለመነኩሴ ቁንጥጫ ወይም ለአለንጋ ሊዳረጉ ይችላሉ፡፡ የወስላታ አይነቱ ብዙ ነው፡፡ ሌባ፤ ቀጣፊ፤ ከሃዲ፣ አጭበርባሪ፣ ዘራፊ  ወዘተ ሁሉ ከወስላታ የሚመደብ ነው፡፡ በእኔ እምነት ቧልተኛና አሉቧልተኛ የወሰላታው ሁሉ ቁንጮዎች ናቸው፡፡ ምክንያቱም ቧልተኛና አሉቧልተኛ በተለይ በዚህ ዕደ-ጥበብ ባደገበት ዘመን ሊበክሉት እሚችሉት ሕዝብ ቁጥር ስፍር የለውም፡፡ ስለዚህ አንደኛው የቧልት ወይም አሉቧልታ መከላከያ አለዚያም መዳኛ መንገድ ታሚ ከቧልተኛ፤ ሰሚም ከአሉቧልተኛ ጋር አለማዋል፤ አለመነካካትና ምስጢርንም አለማሳወቅ ነው፡፡ ለምሳሌ ታሚና ሰሚ ከኢንተርኔት ቧልተኞችና አሉቧልተኞች ራሳቸውን ማግለል አለባቸው ማለት ነው፡፡

ሁለተኛውና ዋናው የቧልትና የአሉቧልታ መከላከያ መንገድ መመራመርን፣መፈተሽን ወይም ደግሞ በቂ መረጃ መጠየቅን ባህላችን ማድረግ ነው፡፡ በተፈጥሮ አምስት ህዋሳትና አንጎል ቢኖሩንም ጆሯችንን በመጠቅም ብቻ ባግበሰበስንው ትርኪ ምሪኪ ለአሁኑ ትውልድ ብቻ ሳይሆን ለሚመጣውም እልቂት እያዘጋጀን ያለን ጉዶች ቁጥር  ብዙ ነው፡፡ እገሌ ወሸላ ቆረጠ፣ እንተና ጡት ቦጨቀ፣ እገሌ መስጊድን ዘጋ፣ እንተና ቤተከስቲያን አቃጠለ እያልን እንንጫጫለን፡፡ ከዚያም አልፈን አንድ ወይም ጥቂቶች ሰሩት የምንለውን በደል ሰፋ ባለ ሕዝብ ላይ እናላክከዋለን፡፡ በቂ እውነተኛ መራጃ ግን በእጃችን የለም፡፡ አለን የምንለው መረጃም ከአፈ-ታሪክ፣ ከአረመኔ ገዥዎች ላንቃ ተላቆ ከማያውቀው አዲስ ዘመን ወይም የአገሪቱን ባህልም ሆነ ታሪክ ከማያውቀው የፈረንጅ መተተኛ ጠልሰም አይዘልም፡፡ ፕሮፌሰር፣ ዶክተር፣ አቶ፣ አባ፣ አቡነ፣ ሼህ፣ ቄስ፣ ፓስተር ወዘተርፈ እየተባልን ቧልትና አሉቧልታ ስናናፍስ የህሊና ልጓማችን አይዘንም፡፡

 

ከቧልታና አሉቧልታ የጠዳው እውነተኛው መርጃ ያለው እዚህቹ ከአለም በፊት ተፈጥራ ነገር ግን እጅና እግሯን በእርጉሞች ታስራ ወደኋላ በመዳህ ላይ ካለችው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡ ከሶስት ሺህ ወይም ከመቶ አመት በፊት እደ-ጥበብ ስላልነበረ በቂ መረጃ ማግኘት አይቻልም የሚለው ተረት ተረት አይሰራም፡፡ ከሶስት ሚሊዮን አመታት በፊት ድንቅነሽ በኖረችበት ዘመን ምንም መረጃ መዘገቢያ መንገድ የነበረ አይመስለኝም፡፡ ነገር ግን ድንቅነሽ ተመርምራ ወጥታለች፤ እድሜዋም ተቆጥሯል፡፡ የድንቅነሽን እድሜ የቆጠረ ጥበብ በሶስት ሺ ዘመናት የነበረውን የኢትዮጵያ ታሪክ እውነታ እንዴት ማወቅ ይሳነዋል? ጠቢብ ነኝ ባዩ ዶክተርና ፖሮፌሰርስ እውነትን ለመቆፈር ከመሻት ይልቅ ለምን ያሉቧልታ ግርሻ ሲያስታውክ ይውላል?

 

አሉቧልተኛ ምሁራን ሆይ! የክፉም የደጉም ታሪካችን መረጃ ተቀብሮ እሚገኘው አገሪቱ ውስጥ ነው፡፡ ችግራችን አእምሮቻንና ህዋሳታችን ከፍርሃት፣ ከጥቅም፣ ከስግብግብነት፡ ከጎጠኝነትና ሌሎችም ሰይጣናዊ ባህሪዎች አለማላቀቃችን ነው፡፡ ችግራችን መዘዘኛው ፈረንጅ ለራሱ እንዲያመች የጠለሰመውን ጠልሰም እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ወይም ቁርአን ማነብነባችን ነው፡፡ በፈረንጅ የመዘዘኛ ክታብ፣ በአፈ ታሪክ መረጃ፣ በጥቅምና በጎጠኝነት ከንቱ መንፈስ እንደ ፊኛ ተወጥረን ሕዝብ የሚያጨራርስ ጫጫታ ከማሰማት ይልቅ አእምሯችንንና ህዋሳታችንን ነፃ እናውጣ፡፡ ከዚያም በእውነተኛ ምሁር ወግ፣ በንጹህ ልቡናና መንፈስ መሬቱን ቆፍረን፣ ውሃውን ቀዝፈን፣ አዬሩን አሽትተን እውነተኛ መረጃ እንሰብስብ፡፡ ይህንን እውነተኛ መረጃ ይዘንም የምንወቅሰውን እንውቀስ፣ የምናመሰግነውንም እናመስግን፡፡ አለበለልዚያ በባእድ የተከተበን ክታብ አንጠልጥሎ ወይም አፈ ታሪክን እያነበነቡ በምድርም ሆነ በኢንተርኔት እየተሰበሰቡ መጨቃጨቅ እልቂት እንጅ መፍትሔ አያመጣም፡፡

 

የመረጃን አስፈላጊነአት ትምህርት ቤት ለመሄድ ያልታደሉት ወላጆቻችን እንኳን ጠንቅቀው ያውቁ ነበር፡፡ ለምንነግራቸው  መርጃ እንድናቀርብ አጥብቀው ይይዙን ነበር፤ ወሬ ስናቀርብ ከየት እንዳገኘነው ለማወቅ ወጥረው ይይዙን ነበር፡፡ “አይተሃል? ያላየኸውን አታውራ!” እያሉ ይገስፁን ነበር፡፡ በዚህ መልክ አባቶቻችን ይጠይቁት የነበረው መረጃ በምርምራዊ ሥነ-ጽሑፍ (scientific literature)  ማስረጃ ወይም ዋቢ (reference) ከሚባለው ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ እኛን በተለይም ፒ ኤች ዲ፣ ዶክተር፣ ማስተርስ፣ ወዘተ የሚባሉ ዲግሪዎች እንደ ታርጋ የምንለጥፍ ፊደል ቆጣሪዎች ለመመረቂያ ወረቀታችን ዋቢ ጠቅሰናል፡፡ ወደ አገራችንና ወደ ሕዝባችን ስንዞር ግን ዋቢና ማስረጃን ለሽንት ቤት ተጠቅመን ቧልትና አሉቧልታን ማነብነብ ይቀናናል፡፡

 

አሉቧልታን እያነበነብን ሰውን ከሰው፤ ቡድንን ከቡድን፣ ሕዝብን ከሕዝብ ስናናክስ ህሊናችንን አይኮረኩረንም፤ ሐፍረት አይሰማንም፡፡  የታወቀ (common knowledge) ወይም የግል አስተያዬት መሆኑን እስካላሳወቀ ድረስ ተናጋሪ ወይም ጸሐፊ በተለይ ሌሎችን ሲከስ መረጃ ማቅረብ ይጠበቅበታል፡፡ አለበለዚያ በሐሜተኛነት፣ በቧልተኛነት ወይም በአሉቧልተኛነት መፈረጅ ይኖርበታል፡፡ ተናጋሪ ወይም የጸሐፊ ስልጣኑ፤ ሐብቱ፣ ለሆዱ ሲል የተቀበለው ዲግሪው፣ እድሜው፣ ጢሙ፣ ወይም ለእንጀራ መበያ የጠመጠመው ጥምጣሙ ወይም ቆቡ እየታዬ ብቻ መደመጥ የለበትም፡፡ ለሚናገረው ዋቢ ሳይጠቅስ ወይም  ትክክለኛ መረጃ ሳያቅርብ አለዚያም የራሱን ፍላጎትና ምኞት ሕዝብ እንዲቀበለው “ዋቢ” ከጓዳው እየፈጠረ  ወይም ሥዕል እያቀነባበረ የሚያምታታን ወስላታ አድማጭ ወይም አንባቢ እንደ ቡግንጅ ወጥሮ መያዝ ይጠበቅበታል፡፡

 

አድማጭ ወይም አንባቢ ተናጋሪን ወይም ጸሐፊን “ከየት አምጥተህ ታወራልህ፤ ማረጋገጫህ ወይም ዋቢህ የት ነው?” እያለ ቧልተኛን ወይም አሉቧልተኛን እንደ ንጋት የሽንት ፊኛ ቢወጥር ቧልተኛና አሉቧልተኛ ከገባበት ማጥ ዉስጥ መዉጫ አያገኝም፡፡ አድማጭ ቤተሰቡን፣ ጓደኛውን፣ ዘመዱን፣ ወዘተርፈ ሳይቀር ለዚህ ወሬ መረጃው የታለ ብሎ እየጠየቀ የመርጃ ባህል ካልዳበረ ቁልቁል ከመንጎድ አንመለስም፡፡ ቧልተኛ ያለቧልት፤ አሉቧልተኛም ያለአሉቧልታ መኖር ስለማይችሉ የቧልትና የአሉቧልታ ሰንሰለት ሲበጠስ ሁለቱም ወደ መቃብር ይሄዳሉ፡፡ መረጃ-፪ን ይመልከቱ፡፡  ሁለቱ ከሰንሰለቱ ሲጠፉ፤ ታሚ በመርጃ የተደገፈችዋን እዉነት ይዞ ሲቀርብ፤ ሰሚም በመረጃ የተደገፈችዋን እውነት አሜን ብሎ ሲቀበል መተማመን ይጠነክራል፤ አንድነት ይፈጠራል፡፡ አንድ ከሆኑ እንኳን ከድቡሽት የተዋቀረን ዛኒጋባ ተራራንም መናድ ይቻላል፡፡

 

መረጃ-፪

ዛሬ በቴሌቪዝን፤ በራዲዮ፣ በፌስቡክ፤ በትዊተርና በኢሜል የምንጫጫውና የምንጨቃጨቀው በቂ መረጃ ሳንይዝ በቧልትና በአሉቧልታ እንደ ፊኛ ተነፍተን ነው፡፡ “ለሁሉም ጊዜ አለው” ብሏል “ጥበበኛው” ሰለሞን፡፡ ጭቅጭቁንም ሆነ ጩኸቱን ከፍለግነው ጊዜ እንስጠው፡፡ መጀመሪያ አእምሯችንና ህዋሳታችን ከማንኛውም ጉድፍ ነጻ እናድርጋቸው፡፡ መልካም አስተዳደራዊ ግንኙነት እንፍጠር፡፡ በንጹሕ ልቡና ታሪካችንንም ሆነ ሌላውን ቁሳዊምና መንፈሳዊ ሐብታችንን እንመርምር፤ እንፈትሽ፡፡ ከጥቅም፣ ከስግብግብነት፣ ከጎሰኝነትና፣ ሌሎችም ከንቱ ባህሪዎች ተላቀን እውነተኛ መረጃ እንሰብስብ፡፡ በእንደዚህ አይነቱ ምርምርና እውነተኛ መረጃ ተመርኩዘን የሚመሰገንውን እናመስግን፣ የሚወቀሰውንም እንዉቀስ፡፡ ለእውነት፣ ለሰብአዊነት፣ ለዛሬውም ሆነ ለመጪው ትውልድ ስንል ቧልትን፣ አሉቧልታንና በእነዚህ ከንቱ መንፈሶች የተመሰረትን ጫጫታ፣ ሐሜት፣ ሥም ማጥፋት፣ ጭቅጪቅና ጠብ እናስወግድ፡፡ ሰሚ ሆይ ራስህን ከቧልተኞችና ከአሉቧልተኞች ጠብቅ! አሉቧልታ ይብቃ! አመሰግናለሁ፡፡

ህዳር ሁለት ሺ ዘጠኝ ዓ.ም.

የዚህ ጽሑፍ አብዛኛው  ክፍል “ግራዋ ለአሉቧልታ” በሚል ርእስ  ከዚህ በፊት ቀርቦ ነበር፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.