ፕሮ. መስፍንና ክሽፈታቸው! [ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው]

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

ሰውየው ሳይጃጁ የቀሩ አልመሰለኝም፡፡ ለነገሩ እኔ ፕሮፌሰር (ሊቀ ማእምራን) መስፍን እንኳን አሁንና እንዲህ እየዘባረቁ ድሮም ቢሆን ለአንድም ቀን ቢሆን ተመችተውኝ አያውቁም፡፡ ለምን እንደሆነ አላውቅም ብስልን ከጥሬ ቀላቅሎ መናገር ወይም መጻፍ ይወዳሉ፡፡

አንዳንዴ ሆን ብለው ነው እንዲህ የሚያደርጉት፡፡ በቀረው ጊዜ ግን የሚሉት ነገር ትክክል ስለሚመስላቸው ነው፡፡

እንዲህም ሆኖ እኔ ለወትሮው ሰው እሳቸውን በአደባባይ ሲያጥላላ ሲነቅፍ ደስ አይለኝም ነበረ፡፡ ምክንያቱም እሳቸውን የሚያጥላሉ ሰዎች እሳቸውን የሚያጥላሉበት ምክንያትና ዓላማ ወያኔን ለማስደሰት ሆኖ ስለማገኘው እሳቸውን የሚያጥላሉትን ሰዎች እገስጽና እዘልፍም ነበረ፡፡ አሁን ግን ሰውየው የወያኔ ጀምበር እንደጠለቀች ገባቸው መሰለኝ “ወያኔ ሲሔድ ገሎኝ ይሔዳል!” ብለው ፈሩ መሰለኝ ወያኔን ለመደለል የሚወሸክቱት ነገር እጅግ ለከት እያጣ ስለመጣ ብእሬን አነሣባቸው ዘንድ ግድ አለኝ፡፡

ይሄንን ለማለት ያስገደደኝ ምንድን ነው መሰላቹህ ሰውየው ሰሞኑን “ጎሰኝነት በባዶ ሜዳ!” የሚል ርእስ ባለው ጽሑፋቸው ላይ ጭምልቅልቅ ብለው ስላገኘኋቸው ነው፡፡

ሰውየው በዚህ ጽሑፋቸው አራት የተለያዩ አካላትን አውግዘውበታል፡፡ ጎሰኞችን፣ ተገንጣዮችን፣ የባዕዳን ባሕልና ማንነት ምርኮኞችንና ስደተኛን ዘልፈዋል ኮንነዋል አበሻቅጠዋል፡፡ የመጀመሪያዎቹ ሦስቱን የኪሳራ አስተሳሰብ ተቀባዮችንና አቀንቃኞችን መኮነናቸው አይደለም የጽሑፉ ችግር፤ ይሄንን ማድረግ እንደሳቸው ካለ የሀገር ሽማግሌ የሚጠበቅና ተገቢም ነውና፤ ሰውየው ግን ምክንያቱን ባልገለጹበት ሁኔታ ውግዘቱ በፍጹም በማይገባቸው ሰዎች ላይ ማለትም ከወያኔ የእርግማን አፍ በማይነጠሉት ከሀገር ተሰደው በሚኖሩ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን ላይ በጅምላ እንዲህ በማለት ወረዱባቸው “…ሀገር ቤት ያለነውን አላዋቂ ሞኞች ለማሳመን ስደተኞች በየቀኑ አዳዲስ ነገሮችን እያለሙ ያድራሉ፡፡ እኛ የምንኖረውን እንንገራቹህ ይሉናል፤ እኛ የምናስበውን እንምራቹህ ይሉናል፤ እኛ የሚሰማንን እንግለጽላቹህ ይሉናል፤ በአጭሩ እኛን የእነሱ አሻንጉሊቶች አድርገውናል፡፡ የእኛን መታፈን ከእነሱ ስድነት ጋር እያወዳደሩ፣ የእኛን ድህነት ከእነሱ ምቾት ጋር እያስተያዩ፣ የእነሱን ቀረርቶ ከእኛ ዋይታ ጋር እያመዛዘኑ ያላግጡብናል ይመጻደቁብናል…..በስደት የገባበትን ማኅበረሰብ ያሰለቸ!” በማለት ወያኔ እንኳን የዚህን ያህል ጥላቻ ይኖረዋል ተብሎ የማይገመተውን ያህል ሰውየው ተገደውም ወደውም ከሀገር በተሰደዱ ወገኖቻችን ላይ ከባድ በፍጹም አግባብ ያልሆነ ጥላቻ አንጸባረቁ አሳዩ፡፡ አሁን ይሄን ምን ትሉታላቹህ? ሰውየውስ እንዴት? ከምን ተነሥተው? ማን ገፋፍቷቸው? ማንን ለማስደሰት? እንዲህ ሊሉ ቻሉ?

እኒህ ሰው እውን በባዕዳን ሀገሮች ያሉ ኢትዮጵያውያን በሀገራችን ፖለቲካ (እምነተ አሥተዳደር) እየተጫወቱት ያለው እጅግ ጠቃሚና የማይተካ ሚና በጣም አስፈለጊ መሆኑን መረዳት መገንዘብ የተሳናቸው  ሆነው ነው? ወይስ “ከሀገር ውጪ በሚደረጉ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎችና ምሥረታዎች እኔ በክብር ተጋብዠና ተሹሜ ሳልካተት ቀረሁ!” ከሚል ራስ ወዳድነት እጅጉን ከተጣባው ደካማ አስተሳሰብ የተነሣ ቅሬታ ስላደረባቸው ነው? ወይስ ለወያኔ ቅጥረኛ ሆነው ኅሊናቸውን ስለሸጡ ነው? ወይስ ከላይ እንዳልኩት በዚህ አባባላቸው ወያኔን በማስደሰት “ሊደርስብኝ ይችላል!” ብለው ከሚፈሩት ችግር ለማምለጥ?

ምክንያቱም አባባላቸው እንደምታዩት ሁሉንም በአንድ ላይ “ስደተኛ” ብሎ ጀምሎ በመፈረጅ የተሰነዘረ ውግዘትና ማበሻቀጥ ከመሆኑም በላይ ምክንያታዊነትን፣ ትክክለኝነትን ሊያሳይ ሊያመለክት የሚችል አንዳችም ፍሬ ነገር የሌለው ከመሆኑ የተነሣ ከዚህ በጅምላ አጠቃሎ ከተሰነዘረ ውግዘትና ዘለፋ ጀርባ አንዳች ነገር እንዳለ በግልጽ ለመረዳት የሚገድ አይመስለኝም፡፡

ሰውየው እነከሌ እነከሌ ይሄ ይሄ ተግባራቹህ በዚህ በዚህ ምክንያት የተሳሳተ ነውና መስተካከል አለበት!” ቢሉ አንድ ነገር ነው፤ ሰውየው ግን ያደረጉት “ስደተኞች” ብለው ጠቅልለው ጀመሉና ምክንያታዊነትና ትክክለኝነት በሌለው ትችት ዘለፉ አበሻቀጡ፡፡ ይሄ ተግባር እንደሳቸው ካለ ፊደል ከቆጠረና “ለሀገሬ ለሕዝቤ መልካም ነገር እመኛለሁ!” ከሚል ሰው የሚጠበቅ ነው ወይ? በፍጹም!

ሰውየው በዚህ አባባላቸው ልጆቹ ወገኖቹ የተወገዙበት የኢትዮጵያ ሕዝብ ይደሰታል ብለው ያስባሉ? “ስደተኛ” ያሏቸው ወገኖቻችንስ እንዴት ሆኖ በምንስ ተአምር ነው የገዛ ሕዝቡ፣ የወገኑና የሀገሩ ጉዳይ የማያሳስበው የማያስጨንቀው የማይገደው ሆኖ “ፕሮፌሰሩ እንዳሉኝ ሀገር ቤት ካለው ሕዝብ በልጨ ስለ ኢትዮጵያ ሕዝብ መከራና ስቃይ ሊሰማኝ፣ ሊያንገበግበኝ፣ ሊያስጮኸኝ፣ ሊያስፎክረኝ፣ ሊያቅራራኝ፣ ሊያማርረኝ፣ ሊያሳስበኝ አይገባኝምና አርፌ ልቀመጥ!” ሊል የሚገባው??? ለምን? ማንንስ ተጠቃሚ ለማድረግ? ለመሆኑ እኝህ ሰው እዚህ ሀገር ቤት ሆነው ምን የፈየዱት ምን የተከሩት ምን ፈቀቅ ያደረጉት ነገር ኖሮ ነው ከሀገር ውጪ ያለውን ስንት እመርታ እያስመዘገበ ያለውን የተጋጋለ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ለማንኳሰስ የደፈሩት?

በዚህ አጋጣሚ እኒሁ ሰውየ መስከረም 2009ዓ.ም. ላይ አብርሃ ደስታ ስለተባለ አክቲቪስት (ስሉጥ) የጻፉትን ጽሑፍ ላንሣ፡፡ አብርሃ ደስታ የተባለው የአረና ትግራይ ፓርቲ (ቡድን) መሥራችና ኃላፊነትም ያለው ሰው ቅሊንጦ ታስሬ በነበርኩበት ወቅት እዚያው ታስረው ካገኘኋቸው ስሉጣን አንዱ ነበር፡፡ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይም ተወያይተናል ተከራክረንማል፡፡ አንድ ቀን ይህ ሰው በወልቃይት መሬትና ሕዝብ ጉዳይ ላይ ያለውን አመለካከት ማወቅ ፈለኩና አነሣሁበት፡፡ ከፊቱ  እንዳነበብኩት በዚህ ጉዳይ ላይ መወያየታችንን አልፈለገም ነበር፡፡ ይሁንና ተወያየን ብቻ ሳይሆን በጣም ተከራከርን፡፡ እሱ ይል የነበረው “ጉዳዩ በሕዝበ ውሳኔ እልባት እንዲያገኝ መደረግ ይኖርበታል!” ነው፡፡ የእኔ ደግሞ  “”ወያኔ በረሀ ከነበረበት ዘመን ጀምሮ የአማራን ዘር ባሕል ማንነት ከአካባቢው በማጥፋት በማፈናቀልና በማሳደድ፣ ሥልጣን ከያዘ በኋላም የትግሬ ተወላጆችን በማስፈር የአካባቢውን ዲሞግራፊ (ነባራዊ ምኅዳር) ሙሉ ለሙሉ ሊባል በሚያስችል ደረጃ የቀየረው ስለሆነ ከቤት ንብረታቸው በግፍ የተፈናቀሉ የተሰደዱና እንዲጠፉ የተደረጉ ወገኖች በግፍ ያጡትንና ለሰፋሪ ተላልፎ የተሰጠባቸውን ቤት ንብረትና መሬት መልሰው እንዲያገኙ ሳይደረግ ይህ ግፍ እንደተፈጸመ ባለበት ሁኔታ “ይህ ጉዳይ በሕዝበ ውሳኔ እልባት ያግኝ!” ብሎ ማለት እጅግ ኢፍትሐዊ ግፈኛና ሸፍጠኛ ብያኔ ነው፡፡ ወይም ደግሞ ሕዝበ ውሳኔው ሰፋሪዎችን የማያካትት፣ ነባር ተወላጆቹ ሀገሬው ብቻ ድምፅ የሚሰጥበት መሆን አለበት፡፡ ይህ ባልሆነበት ሁኔታ መቸም ቢሆን የዜጎችን የፍትሕ ጥያቄ መልሰናል ማለት ፈጽሞ አይቻልም!”” የሚል ነው፡፡ በክርክራችን መጨረሻም ትክክል እንደሆንኩ አምኖ ነበር፡፡ እኔም ታች አምና ከእስር እንደወጣሁ ቅሊንጦ ከተለያዩ ስሉጣን ጋር የነበረኝን ውይይትና ክርክር ጽፌ በማኅበራዊ  የብዙኃን መገናኛዎች ለቅቄው ነበር፡፡

አብርሃ ደስታ ያኔ ለካ ትክክል መሆኔን የተናገረው ከልቡ አልነበረም ኖሯል ወይም ደግሞ ወገኖቹ ጫና አብዝተውበት አቋሙን እንዲቀይር አድርገውት፤ ከወራት በፊት ከእስር ከወጣ በኋላ ጭራሽ እንዲያውም ሕዝበ ውሳኔ የሚለውን ሐሳብ ትቶ “የወልቃይት ችግር የአስተዳደራዊ በደል ጉዳይ እንጅ የማንነት ጉዳይ አይደለም!” በማለት ወልቃይት የትግሬ መሆኗን በጽኑ የሚያምን መሆኑን አረጋገጠ፡፡ ከዚያ በኋላ ይህ ሰው የነበረውን ተወዳጅነት አጥቶ በብዙዎች ይብጠለጠል ጀመር፡፡ እሱም የሰብአዊነትን፣ ፍትሐዊነትን፣ የተጠያቂነትን፣ የእውነታን፣ የሞራልን (የቅስምን) ጥያቄዎች ወደጎን ትቶ ይህ አቋሙ ኢፍትሐዊና አድሏዊ እንደሆነ ልቡ እያወቀ “ለወገኔ ላድላ!” በሚል ወያኔ በቀማኛነትና በውንብድና የወሰደውን መሬት “የኛ ነው!” በሚለው አቋሙ ጸንቶ ቀጠለ፡፡ እስከአሁንም ከየቦታው የተቃውሞ ምላሽ እየተሰጠው ይገኛል፡፡

ታዲያ እላቹህ እኚሁ ነፈዝ ሰውየ (ፕሮ. መስፍን) በዚህ ሁሉ የተቃውሞ ምላሽ እየተቀጠቀጠ ላለው አብርሃ ደስታ ስለእርሱ በጻፉት በዚያ ጽሑፋቸው “…ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አብርሃ ደስታ በሚጽፈው ማናቸውም ርእስ ላይ ቢሆን የሚሰጠው መልስ ስለ አብርሃ ደስታ ሳይወድ በግድ ምርጫ ሳይኖረው በአጋጣሚ ስለተወለደበት መንደር እንጅ አብርሃ ደስታ በምርጫውና በአእምሮው ነጻነት ስለጻፈው ጉዳይ አይደለም መልስ የሚሰጡት፡፡ ሰዎቹ ወይ አልገባቸውም ወይ ሊገባቸው አይችልም ከአቅማቸው በላይ ነው ወይ ከአብርሃ ጋር ችግር አለባቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች መጻፍ ቢቀርባቸውና ለማንበብ ለመረዳት ቢጥሩ ይበልጥ ይጠቅማቸው ነበር” በማለት የአብርሃ ደጋፊና አድናቂ መሆናቸውን በመግለጽ እንደሳቸው ያልተቄለውንና የአብርሃን የተሳሳተ አቋም የሚተቸውን ሁሉ ለመዝለፍ ሞከሩ፡፡

አሁን እኚህ ሰውየ ምናቸው ነው የሰብአዊ መብት ተሟጋችነታቸው? ምናቸው ነው ለሀገር ለወገን አሳሳቢ ተቆርቋሪነታቸው? ምናቸው ነው አማራነታቸው? (ለነገሩ ለእሳቸው አማራ የሚባል ብሔረሰብ የለም!) ምናቸው ነው ምሁር?

ስለ ምሁርነት ሳነሣ የሰውየውን አለመብሰል የሚያሳይ አንድ ንግግራቸው ታወሰኝ፤ እሱን ላንሣና ልጨርስ፡፡

ከሦስት አራት ዓመታት በፊት አሜሪካ ሔደው በነበሩበት ወቅት የአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ (ነጋሪተ ወግ) የአማርኛው አገልግሎት ክፍል በሀገራችን ያለውን የተቃውሞ ፖለቲካ (እምነተ አሥተዳደር) እንቅስቃሴ ጉዳይ ላይ ቃለመጠይቅ ባደረገላቸው ጊዜ ምን አሉ “የተቃዋሚ ፖለቲከኞች ከመተግበር ይልቅ በየምክንያቱ መለያየት የሚቀናቸው ናቸው፤ የትጥቅ ትግል እያደረኩ ነው የሚለውም ገባሁ! መጣሁ! እያለ ከማውራት የዘለለ ነገር ሲያደርግ ያየነው ነገር የለም!” ብለው ሲተቹ የሰማኋቸው ዕለት ነበር ሰውየው የፖለቲከኛነት ብቃት ብስለትና ሰብእና እንደሌላቸው የተረዳሁት፡፡ ያን ሰሞን ደግሞ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ዋሽንግተን ዲሲ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ሰብስቦ “ግንቦት 7 በቂ ኃይል አደራጅቷል በአጭር ጊዜ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ወያኔን አስወግዶ ሥልጣንን ለሕዝብ ያስረክባል!” በማለት የተናገሩበት ወቅት ነበርና ፕሮ. መስፍን አቶ አንዳርጋቸው ፖለቲካ ለመሥራት ማለትም ያው መቸም እኛ ሰዎች ስንባል ከሞቀው መዝፈንን እንጅ አሙቀን መዝፈንን አብዛኞቻችን አንወድምና ደጋፊና ታጋይን በሚፈለገው ደረጃ ለመጥራት ለመሰብሰብ የግንቦት 7 እንቅስቃሴ በተገለጸው ደረጃ ጠንካራና የተደራጀ አስመስሎ ማቅረቡ የግድ አስፈላጊ ስለነበር አቶ አንዳርጋቸው እንዲያ ብለው የተናገሩትን እኒህ ፖለቲካ ያልገባቸው ሰውየ የምር አድርገው ወስደውት ከዛሬ ነገ “ግንቦት 7 በዚህ ቦታ እከሌ የተባለውን የወያኔ ክፍለ ጦር ደመሰሰ!” የሚል ዜና ለመስማት ጆሮአቸውን አቁመው ሲጠባበቁ የውኃ ሽታ ሆነው ሲቀሩባቸው ጊዜ “…የትጥቅ ትግል እያደረኩ ነው የሚለውም ገባሁ! መጣሁ! እያለ ከማውራት የዘለለ ነገር ሲያደርግ ያየነው ነገር የለም!” ብለው አረፉት፡፡

ቆይ እንጅ ፕሮ. መስፍን ግንቦት 7 የሰማይ መላእክትን አሰልፎ የሚመጣ ይመስልዎት ነበር ወይስ ታጋይ ማምረቻ ማሽን (ማሳልጥ) ያለው ነበር የሚመስልዎት? እንዴት አቶ አንዳርጋቸው ለፖለቲካ የተናገሩት ነገር እውነት ሊመስልዎ ቻለ? በወቅቱ እኮ ግንቦት ሰባት የነበሩት ታጋዮች በመቶዎች እንኳን የሚቆጠሩ አልነበሩም፡፡ ያ ቃል የተነገረበት ምክንያት በሕዝብ ላይ መነቃቃትንና መተማመንን ፈጥሮ ወደ ትግሉ ለመጥራት ለመጋበዝ ነበር፡፡ እሱም ተሳክቶ ዛሬ አርበኞች ግንቦት ሰባት በርከት ያለ አብዛኛው የሠራዊቱ አባል ከአማራ የሆነ ሠራዊት ለመገንባት ችሏል፡፡ ይሁንና ይህ ድርጅት ጉልበቱ አማራ የመሆኑን ያህል ግን እንዴት ማሰብና መሥራት እንዳለበት ጠንቅቆ የሚያውቅ አይመስለኝም፡፡ ድርጅቱ ፈጥኖ ላሉ ችግሮችና ለተነሡ ጥያቄዎች መፍትሔና ተገቢውን ምላሽ መስጠት ካልቻለ ምንም ነገር ሳይከውን ሊፈርስ ሁሉ ይችላል፡፡ እርስዎ ግን ፖለቲካ አያውቁምና ብስለትም የለዎትምና የዚያን የአቶ አንዳርጋቸውን ቃል ዓላማ መረዳት ሳይችሉ ቀሩ፡፡ አሁን ታዲያ እርስዎ ነዎት ሰውን ለማሽሟጠጥ ለማንቋሸሽና ለመተቸት የሚበቁት? ልብ ይስጥዎት አሟሟትዎን ያሳምርልዎታ ሌላ ምን እላለሁ!

እኒህ ሰውና መሰሎቻቸው “ሐበሻ እንዲህ እንዲህ ነው!” እያሉ በሕዝባችን ማንነት ላይ ለሚያንጸባርቁት ስም ማጥፋትና ማጠልሸት “የምሁራን ልኂቃን (Intellectual Elite) እስከ ዛሬ በሐበሻ ላይ የሚሰነዝሯቸው ነውረኛና መሠረተቢስ ዘለፋዎቻቸውና አጥጋቢ መልሶቻቸው!” በሚለው ረዘም ያለ ጽሑፌ በሚገባ በጥልቀት መልስ ሰጥቸበታለሁና ስለተቀረው የኒህ ሰውየ የአመለካከት ችግራቸው እዚህ ላይ ምንም ማለት አይጠበቅብኝም፡፡

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

amsalugkidan@gmail.com

 

 

 

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.