አሸዋ የጫነ ሲኖ ትራክ መኪና ቤት ውስጥ ጥሶ በመግባት የሁለት ሰዎችን ህይወት አጥፍቷል ተባለ

c95fዛሬ ማለዳ ላይ ልዩ ስሙ ሸጐሌ አንበሣ ጋራዥ በተባለው አካባቢ የሰሌዳ ቁጥሩ 51516 የሆነ አሸዋ የጫነ ሲኖ ትራክ መኪና ቤት ውስጥ ጥሶ በመግባት የሁለት ሰዎችን ህይወት አጥፍቷል ተባለ…
ይህንን ያለው የአዲስ አበባ እሣትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለሥልጣን ነው፡፡
የባለሥልጣኑ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ የሆኑት አቶ ንጋቱ ማሞ እንደነገሩን ከሆነ ህይወታቸውን ያጡት በ30 እና በ32 የእድሜ ክልል ላይ ያሉ በወተት ንግድ የሚተዳደሩ ሴቶች ናቸው፡፡
ለአንድ ሰዓት ሃያ ጉዳይ ሲል አደጋው እንደደረሰ የተናገሩት ባለሙያው ባለሥልጣኑ ጥሶ የገባውን መኪና በክሬን በማውጣት ተጨማሪ የሰው ጉዳት አለማድረሱን አረጋግጠናል ብለዋል፡፡
አሸዋ የጫነው ሲኖ ትራክ መኪና አደጋውን ያደረሰው ወደ ኋላ በመሽከርከር ላይ እያለ መሆኑን ባለሥልጣኑ ተናግሯል፡፡
በተያያዘም ትላንት ምሽት ላይ ቦሌ ወረዳ 11 ጐሮ መስጊድ በሚባል አካባቢ በአንድ የንግድ ቤት ቃጠሎ ደርሶ 240 ሺ ብር የሚገመት ንብረት መውደሙን ከአቶ ንጋቱ ማሞ ሰምተናል፡፡
የአደጋውን መንስኤ ለማወቅ ገና ማጣራት እየተደረገ እንዳለ የነገሩን አቶ ንጋቱ አደጋውን ለመቆጣጠር ሁለት የእሣት አደጋ መቆጣጠሪያ ተሽከርካሪዎች፣ አሥራ አምስት ባለሙያዎችና እና 12 ሺ ሊትር ውሃ ጥቅም ላይ መዋሉን ነግረውናል፡፡
ምሽት 4 ሰዓት 15 ደቂቃ ላይ የተነሣው ቃጠሎ በሰው ህይወት ላይ ያደረሰው አደጋ የለም ተብሏል፡፡
ቃጠሎውን ለመቆጣጠር 1 ሰዓት የፈጀ ሲሆን ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ ንብረት ለማዳን መቻሉን የባለሥልጣኑ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ለሸገር ተናግረዋል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.