የሜዲያ ሕይወትና ፖለቲካ (ከይገርማል)

conflict-dynamics-for-dummiesበሜዲያ ላይ ተሳትፎ ሳደርግ ጥቂት የማይባሉ አመታትን አስቆጥሬአለሁ:: በመጀመሪያ በጽሁፎች ላይ አስተያየት በመስጠት ነበር የጀመርሁት:: በምጽፋቸው ጽሁፎች ማንነቴ የሚታወቅና የምጠየቅ ይመስለኝ ስለነበረ አስተያየቶቸን የማቀርበው ሀላፊነት በተሞላበት መንፈስ ማንንም በማያስቀይም መልኩ በጥንቃቄ ነበር:: ያም ሆኖ በጻፍኋቸው አስተያየቶች ላይ ተንተርሰው የሚሰጡኝ አሳቃቂ ምላሾች መከሰታቸው አልቀረም:: የሚገርም ነው! የፈለገው ቅዱስ ስራ ብንሰራ ነቃፊ አይጠፋም ማለት ነው! ሌላው ችግሬ ደግሞ የምጠቀምበት ኮምፒዩተር የጋራ ስለነበር ሚስጥራዊ በሆነ መንገድ ሀሳቤን ለመግለጽ አለመቻሌ ነበር:: አስተያየት በምጽፍበት ወቅት የሚያልፉ የሚያገድሙ ሰዎች የምጽፈውን ያነቡብኛል የሚለው የመጀመሪያው ስጋቴ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ አስተያየቱን ጽፌ ፖስት ካደረኩ በኋላ የተጠቀምሁበት ስም የማይጠፋ በመሆኑ ይታወቅብኛል የሚል ፍርሀት ነበር:: ምን ላድርግ በዚህ ዘመን ማን ምን እንደሆነ መች ይታወቃል! ቀስ በቀስ ግን ሁሉንም እየተላመድሁ ሌሎችንም እያየሁ እየተማርሁ ሄድሁ::

በምሰጣቸው አስተያየቶች ከትንሽ እስከትልቅ ስድብ ተሰድቤአለሁ:: ጉድ እኮ ነው! የመንግሥትን ጥሩ ጎን ብናነሳ ሕዝበ-አዳም ይወርድብናል: ግንቦት 7ን ብንደግፍ የመንግሥት ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች ተቃዋሚወችም እንደጉድ ብድግ ብለው ይሰፍሩብናል: ኢሕአፓን ደግፈን ብንጽፍ ‘ትግሉን የገደሉ የ “ያ ትውልድ” የጥላቻና የመጠላለፍ ፖለቲካ አራማጆች ቅሪት’ ተብለን እንወገዛለን: ከፖለቲካ ውጪ ስለሆነ ነገር ብንጽፍ ‘ሀገርና ሕዝብ ችግር ውስጥ ወድቀው ባሉበት ሁኔታ እንዲህ አይነት ጽሁፍ ማቅረብ ሀላፊነት ማጣት ነው’ የሚለን ሞልቷል:: ዝም ማለት ደግሞ አይቻልም:: ይህ ማለት ግን በምጽፋቸው አስተያየቶች የሚደግፉኝ ሰዎች የሉም ማለት አይደለም:: አንዳንድ በግብራቸው ትላልቅ የሆኑ ሰወችም ያልተስማሙባቸውን ነጥቦች አንስተው በማይኮሰኩስ መንገድ ተችተውኝ ያውቃሉ:: አስተማሪነት በሌለው በአፍራሽ መልኩ ማለት በስድብ ወይም በእርግማን የሰውን ቀልብ የሚገፉ ሰዎችን ምን ቢያደርጓቸው ይሻላል? :: አንዳንዴ ሲብስብኝ ሰዳቢየን በሌላ ስም መልሸ አቀምሰዋለሁ:: ምኔ ሞኝ ነው? በአውላላ ሜዳ ላይ ወጥቶ እያቅራሩ መተኮስ ዱሮ ነው የቀረው:: ስለዚህ እንደዘመኑ አካሄድ በምሽግ ውስጥ ሆኘ ጠሽ እያደረኩ እተኩሳለሁ::

ክፉ የምባል ሰው አይደለሁም:: እንዲያውም ሀቀኛ: ግልጽና ቅን ከሚባሉ ሰዎች ውስጥ ልመደብ የሚገባኝ ነኝ:: ነገር ግን ዕድል የሚባል ነገር እንደሌለኝ አውቀዋለሁ:: እኔ ላይ ነገር ይከራል:: የማደርገውም ሆነ የምናገረው ባልጠበኩት መንገድ ይተረጎምብኛል:: ሰው ብወድም ሰው አይወጣልኝም:: ከእኔ እርዳታ የሚያገኝ ሰው ሳይቀር የምሰጠውን እየበላ በሀሜት ያብጠለጥለኛል: ጉድጓዴን ይምስልኛል:: ለምን እንደሆነ አይገባኝም:: ሌላው ቀርቶ በእርጅና ምክንያት መነሳት አቅቶት ከደጅ ተኝቶ የሚውል ውሻ ሳይቀር በማንም ላይ የማያደርገውን የእኔን ኮቴ ከሰማ አንገቱን እንደምንም ቀና አድርጎ “ቡፍ” ይልብኛል:: እንዲህ ብየ ስል ዕውነት ላይመስል ይችላል: ግን የምሬን ነው:: ግምባር ወይም ኮከብ ወይም ዕጣፈንታ የሚባለው ዕውነት ሳይሆን አይቀርም:: ባለቤቴ “ለኔና ለአንተ ገንዘባችን ነው ዘመዳችን:: እጃችንን እንኳ ቆርጠን ብንሰጠው የሚያመሰግነን የለም” ትለኛለች::

ባለቤቴ በአብላጫ ድምጽ ታምናለች:: ማለቴ ብዙሀኑ የደገፈው ሀሳብ ትክክል ነው ብለው ከሚያምኑት ሰዎች ውስጥ አንዷ ናት:: እኔ ደግሞ ከዚህም ከዚያም በግብአትነት ያሰባሰብኋቸውን ጭብጦች ይዠ በመጨረሻ ላይ ትክክል ነው ወይም የተሻለ ነው ብየ የማምንበትን ውሳኔ የማሳልፍ ሰው ነኝ:: ከአናሳው ድምጽ ውስጥም ዕውነት ልትኖር ትችላለች ብየ የማምን ነኝ:: በዚህ ምክንንያት ከብዙሀኑ የማፈነግጥበት አጋጣሚ ብዙ ነው:: ለምሳሌ የአባይን ግድብ ከሚደግፉት ጥቂት ሰዎች ውስጥ አንዱ ነኝ:: የምደግፍበት ምክንያት ጠቃሚ ነው ብየ ስለማምን ነው:: ወያኔ የሕዝብን ገንዘብ ለመዝረፍ የፈጠረው አዲስ ዘዴ ነው ለሚሉት ሰዎች “ምንም ነገር ሳይሰሩ ሲዘርፉ ማን አስቁሟቸው ያውቃል: ሳይሰሩ ከሚበሉ እየሰሩ ቢበሉ አይሻልም ወይ? አዋጡ ብሎ ያስገደዳችሁ የለም:: ካልፈለጋችሁ አታዋጡ:: እነርሱ ግን ከየትም አምጥተው ይስሩት: እኛ እንቅፋት መሆን አይገባንም” ብየ ተከራክሬአለሁ:: ለፖለቲካ ፍጆታ ሲባል ነው የአባይ ግድብ የተጀመረው: አይ አይደለም ውጥረት ስለበዛበት እንደማስቀየሻ የተጠቀመበት መንገድ ነው እንጅ ለሀገር ጥቅም ታስቦ ቢሆን ኖሮ ሱዳን ድንበር አጠገብ ባልተገነባ ነበር ላሉት “የወያኔ ወንጀል አስከፊ ነው: የሚሰራው ግፍ ከልክ ያለፈ ነው::  ስለዚህ  በአባይ ግድብ ምክንያት የሕዝቡ ልብ አይሸነፍም ብየ ተሟግቻለሁ:: ቢያንስ በአባይ ላይ ያገባናል የሚሉትን ወገኖችን እና የአለማቀፉን ማህበረሰብ ፖለቲካዊ ተጽእኖ የምንዳስስበት ሆኖ ሊያገለግል ይችላል” ብየ አቋሜን በግልጽ በማቅረቤ ያልተባልሁት ነገር አልነበረም::

የህትመት ሜዲያውን እየተለማመድሁት ስመጣ ከአስተያየት ሰጭነት ወደጽሁፍ አቅራቢነት አደግሁ:: የምጽፈው ማንንም ለማስቀየም ወይም ለማስደሰት ብየ አይደለም:: በቃ ትክክል ነው ብየ የማምነውን ነው የምጽፈው:: ሁሉንም ማስደሰት እንደማይቻል በሚገባ አውቃለሁ:: እና በሚሰማኝ ጉዳይ ላይ እጽፋለሁ: እተቻለሁ:: የምቃወመውም ሆነ የምደግፈው ሰውን ወይም ቡድንን ሳይሆን ሀሳብንና ድርጊትን ነው:: ነገር ግን የሀሳብ አፍላቂወችና የድርጊት ተዋናዮች ሰዎች ስለሆኑ ዞሮ ዞሮ ትክክል ያልሆነ ሀሳብ ተነስቷል ወይም ጎጅ የሆነ ነገር በተግባር ላይ ውሏል በሚል ዋናወቹ አክተሮች ሊወቀሱና ሊወነጀሉ የግድ ይሆናል:: ለዚያም ነው ተቃዋሚወችንም ሆነ ወያኔወችን ማድረግ ያለባቸውን አላደረጉም ወይም ማድረግ ያልነበረባቸውን አድርገዋል እያልሁ እያወገዝሁ ስጽፍ የነበርሁት:: በዚህ የተነሳ ወያኔ ቢያገኘኝ በጉጠት አፍንጫየን ሊነቅለው ይችላል: ተቃዋሚው ደግሞ አንገቴን::

በወያኔም ሆነ በተቃዋሚው ወገን ያሉ ደጋፊወች ለምን ጭፍን ደጋፊና ጭፍን ተቃዋሚ እንደሚሆኑ አይገባኝም:: እንዴት በሎጅክ አያምኑም! እንዴት ጭንቅላታቸውን አይጠቀሙም! መሬት ላይ በሚያዩት ዕውነታ ተመስርተው ለምን ፍርድ አይሰጡም! አመራር ላይ ያሉት እኮ ሰዎች ናቸው:: የሚገርማችሁ ብዙወች ከማናችንም የሚበልጥ ስብዕና: እውቀትም ይሁን ልምድ የላቸውም:: ለጥቂት ጊዜ ጠጋ ብላችሁ ብታይዋቸው ዕውነቱን ትረዱት ነበር:: የሚሰሩት በአብዛኛው በ trial and error ዘዴ ነው:: ለዚያም ነው ሕዝብንና ሀገርን ቤተሙከራ እያደረጉ ነው እየተባሉ የሚወነጀሉት:: ደጋፊው ግን ምን ነካው? ለምን ጥሩውን ጥሩ መጥፎውን መጥፎ ማለት አይለምድም:: በየትኛውም ወገን ያለ ደጋፊ አመራሩ የሚያወርደውን መመሪያ ተቀብሎ የሚያስተጋባ እንጅ የአመራሩን እንከን ነቅሶ በማውጣት ለማስተካከል የሚሰራ አይደለም:: ለምሳሌ የኮማንድ ፖስቱ በልቡ ቂም ሳይይዝ አልቀረም ተብሎ የሚጠረጠርን ሁሉ እያሰረ እንደሆነ ነው የሚታወቀው:: የትኛው የወያኔ ደጋፊ ነው “ኧረ የሚሰራው ስራ ልክ አይደለም” ብሎ ሲቃወም የተሰማው:: ለነገሩ የሀገር ቤት ተቃዋሚወችስ ወያኔ በፈቀደላቸው ጉዳይ ዙሪያ ብቻ ስለሚንቀሳቀሱ ፍቃድ ካላገኙ በስተቀር ያለቀው ቢያልቅ የሰላማዊ ተቃውሞ ሰልፍስ ቢሆን መች ሊጠሩ ይደፍሩና:: ሰላማዊ ተቃውሞ መንግሥትን ማስገደጃ መንገዶች የሉትም? መንግሥት የፈቀደውን ብቻ የሚፈጽም ተቃዋሚ ተቃዋሚነቱ ምኑ ላይ ነው?

መንግሥት የመሬት ይዞታን በሚመለከት የያዘው አቋም በብዙወች ዘንድ እንደሚወገዝ ይታወቃል:: ሕዝቡ ስለዘላቂ ጥቅሙ ብዙም የማያውቅ በመሆኑ መሬቱን ሊሸጥ ስለሚችል መሬት እንዲሸጥ እንዲለወጥ መፍቀድ አደጋ አለው ይላል:: ‘መሬት ይሸጥ ይለወጥ ቢባል መሬት በጥቂት ባለሀብቶች እጅ እንዲሰባሰብ ምክንያት ይሆናል: ስለዚህ መሬት ሳይሸጥ ሳይለወጥ የሕዝብና የመንግሥት ሆኖ መቀጠል አለበት:: ከሕዝቡ ከራሱ በላይ እኔ ስለማስብለት ነው ይህን የማደርገው:: በጮሌወች የማታለያ ዘዴ ተሸንፎ መሬቱን ሸጦ ለጭሰኝነት እንዳይዳረግ ሲባል መሬት የሚሸጥ የሚለወጠው በኢሕአዴግ ከርሰመቃብር ላይ ነው’: ይልና ራሱ ግን ሕዝቡን እንደፈለገ እያፈናቀለ በካሬሜትር በዶላር ይቸረችራል:: ተቃዋሚው ደግሞ የመሬት በመንግሥት እጅ መዋል ጉዳት አለው:- ሙስናን ያበረታታል: ምርታማነትን ይቀንሳል: ፍርሀትና ጥርጣሬን ይፈጥራል: የዜጎች የንብረት ባለቤትነትን መብት ይገስሳል: – – – ሲሉ ይከራከራሉ (ብዙወች የጎሣ ኃይሎች በመሬት ጉዳይ ያላቸው አቋም ከኢሕአዴግ ጋር ይመሳሰላል) :: ደጋፊውም የየፓርቲወችን አቋም ይዞ አመራሩ የሚለውን ተቀብሎ እንደበቀቀን ይደግማል:: ነገር ግን አሁን ኢሕአዴግ ድንገት ብድግ ብሎ አቋሙን ቀይሮ መሬት እንዲሸጥ እንዲለወጥ ፈቅጃለሁ ቢል የኢሕአዴግ ደጋፊወች ስለመሬት የመሸጥ የመለወጥ ጥቅም ቀድሞ በተቃዋሚው ይባል የነበረውን አስተያየት የራሳቸው አድርገው እንደሚከራከሩ: የተቃዋሚው አመራርና ደጋፊወች ደግሞ በአሁኑ ወቅት ገንዘብ የተሰባሰበው በገዥው ፓርቲ እጅ ስለሆነ የሕዝቡን መሬት በገንዘብ ኃይል አታለው በመውሰድ ሕዝቡን ወደከፋ ጭሰኝነት ሊያወርዱት አስበው ነው ብለው እንደሚቀሰቅሱ መጠራጠር አያስፈልግም:: ጥሩውን ከመጥፎው ሳይለዩ መደገፍና መቃወም የጤና አይደለም:: በዚህ ጉዳይ ላይ ወያኔና ተቃዋሚወች በጣም ይመሳሰላሉ:: የሚያመሳስላቸው የራሳቸው ጉድፍ የማይታወቃቸውና የሌላው ጥሩ ጎን የማይታያቸው መሆኑም ነው:: አመራሩ የሚደግፈውን ሁሉ መደገፍ: የሚቃወመውን ሁሉ መቃወም: ካለ አሳማኝ ምክንያት ሀሳቡን እንደፈለገ ሲቀያይር አብሮ ሀሳብን መቀያየር የሰውነት መለኪያ አይደለም እያልሁ ነው ያለሁት::  የሌላ መንፈስ ተሸካሚ ከመሆን ወጥተን ክፉውን ከደጉ ለመለየት ጭንቅላታችንን እንጠቀም የሚል መልዕክት ነው ለማስተላለፍ የፈለኩት::

ተቃዋሚ ነኝ የሚለው ኃይል ምን ለማድረግ እንደሚፈልግ የማያውቅ ፍጹም ግራ የገባው ነው ማለት ይቻላል:: የምንታገለው የስርአት ለውጥ እንዲመጣ ነው የሚለው ተቃዋሚ ትንሽ ቆይቶ መንግስት አንዳንድ መሻሻሎችን (ጥገናዊ ለውጥ) እንዲያደርግ ተማጽዕኖ ሲያሰማ ይደመጣል:: ለውጥ እንፈልጋለን ይላል: ግን ለለውጥ አይተባበርም:: አሊያም ሊተባበር የሚነሳው በምንም አይነት መልኩ ሊያቀራርብ የሚያስችል የጋራ አጀንዳ ከሌላቸው ቡድኖች ጋር ነው:: እንዲያውም ይግረማችሁ ብለው አንዱን ድርጅት ለሁለት ለሦስት ሲከፍሉትም አይተናል:: አንዱ ተቃዋሚ ነኝ ባይ የስደት መንግሥት እንመስርት ሲል ያወጣውን መግለጫ ሲያጣጥል የነበረው ሌላው ተቃዋሚ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ትንሽ ስሙን ቀይሮ ወይም አሻሽሎ የሽግግር መንግስት እንመስርት ብሎ ጥሪ ሲያደርግ ሀፍረት የሚባል አይሰማውም:: ይኸ ሁሉ ግን ለምን ይሆናል? ተብሎ ቢጠየቅ አርኪ መልስ የሚሰጥ አይገኝም;; እኛ ግን መልሱን በሚገባ እናውቀዋለን:: ሁሉም አለቃ እንጅ ምንዝር መሆን እንደማይፈልግ: ሁሉም መሪ እንጅ ተመሪ ለመሆን እንደማይሻ:: ሁሉም ከፊት እንጅ ከኋላ ለመሆን እንደማይፈቅድ እንረዳለን:: ችግሩ የሚመነጨውም ከዚህ የተዛባ እይታ እንደሆነ እንገነዘባለን::

በፌስቡክም ሆነ በዌብሳይቶች ላይ የሚሰጡ ብዙወች አስተያየቶች አስተማሪ ወይም አዝናኝ ያልሆኑ ተራ ስድቦች ናቸው:: በርግጥ አስተማሪ ባይሆኑም ከልብ የሚያስቁ አንዳንድ በፎቶ ተደግፈው የሚቀርቡ ኮሜንቶች አሉ:: በዕውነት ደስ ይሉኛል: ማሳቅም እኮ ትልቅ ጥበብ ነው:: መጻፍ እንደጀመርሁ በአርቲክሎቼ ያልተደሰተ ወገን  በስድብ ጥርግርግ ሲያደርገኝ እደነግጥ ነበር:: አንዳንዱን ስድብማ ውይ ውይ ውይ እንኳን ደግመው ሊሉት ሊያስቡትም ይከብዳል:: ስንት አይነት ሰው አለ!

ጽሁፍ የሚጻፈው ለጨዋታ አይደለም:: የሆነ መልዕክት ለማስተላለፍ: ቁምነገር ለማስጨብጥ: ወይም አማራጭ የመፍትሔ ሀሳብ ለማቅረብ ነው ጽሁፍ የሚጻፈው:: የምናውቀውን ለማሳወቅ: ስህተት ነው ያልነውን ስህተቱን ለማሳየት ነው:: እንድንማማር ነው:: አስተያየቶችስ በዚህ መልኩ ተቃኝተው በበጐ መልኩ ቢቀርቡ ምን አለበት?

የ”ሀ” ን ዘር የ”ከ” ዘር እያጠፋው ነው በሚለው ጽሁፌ ከጥቂቶች በስተቀር ብዙወች በጎደለ ሞልተው ሀሳቤን ደግፈው አስተያየት ሰጥተውኛል:: ይሁንና ችግሩ የሚቀረፍ ሳይሆን ጭራሽ እየባሰበት ነው የሄደው:: እንዲያውም አሁንማ እንደምን ናቹ: እኔ የምልክ: በልቻለው: ከሚለው አልፎ ተርፎ ከአንድ ርእሰጉዳይ ወደሌላ ርእሰጉዳይ ለመሸጋገር ሲፈለግ “”ይህንን በዚህ ቋጭተን ወደሚቀጥለው አለፍን” ሲሉ ስሰማ በቃ አማረኛ የሜዲያ ሰዎች ሳይቀሩ በዘፈቀደ የሚናገሩት ቋንቋ ሆነ አይደል! ማለቴ አልቀረም:: ይህን በዚህ ቋጭተን ወደሚቀጥለው አለፍን ሲባል ያለፈውን ነገር ለመተረክ ታስቦ ሳይሆን ወደሚቀጥለው ዝግጅት ለመሸጋገር መዘጋጀትን ለመግለጽ እንደሆነ የገባኝ ቆይቶ ነው:: ሀላፊ ግስ(past tense) እና ስለወደፊቱ ገላጭ ግስ (future tense) እንዴት እንደምንጠቀም የማናውቅ ሰዎች በእንደዚያ አይነት መድረክ ምን እንሰራለን:: ይህን በዚህ ቋጭተን ወደሚቀጥለው እናልፋለን በማለት ፈንታ ይህን በዚህ ቋጭተን ወደሚቀጥለው አለፍን ሲባል ስሰማ የመደበኛ ቋንቋ አጠቃቀምን እያዛባን የቋንቋ ስርአተአልበኝነትን እያስፋፋን እንደሆነ አምንና ከልብ አዝናለሁ::

በዚህ ርዕስ ላይ ባለሙያወች አስተያየት ቢሰጡበት ደስ ይለኛል:: ስህተት ለማረም መጀመሪያ ስህተቱ መታወቅ አለበት:: እኔም ተሳስቸ ከሆነ እንድታረም ሊነገረኝ ይገባል::

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.