ተጨማሪ ማብራሪያ ኤርትራ በሚለው ሥያሜ ላይ! [ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው]

eritriaባለፈው ሳምንት “ኤርትራ የሚለው ስም ከመቸ ጀምሮ፣ ከየት፣ በማንና በምንስ ምክንያት መጣ?” የሚል ርእስ ያለው ጽሑፍ ማስነበቤ ይታወሳል፡፡ በርካታ ሰዎች በተለይም የባሕረ ምድር ተወላጆች (ኤርትራውያኑ) ጽሑፉ የገባቸው አልመሰለኝም፡፡ የጻፍኩት ሌላ የተረዱት ሌላ መሆኑን በኢሜይል (በነመልእክት) ከላኩልኝ አስተያየቶች ተረድቻለሁ፡፡

እኔ ጣሊያን ባሕረ ምድርን ኤርትራ ብሎ ከመሠየሙ በፊት ኤርትራ የሚል ስም የባሕረ ምድርም ሆነ የሌላ ሀገር ሥያሜ ሆኖ አያውቅም! አልኩ እንጅ ኤርትራ የሚባል ቃል ወይም ኤርትራ የሚል የሆነ ነገር ወይም ቁስ ስም የለም አላልኩም! ቃሉ አስቀድሞ በቋንቋው ውስጥ ሳይኖር ጣሊያን ታዲያ ከየት አምጥቶ ለሥያሜነት ሊጠቀምበት ቻለ? ከቋንቋው ውስጥ የነበረ ቃል በመሆኑም አይደለም ወይ ሊጠቀምበት የቻለው?

ሌላው ደግሞ እኔ ከአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ በኋላም በግእዝ መጻሕፍት ላይ የኤርትራ ባሕር በማለት የተጠቀሰው ቃል በሸፍጥ እንዲገባ የተደረገ ቃል ነው እንጅ ከጣሊያን ወረራ በፊት የነበረ ቃል አይደለም! ለዚህም ማስረጃው በሌሎች ቋንቋዎች የተጻፉ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችን ብትመለከቱ ቀይ ባሕር ይላል እንጅ የኤርትራ ባሕር፤ ልብ በሉ ኤርትራ ባሕር ሳይሆን ያልኩት የኤርትራ ባሕር ነው ያልኩት፤ እናም እንዲህ የሚል ቃል በተለያዩ ቋንቋዎች በተጻፉ የመጽሐፍ  ቅዱስ ትርጉሞች አለመገኘቱ ነው፡፡ ጣሊያኖች የእኛን ሰዎች በመግዛትና በመደለል የኤርትራ ባሕር የሚልን ቃል በቅዱሳት መጻሕፍቶቻችን ውስጥ እንዲሠፍር ያደረጉበት ምክንያት ከጥንት ጀምሮ ባሕረ ምድር የኢትዮጵያ አካል ያልነበረች ለማስመሰልና ከፋፍሎ ኢትዮጵያን ለማዳከም ባላቸው ሸፍጥ ምክንያት ነው አልኩ እንጅ ቀይ ባሕር ጣሊያኖች በሚጠቀሙበት ቋንቋ በላቲን ኤሪትራ ታላሳ, Erythra thalassa (ቀይ ባሕር) አይባልም አላልኩም! አልወጣኝም!

በርካታ ሰዎች ግን ሁለቱንም ነጥቦች እንዲህ እንዳልኩ አድርገው አዛብተው በመረዳታቸው ኤሪትራ ባሕር ልብ በሉ የኤርትራ አይደለም ያልኩት ኤሪትራ ነው፤ እናም ቀይ ባሕር በላቲን ኤሪትራ ባሕር ይባል እንደነበር የሚያስረዱ ሊንኮችን (ይዞችን) በመላክ እንደተሳሳትኩ ሊነግሩኝ ሞከሩ፡፡

ከዚያ በፊት እኔ ያልኩትን አንብበው ምን እንዳልኩ ቢረዱ አሳስተው ተረድተው ያላልኩትን እንዳልኩ አድርገው ባልወቀሱኝ ነበር፡፡ ማንም ሊረዳው እንደሚችለው የኤርትራ ማለትና ኤሪትራ ማለት ሰፊ የሆነ የትርጉም ልዩነት አላቸው፡፡ የኤርትራ ማለት ኤርትራ የተባለ አካል ንብረት ማለት ሲሆን ኤሪትራ ማለት ግን ባለቤትነትንም የማያጠያይቅ ነጠላ ቃል ወይም ስም ነው፡፡ ትርጉሙም ቀይ ማለት ነው፡፡ ኤሪትራ ታላሳ ማለት ደግሞ ቀይ ባሕር ማለት ነው፡፡ ይህ ሥያሜ መጣ የሚባለው ደግሞ አንደኛው በጥንት ዘመን ኤሪትራ የሚባል የግሪክ ንጉሥ ነበረ ባሕሩንም በስሙ ስለሠየመው ነው ኤሪትራ የተባለው የሚለው ሲሆን፡፡ ሌላኛው ደግሞ የባሕሩ ወለል ላይ ወቅቱን እየጠበቀ በሚያብብ ቀይ አበባ ምክንያት ባሕሩ ቀይ መልክ ይይዝ ስለነበር ከዚህ የተነሣ ቀይ ባሕር ተባለ ይባላል፡፡ ቀይ ባሕር ውስጥ ባለ ቀይ ትል ምክንያት ነው ባሕሩ ቀይ ባሕር የተባለው የሚሉ የባዕዳን መላምትም አለ፡፡ ለማንኛውም የቀይ ባሕር ሥያሜና ምንጩ ይሄው ነው፡፡ አሁንስ ግልጽ ነው ወገኖቻችን? በመሆኑም “ባሕረ ምድርን ኤርትራ በማለት በፋሺስት ጣሊያን የተሰጠው ሥያሜ የባርነት ስም ነው!” ማለቴ ትክክል ነበር፡፡ አመሰግናለሁ፡፡

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

amsalugkidan@gmail.com

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.