ከ4 ሴተኛ አዳሪዎች አንዷ ኤችአይቪ አለባት [መታሰቢያ ካሳዬ]

• በዓመት 17000 ሰዎች ይሞታሉ – በቀን ከ40 በላይ፡፡
• በዓመት ከ24ሺ በላይ ሰዎች በኤችአይቪ ይያዛሉ፡፡
• ኤችአይቪ ያለባቸው ሰዎች፣ 740,000 (አብዛኞቹ ባለትዳር ናቸው)፡፡
• የሴቶች ቁጥር፣ 450,000፤ የወንዶች ቁጥር 290,000፡፡
1993-uganda-posterበመኪና አደጋ ህይወታቸውን ከሚያጡ ሰዎች ይልቅ፣ በኤድስ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በ500% ይበልጣል፡፡ በሌላ አነጋገር፣ ከዋናዎቹ ገዳይ መንስኤዎች መካከል አንዱ፣ ዛሬም ኤች አይቪ ኤድስ ነው፡፡ ነገር ግን ምንም ነገር አልተሻሻለም ማለት አይደለም። በአገር አቀፍ ደረጃ የኤችአይቪ ኤድስ የስርጭት ፍጥነት ትንሽ ቀንሷል፡፡ እንዲያም ሆኖ፣ የበሽታው ስርጭት አሁንም አሳሳቢ እንደሆነ የኤችአይቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽ/ቤት ምክትል ዳይሬክተር ሲገልፁ፣ በዓመት 24ሺ ሰዎች በኤችአይቪ እየተያዙ እንደሆነ ተናግረዋል።
የኤችአይቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽ/ቤት ምክትል ዳይሬክተር አቶ ዓለሙ አኖ፣ ሰሞኑን ለሚዲያ ተቋማት በተዘጋጀ ስልጠና ላይ እንደተናገሩት፤ የበሽታው የስርጭት መጠንና የሞት አደጋው ቁጥር እየቀነሰ ነው፡፡ አሳሳቢነቱ ግን አሁንም ክፉ ነው፡፡  በኢትዮጵያ 740,000 ሰዎች ኤችአይቪ እንደተገኘባቸው የተናገሩት ምክትል ዳይሬክተሩ፤ ከእነዚህ ውስጥ 290,000 ወንዶች መሆናቸውንና የሴቶቹ ቁጥር ከወንዶቹ በእጅጉ እንደሚልቅ ገልፀዋል፡፡ የሴቶቹ ቁጥር 450,000 በላይ ነው፡፡

በኤድስ ምክንያት በዓመት 16,865 ሰዎች እንደሚሞቱም ምክትል ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። በባለትዳር ጥንዶች ላይ አሳሳቢ የኤችአይቪ የስርጭት መጠን እንደሚታይ የጠቆሙት ምክትል ዳይሬክተሩ፣ ከ60% በላይ ኤችአይቪ በደማቸው ውስጥ ያለባቸው ሰዎች ባለትዳር ናቸው ብለዋል፡፡
ከ740 ሺ ኤችአይቪ ፖዚቲቭ ሰዎች መካከል፣ 440 ሺዎቹ ባለትዳር ናቸው፡፡ ነገር ግን፣ ባልና ሚስት በአንድ ጊዜ በኤችአይቪ ይያዛሉ ማለት አይደለም፡፡ እንዲያውም፣ አብዛኞቹ ላይ፣ ወደ 300 ሺ ያህሉ ባለትዳሮች ላይ፣ በኤችአይቪ የተያዙት፣ ባል ብቻ ወይም ሚስት ብቻ ናቸው፡፡
በተለያዩ ከተሞች፣ በቅርቡ ጥናትን መካሄዱን ምክትል ዳይሬክተሩ ገልፀው፣ የኤችአይቪ ስርጭት በሴተኛ አዳሪዎች ዘንድ ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል። ከ100 ሴተኛ አዳሪዎች መካከል፣ 25ቱ ኤችአይቪ ፖዘቲቭ ናቸው፡፡
የተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎችን በንፅፅር ስንመለከት፣ ከፍተኛ የኤችአይቪ ስርጭት የሚታየው በጋምቤላ ክልል ነው፤ ስርጭቱ ከ5% በላይ ይደርሳል። አነስተኛው ስርጭት ደግሞ የደቡብ እና የቤኒሻንጉል ክልሎች ነው – ከ1% በታች እንደሚሆን አቶ አለሙ ተናግረዋል፡፡
በሚቀጥሉት 15 ዓመታት ኤድስን ማጥፋት አለብን በሚል መርህ፣ የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠር የተጀመረው ዘመቻ ግቡን ይመታ ዘንድ፣ የሚዲያ ተቋማትና ጋዜጠኞች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት እንደሚገባቸው የገለፁት ምክትል ዳይሬክተሩ፣ ኤችአይቪ በደሙ ውስጥ የተገኘበት ማንኛውም ሰው መድኃኒቱን በነፃ መጠቀም ይችላል ብለዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.